ወጎች

ገንዘብና የወዳጄ ጨዋታ
አንድ ሙጫ ይቅርታ አንድ ውሪ ወይም ውርጋጥ መሳይ ብቻ ወጣት ወዳጄ ነው ስለገንዘብ አጫወተኝ አኔም ተጫወትኩለት፡፡ ንግግሩን ጀመረ “ገንዘብ ማለት የደም ሥር ነው፡፡ ሰው የደም ሥሩ ከተዛባ መኖር እንደማይችል ሁሉ ገንዘብ የሌለው ሰውም እንዲሁ ነው” አለኝ፡፡ “ምን ለማለት ፈልገህ ነው? ሰው የደም ሥሩ ከተጎዳ የደም ዝውውሩ ሊቆም ስለሚችል ሊሞት ይችላል፡፡ ነገር ግን ሰው ገንዘብ ባይኖረውም መኖር ይችላል” አልኩት፡፡ እርሱ ግን ንግግሩን ቀጠለ “አገራችን አደገች የምትባለው እኮ የነፍስ ወከፍ ገቢያችን ስለጨመረ እንጅ መንገዶች ሰለተስፋፉ፣ የትምህርት ጥራት ስለተሻሻለ፣ የጤና ዋስትናችን ስለተረጋገጠ አይደለም፡፡ ልማት የሚባለው እኮ ገንዘብ ነው! ስለዚህ ገንዘብ ለዕድገታችን ማረጋገጫ ከሆነ የደም ሥር ነው ቢባል ምን ያንሰዋል?” አለኝ፡፡ “ይህን ያህል በጣም የተጋነነ ነገር እኮ ሊኖረው የሚችል አይመስለኝም” አልኩት የውስጡን ዘርዝሮ እንዲነግረኝ በማመቻቸት አይነት ንግግር፡፡ “እንዴ! ኢትዮጵያ ውስጥ እየኖርክ እንዲህ ማለትህ በራሱ ይገርማል” ሳቅ አለ እና ንግግሩን ቀጠለ “ባለፈው አቶ በላቸው የታሰሩት እኮ ሴት ደፍረው አይደለም” አቋረጥኩትና “ታዲያ ምን ሆነው ነው?” አልኩት፡፡ “ንግግሬን አታቋርጠኝ እንጅ ምን ነካህ? አቶ በላቸው የታሠሩት እኮ ሰው ደብድበው፣ ድንበር አፍርሰው፣ ሰው ገጭተው አይደለም” አለኝ፡፡ እንዳላቋርጠው ቁጡ ስለሆነ ያኮርፍና ትቶኝ እንዳይሄድ ዝም አልኩት፡፡ እርሱ አንድን ነገር ለመናገር እንደ እንጀራ ጋጋሪ ብዙ ጊዜ ማዞር ይወዳል፡፡ “አቶ በላቸው የታሰሩት እኮ አሸባሪ ሁነው፣ ሥራ በድለው ወይም በሌላ ነገር አይደለም ገንዘብ ሰረቁ ተብሎ ነው፡፡ ማረሚያ ቤቶች የተሞሉት ገንዘብ ሠርቀዋል ተብለው በተጠረጠሩ ሰዎች ነው፡፡ ሌላ ወንጄል ሳይሰራ ቀርቶ መሰለህ ገንዘብ የደም ሥር ስለሆነ እኮ ነው” አለኝ፡፡ “ሊሆን ይችላል በእርግጥ” አልኩት እርሱም ንግግሩን በማብራራት ቀጠለ “ኢትዮጵያ ውስጥ ለገንዘብ የሚሰጠው ክብር ለዜጎች ከሚሰጠው ክብር እጅጉን ይበልጣል፡፡ ደመወዝ የሚከፍሉ ገንዘብ ያዦችን ተመልከት፡፡ ሁለት ወይም ሦስት ፖሊሶች ይመደቡላቸዋል፡፡ ያን ገንዘብ ያዥ ለመጠበቅ እንዳይመስልህ ገንዘቡን ለመጠበቅ ነው፡፡ ገንዘብ ያዡንማ ገንዘብ ሳይዝ ከቢሮ ሲወጣ ማን ከጉዳይ ይለዋል? ገንዘብ የያዘ ቀን ግን ይሰርቃል ተብሎ ተጠርጥሮ ወይም ገንዘቡ በሌላ ሰው ይሠረቃል ተብሎ ስለሚፈራ ፖሊሶች ይመደቡለታል፡፡ ምንም በማያውቀው ጣጣ እንደ ወንጀለኛ በፖሊሶች ተከብቦ ከፊት ከፊት ይሄዳል፡፡ ገንዘቡን ከፍሎ ሲመለስ ባዶ ቦርሳ ስለሆነ ማንም አይከተለውም፡፡ ጉዳት ቢደርስበት እንኳ ማንም አይደርስለት፡፡ በወር ሁለት ወይም ሦስት ቀናትን የፖሊስ ጥበቃ የሚያገኘው ስለሰውየው ክብር ሳይሆን ስለገንዘቡ ነው፡፡ ታዲያ ገንዘብ የደም ሥር ነው ማለት ምን ስህተት አለው?” አለኝ፡፡ እኔም የይሁዳ ታሪክ ትዝ አለኝና “ልክ ነህ እርሱስ ይሁዳስ አምላኩን የሸጠው ስለገንዘብ አይደል? ዮሴፍንስ ወንድሞቹ የሸጡት ስለገንዘብ አይደል? ሐናንያና ሰጲራስ የተቀሰፉ ስለገንዘብ አይደል? ጌታም በወንጌል ለሁለት ጌቶች መገዛት አይቻላችሁም አይደል ያለው፡፡ ገንዘብ እኮ እንደ አንድ ጌታ ነው በወንጌል የተቀመጠው” አልኩት፡፡ “ዝም ብለህ ታስለፈልፈኛለህ እንጅ እንዲያውስ ጠፍቶህ ነው” አለኝና ንግግሩን ቀጠለ “ሰው እኮ የሚከበረው ሃይማኖት ስላለው ወይም እውቀት ስላለው አይደለም ገንዘብ ስላለው ብቻ ነው፡፡ ሰው ስምህን ከፍ አድርጎ የሚጠራው ገንዘብ ሲኖርህ እንጅ ስታውቅ አይደለም፡፡ ብዙዎች ለጥላቸው ዋናው ምክንያት እሱው ነው፡፡ ባልና ሚስት ሰኞ ተጋብተው ማክሰኞ ፍርድ ቤት የሚካሰሱት በገንዘብ ነው፡፡ ከወረቀት ወይም ከቆዳ በተሰራ ገንዘብ ምትክ የሌላት ነፍስን የሚያጠፉ በርካቶች ናቸው፡፡ አንዳንዶች እንዲያውም ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ እያሉ ያወራሉ፡፡ ለዚህም ነው አገራችን ውስጥ ገንዘብ ለመሰብሰብ በሰዎች ሕይወት ላይ የሚረማመዱት፡፡ ገንዘብ እኮ ሬሳ ነው፡፡ ወድቆ ብታገኘውና ብታነሳው የእገሌ ነኝ አይልህም ያሉ አንድ አባት ትዝ አሉኝ፡፡ እውነታቸውን ነው አኮ!” አለኝ ገንዘብን ከደም ሥርነት ወደ ሬሳነት ቀይሮ፡፡ “ገንዘብ ካለህ እውቀት ይገዛል ምክንያቱም የእውቀት መገለጫው ወረቀት እንጅ ጭንቅላት አይደለማ! እውቀት ቢሆንማ ስንቱ በወረደ ስንቱም በወጣ ነበር፡፡ ገንዘብ ካለህ አንዱ አገር ትሄድና ብዙ ዓመት ኖረህ ዶክተር ነኝ እዚህ ቦታ ተምሬ መጣሁ እያልክ ማስወራት ነው፡፡ ወረቀቱንም በገንዘብህ ትገዛለህ በዚያውም ላይ ሃብታም ከተባልህ ሁሉም ቀና ብሎ የሚጠይቅህ የለም፡፡ እኛ የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ ይሰጠን እያልን ስንጠይቅ መዘጋጃ ቤቱ ወደ ማኅበራት፣ ማኅበራቱ ወደ ማኅበራዊ ፍርድ ቤት፣ ማኅበራዊ ፍርድ ቤቱ ወደ ቀበሌ፣ ቀበሌው ወደ ባንክ፣ ባንኩ ወደ ቤቶች ልማት እያሉ ሲያሽከረክሩን የሚውሉት ገንዘብ ስለሌለን እንጅ እውቀት ስለሌለን ወይም ስላልተማርን አይደለም እኮ፡፡ ገንዘብ ቢኖርህማ ከዚያዚያ ሳትንገላታ ዋናው ኃላፊ ላይ ቀጥታ ሄደህ ኢንቨስት ላደርግ ነበር ብለህ ስታማክረው የት አካባቢ ልስጥህ? ስንት ሄክታር ይበቃሃል? ይልህ ነበር፡፡ ለኢትዮጵያ እኮ አንተ ልጇ ትበልጣት ነበር ነገር ግን ገንዘብ ስለሌለህ ለባዕዳውያን ስትቀራመት ዝም ትላለች፡፡ ኡፍ ኧረ ተወኝ!!” አለና በረጅሙ ተነፈሰ፡፡ ገንዘብ ይህን ያህል ኃይል አለው ማለት ነው ብየ ተገረምኩና “እሽ” አልኩት፡፡ “አገራችን ከሰው ይልቅ ለገንዘብ እያደላች ነው፡፡ በቃ ምን አለው! ገንዘብ ከሌለህ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር አይቻልህም፡፡ ከተማ ውስጥ አታይም እንዴ? መስመር ዳር አካባቢ ያሉ መኖሪያ ቤቶች እኮ ሁልጊዜ ስጋት አለባቸው፡፡ ዛሬ ተነሡ እንባል ይሆን ወይስ ነገ ወይስ ደግሞ  መቼ ተነሡ እንባል ይሆን እያሉ ሲጨነቁ ዕድሜያቸውን እየገፉ የሚገኙት ጥቂት የሚባሉ መሰሉህ እንዴ? አንድ ገንዘብ ያለው ሰው ከመጣ የእነርሱ ቤት ፈርሶ ለፎቅ መሥሪያ ለእርሱ እንደሚሰጥ ያውቃሉ፡፡ ስንቱ የድሃ ቤት ፈርሶ ለባለሃቶች እየተሰጠ ታጥሮ ቀረ መሰለህ፡፡ ባለሃብት የሚባሉትም አይሰሩበትም ድሃዎችም አይኖሩበትም፡፡ ብቻ አጥር ይታጠርና ይቀመጣል፡፡ ይገርመኛል ብቻ ምን ያህል ለገንዘብ እየተገዛን እንደሆነ በቀላሉ የሚነገር አይደለም” አለኝ እጁን እያፋተገ፡፡ “ነፍስህንም ሥጋህንም የምታጣበት ነገር ቢኖር ገ-ን-ዘ-ብ ነው” አለ ፊደላትን ረገጥ እያደረገ፡፡ “ስንቱ በዝሙት አልጋ የሚጋደመው፣ ስንቱ ወንድሙን የሚገድለው ስለገንዘብ ነው፡፡ እንደ አብርሃም የተቸገረ የሚረዳበት የተራበ የሚያበላበት፣ የታረዘ የሚያለብስበት መሰለህ እንዴ? ብቻ አምላክ ልብ ይስጠን እንጅ ልንገዛበት በፈጠርነው ነገር እየተገዛንበት ነው አኮ ያለነው፡፡ አንዳንዶችማ እንዲያውም 100 ብር ላይ የሚረዳኝ የለም እና ከእኔ አትራቅ እያሉ ይጽፉበት ጀምረዋል፡፡ አምላክን ረስቶ ለገንዘብ መገዛት መቼ ይሆን ግን የሚቆመው?” አለኝ፡፡ እኔም ከወዳጄ ጋር ስለገንዘብ ብዙ ነገር አውቄ ተለያየሁ እናንተስ ስለገንዘብ ምን ትላላችሁ?

No comments:

Post a Comment