Thursday, December 31, 2015

“እመ አምላክ ድንግል ማርያም”

© በመልካሙ በየነ
ታህሳስ 21/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ይህ ቃል ለአፍ ስንጠራው ሊቀለን ይችል ይሆናል እንጅ የእምነታችን ትልቁ ምሥጢር የእምነታችን መሠረት የተመሠረተበት እምነታችን የታነጸበት ዋና ቃል ነው፡፡ ስለ ድንግል ማርያም የሚከራከሩን ሰዎች  ይህን ቃል ብትነግሯቸው ቀላል ተራ ቃል ሊመስላቸው ይችላል ከምንም ሳይቆጥሩም ቃሉን ሊጠሩት ይችላሉ ግን አይደለም፡፡ በእውነት ይህንን ቃል እየጠሩ ምን የሚሉት ክህደት ነው? እስኪ ሰው ሆነን እናስበውማ በጣም የረቀቀ ምሥጢርን ያዘለ ቃል እኮ ነው፡፡ በእውነት በእናታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ላይ የሚሸፍት ልብ ምን አይነት ልብ ነው? ስለ እናታችን አማላጅነት ለመከራከር እኮ ይህን ቃል ግዴታ መጥራት አለብን፡፡ ይህን ቃል ከጠራነው ደግሞ ትርጉሙን መገንዘብ ያስፈልገናል፡፡ እስኪ በእውነት አስቡትማ ቢያንስ አሁን  ለደቂቃዎች ሰው እንሁንና አስተውለን እንረዳ “እመ አምላክ ወላዲተ አምላክ” ይህ ቃል ስለእውነት ገብቶን የምንጠራው ስንቶቻችን ነን? የሁለት ተቃራኒ ቃላት ጥምርታ እኮ ነው፡፡ “እመ አምላክ” የአምላክ እናት ማለት ነው “ድንግል ማርያም” ማለት ደግሞ ምንም ወንድ የማታውቅ ሴት ማለት ነው፡፡ “እመ አምላክ ድንግል ማርያም” ስንል ወንድን የማታውቅ በድንግልና በንጽሕና አምላክን ለመውለድ የበቃች አምላክን የወለደች እናት ማለት ነው፡፡ እንግዲህ እስኪ ሴቶች አስቡት እናት ተብሎ ድንግል ይባላልን? ድንግል ሆኖ ባለልጅ መሆንስ ይቻላልን? አይቻልም፡፡ ምንም ይሁን ምን ድንግል የሆነች ሴት ልጅ ልትወልድ አትችልም፤ በተመሳሳይ ልጅ የወለደች ሴትም ድንግል ልትባል አትችልም፡፡ ድንግል ማርያም ግን ድንግል ወእም ስትባል ለዘለዓለም ትኖራለች፡፡ በእውነት ግን ምን ቃል ይገልጻታል እናታችንን ምን ቃል እንፈጥርላታለን ምን ምሳሌስ እንመስልላታለን፡፡ የማይቻለውን ቻለች የማይወሰነውን ወሰነች ዘመን የማይቆጠርለት መለኮትን ዘመን እንዲቆጠርለት አደረገች፡፡ ሰሎሜ ልታዋልድ ስትቀርብ በቅጽበት እጇ ተቃጠለ ቶማስ የተወጋ ጎኑን እዳስሳለሁ ብሎ እጁን ሲያስጠጋው እጁ እርር ኩምትር አለ እመቤታችን ግን በድንግልና ጸንሳ በድንግላ ስትወልደው እሳተ መለኮቱ አላቃጠላትም ከቶ ለምን ይሆን? እነዚያ ደቂቃ ላልሞላ ጊዜ እጃቸውን ማስጠጋት ያልተቻላቸውን እሷ ግን ታቀፈችው አዘለችው አይገርምም፡፡ አረ ቅዱሳኑም ሊቃውንቱም እመቤታችንን የሚገልጹበት ቃል የላቸውም “በመኑ በአምሳለ መኑ ናስተማስለኪ” ያላት ምስጋና የበዛለት አባ ሕርያቆስ አይደል እንዴ? ታዲያ ምሳሌ ሲያጣላት ቃል ባይገልጽለት ምን ያድርግ? ግርምት ድንግል ማርያም ያልገረመች ማን ይግረም፡፡ በዚያ በኃጢአት ዘመን የቀደመው የአዳም በደል በእናቷና በአባቷ ሳለ እርሷ ግን ያ በደል ሳያገኛት ለድህነታችን የተወለደች የተፈጠረች ንጽሕት ዘር  ናት እናታችን እመብርሃን፡፡ በዚህ እንኳ በሰው ሚዛን በሰው ፍርድ እየነዘንና እየለካን ልንከራከር እንፈልጋለን፡፡ ጥንተ አብሶ አባትና እናቷ ስለነበረባቸው እርሷም አለባት ይላሉ ምስጋና ይግባትና፡፡ በዚህ ዘመን አባትና እናት በሽተኛ ሆነው ልጁም በሽተኛ ሆኖ ይወለዳል ብሎ መከራከር እንዴት ያለ ጭንቅላት ነው?
በእውነት ስሟን ጠርቶ የሚሰለች ማነው? እኔ እኮ እመብርሃንን የማከብራት እመ ብርሃንን የማመሰግናት እመ ብርሃንን የምሰግድላት ከመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ስለማልበልጥ ነው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችንን ሲያበስር ሰግዶ ደስታ ይገባሻል ደስ ይበልሽ ብሎ እኮ ነው፡፡ ታዲያ እርሱ እንዲህ ከሰገደላት እንዲህ ካከበራት እኔ ማን ሆኜ ነው እናቴን ላቃልል የስድብ አፍ የምከፍተው? ስሟን መጥራትስ ይቻለኛል እንዴ እንኳን በእናቴ ላይ ስድብን ልሰነዝር የምደፍረው? እናስተውል ወገኖቼ መናፍቃኑ በሚጠሯት አጠራር አንጠራትም እኛ፡፡ ለእኛ እናታችን ናት ለእኛ መድኃኒታችን ናት ለእኛ ተስፋችን ናት ለእኛ ገነት መግቢያችን ናት ለእኛ መመኪያችን ናት ለእኛ ስንቃችን ናት ለእኛ እረፍታችን ናት ለእኛ መሰላላችን ናት ለእኛ የደስታችን መፍሰሻ የደስታችን መፍለቂያ የደስታችን ምንጭ ናት ለእኛ ብርሃናችን ናት ለእኛ አምላክን የወለደችልን ናት ለእኛ አማላጃችን ናት ለእኛ ሁለመናችን ናት ለእኛ በደማችን ውስጥ ያለች በልባችን ውስጥ የታተመች ናት ለእኛ ፍቅሯ በሁለመናችን የመላች እናታችን ናት፡፡ ይህን የምንለው መናፍቃኑን ለመከራከር መናፍቃኑን ለመቃወም አይደለም እናታችን ከዚህም በላይ ስለሆነችልን  ነው፡፡ እኛ ፍቅሯን ቀምሰነዋል እናትነቷን አውቀነዋል መሸሸጊያነቷን አይተነዋል አማላጅነቷን አምነነዋል ሁሉንም እንደሆነችን ተገንዝበናል ለዚህ ሁሉ ክብር ያበቃንም እመ ብርሃንን ለእናትነት የመረጣት ከሴቶች ሁሉ መርጦ ያከበራት አምላካችን ነው፡፡

በእውነት እስኪ አስቡት ማን ነው ኃጢአት መሥራትን የማያውቅ? ከሰው ወገን ሆኖ በገቢር ባይፈጽም በነቢብ፣ በነቢብም ባይፈጽም በሀልዮ ኃጢአትን የማያደርግ ማነው? በእውነት ማነው ይህን ማድረግ የሚቻለው? ንጽሕናን እንደጠበቁ ምንም ኃጢአትን ሳያደርጉ እስከ ዘለዓለም መጽናት ለማን ተሰጠው? ለማንም አልተሰጠውም እኮ መላእክት እንኳ እንደ እርሷ ንጹሕ አይደሉም፡፡ እመቤታችን ግን ምንም አይነት ኃጢአት ርኩሰት የለባትም በሃሳብሽ ድንግል ነሽ በስጋሽም ድንግል ነሽ የምንላት ለምን መሰላችሁ ሃሳቧ ኃጢአትን ለማሳብ ጊዜ የሌለው ስለነበር እኮ ነው፡፡ እናታችን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን እናቴ የማይላት ከቶ ማነው? እርሱ እኮ መዳኑን የማይወድ ተስፋውን የማይሻ መጠጊያውን የማይፈልግ ከለላውን የማያውቅ መከታውን የዘነጋ ምርኩዙን መደገፊያውን የማይወድ ምግብ ስንቁን የሚጠላ ውሉደ አጋንንት ነው፡፡ እንዲያው ሌላውን እንተወውና አምላክን በድንግልና ለመውለድ መመረጧ እንዴት አያስደንቀንም? በድንግልና የሴቶች ልማድ ሳያገኛት በመንፈስ ቅዱስ ጸንሳ መገኘቷ እንዴት አያስደምመንም? ሰው ሆና ሳለች ከኃጢአትና ርኩሰት በሃሳብም በሥጋም ድንግል መሆኗ እንዴት አይገርመንም? መላእክት እንኳ ንጹሕ ባልሆኑበት ዓለም ለብቻዋ ንጽሕት ዘር መሆኗ እንዴት አይደንቀንም? በእውነት ስለእውነት ለስሟ መግለጫ ቃላት እኮ የለንም፡፡ እኛን የሚደንቀን እኮ እንደኛው ሰው ስትሆን እንዲህ ያለውን ንጽሕና ይዛ በመገኘቷ ነው፡፡ እኔ ሰው ነኝ አንተም ሰው ነህ አንችም ሰው ነሽ ማንነታችንን አናውቀውም እንዴ? ለትንሽ ጊዜ እንኳ እስኪ ሰው ሁኑ ያልኳችሁ ለዚህ ነው፡፡ በቅጽበት ውስጥ ምን ያህል ኃጢአትን ነው ስናነሣ ስንጥል የምንውለው? እኛ እንኳን ቆመን ተኝተንስ ኃጢአትን አይደል እንዴ ስንቃዥ የምናድረው እርሷ እንዲህ የሚባል ነገር የለባትም፡፡ ታዲያ እመቤታችን ያልገረመችን ማን ይግረምን? ከመላእክት ወገን ብትሆን እኮ እንዲህም ባልተገረምን ነበር ባልተደነቅንም ነበር ምክንያቱም ባሕርያቸውን ባሕርያችን ስላላደረግን እነርሱ እኮ ከእንደዚህ ባሕርይ ስለተፈጠሩ ነው እንል ነበር እመቤታችን ግን ሰው ናት ለዚያም ነው የደነቀችን የገረመችን፡፡ በእውነት “እመ አምላክ ድንግል ማርያም” የሚለውን ቃል ሳየው ሁልጊዜ አዲስ ነገር አዲስ ትምህርት አዲስ ቃል አዲስ ስብከት ነው ለእኔ፡፡ ዛሬም አዲሴ ነው ነገም እንደዚያው፡፡ ዝም ብሎም እናትና ድንግል ቢል ላይደንቀኝ ይችል ነበር “እመ አምላክ ሲባል ግን እንዴት አይደንቀኝም፡፡ ለሁሉም ነገር ግን አበው ተናግረውት ጽፈውት ያልጨረሱትን የክብሯን ነገር ስጨልፍ ብውል አልጨርሰውምና ዝም ልበል፡፡

“ቀን የወጣላቸው ቃላት”

© በመልካሙ በየነ
ታህሳስ 20/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ዘመን ሲያልፍ ዘመን ሲተካ ያለፈው ዘመን፣ ያለፈው መንግሥት፣ ያለፈው አስተሳሰብ፣ ያለፈው አመለካከት፣ ያለፈው ፍልስፍና፣ ያለፈው ትውልድ ወዘተ የበደላቸው እና አሁን ጊዜ ያን ሁሉ መከራ አልፈው በክብር የተቀመጡ ነገሮች ቀን ወጣላቸው እንላለን፡፡ ያለፈው ዘመን ጨለማቸው ስለነበር አሁን ላይ ብርሃን የሚያዩበት ስለሆነ ቀን ደግሞ ብርሃንን እንጅ ጨለማን ስለማያመጣ ቀን የወጣላቸው ስንል ብርሃን የተገለጠላቸው ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ በድህነት አለንጋ ሲገረፍ የነበረ ሰው በልጁ በኩል ድህነቱ ሁሉ ተገፍፎ ሃብታም የሚባል ሰው ዝናና ሞገስ የለበሰ ሰው ሲሆን አሁንማ እገሌ ቀን ወጣለት እኮ ይባላል፡፡ አሁን ግን ስለ ሰዎች አይደለም ቀን መውጣቱን የምንነጋገረው ስለ ቃላት ነው፡፡ መንግሥት ሲለወጥ ቃላትም አብረው ይለወጣሉ በሆነ ጊዜ በሆነ ዘመን በሆነ ማኅበረሰብ የተጨቆኑ ቃላት በሌላ ጊዜ በሌላ ማኅበረሰብ ላይ ያልፍላቸዋል ቀን ይወጣላቸዋል፡፡ እንዲያውም እነዚያ ቃላት ከመጠን በላይ ተደጋግመው ስለሚደመጡ ድሮ ግን እነዚህ ቃላት ነበሩን ያሰኛል፡፡ ለምሳሌ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተፈለፈሉ ቃላት አሉ “ሕዳሴ፣ ኪራይ ሰብሳቢ፣ አከርካሪ፣ ከማድረግ አኳያ፣ ከማድረግ አንጻር፣ ሰላማችን ይደፈርሳል፣ የልማት ቡድን ወዘተ” እነዚህ ቃላት እና ብዙዎች አሉ ምንም ስለማይጠቅሙን ነው የተውኳቸው፡፡ እነዚህ ቃላት ድሮ ተጨቁነው የነበሩ ናቸው ማንም የማይጠራቸው ቃላት ነበሩ ወይም የሚጠቀምባቸው ጥቂት ሰው ብቻ ነበር አሁን ግን አልፎላቸዋል እፎይ ብለዋል ቀን ወጥቶላቸዋል ብርሃን ፈንጥቆላቸዋል፡፡ እኔ እነዚህን ያመጣሁላቸችሁ “ቃል ደግሞ ቀን ይወጣለታል እንዴ” እንዳትሉ ያህል ነው እንጅ ጉዳዬ ከእነዚህ ቃላት ጋር አይደለም፡፡
አሁን እኔ የምሄደው ወደ ቤታችን ውስጥ ነው፡፡ እነዚህ ቃላት የፈለጉትን ያህል ቀን ይውጣላቸው በሚዲያ ዐሥር ጊዜ ይነገሩ ይተረቱ ይዘመሩ እንጅ ምኔም አይደሉም እንደማንኛውም ሰው ከመስማት አልዘልም አልደነቅም አልገርምም፡፡ እኔን የሚገርመኝ እና የሚያስጨንቀኝ ብሎም የሚያሳዝነኝና የሚያስለቅሰኝ በቤቴ በመኖሪያዬ በርስቴ የሚነገረው ብቻ ነው፡፡ ዛሬ በእኛ ቤትም አሉ ድሮ ያልተጨቆኑ ዛሬ ግን ድሮ እንደተጨቆኑ አስመስለን ቀን እንዲወጣላቸው ያደረግናቸው ቃላት አሉ፡፡ ባለፈው ልኩን ያለፈ አሜን እና እልልታ በሚል መጻፌን ታስታውሳላችሁ አሁንም እደግመዋለሁ ቀን ያለፈላቸው ቀን የወጣላቸው ቃላት እነዚህና መሰሎቻቸው ናቸው፡፡ በእውነት በቤተክርስቲያናችን ውስጥ እነዚህ ቃላት ተጨቁነው ኖረዋልን? አረ በፍጹም ቤተክርስቲያናችን ጭቆናን አላስተማረችም አልጨቆነችምም፡፡ ነገር ግን ቦታና ጊዜ ሰርታ ወስና ወጥና ከሽና አዘጋጅታለች እንጅ፡፡ ታዲያ ስብከት የተጀመረው ዛሬ ይመስል እንዲህ ዓይነቱን ያልተገባ ሥርዓት አልባነት ከየት አመጣነው? የዛሬ ሰባኪ አሜን ካላስባለ ካላስጨበጨበ ያስተማረ የማይመስለው የሰበከ የማይመስለው ለምንድን ነው? በእርግጥ የመናፍቃኑ፣ የተሐድሶ መናፍቃን እንዲሁም የሌሎቹ ተጽእኖ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ እነርሱ በእርግጠኝነት ቀድመውናል በርዘውናል፡፡ እነርሱ ያስተማሩን ትምህርት የነገሩን ቃል ነው በጭንቅላታችን የሚያቃጭለው፡፡ በእውነት እነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ እነ ቅዱስ አትናቴዎስ፣ እነ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ የሰበኩላት የሞቱላት የተገረፉላት የተገፈፉላት የተራቆቱላት ሃይማኖታችን ተዋሕዶ እንዲህ በመድረኮቿ ላይ ማንም የሚፈነጭባት ለምንድን ነው? ስብከት ሳንሰበክ አሜን በሉ እየተባልን የምንንገላታው አጨብጭቡ እየተባልን ዐሥሬ የምናጨበጭበው ለምኑ ነው? ምንም አልገባኝም ሥርዓት እኮ አለን ያውም የሚያምር የሚማርክ ልክና መጠን ጊዜና ዘመን የተወሠነለት፡፡ እንዴት ከመናፍቃን አዳራሽ ቃላትን አፍልሰን ዛሬ ላይ እንቦርቃለን? አሜን የሚለው ቃል እኮ ይሁንልኝ ይደረግልኝ ለማለት የምንጠቀመው ቃል ነው፡፡ እልልታ የሚገባው እኮ የራሱ የሆነ ክብር ለሚያስፈልገው ነገር ነው፡፡ በብዛት የምንጠቀመው ለደስታ ጊዜ ነው፡፡ የሰማዕታትን ነገር ስንናገር “ቅዱስ ጊዮርጊስን በወፍጮ ፈጩት” ሲባል ድምጽን ከፍ ማድረግ አይፈቀድም ሥርዓትም አይደለም፡፡ መከራ ነውና የምንናገረው ክብራቸው ጸጋቸው ትልቅ ነውና እኛ ለዚያ ጸጋ ክብር ስለማንበቃ ድምጻችንን ዝቅ አድርገን መናገር ያስፈልገናል፡፡ ዛሬ ግን እንዲህ የሚባል ነገር የለም ምክንያቱም ለሰማዕታት ክብር ከማይሰጡት ጋር ነዋ የሚውለው፡፡ ደምጹን ለቅቆ ጮኾ “ቅዱስ ጊዮርጊስ በወፍጮ ተፈጨ ደስ ይበላችሁ” ብሎን ያርፈዋል እኛም እንደለመድነው “እልል እንላለን እናጨበጭባለን አሜን እንላለን” ግን ወዴት እያመራን ነው? ስለእውነት እኔ አሁን አሁን ግራ እየገባኝ ነው ቢያንስ እስኪ እኛ እንዲህ ማለቱን እናቁመው፡፡ መጋቤ ሐዲስ እሸቱ አለማየሁ እንዲህ አሉ “ለመሆኑ እኛ ማን ሆነን ነው እግዚአብሔር ያክብርህ፣ ጸጋውን ያብዛልህ የምንለው” ልክ ነው ስንት ትልቆች ባሉበት እኛ እንዲህ እንድንደፍር ያደረገን ምንድን ነው? እንዲህ እያለ በአባቶች ፊት የሚሰብክ ሰው ስላለን እኮ ነው፡፡ ከመናፍቃኑ አፍልሰው ወደ እኛ ያመጧቸው ቃላት ናቸው፡፡ መናፍቃኑ ዘንድ ሁሉም እኩል ናቸው ካህን ምእመን ሴት ወንድ ጻድቅ ኀጥእ የሚባል ልዩነት የለም፡፡ ስለዚህም ማንም የፈለገውን መናገር ማስተማር መስበክ መዘመር ይችላል፡፡ ለካህን ለዲያቆን ለጳጳስ ለምእመን ለሴት ለወንድ ለሕጻን ለአዋቂ የሚለው ነገር አይታወቅም ምክንያቱም ማን ከማን ይበልጣል ማንስ ከማን ያንሳል፡፡ ሁሉም መስበክ ይችላል ሁሉም መዘመር ይችላል ሁሉም መፈወስ ይችላል፡፡ ለዛ ነው የእነርሱ ሥርዓት አልባነት ወደኛም መጥቶ እንዲህ የተሸረሸርነው፡፡ በውኑ ጸጋውን ያብዛልህ የምልህ እኔ ማን የሚሉኝ ጳጳስ ማን የሚሉኝ ቅዱስ ነኝ? የማን አባት የማን እናት ሆኜ ነው? የትኛውን ተጋድሎ የትኛውን ሰይፍ አልፌ ነው? በእውነት በጣም ያሳዝነኛል፡፡ አሁን ትውፊታችንና ባህላችንን ክርስቲያናዊ ምግባራችንን የምንፈትሽበት ጊዜ ነው፡፡ አውቀንም ሆነ ሳናውቅ ቀን ያሳለፍንላቸውን ቃላት መመርመር አለብን፡፡ እነዚያ ቃላት እኮ ዛሬ ቀን ያለፈላቸው ቀን የወጣላቸው ድሮ ስለተጨቆኑ አይደለም ድሮ ሥርዓት ያከብሩ ስለነበር ነው፡፡ ዛሬ እኮ መናገር እንጅ አንመርጥም ለምሳሌ ማንም ሰው ካህኑ ማት የሚገባውን “አሐዱ አብ ቅዱስ፣ አሐዱ ወልድ ቅዱስ፣ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ” እኛ በቅዳሴ ጊዜ ልንለው አንችልም፡፡ ነገ ግን ብንለው ምን ችግር አለው ዜማው በጣም ይመቸኛል ልንል እንችላለን፡፡ የዜማ ምቾት ምን እንደሆነ አላውቅም በእርግጥ ግን ለእኛ አልተገባንም ስለዚህ ለእኛ የሚገቡንን ብቻ ልንመርጥ ይገባናል፡፡
ዛሬ እኮ የእኛ እና የመናፍቃንን ዜማ መለየት እስኪያቅተን ድረስ የደረስን ተው ባይ አጥተን ይመቻል አይመችም እያልን ስንጨቃጨቅ ነው፡፡ በእውነት ሳናውቅ ተበልተናል ተበልጠናልም መንቃት ያሻናል፡፡ ማነው በቤታችን የፈለገውን ነገር የሚናገርበት እኛም እኮ ድርሻ አለን፡፡ ዛሬ ስብከትን መብል መጠጥ ያደረጉ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ ስለሥርዓቱ ስለትውፊቱ አይደንቃቸውም የተሰጣቸውን ጊዜ ብቻ መጠቀማቸውን ነው እነርሱ የሚመለከቱት፡፡ ስለዚህ መንቃት ያስፈልገናል!!!!! ተሐድሶ መናፍቃን በዝተዋል በርትተዋል ማድከም ማዳከም ያስፈልገናል፡፡ ከእኛ ላይ ይውረዱልን በቃ የራሳቸውን ቤተክርስቲያን ይሥሩ በዚያ ላይ የሚፈልጉትን ነገር ሁሉ ያድርጉ እኛ ላይ ግን አንዳች ነገር እንዳያደርጉ መጠበቅ አለብን፡፡ ከዚያ ውጭ ከሆነ ግን የአባቶቻችን አጥንት እሾህ ሆኖ ባይወጋን ምን አለ በሉኝ፡፡

Monday, December 28, 2015

ሲድራቅ----ሚሳቅ----አብደናጎ

© በመልካሙ በየነ
ታህሳስ 18/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
በዱራ ሜዳ ላይ ናቡከደነፆር አምላኩን አቆመው፣
በስድሳ ክንድ ቁመት በስድት ክንድ ወርድ ከወርቅ አቅልጦ ሠራው፡፡
አምላኩን ሊያስመርቅ ያልተመረቀ አምላክ መርቁልኝ ብሎ፣
መኳንንት፣ ሹማምንት፣ አዛዥ፣ አዛውንቱን፣ መጋቢውን ሁሉ ጠራቸው በቶሎ፡፡
የንጉሥ ትዕዛዝ ነው ከታች ባትን ከላይም አንገትን ሊያስቆርጥ የሚችል፣
ታዲያ ማን ይቀራል? ማንስ ይንቀዋል? ማን ያቃልለዋል?
ሁሉም ለምረቃው ተሰበሰቡና፣
በተሠራው አምላክ ፊት ለፊት ቆሙና፣
ያደንቁት ጀመሩ ንጉሣቸውን አምላክን የሠራ ስለሆነ ጀግና፣
በሚሠራ አምላክ ሁሉም አምኗልና፡፡
ከዚያማ ! አዋጅ ተናጋሪው እየጮኸ መጣ፣
ትእዛዙን ሊናገር ካልፈጸምን ሊቀጣ፡፡
ወገኖችና አህዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የምትናገሩ፣
መለከት፣ እንቢልታ፣ መሰንቆ፣ በገና፣ ዋሽንት ክራሩ፣
ዘፈን ግርግሩ፣
እንደተሰማችሁ ንጉሡ ላቆመው ለወርቅ ምስሉ ስግደትን ገብሩ፡፡
ይህን ባታደርጉ በሚነድ እሳት ውስጥ ትጨመራላችሁ፣
ከሰል እስክትሆኑም ትቃጠላላችሁ፡፡
እያለ አስፈራራን እጅግ አስጨነቀን፣
ለጣዖት እንድንሰግድ እያስጠነቀቀን፡፡
ከዚያማ! መለከት፣ እንቢልታ፣ መሰንቆ ክራርን፣
በገና ዘፈንን አዋጅ ተናጋሪው ሁሉንም አሰማን፣
ለጣዖት እንድንሰግድ ፊሽካውን ነፋልን፡፡
ይህን እንደሰሙ አህዛብ በሙሉ፣
በልዩ ልዩ ቋንቋ ተናጋሪው ሁሉ፣
ተደፍተው ሰገዱ ለወርቅ ምስሉ፡፡
ከዚያ ከለዳውያን አይሁድን ከሰሱ፣
ንጉሥ ሽህ ዓመት ንገሥ እያሉ ወደቁ ተነሡ፡፡
መለከት፣ እቢልታ፣ መሰንቆ እና ክራር፣
በገና እና ዘፈን ስንሰማ ልንሰግድም አልነበር?
ታዲያ እነዚህ ሰዎች በባቢሎን ግዛት ሥራ የሾምካቸው፣
ላንተ ለወርቅ ምሥል አንሰግድም እንቢ ማለታቸው፣
ንጉሥ ሺህ ዓመት ንገሥ ችግሩ ምንድን ነው?
እያሉ ከሰሱን እኛም እንድንሰግድ፣
ለወርቅ ምስሉ እንድናጎበድድ፡፡
ናቡከደነፆር ይህን እንደሰማ እጅግ ተበሳጭቶ፣
መልእክተኛ ልኮ ወሰደን ጎትቶ፡፡
ከዚያማ ጮኸብን እጅግ ተቆጥቶ፣
አምላኬን አለማምለካችሁ፣
ላቆምኩትም ምስል አለመስገዳችሁ፣
ከቶ እውነት ከሆነ ንገሩኝ ፈጥናችሁ አለን ተበሳጭቶ፡፡
አሁንም መለከት፣ እንቢልታ፣ መሰንቆ፣ ክራርን፣
በገና ዋሽንትን ዘፈን እንጉርጉሮን፣
በሰማችሁ ጊዜ ድፍት ብላችሁ ገብሩ ስግደትን፣
ይህን ባታደርጉ ተመልከቱ ያንን፣
በዚያ ተጥላችሁ ትቃጠላላችሁ፣
እያለ ጠቆመን የሚነደውን የእሳት እቶንን፡፡
እኛም ተመለከትን ይነዳል እሳቱ፣
ነገር ግን… ከንቱ እንደሆነ የንጉሥ ትምክህቱ
ማሳየት ማስተማር በመፈለጋችን ዝም አልነው በብርቱ፡፡
እርሱም ጀመረ ገባ ያስፈራራን፣
ከእጄ የሚያድናችሁ አምላክ የለም አለን፣
አምላኩ ወርቅ ሆኖ ለወርቅ ሊያሰግደን፡፡
እኛ ግን! እኛስ አምላክ አለን የሚያድን ከምንም፣
ከእጅህ የሚያስመልጥ የሚበልጥ ከሁሉም፡፡
ምንም ንጉሥ ብትሆን ብናከብርህ ቅሉ፣
አንተ ለሠራኸው ለወርቅ ምስሉ፡፡
አንሰግድም በፍጹም እግዚአብሔር እያለን፣
ሰማይና ምድርን አንተንም እኛንም የፈጠረን አምላክ ከላይ ሆኖ እያየን፡፡
የአምላክ ፈቃድ ሆኖ እንኳ ብንቃጠል፣
አንሰግድም በፍጹም ላንተ ለወርቅ ምስል፡፡
ብለን ስንናገር ፊቱ ተለወጠ ናቡከደነፆር፣
የእርሱ የወርቅ ምስል በልጦበት ከእግዚአብሔር፡፡
ቀድሞ ከሚነደው ሰባት እጥፍ ያህል ይቀጣጠል አለ፣
ነበልባል ሲጨምር ይፈራሉ ብሎ ንጉሥ ተታለለ፡፡
እኛ ግን! ከቶ ምንም ቢሆን ምንም ቢመጣብን፣
አንክድም በፍጹም እግዚአብሔር አምላክን፣
መከራ ስቃዩን ችግሩን ካላለፍን፣
መውረስ እንደማንችል መንግሥተ ሰማይን፣
እኛ እናውቀዋለን ከድሮ ጀምረን፣
ነንና ክርስቲያን፣
ስለዚህ በእቶኑ አቃጥሉን አንድዱን፣
አምላክን ከመካድ ሞት እንመርጣለን አልን፣
የንጉሥ ቃል ሆኖ ሁሉም አሽከሮቹ ተጣድፈው መጡና፣
አርባ ዘጠኝ ክንድ ከፍ ከፍ እስከሚል አቀጣጠሉና፡፡
እጃችንን አስረው በዚያ ላይ ጨመሩን፣
ከሰል እስከምንሆን በእሳት ሊያቃጥሉን፡፡
እኛ እኮ አምላክ አለን አምላክ እንደሌለው፣
አናዝንም አናፍርም ከቶም አንቃጠል እግዚአብሔር ከኛ ነው፡፡
ስቡህኒ ውእቱ ወልዑልኒ ውእቱ እንላለን ገና፣
አምላከ አብርሃም ከኛ ጋር ነው፣
እያልን አጨበጨብን እጃችን ተፈታ፣
ምስጋና ይድረሰው ለፈጠረን ጌታ፡፡
እኛ እሳት ውስጥ ወድቀን ምንም ሳንነካ፣
በዳር የነበሩት እኛን የጣሉን ግን ተቃጥለዋል ለካ፡፡
ናቡከደነፆር አሁንስ ደነቀመው፣
አማካሪዎቹን እንደዚህ አላቸው፡፡
ሦስት ሰው አስረን በእሳቱ ውስጥ ጥለን አልነበረምን?
እጃቸው ተፈትቶ አራት ሰዎች ሆነው የሚመላለሱ ይታዩኛል እኔን፣
ማመን አቅቶኛል ዛሬስ ይህን ዓይኔን፡፡
ይህ እንዴት ይሆናል?
 እንዴት ይደረጋል?
አራተኛው ሰው ግን የአማልክት ልጅን በእጅጉ ይመስላል፡፡
እያለ ሲደነቅ ሲገረም ቆየና፣
የልዑል ባሪያዎች ኑ ውጡ! ወደዚህ ቅዱስ ናችሁና፡፡
እሳት ውኃ ሆኖስ ካላቃጠላችሁ፣
እኔም አመልካለሁ እኔም እሰግዳለሁ፣
ከእቶን እሳት ውስጥ ከእጄም ላዳናችሁ፡፡
ከዛሬ ጀምሮ ለሲድራቅ ለሚሳቅ ለአብደናጎ አምላክ፣
እኔም ልወድቅ ልሰግድ ፊቱ ልንበረከክ፣
አምላኬ ጌታዬ ብዬ በእርሱ ብቻ ላመልክ፡፡
ራሴን ሰጠኹኝ እስከመጨረሻ፣
እግዚአብሔር ነውና መነሻ መድረሻ፡፡
ከዛሬ በኋላ በእነዚህ ቅዱሳን ክፉ የሚናገር፣
በአምላካቸውም ላይ የስድብን ነገር ከቶ የሚናገር፡፡
ይቆረጣል  ባቱ፣
ከላይም አንገቱ፡፡
****************************************
እንዲህ ነው እንግዲህ አምላክ የታደገን፣
ቅዱስ ገብርኤልን ልኮ ከመንደድ ያስጣለን፣
በአህዛብ መካከል ከፍ ከፍ ያረገን፡፡
የአማልክት አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን፡፡

(ትንቢተ ዳንኤል ምእራፍ ሦስት በሙሉ ያንብቡ)

Friday, December 25, 2015

ዘጠኙስ ወዴት አሉ? (ሉቃ 17÷17)------ክፍል 3

© በመልካሙ በየነ
ታህሳስ 15/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
እስከመጨረሻው የጸናውን ለማወቅ ወደ ራስቅል ኮረብታ ወደ ቀራንዮ እንውጣ፡፡ ዮሐ19÷25 ጀምራችሁ ተከተሉኝ፡፡ ነገር ግን በኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱ (እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም) የእናቱም እህት (ሰሎሜ የእናቱ የእመቤታችን እኅት ናት፡፡ ሃና ከሞተች በኋላ የቀለዮጳን ሚስት አግብቶ ወልዷታል)፣ የቀለዮጳም ሚስት ማርያም (ማርያም ባውፍሊያ) መግደላዊትም ማርያም ቆመው ነበር፡፡ ኢየሱስም እናቱን ይወደው የነበረውንም ደቀመዝሙር በአጠገቡ ቆሞ ባየ ጊዜ እናቱን አንች ሴት እነሆ ልጅሽ አላት፡፡ ከዚህ በኋላ ደቀመዝሙሩን እናትህ እነኋት አለው፡፡ ከዚህም ሰዓት ጀምሮ ደቀመዝሙሩ ወደ ቤቱ ወሰዳት ይላል፡፡ እንግዲህ ከ12 ቱ ደቀመዛሙርት መካከል መስቀሉ ስር የተገኘው ዮሐንስ ወንጌላዊ ብቻ ነው፡፡ መከራ ላይ እንዲህ ነው ሁሉም ይሸሻል ሁሉም ይርቃል፡፡ አበርክቶ ሲመግብ የተመገበው ሁሉ ዛሬ ላይ የለም፡፡ 5 ገበያ ሕዝብ 4 ገበያ ሕዝብ ከበረከቱ የተመገበው ዛሬ የለም፡፡ ያ መልኩን ለማየት፣ ፈውሱን ለመቀበል፣ከበረከቱ ለመሳተፍ ይከተለው የነበረው ሁሉ ዛሬ ሸሽቷል፡፡ ከዋለበት የዋሉት ካደረበት ያደሩት ሃብት ንብረታቸውን ቤት ልጆቻቸውን ሥራቸውን ሁሉ ትተው የተከተሉት ደቀመዛሙርቱም ራሳቸው በፍርሐት ተይዘው ሸሹት፡፡
እነዚህ 10 ለምጻሞችም እንዲሁ ናቸው፡፡ በዘመናቸው ለምጽ የወጣበት ሰው ኃጢአተኛ ነውና ከከተማ ርቆ ይጣላል፡፡ እንግዲህ እነዚህም እንዲሁ ናቸው፡፡ ዓለም ንቋቸው ሰው ጠልቷቸው የሰው ፍቅር ርቋቸው ከዓለም ሁሉ ተገልለው ለብቻቸው ከከተማ ዳር አውጥተው የጣሏቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን አምላካችን ክብር ምስጋና ይድረሰውና ኃጢአተኛን የማይጠላ እውነተኛ አምላክ ስለሰው ፍቅር ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከንጽሕተ ንጹሐን ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ነሥቶ ሕሙመ ሥጋን በተአምራት ሕሙመ ነፍስን በትምህርት እየፈወሰ ሲመጣ እነዚህንም ተገናኛቸው፡፡ ዓለም የናቃቸውን ሰው የጠላቸውን እርሱ ቀረባቸው፡፡ እነርሱም ተገቢ የሆነውን ልመና አቀረቡ፡፡ “እየጮኹ ኢየሱስ ሆይ አቤቱ ማረን” አሉ፡፡ እርሱም የኃጥአንን ለመና ሰማ ከዚያም “ኺዱ ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ” አላቸው፡፡ ካሕናት እንዲህ ያለ ትልቅ ክብርና ጸጋ አላቸው፡፡ አምላክ ሲሆን እዚያው ላይ ማንጻት ሲቻለው እንዴት ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ ይላቸዋል? ንስሐ ግቡ ራሳችሁን ለካሕናት አሳዩ የማሰር እና የመፍታት ሥልጣንን የሰጠኋቸው ናቸውና፡፡ እነርሱም የአምላክን ቃል አክብረው ራሳቸውን ለካህናት ሊያሳዩ ሄዱ  እነሆም ሲሄዱ ነጹ፡፡ ይህን ከለምጽ መንጻታቸውን ግን ለየግል ጥቅማቸው ተጠቀሙበት፡፡ ዛሬም እንዲሁ ነው ንስሐ እንገባለን ከደዌ ዳኛ ከአልጋ ቁራኛ እንፈወሳለን ሥጋውን እንበላለን ደሙን እንጠጣለን ነገር ግን ይህን ሁሉ ቸርነት ለኃጢአት እንጠቀምበታለን፡፡ ዲቁና፣ ቅስና፣ ቁምስና፣ ጵጵስናን አምላክ ያድለናል እኛ ግን ላልሆነ ነገር እንጠቀምበታል፡፡ መንጻታቸው ከሰው ጋር እንደሰው የሚያስቆጥራቸው ስለሆነ በዚያው እንደነጹ ያነጻቸውን አምላክ ተመስገን ሳይሉ እንደወጡ ቀሩ፡፡ ነገር ግን ከእነርሱም አንዱ እንደ ተፈወሰ ባየ ጊዜ በታላቅ ድምጽ እግዚአብሔርን እያከበረ ተመለሰ፡፡ እያመሰገነውም በእግሩ ፊት በግንባሩ ወደቀ እርሱም ሳምራዊ ነበር፡፡ ኢየሱስም መልሶ ዐሥሩ አልነጹምን ዘጠኙስ ወዴት አሉ? ከዚህ ከልዩ ወገን በቀር እግዚአብሔርን ሊያከብሩ የተመለሱ አልተገኙም አለ፡፡ እርሡም ተነሣና ሂድ እምነትህ አድኖሃል አለው፡፡ እንግዲህ የነጹት ዐሥር ነበሩ መንጻቱን አምኖ ያነጻውን ለማመስገን የመጣ ግን አንድ ቅዱስ ብቻ ነው፡፡ ቅድስናው አምላክ መስክሮለታል “ከዚህ ከልዩ ወገን በቀር” ብሎ ቅዱስ ማለት ልዩ ማለት ነው፡፡ ከሌሎች አስተሳሰብና አመለካከት ተለይቶ ተገኝቷል፡፡ አንድ ሲሆን በዘጠኙ ሃሳብና ምክር ሳይታለል ያዳነኝ ከለምጽም ያነጻኝ አምላኬን ሳላመሰግነው የትም አልሄድም ብሎ ተመልሶ ስለተደረገለት ምስጋና አቅርቧል፡፡
የቀሩቱ ዘጠኞቹ ግን የተደረገላቸውን ድንቅ ነገር ተጠቅመው ተመለሰው ወደ ዓለም ገብተዋል፡፡ ታጥቦ ጭቃ የሚባለው እንዲህ አይነቱ ተግባር ነው፡፡ ስለዚህ አምላካችን ያደረገልንን ውለታ ዘንግተን ዘጠኙስ ወዴት አሉ? ከመባል ይሰውረን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን፡፡

ዘጠኙስ ወዴት አሉ? (ሉቃ 17÷17)------ክፍል 2

© በመልካሙ በየነ
ታህሳስ 14/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
…እስኪ ወደ መከራው ሰዓት እንሂድ፡፡ ማቴ 26÷20 ላይ እንዲህ ይላል “በመሸም ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ ደቀመዛሙርት ጋር በማእድ ተቀመጠ ይላል፡፡ እንግዲህ አሁን 5 ሺህ ሕዝብ የለም 4 ሽህ ሕዝብም የለም አሁን የቀሩት ከዋለበት የሚውሉት ካደረበት የሚያድሩት ደቀመዛሙርቱ ብቻ ናቸው፡፡ ከእነዚህ 12 ቱ መካከልስ እስከ መጨረሻው የሚጸና እስከ እግረ መስቀሉ ድረስ የሚሄድ ማነው? አሁን እዚህ ላይ እራት እየበሉ ሁለት ነገሮች ተከውነዋል፡፡ የመጀመሪያው ነገር ይሁዳ አይሁድ የመዘኑለትን ሰላሣ ብር በከረጢቱ ይዞ አብሯቸው መቀመጡ ነው፡፡ ሌላኛው ነገር ደግሞ የጴጥሮስ “ሁሉም ባንተ ቢሰናከሉ እኔ ከቶ አልሰናከልም” ያለው መልስ ነው፡፡ እንግዲህ እዚህ ላይ ይሁዳ የሚስቱ ወንድም የሆነውን ቀማኛ እና ሽፍታ በርባንን እንዲፈቱለትና ኢየሱስ ክርስቶስን ደግሞ እንዲይዙት ከአይሁድ ጋር ምክሩን ጨርሶ የሚያሲዝበትን ምቹ ጊዜ ይፈልግና ያመቻች ነበር፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም ይህን ያውቅ ስለነበር እንዲህ አለ “እውነት እላችኋለሁ ከእናንተ አንዱ እኔን አሳልፎ ይሰጣል” በዚህ ሰዓት ደቀመዛሙርቱ ሁሉ እጅግ አዝነው “ጌታ ሆይ እኔ እሆንን” እያሉ ይጠይቁት ነበር፡፡ እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው “ከእኔ ጋራ እጁን በወጭቱ ያጠለቀ እኔን አሳልፎ የሚሰጥ እርሱ ነው” ሲል ይሁዳ ራሱን ያውቅ ነበርና “ መምህር ሆይ አኔ እሆንን አለ ኢየሱስም መልሶ አንተ አልህ” አለው፡፡ ጌታ በልማዱ ስድስቱን አቁሞ ስድስቱን አስቀምጦ ይዞ ይበላሉ ይመገባሉ፡፡ ዛሬ የቆሙ ነገ ይቀመጣሉ ወጥ የሚያወጣው በተራ ነው፡፡ ጌታ እያወጣ ይበላል አውጡልኝ አይልም ስድስተኛው ለአምስቱ ለራሱም እያወጣ ይበላል፡፡ በዚህ ቀን ከተቀመጡት አንዱ ይሁዳ ነበር  ወጥ ማውጣትም ተራው ነበርና ከእኔ ጋር እጁን በወጭቱ ያጠለቀ እኔን አሳልፎ ይሰጠኛል” ሲል ይሁዳ እርሱ እንደሆነ አልጠፋውም ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ እንጀራውንና ጽዋውን በየተራ አንሥቶ ባርኮ መግቧቸዋል፡፡ የሐዲስ ኪዳንን የቁርባን ሥርዓት አስተምሯቸዋል፡፡ እንግዲህ የይሁዳ ልብ እንደሸፈተ ነውና ከደቀመዛሙርቱም መካከል አንዱ ቀነሰ ማለት ነው፡፡ ይሁዳ ውሎውና አዳሩ ከአይሁድ ጋር ሆነ የአባቱን ቤት የጌታውን ጋጣ ዘነጋ፡፡ የይሁዳ ዓይን በሰላሣ ብር ተሸፈነ ፈጣሪውን ለወጠው፡፡ ከ12ቱ ደቀመዛሙርት መካከል 11ዱ ቀሩ ማለት ነው፡፡
ሌላው የሚገርመው ነገር የጴጥሮስ መልስ ነው፡፡ ጴጥሮስ እንዲህ አለ “ሁሉም ባንተ ቢሰናከሉ እኔ ከቶ አልሰናከልም” እንግዲህ ጴጥሮስ በራሱ ተመክቶ ነገ የሚሆነውን የሚደረገውን ነገር ስላላወቀ ከሁሉም ይልቅ ጌታውን አብልጦ እንደሚወደውና ከእርሱም እንደማይሸሽ ፈጥኖ ተናገረ፡፡ ኢየሱስም እንዲህ አለው “እውነት እልሃለሁ በዚች ሌሊት ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ጴጥሮስ ግን አሁንም በራሱ እንደተመካ ነበር “ከአንተ ጋራ መሞት እንኳ የሚስፈልገኝ ቢሆን ከቶ አልክድህም አለ” አምላኩ የሚነግረውን እንኳ ማመን አቃተው፡፡ እስከሞት ድረስም እንደሚታመን በራሱ አንደበት ተናገረ፡፡ በእውነት ግን ጴጥሮስ በዚያች ሌሊት እስከሞት ድረስ ይታመን ይሆን? እናንተ ማቴ 26ን በሙሉ እያነበባችሁ ተከተሉኝ አሁን ይሁዳ መምህር ሆይ ሰላም ላንተ ይሁን ብሎ ስሞ ለአይሁድ አሳልፎ ሰጥቷቸዋል፡፡ እነርሱም ወደሊቀ ካህናቱ ቀያፋ ወሰዱት፡፡ በዚህ ጊዜ ያ ማንም ቢክድህ አልክድህም እስከሞት ድረስ እከተልሃለሁ ያለው ጴጥሮስ እስከዚህ ግቢ ድረስ በሩቅ ሆኖ ነበር የሚከተለው፡፡ የአይሁድ ጭፍሮችን ፈራ ነገር ግን ደግሞ አልክድህም ያለው ቃል አሰረው ስለዚህ በሩቅ ሆኖ መከተሉን መረጠ፡፡ ቁጥር 69 ላይ ቅዱስ ጴጥሮስ ከቤቱ ውጭ በዐጥሩ ግቢ ተቀምጦ ነበር አንዲት ገረድም ቀርባ አንተ ደግሞ ከገሊላው ከኢየሱስ ጋር ነበርህ አለችው፡፡ እርሱ ግን የምትዪውን አላውቀውም ብሎ በሁሉ ፊት ካደ፡፡ በተድላና ደስታ ዘመን ምንም መከራ ሳይኖር እስከሞት ድረስ እታመናለሁ ብሎ በአፍ መናገር እስከሞት ድረስ መታመን ማለት አይደለም፡፡ አሁንም ደግሞ ሌላኛዪቱ እንዲህ ጠየቀቸው አሁንም አላውቀውም ብሎ ካደ፡፡ አሁንም ለሦስተኛ ጊዜ አነጋገርህ ይገልጥብሃልና በእውነት አንተ ከእርሱ ወገን ነህ አሉት ሰውየውን አላውቀውም ብሎ ለሦስተኛ ጊዜ ካደ፡፡ ከዚህ በኋላ ዶሮ ጮኸ የዚያን ጊዜ ያ ኢየሱስ ክርቶስ የነገረው ቃል ትዝ አለውና መራራ ልቅሶን አለቀሰ፡፡ አሁን በዚህ በመከራው ሰዓት የ5 ገበያ ሕዝብ የለም ቢኖር እንኳ ለመስቀል እንጅ እንዳይሰቀል ለመከልከል አይደለም፡፡ ሌሎችም ደቀመዛሙርት እንዲሁ በየፊናቸው ልብሳቸውን ጥለው ሁሉ የሸሹ አሉ፡፡ (ማር 14÷51-52) ታዲያ እስከመጨረሻ የጸናው ማነው?

ይቀጥላል…

Tuesday, December 22, 2015

ዘጠኙስ ወዴት አሉ? (ሉቃ 17÷17)--- ክፍል 1

© በመልካሙ በየነ
ታህሳስ 12/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
      የቃሉ ተናጋሪ መድኅን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን ቃሉን የተናገረውም ለአንድ ከለምጹ ለነጻ ሰው ነው፡፡ ይህ ቃል የተነገረበት ምክንያት ከላይ ከቁጥር 12 ጀምረን የምናገኘው ይሆናል፡፡ “ወደ አንዲት መንደርም ሲገባ በሩቅ የቆሙት ዐሥር ለምጻሞች ተገናኙት እነርሱም እየጮኹ ኢየሱስ ሆይ አቤቱ ማረን አሉ፡፡ አይቶም ኺዱ ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ አላቸው፡፡ እነሆም ሲሄዱ ነጹ፡፡ ከእነርሱም አንዱ እንደ ተፈወሰ ባየ ጊዜ በታላቅ ድምጽ እግዚአብሔርን እያከበረ ተመለሰ፡፡ እያመሰገነውም በእግሩ ፊት በግንባሩ ወደቀ እርሱም ሳምራዊ ነበር፡፡ ኢየሱስም መልሶ ዐሥሩ አልነጹምን ዘጠኙስ ወዴት አሉ? ከዚህ ከልዩ ወገን በቀር እግዚአብሔርን ሊያከብሩ የተመለሱ አልተገኙም አለ፡፡ እርሡም ተነሣና ሂድ እምነትህ አድኖሃል አለው” ይላል እስከ ቁጥር 19 ድረስ ያለው ቃል፡፡ ስለቃሉ የቃሉ ባለቤት እግዚአብሔር ስሙ የተመሰገነ ይሁንልን፡፡
እንግዲህ ከዚህ ቃል የምንረዳው እና የምንማረው ነገር ምንድን ነው? እስከ ፍጻሜ ድረስ መጽናት የሚያስገኘውን ዋጋ እንረዳለን፡፡ አበርክቶ ሲመግብ ሲከተለው የነበረው ህዝብ በኋላ መከራን በመስቀል ላይ ሲቀበል  ሸሽቷል፡፡ የ5 ገበያን ሕዝብ በ 5 እንጀራ እና በ2 ዓሣ እስኪጠግቡ ድረስ አበርክቶ አብልቶ 12 መሶብ ፍርፋሪ ሲነሣ የነበረው የሕዝብ ብዛት የሚገርም ነበር፡፡ ማቴ 14÷21 ላይ “ከሴቶችና ከልጆችም በቀር የበሉት 5 ሽህ ወንዶች ያህሉ ነበር” ይላል እናንተ ቃሉን ከላይ ከቁጥር 16 ጀምራችሁ አንብቡት፡፡ በዚህ የበረከት ሰዓት ሴቶችና ሕጻናት አብረው ተሳትፈዋል ነገር ግን ወንዶች ብቻ ናቸው እንደተመገቡ ተደርጎ የተቆጠሩት ምክንያቱም ሴቶች ሲመገቡ ወንዶች ካዩአቸው ያፍራሉ ሕጻናትም ከሚመገቡት ይልቅ የሚደፉት፣ የሚጥሉት እና የሚያበላሹት ይበዛልና ከቁጥር ውስጥ አልተካተቱም፡፡ እዚህ ላይ እንግዲህ በወንዶች ብቻ ብንወስደው 5 ሺህ ህዝብ እንደተከተለው ልብ ይሏል፡፡ እንደዚሁ ያለ ተመሣሣይ ታሪክ አለ ማቴ 15÷34-38 ድረስ ተመልከቱት፡፡ ቁጥር 38 ላይ ያለውን ልጻፍላችሁ እንዲህ ይላል “የበሉትም ከሴቶችና ከልጆች በቀር አራት ሺህ ወንዶች ነበሩ” ይላል፡፡ እንግዲህ እዚህ ላይ ደግሞ ሰባት እንጀራን እና ጥቂት ዓሣን አበርክቶ 4 ሺህ ሕዝብ በበረከቱ መግቧል፡፡ እዚህ ላይ ልብ በሉ እየተከተለው ያለው ህዝብ ምን ያህል እንደሆነ? ለምን ይህ ሁሉ ሕዝብ ይከተለዋል የሚለው መልስ የሚመለሰው በመከራው ጊዜ ነው፡፡ መልኩን ለማየት ይከተለው የነበረው በአይሁድ አጥንቱ እስኪቆጠር ድረስ ተደብድቦ፣ የእሾህ አክሊል ደፍቶ ቀራንዮ ላይ በመልዕልተ መስቀል ላይ ሲሰቀል ለንጊኖስ ጎኑን በጦር ሲወጋው ያን ጊዜ ይሸሹታል፡፡ ምክንያቱም ደም የሸፈነውን ፊቱን መመልከት አይፈልጉምና፡፡ ሲያበረክት ለመመገብ የተከተሉትም ተርቦ ፍሬ አልባ ወደ ሆነችው ዕጸ በለስ ሲቀርብና ፍሬ ሲያጣባት ያን ጊዜ በለስን ሲረግም ይሽሹታል አንድም በመስቀል ላይ ሆኖ ተጠማሁ ሲል የራሱን ጥማት የማያረካ እኛን እንዴት ይመግበናል ብለው ይሸሹታል፡፡ (ማቴ 21÷19፣ ማቴ 27÷48፣ ዮሐ 19÷28) ፈውስን ሽተው የተከተሉትም እንዲሁ በአይሁድ እጅ በፈቃዱ ተይዞ ሲሰቀል ፈያታዊ ዘጸጋም (ዳክርስ) ራስህን አድን እያለ ያልተገባን ንግግር ሲናገር ሲሰሙ ይኼስ ራሱንም ማዳን አልተቻለውም እንኳን እኛን ሊያድን ብለው ትተውት ይሸሻሉ፡፡ (ማቴ 27÷42) ይሸሻሉ የምላችሁ በልባቸው ነው እንጅ በአካልማ ድሮ ነው ችግራቸው ሲፈታ  የሸሹት፡፡ የሰው ልጅ የሚገርመው ታሪኩ እዚህ ላይ የሚጀምር ነው፡፡ ሲያዝ እና ሲለቀቅ በጣም ትልቅ የሆነ ልዩነትን ያሳያል፡፡ በህመም ወቅት እጅግ ከባድ መከራና ሃዘን በደረሰበት ወቅት የሚሰማው አምላኩን የማክበርና በአምላኩ ትእዛዝ የመሄድ ስሜትና በኋላ ይህ ሁሉ አልፎ የደስታ ጊዜ ሲተካለት የሚኖረው ስሜት ይለያያል ስለዚህም አብሮ ፈጣሪውን በደስታው ይለውጠዋል፡፡ በመከራው ጊዜ፣ በፈተናው ጊዜ በስቃዩ ጊዜ፣ በህመሙ ጊዜ፣ በረሃቡ እና በማጣቱ ጊዜ ስእለት የማይሳልበት ቤተክርስቲያን የለም፡፡ አምላክ መሐሪ ነውና ይቅር ይለዋል፣ ይምረዋል በበረከት በደስታ በፈውስ በጥጋብ ይጎበኘዋል ያን ጊዜ የተሳለውን ስእለት እንኳ አይመልስም ኖኅ እንደላከው ቁራ በዚያው እንደወጣ ይቀራል፡፡ ከላይ እየተመለከትነው የሚገኘው ይህንን መሰል ድርጊት ነው፡፡ በዚህ በበረከቱ ሰዓት 5ም 4ም ሺህ ሕዝብ ተሳታፊ ሆኗል፡፡ አሁን ይህ ሕዝብ መከራው ላይስ ይሳተፍ ይሆን?

ይቀጥላል….

Friday, December 18, 2015

‹‹እኛን ያዳነን ከሦስቱ ልደታት የበለጠው ልደት ነው››

© በመልካሙ በየነ
ታህሳስ 8/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
አምላካችን ፍጥረትን መፍጠር የጀመረው እሁድ ዕለት ሲሆን ከሥራው ሁሉ ያረፈው ደግሞ በ7ኛው ቀን ቀዳሚት ሰንበት ነው፡፡ የፍጥረት መጀመሪያው ሰማይና ምድር የፍጥረት መጨረሻው ደግሞ አዳም ነው፡፡ አዳም እንዴት ተወለደ? የአዳም ልደት ከኅቱም ምድር ነው፡፡ እግዚአብሔርም አለ “ሰውን በመልካችን እንደምሳሌያችን እንፍጠር… እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፣ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” ዘፍ1፥26-27 የአዳም ልደት እንዲህ ያለ ነው፡፡ ይህ ልደት በሰው ዘር ውስጥ የዓለማችን ቁጥር አንድ ልደት ነው፡፡ ከምድር አፈር አዳም የተወለደበት ልደት ግሩም ነው፡፡ የአዳም ልደት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በአዳም መወለድ ብቻ የቀረ ነው፡፡ ከአዳም በኋላ በዚህ መልኩ የተወለደ ሰው የለም፡፡ ይህ ልደት ለእኛ ምን ጠቀመን? ምንም አልጠቀመንም ለመዳናችን ሳይሆን ለመጥፋታችን መነሻ ነበር፡፡ አዳም ትእዛዝን የሻረ ሰው ከሆነ በኋላ እንጅ አፈር ትቢያ እንደነበረ አልነበረምና፡፡
ሌላው እና አስገራሚው ልደት የሴቲቱ የሔዋን ልደት ነው፡፡ የሔዋን ልደት ደግሞ ከአዳም ልደት የተለየ ልደት ነው፡፡ “እግዚአብሔር አምላክም በአዳም ከባድ እንቅልፍን ጣለበት አንቀላፋም ከጎኑም አንዲት አጥንትን ወስዶ ስፍራውን በሥጋ ዘጋው” ዘፍ2፥21 አዳም ከኅቱም ምድር እንደተገኘ ሔዋን ደግሞ ከኅቱም ገቦ (ጎን) ተገኝታለች፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ሶሪያዊ “ኦ ዝ መንክር ነሥአ አሐደ አፅመ እም ገቦሁ ለአዳም ወለሐኮ እምኔሁ ብእሲተ ወኵሉ ፍጥረተ ዕጓለ እመሕያው”  ከአዳም ጎን አንዲት ዐጽም መንሳት ምን ይደንቅ? ከእርሱ ሴትን ፈጠረ የሰው ፍጥረትንም ሁሉ ፈጠረ በማለት የሔዋንን ልደት ያስረዳል፡፡ (ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ) የሔዋን ልደትስ ለእኛ መዳን ምን ጠቀመን? እንደ አዳም ሁሉ ለመጥፋታችን እንጅ ለመዳናችን የሚጠቅም ልደት አይደለም፡፡ ምክንያቱም ሔዋን ባደረገችው አመጽ የገነት ደጅ ተዘጋ ስለሚል ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም፡፡ ዘፍ 3 ን ስናነብብ የምንመለከተውም የጥፋታችንን ውጥንና ፍጻሜ ነው፡፡ እንግዲህ እነዚህ ሁለቱ ልደታት እኛን ማዳን አልተቻላቸውምና ሌላ ልደት አስፈለገ፡፡
ሦስተኛው የሰው ልጅ ልደት የቃየን ልደት ነው፡፡ የቃየን ልደት በዘር በሩካቤ የተወለደው ልደት ነው፡፡ ከአፈር የተፈጠረው አዳምና ከአዳም ጎን የተፈጠረችው ሔዋን ሁለቱ ባደረጉት ሩካቤ ቃየን ተወለደ፡፡ በዘር በሩካቤ የተወለደ የመጀመሪያው ሰው ቃየን ነው፡፡ በእርግጥ ሔዋን መንታ ወልዳለች ሉድ የቃየን መንትያ ናት፡፡ ከዚህ በኋላ ደግሞ አቤልና አቅሌማ ተወልደዋል፡፡ (ዘፍ4 ን ተመልከት) አሁን እኛ የምንወለደው ልደት እንዲህ ያለውን ልደት ነው፡፡ ከአባትና ከእናት በዘር በሩካቤ የምንወለደው ልደት ይህ ሦስተኛው ልደት ነው፡፡ የአዳም የሥጋ አባትና እናት ማነው?  የሔዋንስ? የቃየንስ? የሥጋ አባትና እናት መቁጠር የምንጀምረው ከአዳም አባትነትና ከሔዋን እናትነት ነው፡፡ ታዲያ ይህ ልደት ለእኛ መዳን ምን ጠቀመን? ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ፣ ዳንኤል፣ ዘካርያስ፣ ሕዝቅኤል፣ አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብ… እነዚህ ሁሉ በዚህ መልኩ የተወለዱ ቅዱሳን ናቸው ግን ጽድቃቸው ወደ ገነት ማስገባት አልተቻለውም፡፡ ምክንያቱም በአዳም በኩል የመጣው ኃጢአት መርገም ለእነርሱም ተርፎ ስለነበር፡፡ ታዲያ ለገነት ለመንግሥተ ሰማያት ያበቃን ልደት የትኛው ልደት ነው?

ለገነት ያበቃን ልደት አዳም ከኅቱም ምድር፣ ሔዋን ከኅቱም ገቦ፣ ቃየን በዘር በሩካቤ እንደተገኙ ሁሉ በዘር በሩካቤ የተገኘችው እመ ብርሃን ድንግል ማርያም ያለ ዘር ያለ ሩካቤ በኅቱም ድንግልና የለአባት ጸንሳ የወለደችው የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ነው፡፡ የአዳም መርገም ያልነካት ንጽሕት ዘር ድንግል ማርያም ቅድመ ጸኒስ፣ ጊዜ ጸኒስ፣ ድኅረ ጸኒስ፣ ቅድመ ወሊድ፣ ጊዜ ወሊድ፣ ድኅረ ወሊድ ድንግል ናት፡፡ ያለዘር ያለሩካቤ ጸንሳ የወለደችው ልደት ከእነዚህ ሦስቱ ልደታት ሁሉ የበለጠ ልደት ሆነልን፡፡ በሔዋን ምክንያት የተዘጋው ገነት በድንግል ማርያም ምክንያት ተከፈተልን፡፡ ለድኅነታችን ምክንያት፣ የአዳም ተስፋ፣ የነቢያት ትንቢት የተፈጸመላት፣ አምላክን ጸንሳ ለመውለድ በቅታ፣ ነጽታ የተገኘች መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የሌለባት ንጽሕት ዘር ድንግል ማርያም ከእናቷ ሃና እና ከአባቷ ኢያቄም መወለዷ ለእኛ ጠቅሞናል፡፡ ምክንያቱም ከእነዚህ ልደታት ሁሉ የበለጠውን ትልቁን ልደት አምጥታልናለችና፡፡ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ አርጋኖን በተሰኘ መጽሐፉ ድንግልን ሲያመሰግን እንዲህ ይላል “እግዚአብሔር ከሰው ልጅ የማይተባበሩ ሦስት ልደታትን ተወለደ፡፡ እኔም አውቄ አደነቅሁ፡፡ ባራተኛው እንጅ የበጎ ዕረፍት አላገኘሁም፡፡ አዳም ከኅቱም ምድር የተወለደ በተፈጥሮ ነው፡፡ እኔን ግን የጠቀመኝ የለም፡፡ ሔዋንም ከአዳም ግራ ጎን ተወለደች እርሷም በተፈጥሮ ነው፡፡ ለእኔ ግን የጠቀመችኝ የለም፡፡ ቃየንም እንደ ሰው ሁሉ በዘር በሩካቤ ተወለደ የጠቀመኝ የረባኝ የለም፡፡ ስንኳንስ እኔን ራሱንም አልጠቀመም፡፡ እሊህ ሦስቱ ልደታትም ለማንም ለማን አይረቡም አይጠቅሙምም፡፡ ክርስቶስ ግን ያለዘር ያለሩካቤ ከድንግል ተወለደ ለሁሉ የሚረባ ለሁሉ የሚጠቅም ሆነ፡፡ ለዚህ ልደት መስገድ መገዛት ይገባል፡፡ ክብር ምስጋና ለዚህ ልደት ይገባል፡፡ ጌትነትና ገናንነት፣ ኃያልነት፣ አዚዝነት፣ እልልታ፣ ግርግርታ ለዚህ ልደት ይገባል፡፡ (አርጋኖን ዘሰኑይ ምእራፍ 2 ቁጥር 4-7)

Tuesday, December 15, 2015

‹‹ለሃሜት አሳልፈው ሰጡን›› (ክፍል 2)

© በመልካሙ በየነ
ታህሳስ 5/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
…እኔ በመኪናም ይሁን በእግሬ ስጓዝ አብረውኝ የሚጓዙ ሰዎችን ንግግር ማዳመጥ ደስ ይለኛል፡፡ ምክንያቱም ስለምማርበትና ሰውም ስለምመክርበት እኔም ስለምመከርበትና ስለምገሰጽበት ነው፡፡ እናም ስጓዝ የሰማሁትን ላካፍላችሁ ወደድሁ መልካም ንባብ!
በክፍል 1 (http://melkamubeyene.blogspot.com/2015/12/1.html) እንደተመለከትነው የኤማሑስ መንገደኞች አርስ በርሳቸው የሚነጋገሩት ነገር የተቀደሰ በመሆኑ የጉዞ ጉባኤ ብንለው ደስ ይለኛል፡፡ በስሜ ሁለት እና ከዛ በላይ ሆናችሁ ብትሰበሰቡ በዚያ መካከል እኔ እገኛለሁ ያለን አምላክ በእነዚህ በሁለቱ መንገደኞችም መካከል ተገኘ፡፡ የዚያን ጊዜ ወቅታዊው ጉዳይ የክርስቶስ በአይሁድ መገረፍ፣ መደብደብ፣ መሰቀል፣ መሞት፣ መነሣት ነበር እነዚህም የሚነጋገሩበት ጉዳይ ወቅታዊ ስለነበረው ነገር ነበር፡፡ እኔም የሰማኋቸው ሰዎች እንዲሁ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ያነጣጠሩ ናቸው፡፡ አንድ የታወቀ ገዳም አስተዳዳሪ ናቸው ከሆነ ሰው ጋር ሲሄዱ “በ5 ሚሊዮን ብር ዕዳ የተከሰሰ የሃገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ እንዴት ሌላ ሹመት ይሰጠዋል?” ይላሉ፡፡ ያ እሳቸው የሚሉት ሰው ያሉትን ያህል እዳ ይኑርበት አይኑርበት ማን ያውቃል? ሊኖርበት እንደሚችል ሁሉ ላይኖርበትም ይችላል፡፡ ነገር ግን ተበርዘናል የአሁኑ ወቅታዊ ጉዳይ የሆነው ተሐድሶ ከገንዘብ ጋር ንክኪ እየፈጠረ ቤተክርስቲያን ውስጥ ሰላም እንዳይኖር እየፈጠረ ያለው ችግር ለሃሜት አሳልፎ እንደሰጠን እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ዝም እንዳንል ዝም የሚያስብል ጉዳይ የለንም እንዳንናገርም ተናጋሪዎች ተሳዳቢዎች ሃሜተኞች ተንኮለኞች ምቀኞች ወዘተ እንባላለን፡፡ ታዲያ ወዴት ልናዘነብል እንችላለን?
ተሐድሶዎቹ ዓላማቸው ብዙ ዕቅዳቸው ረዥም ነው፡፡ በቤተክርስቲያን ውስጥ በቀላሉ ሰርጎ መግባት አይቻልም መጀመሪያ ክፍተታችንን ማዎቅ አለባቸው ያንን ያወቁትንና ያጠኑትን ክፍተት ደግሞ ውሻ በቀደደው.. እንዲሉ ይገቡበታል ምክንያቱም ጅቦች ናቸውና፡፡ ቤተክርስቲያንን ለመቆጣጠር የሰበካ ጉባኤ አባልና ስራ አስፈጻሚ፣ ዲያቆን፣ ሰባኪ፣ ቄስ፣ ዘማሪ፣ ከፍ ብሎም ቆሞስ፣ ኤጲስ ቆጶስ፣ ጳጳስ፣ ሊቀ ጳጳስ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ለዚህም ነው ዛሬ ላይ በየቦታው በየአጥቢው ብጥብጥ ሲፈጠር የምንመለከተው፡፡ ሁሉም የሰበካ ጉባኤ ጸሐፊ፣ ሰብሳቢ፣ ገ/ያዥ መሆን ይፈልጋል ሁሉም የቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ መሆን ሂሳብ ሹም መሆንን ይሻል፡፡ ሁሉም የአንድ አጥቢያ ቤተክርስቲያን መሪ አስተዳዳሪ መሆን ይፈልጋል ድሮ አባቶቻችን ይሸሹት የነበረውን ሥልጣንና ሹመት የዛሬዎቹ ደግሞ አብዝተው ይፈልጉታል፡፡ ድሮ ጳጳስ ለመሆን የተመረጠ አባት “አይገባኝም” ብሎ ይሸሽ ነበር የዛሬዎቹ ግን ስለሚገባኝ “ጵጵስና እንድትሾሙኝ” የሚል ማመልከቻም ሳያስገቡ አይቀሩም፡፡ ታዲየ ይሄው  እኛም እኮ ለሃሜት ተላልፈን ተሰጠን አማናቸው አይደል፡፡ ሳይገባቸው እንደተገባቸው አድርገው የሚቀርቡ ሰዎች ለብዙ መከራና ስቃይ እየዳረጉን ነው፡፡ ግዴለሽነትን፣ ምን አገባኝነትን፣ ማን አለብኝነትን አስተማሩን፡፡ በመናፍቁ ዘንድ ያለውን ሥርዓት አልባነት እኛ ውስጥም ጨመሩት፡፡ አሥራትና በኩራቱን ታወጣለህ የሆነ አስተዳዳሪ ነኝ ባይ አልያም ሂሳብ ሹም ነኝ ባዩ የራሱን ፎቅ ይሠራበታል፡፡ አንተም አሥራት ማውጣትህን ታቆማለህ ምክንያቱም ግለሰቦች ናቸዋ እየበለጸጉበት ያለው፡፡ ግን ትክክል ሥራ ሠርቻለሁ ትክክለኛ እርምጃ ወስጃለሁ ብለህ ታምናለህ? በፍጹም አያሳምንም፡፡ አሥራት በኩራት አውጣ ያለህ ፈጣሪ ነው ያወጣኸውን ገንዘብ የወሰደው ደግሞ ሰው ነው ላንተ ዋጋህን የሚከፍልህ ፈጣሪ እንጅ ሰው አይደለም ስለዚህ በሁለት መንታ ሃሳቦች መካከል ይጥሉሃል ማለት ነው፡፡ ከዚያስ ግዴለሽ ትሆናለህ “አሥራት ባወጣ የሚበላው እገሌ” እያልክ ትሸሻለህ፡፡ ታዲያ አንተ ለሃሜት ተላልፈህ አልተሰጠህም?

ሳንወድ በግድ ለሃሜት ተላልፈን እየተሰጠን ነው፡፡ ቤተክርስቲያናችን የምትፈልገው እንደ ኤማሑስ መንገደኞች ያሉ ሰዎችን ነው፡፡ ስለዚህ እንደነርሱ ልንሆን ይገባል፡፡ እነርሱ አይሁድ እንዲህ አድርገው ሰቀሉት እንዲህ አድርገው ገደሉት ካሉ በኋላ መጨረሻ ላይ “ወንሕነሰ ነአምን ቦቱ ከመ ውእቱ ሀለዎ ያድኅኖሙ ለእስራኤል” እኛ ግን እርሱ እስራኤልን ያድናቸው ዘንድ እንዳለው እናምናለን ብለው ነው የራሳቸውን አቋም የገለጹ፡፡ ዛሬ ግን እገሌ እንዲህ አደረገ፣ እገሊት እንዲህ አደረገች ከማለት ባለፈ እኔ ብሆን እንዲህ አደርግ ነበር የሚል የቀና መንፈስ የለንም፡፡ ይልቁንም እነርሱ በሳቱበት እንስታለን በወደቁበትም እንወድቃለን እንጅ፡፡ ስለዚህ ከሁለቱ የኤማሑስ መንገደኞች ከሉቃስና ኒቆዲሞስ ልንማር ያስፈልገናል ማለት ነው፡፡

‹‹ለሃሜት አሳልፈው ሰጡን›› (ክፍል 1)

© በመልካሙ በየነ
ታህሳስ 1/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ትምህርታችንን በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 24 እንጀምራለን፡፡ “ወይእተ ዕለተ እንተ የሐውሩ ፪ቱ እምውስቴቶሙ ሀገረ እንተ ትርኅቅ እምኢየሩሳሌም  መጠነ ፷ ምዕራፍ እንተ ስማ ኤማሑስ”   በዚያን ቀን ከርሳቸው ሁለቱ ከኢየሩሳሌም ስሳ ምዕራፍ ያህል የሚርቅ ኤማሑስ ወደምትባል አገር ሲሄዱ (ሁለቱ የተባሉት ሉቃስና ቀለዮጳ ናቸው ሉቃስን ዘውእቱ  ቀለዮጳ ይለዋል ብሎ ሉቃስና  ኒቆዲሞስ ናቸው ይላል) “ወይትናገሩ በበይናቲሆሙ በእንተ ኩሉ ዘኮነ”  ስለተደረገው ነገር ሁሉ ሲጫወቱ “ወእንዘ እሙንቱ ይትናገሩ ወይትኃሠሥዎ ለዝንቱ” ይህን ሲነጋገሩ ሲመራመሩ “ቀርቦሙ እግዚእ ኢየሱስ ወሖረ ምስሌሆሙ” ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ቀርቦ ከርሳቸው ጋራ ሄደ፡፡ “ወተእኅዘ አዕይንቲሆሙ ከመ ኢያእምርዎ” እንዳያውቁት ዓይናቸው ከእውቀት ተገታ “ወይቤሎሙ እግዚእነ ምንትኑ ዝንቱ ነገር ዘትትናገሩ በበይናቲክሙ እንዘ ተሐውሩ ትኩዛኒክሙ” እያዘናችሁ ስትሄዱ እርስ በርሳችሁ የምትነጋገሩት ይህ ነገር ምንድን ነው አላቸው፡፡ “ወአውስአ ፩ዱ እምኔሆሙ ዘስሙ ቀለዮጳ” ከርሳቸው አንዱ ቀለዮጳ የሚባለው መለሰ “ወይቤሎ አንተኑ ባሕቲትከ ነግድ ዘኢሀለውከ በኢየሩሳሌም” አንተ ብቻህን በኢየሩሳሌም አልነበርህምን? “ወኢያእመርከኑ ዘኮነ በውስቴታ በዝንቱ መዋእል” በዚህ ወራት በርሷ የተደረገውን አላወቅህምን አለው፡፡ “ወይቤሎሙ እግዚእ ኢየሱስ ምንትኑ ውእቱ” ጌታም ምንድን ነው አለው፡፡ “ወይቤልዎ በእንተ ኢየሱስ ናዝራዊ” የናዝሬቱን የኢየሱስን ነገር ይነግሩት ጀመር፡፡ “ብእሲ ጻድቅ” ደግ ሰው “ወነቢይ” ዐዋቂ የሆነ “ዘኮነ ከሃሌ በቃሉ ወበምግባሩ በቅድመ እግዚአብሔር ወበቅድመ ሰብእ” በተናገረው ነገር በሚሠራው ሥራ በእግዚአብሔር ዘንድ በሰውም ዘንድ ማድረግ የሚቻለው “ወዘከመ አግብእዎ ሊቃነ ካህናት ወመኳንንቲነ” የካህናት አለቆችና አለቆቻችን አሳልፈው እንደሰጡት “ወሰቀልዎ” ሰቀሉት  “ወንሕነሰ ነአምን ቦቱ ከመ ውእቱ ሀለዎ ያድኅኖሙ ለእስራኤል” እኛ ግን እርሱ እስራኤልን ያድናቸው ዘንድ እንዳለው እናምናለን፡፡ /ሉቃ 24 13-21/
የኤማሑስ መንገደኞች ሉቃስና ኒቆዲሞስ እየተነጋገሩ ይሄዱ የነበረው ስለኢየሱስ ክርስቶስ በአይሁድ ያለበደሉ፣ ያለኃጢአቱ ለሰው ፍቅር ሲል ለመስቀል ሞት ተላልፎ መሰጠት ስለነበር ኢየሱስ ክርስቶስ ከእነርሱ ጋር አብሮ መጓዝ ጀመረ፡፡ በጉዞው መካከልም ስለምን እንደሚነጋገሩ ጠየቃቸው ፍቅራቸው እጅግ ብዙ ስለነበር ኢየሱስ ክርስቶስ የሚባለውን አምላክ አይሁድ ተመቅኝተው እንዴት እንደገደሉት ነገሩት፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ፣ ደግ፣ ለድሆች የሚራራ፣ ለበሽተኞች መድኃኒት፣ ለተራቡት እውነተኛ ምግብ ለተጠሙት ደግሞ እውነተኛ መጠጥ እንደሆነ እነርሱ በጣም የሚወዱት አምላክነቱን የማይጠራጠሩ እንደሆኑ አስረዱት፡፡ ከማን ጋር እንደሚነጋገሩ ባወቁ ኖሮ ዝቅ ብለው ወድቀው በሰገዱለት ነበር ነገር ግን ማን እንደሆነ ስላላወቁ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲያምን ሊያስተምሩት ነበር የሞከሩ፡፡ ምንም እንኳ በኋላ አምላካቸው ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን የሚያውቁ ቢሆኑም ማለት ነው፡፡ እነዚህ የተቀደሱ የኤማሑስ መንገደኞች አይሁዳውያንን ለማማት ያበቃቸው የክርስቶስ ፍቅር ነው (በእርግጥ ይህ ሐሜት አይደለም ምክንያቱም አይሁድ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የሠሩትን እውነተኛ የግፍ ሥራ ስለነበር የሚነጋገሩ) ስለስሙ በሚነጋገሩት ተጓዦች መካከል አምላክ ተገኝቶ ባረካቸው፡፡ ሰውና ሰው ሲገናኝ የሰውን ጥፋት ያቅዳል፣የሌላውን ውድቀት ይመኛል፣ ሰውን እንዴት ማጥፋት እንደሚቻል ይወያያል፣ ሰውን በሌለበት በተሳለ ምላስ በሐሜት ይበላል እንጅ በእውነት የክርስቶስ ፍቅር፣ የእመብርሃን ፍቅር፣ የመላእክት ክብር፣ የቤተክርስቲያን ጉዳይ አገብሮት አንዳች ነገር የሚተነፍስ የሚነጋገር ሰው ከቶ የለም፡፡ እኔ በመኪናም ይሁን በእግሬ ስጓዝ አብረውኝ የሚጓዙ ሰዎችን ንግግር ማዳመጥ ደስ ይለኛል፡፡ ምክንያቱም ስለምማርበትና ሰውም ስለምመክርበት እኔም ስለምመከርበትና ስለምገሰጽበት ነው፡፡ እናም ስጓዝ የሰማሁትን ላካፍላችሁ ወደድሁ መልካም ንባብ…

ይቀጥላል፡፡

Wednesday, December 9, 2015

ኃጢአትየ ዘበንእስየ ወእበድየ ኢትዝክር ሊተ፡፡ /የልጅነቴን ኃጢአትና መተላለፍ አታስብብኝ/ መዝ 24÷7

© በመልካሙ በየነ
ሕዳር 29/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ልበ አምላክ የተባለው ቅዱስ ዳዊት  በመዝሙሩ አምላኩን ሲማጸን “የልጅነቴን ኃጢአትና መተላለፍ አታስብብኝ፡፡ አቤቱ ስለቸርነትህ ብዛት እንደ ምሕረትህ አስበኝ” እያለ ይጸልያል፡፡ የቅዱስ ዳዊት መዝሙር በቁም ላሉት ዕድሜን የሚያረዝም፣ ከሰይጣን ፈተና የሚጠብቅ፣ በበረከትና በምሕረት የሚያኖር ስለሆነ ሁልጊዜም እንጸልየዋለን፡፡ ይህ መዝሙር ለሁሉም የሚገባ ስለሆነ ለሙታን  ፍትሐትም ሳይቀር እንጸልየዋለን፡፡ ሁልጊዜም በቅዳሴ ጊዜ ከዳዊት መዝሙር ሶስት መስመሮችን ወቅቱን የሚዋጁ ዕለቱን የሚመለከቱ ምስባኮች በሚያምረውና በሚመስጠው የዲያቆኑ ድምጽ በሚማርክ ዜማ ይሰበካሉ፡፡ የዳዊት መዝሙር ለማንኛውም አገልግሎት የሚውል ልዩ ጸሎት ነው፡፡ ትንቢትን አቅርቦ የመናገር ጸጋ የበዛለት ነቢዩ ዳዊት ይህንን ልዩ የሆነውን ምስጋናና ጸሎት ለመንፈስ ልጆቹ ሁሉ ሰጥቶናል፡፡ እኛም የተሰጠንን ይህን ልዩ ጸሎት እየተገለገልንበት እየተጠቀምንበት እንገኛለን፡፡
ዳዊት ከትልልቅ ወንድሞቹ ይልቅ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ ሆኖ በመገኘቱ ከእረኝነት ወደ ንግሥና ወንበር የተቀመጠ ነቢይ ነው፡፡ ይህ ነቢይ አባቱ እሴይ እናቱ ደግሞ ሁብሊ ይባላሉ፡፡ ሰባት ልዩ ልዩ ሀብታት  ማለትም ሀብተ ትንቢት፣ ሀብተ ክህነት፣ ሀብተ መዊእ፣ ሀብተ ፈውስ፣ ሀብተ በገና፣ ሀብተ መንግሥት እና ሀብተ ኃይል ተሰጥተውታል፡፡ ይህ ጻድቅ ነው እንግዲህ  ከላይ በአርእስቱ ላይ የጻፍነውን የጸሎት ክፍል ያስተማረን፡፡ ዳዊት “የልጅነቴን ኃጢአትና መተላለፍ አታስብብኝ” አለ፡፡  እስኪ ሁላችንም ወደ ልጅነታችን ወደ ሕጻንነታችን እንመለስ በእውነት ያንን ሁሉ ኃጢአታችንን አምላክ ቢቆጥርብን ኖሮ ዛሬን መኖር እንችል ነበር? በደል ሳይመስለን የሰራነው ያ ሁሉ በደል ቢታሰብብን የዛሬዋን ጸሐይ ለመሞቅ እንታደል ይመስላችኋል? ኃጢአት ሳይመስለን የፈጸምነው ያ ሁሉ ኃጢአት ቢቆጠርብን ሰማይን ቀና ምድርን ዝቅ ብለን ለማየት እንታደል ነበርን? በፍጹም፡፡ አምላካችን ምሕረቱ ብዙ፣ ቸርነቱ ምጡቅ ስለሆነ ያንን በደል አልቆጠረብንም አላሰበብንም፡፡ በልጅነቱ ከእንስሳት ጋር ያልረከሰ፣ ሰውን በሽንገላ ከንፈር ያልተናገረ፣ ሰውን ያልበደለ ማነው? በእርግጥ ልጅነት ማለት ምን ማለት ነው? ለሚለው ጥያቄ ተገቢ ምላሽ መስጠት ይገባል፡፡ ጥንተ ፍጥረት አዳም የ30 ዓመት ጎልማሳ ሆኖ ሄዋንም የ 15 ዓመት ቆንጆ ሆና በአምላክ አምሳያ ከተፈጠሩ እና በገነት መኖር ከጀመሩ በኋላ 7 ዓመት ከ 1 ወር ከ 17 ቀን ሲሞላቸው ሰይጣን አታለላቸውና ከገነት ተባረሩ፡፡ እስከዚያ ቀን  ድረስ ኃጢአት አልሰሩም ነበር ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ይህንን አብነት በማድረግ አንድ ሕጻን ከ 7 ዓመት ጀምሮ መጾም፣ መስገድ፣ መጸለይ፣ መመጽወት  አለበት ንስሐ መግባትም አለበት ማለት ነው፡፡ ያ ማለት ግን ከዚያ በፊት መደረጉ ኃጢአት ሊኖረው አይችልም ምክንያቱም ለሚቀጥለው ሕይወታቸው ልምምድ ስለሆነ ማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ ግን ከ 7 ዓመት ጀምሮ የሚሠራ ኃጢአት ይታሰብብናል ይቆጠርብናል ማለት ነው፡፡
በልጅነታችን ብዙ በድለናል፣ ብዙ ኃጢአት ሰርተናል፣ ለቤተሰቦቻችን አልታዘዝም ብለናል፣ ቤተሰቦቻችንን ሰርቀናል፣ አባት እናቶቻችንን አላከብር ብለናል ወዘተ እሱ ሁሉ ኃጢአት ነው፡፡ አስቡት እንግዲህ ንስሐ መግባት የጀመርን አሁን ነው ያውም እየገባን ከሆነ ማለቴ ነው በአብዛኛው ግን የኃጢአት ክምር ከምረናል፡፡ እንግዲህ ዳዊት ይህንን ሁሉ አታስብብን ይላል፡፡ ምክንያቱም ዛሬ ላይ ሆነን በልጅነታችን የሰራነውን ኃጢአት ሁሉ ማስታወስ ስለማንችል፡፡ ነገር ግን ዳዊት ይህንን የልጅነቴን ኃጢአት አታስብብኝ ማለቱ የማውቀውንም የማላውቀውንም አታስብብኝ አትቁጠርብኝ ማለቱ ነው፡፡ ይህን ጸሎት ስትጸልዩ የልጅነታችሁን በደል ታስባላችሁ ያንን ያሰባችሁትን ያወቃችሁትን በደል አምላክ እንዳይቆጥርባችሁ ትማጸናላችሁ፡፡ ከዚያ ትዝ ካለን ኃጢአት ውጭ ያለውን ደግሞ እንዲሁ እንዳይቆጥርብን እንለምነዋለን፡፡ የልጅነት ኃጢአት የሚሠራ ፈጣሪን በማስታወስ አይደለም፡፡ ፈጣሪን የምንፈራበት ይህን ባደርግ እንዲህ እሆናለሁ እንዲህ እደረጋለሁ በሚል ስጋት ውስጥ ሆነንም አይደለም የምንሠራው፡፡ በማን አለብኝነት የምንሠራው ነውና አሁንም ፈጣሪን ዘንግተን በድፍረት የምንሰራውን ኃጢአት አታስብብን ምክንያቱም አስተሳሰባችን በአእምሮ እንዳልጎለመሱ ሕጻናት ስለሆነ፡፡

አምላካችን የልጅነታችንን ኃጢአትና መተላለፍ አያስብብን፡፡ አቤቱ ስለቸርነቱ ብዛት እንደ ምሕረቱም ያስበን፡፡

Wednesday, December 2, 2015

ሥጋ ወደም

© በመልካሙ በየነ
ሕዳር 22/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ዲያብሎስ እጅግ በጣም አብዝቶ ማራቅ የሚፈልገው ከምሥጢራት ሁሉ የበላይ ከሆነው “ከምሥጢረ ቁርባን” ነው፡፡ ምሥጢራት ሁሉ የሚደመደሙት በሥጋ ወደሙ ነው፡፡ መሥጢረ ጥምቀት፣ ምሥጢረ ንስሓ፣ ምሥጢረ ተክሊል የሚፈጸሙት በቁርባን ነው፡፡ ይህንን የሚያውቅ የውሸት አባት ዲያብሎስ የተለያዩ ምክንያቶችን በመደርደር ከሥጋ ወደሙ ያርቅሃል፡፡ አንተ ግን “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም በእኔ የሚያምንም ከቶ አይጠማም” ያለውን ኢየሱስ ክርስቶስን አምናለሁና ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የነሳውን ሥጋና ደም እመገባለሁ በለው፡፡ /ዮሐ6፥35/ የዘላለም ሕይወትን መውረስ እንደምትፈልግም አሳወቀው፡፡ “ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል” /ዮሐ6፥41/ ስለዚህ ለዘላለም በመንግሥተ ሰማያት ለመኖር ከሰማይ የወረደውን እንጀራ እበላለሁ ብለህ ጠላትህን አሳፍረው፡፡ ጠላት ግን በድፍረት እንድትቀርብ ሊፈትንህ ይችላል፡፡ የምትቀበለውን ሥጋና ደም የዕሩቅ ብእሲ ሥጋና ደም ነው ብሎ ሊያታልልህም ይሞክራል፡፡ አንተ ግን አትስማው የምቀበለው ሥጋና ደም በዕለተ አርብ የተቆረሰውና የፈሰሰውን  ሥጋና ደም ነው በለው፡፡ ሥጋና ደሙም መለኮት የተዋሐደው ነፍስ የተለየው እንጅ ጠላት እንደሚለው መለኮት የተለየው አይደለም፡፡ ጠላት ውጊያውን አሁንም አያቆምም “ንስሓ ሳትገባ ሳትዘጋጅ ተቀበል” ይልሃል፡፡ እርሱን ከሰማኸው የይሁዳ እጣ ፈንታ አንተ ላይም ይደርሳል፡፡ ሳይዘጋጁ ከኃጢአት ሳይነጹ ቢቀበሉት ግሩም ፍዳን የሚያመጣ የሚባላ እሳት ነው፡፡ ይሁዳ በጸሎተ ሐሙስ ከሌሎች ሐዋርያት ጋር ከቁርባኑ ሥርዓት ተካፋይ ነበረ፡፡ ነገር ግን በልቡ የነበረው ጌታን በ30 ብር የመሸጥ ኃጢአት እንደወጣ እንዲቀር አድርጎታል፡፡ /ማቴ26፥14-29/፣ /ማቴ27÷3-9/ ሥጋና ደሙ ግሩም ፍዳ የሚያመጣ ነው የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ ስለዚህ በንጽሕና በትሕትና ንስሓ ገብቶ ሊቀበሉት ይገባል፡፡ በዚህ መልኩ ለሚቀበለው የዘላለም ሕይወትን የሚያወርስ ጥበብን የሚገልጽ ምሥጢርን ሁሉ የሚያድል ነው፡፡ ለዚህም ነው ካህኑ በቅዳሴ ሰዓት “ንጹሕ የሆነ ከቁርባኑ ይቀበል ንጹሕ ያልሆነ ግን አይቀበል ለሰይጣንና ለመልእክተኞቹ በተዘጋጀው በመለኮት እሳት እንዳይቃጠል በልቡናው ቂምን የያዘ ልዩ አሳብም ያለበት ቢኖር አይቅረብ እጄን ከአፍአዊ ደም ንጹሕ እንዳደረግሁ እንዲሁም ከሁላችሁ ደም ንጹሕ ነኝ፡፡ ደፍራችሁ ወደ ክርስቶስ ሥጋና ደም ብትቀርቡ ከእርሱ ለመቀበላችሁ መተላለፍ የለብኝም በደላችሁ በራሳችሁ ይመለሳል እንጅ፡፡ በንጽሕና ሆናችሁ ባትቀርቡ እኔ ከበደላችሁ ንጹሕ ነኝ” ብሎ እጁን የሚታጠበው፡፡ ዲያቆኑም ተቀብሎ “ይህን የቄሱን ቃል ያቃለለ ወይም የሳቀና የተነጋገረ ወይም በቤተክርስቲያን በክፋት የቆመ ቢኖር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዳሳዘነው በእርሱም እንደተነሣሣ ይወቅ ይረዳ ስለበረከት ፈንታ መርገምን ስለኃጢአት ሥርየት ፈንታ ገሃነመ እሳትን ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቀበላል” ይላል፡፡ ይህ አዋጅ የሚታወጀው ከክርስቶስ ሥጋና ደም ርቀን እንድንቆም ወይም የበይ ተመልካቾች እንድንሆን ተፈልጎ ወይም ለማስፈራራት ተብሎ አይደለም ንስሓ ገብተን፣ የበደልነውን ይቅር ብለን፣ የቀማነውን መልሰን፣ ተዘጋጅተን በንጽህና ሆነን እንድንቀበል ነው እንጅ፡፡ በድፍረት በኃጢአት እንደተጨማለቁ ተዘሎ የሚበላና የሚጠጣ አይደለም ፍዳ መቅሰፍት ያመጣልና፡፡ ጠላት ግን ይህንን አዋጅ እያሳሰበና እንደተመቸው እየተረጎመ “ሥጋ ወደሙን ለመቀበል የበቃህ አይደለህም” ብሎ ከሥጋ ወደሙ ያርቅሃል፡፡ የአዋጁ ዋና መልእክት ንስሓ ገብታችሁ፣ ከንስሓ አባታችሁ ጋር ጨርሳችሁ ቅረቡ የሚል ነው፡፡ በዚህ ድል ስትነሳው ደግሞ “አንተ ገና ወጣት ነህ ሽማግሌዎች እንኳን ሳይቆርቡ ያንተ ቁርባን ምንድን ነው” ይልሃል፡፡ አንተ ምክሩን አትቀበል “ሽማግሌዎች የራሳቸው ነፍስ ነው ያላችው እኔም እንደዚሁ የራሴ ነፍስ ነው ያለኝ  ስለዚህ እነርሱ ስላልቆረቡ እኔ መቁረብ የለብኝም? በወጣትነት ዘመንህ ፈጣሪህን አስብ ተባልኩ እንጅ ሽማግሌዎች የሚሠሩትን እያየህ እንደእነርሱ ሁን አልተባልኩም፡፡ በእርግጥ በጎ ሥራ ሲሠሩ ልመስላቸው ግድ ነው መጥፎ ሲሠሩ ግን ልመስላቸው አልሻም፡፡ እነርሱ የሚቆርቡበት የራሳቸው ጊዜ ሊኖራቸው ይችላል የእኔ ጊዜ ግን ዛሬ ብቻ ነው” ብለህ አሳፍረው፡፡ ይህን ሁሉ ብለህ ስታሸንፈው ደግሞ እንደለመደው ከንቱ ውዳሴን ይጨምርብሃል፡፡ ቆራቢ እንድትባል ብቻ መቁረብን ያለማምድሃል፡፡ ከዚያ በኋላ ልምድ ያደርግብህና ሳትዘጋጅ ንስሓ ሳትገባ በድፍረት መቅረብን ያለማምድሃል፡፡ ስለዚህ በጣም ጥንቃቄ ልታደርግ ያስፈልጋል፡፡ ሥጋና ደሙን ለመቀበል የግድ ንስሓ መግባት ከንስሓ አባት ጋር መወያየትን ይጠይቃል፡፡ የዘላለም ሕይወትን ለማግኘት ስትሻ የዘላለም ቅጣት እንዳይመጣብህ ተጠንቀቅ፡፡