Friday, February 10, 2017

ጸሎተ ሃይማኖት አንድምታ ትርጓሜ ሊቃውንት እንደተረጎሙት

© መልካሙ በየነ
የካቲት 03/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT, LIKE ያድርጉ፡-
==============================================
ነአምን በ፩ዱ አምላክ፡፡
በባሕርይ በሕልውና ከወልድ ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ አንድ አምላክ በሚሆን፡፡
እግዚአብሔር አብ፡፡
በእግዚአብሔር አብ እናምናለን፡፡
አኃዜ ኲሉ ገባሬ ሰማያት ወምድር፡፡
ሁሉን የሚገዛ፡፡ አንድም ሁሉን የፈጠረ እግዚኦ አኃዜ ኲሉ ዓለም እንዲል፡፡ አንድም ሁሉን እንደ ጥና እንደ እንቁላል በመሐል እጁ የያዘ፡፡ ሰማይን ምድርን የፈጠረ ሰማየ ሰማያት ለእግዚአብሔር ብሎ ምድረሰ በሀበ ለእጓለ እመሕያው ካለው ሲለይ፡፡ አንድም ኢትፍርህዎሙ ለእለ ይቀትሉ ሥጋክሙ ወለነፍስክሙሰ ኢይክሉ ቀቲሎታ ካለው ሲለይ አንድም መላእክትን ደቂቀ አዳምን የፈጠረ 

ዘያስተርኢ ወዘኢያስተርኢ፡፡
የሚታየውን ግዙፋኑን የማይታየውን ረቂቁን የፈጠረ፡፡ ዘያስተርኢ ሐተታ፡፡ የሚታየው ግዙፋኑ ወዘኢያስተርኢ የማይታዩት ረቂቃኑ በርኅቀት በርቀት፡፡ በርኅቀት አድማስ ናጌብ ብሄሞት ሌዋታን በርቀት ነፍሳት ነፋሳት መላእክት ናቸው አንድም ዘያስተርኢ በዘፈቀደ የሚገለጥ ወዘኢያስተርኢ፡፡ በባሕርዩ የማይገለጥ አንድም ለበቁት የሚገለጥ ላልበቁት የማይገለጥ፡፡ አንድም ዘይርኢ ወዘኢያስተርኢ ይላል ፡፡ የሚጠብቅ ሲጠብቅ የማይታይ፡፡
ወነአምን በ፩ዱ እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ
በተለየ አካሉ አንድ በሚሆን አንድም በባሕርይ በሕልውና ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ አንድ በሚሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን፡፡
ወልደ አብ ዋሕድ፡፡
ተቀዳሚ ተከታይ በሌለው የአብ የባሕርይ ልጁ በሚሆን፡፡
ዘህልው ምስሌሁ እምቅድመ ይትፈጠር ዓለም፡፡
ዓለም ሳይፈጠር በሱ ሕልውና፡፡ አንድም ከሱ ጋራ እንደሱ በነበረ፡፡
ብርሃን ዘእምብርሃን፡፡
ከብርሃን ከአብ በተገኘ በብርሃን በወልድ፡፡
አምላክ ዘእምአምላክ ዘበአማን፡፡
ከባሕርይ አምላክ ከአብ በተገኘ በባሕርይ አምላክ በወልድ፡፡
ዘተወልደ ወአኮ ዘተገብረ፡፡
በተወለደ ወአኮ ዘተገብረ ባልተፈጠረ፡፡ ሐተታ አርዮስ ሸክላ ሠሪ መሥሪያውን ሠርታ እንድትሠራ ደበናንሳ መዶሻውን ሠርቶ ዘመደ ሐፃውንትን እንዲሠራ ፈጥሮ ፈጠረበት ይላልና ወአኮ ዘተገብረ አለ፡፡
ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ፡፡
በሥልጣን በጌትነት በባሕርይ ከአባቱ ጋራ አንድ በሚሆን፡፡
ዘቦቱ ኲሉ ኮነ፡፡
ሁሉ በእርሱ ቃልነት በእሱ ህልውና የተፈጠረ
ወዘእንበሌሁሰ አልቦ ዘኮነ፡፡
ያለሱ ቃልነት ያለሱ ህልውና የተፈጠረ የሌለ፡፡
ወኢምንትኒ፡፡
ምንም የተፈጠረ የሌለ፡፡ ሐተታ አርዮስ ፈጥሮ ፈጠረበት ይላልና ወኢምንትኒ አለበት፡፡
ዘበሰማይኒ ወዘበምድርኒ፡፡
በሰማይ ያሉ ፀሐይ ጨረቃ ከዋክብት መላእክት በምድር ያሉ ዕፀው አዕባን እንስሳት አራዊት ሰውም ቢሆን ያለሱ የተፈጠረ ምንም የሌለ፡፡
ዘበእንቲአነ ለሰብእ ወበእንተ መድኃኒትነ
ዘበእንቲአነና ወበእንተ መድኃኒትነ ወረደ እምሰማያት ፩ድ ወገን ስለእኛ እኛን ለማዳን ከሰማየ ሰማያት ወርዶ፡፡
ተሰብአ ወተሰገወ እመንፈስ ቅዱስ፡፡
ወተሰብአ እመንፈስ ቅዱስ ይላል አብነት እም፡ በ፡ ነው በግብረ መንፈስ ቅዱስ፡፡ ሐተታ የከፈለ ያነፃ ያዋሐደ መንፈስ ቅዱስ ነውና ወእማርያም እምቅድስት ድንግል፡፡ እም እና እም አንድ ወገን ነው እመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ሰው የሆነ፡፡ አንድም መንፈስ ቅዱስ ከመክፈሉ የተነሣ እመቤታችን ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ ከማለቷ የተነሣ ሰው የሆነ፡፡
ኮነ ብእሴ፡፡
የሠላሳ ዓመት ጎልማሳ ሆነ፡፡ ወአመ ኮንኩ ብእሴ አውሰብኩ ብእሲተ ከመ ኲሉ ሰብእ እንዲል፡፡
ወተሰቅለ በእንቲአነ በመዋዕለ ጲላጦስ ጰንጤናዊ፡፡
የጳንጦስ ሰው ጲላጦስ ነግሦበት በነበረ ወራት ስለእኛ የተሰቀለ፡፡ ሐተታ፡፡ እንደ ሰማዕታት ዕሤት ሽቶ እንደ ሌባ እንደ ወምበዴ ስቶ አይደለምና በእንቲአነ አለ፡፡
ሐመ ወሞተ፡፡
ስለእኛ መከራ ተቀብሎ ሞተ፡፡
ወተቀብረ
ተቀበረ፡፡
ወተንሥአ እሙታን አመ ሣልስት ዕለት በከመ ጽሑፍ ውስተ ቅዱሳት መጻሕፍት፡፡
ንጹሐት ክቡራት በሚሆኑ መጻሕፍት እንደተጻፈ በሦስተኛው ቀን ተነሣ ነሥአ ደዌነ ወጾረ ሕማመነ እሁብ እኩያነ ህየንተ ሞቱ ወአብዕልተ ህየንተ መቅበርቱ ወልድየ ዕርግ እምህዝዓትከ ተብሎ እንደተጻፈ አንድም በከመ ጽሑፍ ዓርገ ይላል፡፡
ዓርገ በስብሐት ውስተ ሰማያት፡፡
በብርሃን በቅዳሴ በክብር በሥልጣን ዐረገ፡፡
ወነበረ በየማነ አቡሁ፡፡
ባባቱ ዕሪና ኖረ፡፡ ሐተታ፡፡ ንጉሥ የተጣላውን ሰናፊል አትታጠቅ በትር አታንሣ እንዲህ ካለ ቦታ አትውጣ ብሎ ቦታ እንዲወስንበት ቦታ ወሰነበት ማለት አይደለም፡፡ በምልዓት ሲል ነው እስመ ብሂለ የማን ይመርኅ ኀበ ተዋሕዶቶሙ በክብር እንዲል ነበረ የእንግድነት የማን የባለቤትነት ነው፡፡ አንድም ነበረ የባለቤትነት ነው፡፡ እንግዳን ንበር ይሉታል እንጅ ነበረ ይሉታልን፡፡
ዳግመ ይመጽእ በስብሐት፡፡
ዳግመኛ በብርሃን በሥልጣን በቅዳሴ ይመጣል፡፡
ይኰንን ሕያዋነ ወሙታነ፡፡
በሕያዋን በሙታን ይፈርድ ዘንድ አንድም ሕያዋንን ሙታንን ይገዛ ዘንድ ፡፡ ሐተታ ሕያዋን ያላቸው ጻድቃን ናቸው በነፍስ ሕያዋን ናቸውና አንድም በነፍስ ሕያዋን የሚሆኑበትን ሥራ ይሠራሉና አንድም የሕያው የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ናቸውና ሙታን ያላቸው ኃጥአን ናቸው በነፍስ ሙታን ናቸውና አንድም በነፍስ ሙታን የሚሆኑበትን ሥራ ይሠራሉና አንድም የምውት የዲያብሎስ ማደሪያ ናቸውና አንድም ኃጥአንን ሕያዋን አላቸው ጸላእትየሰ ሕያዋን ወይኄይሉኒ እንዲል በዚህ ዓለም ሕያዋን ናቸውና ጻድቃንን ሙታን አላቸው ምውት አነ በኀበ ዓለም ወዓለምኒ ምውት በኀቤየ እንዲል የሹትን አያገኙትምና አንድም ኃጥአንን ሕያዋን ሙታን አላቸው ሕያዋን እስከዕለተ ምጽአት ሙታን ከዕለተ ምጽአት በኋላ አንድም ሕያዋን አላቸው በዚህ ዓለም ሙታን አላቸው በወዲያው ዓለም አንድም ሕያዋን አላቸው በሥጋ ሙታን አላቸው በነፍስ አንድም ጻድቃንን ሕያዋን ሙታን አላቸው ሙታን አላቸው እስከዕለተ ምጽአት ሕያዋን አላቸው ከዕለተ ምጽአት በኋላ አንድም ሙታን አላቸው በሥጋ ሕያዋን አላቸው በነፍስ አንድም ሙታን አላቸው በዚህ ዓለም ሕያዋን አላቸው በወዲያው ዓለም፡፡
ወአልቦ ማኅለቅት ለመንግሥቱ፡፡
ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም ሐተታ፡፡ ዳዊት ሰሎሞን ቢገዙ ዐርባ ፤ ዐርባ ዘመን ነው ያውም እስከ ዳን እስከ ቤርሳቤህ ነው የሱ ግን ፍጻሜ የለውምና፡፡
ወነአምን በመንፈስ ቅዱስ እግዚእ ማኅየዊ፡፡
የባሕርይ ገዢ በሚሆን በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን፡፡
ዘሠረፀ እምአብ፡፡
ከአብ አካል ዘእምአካል ባሕርይ ዘእምባሕርይ የሠረፀ፡፡
ንስግድ ሎቱ ወንሰብሖ ምስለ አብ ወወልድ፡፡
ከአብ ከወልድ ጋራ እንስገድለት እንደ አብ እንደ ወልድ እናመስግነው፡፡
ዘነበበ በነቢያት፡፡
ምስለ አብ ወወልድ ዘነበበ በነቢያት ብለህ ግጠም ከአብ ከወልድ ጋራ በነቢያት አድሮ የተናገረ ንሰብሖ ምስለ አብ ወወልድ ከአብ ከወልድ ጋራ እናመስግነው፡፡
ታሪክ ከጉባዔ ኒቅያ እስከ ጉባዔ ቍስጥንጥንያ ሃምሳ አምስት ዓመት ነው በዚህ ጊዜ መቅዶንዮስ ለአብ መንበር እንዳለው እግዚአብሔርሰ ይነብር ዲበ መንበሩ ቅዱስ ተብሎ ተነግሯል ለወልድ መንበር እንዳለው መንበርከ እግዚኦ ለዓለመ ዓለም ተብሎ ተነግሯል ለመንፈስ ቅዱስ ግን መንበር እንዳለው የተነገረበት ቦታ የለምና ሕፁፅ ነው ብሎ ተነሣ ንጉሡ ዘየዓቢ ቴዎዶስዮስ ነው በቍስጥንጥንያ ጉባዔ ይሁን ብሎ አዋጅ ነገረ በዚህ ምክንያት መቶ ሃምሳ ሊቃውንት ተሰብስበዋል አፈ ጉባዔው ጢሞቴዎስ ዘአልቦ ጥሪት ነው ኢይቤ ሠናየ ይቤ አብ ኢይቤ ሠናየ ይቤ ወልድ አላ ይቤ፤ ይቤ ሰናየ መንፈስ ቅዱስ በአፈ ሲሳይያስ ነቢይ በዓመተ ሞተ ዖዝያን ንጉሥ ርኢክዎ ለእግዚአብሔር እንዘ ይነብር ዲበ መንበሩ ነዋኅ ወብሩህ ያለውን ይህን ባለመንበር ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ መንፈስ ቅዱስ ብሎ ተርጉሞብሃል ብሎ ረትቶበታል በዚህ ጊዜ እሱን ተከራክረው ረትተው አውግዘው ለይተው ወነአምን በመንፈስ ቅዱስ ብለው ጨምረውበታል፡፡
ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተክርስቲያን እንተ ላዕለ ኲሉ ጉባዔ ዘሐዋርያት፡፡
ሐዋርያት ባነጽዋት ከምኲራበ አረሚ ከምኲራበ አይሁድ በላይ በምትሆን ክብርት ንጽሕት ጽንዕት ልዩ በምትሆን ባንዲት ቤተክርስቲያን እናምናለን ሐተታ አሐቲ አለ በወርቅ በብር በጭቃ በጨፈቃ ቢሠራ በግብጽ በእስክንድርያ በጻድቃን በሰማዕታት በእመቤታችን ስም ቢሠራ አንድ ነውና በወርቅ በብር የተሠራ ቤተክርስቲያን ሥጋውን ደሙን ይለውጣል በጭቃ በጨፈቃ የተሠራ ቤተክርስቲያን ሥጋውን ደሙን አይለውጥም አያከብርም ብለዋልና አሐቲ አለ አንድም ሐዋርያት ያስተማሯት ያሳመኗት ያጠመቋት ከምዕመናነ አሕዛብ በላይ የምትሆን ክብርት ንጽሕት በምትሆን ባንዲት ምዕመን እናምናለን፡፡ ሐተታ አሐቲ አላቸው ምዕመናንን አንድ እምነት ያምናሉ አንድ ጥምቀትይጠመቃሉ አንድ ሥጋውን ደሙን ይቀበላሉና አንድም ምዕመንን በሚያስተምሩ ባንድ መምህራን እናምናለን፡፡ ሐተታ መምህራንን አሐቲ አላቸው አንድ እምነት ያሳምናሉ አንድ ትምህርት ያስተምራሉ፡፡ አንድ ሥጋውን ደሙን ያቀብላሉና፡፡ አንድም በቤተክርስቲያን ምዕመናንን በሚያስተምሩ ባንድ በመምህራን እናምናለን፡፡ ሐተታ ሲያስተምሩ ሲያሳምኑ ሲያጠምቁ በቤተክርስቲያን ነውና ቅድስትን እንደ ሃይማኖተ አበው አትት፡፡
ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት ለሥርየተ ኃጢአት፡፡
ኃጢአት በሚሠረይባት ባንዲት ጥምቀት እናምናል፡፡ ሐተታ በአብ ስም በወልድ ስም በመንፈስ ቅዱስ ስም ቢጠመቁ አንድ ነውና በዐርባ ቀን በሰማንያ ቀን በዐርባ ዘመን በሰማንያ ዘመን ቢጠመቁ አንድ ነውና፡፡ እንድም በሊቀ ጳጳስ በጳጳስ በኤጲስ ቆጶስ በቄስ እጅ ቢጠመቁ አንድ ነውና አንድም በዐቢይ ባሕር በማዕከላዊ ባሕር በንዑስ ባሕር ቢጠመቁ አንድ ነውና ፡፡
ወንሴፎ ትንሣኤ ሙታን፡፡
ከፈረሱ ከበሰበሱ በኋላ አካል አግኝተው ታድሰው ሙታን እንዲነሡም እናምናለን አንድም አንዘ ንሴፎ ይላል ሙታን እንዲነሡ አምነን ባንዲት ጥምቀት እናምናለን፡፡ ሐተታ ማጥመቅ ትንሣኤ ሙታን ካሳመኑ በኋላ ነውና ወሕይወተ ዘይመጽእ ለዓለመ ዓለም፡፡
ሐይው ከመ መላእክት እንዳለ እናምናለን፡፡

No comments:

Post a Comment