Tuesday, April 30, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 77

====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው።
በከመ ተፈነዉ ሐዋርያት።
ምዕራፍ ፲፩።
                    ******   
፩፡ ወሶበ ፈጸመ እግዚእ ኢየሱስ አዝዞቶሙ ለ፲ወ፪ቱ ኃለፈ እምህየ ከመ ይምሀር ወይስብክ ውስተ አህጉሬሆሙ።
                   ******   
፩፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርክቶስ ይኸን አስተምሮ ከፈጸመ በኋላ በየሀገራቸው ዙሮ ሊያስተምር ሔደ።
                    ****** 
በእንተ ኢየሱስ ወበእንተ አርዳኢሁ ለዮሐንስ መጥምቅ፡፡
፪፡ ወሰሚዖ ዮሐንስ ምዳባሮ ለእግዚእ ኢየሱስ እንዘ ሀሎ በቤተ ሞቅሕ ፈነወ ኀቤሁ ፪ተ እምአርዳኢሁ። ሉቃ ፯፥፲፰።
                    ******     
፪፡ ዮሐንስ መጥምቅ በግዞት ቤት ላለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያደረገውን ታምራት ያስተማረውን ትምርት የሠራውን ትሩፋት በሰማ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ወደሱ ላከ አካውህ እሰጢፋኖስ ይባላሉ፡፡
                    ******     
፫፡ ወይቤሎ አንተኑ ዘትመጽእ፡፡
                    ******     
፫፡ ትመጣለህ ብለን ተስፋ የምናደርግህ አንተ ነህ
ወቦኑ ባዕድ ዘንሴፎ።
ወይም ይመጣል ብለን ተስፋ የምናደርገው ሌላ አለ ብሎ
(ሐተታ) እሱ ተጠራጥሮ አይደለም እኒህ ተጠራጥረው ነበርና አይተው አምላክነቱን ይረዱት ብሎ ነው እንጂ።
                    ******     
፬፡ ወአውሥአ ወይቤሎሙ ሐዊረክሙ ዜንውዎ ለዮሐንስ ዘርኢክሙ ወዘሰማዕክሙ።
                    ******     
፬፡ ሂዳችሁ ያያችሁትን የሰማችሁትን ለዮሐንስ ንገሩት ለዮሐንስ ልቡናችሁ ንገሩት
                    ******     
፭፡ ዕውራን ይሬዕዩ። ኢሳ ፴፭፥፭-፮፡፡
                    ******     
፭፡  ዕውራነ ሥጋ በተአምራት ዕውራነ ነፍስ በትምህርት ይድናሉ
ሐንካሳን የሐውሩ
ሐንካሳነ ሥጋ በተአምራት ሐንከሳነ ነፍስ በትምህርት ይድናሉ
እለ ለምጽ ይነጽሑ።
ልሙፃነ ሥጋ በተአምራት ልሙፃነ ነፍስ በትምህርት ይድናሉ
ወጽሙማን ይሰምዑ ።
ጽሙማነ ሥጋ በተአምራት ጽሙማነ ነፍስ በትምህርት ይሰማሉ
ወሙታን ይትነሥኡ።
ሙታነ ሥጋ በተአምራት ሙታነ ነፍስ በትምህርት ይነሣሉ።
ወነዳያን ይዜነዉ።
ይብዕሉ ሲል ነው ነዳያነ ሥጋ በተአምራት ነዳያነ ነፍስ በትምህርት ይከብራሉ።
                    ******     
፮፡ ወብፁዕ ውእቱ ዘኢተዓቅፈ ብየ።
                    ******     
፮፡ ነገር ግን ሰውነቴን አይቶ ዕሩቅ ብእሲ ያላለኝ ንዑድ ክቡር ነው።
(ሐተታ) ጌታ ገልጾ አምላክ እኔ ነኝ አላላቸውም እንዳንድ ፈላስፋ፡፡ አባቱ ሙቶ ያባቱን ቤተ ሰብና የሱን ቤተ ሰብ እየገዛ ሲኖር እየተጣሉ ቢያስቸግሩት ከፈላስፋ ሂዳችሁ ጠይቁልኝ ብሎ ሰዎች ላከ ሂደው ቢነግሩት ዝም አለ፡፡ ኋላ ካታክልት ቦታ ገብቶ የወራውን እየነቀለ ያልወራውን አፈር እያሳቀፈ ቈይቶ መጥቶ ተቀመጠ። ይነግረናል ብለው ቢያዩ  የማይነግራቸው ሆነ ተመልሰው ሄዱ ምን አላችሁ አላቸው። ቀንቶ ቢያየን ከመንገር በተቈጠረ ነበር አሉት። ያውቅለታልና ምን ሲያደርግ ነበር አላቸው። ሂደን ብንነግረው ዝም አለን። ኋላ ከተክል ቦታ ገብቶ የወራ የወራውን ነቅሎ ያልወራውን አፈር እያስታቀፈ ቈይቶ ተመልሶ ተቀመጠ። ይነግረናል ብለን ብናይ የማይነግረን ሆኖ መጣን አሉት። እናንተ ባታውቁት ነው እንጂ እሱስ ነግሯችኋል። የወራውን መንቀሉ ያባትህን ቤተ ሰብ አሰናብት ሲለኝ  ነው። ያልወራውን አፈር ማስታቀፉ ያንተን ቤተ ሰብ ገዝተህ ኑር ሲለኝ ነው ብሎ ያባቱን ቤተ ሰብ አሰናብቶ የሱን ቤተ ሰብ እየገዛ በጤና የሚኖር ሁኑዋል። እንደዚህም ሁሉ ያ ሥራ ሠርቶ አሳያቸው እንጂ ገልጾ እንዳልነገራቸው ጌታም ታምራት አድርጎ አሳያቸው እንጂ ገልጾ አምላክ እኔ ነኝ አላላቸውም።
                    ******     
ዘከመ ወደሶ እግዚእ ኢየሱስ ለዮሐንስ መጥምቅ።
፯፡ ወሶበ ኃለፉ እሉ ላዕካነ ዮሐንስ አኀዘ ይበሎሙ ለሕዝብ በእንተ ዮሐንስ መጥምቅ። ሉቃስ ፯፥፳፬፡፡
                    ******     
፯፡ ከዮሐንስ ተልከው የመጡት ከሄዱ በኋላ  የዮሐንስ መጥምቅን ነገር ለሕዝቡ ይነግራቸው ጀመር። ዮሐንስ መላኩ ተጠራጥሮ እንዳይደለ ሄደው ይረዱት ብሎ እንደ ሆነ፡፡ ሳሉ አለመናገሩ ከሄዱ በኋላ መናገሩ ቢሆን አመስግኖ ቢልከበት አመስግኖ ላከበት ባሉ ነበርና።
                    ******     
፰፡ ምንተኑመ ወፃእክሙ ገዳመ ትርአዩ።
፰፡ በገዳም ምን ልታዩ ወጥታችኋል።
                    ******     
   ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
22/08/2011 ዓ.ም

Sunday, April 28, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 76

====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው።
በከመ ተፈነዉ ሐዋርያት።
ምዕራፍ ፲።
                   ******   
፴፪፡ ኩሉ ዘየአምን ብየ በቅድመ ሰብእ አነኒ አአምኖ በቅድመ አቡየ ዘበሰማያት። ማር ፰፥፴፰፡፡ ሉቃ ፱፥፴፮፡፡ ፲፪፥፰፡፡ ፪፡ጢሞ ፪፥፲፪።
                   ******   
፴፪፡ በሰው ፊት ያመነብኝ ማለት ዘመን የወለደውን ንጉሥ የወደደውን ሳይል በሰው ፊት ያመነብኝን በሰማያዊ አባቴ ፊት ልጄ ወዳጄ እለዋለሁ።
                   ******
፴፫፡ ወለዘሰ ክህደኒ በገጸ ሰብእ አነኒ እክህዶ በገጸ አቡየ ዘበሰማያት።
                    ******   
፴፫፡ ዘመን የወለደውን ንጉሥ የወደደውን ብሎ በሰው ፊት ያላመነብኝን ግን እኔም በሰማያዊ አባቴ ፊት ወለድኩህ ካድኩህ እለዋለሁ፡፡
አንድም በቤተ ዮሴፍ ስበላ ስጠጣ አይቶ እሩቅ ብእሲ ነው ያላለኝን ልጄ ወዳጄ እለዋለሁ። ከቤተ ዮሴፍ ስበላ ስጠጣ አይቶ እሩቅ ብእሲ ያለኝን ግን በሰማያዊ አባቴ ፊት ወለድኩህ ካድኩህ እለዋለሁ፡፡
                    ******   
፴፬፡ ኢይምሰልክሙ ዘአምጻእኩ ሰላመ ለብሔር።
                    ******   
፴፬፡ ለሰው ፍቅርን አንድነትን ያመጣሁ አይምሰላችሁ ኢያምጻእኩ ይላል አላመጣሁም።
አላ መጥባሕተ ።
ሰይፍን ነው እንጅ ማለት ፀብን ክርክርን መለያየትን ነው እንጅ።
                    ******   
፴፭፡ ወመጻእኩሰ አፍልጥ ብእሴ እምአቡሁ።
                    ******   
፴፭፡ ወንድ ልጅን ከአባቱ፡፡
ወወለተኒ እምእማ።
ሴት ልጅን ከናቷ።
ወመርዓተኒ እምሐማታ።
መርዓትን ከአማቷ ልለይ መጥቻለሁ እንጅ።
(ሐተታ) አማትና ምራት ሳይስማሙ ከመሬት እንዲሉ የማይስማሙ ያሉ አይደለምን ቢሉ በሚስማሙት መናገር ነው።
አንድም ወመጻእኩ እፍልጥ ብእሴ እምአቡሁ ብለህ መልስ ወንጌልን ከኦሪት ወወለተኒ፤ አሠርቱ ቃላትን ከሥርዓት ረበናት ወመርዓተኒ ነቢያት ካህናትን ከምኵራብ ልለይ መጥቻለሁ እንጅ፤
አንድም ብእሴ እምአቡሁ ሰውን ከግብር አባቱ ከሰይጣን። ወወለተኒ ፈቃደ ነፍስን ከፈቃደ ሥጋ። ወመርዓተኒ ውሣጣዊት ግብርን ከአፍአዊት ግብር ልለይ መጥቻለሁ እንጅ።
                    ******   
፴፮፡ ወሰብአ ቤቱ ይጻረሮ ለሰብእ፡፡ ማር ፯፥፮፡፡
                    ******   
፴፮፡ ሰውን ቤተ ሰቦቹ ይጣሉታል ዘመን የወለደውን ንጉሥ የወደደውን ይዘህ መስለህ አትኖርም ይሉታል፡፡
አንድም መከራ እቀበላለሁ ባለ ጊዜ ሕዋሳቱ ይፈሩበታል
አንድም ሰብአ ቤቱ ይሁዳ ክርስቶስን ያሰቅለዋል።
                    ******   
፴፯፡ ዘያፈቅር አባሁ ወእሞ እምኔየ ኢይደሉ ሊተ ወኢይክል ይጸመደኒ። ሉቃ ፲፱፥፳፯።
                    ******   
፴፯፡ አባት እናት ክደዋል ልጆች አልካዱም። በሃይማኖት እናት አባቴን ካልመሰልኩ ርስቱን ጉልቱን ለሌላ ያወርሱብኝ የለም ብሎ በሃይማኖት ጊዜ ከኔ ይልቅ አባት እናቱን የወደደ ሰው የኔ ደቀ መዝሙር ሊባል አይገባውም እኔን ሊያገለግለኝ አይቻለውም።
ወዘያፈቅር ወልዶ ወወለቶ እምኔየ ኢይደሉ ሊተ።
አሁን ልጆች ክደዋል ኦባት እናት አልካዱም በሃይማኖት ልጆቼን ካልመሰልኋቸው ኋላ ማን ይረዳኛል ማን ያጸባኛል ብሎ በሃይማኖት ከእኔ ይልቅ ልጆቹን የወደደ የኔ ደቀ መዝሙር ሊባል አይገባውም፡፡
ወኢይክል ይጸመደኒ ።
ሊያገለግለኝ አይችልም።
                    ******   
፴፰፡  ዘኢያጥብዓ ወዘኢነሥአ መስቀለ ሞቱ ወዘኢተለወኒ ኢደደሉ ሊተ።
                    ******   
፴፰፡  ጨክኖ ነፍሱን ከሥጋው የሚለይበትን መከራ ተቀብሎ በመከራ ካልመሰለኝ የኔ ደቀ መዝሙር ሊባል አይገባውም።
                    ******   
፴፱፡ ዘረከባ ለነፍሱ ለይግድፋ። ሉቃ ፱፥፳፬፡፡ ፲፯፥፴፫፡፡ ዮሐ ፲፪፥፳፭፤
                    ******   
፴፱፡ በተፈጥሮ ያገኛት ሰውነቱን በሃይማኖት በጥምቀት ይጣላት
ወዘገደፋ ለነፍሱ በእንቲአየ ይረክባ።
በሃይማኖት በጥምቀት የጣላት ሰውነቱን ይረክባ በኀቤየ በኔ ዘንድ ጽድልት ብርህት ሆና ያገኛታል፡፡
አንድም ዘረከባ በሃይማኖት በጥምቀት ያገኛት ሰውነቱን በገራህተ መስቀል ይጣላት። ወዘገደፋ በእንቲአየ በኔ ስላመነ በገራህተ መስቀል የጣላት ሰውነቱን በክብር ያገኛታል።
                    ******   
፵፡ ዘኪያክሙ ተወክፈ ኪያየ ተወክፈ፡፡ ሉቃ ፳፥፲፮፡፡ ዮሐ ፲፫፥፳፡፡
                    ******   
፵፡ እናንተን የተቀበለ እኔን ተቀበለ ማለት እናንተን በተቀበለ እኔ አድርበታለሁ
ወዘኪያየ ተወክፈ ተወክፎ ለዘፈነወኒ።
እኔን የተቀበለም አባቴን ተቀበለ ማለት እኔ ባደርሁበት አባቴ ያድርበታል።
                    ******   
፵፩፡ ወዘተወክፈ ነቢየ በስመ ነቢይ አስበ ነቢይ ይነሥእ ።
                    ******   
፵፩፡  መምህሩን መምህር ብሎ የተቀበሉ መምህሩ የሚያገኘውን እኔ የምሰጠውን ዋጋ ያገኛል።
ወዘተወክፈ ጻድቀ በስመ ጻድቅ ዓስበ ጻድቅ ይነሥእ።
እውነተኛውን መምህር እውነተኛ መምህር ብሎ የተቀበለ መምህሩ የሚያገኘውን እኔ የምሰጠውን ዋጋ ያገኛል።
አንድም ዘተወክፈ ነቢየ።
ስለ አምላከ ኢሳይያስ ስለ አምላከ ኤርምያስ ብሎ ድሀውን የተቀበለ እኔ የምሰጠውን ነቢይ የሚያገኘውን ዋጋ ያገኛል። ከብተ ነቢ እንዲሉ
ወዘተወክፈ ጻድቀ ስለ አምላከ እንጦንስ ወመቃርስ ስለ አምላከ ተክለ ሃይማኖት ስለ አምላከ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ብሎ ድኃውን የተቀበለ ጻድቁ የሚያገኘውን እኔ የምሰጠውን ዋጋ ያገኛል። ዝራዕ እክለከ ውስተ መቃብረ ጻድቃን ዕደው ጻድቃን የሀልው ውስተ ምሳህክ ወለእመ እግረ ጻድቃን ሐፀበት እንዲል።
አንድም ነቢየ ያነሥእ ለክሙ ተብሎ የተነገረልኝ እኔን እውነተኛ የባሕርይ አምላክ ብሎ ያመነብኝ እኔ የምሰጠውን ዋጋ ያገኛል። ወዘተወክፈ ጻድቀ ብእሴ ጻድቀ ዘጽድቀ ይነግረክሙ እንዲል እውነተኛ መምህር የባሕርይ አምላክ ብሎ የተቀበለ እኔ የምሰጠውን ዋጋ ያገኛል።
                    ******   
፵፪፡ ወዘአስተየ ለ፩ዱ እምእሉ ንዑሳን ጽዋዓ ማይ ቈሪር ባሕቲቶ በስመ ረድእየ አማን እብለክሙ ኢየኃጕል ዓስቦ ማር ፱፥፵፡፡
                    ******   
፵፪፡ ቈሪር ቈሪረ ይላል ንዑሳን የብዕል የቊጥር ስለ አምላከ ጴጥሮስ ስለ አምላከ
ጳውሎስ ብሎ በኔ ካመኑ ምዕመናን ላንዱ ጽዋ ውሃ ያጠጣ ዋጋውን አያጣም ብዬ እንዳያጣ በእውነት እነግራችኋለሁ
(ሐተታ) ጠጅ ጠላ ሳለው አደደለም ባይኖረው ነው እንጂ። ሳለውስ እንዳይገባ ለማጠየቅ እመቦ ብእሲ ዘቦ ዝክር ሠናይ ወያበውእ በግዓ ንውረ ርጉም ውእቱ ትላለች ኦሪት ካልጀመሩት አይሆንምና ዘአስተየ አለ።
አንድም ወርቁንም ዕንቊንም ጽዋዓ ማይ በማለት ተናገረው የመንግሥተ ሰማይ ዋጋ አይሆንምና።
                    ******   
ምዕራፍ ፲፩።
፩፡ ወሶበ ፈጸመ እግዚእ ኢየሱስ አዝዞቶሙ ለ፲ወ፪ቱ ኃለፈ እምህየ ከመ ይምሀር ወይስብክ ውስተ አህጉሬሆሙ።
፩፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርክቶስ ይኸን አስተምሮ ከፈጸመ በኋላ በየሀገራቸው ዙሮ ሊያስተምር ሔደ።
                    ******     
ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
21/08/2011 ዓ.ም

Thursday, April 25, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 75

====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው።
በከመ ተፈነዉ ሐዋርያት።
ምዕራፍ ፲።
                   ******   
፳፫፡ ወሶበ ይሰድዱክሙ እምዛቲ ሀገር ጕዩ ውስተ ካልዕታ።
                   ******   
፳፫፡ ከአንዱ አገር አስወጥተው ቢሰዷችሁ ወደ አንዱ አገር ሽሹ፡፡
አማን እብለክሙ ኢይትፌጸማ አኅጉረ እስራኤል እስከ ሶበ ይመጽእ ወልደ አጓለ እመሕያው
ከአንዱ ወደ አንዱ ስንል ያለ ክብር መቅረታችን አይደለምን ትሉኝ እንደሆነ። ወልደ እጓለ እመሕያው እስኪመጣ ማለት እኔ መጥቼ እስካድርባችሁ ድረስ የእስራኤል ዘነፍስ አገር አትፈጸምም ብዬ እንዳትፈጸም በእውነት እነግራችኋለሁ።
አንድም ምድረ እስራኤል ጸባብ ናት በስምንት ቀን ትፈጸም የለምን ትሉኝ እንደሆነ ወልደ እጓለ እመሕያው እኔ እስክመጣ ጠባቢቱ ምድረ እስራኤል ቅሉ እንዳትፈጸም በእውነት እነግራችኋለሁ
                   ******   
፳፬፡ አልቦ ረድእ ዘየዓቢ እምሊቁ፡፡ ሉቃ ፮፥፵፡፡ ዮሐ ፲፫፥፲፮፡፡ ፲፭፥፳፡፡
                   ******   
፳፬፡  በዚያውም ላይ ከመምህሩ የሚበልጥ ደቀ መዝሙር የለም።
ወኢገብርኒ ዘየዓቢ እምእግዚኡ።
ከጌታውም የሚበልጥ ባሪያ የለም ከሳኦል ዳዊት ከሐናንያ ቅዱስ ጳውሎስ ይበልጡ የለምን ቢሉ የኒያ መብለጣቸው ሳሉ አይደለም።
                   ******   
፳፭፡ መጠኑ ለረድእ እምከመ ኮነ ከመ ሊቁ።
                   ******   
፳፭፡ የደቀ መዝሙር መጠኑ እንደ መምህሩ ቢሆን ነው እንደ መምህሩ ቢሆን እንጂ ነው እንደ መምህሩ ቢሆን በጎ ነው። እንደ መምህሩ ቢሆን መጠኑ ነው ወለገብርኒ ከመ እግዚኡ የባሪያም መጠኑ እንደ ጌታው ነው እንደ ጌታው ቢሆን ነው እንደ ጌታው ቢሆን እንጂ ነው፤ እንደ ጌታው ቢሆን መጠኑ ነው።
ወሶበ ኮነ ለበዓለ ቤት በብዔል ዜቡል እፎ ፈድፋደ ለሰብአ ቤቱ አምጻኤ ዓለማት ፈጣሬ ዓለማት እኔን በብዔል ዜቡል ያወጣቸዋል ካሉኝ እናንተንማ እንደምን አይሏችሁ።
                   ******   
፳፮፡ ኢትፍርህዎሙኬ እንከ። ማር ፬፥፭፡፡ ሉቃ ፰፥፲፯፡፡ ፲፪፥፪፡፡
                   ******   
፳፮፡ አትፍሯቸው።
እስመ አልቦ ክዱን ዘኢይትከሰት ወአልቦ ኅቡዕ ዘኢይትዓወቅ።
የማይገለጽና የማይታወቅ የለምና ማለት የናንተ ተርታነት የነሱ ደግነት ሳይገለጥ አይቀርምና።
                   ******   
፳፯፡ ዘነገርኩክሙ በጽልመት ንግርዎ በብርሃን ።
                   ******   
፳፯፡ በጨለማ የነገርኋችሁን በብርሃን አስተምሩት።
ወዘኒ አልኆሰስኩ ውስተ ዕዝንክሙ ስብክዎ በዲበ አንሕስት
በጆሮዋቸሁ የነገርኋችሁን በሰገነት ወጥታችሁ አስተምሩት፤
(ሐተታ) ለመቶ ፳ ሰው ማስተማሩን በጨለማ በጆሮ መናገር ብሎ እንዲህ አለ።
አንድም ልጅነት ሳታገኙ የተማራችሁትን ልጅነት አግኝታችሁ አስተምሩት ልዕልና ነፍስ ሳታገኙ የተማራችሁትን ልዕልና ነፍስ አግኝታችሁ አስተምሩ።
                   ******   
፳፰፡ ኢትፍርህዎሙ ለእለ ይቀትሉ ሥጋክሙ ።
                   ******   
፳፰፡  በሥጋችሁ የሚገድሏችሁን አትፍሯቸው
ወለነፍስክሙሰ ኢይክሉ ቀቲሎታ
ነፍሳችሁን መግደል አይቻላቸውምና ።
ወባሕቱ ፍርህዎሰ ለዘእምድኅረ ቀተለ ዘቦ ሥልጣን ወይክል ነፍሰኒ ወሥጋኒ ኅቡረ አኅጕሎ በውስተ ገሃነም።
መፍራትስ ከገደለ በኋላ ነፍስና ሥጋን አዋሕዶ አሥነሥቶ በገሃነም ፍዳ ያመጣ ዘንድ ሥልጣን ያለው እሱን ፍሩት።
                   ******   
፳፱፡ አኮኑ ፪ቲ አዕዋፍ ይሰየጣ ለ፪ኤ ጸሪቀ አሶርዮን። ፪፡ነገ ፲፱፥፲፩። ግብ ፳፯፥፴፬።
                   ******   
፳፱፡ እንዲህማ ከሆነ ወድቀን ወድቀን መቅረታችን አይደለም ትሉኝ እንደሆነ፡፡ ሁለት አዕዋፍ በሁለት ሻሜ መሐልቅ ይሸጡ የለምን አሶርዮን የገበያ የሚዛን ስም።
ወአሐቲ እምኔሆን ኢትወድቅ ውስተ ምድር ዘእንበለ ያአምር አቡክመ ሰማያዊ።
ሰማያዊ አባታችሁ ሳያውቅ ከሁለቱ አንዲቱ አትጠፋም በወጥመድ አትያዝም።
                   ******   
፴፡ ወለክሙሰ ስእርተ ርአስክሙኒ ኵሉ ኍሉቊ ውእቱ።
                   ******   
፴፡ እናንተስ የራሳችሁ ፀጕር ሳይቀር የተቈጠረ ነው የተቈጠረ እንዳይጠፋ አትጠፉም።
                   ******   
፴፩፡ ኢትፍርኁኬ እስመ እምብዙኅ አዕዋፍ ትኄይሱ አንትሙ
                   ******   
፴፩፡ ከተፈጥሮተ አዕዋፍ ተፈጥሮተ ሰብእ ይበልጣልና አይዟችሁ።
አንድም አኮኑ ብለህ መልስ በኦሪት በነቢያት ያሉ ሰዎች በሃይማኖት በጥምቀት ይኖሩ የለምን ወአሐቲ እምኔሆን። በኦሪት በነቢያት ከአሉ ሰዎች ሰማያዊ አባታችሁ ሳያውቅ አንዱ አይጠፋም፤ ወለክሙሰ የናንተስ ደቀመዛሙርቶቻችሁ ሳይቀሩ የተቈጠሩ ናቸው ሥእርት አላቸው አርድእትን ፀጉር የራስ ጌጽ እንደሆነ ደቀ መዝሙር ለመምህሩ ጌጽ ነውና ፀጉር ያደገው ሲወድቅ ያላደገው ሲወጣ ደስ እንዲያሰኝ ደቀ መዝሙር ያጠናው ሲወጣ ያላጠናው ሲገባ ደስ ያሰኛልና ኢትፍርሁኬ በኦሪት በነቢያት ካሉ በሃይማኖት በጥምቀት ያላችሁ እናንት ትበልጣላችሁና አይዟችሁ፡፡
አንድም አኮኑ ብለህ መልስ በሃይማኖት በጥምቀት ያሉ ሰዎች በምክረ ካህን በፈቃደ ካሀን ይኖሩ የለምን ወአሐቲ እምኔሆን በሃይማኖት በጥምቀት ካሉ ሰማያዊ አባታችሁ ሳያውቅ አንዱ አይጠፋም ወለክሙሰ እንዳለፈው ኢትፍርሁ በሃይማኖት በጥምቀት ካሉ በምክረ ካህን በፈቃደ ካህን ያላችሁ እናንተ ትበልጣላችሁና አትፍሩ።
                   ******   
፴፪፡ ኩሉ ዘየአምን ብየ በቅድመ ሰብእ አነኒ አአምኖ በቅድመ አቡየ ዘበሰማያት። ማር ፰፥፴፰፡፡ ሉቃ ፱፥፴፮፡፡ ፲፪፥፰፡፡ ፪፡ጢሞ ፪፥፲፪።
፴፪፡ በሰው ፊት ያመነብኝ ማለት ዘመን የወለደውን ንጉሥ የወደደውን ሳይል በሰው ፊት ያመነብኝን በሰማያዊ አባቴ ፊት ልጄ ወዳጄ እለዋለሁ።
                   ******   
ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
17/08/2011 ዓ.ም

Tuesday, April 23, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 74


====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው።
በከመ ተፈነዉ ሐዋርያት።
ምዕራፍ ፲።
                   ******    
፲፮፡ ወናሁ አነ እፌንወክሙ ከመ አባግዕ ማዕከለ ተኲላት። ሉቃ ፲፥፫፡፡
                   ******    
፲፮፡ ተኲላ አለና ብለው አባግዕን ከቤት እንዳያውሏቸው ተኲላ ወዳለበት እንዲያሰማሯቸው፡፡
ወደ ነገሥተ አሕዛብ ወደ መኳንንተ አሕዛብ እሰዳችኋለሁና።
ኩኑ እንከ ጠቢባነ ከመ አርዌ ምድር ወየውሃነ ከመ ርግብ
እንደ እባብ ብልህ ሁኑ እንደ ርግብም የዋህ ሁኑ።
አንድም በሉቃስ እፌንወክሙ ማዕከለ ተኩሉት ይላል። ወደ ነገሥተ አሕዛብ ወደ መኳንንተ አሕዛብ እሰዳችኋለሁና ኩኑ ጠቢባነ።
(ሐተታ) የእባብ ብልሃቱ ምንድነው ቢሉ ከመንገድ ዳር ሲተኛ ራሱን ቀብሮ ይተኛል እናንተም ራሳችሁን እኔን አትካዱኝ ሲል።
አንድም ውሀ ሲጠጣ መርዙን ከየብስ አኑሮ ነው ከውሀው የገባ እንደሆነ ተሰራጭቶ ያጠፋኛል ብሎ እናንተም ቂም በቀል ይዛችሁ አትጸልዩ ሲል ቂም በቀል ይዞ የጸለዩት ጸሎት አይረባም አይጠቅምምና።
እስመ ዘይነብር ቂመ ውስተ ልቡ ኢውክፍት ጸሎቱ ቅድመ እግዚአብሔር አንዲል አንድም በኖኅ ጊዜ አፉን ከፍቶ ሳለ ርግብ ዋሻ መስሏት ገብታ እንቊላሏን ጣለች እሷን የበላኋት እንደሆነ ኖኅ አስወጥቶ ይጥለኛል ብሎ እስክትወጣ አፉን እንደከፈተ ቆይቷል ምክንያት አድርጎ እናንተን የሚያጠፋበትን ሥራ አትሥሩ ሲል ነው።
አንድም ዕፀ ዘዌ የሚባል ፍሬውን ይወደዋል ጥላው ሲያርፍበት ያደክመዋል ብልህ ነውና ጧት በምሥራቅ ማታ በምዕራብ ሁኖ ይመገበዋል ምክንያት አድርጎ እናንተን የሚያዳክምበትን ሥራ አትሥሩ ሲል
አንድም ጥግ ሳይዝ አይጣላም ምክንያት አድርጎ እናንተን የሚጣላበትን ሥራ አትሥሩ ሲል ራቁቱን የሆነ አይነድፍም ምክንያት አድርጎ እናንተን የሚጣላበትን ሥራ አትሥሩ ሲል፤ ርግብ የዋህ ናት በቀል የላትም እናንተም ኃዳግያነ በቀል ሁኑ ሲል በኖኅ ጊዜ ዋሻ መስሏት ከዘንዶ አፍ ገብታ በየውሃት ተጠብቃለች እናንተም በየውሃት ሆናችሁ ተጠብቃችሁ ኑሩ ሲል፡፡
አንድም ከፅፀ ዘዌ ሥር አርፋ በየውሃት ትጠበቃለች። እናንተም በየውሃት ተጠብቃችሁ ኑሩ ሲል። ፀሐይ ልትሞቅ ስትወጣ በምዕራብ ሸምቆ ቈይቶ እያነቀ ይፈጃታል። እናንተም በየውሃት ሁናችሁ መከራውን ተቀበሉ ሲል።
                   ******    
፲፯፡ ወተዓቀቡ እምሰብአ እኵያን
                   ******    
፲፯፡ ከክፉ ሰዎች ተጠበቁ
እስመ ያገብኡክሙ ውስተ አዕዋዳት አዳርሱን ብለው ወደ አደባባይ ይወስዷችኋልና
ወይቀሥፉክሙ በምኵራባቲሆሙ
በምኵራባቸው አግብተው ይገርፏችኋልና
                   ******    
፲፰፡ ወይወስዱክሙ ኀበ መሳፍንት ወነገሥት በእንቲአየ
                   ******    
፲፰፡  በስሜ ስለ አመናችሁ በስሜ ስለ ተጠራችሁ በስሜ ስለ አስተማራችሁ ወደ መኳንንተ አሕዛብ ወደ ነገሥተ አሕዛብ ይወስዷችኋልና፤
ከመ ይኩን ስምዓ ላእሌሆሙ
በእስራኤል መፈራረጃ ይሆንባቸው ዘንድ ምነው ያላመናችሁበት ይሏቸዋል ምን አይተን እንመን ይላሉ ያውሳ በጸባብ ደረት በአጭር ቁመት ተወስኖ ቢያስተምራችሁ ጸልታችሁ ተመቅኝታችሁ ሰቅላችሁ የገደላችሁት ተብሎ፡፡
አንድም ምነው ያላመናችሁበት ይሏቸዋል ምን አይተን እንመን ይላሉ ያውሳ ሐዋርያት የሱን ነገር ቢያስተምሯችሁ አንቀበላቸው ብላችሁ ለአሕዛብ እያሳለፋችሁ ትሰጧቸው የነበረ ተብሎ።
ወላዕለ አሕዛብ
በአሕዛብም መፈራረጃ ይሆንባቸው ዘንድ። ምነው ያላመናችሁበት ይሏቸዋል ምን አይተን እንመን ይላሉ። ያውሳ ሐዋርያት የሱን ነገር ወረደ ተወለደ ብለው ቢያስተምሯቸው አይሁድ አንቀበላቸው ብለው አሳልፈው ሰጥተዋችሁ የቊልቊሊት ትሰቅሏቸው አቅማዳ ታወጧቸው የነበረ ተብሎ።
                   ******    
፲፱፡ ወሶበ ያገብኡክሙ ኢተሐልዩ ዘትብሉ ወዘትነቡ። ሉቃ ፲፪፥፲፩፡፡
                   ******    
፲፱፡  አዳርሱን ብለው በወሰዷችሁ ጊዜ የምትናገሩትን አታስቡ ማለት አንዲህ ቢሉን እንዲህ ብለን እንመልሳለን ብላችሁ አታስቡ፡፡
እስመ ይትወሀበክሙ በይእቲ ሰዓት ዘትትናገሩ።
የምትናገሩት ፈጥኖ ይሰጣችኋል ማለት በጠየቋችሁ ጊዜ የምትመልሱት ይገለጽላችኋልና፡፡
                   ******    
፳፡ እስመ ኢኮንክሙ አንትሙ ዘትትናገሩ አላ መንፈሱ ለአቡክሙ ውእቱ ይትናገር በላእሌክሙ።
                   ******    
፳፡ የምትናገሩት እናንተ አይደላችሁምና የሰማይ አባታችሁ የእግዚአብሔር ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስ በእናንተ አድሮ ይናገራል እንጂ።
                   ******    
፳፩፡ ወያገብእ እኁ አኅዋሁ ለሞት
                   ******    
፳፩፡ በሃይማኖት ወንድም ወንድሙን ለሕማም ለሞት አሳልፎ ይሰጣል።
ወአብኒ ወልዶ
አባት ልጁን ኅርማኖስ ፊቅጦርን አሳልፎ እንደ ሰጠው
ወይትነሥኡ ውሉድ ላእለ አዝማዲሆሙ።
ልጆችም በአባት በእናታቸው በጠላትነት ይነሡባቸዋል
ወይቀትልዎሙ።
ይጣሏቸዋል
ወትከውኑ ጽሉዓነ በኅበ ኵሉ ሰብእ በእንተ ስምየ።
በኔ ስም ስላመናችሁ በኔ ስም ስለ ተጠራችሁ በኔ ስም ስለ አስተማራችሁ በሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤
ወዘአዝለፈ ትዕግሥቶ ውእቱ ይድኅን፡፡
ታግሦ መከራውን የተቀበለ እሱ ይድናል እስከ ፍጻሜ ይላል በሉቃስ እስከ ዕለተ ሞት መከራውን የታገሠ ከፍዳ የሚድን እሱ ነው፡፡
                   ******    
፳፫፡ ወሶበ ይሰድዱክሙ እምዛቲ ሀገር ጕዩ ውስተ ካልዕታ።
፳፫፡ ካንዱ አገር አስወጥተው ቢሰዷችሁ ወደ አንዱ አገር ሽሹ፡፡
                   ******    
ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
16/08/2011 ዓ.ም