፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠


በዚህ ልናገባድደው ጥቂት ቀናት በቀሩት ወር ብቻ አቡነ ማርቆስ ከአራት በላይ የፊት ለፊት
ተቃውሞዎች ገጥሟቸዋል፡፡ ታህሳስ ፫ በዓታ ለማርያም ቤተክርስቲያን በአንዲት የተዋሕዶ እናት ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟቸው ነበር፡፡
እርሳቸውም “ይችን እብድ ዝም አስብሏት” ሲሉ ተሰምተዋል፡፡ እርሷ ግን በቀጥታ “ቅባት ጳጳስ አያስተዳድረንም በቅባት አንገዛም
እምነታችን ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነው” በማለት እውነቱን በቆራጥነት መስክራለች፡፡ ይህን በመናገሯም ለሦስት ቀናት ያህል ለመታሰር
በቅታለች፡፡ ክብር አግኝታለች የዛሬው ሰማእትነት ይኸው ነው፡፡
ታህሳስ ፲፱ የቅዱስ ገብርኤል በዓል በተከበረበት ጊዜ እንደለመዱት “ዳግም ጥምቀት” እና “ጎጃም
ተጠመቅ ተባልህ” እያሉ ሲያስተምሩ “ቅባት አያስተምረንም እስላም አያስተምረንም፡፡ ቅባት የሆነ የግድ ይጠመቃል” በማለት ምእመናን
ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡ በዚህም ሳቢያ ብዙዎች ተደብድበዋል ክብር ሰማእትነት ነውና በረከታቸው ይድረሰን፡፡

ታህሳስ ፳፪ ቀን አቡነ ማርቆስ የእድ ውኃ እንደሚሄዱ ተናግረው ነበር፡፡ ሆኖም ግን በሸበል
በረንታ ልጆች ከፍተኛ እልህ አስጨራሽ ትግል በቦታው እንዳይገኙ ተደርገዋል፡፡
ታህሳስ ፳፬ በገዳመ አስቄጥስ አቡነ ተክለ ሃማት ገዳም እንደድሮው ግቢ ጉባዔን ማኅበረ ቅዱሳንን
ሰንበት ትምሀርት ቤትን እየነቀፉ ሲገሩ ከፍተኛ የምእመናን ተቃውሞ ተነሥቶባቸዋል፡፡ “ቅባት አያስተምረንም ቅባት አያስተዳረንም”
የሚሉ ድምጾች ጎልተው ተሰምተዋል፡፡ ብጹእነታቸውም “ካህናት ዝም አላችሁ” በማለት የሚቃወሟቸውን እንዲደበድቡላቸው አዝዘዋል፡፡
በዚህም መሠረት የገዳመ ፀሐፊ በያዘው መቋሚያ ለመደባደብ ሲሞክር ፖሊስ መቋሚያውን ሲነጥቀው ጫማውን አውልቆ በጫማ አንድን ወጣተ
ፈንክቷል፡፡ የተፈነከተው ወጣትም ሆስፒታል ገብቶ ህክምና ተደርጎለት ምሽት አካባቢ ወደ ቤቱ ተመልሷል፡፡ የተደበደቡ በርካታ ወጣቶች
ሲሆኑ ስምንት ያህሉ እስካሁንም ድረስ በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡

ተደብድበው ከተጎዱት ውጭ አሁን ፲፫ ፍርድ ቤት ተከሰው ብይን የሚጠብቁ የተዋሕዶ ልጆች አሉ፡፡
፰ቱ ደግሞ ገና ማረፊያ ክፍል ላይ ያሉ ናቸው፡፡ ወደ ማረሚያ ቤት ሊዛወሩ እና ክስ ሊመሠረትባቸው እንደሚችል ይታወቃል፡፡ ጫማ
አውልቀው ሰውን የሚፈነክቱ ጠብደል መነኮሳት ግን ከሳሽ የላቸውም እግዚአብሔር ይፋረዳቸው እንጅ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ቅዱስ ሲኖዶሱ
ዝም ማለቱ ቅዱስ ፓትርያርኩም ጆሮ ዳባ ልበስ ማለታቸው ለቤተክርስቲያናችን ትልቅ ጠባሳ ነው፡፡ ስለዚህ ብጹአን አባቶች ይህንን
ትኩረት ሊያደርጉበት ይገባል፡፡ በቦታው እንዲሰጥ በቅዱስ ሲኖዶስ የተወሰነው የሃይማኖት ትምህርትም ሊጀመር ይገባዋል፡፡ በአንድ
ቤተክርስቲያን ሁለት ሃይማኖት ተጫፍሮ ሊኖር አይችልም፡፡
ብጹእ አቡነ ዘካርያስን እንቅልፍ
የነሣቸው ጉዳይም ይኼው ነው፡፡ ብጹእነታቸው አቡነ ዘካርያስ ምሥራቅ ጎጃምን በሊቀ ጳጳስነት ያስተዳደሩት ስለሆነ የህዝቡን ጥያቄ
በሚገባ ይረዱታል፡፡ ለዚህም ነው ከሌሎች ሊቃነ ጳጳሳት በተለየ ለቅዱስ ፓትርያርኩ እና ለቅዱስ ሲኖዶስ በማሳሰብ ላይ የሚገኙት፡፡
አጣሪ ኮሚቴው ቤተክርስቲያን የሰጠችውን ትልቅ ኃላፊነት ወደ ጎን በማለት በገንዘብ ተገዝቶ ሥራውን ሳሠራ በመሄዱ አቡነ ማርቆስ
እንዳሸነፉ አድርገው ካህናትን ሰብስበው የአቋም መግለጫ ማውጣታቸው ይታወቃል፡፡ ያንን የአቋም መግለጫም ለፓትርያርኩ በማሳወቅ ፓትርያርኩም
ማንንም ሳያሳውቁ በሸኝ አድርገው ለምሥራቅ ጎጃም መልሰው መላካቸው ይታወቃል፡፡ ይህንንም በማስመልከት ብጹእነታቸው አቡነ ዘካርያስ
ቅዱስ ፓትርያርኩ የሠሩት ስህተት እንደሆነ አሳስበዋል፡፡
ብጹእነታቸው አቡነ ዘካርያስ ይህን ያህል ተጋድሎ
እያደረጉ ያሉት ምሥራቅ ጎጃሞችን ደስ እንዲለን ብለው አይደለም፡፡ ሃይማኖታቸው አባትነታቸው ስለሚያስገድዳቸው እንጅ፡፡ ብጹእነታቸው የጻፉትን ደብዳቤ ከዚህ ጋር አያይዠላችኋለሁ፡፡ የብጹእነታቸው
በረከት ይድረሰን!!!
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
© መልካሙ በየነ
ታህሳስ ፳፮
/ ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣
ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
No comments:
Post a Comment