Wednesday, December 25, 2019

ምርጫ 2012 እና እኛ!


  ==============
ከዚህ በፊት የምርጫ ካርድ እና እኛ ሆድና ጀርባዎች እንደነበርን ማስታወሱ  አይከፋም፡፡ በተለይ እኔ የምርጫ ካርድ ማውጣትን እንደ ኃጢአት ነበር የምቆጥረው፡፡ በርግጥም ኃጢአት ሆኖ ነበር፡፡ ምክንያቱም ካርዳችን ዋጋዋ ምንም ስላልነበር፡፡ 1997 ዓ.ም ዕድሜዬ ለመምረጥ አልደርስልኝ ቢል መታወቂያየ ላይ ዕድሜየ እንዲሞላ ፍቄ ሰርዤ ነበር ካርድ ያወጣሁ፡፡ ያ ይመስለኛል በተከታታይ ለነበሩ ምርጫዎች ካርድ የሚባል ነገር እንዳላይ ብዬ የመምረጥ መብቴን ከራሴ ላይ እንድገፍ ያደረገኝ፡፡ ዘንድሮ 2012 ዓ.ም በትክክል ምርጫው መካሄድ አለመካሄዱን ባላውቅም መምረጥ ብቻ አይደለም መመረጥም ይኖርብናል ብየ አስባለሁ፡፡
መምረጥ መመረጥ ለሀገር ቅን ከማሰብ የሚመጣ ፍቱን ሃሳብ ነው፡፡ የአንተ ካርድ ቤተ ክርስቲያንን እንድትቃጠል ለማድረግም ላለማድረግም ዋጋ አላት፡፡ የአንተ ካርድ ሀገርህ በሰላም እንድትኖርም እንዳትኖርም የማድረግ ልዩ ኃይል አላት፡፡ የአንተ ካርድ የሕይወትም የሞትም ካርድ ናት፡፡ ያችን ካርድ በእጅህ መያዝ ግድ ይላል፡፡ የክልልም ሆነ የፌዴራል ምክር ቤቶች ውስጥ ካህናት ጠምጥመው ቁጭ ብለው ሳይ ደሜ ይፈላ ነበር፡፡ ለካ ደሜ ይፈላ የነበረው እነርሱ ቢያንስ የአንድን አሕዛብ ወንበር መውረሳቸውን ስላላወቅሁ ነበር፡፡ ለሀገር ሰላም ማምጣት ከተፈለገ ወንበሮች ሁሉ  በጠመጠሙ ካህናት መሞላት አለበት፡፡  እነላሊበላ ንግሥናውን ከቤተ ክህነቱ ጋር ደርበው ሊያስተዳድሩ መነሣት አለባቸው፡፡ ከዚህ በኋላ የሞት የሽረት ትግል ውስጥ መግባት ግዴታችን የሚሆን ይመስለኛል፡፡ አሁን በርካታ ዕድሎች እጃችን ላይ አሉ እነዚያን እድሎች በሙሉ እንጠቀምባቸው፡፡ ግብጽ፣ ሶሪያ፣ ሕንድ ወዘተ በተጓዙበት እንቅልፍ የበዛበት ጉዞ መሄድ አይገባንም፡፡ እኛ መምራቱንም መመራቱንም ከልክ በላይ እናውቅበታለን፡፡ ስለዚህ ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ድረስ ሕዝቡን ሊወክሉ የሚችሉ ሰዎችን በጥንቃቄ እንድንመርጥ ማሳሰብ ግዴታ ነው፡፡ የምርጫ ካርዳችንንም በጊዜው ማውጣት ግዴታችን ይሆናል፡፡ 
 
አባቶቻችን ሞተው ያቆዩንን ታሪካችንን እኛም በደማችን ጽፈን ለሚመጣው ትውልድ ሳይበረዝ ሳይከለስ ማውረስ ይኖርብናል፡፡ ድምጹ ተጽእኖ የሚፈጥር የምክር ቤት አባል ሊኖረን ይገባል፡፡ የገቡትን አንግፋቸው ሊገቡ ያሰቡትን እንደግፋቸው፡፡ እኔ ፖለቲከኛ አይደለሁም፡፡ እንዴት ማሳመን እንደሚቻልም አላውቅም፡፡ ነገር ግን ሀገርን ለማፍረስ ፖለቲካን ሽፋን አድርጎ ከሚመጣ ሰው ለሀገሬ መልካም ነገር አስባለሁ ብየ እገምታለሁ፡፡ ታዲያ ምንም ባልሠራ እንኳ የዚያን ሰው ወንበር መያዜ ትልቅ ነገር እንደሆነ አስባለሁ፡፡ ስለዚህ የተሻለውን የምንመርጥበትና ተሽለን በመገኘትም የምንመረጥበትን ነገር ከወዲሁ ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ ሌሎች ቀድመውናል ነገር ግን ዕድሉ አለን ተስፋ የሚያስቆርጥ ደረጃ ላይ አይደለንም፡፡ ሠርተን እናሳይ!
ሃይማኖትና ፖለቲካ ለየግል ናቸው በሚል የጅልነት ብሂል ሀገራችንን ለጠላት አሳልፈን ልንሰጣት አይገባም፡፡ ዳዊትም ሰሎሞንም ንጉሦች ነበሩ፡፡ በሀገራችን ቅዱስ ላሊበላም ንጉ ነበር፡፡ ነገር ግን ከቤተ ክህነት ጋር ያጋጫቸው ነገር አልነበረም፡፡ በመልካም ጥበብ መሩ አስተዳደሩ እንጅ፡፡ ንግሥናን ከክህነት ጋር አስተባብሮ መምራትን አስተምረውን አልፈዋልና በግብር በሃይማኖት ልንመስላቸው ይገባል፡፡

Thursday, December 5, 2019

‹‹ዝምታ ይበጃልም አይበጅምም!››

ዝም ብሎ እንደመመልከት ያለ ቁም ነገር የሚገኝበት ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ ሀገርን ያህል ነገር የዕቃ ዕቃ ጨዋታ በሚጫዎቱ መሪዎች እጅ ስትወድቅ ስታይ ዝም ከማለት ውጭ በእጅህ የሚገኝ ሌላ መፍትሔ የለም፡፡ በአህዮች የእርስ በርስ እርግጫ ብዙዎችን የሚያጠግበው ምስኪኑ ሳር እየተነቃቀለ ሲወድቅ ስትመለከት እጅህን በአፍህ ላይ ጭነህ “እግዚኦ” ከማለት ውጭ ሌላ ምንም መፍትሔ አይመጣልህም፡፡ ዶክትሬቱን ይዞ የሀገራችን አህዮች ከሚያስቡት ለመድረስ ዕድሜ ልኩ የማይበቃው ሰው እንደ ዐዋቂ በየሚዲያው ሲቦርቅ ስትመለከት ዝም ብለህ ከማየት ውጭ ሌላ አማራጭ የለህም፡፡ ልታደርገው የምትችለው በእጅህ ያለው ቀላሉ ነገር “ሪሞት” ህን ተጭነህ አንደበቱን መዝጋት ብቻ ነው፡፡

 
ታሪኩን ሳያውቅ የታሪክ አስተማሪ ሊሆን የሚዳዳውን የታሪክ ጠላት ስትመለከት ዝምታን ትመርጣለህ፡፡ የተናገርከውን በውል ሳይረዳ ለማጨብጨብ ብቻ የተፈጠረ በሚመስል እጁ ጣሪያውን በጭብጨባ የሚያናጋውን የአጨብጫቢዎች ማኅበር ስትመለከት ዝም ትላለህ፡፡  ነገን አርቆ በማይመለከት ሰው በተፈጠረ ሴራ እርስ በእርሳችን ስንተራረድ ስታይ ዝምታን ትመርጣለህ፡፡ ወሬ ማመላለስን ትልቁ ሥራው አድርጎ አምራች የሆነ ጉልበቱን ለወሬ ሞትኩ እያለ ሲደክምበት ስትመለከት ዝም ትላለህ፡፡ ሰው መሆኑን ዘንግቶ “ከየት ነው” በሚል ቦታ አምላኪነት ጦር የተነደፈ ወጣት ስትመለከት ዝም ትላለህ፡፡ በባዶ እግሩ ዘምቶ የታጠቀ ጠላትን በጦር እና በጎራዴ አፈር አስግጦ “ሀገርህ ይች ናት” ብሎ በነጻነት እንዲኖርባት ያስረከበውን ባለውለታውን ዘንግቶ አፉን ለስድብ የሚከፍት የተማረ ማይም አፉን ለስድብ ሲከፍት ስታይ ዝም ትላለህ፡፡ እኔን ብቻ ስሙኝ እያለ ወሬውን  ሊግትህ የሚጥር መስማት የተሳነው ትውልድ ሲነሣ ዝም ከማለት ውጭ አማራጭ የለህም፡፡


ዝምታ መልስ ነው፡፡ በርግጥም ለሚገባው ሰው መልስ ነው፡፡ ነገር ግን ዝም በማለት ሀገሪቱን የወሬ ማምረቻ ፋብሪካ ሲያደርጓት መመልከት ደግሞ የራስ ምታት ነው፡፡ የሚበጀው ነገር ከሚጮሁት ጋር አብሮ መጮህ ሳይሆን ረጋ ብሎ እያደመጡ ምላሽ መስጠት ነው፡፡ የሆነውን እና እየሆነ ያለውን ነገር እየተመለከትህ ነገ ምን ሊሆን እንደሚችል ለመገመት የግድ ነቢይ መሆን አይጠበቅብህም፡፡ የሀገራችን ፖለቲካ ህዝብን በቀላሉ እንዴት ማሳመን እና ድጋፉን ማግኘት እችላለሁ የሚል ሴራ የተሴረበት ነው፡፡ ለአንተ አስቦ ሳይሆን ለራሱ አስቦ ዕድሜውን ለማራዘም የሚጠቀምበት ቁልፍ መሳሪያ ነው ፖለቲካ፡፡ ኢህአዴግ ይባል የነበረው የግንባሮች ስብስብ ሀገራዊ ፓርቲ ሆኖ ብልጽግና ተባለ አሉን፡፡ ስሙን መቀየሩ ጥሩ ነው ምክንያቱም ሰው ሁሉ በድሮ ጠባዩ የሚጠላ ግንባር ስለነበር፡፡ ውሕደቱም መልካም ነው አንድነትን ያመጣ ይመስላል (የታይታ እና የማስመሰል)፡፡ ይህ ሁሉ በሰው ልብ ለመጎዝጎዝ የተሠራ ሴራ ይመስለኛል፡፡ “ለማ እና ዐቢይ ተጣሉ” ብለው ደግሞ ጮቤ የሚረግጡ ሰዎችን አያለሁ፡፡ የእነርሱ ጠብ የጉልቻ ጠብ ነው (የወንድማማች ማለት ነው)፡፡ ለማ መላ ኦሮምያን ይዟል፡፡ በዚያ ሁሉም ይወደዋል ሁሉም ያከብረዋል፡፡ ዓቢይን ደግሞ ሀገሪቱ ላይ እየተሠራ ባለው ነገር ህዝቡ ፊቱን መልሶበታል፡፡ ህዝቡ የመለሰበትን ፊት ለመመለስ የሁለቱ የተጣሉ መስለው ድራማ መተወን አንዱ አማራጫቸው ይመስለኛል፡፡ ዓቢይ ኢትዮጵያ እያለ ሲያቀነቅን ኢትዮጵያ ትቅደም የሚለውን የዜግነት ፖለቲካ አራማጅ ሁሉ ወደ ራሱ የመሰብሰብ አቅሙን ያጠናክራል፡፡ ለማ ኦሮምያ እያለ ሲያቀነቅን ኦሮሞ ትቅደም የሚለውን የጃዋር ሥሪት በሙሉ ወደ ራሱ ይስባል፡፡ ለማ የጃዋርን መመሪያ እየተቀበለ ወጣቱን ያደራጃል፡፡ በዚህ መካከል ኢትዮጵያ ትቅደም እያሉ በዓላማ ቆመው የቀሩ በተለይ እንደ አማራ ክልል ያሉ መሪዎች  ህዝባቸውን ከማስበላት በቀር አማራጭ አይኖራቸውም፡፡ በዚህ ጉዳይ የፖለቲካ ተንታኝ ለመሆን ያምረኛል አልተማርኩም እንጂ፡፡ በዚህ መስመር እኔ የሚታየኝ ለሌሎች ክልሎች የጨለመ መንገድ ነው (በተለይ ለአማራ)፡፡ ይህ በዚህ ይብቃኝ አክቲቪስት አይደለሁ ወይ የፖለቲካ ተንታኝ አያያዜ ላያምር ይችላል፡፡ ከጻፍኩ ደግሞ ያጎበደደ ጽሑፍ መጻፍ ደስ አይለኝም፡፡ እና ወደ ርእሴ ልመለስ፡፡


የእኔ መጥፋት ምንም የሚፈጥረው ተጽዕኖ እንደሌለ ባውቅም እኔ ዝምታ ይበጃል ብየ ከፌስቡክ መንደር ራቅ ብየ ነበር፡፡ ግን ሳየው መፍትሔ አይደለም፡፡ ዶክተርና ፕሮፌሰር ተብለው በዚያ ልክ ብቻ ከሆነ የማሰብ አድማሳቸው እኔ እልቃቸዋለሁ ብየ ራሴን ከፍ እንዳደርግ እድል ፈጥረውልኛል፡፡ ከእነርሱ ፕሮፌሰርነትና ዶክተርነት ይልቅ የእኔ ከ12 ዓመታት በፊት በሒሳብ ትምህርት የያዝኳት ዲፕሎማ እና ከ9 ዓመታት በፊት የያዝኳት የሒሳብ ትምህርት ዲግሪ እጅግ ትልቃቸዋለች ብዬ ለራሴ ሞራል ሰጠሁ፡፡ በጠፋሁባቸው ወቅቶች ብዙ ልጽፋቸው እያሰብኩ የተውኳቸው ነገሮች ነበሩ እነዚያን ዝም ብዬ በማሳለፌ ደስ ይለኛል፡፡ ምክንያቱም እነዚያን ነገሮች ብጽፋቸውም ባልጽፋቸውም አመለካከቱን የምለውጠው ሰው ስለማይኖረኝ ነው፡፡  ምክንያቱም ሰውን ለመለወጥ ከመነሣት አስቀድሞ ራስን መለወጥ ይበጃልና፡፡ በዚህ ጊዜ ንስሐ ገብቶ የጥሪ ቀንን እንደመጠበቅ ያለ ዕድለኛነት የለም፡፡ ግን እሱን እንኳ ለማድረግ ቀጠሮ በሚባል ውል አልባ ገመድ ተጠፍሬ አልፈጸምኩትም፡፡
ዝምታ የሚበጅ እና የማይበጅ አለው፡፡ የሚበጀው ዝምታ ሌሎችን ለማዳመጥ ሌሎችን ለመስማት የሚረዳ ነው፡፡ የማይበጀው ዝምታ ግን አላዋቂዎች እና ፍሬ አልባ ንግግር የሚናገሩ ሰዎችን ዝም ብሎ መስማት ነው፡፡ ስለዚህ ዝም በማለትም ዝም ባለማለትም ለሀገራችን ሰላም የራሳችንን ድርሻ እንወጣ እላለሁ፡፡
መልካሙ በየነ
25/03/2012 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ