Sunday, August 31, 2014

የኃጢአት ተራራ

በአንድ አካባቢ የሚገኝ ሥሙ ኃጢአት በመባል የሚታወቅ ትልቅ ተራራ ነበር፡፡ ከከፍታው የተነሣ  የተስተካከለውን የቅድስና ሜዳ ጋርዶት የሚኖር እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ ታዲያ ይህን ተራራ ንዶና አፍርሶ እንደ ቅድስና ሜዳ የተስተካከለ ለማድረግ ተራራው የሚገኝበት አገር መንግሥት በራሱ ኃይል ማስተካከል የሚችል ባይሆንም ተስፋ ባለመቁረጥ አማካሪዎቹን ጠርቶ ሲያወያያቸው ተራራውን ሊያፈርሱ የሚችሉ "የሰለጠኑ ኢንጅነሮች" ካህናት ንስሓ የተባለ የማፍረሻ "ደመሚት" እንዳላቸው ይጠቁሙታል፡፡ የአማካሪዎቹን ጥቆማ እንደሰማ ሳይውል ሳያድር ወደ አንዱ"ኢንጅነር" በመጠጋት የተራራውን ባሕርያት ከገለጸ በኋላ "ደመሚቱን" ተረክቦ እንደወሰደ ተራራውን በማፍረስ ለማየት ጋርዶት ይኖር የነበረውን የተስተካከለውን የቅድስና ሜዳ እንደፈለገ ለማየት በቃ፡፡ ወገኖቼ! ኃጢአት ስለሠራን ለምን እንዲህ አደረጋችሁ የሚል ፈጣሪ የለንም ንስሓ ግቡ በንስሓ ልቀበላችሁ የሚል እንጅ፡፡  እግዚአብሔር የሟቹን ሞት አይፈቅድምና በሕይወት እንድንኖር በንስሓ ይቀበለናል፡፡ ኃጢአታችን በዝቶ ተራራ የሚያህል እስከመሆን ቢደርስ እንኳ "የሽሮ ኩራቱ ውኃ እስኪገባው ነው" እንዲሉ የኃጢአትም ተራራነት ንስሓ እስኪነካው ድረስ እንጅ ፈርሶ ፈራርሶ ተንዶ የት እንደደረሰ የት እንደገባ አድራሻው ብን ብሎ ይጠፋል፡፡  አብርሃምን፣ ዳዊትን፣ሕዝቅያስን፣ጴጥሮስን፣ጳውሎስን እና ሌሎችንም በንስሓ የተቀበለ አምላክ እኛንም በንስሓ ሊቀበለን የታመነ ነው፡፡ ንስሓ ዘማውን ድንግል ታደርጋለች፡፡ ይህ ማለት የሥጋ ድንግልና ይመለሳል ማለት ሳይሆን የነፍስ ድንግልና ይገኛል ለማለት ነው፡፡ በዚህ የነፍስ ድንግልናም የአምላክ ቸርነት ተጨምሮበት መንግሥተ ሰማያትን መውረስ ይቻላል፡፡ የመጨረሻ ዓላማችን ይህ ነውና፡፡ በአጠቃላይ ንስሓ ኃጥኡን ጻድቅ የምታደርግ፣ የመንግሥተ ሰማያት መውረሻ ፣ ከእግዚአብሔር  አንድነትን መፍጠሪያ  መሣሪያ ናት፡፡ ስለዚህ ሁላችን በክርስቶስ ክርስቲያን የተሰኘን ከሰባት ዓመታችን ጀምረን የንስሓ አባት በመያዝ ለኃጢአታችን ንስሓ እየገባን የኃጢአት ሥርየትን በማግኘት በቤቱ መጽናት ያስፈልጋል፡፡  ምክንያቱም ንስሓ በኃጢአት ለታመመ  መድኃኒት ፣በኃጢአት ለቆሸሸ ሳሙና ነውና! ንስሓ ገብተን ሥጋውን በልተን ደሙን ጠጥተን የመንግሥቱ ወራሾች የሥሙ ቀዳሾች ያደርገን ዘንድ አምላከ አብርሃም ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡ አሜን፡፡
ማጣቀሻ ፡- 1ኛ ነገ 20÷27-29፣ 2ኛ ነገ20÷1-7፣ ሕዝ3÷17-27፣ ሆሴ4÷6-10፣ ኢዩ2÷12-14፣ ማቴ8÷4፣ ማቴ16÷19-20፣ ማቴ26÷75፣ ዕብ10÷21

የጉርጦች ጩኸት

ከዘመናት በአንዱ ዘመን ሰፊ ባሕር ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ሁለት ጉርጦች ነበሩ፡፡ ከዕለታት በአንዱ ዕለት ከዚህ ባሕር በግምት 1 ኪ.ሜ ርቀት አካባቢ የምትገኝ መንደር በእሳት ክፉኛ ትቃጠላለች፡፡ የከተማዋን መቃጠል የተመለከቱ እነኚህ ጉርጦች በሁለት ተቃራኒ ሀሳቦች መካከል ወደቁ፡፡የመጀመሪያዋ የከተማዋ መቃጠል ለእርሷ ምንም ማለት ስላልሆነ በተለይም ደግሞ በውኃ ውስጥ መኖሯ እሳት ሊያቃጥላት እንደማይችል በማሰብ አብዝታ ቁርርርርር… እያለች በትዕይንቱ መገረምና መሳቅ ጀመረች፡፡ የዚህች ተቃራኒ የሆነችው ሁለተኛዋ ጉርጥ ግን የከተማዋ መቃጠል እጅግ አሳዘናት በተለይም በከተማው የሚኖሩ እንስሳት፣ ሰዎችም ሳይቀሩ የሚቃጠሉ መሆናቸው የልቧን ኃዘን አጸናባት፡፡ ይህን ኀዘኗን የተመለከተች ጓደኛዋ ምን ያሳዝንሻል? እኛ የምንኖረው በውኃ ውስጥ ነው፡፡ ደግሞም እኮ ከተማዋ የተቃጠለችው በሥራዋ ነው እኛ ምን በድለናል እያለች ማንቋረሯን ቀጠለች፡፡ በኃዘን ላይ ያለችው ጉርጥ ግን አሁንም ቢሆን በጓደኛዋ ምክር መጽናናት አልቻለችም፡፡ በደስታ ያለች ጓደኛዋንም እንድታዝን እንጅ ቁርርርርር… እያለች እንድትጮህ ባለመፍቀዷ ተጣሉ፡፡ ከሴት ብልሐት አይታጣምና ከከተማዋ መቃጠል ጋር ከተቃጠሉት የተረፉ ሴቶች መቃጠሉን ለማቆም ከአጠገባቸው ከለው ባሕር ውኃ እየቀዱ እሳቱን ማጥፋት ጀመሩ፡፡ በዚህ ጊዜ በደስታ ቁርርርርር… እያለች ትስቅ የነበረችዋ ጉርጥ ድምጿን ማጥፋት ጀመረች ሆኖም ግን ብዙ ውኃ ከመቀዳቱ የተነሣ ያች ጉርጥ ከውኃ ጋር ተቀድታ ሄዳ የእሳት ማጥፊያ ሆና በእሳቱ መካከል ገብታ እርር ኩምትር ብላ ሞተች፡፡ ያች ስታዝን የነበረችው ጉርጥ ግን ከባሕሩ ወጥታ የከተማዋን ሁኔታ እየተመለከተች ታዝን ስለነበር በእሳት ከመቃጠል ነጻ ወጣች፡፡ ብዙ ጊዜ የሌሎች ችግር የእኛ ሊሆን እንደሚችል የማንገምት በመሆኑ ሌሎች በተጎዱበት ጉዳት ለመውደቅ እንገደዳለን፡፡ ሌሎች በኃዘን ሲጎሳቆሉ እኛ በደስታ የምንዘል የሌሎችን ሸክም የማንጋራ ጨካኞች የምንሆን ከሆነ ማሰብ የሚገባን ነገ የእኛ ተራ መሆኑን ነው፡፡ ለሌሎች መራራት ሌሎች ለእኛ እንዲራሩ ማድረጊያ መሣሪያ ነው፡፡ የድረሱልኝ ጥሪ እየሰማን እንዳልሰማን የምናልፍ ከሆነ የእኛን የድረሱልኝ ጥሪ ማንም ሊሰማን አይችልም፡፡ ከላይ ያየናቸው ሁለት ጉርጦች ተመሳሳይ ፍጡራን ሁለቱም በውኃ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ናቸው፡፡ የጥፋት ጊዜያቸው ግን በተግባራቸው ተገልጦ ስትስቅ የነበረችው አልቅሳ ያለቀሰችውን እንድትስቅ ታሪካቸውን አምላክ ቀየረው፡፡ የሰው ልጅ እነዚህን ጉርጦች ልብ ብሎ መማር ይገባዋል፡፡ መራራት ምን ያህል ትልቅ በረከት እንደሚያስገኝ አስተውሉ፡፡ ስለዚህ ለሌሎች በመራራት መኖርን የእምነታችን ተግባር ልናደርገው ይገባናል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለሁላችንም የሚራራ ልብ ይስጠን፡፡ አሜን፡፡

Saturday, August 30, 2014

የያዝከውን ልቀቀው


እንደዘመኑ መጓጓዣ ቴክኖሎጅ በሌለበት ወቅት ነበር አንድ ወጣት የማይቀርበት አስቸኳይ መልእክት የደረሰው፡፡ ወጣቱ መልእክቱ እንደደረሰው ሳይውል ሳያድር ጉዞውን ቀጠለ፡፡ ከብዙ ድካምና ውጣ ውረድ በኋላ ሰፊ ወንዝ ውኃው እስከ አፉ ድረስ ሞልቶ ከሚያጉረመርመው  በዋና መሻገር ከማይችለው ወንዝ ይደርሳል፡፡ በዋና መሻገር ቢፈልግም ዋና ስለማይችልና ወንዙ ሰፊ ስለነበር በዚህ ሐሳብ ጊዜ አላጠፋም፡፡ ሌላ ሊያሻግረው የሚችል ሰው ከአጠገቡ አለመኖሩ  ልቡን አሸበረው፡፡ የፀሐይ  ጉዞ ወደ መስኮቷ ገብታ ጨለማን ለማምጣት  ትቻኮላለች፡፡ ከዚያ  አካባቢ  ካልሄደ የዱር እንስሳት ጨለማውን ለብሰው ሊሰባብሩትና ሊገድሉት እንደሚችሉ እያወጣና እያወረደ ፈጣሪውን መለመን ጀመረ፡፡ በመከራህ ቀን ጥራኝ አድንህማለሁ ያለ አምላክ የወጣቱን የመከራ ጊዜ ሊለውጥለት የታመነ ስለሆነ የወጣቱን የልመና ቃል ሰማው፡፡ የወጣቱ ልመና "አምላኬ እግዚአብሔር ሆይ በጭንቄ ቀን እጠራሃለሁና የልመናዬን ቃል ስማ፡፡ ይህን በዋና መሻገር የማልችለውን ትልቅ ወንዝ በጥበብህ አሳልፈኝ፡፡ ሙሴንና እስራኤላውያንን የኤርትራን ባሕር ከፍለህ ያሻገርህ አምላክ የሚሳንህ እንደሌለ አምናለሁና ለእኔ ለባሪያህ በወንዙ ዳር ካሉት ዛፎች አንዲቷን እዘዛትና ጎንበስ ብላ እኔን ተሸክማ ከወንዙ ማዶ ታድርሰኝ፡፡ " የሚል ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ልመናውን ሰምቶ  ፈጸመለት፡፡ የዛፏን ጫፍ ይዞ ሳለ ዛፏ እርሱን ተሸክማ ከፍ ከፍ እያለች መጓዝ  ጀመረች፡፡ በእምነቱ ዛፏን እየጋለበ ያለው ወጣት በዛፏ እንቅስቃሴ በእምነቱ መዛል ሲጀምር የፈጣሪ ድምጽ ወደዚህ ወጣት መጣ፡፡ የዛፏ እንቅስቃሴ በሙሉ ከወንዙ መሐል ላይ እንደደረሰች ቆማለች፡፡ ወጣቱ የዛፏን ጫፍ እንደያዘ "እኔን ከወደድከኝ የያዝከውን ልቀቀው" የሚል ቃል ከአምላኩ ደረሰው፡፡ ወጣቱ  "አምላኬ ሆይ አንተን እወድሃለሁ ዛፏን ግን አልለቅም" የሚል መልስ መለሰ፡፡ ይህ ወጣት በእምነት ስለዛለ እንጅ የያዛትን ዛፍ ቢለቅ እግዚአብሔር በኪነ ጥበቡ ማዳን የሚችል አምላክ ነው፡፡ ወጣቱ ግን የእግዚአብሔርን ድምጽ መስማት አልፈለገም፡፡ እግዚአብሔር ደጋግሞ  "የያዝከውን ልቀቀው" አለው በዚሁ ልክ ወጣቱ "የያዝኩትን አልለቅም" የሚል መልስ ሰጠ፡፡ የእምነቱን መዛል የመረመረ እግዚአብሔር ዛፏ ከሥሯ ተቆርጣ እንድትወድቅ ባደረገ ጊዜ የዛፏን ጫፍ እንደያዘ ወጣቱ በወንዙ መሐል ወደቀ፡፡ ወንዙ በውኃ የተሞላ ነበርና ወጣቱ የዛፏን ጫፍ እንደያዘ እያገለባበጠ ወሰደው ወጣቱም በከፋ አሟሟት ሞተ፡፡ እግዚአብሔርን እንወዳለን የምንል እኛ ትዕዛዙን ልንጠብቅ ግዴታ አለብን፡፡ በአፍ ማመንና መውደድ ብቻ ለድኅነት የሚያበቃ ባለመሆኑ የልብ ንጽሕና ሊኖረን ይገባል፡፡ እግዚአብሔርን ስንወድ ደግሞ ልቀቁ የተባልነውን ሳንለቅ አይደለም እርግፍ አድርገን ለቅቀን እንጅ፡፡ በእምነት ሳለን እኛ እንድንይዛቸው ያልተፈቀዱ ነገሮች አሉ፡፡ እነዚህም ጣዖት ማምለክ፣ ዝሙት፣ ኃጢአት፣ስግብግብነት በአጠቃላይ የሥጋ ሥራዎች ናቸው፡፡ እነዚህን መጽሐፍ ልቀቁ ሲሉን መምህራን ልቀቁ ሲሉን አንቀን ይዘን አንለቅም እያልን እግዚአብሔርን እወዳለሁ ማለት የማይታለለውን መንፈስ ቅዱስ ለማታለል መሞከር በመሆኑ ይህ የድፍረት ኃጢአታችን እንደ ሐናንያና ሰጲራ ለከፋ ሞት ያደርሰናል፡፡  ሐዋ5÷1-10 ፡፡ የዚህ ወጣት ጉዳቶቹ በእምነቱ መዛሉ እና የአምላኩን ትዕዛዝ አለመቀበሉ ናቸው፡፡ የአብርሃምን ታሪክ ልብ በሉ፡፡እግዚአብሔር  አብርሃምን ከዘመዶችህ ከወገኖችህ ተለይተህ አገርህን ለቅቀህ ውጣ ባለው ጊዜ አብርሃም ሳያቅማማ ዘመድ ወገኑን ትቶ ሀገሩን ለቅቆ የእግዚአብሔርን ድምጽ እየሰማ ሔዷል፡፡ በዚህም ትልቅ በረከትን ለማግኘት በቅቷል፡፡ ስለዚህ እምነት አለን የምንል ሁሉ የያዝነውን የኃጢአት ሥራ ሁሉ ልንለቅ ያስፈልጋል፡፡ ወጣቱ ቤተክርስቲያን የምትልህን ስማ! ሲጋራ፣ ጫት፣ ዝሙት፣ ርኩሰት፣ ማመንዘር፣ መዳራት፣መስረቅ፣መግደል፣ ወዘተ… ልቀቅ፡፡ ይህን ካደረክ በኋላ ነው እግዚአብሔርን መውደድ የምትችለው፡፡ ከዚያ ውጭ ግን ዛፏን አልለቅም እንዳለው ወጣት ፈጥኖ ያጠፋሃል፡፡ አንተን የሚታገስ ኃጢአትህ እስኪፈጸም ድረስ ብቻ ነው፡፡ ኃጢአትህ በተፈጸመ ጊዜ ግን ያጠፋሃል፡፡ በተቃራኒው ግን "የያዝከውን ልቀቅ" ተብያለሁ በማለት ለራሳችን በሚመች ተርጉመን እምነታችንን፣እግዚአብሔርን፣ድንግል ማርያምን፣ ቅዱሳንን፣ ቤተ ክርስቲያንን ወዘተ… ልንለቅ አይገባም፡፡ ምክንያቱም እነዚህን ለቅቃችሁ እኔን ውደዱኝ አምልኩኝ የሚል አምላክ የአጋንንት ነውና፡፡ እኛ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች የምንረዳው የያዝከውን ልቀቅ ሲባል የሥጋ ሥራን መልቀቅ፤ የያዝከውን አትልቀቅ ሲባል ደግሞ የነፍስን ሥራ ማጽናት እንደሚገባን ነው፡፡  ስለዚህ የሥጋን ሥራ ለቅቀን የነፍስን ሥራ አጽንተን የፈጣሪን ትዕዛዝ ፈጽመን ለመኖር አምላካችን ይፍቀድልን፡፡ አሜን፡፡

Friday, August 29, 2014

ተፈጥሮን ካስተዋልን

የሁሉም አስገኝ እግዚአብሔር ለሥራው ሁሉ ጊዜ አለውና ፍጥረታትን መፍጠር የጀመረ እሁድ ሲሆን ሥራውን አርብ ፈጽሞ ቅዳሜ ከሥራው ሁሉ አርፏል፡፡ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ አክሲማሮስ በሚባል መጽሐፉ በእነዚህ ዕለታት የተፈጠሩ ፍጥረታት በቁጥር ብዙውን አንድ በማለት ሃያ ሁለት ናቸው በማለት ይናገራል፡፡ መዝ118፥126፣ ዘፍ 1፥1-25፣ መክ3፥1 ፣ መጽሐፈ አክሲማሮስ
መቼ ምን ተፈጠረ ቢሉ፡-
በስድስቱ ዕለታት የተፈጠሩት ሃያ ሁለት ፍጥረታት የሚከተሉት ናቸው፡፡
1.      እሁድ ፡- ስምንት ፍጥረታት ተፈጥረዋል፡፡
v  ሳት፣ኃ፣ ነፋስ፣ ጨለማ፣ ብርሃን፣ መሬት፣ ሰባቱ ሰማያትና መላእክት፡፡
2.     ሰኞ ፡- አንድ ፍጡር ተፈጥሯል፡፡
v  በሦስት የተከፈለው ውኃ ከምድር በታች ውቅያኖስ፣ ከጠፈር በላይ ሐኖስ የተባለውና ከአየር በላይ ጸንቶ ጠፈር የሆነው ውኃ፡፡
3.     ማክሰኞ ፡-ሦስት ፍጥረታት ተፈጥረዋል፡፡
v  ዕፅዋት፣ አዝርእትና አትክልት፡፡
4.     ረቡዕ ፡- ሦስት ፍጥረታት ተፈጥረዋል፡፡
v  ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት
5.     ሐሙስ ፡-አራት ፍጥረታት ተፈጥረዋል፡፡
v  በልብ የሚሳቡ፣በእግር የሚሽከረከሩ፣ በክንፍ የሚበሩና በደመ ነፍስ ህያዋን ሆነው የሚኖሩ በባሕር የተፈጠሩ፡፡
6.     አርብ ፡-አራት ፍጥረታት ተፈጥረዋል፡፡
v  ሰው፣ በየብስ የሚገኙ በደመ ነፍስ ህያዋን የሆኑ እንስሳት፣ አራዊትና አዕዋፍ
እነዚህን ፍጥረታት ካስተዋልናቸውና ከተረዳናቸው እጅግ በጣም አስተማሪዎች ናቸው፡፡ በተሰጠን ከሁሉም በሚበልጥ አእምሮ ፍጥረታትን ማስተዋል ከቻልን ብዙ የምንገበያቸው ቁም ነገሮች አሉ፡፡ ከብዙ አስተማሪ ፍጥረታት መካከል ጥቂቶችን ለመማሪያ ያህል እነሆ!
Ø 
ፀሐይ ፡- ለዓለም ሁሉ የምታበራ ጊዜዋን ጠብቃ በምሥራቅ የምትወጣና በምዕራብ የምትገባ ፍጡር ናት፡፡ መዝ103፥19፡፡ ከዚች ፍጡር ሁለት ነገር እንማራለን፡፡ የመጀመሪያው ብርሃን መሆን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ጊዜን በአግባቡ መጠቀምን ነው፡፡ ፀሐይ ለዓለም ሁሉ ብርሃን እንደሆነች ሁሉ እኛም በሥራችን ፣ በኑሯችን ለሌሎችም ሆነ ለራሳችን ብርሃን መሆን እንደሚገባን መማር እንችላለን፡፡ ብርሃን መሆን ማለት አስተማሪ የሆነ አኗኗር መኖር ማለት ነው፡፡ በቤተሰብ አመራር፣ በልጅ አስተዳደግ፣ በሥራ፣ በትምህርት፣ ለሰው በመራራት፣ ክርስትና ሕይወትን በተግባር መኖርን ወዘተ… ያካትታል፡፡ ሌላው ከፀሐይ የምንማረው ነገር ጊዜን በአግባቡ መጠቀምን ነው፡፡ ፀሐይ ጊዜዋን ጠብቃ እንደምትወጣና እንደምትገባ ሁሉ እኛም ጊዜያችንን ጠብቀን ቤተክርስቲያን ለጸሎት ለስግደት ለአገልግሎት መሄድ እንዲገባን እንማራለን፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ ግን ከዚህ በመለየቱ ጊዜውን ጠብቆ ባለመግባቱና ባለመውጣቱ ወጣቱ ሽማግሌው በአልባሌ ቦታ ወድቆ የበሽታ ሰለባ የወንጀል ተቋዳሽ ለመሆን ተገዷል፡፡ ስለዚህ ከፀሐይ በመማር ጊዜያችንን በትክክል ለሚፈለገው ተግባር ብቻ ማዋል አርአያነታችንን ለዓለም ሁሉ እንዲያበራ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡
Ø  ዕፅዋት፡- ከቦታ ቦታ የማይንቀሳቀሱ ለሰው ልጅ ኑሮ ተስማሚ የሆነውን ንጹህ አየር የሚለግሱ ናቸው፡፡ የሰው ልጅ ሊጠቀምባቸው ፈልጎ በምሳር በመጋዝ ቢቆርጣቸው እንኳ  ለምልመው አቆጥቁጠው ይወጣሉ እንጅ ፈጽመው አይጠፉም ጥቂት ከሚባሉ ዕፅዋት በስተቀር፡፡ዕፅዋት ከተተከሉበት ቦታ የማይንንቀሳቀሱ እንደሆኑ ሁሉ እኛም ከሥላሴ ልጅነት ከተተከልንባት ቅድስት ቤተክርስቲያን ካደግንባት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ውጭ ልንንቀሳቀስ እንደማይገባ እንማራለን፡፡ ከጥቂት ዕፅዋት በቀር ሲቆረጡ እንደሚለመልሙ እንደሚያቆጠቁጡ ሁሉ እኛም ሰይጣን በተለያየ ዘዴ በኃጢአት ቢቆርጠን በመማርና በንስሓ መለምለም ማቆጥቆጥ እንዳለብን እንማራለን፡፡ስለዚህ ከዕፅዋት ተምረን በእምነታችን ጸንተን ከቤተክርስቲያን ተተክለን በንስሓ ለምልመን መኖር ይጠበቅብናል፡፡
Ø 
በሬ፡- ትልቅ እንስሳ ሆኖ ሳለ ሕጻናት ሳይቀሩ በፈለጉት አቅጣጫ ይነዱታል፡፡ ምንም እንኳ ክረምት ከበጋ ለሰው ልጅ የሚደክም ቢሆንም የድካሙ ክፍያ ፍሬ ሳይሆን ገለባ ጭድ ነው፡፡ በትሕትና ዝቅ ብሎ የቀረበለትን ገለባ ጭድ ይመገባል፤ ገለባ ጭድ ካላቀረቡለት ጎንበስ ብሎ ሣር ይግጣል፡፡ ይህን ተመግቦ የሚጥለው እበት ለቤት ማስጌጫነትና ለማገዶነት  ይውላል፡፡  አስተዋላችሁ ወገኖቼ! እኛም ከበሬ በመማር ለራሳችን ትልቆች ስንሆን የታናናሾችን ምክርና ተግሳጽ ያለመናቅ በማክበርና በማስተዋል መቀበል ይገባናል፡፡ ትሕትና መማር አለብን ማለት ነው፡፡ በሬ በትልቅነቱ ተመክቶ ሕጻናት ሲነዱት በሕጻናት ላይ አመጸኛ እንዳይደለ እኛም ሕጻናትን አይጠቅሙም በማለት ከቤተክርስቲያን እንዲወጡና ከማመስገን ዝም እንዲሉ ልናምጽባቸው አይገባም፡፡ ማቴ 19፥14፣ማቴ21፥16  የበሬ የድካም ክፍያ ገለባ ጭድ ቢሆንም በዚህ ተበሳጭቶ ሥራውን እንደማያቆም ሁሉ በቤተክርስቲያን አገልግሎት ስንሳተፍ ደመወዙ ዝቅተኛ ቢሆንብን ወይም ባይከፈለን በዚያ ተበሳጭተን ኪዳን ከማድረስ፣ ቅዳሴ ከመቀደስ፣ ሰዓታት ከመቆም፣ ወንጌል ከማስተማር ወዘተ… ልንርቅ አይገባንም፡፡ ሌላው አስተማሪ ነገር በኩራት ፈረስ የምንጋልብ ራሳችንን ከፍ ከፍ ማድረግ የሁልጊዜ ተግባራችን የሆነ እኛ ያማረ መብልና መጠጥ መርጠን ተመግበን የሚወጣን አሰር ሽታ ለራሳችን ሳይቀር አያስቀርብም፡፡ ስለዚህ ከበሬ በመማር ኩራትንና ራስን ከፍከፍ ማድረግን በማራቅ በትሕትና ራሳችንን ዝቅ አድርገን በፈሪሐ እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያን ልንኖር ይገባናል፡፡
Ø 
ርግብ፡- የመንፈስ ቅዱስ (ማቴ 3፥16) ፤ የእመቤታችን (ዘፍ 8፥8-11) ምሳሌ ሆና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ጊዜ ተጽፋ እናገኛለን፡፡ ርግብ በአንድ ባል ጸንታ የምትኖር ባሏ የሞተ እንደሆነም ምላሷን ሰንጥቃ በብቸኝነት ትኖራለች፡፡ ሌላ ወንድ የመጣባት እንደሆነ የተሰነጠቀ ምላሷን በማሳየት ትመልሰዋለች፡፡ በርግቦች ዘንድ ድጋሜ ሌላ ወንድ ማግባት ነውር ነው፡፡ ትንሣኤ ሙታን ያለን እኛስ? አስቡት እንኳን የትዳር አጋራችን ሞቶብን ቀርቶ በሕይወት እያሉ በላያቸው ላይ የምንነግድባቸው ቀላል ነን እንዴ? ርግብን ማስተዋል ከቻልን በሥጋና ደሙ ጋብቻችንን መሥርተን በአንድ ጸንተን በመተሳሰብ፣ በመረዳዳትና በመፈቃቀር የምንኖር እንሆናለን፡፡ ምናልባት በሞት የምንለያይ ከሆነና ብቻን ለመኖር አስቸጋሪ ሆኖ ከተገኘ በድጋሜ በሥጋና ደሙ ማግባት ይቻላል፡፡ ይህ ሥርዓት የሚፈጸመው ለምዕመናን ሦስት ጊዜ ለካህን ሁለት ጊዜ (ክሕነቱ ፈርሶ) ከዚህ የዘለለ ጋብቻ ግን ከዝሙት ይቆጠራል፡፡ ስለዚህ ከርግብ በመማር ለትዳራችን ታማኝ በመሆን እግዚአብሔርን በመፍራት ልንኖር ይገባናል፡፡
Ø
 
ጉንዳን፡- በመጠን በጣም ትንሽ ፍጡር ብትሆንም በትጋት የክረምት ምግቧን በበጋ ትሰበስባለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በመተባበርና በመረዳዳት ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ፍጡር ናት፡፡ በጣም ከባድና አስቸጋሪ የሆነን ነገር ሳይቀር በመተባበር ከቦታቦታ የማንቀሳቀስ ችሎታ አላት፡፡ ከዚች ፍጡር መማር የተሳነው የሰው ልጅ የሰማይ ምግቡን በምድር መሰብሰብ አልቻለም፡፡ የሰማይ ምግባችንን ክረምት ሳይቀርብ መንቀሳቀስ በምንችልበት ወቅት ልንሰበስብ ይገባናል፡፡ እንደ ጉንዳን በመረዳዳትና በመተባበር  ለሀገራችን፣ ለወገናችንና ለቤተ ክርስቲያናችን አስቸጋሪ የሆነን ፈተና ማንከባለልና ማስወገድ ይጠበቅብናል፡፡ ስለዚህ ከጉንዳን በመማር በፍቅር መተባበርን፣ ለሰማይ ምግባችን ስብሰባ መትጋትን የሁልጊዜ ተግባራችን ልናደርግ ይገባናል፡፡
Ø  አውራ ዶሮ፡-ከጥንት ጀምሮ ዶሮ ሲጮኽ ሌሊቱ እንደነጋ ማረጋገጫ ነው፡፡ ለዚህም ነው “ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት …”  የሚባለው፡፡ ሰዓቱን ጠብቆና አክብሮ በመጮኽ የሚታወቅ እንስሳ ነው ዶሮ፡፡ ከዚህ በመማር እኛም ጊዜውን ጠብቀን በጸሎት በስግደት በጾም ወደ እግዚአብሔር ልንጮኽ ያስፈልጋል፡፡ ዳዊት በቀን ሰባት ጊዜ አመሰግንሃለሁ፡፡ መዝ118፥164   እንዳለ በሰዓቱ ምስጋና ገንዘቡ የሆነውን እግዚአብሔር በማመስገን መጮኽ አለብን፡፡
በአጠቃላይ እነዚህን እጅግ ጥቂት ፍጥረታትን ለመግለጽ ሞከርን እንጅ ተፈጥሮን ካስተዋልን ተራ የሚመስሉ ነገሮች ሁሉ አስተማሪዎች ናቸው፡፡ ቅዱስ ያሬድን ለዚያ ሁሉ ክብርና ቅድስና ያበቃው ተራ ከምንለው ትል መማሩ ነው፡፡ ስለዚህ ተፈጥሮን በመረዳትና በማስተዋል ልንማር ያስፈልጋል፡፡ ሰባኪ መምህር፣ ዘማሪ ወይም መጽሐፍ ባናገኝ እንኳ በአካባቢያችን ከምናያቸው ፍጥረታት መማር ያስፈልገናል፡፡ ፈጣሬ ዓለማት እግዚአብሔር ማስተዋልን ያድለን፡፡ አሜን፡፡ መድረሻ እሳቱ የማይጠፋ ትሉ የማያንቀላፋ የኩነኔ ቦታ በመሆኑ፡፡ የመንግሥተ ሰማያት መድረሻ ሀዲድ እጅግ ጠባብ ብትሆንም ፍጻሜዋ ተድላ ደስታ የሞላባት የጽድቅ ቦታ በመሆኗ ወደዚች በሚወስደው ሀዲድ ላይ መሽከርከር አለብን፡፡ ስለዚህ የመንግሥተ ሰማያት ወራሾች እንሆን ዘንድ የጽድቅ ሥራ እየሠራን እንድንኖር ሁልጊዜ በጸሎት መትጋት ይገባናል፡፡   የዲያብሎስ ባቡሮች ከመሆን ተቆጥበን ራሳችንን ለፈጠረን እግዚአብሔር በማስገዛት ለመኖር በቸርነቱ ይርዳን፡፡

Thursday, August 28, 2014

የቅናቱ መቅናት

እግዚአብሔር አምላክ ሰይጣናዊ ቅንዓትን ወደ መልካም ሲቀይር የጥበቡን ስፋት ተመልከቱ፡፡ አንድ ሁሉ የሞላው ንፉግና ቅንዓተኛ ባለጠጋ  እና ከዕለት ጉርሱ ከዓመት ልብሱ የሚተርፍ ገንዘብ የሌለው እግዚአብሔርን የሚፈራና የሚያመሰግን ድሃ በአንድ ሰፈር  በጉርብትና ይኖሩ ነበር፡፡የድሃው የሁልጊዜ ልመናና ጸሎት እንዲሁም የልቡ ምኞት የዕለት ምግቡን እንዳይነፍገው፣ ጤናውን እንዲሰጠውና ያለውን ጥቂት ነገር እንዲባርክለት፣ በዓለም ፍጻሜም ከቅዱሳኑ ጋር በቀኙ እንዲያቆመው ነው፡፡ በአንጻሩ የባለጠጋው ምኞት ደግሞ ይህ ድሃ ሰው ከአጠገቡ ተነቅሎ እንዲሄድለትና መሬቱን የራሱ አድርጎ መኖር ነበር፡፡ ይህ ንፉግ ባለጠጋ ድሃው ለምግብ ያህል ሰርቶ በሚያገኛት ጥቂት ገንዘብ እጅግ አብዝቶ ይቀና ነበር፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀን ድሃው የነበረችውን ትንሽ መሬት በጥሩ ሁኔታ አርሶና አለስልሶ የሚዘራው የጤፍ ዘር ስላልነበረው ከአጠገቡ ከሚገኝ ቤተክርስቲያን ሄዶ በእምነት "አምላኬ ሆይ ጉልበቱን ሰጥተህ ከእኔ የሚጠበቀውን ተግባር ሁሉ ፈጽሜያለሁ ነገር ግን የምዘራው የጤፍ ዘር የለኝምና ድካሜን ከንቱ አታስቀርብኝ የምዘራው ዘር ስጠኝ፡፡ አዳምን ከኅቱም ምድር የፈጠርህ በባዶ ግንባር ላይ ዓይንን የሠራህ አምላክ የሚሳንህ ነገር እንደሌለ አምናለሁና የባሪያህን ልመና ተቀብለህ የልቤን መሻት ፈጽምልኝ " በማለት የሚመካበትን እግዚአብሔር ለመነ፡፡ ከዚህ በኋላ ይህ ድሃ እግዚአብሔር ልመናውን እንደሚፈጽምለት አምኖ ወደቤቱ ተመልሶ መሬቱን አርሶ ለዘር ምቹ አደረገው፡፡ በዚህ ተግባሩ ዓይኑ ደም የለበሰው ባለጠጋ "ይህ የሚልሰው የሚቀምሰው የሌለው ድሃ ምን የሚዘራው ነገር ኖሮት ይሆን እንዲህ የሚደክም? ይህን መሬት ለእኔ ያላደረኩት እንደሆነ ሰው አይደለሁም " ሲል ዛተ፡፡ የእግዚአብሔርን ኃያልነትና ጠቢብነት የተረዳው ድሃ ጀንበሯ ስትጠልቅ ኩልል ባለችው ጨረቃ የምድጃውን አመድ በቁና እያፈሰ ለዘር ባመቻቸው መሬት ላይ በእምነት ዘራው፡፡ ይህን ሲያደርግ በቤቱ መስኮት ቀዳዳ ይመለከት የነበረው ባለጠጋ ድሃው ነጭ ጤፍ የዘራ ስለመሰለው በቅንዓት አረረ፡፡ በሌሊትም ተነሥቶ "ነጭ ጤፍ" በተዘራበት በድሃው መሬት ላይ ቀይ ጤፍ ዘራበት፡፡ ድሃውም ጤፍ እንደበቀለለት ባየ ጊዜ እጅጉን ተደስቶ እግዚአብሔርን በማመስገን ጤፉን በማረምና በመንከባከብ አጭዶ ሰብስቦ በብዙ ኩንታል የሚቆጠር ቀይ ጤፍ አምርቶ አሥራቱን ከፍሎ ለድሆች መጽውቶ የተረፈውን በጎተራ አስገብቶ እግዚአብሔርን እያመሰገነ ኖረ፡፡ " ለምኑ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ ታገኙማላችሁ " ማቴ7÷7  በማለት የተናገረ አምላክ የድሃውን የልመና ቃል ሰምቶ ፈጸመለት፡፡ የባሕራንን የሞት ደባዳቤ ወደ ሕይወት የለወጠ፣ ዳንኤልን ከአናብስት አፍ የጠበቀው፣ ሶስናን ከዕደ ረበናት ያተረፈ፣ ቂርቆስና ኢየሉጣን ከፈላ ውኃ ያዳነ፣ የአንጢላርዮስን ንፍገት ወደ ለጋስነት የቀየረ፣… ተዘርዝሮ የማያልቅ ተአምራትን ያደረገ አምላክ የዚህን ድሃ ልመና ሰምቶ የባለጠጋውን ቅንዓት አቀናለት አመድን ጤፍ አደረገለት፡፡ "አንተን ተስፋ የሚያደርጉ አያፍሩም" መዘ24÷3  ተብሎ እንደተጻፈ እግዚአብሔርን ተስፋ ብናደርግ የሚያሳጣን ነገር እንደሌለ ልናምን ያስፈልጋል፡፡ እግዚአብሔር ከዚህም በላይ ሊያደርግልን ይቻለዋል ለሰው የማይቻል ሁሉ በእርሱ ዘንድ ይቻላልና፡፡ በመጀመሪያ ጽድቅና መንግሥቱን እንፈልግ እንጅ ሌላውን ይጨምርልናል፡፡ ምክንያቱም እርሱ እኛ ለእኛ ከምናስበው በበለጠ ያስብልናልና፡፡ ለኛ መቼ ምን እንደሚያስፈልገን ያውቃልና ሁሉንም በጊዜው መጠበቅ ከኛ ይጠበቃል፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔርን አምላክነት፣ ቸርነት፣ ፍቅርና ርኅራኄ አምነን ሥሙን በማመስገን  ለመኖር አምላከ ቅዱሳን ይርዳን፡፡ አሜን፡

Monday, August 25, 2014

ጎጆ ቤት እና የባቄላ እሸት

በአንድ አካባቢ ሁለት ጎረቤታሞች ይኖሩ ነበር፡፡ አንዱ ገንዘብ የበዛለት ይህ ቀረህ የማይባል ንብረቱ ስፍር ቁጥር የሌለው ባማረና በተዋበ ቤት በምቾትና በቅንጦት የሚኖር ተንኮለኛና ምቀኛ ባለጠጋ ሲሆን ሌላኛው ግን ከአንዲት የጎሰቆለች ጎጆ ቤት በቀር ምንም የሌለው አዛኝና ርኅሩኅ ፈሪሐ እግዚአብሔርን ገንዘቡ ያደረገ ድሃ ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ያ ተንኮለኛና ምቀኛ ባለጠጋ ተንኮሉን ለመጀመር ከድኃው ጎጆ ጋር አያይዞ ጎጆ ቤት ሠራ፡፡ ከተወሰኑ ጊዜያት በኋላ ባለጠጋው ያንን መከረኛ ድሃ ጎረቤቱን “ብርዱ በጣም ስለጨመረ ጎጆዬን በእሳት አቃጥዬ ልሞቃት ስለሆነ ያንተ ጎጆ እንዳትቃጠል ከፈለግህ ራቅ አድርጋት” አለው ድሃው ጎጆውን አፍርሶ የሚሠራበት ገንዘብ እንደሌለው ስለሚያውቅ አብሮ ለማቃጠል ልቡ በተንኮል ስለተነሣሣ፡፡ ድሃውም በተንኮል እንደተነሣሣበት ስለገባው ቤቱን ለማትረፍ ገንዘብ ተበድሮ አፍርሶ ራቅ አድርጎ ለመሥራት ቢሞክርም ገንዘብ የሚያበድረው ሰው በማጣቱ ባለጠጋው የራሱን ቤት ሲያቃጥል የድሃውም ቤት አብሮ ተቃጠለ፡፡ በቀል የእግዚአብሔር መሆኑን በሚገባ የሚያውቀው ድሃ በቀሉን ለእግዚአብሔር ትቶ ቤቱ የተቃጠለበትን ቦታ አጥሮ ከቆፈረ በኋላ ባቄላ ዘርቶት ወደ ሩቅ አገር ተሰደደ፡፡ ባቄላው ለእሸት በደረሰ ጊዜ ያ ድሃ ሁኔታውን ለማየት ከስደት ተመልሶ ሳለ የባለጠጋው ልጅ እሸቱን እየቀጠፈ ሲበላ ስለደረሰበት ምስክር ለሚሆኑ ሽማግሌዎች ያሳያቸዋል፡፡ ወዲያውኑ ከዳኛ ዘንድ ሄዶ የደረሰበትን መከራና ግፍ በምሬት “በጉርብትና ሳለን ቤቴን አቃጠለብኝ እኔም ቦታዬን ባቄላ ዘርቼ ተሰደድኩለት፡፡ የባቄላውን ሁኔታ ለማየት ከስደት ስመለስ ልጁ አጥሩን ጥሶ የባቄላውን እሸት ሲቀጥፍ ደረሰኩበት፡፡ ይህንንም የአካባቢው ሽማግሌዎች ሳይቀሩ አይተዋል፡፡ ስለዚህ ለተበደልኩ ለእኔ ፍረድልኝ ፡፡”  ሲል ተናገረ  ዳኛውም ይህን የተበደለ ሰው ድምጽ እንደሰማ ያን ባለጠጋ ከነልጁ አስጠርቶ መልስ እንዲሰጥ አደረገው፡፡ የባለጠጋው መልስ ግን “የባቄለውን  ሸት እተካለታለሁ፡፡ ቤቱን ግን እኔ አላቃጠልኩበትም የራሴን ቤት እንጅ” የሚል ነበር፡፡ ልቡ በግፍ ብዛት የቆሰለው ድሃ ግን “ምትክ አልፈልግም የልጁ ሆድ ተሰንጥቆ የራሴ የሆነው ባቄላ ወጥቶ እንዲሰጠኝ እፈልጋለሁ፡፡በማለት በዳኛው ፊት ተናገረ፡፡ ዳኛውም ግፍህ በዝቷልና የወደድከውና የፈቀድከው ይሁን ብሎ ፈረደለት፡፡ ያ ባለጠጋ ደንግጦ ፈዘዘ ደነገዘ፡፡ ልቡ ሲመለስለት “የልጄ ሆድ ከሚሠነጠቅ ያለኝን ሀብትና ንብረት እኩል ላካፍለው”  በማለት በዳኛው ፊት ተማጸነው፡፡ ድሃውም ከብዙ ልመና በኋላ “ምን ያህል ግፍ እንደፈጸምክብኝ እንድትረዳ በመፈለጌ እንጅ የልጅህን ሞት ፈልጌ አይደለም፡፡ አሁን ግን ሥራህን ሁሉ ስላወቅኸው እንድትማርበት ትቼዋለሁ” በማለት ገንዘቡን እኩል ለመካፈል ተስማማ፡፡ ዳኛውና ሽማግሌዎች የባለጠጋውን ሀብትና ንብረት በሙሉ ለሁለት እኩል ከፍለው ሠጡት፡፡ ያ ድሃም በግፍ ከተባረረበት ቦታው ላይ ያማረ ቤት ሠርቶ በደስታ እግዚአብሔርን በማመስገን ኖረ፡፡ “በመከራህ ቀን ጥራኝ አድንህማለሁ አንተም ታከብረኛለህ፡፡”መዝ 49÷15 በማለት የተናገረ አምላክ “አቤቱ ፍረድልኝ ከጽድቅ ከራቁ ሕዝብም ክርክሬን ተከራከር ከሸንጋይና ከግፈኛ ሰው አድነኝ፡፡” መዝ 4÷21 በማለት የዳዊትን ልመና በመለመን ላይ የነበረውን ድሃ ልመና እግዚአብሔር ሰማ፡፡ መዝ33÷6  ይህ ድሃ በበቀል ተነሣስቶ በባለጠጋው ላይ አንዲትም ጉዳት አላደረሰበትም፡፡ በቀል የእግዚአብሔር መሆኑን ያውቅ ስለነበር “አቤቱ ተነሥ በቀልህንም ተበቀል፡፡” መዝ73÷22 የሚለውን የዳዊት መዝሙር እየዘመረ ቦታውን ለቅቆ ተሰደደ፡፡ “እግዚአብሔር የበቀል አምላክ ነው፡፡ የበቀል አምላክ ተገለጠ፡፡”መዝ 93÷1 በማለት ዳዊት ያመሰገነው እግዚአብሔር ለድሃው የልመናውን ዋጋ ሰጥቶታል፡፡ ስለዚህ በባለጠግነታችን ተመክተን በድሆች ላይ አንዳች ግፍ ልንፈጽም አይገባም፡፡ ምክንያቱም በገንዘባችን ብዛት መግዛት የማንችላቸው ነገሮች በርካታ ስለሆኑ፡፡ ገንዘብ እንደ በረሐ አበባ ታይቶ የሚጠፋ ከንቱ ነገር ነው፡፡ በአግባቡ ሲጠቀሙበት የሚጠቅም በአግባቡ ካልተጠቀሙበት ደግሞ የሚጎዳ ነው፡፡ ገንዘብ የምንገዛበት እንጅ የሚገዛን አይደለም፡፡ በገንዘባችን ከገዛንበት ጥቅም ላይ ዋለ ማለት ነው፤ ነገር ግን ገንዘቡ ከገዛን ትልቅ ጉዳት ይሏችኋል ይህ ነው፡፡ “ለችግረኛና ለምስኪን የሚራራ ምስጉን ነው፡፡” መዝ40÷1  ይላልና ለድሆች ራርተን የምንመጸውት ከሆነ ገንዘባችንን እንደ አብርሃም ጥቅም ላይ ማዋል ቻልን ማለት ነው፡፡ ወገኖቼ ገንዘብ በአግባቡ ካልተያዘ ጥፋቱ ይበዛልና በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ባለጠግነት ደግሞ ከአምላክ ካልተሰጠ በቀር ከየትም አይገኝም፡፡ አንዳንድ ሞኞች ስለወጡ ስለወረዱ ያገኙ ይመስላቸዋል፤ ለማግኘት መሥራት ግዴታ ነው፤ ነገር ግን አምላክም እንዲጨመርበት ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ከአምላክ ፈቃድ ውጭ የትም መሄድ አይቻልምና፡፡ ስለዚህ ለድሆች ራርተን ካለን መጽውተን በእግዚአብሔር ቤት መኖር ያስፈልጋል፡፡ ይህንንም ለማድረግ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡ አሜን፡፡
ማጣቀሻ፡- መዝ61÷10፣ ማቴ 19÷24፣ ሉቃ12÷15፣ ሉቃ21÷1-4

Sunday, August 24, 2014

ቁልፉ የት ነው?

“በሔዋን ምክንያት የተዘጋ የገነት ደጅ በድንግል ማርያም ተከፈተልን፡፡” ውዳሴ ዘሐሙስ በሔዋን ምክንያት ለ5500 ዘመን ያህል ተዘግታ የነበረችው ገነት በኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ላይ ቤዛነት በፈሰሰ ደሙ ተከፍታለች፡፡ በአሁኑ ጊዜ ይህች ገነት ክፍት ብትሆንም መግባት የሚችሉት ጻድቃን እንጅ ኃጥአን አይደሉም፡፡ ኃጢአት ገነት ስለማያስገባ ለኃጥአን አሁንም ቢሆን ዝግ ናት፡፡ ታዲያ በኃጢአታችን የተዘጋችብንን ገነት እንዴት ልንከፍታት እንችላለን? መክፈቻ ቁልፉ የት ይገኛል? የሚሉትን ለማየት እንሞክር፡፡ በክርስቶስ ደም መፍሰስ ነጻነት የታወጀልን ክርስቲያኖች በኃጢአታችን ዳግም በባርነት ቀንበር ውስጥ የተያዝን ከሆነ ገነት ተዘግታብናለችና መክፈቻ ቁልፍ ያስፈልጋል፡፡ መክፈቻ ሳንይዝ ምድራዊ ቤታችንን እንኳ መክፈት አይቻልም፡፡ የምድራዊ ቤታችንንስ ቁልፉን ሰብረን ልንገባ አልያም መክፈቻ ቁልፉን ተመልሰን ልንፈልግ እንችል ይሆናል፤ የሰማያዊ ቤታችን ግን እንዲህ አድርገን ልንከፍት ወይም ተመልሰን ቁልፉን ልንፈልግ ጥቂት እንኳ ሥልጣን የለንም፡፡ ከሞት በፊት የሰማይ ቤት መክፈቻ ቁልፎችን መፈለግ ብልህነት ነው፡፡ እነዚህ መክፈቻ ቁልፎችን በካህናት እጅ ሁል ጊዜ እናያቸዋለን ነገር ግን እንዲሠጡን ጠይቀናቸው አናውቅ  ይሆናል፡፡ ታዲያ ቁልፉን ሳንይዝ ወዴት ልንገባ ነው? እስከ ሞት ድረስ ንስሓ አባት ሳንይዝ በኃጢአት ላይ ኃጢአት በበደል ላይ በደል ስንሠራ የምንገኝ፡፡ ወደድንም ጠላንም የገነት መክፈቻ ቁልፍ ማግኘት የምንችለው በንስሓ የምንመለስ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ኑሯችን በምክረ ካህን የተመሠረተ ከሆነ ገነት የተቆለፈችባቸውን ቁልፎች ሰብረን ሳይሆን ከፍተን የምገባባቸውን መክፈቻዎች ተረክበን ለመሄድ ሥልጣን ይሰጠናል፡፡ ገነት የተዘጋችባቸው ታላላቅ ቁልፎች ሁለት ሲሆኑ እነዚህም አሥር እና ስድስት መክፈቻዎች ያሏቸው ናቸው፡፡ ስለዚህ ገነትን ከፍቶ ለመግባት በጠቅላላ አሥራ ስድስት መክፈቻዎችን ከአባቶቻችን መረከባችንን ማረጋገጥ ግዴታችን ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ቁልፎች የሚከተሉት ናቸው፡፡
ቁልፍ 1፡- ፲ቱ ትዕዛዛተ ኦሪት
ይህ የገነት ቁልፍ የሚከፈተው የሚከተሉትን አሥር መክፈቻዎች መያዝ ስንችል ብቻ ነው፡፡
፩. እግዚአብሔር አምላክህ እኔ ነኝ፡፡ ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ፡፡
፪. የአምላክህን ሥም በከንቱ አትጥራ፡፡
፫. የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ፡፡
፬. አባትህንና እናትህን አክብር፡፡
፭. አትግደል፡፡
፮. አታመንዝር፡፡
፯. አትስረቅ፡፡
፰. በሐሰት አትመስክር፡፡
፱. ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፡፡
፲. የባልንጀራህን ቤት አትመኝ፡፡
በእነዚህ አሥር መክፈቻዎች  የመጀመሪያውን ቁልፍ ስንከፍት ስድስት መክፈቻ ያለውን ሁለተኛ ቁልፍ ተቆልፎ እናገኛዋለን፡፡
ቁልፍ 2፡- ፮ቱ ሕግጋተ ወንጌል
ይህን ቁልፍ ለመክፈት ስድስት መክፈቻዎችን መያዝ ይኖርብናል፡፡ እነዚህም፡-
  . በወንድምህ ላይ በከንቱ አትቆጣ፡፡
  . ወደ ሴት አትመልት በልብህም አታመዝር፡፡
  . ሚስትህን ያለ ዝሙት ምክንያት በሌላ ነውር አትፍታ፡፡
  . ፈጽመህ አትማል፡፡
  . ክፉን በክፉ አትመልስ፡፡
  . ጠላትህን ውደድ፡፡
ይህን ሁለተኛ ቁልፍ መክፈት ከቻልን ጻድቃን የሚኖሩባትን ገነት መግባት የምችልበት ፈቃድ እናገኛለን፡፡ ነገር ግን ከእነዚህ አሥራ ስድስት መክፈቻዎች መካከል አንዲቷ እንኳ ብትጠፋን የገነት መግቢያ ፈቃድ ስለማናገኝ የጠፋብንን ቁልፍ በቀጥታ ወደ ካህናት በመሄድ ንስሓ በመግባት መረከብ የምንችልበት መብት ስላለን ተረክበን ጉዟችንን መጠበቅ ብቻ ነው፡፡ እነዚህ ቁልፎች ደግሞ በትክክል መክፈት እንዲችሉ ለማድረግ ተርቤ አብልታችሁኛል? ተጠምቼ አጠጥታችሁኛል? እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛል? ታርዤ አልብሳችሁኛል? ታምሜ ጠይቃችሁኛል? ታስሬ ወደ እኔ መጥታችኋል? የሚሉትን ጥያቄዎች አሁን እየመለስናቸው መሆኑን ቆም ብለን ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ ጉዞው ሩቅ ስለሆነ ለመመለስ የሚቻል ባለመሆኑ ከመጓዛችን በፊት የመክፈቻ ቁልፎችን መዘንጋት የለብንም፡፡ ካህናት አባቶቻችን ያላቸው ሥልጣን ቀላል የሚመስለው ካለ ያ ሰው መክፈቻ በማያስፈልገው ሲኦል መቃጠሉ አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ገነት በዋዛና በፈዛዛ ኖረን የምንገባባት ተራ ቦታ አይደለችምና፡፡ ማንም በኃጢአት የኖረ ሁሉ ያለምንም መክፈቻ ሲኦል ሊገባ ይችላል ገነትን ግን ያለ መክፈቻ ከፍቶ የሚገባ ማንም የለም፡፡ ስለዚህ ገነት መግባት የምንፈልግ ሁሉ በቸርነቱ የሚሰጠንን መክፈቻ ከካህናት አባቶቻን ልንረከብ ግድ ነው፡፡   

Friday, August 22, 2014

ቀስቃሹ ተቀስቃሽ

ክብርና ምስጋና ይግባውና ኢየሱስ ክርስቶስ ነፋስና ባሕር እንዴት እንደታዘዙለት የአምላክነቱን ጥበብ በወንጌል ላይ እንዲህ እናነባለን፡፡ “በዚያም ቀን በመሸ ጊዜ፡- ወደ ማዶ እንሻገር አላቸው፡፡ ሕዝቡንም ትተው በታንኳ እንዲያው ወሰዱት ሌሎች ታንኳዎችም ከእርሱ ጋር ነበሩ፡፡ ብርቱ ዐውሎ ነፋስም ተነሣና ውኃ በታንኳይቱ እስኪሞላ ድረስ ማዕበሉ በታንኳይቱ ይገባ ነበር፡፡ እርሱም በስተኋላዋ ትራስ ተንተርሶ ተኝቶ ነበር፡፡ አንቅተውም መምህር ሆይ ስንጠፋ አይገድህምን? አሉት፡፡ ነቅቶም ነፋሱን ገሰጸው ባሕሩንም ዝም በል ፀጥ በል አለው፡፡ ነፋሱም ተወ ታላቅ ፀጥታ ሆነ፡፡ እንዲህ የምትፈሩ ስለምን ነው?  እንዴትስ እምነት የላችሁም? አላቸው፡፡ እጅግም ፈሩና እንግዲህ ነፋስም ባሕርም የሚታዘዙለት ይህ ማነው ተባባሉ?” ማር4፥35-41፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ደካማ ሥጋ መልበሱን ፣ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ መሆኑን ያስተማረበት ክፍል ነው፡፡ ምክንያቱም እንደ ሰውነቱ ተኝቶ ተቀሰቀሰ እንደ አምላክነቱ ነፋሱን ባሕሩን ገስጾ ያሳየበት በመሆኑ፡፡ ባሕር መገሰጽማ እነሙሴስ አድርገውት የለም? ትለኝ እንደሆነ አድርገውታል ነገር ግን እነርሱ በጸጋ እርሱ ግን በባሕርይው ነው፡፡ በታንኳይቱ የነበሩት ሰዎች መገሰጽ የሚችሉ ባለመሆናቸው ኢየሱስ ክርስቶስን አንቅተው “አቤቱ ስንጠፋ አይገድህምን?” ማለታቸው ደግሞ ከእነርሱ የሚበልጥ እንደሆነ በመረዳታቸው ነው፡፡ ባሕሩንና ነፋሱን በገሰጸውና ማዕበሉ ፀጥ ባለ ጊዜ ፈርተው ነፋስም ባሕርም የሚታዘዙለት ይህ ማነው? ብለው የአምላክነት ሥራውን አድንቀዋል፡፡ ይህ ነፋስም ባሕርም የሚታዘዙለትን የጌቶች ጌታ፣ የነገሥታት ንጉሥ፣ የአማልክት አምላክ ክርስቶስ ኢየሱስ እንደሆነ እናምናለን፡፡ “ክርስቶስ በሥጋ መጣ እርሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው፡፡” ሮሜ 9፥5 ተብሎ እንደተጻፈ ክርስቶስ በተዋሕዶ በሥጋ ማርያም ቢገለጥ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ አላነሰም አልበለጠምም ትክክል ነው እንጅ፡፡ ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና የቀስቃሹን ተቀስቃሽ መሆን እንመልከት፡፡ ክርስቶስን አንቅተው ስንጠፋ አይገድህምን? ያሉት በእርሱ የተፈጠሩ በክብራቸው በማዕርጋቸው ዝቅተኛ የሆኑ ፍጡራን ናቸው፡፡ እነርሱ በጊዜው የተሸለ ልመና አቅርበዋል፡፡ በዚያ ሰዓት ከእርሱ ውጭ ሌላ አካል ሊያድናቸው እንደማይችል ያውቃሉና፡፡ ይህን ወደ እኛ ሕይወት እንመልሰው፡፡ አንዳንድ ጊዜ እንደ እኛ አመለካከት ያልተማሩ ፣ አላዋቂ የሚመስሉን ሥልጣንና ማዕርግ የሌላቸው ሰዎች የተማሩ፣ አዋቂ ከሚባሉ ሥልጣንና ማዕርግ ካላቸው በአስተሳሰብና በአመለካት በልጠው ወይም ተሽለው የሚገኙበት ጊዜ አለ፡፡ ምእመናን ከዲያቆናት፣ ዲያቆናት ከቀሳውስት፣ቀሳውስት ከጳጳሳት፣ ጳጳሳት ከሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃነ ጳጳሳት ከፓትርያርኩ የተሻለ አስተሳሰብና አመለካከት ይዘው ስለሚገኙ በማዕርግ የሚበልጧቸውን መካሪና አስተማሪ እንዲሁም ቀስቃሽና ተግሳፅ የሚሰጡ ሆነው የሚገኙበት አጋጣሚ አለ፡፡ በተለይ በአሁኑ ወቅት ምእመናን ሥርዓት ተጣሰብን ቀኖና ፈረሰብን በማለት በክብርና በማዕርግ የሚበልጧቸውን በልዩ ልዩ አጋጣሚዎች በመቀስቀስና በማንቃት “ስንጠፋ አይገዳችሁምን?” በማለት ላይ ናቸው “ጆሮ ዳባ ልበስ” ብለው ከተኙት በቀር፡፡“አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም” እንዲሉ ሆን ብለው ሥርዓት በመጣስ ቀኖና በማፍረስ ላይ የተሰማሩት ግን የምእመናን ጩኸት “የዝኆን ጆሮ ስጠኝ” ብለው ላይነቁ እሰከወዲኛው ያንቀላፉ ሆነዋል፡፡ ለቅዱስ ጴጥሮስ የተሰጠውን የነባብያን በጎች እረኝነት መቀበላቸውን ዘንግተው /ዮሐ21፥16-17/ ሊጠብቋቸው አደራ በተረከቧቸው በጎች የማንቂያ ቅስቀሳ ሲደርሳቸው ዞር ብለው የሆነውን ነገር ከማየት ይልቅ “በምድር ያሰራችሁት በሰማይም የታሰረ ነው፡፡” ማቴ 18፥18 የሚለውን ሰማያዊ ሥልጣን ብቻ በመጠቀም ለመገዘት /ለማሰር/ ይፈጥናሉ፡፡መምህራችን ክርስቶስ እንዳስተማረን የምንጓዝ ከሆነ “ስንጠፋ አይገዳችሁምን” የሚለውን የምእመናን ጩኸት ልንሰማና ተገቢውን መልስ ልንሰጥ እንገደዳልን፡፡ከዚያ ውጭ ግን ሥልጣን ማሰሪያ ብቻ ሳይሆን መፍቻም ጭምር መሆኑን ልንረዳው ይገባል፡፡ “መምህር ሆይ መምህር ሆይ ተብለው እንዲጠሩ ይወዳሉ፡፡” ማቴ 23፥7 ተብሎ እንደተጻፈ ስሙን ብቻ የምንፈልግ ከሆነ ግብዝነት ነው፡፡ ገንዘባቸውን ፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ዓለማዊ አውቀታቸውን ለቤተ ክርስቲያን ለማፍሰስ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚጠጉትን የግል ጥቅም የሚቀርብን የሚመስላቸው አንዳንዶች ሊገልጻቸው የማይችል ሥም ይለጥፉባቸዋል፡፡ መቼም እናትም ትሁን አባት የልጃቸውን ቅስቀሳ ካልሰሙ የእናትነትና የአባትነት ክብራቸው በልጆቻቸው ዘንድ መቀነሱ አይቀርም፡፡ ተቀስቃሽ ላለመሆን አለማንቀላፋት፤ ካንቀላፋን ግን ተቀስቃሽ መሆንን መጥላት የለብንም፡፡ ክርስቶስ ኢየሱስ በፍጡር ከተቀሰቀሰ እኛ ደግሞ በወንድሞቻችን፣ በእህቶቻችን፣ በልጆቻችን ቅስቀሳ  መንቃት የማንፈልግ ከክርስቶስ በልጠን ነውን? የምእመኑ ጥያቄ “ስንጠፋ አይገዳችሁምን?” የሚል ነው፡፡ ምክንያቱም በአንዳንድ የግል ጥቅም ፈላጊዎች በተፈጠረ ማዕበል የሚናወጠው ምእመን ቁጥሩ እየጨመረ ነውና፡፡ ምእመኑ ሲጠፋ የማይገደው እረኛ ደግሞ “የቀስቃሽ ተቀስቃሽ” የሆነ በእንቅልፍ የተጠቃ ያለቦታው የተቀመጠ ግዴለሽ ነው፡፡ መቼም ቢሆን በልጅነት ፍቅር የምንለምነው አርአያችን የሆነውን መምህር ክርስቶስን እንድንከተል ነው፡፡ መቀስቀስ ስንችል ተቀስቃሽ ልንሆን አይገባም፤ ይልቁንም “እንዲህ የምትፈሩ ስለምን ነው? እንዲህ  የምታለቅሱት ስለምን ነው? በማለት አለንላችሁ ብለን ልናጽናና የአባትነት አደራ ሐይማኖታዊ ግዴታ አለብን፡፡ ይህን በሚገባ ለመወጣት የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ዓይነ ልቡናችንን ያብራልን፡፡ አሜን፡፡

Wednesday, August 20, 2014

አምላካችን ስንት ነው?


የሰው ልጅ በጥበብ ቢራቀቅም በፍልስፍና ቢበለጽግም እንኳ ከእርሱ የበለጠ ኃይል አለበት:: ያን አንድ ኃይል ያስገኘው አካል የለም:: ይህን የሁሉ አስገኝ ፈጣሬ ኩሉ ዓለማት አምላክ እንለዋለን:: ማንኛውም ሰው እርሱን የፈጠረ አምላክ እንዳለው ያምናል:: አምላክ መኖሩን የሚያምን ሰው አምላኬ የሚለው ነገር ከእርሱ የበለጠ መሆን አለበት:: አምላኬ ብሎ የሚያምነው ነገር የሚሸነፍ መሆን የለበትም ወይም አምላክ ከሚባለው ነገር የበለጠ ሌላ ነገር ሊኖር አይገባውም:: ለምሳሌ፡-
- ሰው ዛፍን  የማምለክ ነጻ ፈቃድ አለው:: ነገር ግን ያ አምላክ የተባለውን ዛፍ ሰው ራሱ ይቆርጠዋል:: ሰው በፈለገው ቅርጽ ያደርገዋል፡፡ ይጠርበዋል ይፈልጠዋል፡፡ ይህ ማለት አምላክ የተባለው ዛፍ አምላኬ ብለው ከሚጠሩት ሰዎች እጅግ ያነሰ ነው ማለት ነው:: በመሆኑም ዛፍ አምላክ ሊሆን አይችልም::
-
ፀሐይ ለዓለም ሁሉ ታበራለች ሙቀትም ትሰጣለች፡፡ብርሃኗም እንደፈለግን እንወጣለን እንገባለን:: ዕፅዋት ምግባቸውን የሚሰሩት በፀሐይ ብርሃን ነው፡፡ ለመኖር ፀሐይ የግድ ታስፈልገናለች፡፡ በዚህም የተነሳ ከሰው ልጅ የበለጠች አድርገን ቆጥረን አምላኬ ልንላት እንችላለን:: ነገር ግን የሚጎድላት ነገር አለ:: ጨለማ ያሸንፋታል ተራራ ይከልላታል፣ ዛፍ ይጋርዳታል:: ስለዚህ ፀሐይ አምላክ ልትሆን የማትችልበት ጉድለት አለባት ማለት ነው:: ስለዚህ  ፀሐይ አምላክ አይደለችም::
-
ውኃ ሲታጠቡበት ያጠራል ሲጠጡት ያረካል ዕጽዋትን ያለመልማል:: ለሰውም ለሌላውም ፍጡር ውኃ ለመኖር መሠረት ነው:: ውኃ ከሌለ በሕይወት መኖር ስለማይቻል ውኃ አምላክ ነው ልንል እንችላለን:: ነገር ግን ውኃ በሰው ይገደባል፣በእንስራ ይቀዳልሰው በሚፈልገው አቅጣጫ ይመረዋል:: ስለዚህ ሕፀፅ አለበት ማለት ነው:: ይህን ሕፀፅ የያዘ ደግሞ አምላክ ሊሆን የሚችልበት ነገር የለም::  በመሆኑም ውኃ አምላክ አይደለም፡፡
-
ጨረቃ በሌሊት ብርሃን ትሰጣለች ጨለማን የማሸነፍ ብቃት አላት:: በዚህም አምላክ ልናደርጋት እንችላለን ነገር ግን ከእርሷ የበለጠ ብርሃን አስገኝ አካል አለ:: ጨረቃ በጨለማ ከምትሸነፈው ፀሐይ እንኳ ታንሳለች:: የጨረቃ ብርሃን ከራሷ የሚወጣ ሳይሆን ከፀሐይ የተገኘ ነው:: ስለሆነም ጨረቃ በፀሐይ ትበለጣለች፡፡ ስለዚህ አምላክ ልትሆን አትችልም ማለት ነው::
-
ነቢያት ትንቢት ይናገራሉ፣የሚመጣውን ነገር ያውቃሉ፣ሙት ያነሣሉ፣ድውይ ይፈውሳሉፀሐይን ያቆማሉ፣ሰማይን ይለጉማሉ:: ስለዚህ ከነቢያት መካከል አንዱን አምላኬ ልንለው እንችላለን:: ነገር ግን ነቢያት በፀጋ ያገኙት እንጅ በባሕርያቸው ያለ አይደለም:: ለዚህም ነው ትንቢት የሚነፈጉበት፣ ተአምራት የሚከለከሉበት ጊዜነበረው:: ከዚህ የምንረዳው ከነቢያትም የሚበልጥ ነገር መኖሩን ነው:: ስለዚህ አምላክ አይደሉም ማለት ነው::
-ጻድቃን ሰማዕታት ብዙ ተአምራትን ያደርጋሉ፣በመከራ ይጸናሉ፣  በሕይወታቸውም ምሥክር ይሆናሉ፣ መራራ ሞትንም ይታገሳሉ:: ከእነዚህ መካከል አንዱን አምላኬ ብንል መብታችን ነው:: ነገር ግን ከእነርሱ የበለጠ በመከራ እንዲጸኑ፣ተአምራትን እንዲያደርጉ የሚያበረታቸው አካል አለ:: በመሆኑም አምላካችን ፈጣሪያችን አንላቸውም፡፡ እስከ አሁን ድረስ የጠቀስናቸው ሁሉ የራሳቸው የሆነ ከሌሎች የሚበልጡበት ነገር አላቸው:: ነገር ግን የራሳቸው የሆነ ጉድለትም ስላለባቸው አምላክ ብለን አናመልካቸውም:: ሁሉም የሚጎድላቸው ነገር አላቸው ከእነርሱ የበለጠ እነርሱን የሚያሸንፍ ኃይልም አለባቸው:: ኅልፈት ውላጤ ያገኛቸዋል:: ስለህም እነርሱን ያስገኘ ሌላ አካል ለመኖሩ እነዚህ ማረጋገጫዎቻችን ናቸው:: በመሆኑም እንደሰው ሰውኛው የምናወጣውን አምላክ የመሆንን መስፈርት አያሟሉም ማለት ነው::
እኛ አምላክ ብለን የምናመልከው:-
v  አስገኝ የሌለው፣
v  ማንም ማን ሊተካከለው የማይችል፣
v  ዓለምን ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣ፣
v  ሁሉን የሚመግብ፣
v  የሚያሸንፈው የሌለ፣
v  እርሱን የሚገድበው የሌለ፣
v  ከእርሱ የሚበልጥ የሌለበት፣
v  ሰማይን የዘረጋ ምድርን በውኃ ላይ ያጸና፣
v  ጊዜ የማይለውጠው ዘመን የማይሽረው፣
v  ዓለምን አሳልፎ የሚኖር ዘላለማዊ፣
v  የሚመጣውን የሚያውቅ፣
v  ሁሉን በፈቃዱ የሚያደርግ፣
v  ድካም የሌለበት፣
v  እንቅልፍ የማያሸንፈው፣
v  አማክሩኝ የማይል፣
v  ሌላ አጋዥ የማይሻ፣
v  ዘመናትን በዘመናት ጊዜያትን በጊዜያት የሚተካ፣
v  ሁሉን የሚገዛ፣
v  ሁሉን የሚያስተደድር፣
v  በሥራው የማይፀፀት፣
v  የማይዳሰስ፣ የማይጨበጥ ረቂቅ፣
v  በሁሉ ቦታ ያለ /ምሉዕ በኩለሄ የሆነ/፣
v  ከእርሱ ውጭ አንድ ነገር እንኳ የማይደረግ፣
v  እውነተኛ ፈራጅ፣
v  ውሸት የሌለበት፣
v  ንፁሕ፣ ኃጢአት የማይስማማው፣
v  በማንም የማይመራ
v  ሁሉ በእርሱ የሆነ፣
v  ተመርምሮ ሊደረስበት የማይችል፣
v  ከአእምሮ በላይ የሆነ ነው::

እኛአምላካችን ብለን የምናመልከው ከላይ የተዘረዘሩትን በሙሉ የሚያሟላ ከሆነ ብቻ ነው:: ይህን አምላክ እግዚአብሔር እንለዋለን፡፡ አምላክ ዓለምን የሚያስተዳድር ነው:: ዓለምን ሲገዛ ደግሞ የሚያግዘው አይሻም:: መለኮት በጋርዮሽ ሥርዓት አይመራም:: አምላክ ልዩነት ያለባቸውን ተቃራኒ የሆኑ መለኮታዊ ሥራዎችን አይሠራም:: ዓለምን የሚሠራ አንድ አምላክ ዓለምን የሚያፈርስ ሌላ አምላክ የለም:: ግማሹን ዓለም አንዱ ግማሹን ሌላ አምላክ አይመራም ሁሉንም አንድ አምላክ ይገዛዋል እንጅ:: አምላክነት ዕገዛን አይሻም ሁለት ተቃራኒ ሃሳቦችም የሉበትም:: አንዱ ወደ ግራ ሌላው ወደ ቀኝ የሚሉ የተለያዩ አመለካከቶች ጥምርታም አይደለም:: የተለያዩ የእምነት ድርጅቶች መነሻቸው ምሥጢረ ሥጋዌ ነው:: አምላክ በሥጋ ማርያም በተገለጠ  ጊዜ ዓለም የራሷን ሥም እየሰጠች አዳዲስ እምነቶችን መፈልፈል ጀመረች:: ከነቢያት መካከል አንዱ ነው ያሉት የራሳቸውን እምነት አንድ አሉ:: ከድንግል የተወለደው አምላክ አይደለም ዕሩቅ ብእሲ ነው ያሉት ሌላ እምነት መሠረቱ:: ይህ ከድንግል የተወለደው ከአምላክ ጋር የሚያስታርቀን አማላጅ እንጅ አምላክ አይደለም ያሉት ሌላ እምነትን ፈጠሩ:: በቅርብ ጊዜ የተመሠረቱት እምነቶች ሁሉ መነሻቸው ምሥጢረ ሥጋዌን በሚገባ ካለመረዳት የመጣ ነው:: በሰው አእምሮ መርምረው ለመድረስ ሞክረው መድረስ ያልቻሉ ሰዎች ሁሉ የራሳቸውን እምነት መሥርተዋል:: የተዋሕዶ እምነት ግን መሠረቱ ወልድ ዋሕድ እግዚአብሔር በተዋሕዶ ከበረየ ሚል ነው:: መሥራቹ ደግሞ ራሱ ባሕርይው ረቂቅ የሆነው አምላካችን ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፡፡ በዚህ እምነት ውስጥ አምላካችን አንድ ብቻ ነው ብለን እናምናለን:: ሌሎች እምነቶች ግን በግልጽ አይናገሩ እንጅ ከአንድ በላይ የሆኑ አማልእክትን ያመልካሉ:: እንደ እነርሱ እየመሰላቸው ቅዱሳን ያማልዳሉ ስንል ቅዱሳንን አምላካችን ናቸው አሉ ይሉናል:: ድንግል ማርያምን ወላዲተ አምላክ የዓለም ሁሉ አማላጅ ናት ስንል አምላካቸው ድንግል ማርያም ናት ይሉናል:: እኛ የተዋሕዶ አማኞች አንድነቱ ሦስትነቱን በማይጠቀልለው ሦስትነቱም አንድነቱን በማይከፋፍለው አምላክ ብቻ እናመልካለን:: አምላካችን እግዚአብሔር አንድ ሲሆን ሦስትሦስት ሲሆንም አንድ ነው:: አንድነቱ በመለኮት፣ በአገዛዝ፣ በሥልጣን፣ በባሕርይ፣ በህልውና ወዘተ ነው:: ሦስትነቱም በሥም፣ በአካል፣ በግብር ነው:: የሥም ሦስትነት አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ መባል ነው:: አንዱ በሌላው ሥም አይጠራም:: የግብር ሦስትነት አብ ወላዲ፣ አስራፂ፤ ወልድ ተወላዲ፤ መንፈስ ቅዱስ ሰራፂ ይባላል:: አብ ቢወልድ ቢያሰርጽ እንጅ አይወለድም አይሰርጽምም፤ወልድ ቢወለድ እንጅ አይወልድም፣ አያሰርጽም፣ አይሰርጽምም፤ መንፈስ ቅዱስ ቢሰርጽ እንጅ አይወልድም፣ አይወለድም፣ አያሰርጽምም፡፡ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስቅዱስ ለየራሳቸው ፍጹም ገጽ ፍጹም  አካል አላቸው:: እግዚአብሔር እንዲህ ባለ አንድነትና ሦስትነት ጸንቶ ይኖራል:: አንዱ ወልድ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ሲወለድ ከላይ ከአምላክነቱ (ከአንድነቱና ከሦስትነቱ) አልጎደለም አልጨመረምም:: በታችም በአንድነቱና በሦስትነቱ ላይ አልተጨመረም አልተቀነሰም:: እግዚአብሔር ወልድ ከድንግል ማርያም መወለዱ ከአምላክነት ዝቅ አላደረገውም:: አምላክ ሰው ሆነ ሰው አምላክ ሆነ ብለን እናምናለን:: የጠፋ በግ አዳምን ሊፈልግ የመጣው ወልድ ከራሱ ጋር አስታረቀን:: ደሙን አፍስሶ ሥጋውን ቆርሶ በዘመነ ሥጋዌው ሰውን ከራሱ ጋር አስታረቀ:: ከዘመነ ሥጋዌው በኋላ አሁን ግን አማላጅ አንለውም ምክንያቱም ማማለድና አምላክነት የተለያዩ ናቸውና፡፡ ሁለት የማይገናኙና የማይተዋወቁ ነገሮችን ሦስተኛ አካል በመካከላቸው ገብቶ ቢያገናኛቸው ወይም ቢያስተዋውቃቸው ምልጃ ነው:: እኛ በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም የማንችል በመሆኑ ቅዱሳን ስለእኛ ከእግዚአብሔር ዘንድ ቢለምኑልን ምልጃ ነው:: ከዚህ እንደምንረዳው ምልጃ የፍጡር ሥራ ነው:: በፍጡራን መካከል ደግሞ እኩል የሆነ ቅድስና የለም:: ስለዚህ በቅድስና የሚበልጠው ለሌሎች ይማልዳል:: ሙሴ ለሕዝበ እስራኤል ይማልድ የነበረው ቅዱስ ስለነበረ ነው:: አምላካችን አንድ እንደሆነ አይተናል በሥም ሦስት መሆኑንም እንዲሁ:: ከሥስቱ አካል አንዱን አካል ወልድ አማላጅ ነው የሚሉ እምነቶች አሉ:: እነዚህ እምነቶች ኢየሱስ በሥጋ ማርያም ለምን እንደተገለጠ ያልተረዱ ናቸው:: ምልጃ የፍጡር ሥራ ነው ብለናል ስለዚህ ኢየሱስ ፍጡር ነውን? ይቅር ይበለን:: እርሱስ የባሕርይ አምላክ ነው:: አምላካችን ደግሞ አንድ ነው:: ማማለድ እና አምላክነት የተለያዩ ነገሮች ናቸው:: ምልጃ የሚቀርበው እኮ ለሚበልጥ አካል ነው:: ኢየሱስ ይማልዳል ማለት ከኢየሱስ የሚበልጥ ሌላ አካል አለ ማለት ነው:: ከአምላክ የሚበልጥ ነገር ካለ ደግሞ አምላክ ሊሆን የሚችለው ያ የበለጠው ነገር ነው:: ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ አንዳንዶች እንደሚሉት አማላጅ ሳይሆን የባሕርይ አምላክ ነው:: አምላክን አማላጅ ማለት ነጭን ጥቁር፣ ወፍራምን ቀጭን እንደ ማለት ነው:: ስለዚህ አምላካችን አንድ ነው እርሱም እግዚአብሔር ነው፡፡