Wednesday, August 30, 2017

ያልሰሙትን ሲናገሩ ስሰማ አፈርሁ!

© መልካሙ በየነ
ነሐሴ 25/2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ


እናንተ አንባቢዎች ሆይ! ከዚህ ጽሑፍ ጋራ የተያያዘውን ቪዲዮ ተመልከቱና እውነቱን ፍረዱ፡፡ በሁለቱም ቦታዎች ላይ ሁለቱም ሰባኪዎች ያነሷቸው ጉዳዮች ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ከታች ያስቀመጥሁላችሁንም ሊንክ ተጭናችሁ የእኔን ጽሑፍ ሙሉውን አንብቡት፡፡

1ኛ. አብማ ማርያም አትቁረቡ ክርስትና አታስነሡ ብሏል፡፡ የአብማ ማርያም አገልጋይ ካህናትም በሙሉ ክህነት የላቸውም ሁሉም ቅባቶች ናቸው በሏል የሚል ነው፡፡
2ኛ. ከምሥራቅ ጎጃም ሊቀጳጳስ መሾም መመረጥ የለበትም ብሏል የሚሉ ናቸው፡፡
3ኛ. ሊቃውንቱን የእምነት ህጸጽ አለባቸው ብሏል የሚሉ ናቸው፡፡
እኔ ግን ይህንን አላልኩም ወደፊትም አልልም፡፡ ምክንያቱም አብማ ማርያም እኮ ቤተክርስቲያናችን ናት፡፡ ቤተክርስቲያናችን ደግሞ ቅባት አይደለችም ተዋሕዶ እንጅ ግለሰቦች ላይ ነው ይህ ችግር የሚገኘው፡፡ አንዳንድ ካህናት በዚህ በቅባት እምነት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ይህንን ደግሞ ከእኔ ይበልጥ ራሳችሁ አሳምራችሁ ታውቁታላችሁ፡፡ ቅባት የሆነ ቢያንስ አንድ ካህን አለ አልኩ እንጅ አብማ ማርያም ቅባት ናት አላልኩም ወዴት ጠጋ ጠጋ ነው፡፡ እኔ አብማ ማርያምን ያነሣሁት ከዚህ ጋራ በተያያዘ ጉዳይ አልነበረም በርግጥ እነርሱ በተረዱበት መጠን ልናገር ብየ እንጅ፡፡
ከምሥራቅ ጎጃም ሊቀጳጳስ መሾም መመረጥ የለበትም አላልኩም አልልምም፡፡ እኔ ምን አገባኝና ማንስ ሆኘ ነው በእግዚአብሔር አሠራር ውስጥ ገብቼ ልፈተፍት የምችለው፡፡ እኔ ያልሁት ምሥራቅ ጎጃም አካባቢ የተወለዱት ጳጳሳት እዚህ ምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ላይ በሊቀጳጳስነት አይመደቡ ነው፡፡ ይህን የምልበት ምክንያት ደግሞ ከዚሁ ከእምነቱ ጋራ አያይዠ ስላየሁት ነው፡፡ አባ ማርቆስ ዝዋይ በቆሞስነት ሳሉ እኮ ይሠሩት የነበረውን ሥራ አሁን እዚህ በሊቀጳጳስነት ሆነው አልሠሩትም፡፡ እዚህ የአገር ልጅ የወንዝ ልጅ የሚል አጉል ኮተት ይከተላል ሌላ ቦታ ቢሆኑ ግን በሚገባ ያስተምራሉ ይሠራሉ፡፡ እዚሁ ተወላጅ የሆነ ከሆነ ግን ምን ተምረሃል ሳይሆን የት ወረዳ ነህ መባባል ይመጣል፡፡ ከዚህ አንጻር ይህንን አልኩ እንጅ መሾምማ እንዴት አይሾሙም ታላላቅ ሊቃውንት የወጡበት አገር ጎጃም እኮ ነው፡፡ ስረሳ ብውል አቡነ ቴዎፍሎስን እንዴት እረሳቸዋለሁ ሊቃውንቱንስ ቢሆን እነ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬን እነ አለቃ አያሌው ታምሩን እንዴት ከኅሊናየ ላጠፋቸው እችላለሁ አልችልም፡፡
እውነተኞቹን ሊቃውንቱ የእምነት ህጸጽ አለባቸው ያልኩበት ቦታ የለም አልልምም፡፡ ነገር ግን በካባ ብቻ ሊቅ ናቸው ማለት ይከብደኛል፡፡ በነገራችን ላይ ሊቅነት እና እምነት አንድ አይደሉም አዋቂነት እና እምነት አንድ የሚሆኑለት ሰው እርሱ ብጹእ ነው፡፡ ግን አርዮስን ያህል ሊቅ የለም ነበር ግን ምን አለ “ወልድ ፍጡር በመለኮቱ” ሎቱ ስብሐት፡፡ አዚህ የምናያቸው “ወልደ አብ” ን ያሳተሙት ገብረ መድኅን እንዳለው እኮ ሊቅ ናቸው፡፡ ግን ሊቅነታቸው እንደ አርዮስ ነው፡፡ ስለዚህ እውቀትን ወይም ሊቅነትን ከሃይማኖት ቀጥተኛነት ጋራ አታያይዙት፡፡ እነዚያማ እነ አለቃ አያሌው እነ መልአከ ብርሃን አድማሱ ናቸው፡፡

አብማ ላይ መግለጫ የሰጡትን በአካል አላውቃቸውም በርግጥ እምነታቸውም ምን እንደሆነ አላውቅም፡፡ ቅባት የሚባል አላውቅም ብለው ስለካዱ ግን እጠራጠራቸዋለሁ፡፡ ቅባት ከሌለ “ወልደ አብ” እና “ሚሥጢረ ሃይማኖት” የሚሉ መጻሕፍት ማን አሳተማቸው በሉ መልሱልኝ፡፡ በስም የጠቃቀሷቸውን መምህራንን እና ሊቃውንትን እኔ በምንም ጉዳይ አላነሣኋቸውም እርስዎ ነዎት ያነሷቸው፡፡ አሁንም እኮ “ተዋሕዶ” ብለው ሲጠሩ ድምጽዎትን በጣም ቀንሰው ነው ለምን ቀነሡት ግን፡፡ ይህንን የሚጽፈው ሰው ቅባት ይሆናል ብለው ለማጠራጠር ሞክረዋል ቅባትማ ቅባት የለም ብሎ የሚክድ ሰው ነው፡፡ ቅባት ለመኖሩ እኮ ሁለቱን ቆጋ ኪዳነ ምሕረት የታተሙትን መጥቀስ በቂ ነው፡፡

ገዳመ አስቄጥስ ላይ የተናገሩትን ሊቀ ሊቃውንት ሰሎሞን በሚገባ አውቃቸዋለሁ፡፡ ተዋሕዶን አስተምረው ምእመናንን በተዋሕዶ እምነት ያጸናሉ ብለን ተስፋ ያደረግንባቸው መምህር ነበሩ አሁን ግን የታዘዝኩትን ነው የምሠራ በሚል ምን እንደተጻፈ እንኳ ሳያነቡ መድረክ ላይ በስማ በለው ብቻ ሲያወሩ ሳይ አዘንሁላቸው፡፡ ሊቀ ሊቃውንት በእውነት ለእምነትዎ የሚጨነቁስ ከሆነ “ወልደ አብ” የተባለውን ቅባቶች ያሳተሙትን መጽሐፍ እንደሰጠንዎ በሚገባ አንብበው መልስ በሰጡበት ነበር ግን ምን ይሆናል፡፡ ለማንኛውም የጀመሩትን መንጃ ፈቃድ ያውጡና እዛው በሹፌርነት መኖሩ ይሻላል፡፡

ሁለቱም የቅባት መጻሕፍት የታተሙበትን ቦታ የቅዱሳን መገኛ ነው እያሉ ብዙ ጊዜ ደጋግመው ደጋግመው ይናገራሉ፡፡ አባታችን ይህን ቦታ የቅዱሳን መገኛ ነው ካሉ ታዲያ ምን እንጠብቃለን ቅባት ናቸው ብንል እኮ ፍርድ የለብንም፡፡ ይህንንም ከዚሁ ጋራ አያይዠላችኋለሁ ተመልከቱት፡፡

እኔ የጻፍሁትን ጽሑፍ ሙሉውን ከዚህ በታች ያለውን ሊንክ ተጭናችሁ አንብቡ እና አመዛዝኑት፡፡


=====================================
አንብባችሁ ከጨረሳችሁ አስተያየት
#comment ስጡ
#share አድርጉ፡፡

ተዋሕዶ ነን ቅባት ካለ ራሱን ይፈትሽ!

© መልካሙ በየነ
ነሐሴ 24/2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

ነሐሴ 19/2009 ዓ.ም “አክሊሌን ተንጠልጥሎ አየሁት” በሚል በራሴ ውስጥ ብቻ በኅሊናየ የሚመላለሰውን ጥያቄ መጻፌን ተከትሎ በደብረ ማርቆስ ከተማ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ መነጋገሪያ እንደነበርሁ በብዙዎች በውስጥ መስመር መረጃው ደርሶኛል፡፡ በተለይ ነሐሴ 21/2009 ዓ.ም በዕለተ ሰንበት በእናታችን በእግዝእትነ ቅድስት ድንግል ማርያም በዓል ቀን አብማ ማርያም፣ ዋሻው ቅዱስ ሚካኤል እና ግምጃ ቤት ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን ይህንን ጽሑፍ ፕሪንት በማድረግ ተአምረ ማርያምን አስተካክሎ በማንበብ ፈንታ የአንድን ግለሰብ ስሜት ሲያነብቡ እና መግለጫ ሲሰጡ እንደነበር ጠቁመውኛል፡፡ እኔ የጻፍሁት ለራሴ የተሰማኝን ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ የእኔን አስተሳሰብ መከተል አለባችሁ ብየም ማንንም አልወተውትም ማንንም ለማሳመንም ሆነ ወደ እኔ መስመር እንዲገባ አላስገድድም፡፡

#አብማ #ማርያም ላይ “አብማ አትቁረቡ አብማ የቅባት አገልጋዮች ብቻ ናቸው የሚኖሩ” ብሏል በሚል መግለጫ ሲሰጡ እንደ ነበር አውቄያለሁ፡፡ እኔ #አብማ #ማርያምን እናቴን ያሳደገችኝን ከጥንት ጀምሬ የማውቃትን ስባረክባት በረከትን ስቀበልባት የነበረችውን ቤተክርስቲያኔን እንዴት እንዲህ ልል እችላለሁ? በፍጹም ልል አልችልም ምናልባት ግን ያልተገናኘንበት የአተረጓጎም ስልት እንዳለ ተረድቻለሁ፡፡ አብማን በተመለከተ የጻፍሁት እንዲህ የሚል ነው፡፡ “ድሮ በንጹሕ ኅሊናየ ሳለሁ ቅባት ተዋሕዶ የሚለው ምሥጢር ሳይገባኝ በነበርሁበት ወቅት አብማ ማርያምን ሳልሳለም ከዋልሁ ይጨንቀኝ ነበር፡፡ ከዚህች ቦታ የማገኘው የልብ ደስታ ቀኑን ሙሉ በብሩኅ ገጽ እንድውል ያደርገኝ ነበረ፡፡ ዛሬ ግን ኅሊናየ ውስጥ የታጨቀው የሁለቱ እምነቶች ልዩነት ኅሊናየን እያረሰው በረከትን ማግኘት አላስቻለኝም፡፡ ጸሎቴን በቤቴ አድርጌ በበዓላት ቀናት እንኳ የምወዳቸውን ቤተክርስቲያናት ሳልሳለማቸው ስውል እስከመቼ በሚለው ጥያቄ ጽኑእ የኅሊና ክርክር ውስጥ እወድቃለሁ” የሚል ነው፡፡ ለምን ከደብረ ማርቆስ ከተማ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ #አብማ #ማርያምን አነሣህ ብትሉኝ መልካም ነበር፡፡ እኔ ከ1997 ዓ.ም ጀምሬ ደብረማርቆስን አውቀዋለሁ፡፡ ከዛሬ 12 ዓመት በፊት መሆኑ ነው እንግዲህ፡፡ ያኔ ከአብማ በስተምእራብ በኩል የ3 ደቂቃ መንገድ ያህል ነበር የምርቀው፡፡ እዛው #አብማ #ማርያም አጠገብ ነበርሁ፡፡ በ30 ብር በተከራየሁት ዶርሜ ውስጥ ስኖር #አብማ #ማርያም ለእኔ እጅግ ቅርቤ ነበረች፡፡ እናም #አብማ #ማርያም ሳልሳለም ከዋልሁ ይጨንቀኝ ነበር ለማለት የቻልሁት ከዚህ አንጻር ነው እንጅ ከሌላ አንጻር አይደለም፡፡ ዛሬ ግን “ቅባት” እና “ተዋሕዶ” የሚባሉ እምነቶች በአንድ ጥላ ሥር ተጠልለው ለየራሳቸው መጽሐፍ ሲደጉሱ ቅኔ ሲያፈሱ ባይ ጊዜ ኅሊናየ ውስጥ ሙግት ተፈጠረብኝ፡፡ እነዚህ የእምነት ልዩነቶችያሉት ደግሞ አብማ ማርያም ውስጥ ብቻ ነው አላልሁም፡፡ አብማ ማርያም ውስጥ አንድም የቅባት አባት የለም ሊባል ይችል ይሆናል አላውቅም እኔ ውስጥ ግን ቢያንስ በደንብ የማውቀው አንድ ቅባት የሆነ አባት አላጣም ባይ ነኝ፡፡ እርሱ ራሱን ይፈትሽ ካልሆነ አይመለከተውምና፡፡ የሚመለከተው ሰው ግን የግድ ይመለከተዋል፡፡ ስለዚህ አብማን ያነሣሁት በዚህ ምክንያት እንጅ አንድኛየን ጨርቅ ጥየ አብጀ አይደለም፡፡

#አብማ #ማርያም ላይ የእኔን ጽሑፍ ፕሪንት አድርጎ መድረክ ላይ ያነበበው አካል “እኛ ተዋሕዶዎች ነን፡፡ ቅባት የሚባል እምነት የለም፡፡ ካለም ራሱን ይፈትሽ፡፡ የሰበካ ጉባዐየ መታወቂያችሁን አውጥታችሁ እዩት እስኪ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እንጅ ኦርቶዶክስ ቅባት ይላል እንዴ” በማለት ቅባትን እንደማያውቁ አድርገው ተናግረዋል፡፡ ድከሙ ቢላችሁ እንጅ ህዝቡ እኮ ይህን ልዩነት ያወቀው ድሮ ነው፡፡ ቆጋ ኪዳነ ምሕረት ወልደ አብ እና ምሥጢረ ሃይማኖት የተሰኑ የቅባት የክህደት መጻሕፍት ሲታተሙ አልሰሙም አላዩምን ካልሰሙ ካላዩ ችግር አለ፡፡ ቅባት የለም የሚለው አነጋገር ተቀባይነት ባይኖረውም ከተዋሕዶ ውጭ ሌላ የለም ብለው በመናገራቸው ግን አመሰግናቸዋለሁ፡፡ ምን ያህል ውስጣቸውን እንደኮረኮርሁት የተረዳሁም ያኔ ነው፡፡ የሰበካ ጉባዔው መታወቂያማ “በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን” እንደሚል ይታወቃል ምክንያቱም ይህን ያሳተመችው ጥንታዊቷ ቤተክርስቲያናችን ናትና፡፡ የእኔስ ጠብ ምን ሆነና ነው፡፡ እኔ እኮ የማላዝነው ለምን በቤተክርስቲያናችን ስም ይነገድብናል ብየ እንጅ ራሱን ችሎ ለሄደውማ መብቱ ነው አምላክ የፈቀደለት እኮ ነው፡፡ መታወቂያ ደግሞ ሥምን እንጅ ግብርን የሚገልጥ አይደለም፡፡ አባታችን አቡነ ማርቆስ ሲያስተምሩ #ቅባት #ተዋሕዶ #ካራ #ጸጋ የሚባል እምነት የለም ይህ እኮ ቃል ነው ቃል ሃይማኖት ይሆናል እንዴ ብለው ማመን ወልደ አብ ወልደ ማርያም ተወለደ ብሎ ነው ክርስቲያን መባል እንጅ #ቅባት #ተዋሕዶ #ካራ #ጸጋ መባል አያስፈልግም ብለው አስተምረዋል፡፡ የዚህንም ቪዲዮ አያይዠላችኋለሁ ስሙት፡፡ ታዲያ እርሳቸው ሊቀ ጳጳስ የሚባሉት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አይደለምን ነው እንጅ፡፡ ታዲያ መታወቂያቸው ግብራቸውን እምነታቸውን ገለጠላቸውን አልገለጠላቸውም፡፡ መጠራት በማይፈልጉት ስም እኮ ነው እየተጠሩ የሚገኙት፡፡ ስለዚህ አሁንም ራሳችንን እናት ራሻችንን እንፈትሽ፡፡ የንስሐ አባት እንዲሆኑኝ ከፈለጉ የግድ በሃይማኖት እኔን መምሰል አለባቸው፡፡ በእጃቸው እንድቆርብ ከፈለጉ እምነታቸው እኔን መመስል አለበት፡፡ ልጆችን ክርስትና እንዲያነሡ ካስፈለግ በመጀመሪያ እምነታቸው እኛን መምሰል አለበት ፡፡ እኔ አሁንም ወደፊትም አቋሜ ይኼው ነው፡፡ ይህንን አቋም የምይዘው ደግሞ ዝም ብየ ሳይሆን ሕገ ቤተክርስቲያን መሠረት አድርጌ የአባቶቻችንን ትምህርት ምክንያት አድርጌ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይህ የእምነት ልዩነት ያልገባው ሰው በኅሊናው ንጹሕ ስለሆነ ቢቆርብ፣ ቢጸልይ፣ ቢሰግድ፣ ንስሐ ቢገባ በረከቱን ማንም አይቀማውም፡፡ እኔም እኮ ይህንን እንድጽፍ ያደረገኝ ይኼው ነው፡፡ በፊት ልዩነቱን ሳላውቀው በረከትን አገኝበት የነበረውን ነገር ዛሬ ላይ በረከትን አጣሁበት የበረከቴ አክሊል ከሰማይ ወርዳ እኔ ላይ ሳይሆን በንጹኅ ኅሊና ላስቀደሰው ሰው ተደረበችለት ነው፡፡  እዚህ ያስቀደሰ በረከትን አያገኝም እዚህ የቆረበ ዋጋ የለውም እዚህ የጸለየ ኃጢአት ሰርቷል አላልኩም እኮ ወገኖቼ በደንብ አንብቡት እንጅ፡፡ ሳጠቃልል የተጠቀምሁበትን ቃል እነሆ አንብቡት፡፡

ነጭ ነጠላውን አጣፍቶ መብሩቁን ለብሶ በጠዋቱ ተነሥቶ ቤተክርስቲያን ገብቶ ጸሎትን ጨርሶ ኪዳን አስደርሶ ቅዳሴውን አስቀድሶ ቆርቦ መመለስ ምንኛ ውብ ነገር ነበር፡፡ ግን ምን ይሆናል አይ አለመታደል! ሁል ጊዜ የበረከት አክሊሌ ተንጠልጥላ ትታየኛለች፡፡ ይችን አክሊል እንዳልቀዳጃት በቦታው የለውም ስለዚህም ይች አክሊል ለሌላው ትደረብለታለች ትጨመርለታለች፡፡ ይህ ሀገረ ስብከት መቼ ይሆን ከዚህ ሁሉ ነገር ነጻ ወጥቶ በአባቶቻችን እየተባረክን በጸሎታችሁ አስቡን እያልን የምንባረከው” የሚል ነው፡፡ እዚህ ላይ ልብ በሉ “ይችን አክሊል እንዳልቀዳጃት በቦታው የለውም ስለዚህም ይች አክሊል ለሌላው ትደረብለታለች ትጨመርለታለች” ነው ያልሁት ምን ማለት ይመስላችኋል፡፡ እኔ ይህ ልዩነት ኅሊናየ ውስጥ ሙግት ስለፈጠረብኝ በቦታው አልተገኘሁም በቦታው ባለመገኘቴም ለእኔ የወረደችውን አክሊል አልተቀዳጀኋትም ስለዚህም ለሌላው ተጨመረችለት ማለቴ ነው፡፡ ለሌላው የሚጨመርለት እኮ በረከትን ስላገኘበት ነው፡፡ እያስተዋልን እናንብብ እንጅ!

#ግምጃ #ቤት #ኪዳነ #ምሕረት ቤተክርስቲያን ግን የተላለፈው መልእክት በፍጹም እኔ ያላልሁት እነርሱ ብቻ የሚያውቁት ሀሳብ ነው፡፡ በእርግጥ እነርሱ ያሉትን ጉዳይ እኔም ሰምቸዋለሁ ቀድሜ አውቄዋለሁ ሆኖም ግን አደባባይ ላይ የምለጥፈው ሃሳብ አይደለም፡፡ ስለዚህ ቢያንስ እኔ ያልሁትን ብላችሁ እንድነቀፍ እና እንድወገዝ ብታደርጉ በተሸለ ነበር፡፡

#ገዳመ #ሕያዋን #ቅዱስ #ሚካኤል ቤተክርስቲያንም እንደ አብማው ተመሳሳይ የሆነ ነገር ነው የተናገሩት፡፡ ሆኖም ግን እነርሱ የተረዱበት እና እኔ የጻፍሁበት መንገድ እና ስልት ለየቅል መሆኑን ልብ በሉልኝ፡፡ በፌስ ቡክ የአባታችንን ስም እያጠፋሁ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ እኔ እርሳቸው ያላሉትን እርሳቸው ያልተናገሩትን ነገር በራሴ ፈጥሬ ጽፌ ከሆነ ከላይ አንገቴን ከታችም ባቴን ቁረጡኝ፡፡ ይኼው ከዚህ ጋራ የተያያዘውን እንኳ ተመልከቱት እስኪ፡፡

#የዛሬው ደግሞ ይባስ #ገዳመ #አስቄጥ #አቡነ #ተክለሃይማኖት ዛሬ በተከበረው የአባታችን የአቡነ ተክለሃይማኖት በዓል ላይ #ሊቀ #ሊቃውንት #ሰሎሞን ይህንኑ ተመሳሳይ መልእክት ሲያስተጋቡ መዋላቸው አስደነቀኝ፡፡ ምን አደረጋችሁ ተብለው ሲጠየቁ እኔ ከላይ ታዝዠ ነው በማለት ሲመልሱ ደግሞ ይበልጥ በሳቅ ፈረስሁ፡፡ አይ! ወይኔ! እርስዎም እንዲህ የእሳት ልጅ አመድ ይሆኑ! ከልቤ አዝንብዎታለሁ፡፡ ራስዎን ጥለው ጎስቁለው ስመለከትዎ ስለቤተክርስቲያናችን እየተጨነቁ ይመስለኝ ነበር ለካ ጭንቀትዎ ከላይ የሚመጣልዎ ትእዛዝ ነው፡፡ እስከ ላይ እስከ ሀገረ ስብከቱ ድረስ እንዲህ መነጋገሪያ ያደረጋችሁኝ ግን ምን ሳስተምር አግኝታችሁኝ ነው፡፡ እኔ ግን ከላይ ከአቡኑ እስከታችኛው ድረስ ምሥራቅ ጎጃም ውስጥ ምን እያስተማራችሁ እንደሆነ የሚያሳይ ሙሉ መረጃ አለኝ፡፡ ግን አሁን አላወጣውም ምናልባትም ከወዴት እንደቆመ አስቦ ራሱን ለቤተክርስቲያን እውነተኛ አገልግሎት አሳልፎ የሚሰጥ ሊሆን ይችላልና በትእግሥት እጠብቃለሁ፡፡
#ሊቀ #ሊቃውንት #ሰሎሞን የቅባትን ጉዳይ ያግዙናል ብለን ተስፋ ካደረግንባቸው ሊቃውንት መካከል አንዱ ናቸው፡፡ እኔ ከላይ እስከ ታች አውቃቸዋለሁ እርሳቸው ግን ከነመፈጠሬም አያውቁኝም ዛሬም ስሜን አሸምድደዋቸው ካልሆነ በቀር በጭራሽ አያውቅኝም፡፡ “ወልደ አብ” እንደታተመ መልስ ይሰጡበታል ብለን መጽሐፉን ገዝተን ሰጠናቸው በዚያው የውኃ ሽታ ሆነው ቀሩ፡፡ አሁን በቅርቡ ደግሞ “ሚሥጢረ ሃይማኖት” የሚለው ሁለተኛው መጽሐፋቸው ሲታተም እንዲሁ ገዝተን እንድንሰጣቸው በብርቱ ሲጥሩ ነበር፡፡ እኛ ግን ማንነታቸውን በሚገባ ስለተረዳን ሳንቲማችንን ማባከን አልፈለግንም ነበር፡፡ ዛሬ ግን “መልካሙ በየነ” ስለቅባት የሚጽፈው ሁሉ ውሸት ነው ለማለት በቁና አረፉት፡፡ የዚህ ንግግራቸው እና የሌሎችንም እንዲሁ በምስል አቀናብሬ የምልክላችሁ ይሆናል፡፡


በነገራችን ላይ ስማቸውን ወደፊት የምንገልጻቸው አንድ የገዳሙ የሰበካ ጉባዔ አባል “ልጆቻችን ለምን በእኛ ላይ ተነሡብን ብላችሁ ራሳችሁን ፈትሹ” ብለው አባቶችን የገሰጹበት የዛሬው ንግግራቸው ወደ እውነት ልንቀርብ ትንሽ ዳገት ብቻ እንደቀረችኝ ማሳያ ነው፡፡ የነገውን ደግሞ ማን ያውቃል ሁላችሁም ጸልዩልን!!!

ምንም በሉኝ ምን ግን በጣም ደስ የሚለኝ ነገር ቅባቶች በድብቅ የሚያካሄዱትን ሴራ አደባባይ ላይ አውጥቼ ለተዋሕዶ ልጆች ግንዛቤ መፍጠሬ ነው፡፡ ደብረ ማርቆስ ከተማ እኮ ጥቂት የሚባሉ ከሌላ ቦታ እዚህ እንዲያገለግሉ የተመደቡት ናቸው እንጅ ማኅበረሰቡማ እናውቀዋለን እኮ ጽድት ያለ ተዋሕዶ ነው፡፡ ለመቁረብ የሚያስቸግረው አንዳንድ የቅባት ካህናት አብረው ስለሚቀድሱ ነው እንጅ የማርቆስ ሕዝብማ እያነው እኮ ነው፡፡ ሌት ከቀን ተዋሕዶ ተዋሕዶ ሲል የሚውል ምርጥ የእመብርሃን ልጅ እኮ ነው፡፡ ከዚህ ህዝብስ በምንም ልትለዩኝ አትችሉም በፍጹም እኛ እና እነርሱ ተግባብተናል ያልተግባባነው ከቅባቶቹ ጋር ብቻ ነው፡፡

=====================================
አንብባችሁ ከጨረሳችሁ አስተያየት
#comment ስጡ
#share አድርጉ፡፡

Sunday, August 27, 2017

እኔ ለመነጋገሪያ አጀንዳ የበቃሁ አይደለሁም




© መልካሙ በየነ
ነሐሴ 21/2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
መረጃዎችን ለማግኘት ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/tomarthetewahido ) ላይክ ያድርጉ፡፡
===================================================

ዛሬ በእናታችን በቅድስት ድንግል ማርያም በዓል ቀን በደብረ ማርቆስ ከተማ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ላስቀደሱ ምእመናን ነሐሴ 19/2009 ዓ.ም የለጠፍሁትን ጽሑፍ ፕሪንት አድርገው መድረክ ላይ እያነበቡ ለምእመናን ግንዛቤ ሲፈጥሩ ውለዋል፡፡ ይህ ጽሑፍ ዋና መልእክቱ መድረክ ላይ ተጣሞ እንደተላለፈው ያለ አይደለም፡፡ እኔ የጻፍሁት ስለራሴ ብቻ የራሴን ሃሳብ ይዠ ነው፡፡ የራሴን ሃሳብ ይዠ ይሁን እንጅ እናት ቤተክርስቲያን እንድትሰደብ እና እውነተኛ ካህናት እንዲጠሉ አላደረግሁም ወደፊትም አላደርግም፡፡ “አክሊሌን ተንጠልጥሎ አየሁት” የሚለው ጽሑፌ ላይ በዋናነት ማንሣት የፈለግሁት ኅሊናየ ውስጥ የሚመላለሰውን ጥያቄየን ነው፡፡ ማሰቀደስ እፈልጋለሁ ግን የእምነት ልዩነት ያላቸው ካህናት አብረው እንደሚቀድሱ ሳስብ ኅሊናየ እረፍት ያጣል ታዲያ እንዴት ላስቀድስ የሚል ነው፡፡ ታዲያ ለዚህ እኮ ተገቢ መልስ እንደአባትነታችሁ ልትሰጡኝ ይገባ ነበር እንጅ እንዲህ መድረክ ላይ አጀንዳ አድርጋችሁ ልታነሡኝ አይገባም ነበር፡፡ ሊቃውንቱ ተሰብስበው ሊፈቱት የሚገባውን ጥያቄ ለምን አጣማችሁ መድረክ ላይ እንዳመጣችሁት ባላውቅም እኔ ግን ኅሊናየን የሚያሳርፍልኝ መልስ እሻለሁ፡፡
ልብ በሉልኝ! እኔ በደፈናው አልወቅስም፡፡ ሁሉም የእምነት ህጸጽ አለባቸው አላልኩም አልልምም ምክንያቱም ጊዜ አልመቻች ብሎኝ እንጅ ቁጭ ብየ ብማር የምመኛቸው ሊቃውንት እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ “መልካሙ በየነ የሚባል ሰው እዚህ ደብረ ማርቆስ የሚኖር ሰው ቤተክርስቲያንን ሰድቧል አባቶቻችንንም የሃይማኖት ሕጸጽ አለባቸው ብሏል” ተብሎ ወንጌል ከሚሰበክበት መድረክ ላይ ይህን መስማት በጣም ያሣዝናል፡፡ እኔ ለዚህ አጀንዳ የምበቃ ሰው አይደለሁም፡፡ እኔ ለማለት የፈለግሁት እና እናንተ መድረክ ላይ ያስተላለፋችሁት መልእክት በጭራሽ ስለማይስማማ ጥሩ ተርጓሜ ያሻዋል፡፡ እኔን ክርስቲያን እንድባል በ40 ቀኔ ሀብተ ወልድን ያገኘሁባትን ቤተክርስቲያኔን የምሳደበው በእውነት እኔ አረማዊ ነኝን ? ያልተደረገውን ተደረገ ብላችሁ ቅዱሱ መድረክ ላይ አንድን ተራ ግለሰብ አንሥታችሁ መነጋገሪያ ስታደርጉ መስማት ያሳዝናል፡፡ በ19/12/2009 ዓ.ም የጻፍሁትን ጽሑፍ ሁላችሁም አንብቡትና የሚያስቀይማችሁ ምንባብ ካገኛችሁ አስተያየት ስጡ ስህተት ከሆነ አርመዋለሁ፡፡ መድረክ ላይ ያስተላለፉትን መልእክት ይዛችሁ እኔ የጻፍሁትን ሳታነቡ ወደ ፍርድ እንዳትሄዱ አደራ፡፡
እኔ የመነጋገሪያ አጀንዳ መሆኔን ስሰማ የእኔን ገጽ የማይከታተል ካህን የለም ማለት ነው እንዴ አልኩኝ፡፡ ይህን ያህል ትልቅ አጀንዳ የምሆን ሰው አይደለሁም እኮ፡፡ የሚከታተለኝም ሰው ይህን ያህል ብዙ የሚባል ስላልሆነ ስጋታችሁ ልሆን እንደማልችል ይገባኛል፡፡ ስለዚህ ወደ መፍትሔው ብናተኩር መልካም ይመስለኛል፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ግን እኔን ወደ በረከት እንደምትመሩኝ አልጠራጠርም፡፡ ሰማእትነትም አለና፡፡ እዚሁ በመካከላችሁ ስላለሁኝ የሚመጣውን ማንኛውንም ነገር ለመቀበል ዝግጁ ነኝ ምክንያቱም ከውስጤ ፍቄ የማላወጣው ተዋሕዶ እምነቴ ያስገድደኛልና፡፡
=====================================
አንብባችሁ ከጨረሳችሁ አስተያየት
#comment ስጡ
#share አድርጉ፡፡

Friday, August 25, 2017

አክሊሌን ተንጠልጥሎ አየሁት



© መልካሙ በየነ
ነሐሴ 19/2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
መረጃዎችን ለማግኘት ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/tomarthetewahido ) ላይክ ያድርጉ፡፡
===================================================
ወይ የእኔ ነገር በጣም እገርማለሁ በጣም ሲበዛ! “መካን ይቄድሶ  ለሰብእ፤ ሰብእ ይቄድሶ ለመካን” ሲሉ አባቶቸን እሰማቸዋለሁ ግን ብዙም አላስተዋልሁትም ነበር፡፡ አሁን ግን በራሴ ሕይወት ተረዳሁት ከልክም በላይ ተገነዘብኩት፡፡ “ሰብእ ይቄድሶ ለመካን” የተባለላቸው ግሩማን መካናት አሉ፡፡ ታላቁ ጻድቅ ሐዲስ ሐዋርያ ተብለው የሚታወቁት አባታችን ተክለ ሃይማኖት የተጋደሉበት ደብረ ሊባኖስን መጥቀስ እንችላለን፡፡ አባታችን አቡነ ሐብተ ማርያምም እንዲሁ የተጋደሉበትን ገዳማቸውን መመልከት እንችላለን፡፡ ቅዱሳን አባቶቻችን  ጸብአ አጋንንቱን ድምጸ አራዊቱን ግርማ ሌሊቱን በመታገስ ጤዛ ልሰው ድንጋይ ተንተርሰው በቅዱሱ ተጋድሎ ራሳቸውን ለአምላካቸው በመስጠት ቃልኪዳን የተቀበሉባቸውን ቦታዎች መመልከት እንችላለን፡፡ ሚዳ አቡነ መልከጼዴቅ ገዳምን ስንመለከትም ተመሳሳይ ታሪክ ነው ያለው፡፡ ይህ ቦታ አባታችን አቡነ መልከጼዴቅ መልካሙን ተጋድሎ የተጋደሉበት ቦታ በመሆኑ እርሳቸው ይህን ቦታ ቀድሰውታል ልዩ አድርገውታልም፡፡ በዚህ ቦታ የተቀበረ ሰው አጽሙ አይበሰብስም አይፈራርስም ስለዚህም “ሰብእ ይቄድሶ ለመካን” ቢሉ የቀና ንግግር ነው፡፡ ይህንን አነጋገራችንን ምናልባትም ሊቃወመን የሚችል ቢኖር ዲያብሎስ እና ተከታዮቹ እነ መናፍቃን እነ ተሐድሶ ናቸው፡፡ እኛ ግን ብዙ ተአምራትን እና ድንቆችን ተመልክተንባቸዋል፡፡

“መካን ይቄድሶ ለሰብእ” ይህ አነጋገር ደግሞ ለላይኛው ተቃራኒ የመሰለ የቀና ንግግር ነው፡፡ ቦታ ሰውን ያከብራል የሚል ትርጉም ያለው ነው፡፡ የላይኛው ግን ሰው ቦታን ያከብራል ይቀድሳል የሚል ትርጉም የያዘ ነበር፡፡ የአሁኑ አነጋገርም ቢሆን የቀና እና ለሁሉ በጎላ የተረዳ ቀጥተኛ ንግግር ነው፡፡ ታዲያ በዚህ አነጋገር መሠረት እኛን ወደ ክብር ወደ በረከት ሊያሸጋግሩን የሚችሉ መካናት ወይም ቅዱሳን ቦታዎች አሉ ማለት ነው፡፡ ቤትህ ውስጥ መጸለይ እና ከቤተክርስቲያን ሂደህ መጸለይ በጸሎትህ ተመስጦ ውስጥ ተመሳሳይ ቦታ የላቸውም፡፡ ከአብያተ ክርስቲያናትም ልዩ የሆነ የቅዱሳን ቃል ኪዳን የተሰጠባቸው ፈጣሪ አብዝቶ የባረካቸው ቦታዎች አሉ፡፡ እንደ ዲማ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለው በአቡነ ተከስተ ብርሃን በአቡነ ተክለ አልፋ እና በሌሎችም እልፍ በሚሆኑ ቅዱሳን ጸሎት እና ተጋድሎ የተባረከው ቦታ እኛን ሊቀድስ የተሰጠን ቦታ ነው፡፡ እንደ ጣና ቂርቆስ የመሣሰሉት እንደ አክሱም ጽዮን እንደ ግሸን ደብረ ከርቤ እንደ ደብረ ሊባኖስ እንደ ደብረ ዳሞ እንደ ዝቋላ እንደ ዋልድባ ያሉ ቅዱሳን በሰፊው የተጋደሉባቸው ቦታዎች እኛን ይቀድሳሉ ያከብራሉ ከቃል ኪዳናቸው በረከት ያሳትፉናል፡፡ በአንድ አቡነ ዘበሰማያት የኃጢአታችን ክምር የሚናድባቸው የቃል ኪዳን ቦታዎች አሉ፡፡ ስለዚህም “መካን ይቄድሶ ለሰብእ ሰብእ ይቄድሶ ለመካን” ማለት የተገባ ንግግር መሆኑን ተረዳሁት፡፡
 
በዚህም መሠረት በያለንበት አካባቢ ሁሉ ሰው ያከበራቸውም ቦታዎች ቦታ ያከበራቸውንም ሰዎች ልንመለከት እንችላለን፡፡ በተቃራኒው ደግሞ በሰው ምክንያት የተረገሙ ቦታዎች አሉ፡፡ በቦታዎች ምክንያትም የተረገሙ ሰዎች አሉ፡፡ ቦታ የረገማቸው ሰዎች እምነታቸውን እንኳ በይፋ እስካለመረዳት ድረስ በጣዖት አምልኮ ውስጥ የተደበቁ ናቸው፡፡ በሰው ምክንያት የተረገሙ ቦታዎችም እንደሰዶም እና እንደ ገሞራ ይጠፋሉ፡፡ ሰው ለቦታ ቦታም ለሰው መልማትም ሆነ መጥፋት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ እኛ ኢትዮጵያ ውስጥ በመወለዳችን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን አምነን ተቀብለናል፡፡ በርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነንም ቢሆን ቦታው ይለያያል፡፡ እስልምና አለ ፕሮቴስታንት አለ ካቶሊክ አለ ሌላም ሌላም እምነት እንዲሁ አለ በቀደመው መናገር ነው እንጅ፡፡ አጋጣሚ ሆኖ አሜሪካ ተወልደህ ቢሆን አረብ ተወልደህ ቢሆን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን አታገኛትም ነበር ብታገኛት እንኳ የአብርሃምን ፈጣሪን የመመርመር ልዩ ጥበብ ሲሰጥህ ብቻ ነው፡፡ እኔ ግን እላለሁ አምላኬ ሆይ ተመስገን ከአገራት ሁሉ መርጠህ በኢትዮጵያ እንደፈጠር ስለፈቀድክልኝ፡፡

ዛሬ በጣም አዝናለሁ፡፡ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶነታችንን የሚፈታተን ተግባር ሳይ እበሳጫለሁ፡፡ መቼ ይሆን በሰላም በተመስጦ ጸልየን ተገቢ ምላሽ አግኝተን እንዳንተ ፈቃድ የምንመላለስ እላለሁ፡፡ አስቀድሰን የማንቆርበበት ቦታ ንስሐ የምንገባበት ደግ ካህን ማግኘት ተቸግረናል፡፡ እኔ የማወራችሁ ስለራሴ ብቻ ነው ስለደብረማርቆስ ከተማ ማለቴ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ሆነህ በቀደመው የዋሕነት ምንም ሳትሰማ በንጹሕ ኅሊና ካለህ  ብቻ ነው በረከት የሚሰጥህ፡፡ ይህንን የኅሊና ንጽሕና ግን እንዴት ማምጣት እችላለሁ የሚለው ጥያቄ መልስ የለውም ለእኔ፡፡ ባላውቀው ጥሩ ባልሰማው መልካም ነበር ግን ሰምቸዋለሁ አውቄዋለሁም ታዲያ ኅሊናየን እንዴት ላነጻው እችላለሁ፡፡ ንስሐ አባት የምይዘው ደግ ካህን ባገኝ እንኳ እርሳቸው በሚቀድሱበት ቦታ ቢያንስ አንድ ቅባት አብሯቸው ይቀድሳል፡፡ ታዲያ በማን እጅ ነው ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን የምቀበለው፡፡ ይኼ አሳብ በኅሊናዬ ውስጥ እየተመላለሰ በድፍረት ወደ ሥጋ ወደሙ መቅረብ ደግሞ ቅስፈት ነው ታዲያ ምን ይሻላል ብየ ራሴን ስጠይቅ መልስ አጣለትና እጨነቃለሁ፡፡ ከላይ ያሉት የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ ከታች ያሉት የአጥቢያ አስተዳዳሪዎች እና ቀዳሾች በዚህ እምነት ውስጥ ካሉ በማን እንጅ እንቆርባለን፡፡ ጊዜ ያላቸው የከተማው ነዋሪዎች ብዙ ኪሎሜትሮችን አቆራርጠው ንስሐ ይገባሉ ሥጋውን ደሙን ይቀበላሉ፡፡ ክርስትና የሚያስነሡት እንዲሁ በስንት ውጣ ውረድ ከሚያገኙት ቦታ ነው፡፡  ጊዜ የሌላቸው ታዲያ ምን ይዋጣቸው፡፡ ድሮ በንጹሕ ኅሊናየ ሳለሁ ቅባት ተዋሕዶ የሚለው ምሥጢር ሳይገባኝ በነበርሁበት ወቅት አብማ ማርያምን ሳልሳለም ከዋልሁ ይጨንቀኝ ነበር፡፡ ከዚህች ቦታ የማገኘው የልብ ደስታ ቀኑን ሙሉ በብሩኅ ገጽ እንድውል ያደርገኝ ነበረ፡፡ ዛሬ ግን ኅሊናየ ውስጥ የታጨቀው የሁለቱ እምነቶች ልዩነት ኅሊናየን እያረሰው በረከትን ማግኘት አላስቻለኝም፡፡ ጸሎቴን በቤቴ አድርጌ በበዓላት ቀናት እንኳ የምወዳቸውን ቤተክርስቲያናት ሳልሳለማቸው ስውል እስከመቼ በሚለው ጥያቄ ጽኑእ የኅሊና ክርክር ውስጥ እወድቃለሁ፡፡ ነጭ ነጠላውን አጣፍቶ መብሩቁን ለብሶ በጠዋቱ ተነሥቶ ቤተክርስቲያን ገብቶ ጸሎትን ጨርሶ ኪዳን አስደርሶ ቅዳሴውን አስቀድሶ ቆርቦ መመለስ ምንኛ ውብ ነገር ነበር፡፡ ግን ምን ይሆናል አይ አለመታደል! ሁል ጊዜ የበረከት አክሊሌ ተንጠልጥላ ትታየኛለች፡፡ ይችን አክሊል እንዳልቀዳጃት በቦታው የለውም ስለዚህም ይች አክሊል ለሌላው ትደረብለታለች ትጨመርለታለች፡፡ ይህ ሀገረ ስብከት መቼ ይሆን ከዚህ ሁሉ ነገር ነጻ ወጥቶ በአባቶቻችን እየተባረክን በጸሎታችሁ አስቡን እያልን የምንባረከው፡፡

እግር መንገዴን አንዳንድ መረጃዎችን ልስጣችሁ፡፡ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ይህንን ቦታ እንዲለቁት እና ደግ አባት እንዲመደብልን በሚል ህዝበ ክርስቲያኑ ይህን ዓመት ሙሉውን በመጠየቅ ላይ ነው፡፡ ለቅዱስ ሲኖዶስም የድምጽም የምስልም የጽሑፍም ማስረጃዎችን አድርሰዋል፡፡ ሲኖዶሱም ለኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ ቅድሚያ በመስጠት ጉዳዩ ከመያዙ ውጭ መፍትሔ አላመጣም ነበር፡፡ ይህንን ዝምታ የተመለከቱ የከተማው ነዋሪዎች በድጋሜ በመሄድ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡ በዚህ ወቅት የተሰጣቸው ምላሽ “ይቅርታ በመዘግየታችን በሥራዎች ስለተወጠርን ነው፡፡ አሁን ግን አጣሪ ኮሚቴ ወደ ቦታው እንልካለን፡፡ የዝውውር ጉዳይ ግን አሁን አንመለከትም ምክንያቱም በቅርቡ ሰርተናልና፡፡ በጥቅምት ሲኖዶስ ግን ጥያቄያችሁን እንመለከታለን፡፡ ዝውውሩንም እንሰራለን” በማለት ነበር መልስ የሰጡ፡፡ በዚህ ጊዜ ሁኔታው ያላማራቸው ክርስቲያኖች “ከዚህ በኋላ ወደዚያ ቦታ ብትልኳቸው ክፉ ነገር ይፈጠራል” በማለት በጥብቅ ማሳሰባቸው ይታወሳል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ምንም እንኳ ሊቀጳጳሱ ከመንበራቸው ላይ ባይገኙም ነሐሴ 16 በእመቤታችን ዕርገት ቀን ህዝበ ክርስቲያኑ “አባታችን እንዳይመጡብን” በሚል ድምጻቸውን በሰላማዊ መንገድ ማሰማታቸው ይታወቃል፡፡ በአጠቃላይ ስንመለከተው በጥቅምቱ ሲኖዶስ እንደሚነሡ ግልጽ ነገር ነው፡፡ ሆኖም ግን ይህን ሀገረ ስብከት ማን ይቀመጥበት ይሆን የሚለው እና አባታችንስ የት ይሄዱ ይሆን የሚለው ከባድ ጥያቄ መልስ አላገኘም፡፡ አሁንም ሆነ ወደፊት የእኛ ጥያቄ መሆን ያለበት ከምሥራቅ ጎጃም ተወላጅ ምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ላይ አይመደብብን የሚል ነው፡፡ ምክንያቱም ከምሥራቅ ጎጃም ለጵጵስና የተመረጡትን ስትመለከቱ አብዛኞቹ በእምነት ዙሪያ ህጸጽ አለባቸው “ቅብአት” ናቸውና፡፡ አዲስ ከተሾሙት እንኳ በግልጽ የምናውቃቸው አሉበት፡፡ ስለዚህ ለዚህ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ የምናገኝበትን ዘመን ልንናፍቅ ያስፈልጋል፡፡ ህዝበ ክርስቲያኑ ግን ከምንጊዜውም በላይ ስለሃይማኖቱ ግንባር ቀደም በመሆን ለሚደርገው ክርስቲያናዊ ተጋድሎ አድናቆቴን መቸር እሻለሁ፡፡

ይህን የደግ ዘመን መቼ እናገኘው ይሆን? ለእኛ የመጣውን አክሊል ራሳችን የምንቀበለውስ መቼ ይሆን? የእኔ የሁልጊዜ ጥያቄዬ በስማችን ለምን ይነገድብናል የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ ራሱን ለይቶ በይፋ ለሕዝቡ አሳውቆ የራሱን መሠረተ እምነት ማራመድ ህገ መንግሥታዊ መብቱ መሆኑን እያወቀ በእኛው ቤት ውስጥ ተደብቆ እንዴት ምንፍቅናውን ሊዘራ ይችላል? የመጨረሻ አማራጭ የምናደርገው ሕጋዊ በሆነ መንገድ ለፍርድ ማብቃት ብቻ ነው፡፡ እዚህ ላይ መንግሥትም ዝም የሚለው ጉዳይ አይመስለኝም፡፡ አንድ እስላም እኛ ቤተክርስቲያን ውስጥ ገብቶ የራሱን ሥርዓት ላስፈጽም ቢል አይችልም መንግሥትም ለፍርድ እንደሚያበቃው አልጠራጠርም እኛም እንዲሁ ወደ መስጊድ ገብተን የእኛን ሥርዓት ብንከውን ለፍርድ መቆማችን ግልጽ ነው፡፡ ምክንያቱም ያልተፈቀደልንን ድንበር ጥሰን ገብተናልና ነው፡፡ ታዲያ እነዚህ የቅባት መናፍቃንስ በእኛ ቤት ገብተው በማያገባቸው ሲፈተፍቱ ዝም ሊባሉ ይገባል ወይ?

=====================================
አንብባችሁ ከጨረሳችሁ አስተያየት
#comment ስጡ
#share አድርጉ፡፡

Sunday, August 13, 2017

ያለማየት ደግነት


© መልካሙ በየነ
ነሐሴ 8/2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
መረጃዎችን ለማግኘት ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/tomarthetewahido ) ላይክ ያድርጉ፡፡
===================================================

ከአንድ ቤተ ክርስቲያን በር አጠገብ ሳለሁ “በማየታችን ተጎድተናል፡፡ አዎ በጣም ችግር ውስጥ ወድቀናል” አሉ አንድ ሽማግሌ ሰው፡፡ ነገሩ ስላልገባኝ እብድ ናቸው እንዴ ብየ በውስጤ አሰብኩ፡፡ እርሳቸው ግን ልቤ በጎ ነገርን አወጣ ብሎ በከሳሾቹ እና በናቁት ፊት አዲስ ምስጋናን እናዳፈለቀው አባ ሕርያቆስ ልቡናቸው በጎ ነገርን ያፈለቀላቸው ሰው ናቸው፡፡ “ማየት እና መመልከት ለየቅል ናቸው” አሉ፡፡ ይህን ጊዜ እርሳቸው ረቂቅ ምሥጢር የተገለጠላቸው ልዩ ሰው መሰሉኝና ጉዳየን ሁሉ ወደኋላ ጣል አድርጌ ጆሮየን አዘነበልሁላቸው፡፡ እርሳቸው የሚናገሩትን መስማት ሳይማር መድረክ ላይ ወጥቶ ወዮልሽ ኮራዚን ወዮልሽ ቤተሳይዳ እያለ ከሚያሸብር ሰባኪ ይልቅ የተሻለ ስለመሰለኝ ሙሉ ቀልቤን ለእርሳቸው ሰጥቻለሁ፡፡
“ማየት የአፍአ ነው መመልከት የውስጥ ነው፡፡ ማየት በውጫዊው ዓይን ነው መመልከት ግን በውስጣዊው ዓይን ነው” አሉ፡፡ አንድ አልፎ የሚሄድ ሰው “ማየት በውጫዊ ዓይን ነው የሚሉት ልክ ነው መመልከት በውስጣዊ ዓይን ነው የሚሉት ግን ተረት ተረት መስሎ ታየኝ፡፡ የውጫዊ ዓይን አለን ሁሉም ያየዋል ይመለከተዋልም የውስጥ ዓይን ግን የት ነው ያለ ይኼ እንግዳ ነገር ነው የሆነብኝ” አለ፡፡ እርሳቸውም በትህትና ማስረዳታቸውን ቀጠሉ፡፡ “ውጫዊ ዓይን መኖሩን ያመንክ ስላየኸው ነው ውስጣዊውንም ዓይን የተጠራጠርከው ስላላየኸው ነው፡፡ ነፋስ አይታይም አይጨበጥም አይዳሰስም ረቂቅ ነው ታዲያ ስላላየሁት ነፋስ የለም ብለህ ልትደመድም ትችላለህን፡፡ ፈጣሪህን አይተኸው ታውቃለህን! ታዲያ አይተኸው ስለማታውቅ ፈጣሪ የለም ልትል ነውን፡፡ በፍጹም እንዲህ ማለት አይገባህም” አሉ፡፡ ይኼኔ አልፎ የሚሄደው ሰው “በቃኝ በቃኝ ገብቶኛል እርስዎ ነገር የሚቻሉ ሰው አይደሉም፡፡ በሉ ደህና ሁኑ” ብሎ እየተገረመ ትቷቸው ሄደ፡፡
እርሳቸው ግን ቀጠሉ፡፡ “ይኼ ከግንባራችን ላይ ያለው ዓይን እኮ ማየት እንጅ መመልከት አያውቅም፡፡ ትልቁ ዓይን የልቡና ዓይን ነው፡፡ ይህ የልቡና ዓይን ያያል ይመለከታልም፡፡ ስለዚህም ይህንን ዓይን መጠበቅ ይገባል፡፡ የውጫዊው ዓይንማ ቢጠፋስ ምን ችግር አለው፡፡ መንግሥተ ሰማያት መግባት የሚከለክለው እኮ የልቡና ዓይን እውርነት እንጅ የውጫዊው ዓይን እውርነት አይደለም፡፡ ወንጌል እንዲያውም ዓይንህ ብታሰናክልህ አውጥተህ ጣላት ሁለት ዓይን ይዘህ ሲዖል ከምትገባ ዓይን ሳይኖርህ ገነት መንግሥተ ሰማያት ብትገባ ይሻላል ይላል፡፡ ስምዖን የተባለ ጫማ ሰፊ ይህንን በተግባር ቃል በቃል ፈጽሞታል፡፡ ዓይኑን ጫማ በሚሰፋበት ወስፌ እኮ ነው አውጥቶ የጣላት፡፡ አየህ የሥጋህ ዓይን አለማየቱ ገነትን አይከለክልህም የልቡናህ ዓይን አለማየቱ ግን ሲዖል ያስገባሃል፡፡ ስለዚህ የልቡናህ ዓይን እንዲበራልህ ፈጣሪህን ዕለት ዕለት መለመን አለብህ” አሉ፡፡ እነኝህ ሰው በጣም የተማሩ ምሥጢር የጠነቀቁ ስለመሰሉኝ ጆሮየን ይበልጥ ሰጠኋቸው፡፡
“በጣም የሚገርም ታሪክ ልንገራችሁ፡፡ አንድ ወቅት አንድ ሺህ ብር ለቤተክርስቲያን ልሰጥ ተነሣሁ፡፡ ከዚያ እኔም ራሴ ሄጀ እንዳላስገባ ከንቱ ውዳሴውን ፈራሁ፡፡ አሁን የምነግራችሁ እንድትማሩበት ብየ ነው እንጅ ከንቱ ውዳሴ ሽቸ አይደለም፡፡ እና ብሩን ይዤ ስጠባበቅ አንድ ዓይነ ሥውር ምድሩን በዘንጋቸው እየደበደቡ መጡ፡፡ ይኼኔ አባቴ! ይህን ብር እዚያ ሙዳየ ምጽዋቱ ሥር ላሉት የሰበካ ጉባዔው አባላት ይስጡልኝ አልኳቸው፡፡ እርሳቸውም ቆጥረው ተቀበሉኝ፡፡ ዐሥር ብር ነው አሉኝ፡፡ አያችሁ አይደል አለማየታቸው እንዴት እንደጠቀማቸው፡፡ እርሳቸው የቆጠሩት የቅጠሉን ብዛት እንጅ እያንዳንዱ ቅጠል ስንት ብር እንደሆነ አላወቁም፡፡ ቢያዩት ኖሮ እኮ አንድም ገንዘቡን ለራሳቸው ለማድረግ በተመኙ ነበር፡፡ አንድም ይህን ያህል ብር እንዴት ትሰጣለህ ብለው በከንቱ ውዳሴ በጠለፉኝ ነበር፡፡ ነገር ግን ባለማየታቸው እሽ ብለው እንደ ዐሥር ብር አንጠልጥለው ወሰዱት” አሉ፡፡ እርሳቸው እየተናገሩት ያለው ነገር ገብቶኛል፡፡ ዓይነ ሥውሩ ዐሥር ብር ነው ብለው የቆጠሩት አንዱን ድፍን መቶ ብር እንደ አንድ ብር ቆጥረውት ነው፡፡ ምክንያቱም አያዩማ! ቢያዩ ኖሮማ አንድ ሽህ ብርን ዐሥር ብር ነው ባላሉም ነበር፡፡
“ከዚያ እኒያ ዐይነ ሥውር ሰው እንደዐሥር ብር ጠቅልለው ለሰበካ ጉባዔው አባላት አስረከቡ፡፡ ይህን ጊዜ አንድ ሽህ ብር! እርስዎ ነዎት ይህን ገንዘብ ገቢ ያደረጉ? እግዚአብሔር ይስጥልን አሏቸው፡፡ ያንጊዜ እኒያ ዐይነ ሥውር ለካ የመቶ ብር ቅጠሎችን ነው እንደ አንድ ብር ስቆጥር የነበረው፡፡ እኔ እኮ ዐሥር ብር ያስገባሁ መስሎኝ ነው፡፡ የአንድ የአንድ ብር ቅጠል መስሎኝ ዐሥር ብር ቆጥሬ መስጠቴ ነበር ለካ የመቶ የመቶ ብር ነበር እንዴ እንዲህ የቆጠርሁት፡፡ በጣም ይቅርታ የደብራችን ሰበካዎች እባካችሁ ዐሥር ብር አስቀርታችሁ ትርፉን መልሱልኝ አሉ፡፡ የሰበካው አባላትም ዘጠኝ መቶውን መልሰው ከመቶው ብር ላይ ዐሥር ብር ሊቆርጡ እየቆጠሩ ሳለ አባቴ ምነው እንዲህ ያደርጋሉ? የእርስዎ ያልሆነውን ገንዘብ እንዴት የእኔ ነው ብለው ሊወስዱ ይደፍራሉ፡፡ ያውም የተወለዱበትን ደብር ገንዘብ ብየ እውነቱን ገለጥሁላቸው” አሉ፡፡ በጣም የሚገርም ታሪክ ነው እየነገሩን ያለው፡፡ አባታችን ከዚያ በኋላ ምን ተፈጠረ ስል ጠየቅኋቸው እርሳቸውም መለሱልኝ፡፡ “ከዚያማ ዓይነ ሥውሩ በጣም ደነገጡና በፊት እኮ በፍጹም ልቤ ገቢ ላደርገው የነበረው ዐሥር ብር እንደሆነ በልቤ ስለተመለከትሁ ነው፡፡ ዓይኔ ስለማያይ በፍጹም እምነት ነበር ወደ ሰበካችን ገቢ ያደረግሁት፡፡ አንድ ሽህ ብር መሆኑን የነገሩኝ እነርሱ ናቸው፡፡ አንድ ሽህ ብር ነው ሲሉኝ ልቤ ክፉን ነገር ተመለከተ፡፡ የውስጡ ዓይኔ በራልኝ፡፡ አንድ ሺህ ብር መሆኑን ተመለከተብኝ፡፡ ታዲያ አንድ ሺህ ብር እዚህ ከምጥል ዐሥር ብር መስሎኝ ነው ብየ በአፍአዊው ዓይኔ አለማየት ምክንያት ፈጠርሁ፡፡ ዓይኔ ቢያይ ኖሮ እኮ አንዱን ሺህ ብር ዐሥር ብር መስሎኝ ነው ብል አያምኑኝም ነበር ዘጠኝ መቶ ዘጠና ብርም ሊመልሱልኝ አይችሉም ነበር አለን” አሉ፡፡ በእውነት በጣም የሚገርም ነገር ነው፡፡
ለካ በማየታችን ተጎድተናል ባለማየታችንም ተጠቅመናል አልሁ በልቤ፡፡ አለማየት ደግነት ነው አለመመልከት ድህነት ነው፡፡ ባለማየታችን ገንዘቡን ወረቀት ነው ብለን ንቀን ወርውረነዋል፡፡ ባለማየታችን በመልካቸው በውበታቸው በሚመኩ ሰዎች በሐጸ ዝሙት አልወደቅንም፡፡ ባለማየታችን የቀዩን ውበት ከጥቁሩ ውበት መለየት አልቻልንም፡፡ ባለማየታችን በምግብ አመራረጥ ላይ ጊዜ አላባከንንም፡፡ ባለማየታችን ልብስ አላማረጥንም ያገኘነውን ሁሉ እንለብሳለን እንጅ፡፡ ባለማየታችን ከኃጢአት በብዙ መልኩ ተቆጥበናል፡፡ በማየታችን ግን ብዙ ተጎድተናል፡፡ በማየታችን እንዘላለን ስንል ተሰብረናል፡፡ በማየታችን ፈተና ኮርጀን የሀገር የወገን ሸክም ሆነናል፡፡ በማየታችን በሐጸ ዝሙት ተነድፈናል፡፡ በማየታችን ከማን አንሸ በሚል ስንቱን አድርገናል፡፡ በማየታችን ተጎድተናል፡፡
በማየታችን የተጎዳነው ባለማየታችንም የተጠቀምነው ማየታችንን ለክፉ ሥራ አለማየታችንንም ለበጎ ነገር ካዋልነው ብቻ ነው፡፡ ማየታችን ሁሌ አይጎዳንም አለማየታችንም ሁሌ አይጠቅመንም፡፡ ስለዚህም ከማየት እና ካለማየት ይልቅ መመልከት ላይ እናተኩር፡፡ ውጫዊውን ያደለ ውሳጣዊውን ዓይናችንን ያበራልን ዘንድ ፈጣሪያችንን እንለምነው፡፡ የውዳሴ ማርያም መክፈያው ሰዓ(አ)ሊ ለነ ቅድስት ሲተረጎም አልሰማችሁም፡፡ ጽንእት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኝለን፡፡ አእምሮውን ለብዎውን በልቡናችን ሳይብን አሳድሪብን የሚል ነው፡፡ በልቡናችን ሳይብን የምንለው ምንድን ነው ካልን አንዱ የልቡና ዓይን ነው፡፡

=====================================
አንብባችሁ ከጨረሳችሁ አስተያየት
#comment ስጡ
#share አድርጉ፡፡