Friday, April 27, 2018

የቁጥሮች ምክር ቤት


፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
በአንድ ወቅት የቁጥር መስመር የተባለው የቁጥሮች አለቃ ቁጥሮችን ለስብሰባ ጠራቸው። የስብሰባው ዓላማ የዜሮን የማንነት ጥያቄ ተቀብሎ በዚያ ላይ በሰፊው ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፍ ነበር። ቁጥሮች በሙሉ ተሰብስበዋል። ጎደሎ ቁጥሮችም (ኢ ተጋማሽ)፣ ሙሉ ቁጥሮችም (ተጋማሽ) አዎንታ ቁጥሮችም አሉታ ቁጥሮችም ክፍልፋዮችም ዐሥርዮሾችም ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ታዳሚዎች ኾነዋል።
ሰብሳቢው ወደተዘጋጀለት ወንበር እያመራ ነው። ቁጥሮች ኹሉ ተነሥተው አጨበጨቡለት ላንቃቸው እስኪላቀቅ ድረስ አፏጩለት። እርሱም እጁን ከፍ አድርጎ እንደሚባርክ ሊቀ ጳጳሳ እጁን አንሥቶ ፉጨታቸውን እና ጭብጨባቸውን መቀበሉን አረጋገጠ። ኹለት እጁን ሲያነሣ ለተመለከተው ግን ደህና ሁኑ ብሎ አውሮፕላን ውስጥ የሚገባ ባለሥልጣን ይመስል ነበር።
ሰብሳቢው ወንበሩ ላይ ሲቀመጥ ኹሉም ጭብጨባ እና ፉጨታቸውን አቁመው አዳራሹን በጸጥታ አስወረሩት። ሰብሳቢው የድምጽ ማጉያውን ተረከበና ስብሰባውን እንዲኽ ሲል ጀመረ።
«የተከበሩ የአዎንታ ቁጥሮች ተወካይ፣
የተከበሩ የአሉታ ቁጥሮች ተወካይ፣
የተከበሩ የክፍልፋይ ቁጥሮች ተወካይ፣
የተከበሩ የዐሥርዮሽ ቁጥሮች ተወካይ፣
የተከበራችሁ ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች፣
ክቡራን እና ክቡራት ከኹሉ አስቀድሜ ምንም ስለኾነችው ቁጥር የማንነት ጉዳይ ላይ ለመወያየት ጥሪያችንን አክብራችሁ ስለተገኛችሁ በእኔና በቁጥሮች ማኅበር ስም ከፍ ያለ ምስጋናዬን ሳቀርብ በታላቅ ደስታ ነው»
አዳራሹ በጭብጨባ በፉጨት ተናጠ።  በተለይ ዜሮ ብሎ በስሟ በመጥራት ፈንታ «ምንም ስለኾነችው ቁጥር» ብሎ ነገር ባስረዘመበት የሰብሳቢው ንግግር ተደስተዋል። ነገሩ የረዘመ ቢኾንም እንዲኽ ባለ ሰፊ የውይይት መድረክ ላይ «ምንም» መባሏ በሰብሳቢው በኩል እንኳ ሳይቀር የቁጥር ማንነቷ እንዳልተረጋገጠ ወደፊትም እንደማይረጋገጥ ማሳያ ኾኗልና ነው።
ሰብሳቢው ቀጠለ «ዛሬ ለዚኽ ውይይት መጠራት ዋና ምክንያት የኾነው የዜሮ የቁጥር ማንነት ነው። በቁጥሮች የመተዳደሪያ ደንብ መሠረት ጉዳዩ ታይቶ እልባት እንዲሰጣት ጠይቃለች። በዚኽም መሠረት ዜሮ ቁጥር የመኾን እና ያለመኾን ከማኅበራችን ጋር የመቀላቀል እና ያለመቀላቀል ውሳኔ በማሳረፍ ከዚኽ በኋላ የማያዳግም ምላሽ መስጠት ይጠበቅብናል» አለ።
ታዳሚው ቅድም የተደሰተውን ደስታ ከመቅጽበት ተነጠቀ። ኹሉም ፊታቸውን ኮሶ አስመሰሉት። ዜሮ ምን ከዕቁብ ብትገባ ነው በዚኽ ኹሉ የቁጥሮች ማኅበር ላይ ስሟ የሚጠራ ተባባሉ ጎን ለጎን እየተያዩ።
ሰብሳቢው ቀጠለ «ጉዳዩ የኹላችን ነው። ጥቅምና ጉዳቱን አመዛዝናችሁ የዜሮን የማንነት ጥያቄ እልባት እንድትሰጡበት መድረኩን ለናንተ ዘርግቻለሁ። ሰፊ ውይይት አድርገን መልካም ውሳኔ እንደምናሳርፍ እተማመናለሁ። በሉ ከዚኽ በኋላ መድረኩ የእናንተ ነው» በማለት ለተሳታፊዎች መድረኩን ለቀቀ።
የአዎንታ ቁጥሮች ተወካይ ተነሣና ጎርነን ባለ የተንደላቀቀ ንግግር «እኛ የአዎንታ ቁጥር አባላት በዚኽ ጉዳይ ላይ ሰፊ ውይይትና ምክክር አድርገናል። ዜሮ ማለት ምንም ባዶ ማለት ናት። ምንም የኾነች ባዶ ነገር ደግሞ ከእኛ ጋር አንድነት ሊኖራት አይችልም። እኛ አንድ ኹለት ተብለን እንቆጠራለን ዜሮ ግን ምንም ተብላ አትቆጠርም። እስኪ በኪሱ ብር ያልያዘ ሰው ይጠየቅ። ስንት ብር ይዘሃል ብለን ብንጠይቀው ምንድን ነው የሚመልሰው? ምንም አልያዝሁም ነው የሚለን። ሃምሳ ብር በኪሱ የያዘን ሰው ብንጠይቅ ግን ሃምሳ ብር ብሎ በስማችን ይጠራናል። ስለዚኽ ዜሮን የቁጥሮች አባል ማድረግ ምንም ረብ የለውም» አለ። ክፍሉ በፉጨትና በጭብጨባ ተናወጠ። የኹላችን ሃሳብ ነው ማለታቸው ነው።
ሰብሳቢው «ተጨማሪ ካለ» አለ።
የአሉታ ቁጥሮች ተወካይ ተነሣ «እኛ የአሉታ ቁጥሮች እንደ አዎንታ ወንድሞቻችን ኹሉ የዜሮ ማንነት ላይ ተመሳሳይ አቋም አለን። የተበደረ ሰው በእኛ ይገለጣል፣ ኪሣራ በእኛ ይገለጣል፣ ዝቅታ በእኛ ይገለጣል፣ ወደ ታች መውረድ በእኛ ይገለጣል እስኪ በዜሮ የሚገለጥ ነገር አሳዩን? ምንም የሚታይ የሚጨበጥ የሚዳሰስ ነገር የለም እኮ። ታዲያ በምን መስፈርት ነው ዜሮ የእኛ ማኅበር አባል ልትሆን የምትችለው? ስለዚህ በዜሮ ላይ ያለን አቋም ይኼው ነው» ብሎ ተቀመጠ።
የስብሰባ አዳራሹ አሁንም በፉጨት እና በጭብጨባ ተናወጠ።
ሰብሳቢው «ሌላ ተጨማሪ ሐሳብ ያለው» አለ።
የሙሉ ቁጥሮች (ተጋማሽ) ተወካይ ተነሣ «ዜሮ ምንም ናት ባዶ ናት። ይህንንም የምለው ዝም ብየ አይደለም በማስረጃ ነው። ዜሮ ከእኛ ጋር ተደምራ ፈቀቅ አታደርገንም ከእኛ ላይ ተቀንሳም ምናችንንም አትቀንሰውም። እንዲያውም ከእኛ ጋር ከተባዛችማ እኛን ጨምራ ነው ማንነት አልባ የምታደርገን። በጣም የሚገርማችሁ ግን በዜሮ ማካፈል ነውር መሆኑ ነው። ይህ እኮ ከጥንት ከመሠረቱ ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የነበረ እውነታ ነው። ታዲያ ከእኛ ጋር ተባዝታ እኛን ጨምራ ማንነት አልባ እንድታደርገን የሚፈልግ ቁጥር አለ? ታዲያ ማንነት አልባ የምታደርገንን ዜሮ እንዴት ማንነቷን እናረጋግጥላት ይባላል?» አለ በቁጭት።
በፊት ከነበረው ጭብጨባ እና ፉጨት ይልቅ ተሳታፊው አሁን ይበልጥ አዳራሹን አናወጠው።
ዜሮ በማንነቷ ኩራቷ እየጨመረ መጣ። በማንነቷ ይበልጥ ኮራች። አዎንታም አሉታም ዜሮን ያናደዱ መስሏቸው ስሟን ላለመጥራት ሲጠየፉ ስትመለከት ዜሮ በማንነቷ ይበልጥ ኮራች። ራሷን የምታውቅ ኩሩ። እርሷ ምንም ተብላ ሌሎችን ምንም ከመባል የምትታደግ። እርሷ ተሰድባ ሌሎችን ከስድብ የምታወጣ። እርሷ ጥቅም አልባ ተብላ ሌሎችን ተጠቃሚ የምታደርግ። እርሷ እርባና ቢስ ተብላ ሌሎችን እንዲኽ ከመባል የምትሰውር ልዩ ቁጥር ዜሮ። ኹላቸው ስለነርሱ ግዝፈት እንጅ ውስጣቸው ስለተሠራበት ጥሬ ዕቃ ምንም አልተጨነቁም ምንም አላሰቡም ማሰብም አይሹም። ዜሮ ግን ከራሷ አልፋ ተርፋ የሌሎችንም ማንነት የገነባች ኩሩ ቁጥር ናት።
ሰብሳቢው ነገሩን በአጭሩ ለመቅጨት ስላሰበ ሌላ ተጨማሪ ዕድል መስጠት አላስፈለገውም ነበር። «ስብሰባችንን በዚሁ ብንጨርስና የዜሮን የቁጥር ማንነት በአጀንዳ ዘግተን በአዋጅ ብናጸድቀው ሳይሻል አይቀርም» አላቸው።
ሁሉም የሰብሳቢውን ሐሳብ እንደደገፉ ለማረጋገጥ በጭብጨባ እና በፉጨት አዳራሹን አናወጡት።
«ከዚያ በፊት ማንነት ጠያቂዋ ዜሮ ያላትን ሐሳብ ብታቀርብ» አለ ሰብሳቢው።
«በፍጹም በፍጹም በፍጹም» አለ ተሰብሳቢው በአንድ ድምፅ።
ስቅሎ ስቅሎ ስቅሎ ያሉትን የአይሁድ ካህናት አለቃ አስታወሱኝ። ጌታችን ያለበደሉ በፍርድ አደባባይ በቆመ ጊዜ የአይሁድ ካህናት ጌታችን ተሰቅሎ መሞት  እንደሚገባው ላንቃቸው እስኪላቀቅ ድረስ ስቀለው ስቀለው ስቀለው ብለው ነበር። ዛሬ ዜሮ ላይ እየተፈጸመ ያለው ግፍም እንደዚያ ይመስል ነበር። ዜሮ ራሷን ማንነቷን አሳውቃ የሚቀበል ቢቀበላት የማይቀበል ባይቀበላት ምን ነበረበት? ዝም ብሎ መጮኽ፣ ዝም ብሎ መነፍረቅ፣ ሌሎች ሲያላዝኑ አብሮ ማላዘን ብቻ።
ዜሮን ከኋላቸው አስከትለው እነርሱ ከፊት በመቆማቸው ብቻ ቁጥር ሆነው የቆሙ የመሰላቸው ማንነታቸውን የማያውቁ ኅሊና ቢሶች በዝተዋል። 1፣10፣100፣1000፣10000 ወዘተ እነዚኽ ቁጥሮች ማንነታቸው ቢፈተሽ ከዜሮ ማንነታቸው ይልቅ በ1 ማንነታቸው ነው የሚኮሩ ግን ለምን? ከ 1 እና ከ 0 ለእነዚህ ቁጥሮች ትልቁ ማንነታቸው ማን ሆኖ ነው? ዜሮ በማንነታቸው ውስጥ ሰፊውን ድርሻ መያዟን በመዘንጋት «ምንም» «ባዶ» የሚለውን ስድብ ለማረፍ ብቻ በ 1 ማንነታቸው ይንጠራራሉ። እስኪ 0 ን ከእነዚህ ቁጥሮች ማንነት ውስጥ እናውጣት ሁሉም 1 ሆነው ይቀራሉ። 1 ወደ 10 ከፍ ልበል ካለች ከዜሮ ጋር መኖር የዜሮንም ማንነት መቀበል የግድ ይላታል። 1 ወደ 100 ከዚህም ወደ በለጠ ቁጥር ከፍ ለማለት የዜሮን ማንነት የግድ መቀበል ይገባል። ነገር ግን ይህን የራሳቸውን ማንነት ካለማወቅ የተነሣ የሌሎችን ማንነት ሲጨፈልቁ በአዳራሽ መካከል ሲያጨበጭቡ ሲያፏጩ ተመለከትናቸው። 99 ሲያጨበጭብ 100 ም ያጨበጭባል። 999 ሲያፏጭ 1000ም አብሮ ያፏጫል። ጎረቤትህን ሳይሆን ራስህን መስለህ መገኘት ካልቻልህ ከባድ ነው። አንተ እኮ 1000 ተብለህ ከ999 ገዝፈህ የታየኸው 0ን ከኋላህ ስላስከተልህ በዜሮ ማንነት ላይ ራስህን ስለገነባህ ብቻ ነው። ግን አላስተዋልኸውምና ዜሮ ምንም ናት ባዶ ናት ጥቅም የላትም ማንነትም የላትም ትላለህ።
ሰብሳቢው የአጀንዳውን ቃል አነበበ። «ዜሮ የተባለች የቁጥር ማንነት ፈላጊ ባመለከትችው ማመልከቻ መሠረት ዛሬ የተሰበሰበው የቁጥሮች ምክር ቤት በዜሮ የቁጥር ማንነት ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ የሚከተለውን የማያዳግም የመጨረሻ ውሳኔ ወስኗል» አለ። የምክር ቤቱ አባላት የተወሰነውን ውሳኔ በጭብጨባ እና በፉጨት ለመደገፍ ተዘጋጅተዋል።
«ዜሮ ምንም ናት፣ ባዶ ናት፣ ጥቅም አልባ ናት በሚል ምክር ቤቱ የዜሮን የቁጥር ማንነት አልተቀበለውም። በዚህም መሠረት ዜሮ ቁጥር እንዳልሆነች ማንነቷም ተቀባይነት እንደሌለው በአዋጅ እንደነግጋለን። የዛሬውን የስብሰባ ውሎ በዚህ እንፈጽማለን» አለ።
የምክር ቤቱ አባላት በሙሉ፣ እጃቸው እስኪያብጥ አጨበጨቡ ላንቃቸው እስኪላቀቅ ድረስ አፏጩ። ዜሮ ግን በብዙኃኑ ድምጽ በመረገጧ ሳታዝን በማንነቷ ኮርታ ከአዳራሹ ወጣች።
ያለዜሮ ማንነት የሚደምቅ ቁጥር ማነው? ዜሮ ጥቅም አልባ ናት የሚለው አረ ማነው? ዜሮ ባዶ ናት ምንም ናት የሚለውስ የቱ ነው? ቁጥሮች ዜሮን ያናደዱ መስሏቸው የማንነት ጥያቄዋን ውድቅ ቢያደርጉትም ለራቸው ህልውና ግን የዜሮ ማንነት ወሳኝ ቦታ አለው። ይህ ስብሰባ ላይ ብቻ አጀንዳ ለማርቀቅ አዋጅ ለማጽደቅ እንጅ መሬት ላይ ያለው እውነታ ይኼ አይደለም።
ከስብሰባው ወጥቶ ኹሉም የራሱን ኑሮ መኖር ጀመረ። ግን ከዜሮ ማንነት ጋር በተያያዘ እክል የገጠማቸው ነበሩ። እነዚኽ ቁጥሮችም በዜሮ ላይ የተገነቡ ዜሮን ከኋላቸው አስከትለው እነርሱ ከፊት የሚታዩ ቁጥሮች ነበሩ። 10፣20፣30፣40፣50፣60፣70፣80፣90፣100፣200፣300፣400፣500፣600፣700፣800፣900፣1000፣2000፣3000፣4000፣…፣100000000000000000000000000000000000000000 እና ሌሎችም ለንባብ እንኳ የሚያዳግቱ በዜሮ ማንነት ላይ የተገነቡ ቁጥሮች ያለዜሮ ምንም እንዳልሆኑ ገባቸው። 10 አንተ ማነህ ሲሉት ዐሥር ነኝ ይላል ዐሥርማ ማንነት ከሌላት ዜሮ ጋራ የተወዳጀ አይደለምን? እያሉ ይሳለቁበት ጀመር። በአዳራሽ አጨብጭበው ጥቅም አልባ ናት ማንነት የላትም ያሏት ዜሮ የራሳቸው ማንነት ሆና ተገኘች። 100ን ማነህ ሲሉ መቶ ነኝ ይላል። አንተማ ከኹለት 0ዎች ጋር የተቆራኘህ ማንነት አልባ ከሆነችው ጋር የተዛመድህ አይደለህምን? እያሉ ያሸማቅቁት ጀመር። በራሱ ፊርማ በራሱ ድምፅ በራሱ ፉጨት በራሱ ጭብጨባ የዜሮን ማንነት የነፈገው 100 ዛሬ የራሱም ማንነት 0 ሆና ስትገኝ ምን ይበል? ማስተዋል የጎደለው ግራ ቀኙን አይቶ የማይወስን የቁጥሮች ምክር ቤት ሁሉም የሚስቅበት ሁሉም የሚቀልድበት ሁሉም የሚሳለቅበት ሆነ።
0ን የያዙ ሁሉ ከትንሹ 10 ጀምረው መጨረሻው እስከማይታወቀው ቁጥር ድረስ የቁጥር መስመርን የዜሮ ማንነት ይረጋገጥልን ብለው ጠየቁ። በሰላማዊ ሰልፍ የዜሮ ማንነት ይረጋገጥ ብለው ጮኹ። ሰብሳቢው ግን አፋጣኝ ምላሽ አልሰጣቸውም ነበር። አሁንም መጡ በደብዳቤም ጠየቁ ምክር ቤቱ እንዲሰበሰብና የዜሮ ማንነት እንዲረጋገጥ ጠየቁ። ጩኸቱ የበዛበት ሰብሳቢ «የማያዳግም የመጨረሻ ውሳኔ ወስኗል» በማለት በአዋጅ ደንግጎ ከመውጣቱ በጥቂት ጊዜ ውስጥ እንዲህ ያለ ቀውስ ሲመጣበት ጊዜ የምክር ቤቱን አባላት ሰበሰባቸውና በዜሮ ማንነት ላይ ድጋሜ ለመወያየት ተቀመጠ። ሁሉም ቁጥሮች በቦታቸው ተቀምጠዋል ሰብሳቢውም ተቀምጧል። ዛሬ ስብሰባው የሚደረገው 0 ስለጠየቀች አይደለም ሌሎች ስለጠየቁ ነው። ዜሮ ማንነቷ ስለተጨፈለቀ ቁጥርም አይደለሽም ተብላ ስለነበር በስብሰባው አልተገኘችም ነበር። «የዛሬው ስብሰባ የ0ን ማንነት ማጽደቅ ነው» አለ ሰብሳቢው። ውይይት ድርድር ክርክር የሌለው በቃ ማጽደቅ ብቻ። ሁሉም ወደ 0 መቀመጫ ተመለከቱ 0 ግን በቦታው የለችም።
«0 እኮ በቦታው የለችም ያለጥያቄዋ ለምን» አለ አንዱ አባል።
«0ማ ድሮ ጠይቃን ነበር እኛም ምላሽ ሰጥተናት ነበር። አሁን ግን ከእኛ መካከል በዜሮ ማንነት ማጣት የተነሣ የተጎዱ ቁጥሮች በመኖራቸው እነርሱ በጠየቁት መሠረት ነው የምናጸድቀው» አለ።  
«ማን ነው?» አለ አንዱ ተወካይ።
«ለምሳሌ10፣1000፣1000000፣1000000000000…» ወዘተ አለ ሰብሳቢው።
«እንዴ በ0 የተነሣ እነ 1000000000000ም ማንነታቸው ላይ ጥያቄ ፈጠረ? ይህ ከሆነማ 0ን እንቀበልና የቁጥር ማንነቷን እናረጋግጥላት» አሉ።
በሕጉ በአግባቡ የማንነት ጥያቄ የጠየቀችውን 0 አንሰማም ብሎ ማንነቷን የጨፈለቀው ምክር ቤት ዛሬ ግን በሌሎች ጥያቄ ማንነቷ ይጽደቅ ተባለ።
«የ0ን ማንነት የሚቃወም ካለ» ብሎ ሰብሳቢው ዕድሉን ለተሳታፊው ሰጠ። አንድ የሚቃወም ጠፋ።
ይገርማል ይሰቀል ሲሉ ይሰቀል ይሙት ሲሉ ይሙት በቃ ያለማመዛዘን የራስን ውሳኔ የማይወሰንበት የምክር ቤት ስብሰባ። ሁሉን ነገር በሙሉ ድምፅ ማጽደቅ ሁሉን ነገር ይፈጸም ማለት። ለድጋፍ ብቻ እጅ ማስቆጠር። አቤት ስብሰባ አቤት ውሳኔ።
ሁሉም የ0ን ማንነት በሌለችበት አጸደቁት። 0ን ማን እንደሆች የተረዱ በራሷ ጥያቄ ሳይሆን በሌሎች ጥያቄ ነው። በቃ ከእኛ ጋር ተባዝታ እኛን እንደርሷ ታድርገን፣ ከእኛ ጋር ትደመር ከእኛ ላይ ትቀነስ በቃ ችግር የለውም ተባለላት። 0ንም ያከበሩ ስለመሰላቸው ማንነቷን የተቀበሉበትን አጀንዳ በወርቅ ቀለም ጻፉት።
በሕይወታችን ራሳችንን ችለን ግራ ቀኙን አመዛዝነን ውሳኔ መስጠት ካልቻልን ራሳችንን እንጎዳለን። ማንነትህ የራስህ ነውና ሰው ባይቀበልልህም አትዘን ይልቁንም ተደሰት እንጅ። 0 ማንነቷን ሲጨፈልቁባት ምንም አልተበሳጨችም በደስታ ከስብሰባው ወጣች እንጅ ምክንያቱም ማንነቷን ራሷ ታውቃለችና አሁን ግን በግድ ተለምና ማንነቷን በወርቅ መዝገብ ላይ አስጻፈች። በዚህ ትዕግስቷም ማንም ማንነቱ ቀድሞ የተረጋገጠለት ቁጥር ባልተጻፈበት ወርቅ ቀለም ለመጻፍ በቃች።
መልእክቱ ምንድን ነው? ለሚል ሁሉ መልእክቱ አሁን አንብበህ ስትጨርስ የተረዳኸው ነገር ነው።
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
መልካሙ በየነ
ሚያዝያ ፲፱/ ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍