Friday, September 30, 2016

“አባታችን ስንለው ልጆቼ የሚለን እረኛ አግኝተናል”

መስከረም 18/ 2009 ዓ.ም


እረኛ እንደመሆን ከባድ  አደራ የለም፡፡ አደራው ከእግዚአብሔር ዘንድ ሲሆን ደግሞ ይበልጥ ያከብደዋል፡፡ ለጴጥሮስ የተሠጠው የእረኝነት ሥልጣን በጎችን እንዲጠብቅ ብቻ ሳይሆን በሚገባ እንዲያሰማራ ጭምር ነበር፡፡ መጠበቅ ቀላል ነው ማሰማራት ግን ከባድ ነው፡፡ የለመለመ ሣር በሌለበት፣ የእረፍት ውኃ በማይገኝበት ቦታ መጠበቅ ቀላል ነው፡፡ ነገር ግን በጎቹ ይከሳሉ፣ ይጠቁራሉ፣ ይደክማሉ፣ ይራባሉ፣ ይጠማሉ በመጨረሻም ይሞታሉ፡፡ ይህ እረኝነት ችግር አለበት፡፡ ተኩላ ሊነጥቃቸው ቢመጣ ስለበጎቹ ራሱን አሳልፎ አይሰጥም፡፡ ስለዚህ ነው ይህን እረኝነት ችግር አለበት የምንለው፡፡ እረኝነት መጠበቅ ብቻ ሳይሆን በአግባቡ ማሰማራትንም ይጠይቃል፡፡  ይህን ለማድረግ ደግሞ የበጎቹን ባሕርይ በሚገባ ማዎቅ ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም የምናሰማራበትን ቦታ ለመምረጥ የበጎቹን ፍላጎት መረዳት ግድ ይላል፡፡ ውኃ የጠማቸውን በጎች ከለመለመ ሳር ውስጥ፣ የተራቡ በጎችን ደግሞ በእረፍት ውኃ ዘንድ ብናሰማራቸው ምንም ዋጋ የለውም፡፡ ምክንያቱም ለጠማው ውኃ፤ ለራበው ደግሞ ሳር እንጅ ሌላ ፍላጎት እንደማይኖራቸው የታወቀ ነውና፡፡ ስለዚህ ነው እንግዲህ እረኝነት ከባድ አደራ ነው የምንለው፡፡ እውነተኛው እረኛ ስለበጎቹ ራሱን አሳልፎ ይሰጣል፡፡ ተኩላ ሊነጥቃቸው ቢመጣ በመጀመሪያ እረኛው ከተኩላው ጋር ይታገላል፡፡ እረኛው በትግሉ ከተሸነፈ ከዚያ በኋላ ነው እንግዲህ በጎቹን ተኩላ ሊነጥቃቸው የሚችለው፡፡ ከዚያ ውጭ ግን በጎቹ በማንም አይነጠቁም፡፡ እረኝነት ይህ ነው ከእግዚአብሔር ስንቀበለው ደግሞ እጅግ በጣም ከባድ ነው፡፡
በዚህ አስከፊ ዘመን እርስ በርሳችን ደም ስንፋሰስ ሰላም ስትርቀን ወንድሞቻችን ሲሞቱ፣ ሕጻናት ሳይቀር ሲጨፈጨፉ፣ እናቶች በልጆቻቸው አስከሬን ላይ ቁጭ በሉ እየተባሉ ሲደበደቡ የሚያጽናናን አባት ማጣታችን ልባችንን ሰብሮት ነበር፡፡ እንዲያውም ይባስ ብሎ ፓትርያርኩ ከምእመናን በተሰበሰበ ሽራፊ ሳንቲም በሚንቀሳቀሰው የቤተክርስቲያናችን ቴሌቪዥን ላይ ብቅ እያሉ ማን የጻፈላቸውን እንደሆነ ባናውቅም ከአንድ እረኛ የማይጠበቅ መግለጫ መሰል ንግግራቸውን ሲያነበንቡብን በጣም እጅግ አዝነን ነበር፡፡ ኤልያስ ስለ ናቡቴ ከንጉሡ አክአብና ንግሥት ኤልዛቤል ጋር የተጋጨው፣ ዮሐንስ መጥምቅ የወንድምህን ሚስት ልታገባት ህግ አይፈቅድልህም በማለት ከንጉሥ ሔሮድስ ጋር የተጋፈጠው፣ ዮሐንስ አፈወርቅ ስለ አንዲት ደሃ መበለት ከንግሥት አውዶክስያ ጋር የተከራከረው እና መከራን የተቀበለው፣ አቡነ ጴጥሮስ ኢትዮጵያ ለፋሽስት ባህል እምነት  እንዳትገዛ በማውገዛቸው በጥይት የተገደሉ  እረኝነታቸው እውነተኛ ስለነበር ነው፡፡ ዛሬ ግን ፓትርያርኩ የሚሰጡት መግለጫ እረኝነታቸውን የማያሳይ ምእመናንን ይበልጥ ውስጣቸውን እየጎዳቸው ያለ ነገር ነው፡፡ እረኝነት የሞቱ በጎቹን እየፈታ መቅበር ከዚያም ነፍሳቸውን ማርልን ብሎ ማስተጋባት ብቻ አይደለም እንዳይሞቱ መጠበቅ ጭምር እንጅ፡፡
ለብዙ ዘመናት አባት የሌለን ልጆች ነን ስንል ነበር፡፡ ፓትርያርኩ የሚሰጡት መግለጫ የቅዱስ ሲኖዶሱ እየመሰለን አባቶቻችንን ስንጠላቸው ኖረናል፡፡ ግን አይደለም፡፡ አባት አለን ልጆች መሆን ብቻ ነው የሚጠበቅብን፡፡ በደመራ በዓል ላይ የምእራብ ጎጃም፣ የአዊ እና የመተከል አህጉረ ስብከቶች ሊቀጳጳስ  የሆኑት አቡነ አብርሃም የብዙ ንጹሐን ወገኖቻችን ደም በፈሰሰባት በባህር ዳር ከተማ መስቀል አደባባይ ላይ ተገኝተው ከአንድ መልካም እረኛ የምንጠብቀውን ስንናፍቀው የኖርነውን የተመኘነውን የአባት ፍቅር ሰጥተውን ተመለከትን እና በጣም ደስ አለን፡፡ አባታችን እንደሚከተለው ነበር በህዝብና በመንግሥት መካከል በመሆን የሰላም ንግግር ያደረጉት፡፡
ከዚህ የተረዳነው ትልቁ ነገር የፓትርያርኩ መግለጫ የቤተክርስቲያናችን አለመሆኑን ነው፡፡ እርሳቸውንማ ግማደ መስቀሉ ያለው ግሸን መሆኑን ዘንግተው አዲግራት ላይ አየናቸው እኮ፡፡
የእናት ሆድ ዥንጉርጉር እንደሚባለው ከአንድ ማኅጸን ተወልደው በአንድ ቤት አድገው የምሥራቅ ጎጃሙ ሊቀጳጳስ አቡነ ማርቆስ  ከአሜሪካ ስልክ መትተው “መስቀል አብርሃ” ከሚለው መዝሙር ውጭ ሌላ እንዳይዘመር ሰንበት ትምህርት ቤቶችን አስጠነቀቁ አሉን፡፡ “አንመካም በጉልበታችን እግዚአብሔር ነው የእኛ ኃይላችን፤ መስቀል ኃይልነ መስቀል ጽንእነ መስቀል ቤዛነ” እየተባለ እንዳይዘመር አስጠነቀቁ ተባልን እኛም “መስቀል አብርሃ” ስንል ዋልን፡፡ አቡነ አብርሃም ደግሞ “ወታደሮች ከተሸከሙት መሣሪያ ይልቅ መስቀል ይበልጣል” በማለት በከበቧቸው ወታደርች መካከል ቆመው እውነቱን መሰከሩ፡፡ ልጆቼ ከቤታቸው በሰላም ሲገቡ ሳላይ ወደ መንበሬ አልሄድም ብለው ልጆቻቸው በሰላም መግባታቸውን አይተው በእግራቸው ወደ መንበራቸው ገቡ አሉን ደስ አለን፡፡

በዘመናችን መራራ የሆነውን እውነት ተጋፋጭ አቡነ አብርሃም ዳግማዊ አቡነ ጴጥሮስ ብላቸው እንዴት ደስ ባለኝ ነበር ዳሩ ግን እኔ ስም የማውጣት መብቱ የለኝም፡፡ ለአባታችን ረዥም ዕድሜ ዘመንን ይስጥልን፡፡ አባታችን ስንለው ልጆቼ የሚለን በማግኘታችንም ሁላችንም ኮርተናል ደስም ብሎናል፡፡ ነገር ግን በዚህ ንግግራቸው መከራ እና ስቃይ ሊደርስባቸው እንደሚችል የታመነ ነው፡፡ በርግጥ እርሳቸው ለዚህ እንደማይበገሩ እናምናለን ምክንያቱም እግዚአብሔር ህዝቡን እንዲጠብቁ አደራ ሰጥቷቸዋልና፡፡ ሆኖም ግን ጠባቂው እግዚአብሔር እንደሆነ ብናውቅም  የአባታችንን ጉዳይ ግነ በቅርበት መከታተል እንደሚገባን አሳስባለሁ፡፡

Monday, September 26, 2016

“ደርሰናል!”

© መልካሙ በየነ

መስከረም 16/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================

==============================================
እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላም እና በአንድነት አደረሳችሁ! ይህን የምለው ግን ለ2009 ዓ.ም ማለቴ ለአዲሱ ዓመት የመጀመሪያየ ጽሑፍ ስለሆነ ነው እንጅ አዲሱ ዓመት ከገባ በጣም ቆይቷል እናም እንኳን አደረሳችሁ ለማለት በጣም ዘግይቻለሁ፡፡ የሆነው ሆኖ ግን አምላክ በወደደው እና በፈቀደው መጠን ደርሰናል፡፡ ለነገሩ ችግሩ ያለ ከእኔ ጋር ነው፡፡ እንኳን አደረሳችሁ የምንባባለው በዓላትን ጠብቀን ብቻ ነው እንዴ? አረ አይደለም፡፡ ብቻ ግን ልማድ የሆነብን ይመስለኛል፡፡ እንኳን አደረሳችሁ የምንባባለው በዓላትን ጠብቀን ብቻ ነው፡፡ በእርግጥ በርካታ ትውስታዎች  ያሉ በበዓላት ወቅት ስለሆነ እንኳን አደረሳችሁ መባባል ልማድ ቢሆንብንም አይገርምም፡፡ ግን እንጅ በዓል ባልሆኑባቸው ቀናትስ ለምን እንኳን አደረሳችሁ አንባባልም፡፡ በበዓላት ቀን ለመድረስ እኮ በዓላት ያልሆኑ ቀናትን ማለፍ ግድ ነው፡፡ ስለዚህ እንደእኔ በእነዚያ ቀናትም እንኳን አደረሳችሁ ብንባባል መልካም ነው እላለሁ፡፡ ለዚያም ነው አንኳን አደረሳችሁ የምላችሁ፡፡ ዛሬ ላይ መድረስ ቀላል አይደለም ምክንያቱም ለዚህ የደረስነው በራሳችን ፈቃድ ስላልሆነ ነው፡፡
የሆነው ሆኖ ግን ደርሰናል፡፡ ለዛሬም ደርሰናል ነገም እንደርስ ይሆናል የአምላክ ፈቃድ ነው፡፡ ግን የመድረሳችን ትርጉሙ ምን እንደሆነ መረዳት ያስፈልገናል፡፡ አምላክ ለዚህ ቀን ሲያደርሰን ምክንያት አለው እኛ ለዚህ ቀን ስንደርስ ግን ምክንያት የለንም፡፡ ስለዚህ ትልቁ ነገር መድረሱ ሳይሆን የደረስንበትን ምክንያት ማወቅ ነው፡፡ ባለፈው ኃጢአትን አደረግን፣ ባለፈው ሰውን ገደልን፣ ባለፈው ሰውን አማን፣ ባለፈው የሰው ንብረት ሰረቅን፣ ባለፈው በዝሙት ወደቅን ግን ዘንድሮ ደረስን ለምን? ትልቁ ጥያቄ ይኼ ነው፡፡ መድረስማ ደረስን እኮ ግን ምን ቀሪ ሥራ ቢኖረን ነው ለዚህ ቀን የደረስነው የሚለውን መመለስ ተገቢ ነው፡፡ መድረሳችንን ለመልካም ምኞት መግለጫ ብቻ አድርገነው ከቀረን ዋጋ የለንም፡፡ ቸርነቱ ለዚህ ካደረሰን ቸርነቱን ለኃጢአት ሳይሆን ለጽድቅ፣ ለክፉ ሳይሆን ለበጎ ልንጠቀምበት ይገባል፡፡ አምና በነበርንበት ኃጢአት ሳለን እንኳን አደረሳችሁ መባባላችን እንኳን ለኃጢአት አደረሳችሁ ማለታችን እንደሆነ መረሳት የለበትም፡፡ ስለዚህ ለዚህ ቀን መድረሳችንን ለምን እንጠቀመው የሚለውን መመለስ ትልቅነት ነው፡፡ ይህ በሁሉም ዘንድ ይስተዋላል አዲስ ዘመን ሲመጣ አዲስ እቅድ ይዘጋጃል፡፡ አንዳንዱ ለጽድቁ አንዳንዱም ለኃጢአቱ ፤ አንዳንዱ ለሕይወቱ አንዳንዱም ለሞቱ ያቅዳል፡፡ ግን የዚህ ዕቅድ ተግባራዊነት መመዘኛ የለውም፡፡ ደስ ሲለን ለሚቀጥለው ዓመት ልናሸጋግረው መብቱ የራሳችን ስለሆነ ቸል ማለት እናበዛለን፡፡
በቃ አሁን ምንም ጥርጥር የለውም 2009 ዓ.ም ላይ ደርሰናል፡፡ ስለዚህ ነገን ስለመኖራችን ባናውቅም በዚህ ዓመት ምን ልናደርግ አቅደናል? ለሕይወታችን ወይስ ለሞታችን? ለጽድቃችን ወይስ ለኃጢአታችን? ለመጾም ወይስ ለመብላት? ለመዘመር ወይስ ለመዝፈን? ለመቀደስ ወይስ ለመርከስ? ለመነሣት ወይስ ለመውደቅ? ለንስሐ ወይስ ለበደል? ብቻ የራሳችን እቅድ ስለሆነ ራሳችን ብቻ ነን መፈተሸ የምንችለው፡፡ ሁላችሁም እቅዳችሁን ፈትሹት እስኪ ለሕይወት ይጠቅማል? ከጠቀመ ቀጥሉበት ካልጠቀመ ደግሞ ሰርዙት፡፡ ምክንያቱም ለሞት ማቀድ ሳያስፈልግ መሞት ስለሚቻል፡፡ ንስሐ መግባት እንጅ ኃጢአት መሥራት እኮ አይከብድም፡፡ በሕይወት መኖር እንጅ መሞት እኮ ቀላል ነው፡፡ ስለዚህ በጎ እቅድ አቅደን ራሳችንን በሕይወት ማኖር ይገባናል፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ፈቃደ እግዚአብሔርን መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡
አምላከ ቅዱሳን በሕይወት እንድንኖር ይርዳን!!!

Friday, September 9, 2016

“ዘመን ለዘመናት”

ጳጉሜን 4/ 2008 ዓ.ም

ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ 
=============================================
በመጀመሪያ ይህንን ገጽ ላይክ ያድርጉ facebook.com/beyenemlkm
==============================================

ዓለም ከተፈጠረችበት ዕለት ጀምሮ ያለውን ያለፈና የሚመጣ ዘመን በተለያዩ የቀን አቆጣጠሮች እንቆጥራለን። ከእነዚህ የዘመንና የቀን አቆጣጠር ስልቶች መካከል አንዱ ያልተበረዘውና ያልተከለሰው የእኛው የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ነው። የእኛ ዘመን አቆጣጠር ዓመትን በ ፲፫ ወር ይከፍላል። ፲፫ ኛዋ ወር ጳጉሜን ትባላለች። ይህች ወር የወርን ቀመር አታከብርም። ፩ ወር ፴ ቀናትን ይይዛል ይህች ጳጉሜን ግን ስትፈልግ ፭ ሲያሻት ደግሞ ፮ ትሆናለች።
ደስ የሚለው ነገር የቤት ኪራይ አይታሰብባትም በእርግጥ ደመወዝም አንቀበልባትም። ባትሰራ ደመወዝህ የሚቆረጥባት ብትሰራ ደግሞ ክፍያ የማታገኝባት ወር ...... ጳጉሜን። የውኃ፣ የመብራት፣ የስልክ ወጭ ግን ከምንጊዜውም በላይ የሚልቅባት ጭማሪ ወይም ትርፍ ወር ናት ……. ጳጉሜን። ይህች ወር መሸጋገሪያ ድልድይ ናት። አሮጌውን ዓመት ሽኝተን አዲሱን ዘመን የምንቀበልባት መሸጋገሪያ ናት። አሮጌው ዘመን ለሚመጣው አዲስ ዘመን ቦታውን ሲለቅ የመልቀቂያ ውሉ  መፈጸሚያና መፈራረሚያ ጳጉሜን ናት።
በባህላችን ዘመን ሲተካ እንኳን አደረሳችሁ እንባባላለን፡፡ እንቁጣጣሽ እየተባባልን መልካም ምኞት እናቀርባለን። አዲስ ዘመን ላይ ብዙ ተስፋ እንጥላለን አዲስ እቅድ እናቅዳለን፣ አዲስ መሠረት እንመሠርታለን። በመንፈሳዊውም ሆነ በሥጋዊው መንገድ እቅድ እናቅዳለን። ዘመኑን መኖር ስንጀምር የተወሰነውን እቅድ እንሰራዋለን፤ የተወሰነውን እንረሳዋለን፤ የተወሰነውንም ለሚቀጥለው ዓመት እናዞረዋለን። ዘመን ወደፊት አሻግሮ ሲያዩት የሚያልቅ አይመስልም፤ ነገር ግን ባላወቅነውና ባላሰብነው ሰዓት ፀሐይ ይጠልቅብናል ዘመን ያልቅብናል። ዘመን ማለት እንዲህ ነው፡፡ በጣም የሚገርመው ግን ላንተ የተሰጠ ዘመን ለእኔ አልተሰጠኝም ምናልባት ግን የሆነ ዘመን የጋራችን ሊሆን ይችላል። 
እንቁጣጣሽ የሚለውን ቃል እንደመልካም ምኞት መግለጫ የምንጠቀመው ዘመኑን በሚገባ ስለምናውቅና ስለምንረዳ ነው። እንቁጣጣሽ የሚለው ቃል የሁለት ቃላት ጥምርታ ነው የ "እንቊ" እና የ "ጣጣሽ" ማለት ነው። የዘመን መለወጫ ወር መስከረም በእኛ አገር ልዩ ወር ነው። ገደሉ፣ ሜዳው፣ ጋራው፤ ሸንተረሩ ሁሉ በተፈጥሮ አበባ የሚያምርበት የሚያጌጥበት የሚፈካበት ወር ነው። የአበቦች መዓዛ እንኳንስ ንቦችን ዝንቦችንም የሚስብበት ወቅት ነው። ስለዚህ ነው እንግዲህ እንቁ የሚያስብለው። ውኃው የሚጠራበት ጋራው የሚያሸበርቅበት እንቁ የሚሆንበት ነው። በሌላ ጎን ደግሞ መስከረም ማለት የተዘራው የማይደርስበት፣ የጎተራው የሚያልቅበት ወቅት ነው። በዓሉን ደግሞ ለማክበር በጉን ዶሮውን ማረድ ለምደናል። ጎተራችን አልቆ በግ እና ዶሮው  በሌለበት ሁኔታ አዲስ ዘመን ስንቀበል ደግሞ ቅር ያሰኘን ይሆናል። ነገር ግን ካልቻልን ምን ማድረግ እንችላላን? ምንም። በተለይ በዚህ ወቅት ደግሞ ከባድ ፈተና ነው። በጉን ከጓሮ ጎትተን አናቀርበው ነገር የለንም። ስለዚህ ምርጫችን መግዛት ብቻ ነው። ያንን ማድረግ ደግሞ አንችልም። ከዚህ በተጨማሪም ልጆች አዲሱን ዘመን ምክንያት አድርገው ልብስ ጫማ እንዲገዛላቸው ይጠይቃሉ፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ ትምህርት ቤቶች የሚከፈቱበት ወር በመሆኑ ደብተር እስክብሪቶ እርሳስ ይፈልጋሉ። አቤት የዘመን መለወጭ ጣጣ! እውነትም ጣጣሽ ብንላት ሲያሳት እንጅ አይበዛባትም። ለዚህ ነው እንግዲህ " እንቁጣጣሽ " የምንባባለው። 
ዘንድሮ ደግሞ ማለቴ አዲሱ ዓመት 2009 ዓ.ም ለሀገራችን የደስታ የዘመን መለወጫ አልሆነልንም የሀዘን ሆነብን እንጅ፡፡ ወገኖቻችን በግፍ ደማቸው ፈስሷል፣ ወንድሞቻችን፣ እህቶቻችን ያለርኅራኄ በጭቃኔ ተገድለዋል፡፡ በዚህም አንገታችንን ደፍተናል፡፡ እንደእኔ ከሆናችሁ የዘንድሮው የዘመን መለወጫ በዓል ምንም አልመስልህ ብሎኛል፡፡ በዓል በዓልም አልሸተተኝም ውስጤ በዓሉን ለመቀበል ደስተኛ አይደለም፡፡ ብቻ ግን ዘመናትን የሚያቀዳጅ ፈጣሪ ይህንን ዘመን አሳልፎ መጭውን ዘመን እንድቀበል በሕይወት ስላኖረኝ አመሰግነዋለሁ፡፡
አዲሱን ዓመት የንስሐ፣ የፍቅር፣ የአንድነት፣ የመልካም ነገር፤ የሰላም፣ የመረጋጋት፣ የመደማመጥ፣ የመተሳሰብ፣ ያድርግልን። ከዘመነ ዮሐንስ ወደ ዘመነ ማቴዎስ በሰላም ያሸጋግረን።
አሜን፡፡

Thursday, September 8, 2016

“ሰውነታችንን ካላስቀደምን ሰላምን አናመጣም”

ጳጉሜን 3/ 2008 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
========================
በመጀመሪያ ይህንን ገጽ ላይክ ያድርጉ facebook.com/beyenemlkm
========================
ሁላችን አሁን ከደረስንበት ደረጃ ከመብቃታችን በፊት ሰው ነበርን፡፡ ሰው ሳንሆን ቀድሞ ሃይማኖት የለንም፣ ሰው ሳንሆን ቀድሞ ብሔር የለንም፣ ሰው ሳንሆን ቀድሞ ዘር የለንም፣ ሰው ሳንሆን ቀድሞ ጎሳ የለንም፣ ሰው ሳንሆን ቀድሞ ጎጥ የለንም፡፡ ከዚህ ሁሉ ቀድሞ የነበረው ሰውነት ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ በስፋት ከሚያስተምሩ የቤተክርስቲያናችን ፈርጦች መካከል አንዱ የሆኑት ብርቅየ ሊቅ መጋቤ ሐዲስ እሸቱ አለማየሁ ናቸው፡፡ እርሳቸው ሰው እንሁን እንደ ሰው እናስብ እያሉ ሁልጊዜ ይሰብካሉ ያስተምራሉ ይመክራሉ ነገር ግን ሰሚ ጆሮ ያጡ ይመስላል፡፡ ሰው እንሁን ሰውነታችንን እናስቀድም ማለት ፖለቲካ አልያም ሃይማኖታዊ ስብከት አይደለም፡፡
ሰውነታችንን ስናስቀድም በሃይማኖት አንለያይም ምክንያቱም ሃይማኖት ሰው ከመሆናችን በኋላ የሚመጣ ጉዳይ ነውና፡፡ የኦርቶዶክ ተዋሕዶ፣ የፕሮቴስታንት፣ የእስልምና፣ የካቶሊክ ወዘተ እምነት ተከታዮች መሆን የጀመርነው ሰው ከመሆናችን በኋላ ነው፡፡ ስለዚህ በሃይማኖት ልዩነትን ፈጥረን አንዱ ለአንዱ ጠላት የሚሆነው ሰውነታችንን ስለማናስቀድም ብቻ ነው፡፡ አብያተ ክርስቲያናት ሲቃጠሉ እንመለከታለን፣ መስጊዶች ሲፈራርሱ እናስተውላለን ይህ ክስተት የሚፈጠረው ሰውነታቸውን ባላስቀደሙ ሰዎች ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ሃይማኖታቸውን ሰው ከመሆናቸው ያስቀደሙ ናቸው፡፡ ስለዚህ ሃይማኖትን እንደልዩነት በመጠቀም ከሰውነት አንድነታችን መውጣት የለብንም፡፡ ምንም እንኳ በሃይማኖት ብንለያይም ሰው በመሆናችን ግን እንተባበራለን፡፡ ትብብራችን ደግሞ ቀድሞ ባገኘነው የሰውነት ጸጋ እንጅ በኋላ ባገኘነው የሃይማኖት ጸጋ መሆን አይገባውም፡፡
ሌላው ሰውነታችንን ስናስቀድም በሃገር፣ በዘር፣ በብሔር፣ በጎሳ፣በጎጥ ወዘተ አንለያይም፡፡ አገሬ፣ ዘሬ፣ ብሔሬ፣ ጎሳየ፣ ጎጤ ወዘተ ከማለታችን በፊት ሰው መሆናችን ይቀድማል፡፡ ሰው ስንሆን ያን ጊዜ አምላክ ባወቀ በሆነ አገር፣ በሆነ ብሔር፣ በሆነ ጎጥ፣ ከሆነ ዘር እንድንወለድ አደረገን፡፡ እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባው ጉዳይ ፈልገን የተወለድንበት አገር፣ ብሔር፣ ዘር፣ ጎሳ እንደሌለ ነው፡፡ የአምላክ ፈቃድ ሆኖ ከሆነ አገር፣ ከሆነ ብሔር፣ ከሆነ ጎጥ፣ ከሆነ ዘር ፈጠረን እንጅ እኛ የመረጥነው እንዳልሆነ እናስተውላለን፡፡ ስለዚህ በብሔር፣ በቋንቋ፣ በዘር ከመከፋፈላችን እና አንድነታችንን ከመበታተናችን በፊት ሰውነታችንን እናስቀድም፡፡ ሰውነታችንን ካስቀደምን በዘር፣ በጎሳ፣ በቋንቋ በብሔር አንከፋፈልም፡፡ ደግሞም እኮ ሁሉን ያደረገልንን አምላክ ልናመሰግነው ይገባል እንጅ በእነዚህ ነገሮች መለያየትን እንዴት እንቀበላለን፡፡ ዛሬ በብሔር በቋንቋ እና በዘር እንድንከፋፈል ያደረገን ሰውነታችንን ስላላስቀደምን ብቻ ነው፡፡ የትም ተወለድ የት፣ የትም ተፈጠር የት ሰው ነህ፡፡ ሰው በመሆንህ ደግሞ አንድነትን ታጠነክርበታለህ እንጅ ልዩነትን አትፈጥርበትም፡፡ ምክንያቱም ሰው ከሰው በምንም ሊለያይ አይችልምና፡፡
ሰውነታችንን ስናስቀድም ማንም ማንንም አይገድልም፤ ማንም በማንም አይሞትም አይገደልምም፡፡ አንዱ ባለስልጣን ሌላው ሎሌ፣ አንዱ ገዳይ ሌላው ተገዳይ፣ አንዱ ሰጭ ሌላው ተቀባይ፣ አንዱ ጠጋቢ ሌላው ተራቢ፣ አንዱ ረጋጭ ሌላው ተረጋጭ በመሆን መለያየት የመጣው ሰው ከመሆናችን በኋላ ነው፡፡ እንደ ሰው ስታሰብ ሌሎች ባንተ ላይ ሊያደርግብህ የማትፈቅደውን ነገር በሌሎች ላይ አታደርግም፡፡ ስለዚህ አንተን እንዲገድሉህ እንደማትፈቅድ ሁሉ ሌሎችን ለመግደል አትፈቅድም፡፡ አንተን ሲረግጡህ ሲጨቁኑህ እንደማትወድ ሁሉ ሌላውን አትረግጥም አትጨቁንም፡፡ ስለዚህ ነው ሰውነታችንን ማስቀደም አለብን የምንለው፡፡ አንተ ባማረ በተዋበ ባሸበረቀ በዕንቁ ባጌጠ ቪላ ቤት ላይ እየተንፈላሰስክ ሌላው መንገድ ላይ ወድቆ በብርድ ሲሰቃይ መመልከት እንደ ሰውነቱ ለማያስብ እንጅ እንደሰውነቱ ለሚያስብ ሰው እጅግ በጣም ከባድ ነው፡፡
እንደሰውነታችን ስናስብ ሰውን አንገድልም ምክንያቱም እኛን እንዲገድሉን ስለማንፈልግ፡፡ አሁን ግን እያስቀደምነው ያለ ጉዳይ ከሰውነታችን በኋላ የመጡ ጉዳዮችን ሆኗል፡፡ በቅርቡ ያየነው እና ያስተዋልነው የአገራችን ጉዳይ ሰውነታቸውን ካላስቀደሙ ወገኖች በተሰነዘረ ጥቃት የብዙዎች ደም ፈስሷል፡፡ ሁልጊዜ ሳስበው ከኅሊናየ አልወጣልህ ያለኝ ግን ማረሚያ ቤቶች ሲቃጠሉ ለማምለጥ ሞክረዋል ተብለው በጸጥታ ኃይሎች የተገደሉት ንጹሐን ወገኖቻችን ናቸው፡፡ በእውነት እንደሰውነት ለሚያስብ ሰው ማረሚያ ቤቱ ሲቃጠል ታሳሪዎች ምን ማድረግ ነበረባቸው? በእሳት ላለመቃጠል ከማምለጥ ውጭ ምን ተስፋ አላቸው? ከእሳቱ ከማምለጥ ውጭስ ምን ዓይነት እርምጃ መውሰድ ነበረባቸው? ሳስበው በጣም ይዘገንነኛል፡፡ በእሳት ተቃጥለው እንዲሞቱ መወሰን ሰው ከመሆን ውጭ ያለው የሚያስበው ከንቱ ሀሳብ ነው፡፡ እንደ ሰውነታችን ካሰብን በእርግጠኝነት እንዳይቃጠሉ እንተባበራቸው ነበር እንጅ አመለጡ ብለን ተኩሰን አንገድላቸውም ነበር፡፡
ሰውነት አንድ ያደርጋል፡፡ በመወለድ አንድ ሆነናል በመሞትም አንድ እንሆናለን፡፡ በመብላት አንድ ሆነናል በመጠጣትም አንድ እንሆናለን፡፡ ዘርን በመተካት አንድ ሆነናል በማሰብም አንድ እንሆናለን፡፡ ስለዚህ ከሁሉ አስቀድመን ሰው መሆናችንን እናረጋግጥ ከዚያ በኋላ ሃይማኖት፣ ብሔር፣ ቋንቋ፣ ጎሳ ከዚህ በኋላ የሚመጣ ጉዳይ ነው፡፡ ሰው ስንሆን ለሁሉ እንራራለን፣ ሰው ስንሆን ለሁሉ እናስባለን፣ ሰው ስንሆን ሁሉን እንመግባለን፣ ሰው ስንሆን ሁሉን እንታደጋለን፣ ሰው ስንሆን ሁሉን በፍቅር እንመለከታለን፣ ሰው ስንሆን አድልዎ አንፈጽምም፣ ሰው ስንሆን ለሁሉ እኩል እንጨነቃለን፡፡ ሰው ካልሆንን ግን የዚህ ተቃራኒ እንሆናለን፡፡ እኛ ጮማ እየቆረጥን ጠጅ እያንቆረቆርን ሌላው በረሃብ ሲያልቅ እንስቃለን፡፡ እኛ ባማረ ቤት ሞቆን እየኖርን የሚወጥሩት ሸራ እንኳን አጥተው መንገድ ላይ የሚያድሩትን ወገኖቻችንን አናስባቸውም፡፡ ስለዚህ እንደሰውነታችን እናስብ እንደሰውነታችን ካሰብን ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነት ማንም ሊቀማን ማንም ሊነፍገን የማይችላቸው ሃብቶቻችን ይሆናሉ፡፡

Wednesday, September 7, 2016

“የወላጅ ቁንጥጫ ረሃብን አያጠፋም”

ጳጉሜን 2/ 2008 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

=======================
በመጀመሪያ ይህንን ገጽ ላይክ ያድርጉ facebook.com/beyenemlkm 
=======================

አንድ ነገር አሰብኩ፤ ያሰብኩትንም እንዲህ ጻፍኩት፡፡ ልጆች ሲርባቸው፣ ሲበርዳቸው፣ ሲታመሙ ወዘተ ያለቅሳሉ፡፡ የሚያለቅሱበትን ምክንያት በአግባቡ መለየት የወላጆች ድርሻ ነው፡፡ የሕጻንኛን ቋንቋ በሚገባ ያልተረዳ ወላጅ በማይመክርና በማያስተምር እንዲሁም በማይገስጽ መልኩ ልጆቹን ይቀጣል፡፡ ልጆቹም ለጥቂት ጊዜ ከማልቀሳቸው ዝም ይላሉ፡፡ ከማልቀሳቸው ዝም ስላሉለት ብቻ ግን ለልጆቹና ለራሱ ሰላም የፈጠረ የመሰለው ወላጅ ጅል ነው፡፡ ምክንያቱም ልጆቹ ከማልቀሳቸው ዝም ያሉ ችግራቸው ስለተፈታላቸው ወይም ጥያቄያቸው ስለተመለሰላቸው ሳይሆን ስለቆነጠጣቸው እና ስላስፈራራቸው እንደሆነ አልተረዳም ማለት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ወላጅ የወላጅነት ድርሻው ለስሙ አባት ወይም እናት ለመባል ብቻ ነው፡፡
ራበኝ አብላኝ ጠማኝ አጠጣኝ እያለ ረሃብ ጎድቶት የሚያለቅስብንን ህጻን እንደወላጅነታችን ማብላትና ማጠጣት ካልቻልን ያልቻልንበትን ምክንያት ማስረዳት ይጠበቅብናል እንጅ ቆንጥጠን ዝም ማስባል አይገባንም፡፡ ልጆቹ እኮ ያለቀሱብን ስለራባቸው እና ስለጠማቸው ነው፤ ታዲያ የእኛ ቁንጥጫ እና ኩርኩም ረሃብን የሚያስታግስ ይመስል ለምን ቁንጥጫና ኩርኩሙ አስፈለገ? በተገቢው መልኩ ልጆቻችን ያለቀሱበትን መረዳትና ተገቢውን መልስ መስጠት የወላጅነት ድርሻችን ነው፡፡ እንደወላጅነታችን ተገቢውን መልስ መስጠት ከእኛ የሚጠበቅ ነው፡፡ ለምን አለቀሱብን አትበሉ ሲርባቸው ያለቅሳሉ፣ ሲጠማቸው ያለቅሳሉ፣ ሲበርዳቸው ያለቅሳሉ፣ ግፍ ሲበዛባቸው ያለቅሳሉ፡፡ የወላጅ ቁንጥጫ ደግሞ ረሃብን አያስታግስምና ልጆች ለጊዜው ከማልቀሳቸው ቢቆጠቡም ቆይተው ግን ለቅሷቸውን በአዲስ መልኩ ይጀምሩታል፡፡ ስለዚህ ሁነኛው መፍትሔ የወላጅነትን ምግባር ተላብሶ የልጆችን እንባ ማበስ  ነው፡፡ ምክንያቱም የልጆች ጥያቄ ረሃብና ጥማት በዛብን የሚል እንጅ ማልቀስ አይደለም፡፡ ወላጆችም እንዳያለቅሱባቸው ከመደብደብ ባለፈ ለምን እንዳለቀሱባቸው መረዳት አይፈልጉም፡፡ ይህ ደግሞ ዘላቂ መፍትሔ የሚሆንበት አንዳች ነገር የለውም፡፡
በርካቶቻችን መፍትሔ የምንሰጠው ለችግሩ ሳይሆን ችግሩ ለወለደው ሌላ ችግር ነው፡፡ ጎርፍ ቤታችን ውስጥ ሲገባ የገባውን ውኃ ወደ ውጭ እየረጨን መጨረስ መፍትሔ እናደርጋለን፡፡ ከዚያም በጎርፉ የተበላሹ ዕቃዎቻችንን ፀሐይ ላይ በማስጣት ማድረቅ እንጀምራለን፡፡  ነገር ግን ይህ ሁሉ መፍትሔ ሊሆን አይችልም፡፡ ምክንያቱም ነገ ጎርፉ ቤታችን ላለመግባቱ ምንም ዋስትና የለንምና፡፡ ስለዚህ ዘላቂ የሚሆነው መፍትሔ የጎርፉን አቅጣጫ ማስቀየር አልያም ቤትን ማስተካከል ብቻ ነው፡፡
በሀገራችን እየሆነ ያለውም እንደዚሁ ያለ ነው፡፡ ሰልፍ እንዳይወጡ በማስፈራራት ወይም የወጡትን በመደብደብ የህግ የበላይነትን አስከብረናል ሰላምንም አስፍነናል ማለት ያስቸግራል፡፡ ህዝቡ ሰልፍ እንዳይወጣ ማድረግ ወይም የተሰለፈውን መበተን በምንም መልኩ ዘላቂ መፍትሔ ሊሆን አይችልም፡፡ ችግሩ እኮ ሰልፍ መውጣታቸው አይደለም ሰልፍ እንዲወጡ ያደረጋቸው ጉዳይ እንጅ፡፡ ሰልፍ እንዲወጡ ያደረጋቸው ምክንያት ሰልፉ ቢበተንም አብሮ አይበተንም፡፡ የተሰለፈውን ሰው ብናስፈራራው እና ብንገድለውም ሰልፉን ሊበትነው የሰውን ቁጥር ሊቀንሰው ይችላል እንጅ ችግሩን ሊፈታው አይችልም፡፡ ስለዚህ መፍትሔ ሊሆን የሚችለውን ነገር እንደተማረ፣ ለሀገር እንደሚያስብ፣ ለወገን እንደሚቆረቆር ሰው ሆነን በጋራ ልንፈታው ያስፈልጋል፡፡ ህጻናት ተርበው ሲያለቅሱ በወላጅ ቁንጥጫ ለጊዜው ዝም ቢሉም ረሃቡ ሲጸናባቸው ቁንጥጫውን ከምንም ሳይቆጥሩ አብልጠው እንደሚያለቅሱ ሁሉ ችግሩ ካልተፈታለት ይህ ህዝብም ሞትን ሳይሰቀቅ ወደፊት ማለቱ አይቀርም፡፡ ስለዚህ የወገኖቻችን ደም ሳይፈስ ዘላቂ መፍትሔ የሚፈለግበትን መንገድ መፈለግ ይገባናል፡፡