Thursday, October 30, 2014

‹‹ስትሆን አለመሆን››

ሰላም ለሁላችሁ ይሁን፡፡ አንድ ጓደኛዬ ያጫወተኝን ጨዋታ ላካፍላችሁ ሳስብ ርእሱን ምን እንደምለው በጣም ብዙ ጊዜያትን ወስጄ ነበር፡፡ አሁን ከብዙ ድካም በኋላ ከላይ ያለውን ርእስ ሰጠሁት ፡፡ ርእሱ ምን ያህል ደረጃ እንዳለው ባላውቅም ‹‹ስትሆን አለመሆን›› በሚል ሰይሜዋለሁ፡፡ ወሬ አበዛሁባችሁ መሰለኝ… “አዎ አብዝተሃል” ይለኝ ነበር አንድ ወጣት እንዲህ የሚል ነገር ሳነሣበት፡፡ ነገር ስዘበዝብበት አይወድም ወይ ጉዴ በነገር ላይ ሌላ ነገር ደረብኩባችሁ በእርግጥ ርእሱም ‹‹ስትሆን አለመሆን›› ስለሚል መድረኩ ሲመቻችልኝ እንደ መድረኩ ሆኜ አልተገኘሁም፡፡ ነገሩ ከጓደኛዬ የተገኘ ነው፡፡ ጓደኛዬ በስእለት ይሁን በሹመት በወሬም ይሁን በሆነ አጋጣሚ ብቻ ‹‹ስልጣን›› ነገር አለችው፡፡ ብዙ ጊዜውን የሚያሳልፈው ተሸከርካሪ ወንበር ላይ ነው፡፡ ስልኩም አይቆጥርበትም መሰል የቢሮው ስልክ እንደ ሴቶች የጆሮ ጌጥ ከጆሮው ላይ ተጣብቆ ይውላል፡፡ ባለጉዳይ የሚያስተናግደው መስማት እንደተሣናቸው ወገኖቻችን በምልክት ብቻ ነው፡፡ አንድ ባለጉዳይ ባለፈው ትዝ አለኝ “ስልኩን ይጨርሳል ብዬ ወንበር ላይ ተቀምጬ ብጠብቀው! ብጠብቀው! አንዱን ሲጨርስ ሌላውን ሌላ ሲጨርስ ደግሞ ሌላውን እያለ እኔም ሲመሽብኝ ተስፋ ቆርጬ ከቢሮ ወጣሁና ጉዳዬን ስልክ ደውዬ አናገርኩት” ሲለኝ እንባ እስኪወጣኝ ድረስ ነው የሳቅሁት፡፡ በእርግጥ ጓደኛዬ ነው… ቢሆንም ግን በሰው ልጅ ላይ የሚፈጸም ታሪክ በመሆኑ ብዙም አልገረመኝም፡፡ እንዲህ አይነት ነገር በጣም ያበሳጨው የነበረ ሰው ሲበሳጭበት በነበረው ነገር ውስጥ ሲገባ በጣም ያሳዝናል፡፡ አንድ ቀን የዓመት ፈቃዱን ሊጠይቅ ወደ ቢሮ ጎራ ይላል፡፡ ከቢሮ ሲገባ ጉዳይ ያለው ሰው አልነበረም፡፡ ጉሮሮውን ሞረደና “የዓመት ፈቃድ ፈልጌ ነበር” አላቸው፡፡ አንዲት የማይመለከታት ሰራተኛ “አንተ ደግሞ ሰራተኛ ሆነህ ሞተህ የዓመት ፈቃድ ትጠይቃለህ?” አለችው፡፡ “ምን ለማለት ፈልገሽ ነው? እኔ ሠራተኛ አይደለሁም ማለት ነው? የምትሰሪልኝ ከሆነ በሥርዓት አስተናግጅኝ” በማለት ጮኸባት፡፡ ከዚያ ዚያ እየተንጎራደደች “በእርግጥ የዓመት ፈቃድ የምጽፍ እኔ አይደለሁም፡፡ እርሱ እስኪመጣ መጠበቅ ከፈለግህ ተቀምጠህ ጠብቀው አለችው፡፡” እርሱም በጣም ተናድዶ ወንበሩን ሳበና ተቀመጠ፡፡ ቢጠብቀው ቢጠብቀው በፍጹም ሊመጣለት አልቻለም፡፡ ልክ 11፡20 ሲሆን በጣም ተበሳጨና “ስልኩን ስጡኝ” አላቸው፡፡ አንዲት ስልኩን ሰጠችው ስልክ ሞከረለት፡፡ ስልኩ “ጥሪ አይቀበልም” ይላል፡፡ ከቅድሙ የባሰ አሁን ቅጥል እስኪል ድረስ ተናደደ፡፡ የቢሮውን በር በርግዶት ወጣ፡፡ ፊቱ በርበሬ መስሏል፤ ግንባሩ ተቋጥሯል፡፡ “ምን ሆነህ ነው?” አልኩት፡፡ “እባክህ የቢሯቸው ቢሮክራሲ በጣም ያናድዳል፡፡ እነዚህ ሰዎች ግን ድንጋዮች ናቸው ወይስ አስተናጋጅ ናቸው፡፡ የሰውን ጉዳይ ከምንም አይቆጥሩም እኮ፡፡ ይገርምሃል አንዲት ሰራተኛ ተብዬ በማያገባት ነገር ገብታ አንተ ደግሞ ሰራተኛ ሆነህ ሞተህ የዓመት ፈቃድ ስትል አታፍርም አለችኝ እኮ! ይች ደደብ ባልሠራላት እኔ አይደለሁም” አለኝ፡፡ “አይዞህ!!! ግን የሰውን ልጅ ያህል ፍጡር ደደብ ብለህ በመሳደብህ ቅር ብሎኛል፡፡ በእርግጥ የሰው ልጅ ወደኋላ ዞር ብሎ ያለፈ ተጋሪኩን ስለማያስታውስ ያናድድ ይሆናል፡፡ ግን ምንም ማድረግ አይቻልም ዘመኑ ነው እያልክ መቀመጥ ነው” አልኩት፡፡ “እንዴ ተው እንጅ ምን ዓይነት ጅልነት ነው የምታወራው? ዘመኑ ነው እያልክ እስከመቼ ድረስ ዝም ብለህ ትቀመጣለህ? እንደዚህ ዓይነቱን ሰው እኮ መንጥረን ማውጣት አለብን፡፡ ዘመኑ ድሮም ዘመን ነበር አሁንም ዘመን ነው እኛ ሰዎች ግን በየጊዜው እንደ እስስት እንለዋወጣለን፡፡ ብቻ ተወው የእኛ ጉድ እንዲህ በቀላሉ የሚነገር አይደለም” ብሎ በረዥሙ ተነፈሰ፡፡ “ይህ እኮ የሚያናድድ ነገር አይደለም፡፡ የሰው ልጅ እኮ ማግኘት የተመኘውን ነገር ሲያገኝ እንደ ድሮው አይሆንም አንተም ነገ ይህን ወንበር ብታገኘው ብትብስ እንጅ አትሻልም አልኩት፡፡ ድሮ ላይ የነገርኩት ነገር ዛሬ ላይ ሲፈጸም እኔ እንደ ነቢይ ትንቢት ተናጋሪ ሆኜ ራሴን አገኘሁት፡፡ ያ ድሮ ላይ ሲለው የነበረውን ነገር ዛሬ ራሱ ላይ ሲደገም በጣም ገረመኝ፡፡ ሰዎች ስለእርሱ ብዙ ነገር ሲሉኝ አንድ ቀን ስልክ ደወልኩለትና ተቀጣጠርን፡፡ በቀጠሯችን ተገናኘንና ከነገር ነገር ያን የድሯችንን ነገር ስናነሣ ስንጥል ብዙ ሰዓታትን አሳለፍን፡፡ እየተሳሳቅን “አንተስ ያው ሆነሃል አላሉ” አልኩት፡፡ “ተወው እባክህ?” አለኝ፡፡ “ግን ለምንድን ነው የሰው ልጅ ድሮ ሲበሳጭበት በነበረው ነገር ውስጥ ራሱ የሚወድቅ? አልኩት፡፡ እርሱም ብዙ ሳያስብ በሳቅ ፍርስ የሚያደርገውን ንግግር ነገረኛ!፡፡ “ምን መሰለህ የሰው ልጅ ድሮ በተጎዳበት ነገር ይጎዳበታል እንጅ አይጠቅምበትም፤ ሰው ድሮ በተበሳጨበት ነገር ያበሳጭበታል እንጅ አያስደስትበትም፤ ሰው ድሮ በታሰረበት ነገር ያስርበታል እንጅ አይፈታበትም፡፡ ድሮ ላይ እኔ እበሳጭ የነበረው እኮ እነርሱ ቦታ ላይ እኔ ስላልሆንኩ ነው፡፡ ዛሬ ግን እኔ በእነርሱ ቦታ ላይ ስላለው በራሴ ስለማልበሳጭ ሌሎች በእኔ መበሳጨት አለመበሳጨታቸው አይገባኝም፡፡ እኔ ጥሩ የሰራሁ እንጅ መጥፎ ነገር ያደረግሁ አይመስለኝም፡፡ ጠቅለል ሲል ‹‹ስትሆን አትሆንም›› ማለቴ ለመሆን የተመኘኸውን ነገር ስትሆን ድሮ እንደተመኘኸው አትሆንም፡፡ በእጅ የያዙት ወርቅ ከመዳብ ይቆጠራል ይሉ የለም፡፡ ተማሪ ሆነህ ሰራተኞችን ስታይ እንደእነርሱ መሆንን ትሻለህ፡፡ ነገር ግን አንተ ያንን የተመኘኸውን ስትሆን አትሰራበትም፡፡ ስንቱ ሰዎችን ሲኮንን በነበረበት ሃሳብ ገብቶ አይደል እንዴ ራሱ የሚሠራው፡፡ ሙስና የሚፈጽም ሰራተኛ ያየ ሰው ለምን ሙስና ይፈጽማል ብሎ ይደነፋል፡፡ ነገ በዚያ ሰው ቦታ ሲቀመጥ ግን የበለጠ ሙስና ሰሪ ራሱ ይሆናል፡፡ መሆን እና መናገር እኮ የሰማይ እና የምድርን ያህል ይራራቃሉ፡፡ ሰው የተባለ ፍጡር በአጠቃላይ “ሲሆን አይሆንም” --› ታማኝ አይሆንም ማለቴ ነው፡፡ የሚፈልገውን ነገር ሲያገኝ እንደሞፈልገው ሆኖ አይገኝም” አለኝ፡፡ እኔም በጣም ገረመኝና በሳቅ ተለያየን፡፡

Tuesday, October 7, 2014

ንቁም በበሕላዌነ / በያለንበት ጸንተን እንቁም/

ማተባችን መለያ ማኅተማችን ነው፡፡
በሥነ ፍጥረት ታሪክ ላይ የመጀመሪያዎቹ ፍጥረታት ላይ ማለትም በመላእክት ዘንድ የተፈጠረ ሽብር ነበር፡፡ የሽብሩ ቀስቃሽ የዚያን ጊዜ አኃዜ መንጦላእት የነበረው በክብር ስሙ ሳጥናኤል በውርደት ስሙ ደግሞ ዲያብሎስ ነበር፡፡ ዲያብሎስ ቀና ቢል ከእርሱ የበለጠ ፍጡር አጣ ፈጣሪም ተሰውሮበታልና ባለማስተዋል ዝቅ ብሎ ሲመለከት እልፍ አእላፋት መላእክትን ተመለከተ፡፡ ያን ጊዜ “አነ ፈጣሪሆሙ ለእሉ ፍጡራን” ብሎ አረፈው፡፡ ምን ማለት ነው “እነዚህን ሁሉ የፈጠርኳቸው እኔ ነኝ” አለ፡፡ ልብ በሉ ወገኖቼ በማእረግ ከሌሎች መብለጥ ወይም ከሌላው በስልጣን ከፍ ብሎ መገኘት ማለት መፍጠር ማለት አይደለም፡፡ ምናልባት ከአንተ በላይ ሌላ የሚበልጥህ ነገር ላይኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን ከአንተ በታች ያለውን ሁሉ የፈጠርከው አንተ አይደለህም፡፡ የሳጥናኤል ጉዳይ ግን ይህ ነበር፡፡ ከእርሱ በታች እልፍ አእላፋት መላእክት ስለተረበረቡ የእነዚያ ሁሉ ፈጣሪ እርሱ እንደሆነ አሰበ አስቦም ተናገረ ተናግሮም አሸበረ፡፡ በዚህ ሽብር መካከል እርሱን ተከትልው የሄዱ ነበሩ፡፡ ነገር ግን እርሱን የተጠራጠሩም ነበሩ፡፡ እርሱን መጠራጠር ብቻም አይደለም አምላክ አይደለም ብለው ያመኑ መላእክት ነበሩ፡፡ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል “ንቁም በበሕላዌነ / በያለንበት ጸንተን እንቁም/” በማለት መላእክትን አጽናናቸው፡፡ ሽብሩን ዲያብሎስ ቢፈጥረውም ቅሉ በቅዱስ ገብርኤል ከሽፎበታል ምንም እንኳ የተወሰኑ ተከታዮችን ይዞ ቢጠፋም፡፡ ወገኖቼ ከመቸውም በላይ በቅዱስ ገብርኤል ቃል የምንጽናናበት ዘመን ዛሬ ነው፡፡ ማንም ምንም ሊል ይችላል፡፡ ከእኔ በላይ ማንም የለም ብሎ የሚያስብ ሰው በርካታ ነገሮችን ሊናገርና ሽብርና ሁከትን ሊፈጥር ይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ለሁሉም ጊዜ አለውና ቅዱስ ገብርኤል በያላችሁበት ጸንታችሁ ቁሙ ማንም አያስፈራችሁ የሚልበትን ሰዓት መጠበቅ አለብን፡፡ አንድ ፈራሽ በስባሽ ሰው ማተብህን አታስርም ስላለኝ ማተቤን አልበጥሰውም ይህን በሚገባ አውቀዋለሁ፡፡ ከእርሱ በላይ ሌላ አካል የሌለ የሚመስለው አእምሮ ቢስ ሁሉንም በእርሱ ቁጥጥር ሥር ማኖር ይፈልጋል፡፡ ነገር ግን ከእርሱ የበለጠ አካል ፈጣሪያችን የተሰቀለበትን መስቀል እናስረዋለን፡፡ በዚህም ብዙ ዘመናትን አሳልፈናል ወደፊትም እንዲሁ እናደርጋለን፡፡ የትምህርት ተቋማት ከዚህ ነጻ ናቸው ካሉንም ትምህርቱ እና ሥራው ይቀራል እንጅ ማተቡ መታሰሩ አይቀርም ፡፡ ማተብ ሌላ ጉዳይ ነው ትምህርት ደግሞ ሌላ ነው፡፡ ምንም ሊገናኙ የሚችሉ ጉዳዮች አይደሉም፡፡ ወገኖቼ ማንም ምንም ነገር ስለተናገረ ብቻ አትሸበሩ፡፡ ይህ ሽብር የተጀመረው በመላእክት ዘንድ ነው፡፡ አሁን ደግሞ በእኛ መካከል ተፈጠረ ይሁን እንጅ በያለንበት ጸንተን ልንቆም ያስፈልገናል፡፡ በያሉበት ጸንተው የቆሙት ፈጣሪያቸውን አግኝተውታል፡፡ እኛም እንዲሁ ጸንተን እንቆይ ፈጣሪያችንን እናገኘዋለን፡፡ አትጠራጠሩ ይህን ሃሳባ ያመጣው ሰው እንጦሮጦስ ይወርዳል ምክንያቱም ሃሳቡ ዲያብሎሳዊ ስለሆነ፡፡ በእርግጥ ዘመኑ ዘመናቸው ጊዜው ጊዜያቸው ነው ነገ ደግሞ የሌላ ዘመንና ጊዜ ነው፡፡ ስለዚህ ጸንተን እንቆይ፡፡ አንድ ተራ ሰው በተናገረው ተራ ወሬ ቦታ ሰጥታችሁ አትሸበሩ፡፡

Tuesday, September 23, 2014

ትምህርት በምሳሌያዊ አነጋገር ክፍል ሦስት

በሬ ሆይ…
ሥነ ቃሉ “በሬ ሆይ ሳሩን አየህና ገደሉን ሳታይ” ተብሎ ይሟላል፡፡ በሬ ሣር አብዝቶ የሚመገብ እንስሳ ከመሆኑ የተነሣ ሣሩ የበቀለበት ከገደል መሆኑን ሳያውቅ ለሆዱ ሲል ብቻ ገደል ይገባል፡፡ ከሥነ ቃሉ የምንረዳው በሬ ሕይወቱን የሚያጣው ሳያስተውልና ሳያገናዝብ ገደሉን ሳያይ ሣሩን ብቻ በመመልከቱ ነው፡፡ ይህ ምሳሌያዊ አነጋገር መናፍቃንን ይጠቁማል፡፡ መናፍቃን በገንዘብ ተታልለው ፈጣሪያቸውን ክደው ለጣዖት ሰግደው ባለማስተዋል የሚኖሩ ናቸው፡፡ “መክፈልት ሲሹ መቅሰፍት” እንዲሉ ገደል የተባለ ሲኦልን ሳያዩ ገንዘቡን ብቻ አይተው ሊበሉ ሲጠጉ ባልገመቱት የሲኦል ገደል ይወድቃሉ፡፡ በሬ ሣርን ብቻ እንዳየ እነርሱም ገንዘብን ብቻ ይመለከታሉና በዘላለም እሳት ለመቃጠል የሞት ሞት ይፈረድባቸዋል፡፡ በአጠቃላይ ይህ ምሳሌያዊ አነጋገር ለምንሠራት ለእያንዳንዲቱ ተግባር በማስተዋልና በመገንዘብ ልንንቀሳቀስ እናደሚገባ የሚገልጽ ነው፡፡ ክርስቲያን የሆነ ሁሉ ከመሥራቱ በፊት ሥርዓትን ሊገነዘብ ግዴታ አለበት ሰማይ ሰማይ እያየ የሚሄድ የሚረግጠውን እንደማያስተውል የሚበላውን ፣ የሚጠጣውን ፣ ገንዘብን እየተመለከተ የሚሄድም የሚገባበትን አያስተውልምና ለከፋ አደጋ ይጋለጣል፡፡ ስለዚህ በምኞት ጎምጅተን የምንገባበትን ሳናስተውል ልንንቀሳቀስ አይገባም፡፡
ድመት መንኩሳ… 
ድመት የቤት እንስሳ ከሚባሉት ውስጥ አንዷ መሆኗ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ይህ ምሳሌያዊ አነጋገር የሚነገረው ድመት የምትመነኩስ ሆና ሳይሆን በግብር የሚመስሏትን ለመጠቆም ነው፡፡ ድመትን ምንም ያህል ጊዜ ቢያሠለጥኗት፣ ንጹህ ውኃ ቢያቀርቡላት ፣ ፊቷን በምራቅ ማበሷን ፣ አይጥ በሰው ፊት መብላቷን ወዘተ… አትተውምና “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ” ይባላል፡፡ ከሰው ልጅ ሕይወት ጋር ስናያይዘው ከኃጢአት ተመልሰው ንስሓ ገብተው ሥጋና ደሙን ተቀብለው ሳለ የቀደመ አመላቸውን /ግብራቸውን/ ባለመርሳት ሲፈጽሙ የሚገኙ አሉ፡፡ ለምሳሌ፡- ቤተሰብ ሲበጠብጥ የነበረን ልጅ ተማሪ ብታደርጉት ተማሪዎችን፤ ዲያቆን ሆኖ ቢሾም ቀዳስያንን መበጥበጥ ይጀምራል፡፡  ከዚህም ወደ በለጠ ማዕርግ ቢደርስ ያን የቀደመ ግብሩን የሚተው ስላልሆነ “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ” ይባልበታል፡፡ በወጣትነቱ በዘማዊነት የሚታወቅ ሰው ዕድሜው ገፍቶ አርጅቶ ዓይኑ ፈዞ ሳለም ያንኑ የቀደመ ግብሩን የሚፈጽም ከሆነ ዕድሜው ዋጋ አጥቷልና “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ” የሚለውን ምሳሌያዊ አነጋገር ይጠቅሱለታል፡፡ እንግዳ ባለመቀበል የሚታወቅ ሰው ሕግጋቱን እጠብቃለሁ ብሎ ለምንኩስና ማዕርግ በቅቶ ሳለ እንደቀድሞው እንግዳ ሲያይ ዓይኑ የሚቀላ ከሆነ ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ የሚለው ምሳሌያዊ አነጋገር ይለጠፍበታል፡፡
በአጠቃላይ አንድ ሰው ለውጥ ማምጣት ባለበት ደረጃ ምንም ለውጥ ማምጣት የማይችል፣ የማይመከር፣ የማይመለስ ወዘተ ከሆነ ዕድሜው፣ ማዕርጉ፣ ሥልጣኑ ወዘተ… ሊያስተምረው የማይችል ስለሆነ “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ” ተብሎ ይነገርበታል፡፡ ስለዚህ ባለንበት ማዕርግ፣ዕድሜ፣ ሥልጣን ደረጃ ልንሠራ የሚገባን ትተን ለደረጃችን የማይመጥን ሥራ በመሥራት በረከሰ ቦታ ልንገኝ አይገባም፡፡ ዳግም ላንፈጽመው በንስሓ ከተመለስን በኋላ ወደ ቀደመው ኃጢአታችን ልንመለስ እንዲሁም አላስፈላጊ የሆነን ነገር ለውጥ ባለማምጣት ይዘን ልንገኝ ተገቢ አይደለም፡፡
ዓሣ ጎርጓሪ… 
ይህን ምሳሌያዊ አነጋገር ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጋር አያይዘን እንመልከተው፡፡ የለመድነውን፣ የምናውቀውን መልካም ነገር በጥልቀት ስንመረምር ያልለመድነው፣ የማናውቀው ክፉ ነገር የሚያጋጥመን ከሆነ “ዓሣ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል” በሚለው ምሳሌያዊ አነጋገር ይገስጹናል፡፡ ለምሳሌ፡-መጽሐፍ ቅዱስን ለመልካም ብለን አላዋቂ በሆነ አእምሯችን በማንበብ ላይ ሳለን በምናገኛቸው ጥሬ ቃላት ተደናገረን ፣ በራሳችን አስተሳሰብ ተርጉመን እግዚአብሔርን እስከ መካድ በደረሰ ኑፋቄ ልንወድቅ እንችላለን፡፡ ብዙዎች ለምንፍቅና ሕይወት የተጋለጡት መርዝ የሌለበትን የለመዱትን ዓሣ ሊያወጡ ሲጎረጉሩ መርዝ ያለበት ዘንዶ እየወጣባቸው ነው፡፡ የሚያውቁትን ዓሣ ጎርጉረው አውጥተው ለመብላት ሲጥሩ የማያውቁት ዘንዶ ወጥቶ ይበላቸዋል፡፡ “መጽሐፍ ቅዱስ ቃል በጥሬው የብረት ቆሎ ነው” የሚሉት ትርጓሜ ስለሚያስፈልገው ነው፡፡ “ፊደል ይገድላልና መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል” 2ኛቆሮ 3÷6  ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ ከዚህ በፊት የምናውቀውን ፣ የለመድነውን ነገር በጠባብ አእምሯችን በጥልቀት እንመርምር ስንል ክህደት ይመጣብናል፡፡ “ዓሣ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል” የሚለው ምሳሌያዊ አነጋገር ገንዘባችን ይሆናል፡፡ የሥላሴን አንድነት ሦስትነት፣ የቃል ሥጋ መሆንን፣ በጥምቀት ያገኘነውን የሥላሴ ልጅነት፣ የሥጋ ወደሙን ምሥጢር፣ የሙታንን መነሣት በጥልቀት መመርመር በማይችል የሰው አእምሮ እንመርምር ብንል ከጥልቀቱ ከምጥቀቱ የተነሣ የማንደርስበት ስለሚሆን የመጨረሻ ውሳኔያችን ክህደት ይሆናል፡፡ አርዮስ ከመመራመሩ የተነሣ “ወልድን ፍጡር”፣  “ድንግል ማርያምን ወላዲተ ሰብእ” በማለት ክህደቱን ጀመረ፡፡ ሌሎችም ቢሆኑ እንዲሁ ነው ክህደት የመጣባቸው ሳያውቁ ያወቅን እየመሰላቸው፡፡
ስለዚህ በመጽሐፍ የተጻፉትን በግላችን የምናነብ ከሆነ በራሳችን ፍልስፍና ከመተርጎም ይልቅ መንፈስ ቅዱስ የቀደሳቸው አባቶችን ይህ ማለት ምን ማለት ነው? ለምን እንዲህ ሆነ? መቼ ተደረገ? እንዴት ሊሆን ይችላል? ወዘተ… የሚሉ ጥያቄዎችን በሰከነ አስተዋይ አእምሮ ሆነን በመጠየቅ መረዳት ያስፈልጋል፡፡  ከዚያ ውጭ ለበረከት ያልነው ለመርገም ፣ ለጽድቅ ያልነው ለኃጢአት ፣ ለትርፍ ያልነው ለኪሳራ ፣ ለመክፈልት ያልነው ለመቅሰፍት፣ ለእምነት ያልነው ለክህደት ፣ ለመጽናት ያልነው ለመናወጥ ፣ ለዓሣ ያልነው ለዘንዶ ሊሆንብን ስለሚችል ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝንብናል፡፡ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ ስምንት ቁጥር ሠላሳ አራት ላይ የተገለጸው ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ትንቢተ ኢሳይያስን ሲያነብብ በነበረበት ወቅት ተርጓሚ ሳላገኝ እንዴት እረዳዋለሁ በማለቱ ተርጓሚ ተሰጠው፡፡ በአግባቡም ትርጉሙን ከተረዳ በኋላ ለመጠመቅ ወሰነ ተጠመቀም፡፡ ያለ ተርጓሚ እያነበበ ቢሆን ኖሮ ግን የቃሉ ምንነት ስለማይገባው ለመጠመቅ ባልቻለ ነበር፡፡
ነገርን ከሥሩ…
ለውጤታማ ሥራ መነሻ ከታች መጀመር ነው፡፡ ጥሩ ቤት ለመሥራት መጀመሪያ ከታች ከመሠረቱ መጀመር አለብን፡፡ መሠረት የሌለው ነገር ሁሉ ከንቱ ነው፡፡ በትምህርት ዓለም ውስጥ ከማንበብ አስቀድሞ ፊደል መቁጠር መሠራታችን ነው፡፡ ማንበብ መጻፍ የምንችለው ፊደላትን መለየት ከቻልን ብቻ ነው፡፡ በሒሳብ ትምህርት ደግሞ የቁጥሮችን አጻጻፍ ማዎቅ ለመደመር፣ ለመቀነስ፣ ለማባዛትና ለማካፈል መሠረት ነው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በሕጻንነት የለመድነው ማንኛውም ነገር ለወጣትነትና ለሽምግልና ጊዜያችን መሠረት ነው፡፡ ከሕጻንነቱ ጀምሮ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ያደገ በወጣትነትም ጊዜው ቤተ ክርስቲያን ይገኛል፡፡ በሕጻንነቱ ከእናቱ ቦርሳ ሣንቲም በመስረቅ ያደገ በወጣትነቱም የሰውን ንብረት ሲዘርፍ የሚገኝ ይሆናል፡፡ ከመሠረቱ በሥርዓት ያልታነጸ ገና በለጋነቱ ያልተቀጨ ነገር መራራ ፍሬ ስለሚያፈራ አስቀድሞ ከሥሩ መቆጣጠር አስፈላጊ እንደሆነ ለመግለጽ “ነገርን ከሥሩ ውኃን ከጥሩ” የሚለው ምሳሌያዊ አነጋገር ይቀጸላል፡፡ “ታሞ ከመማቀቅቀ አስቀድሞ መጠንቀቅ” እንዲሉ የማይጾም፣ የማይጸልይ፣ የማይሰግድ፣ የሚሰርቅ፣ የሚገድል ትውልድ እንዳይፈጠር በፈለግነው አቅጣጫ መምራት በምንችልበት በሕጻንነት ጊዜ ልጆችን ሥርዓት ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ በእውነት ሁላችንም ልጆቻችንን ቤተ ክርስቲያን ወስደን ዕጣኑ ቢሸታቸው ፣ ቅዳሴው ቢሰማቸው፣ ሥጋና ደሙን ተቀበለው፣ የቅዳሴ ጸበል ጠጥተው አብረውን ወደ ቤታችን ቢመለሱ እኛ የምንጎዳው ነገር ምንድን ነው? በእርግጥ እኛ ላናስቀድስ ፣ ሥጋና ደሙን ላንቀበል እንችል ይሆናል፡፡ ታዲያ ልጆቻችን ማንን ሊመስሉ ነው? እኛን ወይስ ሌላውን? አስቡት እኛን ከመሰሉ ማስቀደስን ሥጋና ደሙን መቀበልን መቼ ልናሳውቃቸው ነው? ወይስ ምን እንደሆነ ሳያውቁት ይኑሩ? ይኼ ምቀኝነት ይመስላል፡፡ እኔ ስለማስቀድስ ልጄም ማስቀደስ የለበትም፣ እኔ ስለማልቆርብ ልጄም መቁረብ የለትም የሚል አስተሳሰብ ለክርስትና ሕይወት አደገኛ ነው፡፡ ምክንያቱም ነገርን ከሥሩ መንከባከብ አስፈላጊ ነውና፡፡ ነገ ልጄ ሰርቆኝ፣ ልጄ ደብድቦኝ ወዘተ… እያልን በየፍርድ ቤቶች ቆመን ከምናነባ ዛሬ ልጆቻችንን በሥርዓት ማሳደግ መንከባከብ ግዴታችን ነው፡፡ ከልጅነት ጀምሮ የሚቆራኝን ጋኔን ከሥሩ ነቅለን ካልጣልንላቸው የሚመጣውን ዕዳ ራሳችን የምንሸከመው ይሆናል፡፡ ማንኛውም ነገር እንክብካቤ የሚፈልገው ራሱን ባልቻለበት በለጋነት ዕድሜው እንጅ በበሰለበት ራሱን በቻለበት ወቅት አይደለም፡፡ ሲሳደብ ያልገሰጻችሁት ሕጻን ሲያድግ ቢደበድባችሁ ማንም አይደነቅም፡፡ ምክንያቱም መጀመሪያ ሲሳደብ ዝም ያልነው ለዚሁ ነዋ! ኃጢአትን ካልተውናት ከሐልዮ ወደ ነቢብ፣ ከነቢብ ወደ ገቢር እንደምታድግ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ኃጢአትን ከመሠረቱ በለጋነቱ እየነቀልን ልንጥለው ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ነው ኃጢአት እያሠራ ወደ ሲኦል የሚያግዝ ዲያብሎስ የኃጢአት ሁሉ ሥር በመሆኑ እናታችን ቅድስት ቤተ ክርስቶስ ሰምራ እግዚአብሔር እንዲምረው የለመነች፡፡ እናታችን ዲያብሎስን ወድዳው መሰላችሁ እንዴ? ነገርን ከሥሩ ውኃን ከጥሩ እንዲሉ የሰው ልጆች ወደ ሲኦል እንዳይወርዱ የኃጢአትን ሥር ለማድረቅ እንጅ፡፡ ዲያብሎስ ምሕረት ካገኘ የሰው ልጆችን ስለማያስት ሁሉም የአዳም ልጆች ገነት ይገባሉ የሚል ቅን አስተሳሰብ ስለነበራት ነው፡፡ ይህ ነው ነገርን ከሥሩ ውኃን ከጥሩ ማለት፡፡
በርካታ አስተማሪ የሆኑ ሥነ ቃሎች እንዳሉ ቢታወቅም ከላይ ያየናቸው ስምንት ሥነ ቃሎችን ለማንሣት ተገድደናል፡፡ እነዚህ የተነሡት ሥነ ቃሎች በውስጣቸው ያለው ትምህርት የተጠቀሰው ብቻ ነው የሚል ግምት የለንም፡፡ አንድ ምሳሌያዊ አነጋገር ከአንድ በላይ ብዙ ትምህርቶች እንደሚይዝ ይታወቃል፡፡ ከመጽሐፉ ርእስ ጋር የሚሔዱትን ትምህርቶች ብቻ ያነሣን በመሆኑ ለአንድ ምሳሌያዊ አነጋገር በርካታ ትርጉም ላንሰጠው ተገድደናል፡፡
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠


ትምህርት በምሳሌያዊ አነጋገር ክፍል ሁለት

ውሻ በቀደደው…   
ሥነ ቃሉ “ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል” ተብሎ ይሟላል፡፡ ውሻ የጌታውን አጥር ከቀደደው በዚያ ጅብ ገብቶ በበረት ያሉ እንስሳትን ይጎዳል፡፡ ጅብ እንስሳቱን ለመጉዳት አጥሩን ጥሶ መግባት ስለማይችል የሚገባበትን ትንሽ ቀዳዳ ይፈልጋልና ትንሽ ቀዳዳ በውሻ ከተከፈተችለት ያችን ቀዳዳ አስፍቶ ለመግባት ስለማይቸገር “ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል” ይባላል፡፡ ሰይጣን እንዲህ ያለ የጅብ ባሕርይ አለው፡፡ ሰይጣን ትንሽ ቀዳዳ ካገኘ ያችን ተጠቅሞ በሰው ልቡና ለማደር አይቸገርም፡፡ ትልቅ መርከብ የመርፌ ቀዳዳ በምታክል ቀዳዳ በሚገባ ውኃ እንዲሰጥም የሰው ልጅም እንዲሁ ነው፡፡ አጥራችንን በሚገባ አጥረን ትንሽ ቀዳዳ ከተውን ያችን የማስፋት ልምድ ያለው ሁሉ ሊያጠቃን ይችላል፡፡ ሁሉንም ትዕዛዛት ጠብቀን አንዷን ከጣስን ስለተጣሰችዋ ትዕዛዝ ይፈረድብናል፡፡ አሥር መስኮቶች ያሉትን ቤት ዘጠኙን ዘግተን አንዷን ብንተዋት በዚያች የገባ ሌባ ቤቱ ውስጥ ያለውን ንብረት በሙሉ ለመዝረፍ እንደማይቸገር ሁሉ ብዙ የጽድቅ ሥራ እየሠራን አንዲት ኃጢአት ብንሠራ ስለዚያች ኃጢአት የጽድቃችን ሥራ ዋጋ ያጣል፡፡ ሠይጣን ምቹ ጊዜና ሁኔታን ካገኘ በልቡናችን አድሮ እግዚአብሔርን ለማስካድ ፣ለጣዖት ለማሰገድና ኃጢአት ለማሠራት ዝግጁ ነው፡፡ ሰይጣን የምንወድደውን ኃጢአት እንደቀዳዳ ተጠቅሞ ወደ ሌሎች ኃጢአቶች አስፋፍቶ ወደ ሲዖል ይጥለናል፡፡ ለምሳሌ ፡- የመጠጥ ሱስ ያለበትን ሰው ከአንድ ወደ ሁለት ፣ ከሁለት ወደ ሦስት ፣ ከዚያም ወደ አራት እንዲህ ትንሿን ካሰፋ በኋላ እስክንሰክር እንድንጠጣ ያደርግና ሰካራም በሚለው ሥም እንድንጠራ ያደርጋል፡፡ ስካርንም አስፍቶ አሳድጎ በዝሙት እንድንወድቅ ያደርገናል፡፡ ተመልከቱ ሰይጣን በዝሙት ለመጣል የተጠቀመው ትንሽ ቀዳዳ አንድ መጠጣትን ነው፡፡ ሰይጣን ከዜሮ ተነስቶ አያጠቃም፤ መነሻ የሚያደርገው ጥቂት ቀዳዳን ይፈልጋል እንጅ፡፡ ስለዚህ ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል ነውና አውቀን በቀደድነው የማናውቀው እንዳይገባ የልቡና አጥራችንን በሚገባ ልናጥር ይገባናል፡፡ 
አባት ያበጀው…
ይህ ምሳሌያዊ አነጋገር ዕብ13÷6 የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሯችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፡፡ የኑሯቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሏቸው” የሚለውን የቅዱስ ጳውሎስ መልእክት ይደግፋል፡፡ ሥነ ቃሉ “አባት ያበጀው ለልጅ ይበጀው” የሚል ነው፡፡ የሥጋም ሆኑ የመንፈስ አባቶቻችን ለእኛ ለልጆቻቸው ያሳዩን በርካታ መንገዶች አሉ፡፡ ከእነዚህ መንገዶች መካከል ለእኛ የሚበጁንም የማይበጁንም አሉ፡፡ ለእኛ ለክርስቲያኖች የሚበጁን አባቶቻችን የነገሩን የእግዚአብሔር ቃል ፣ የኑሯቸው ፍሬ፣ እምነታቸው ፣ የሠሩልን ሥርዓት ፣ ዜማው፣ ቅኔው፣ ጸሎቱ፣ ጾሙ፣ ስግደቱ ወዘተ… ነው፡፡ አባቶቻችን ጤዛ ልሰው፣ ዳዋ ጥሰው፣ ድንጋይ ተንተርሰው፣ በዱር በበረሐ በገደል ተንከራትተው ቅዱሳት መጻሕፍቱን ፣ጽላቱን ደብቀው ባያቆዩን፣ ያሬድም መጻሕፍትን በዜማ ባይደርስልን፣ አብያተ ክርስቲያናትን ባያንጹልን፣ የጥምቀት ፣ የቁርባን፣የተክሊል፣የቅዳሴ፣ የንስሓ ወዘተ… ሥርዓት ባይሠሩልን እኛ ልጆቻቸው ምን ይበጀን ነበር? አባቶቻችን ባበጁልን ሥርዓት የማንጓዝ ከሆነ አባት ያበጀው ለልጅ ይበጀው እንዲሉ ራሳችንን ፈትሸን ዋኖቻችንን ልናስባቸው በእምነት ልንመስላቸው ይገባናል፡፡
በሌላ መልኩ የሥጋ አባቶቻችን ጣዖት በማምለክ ፣ ጾም በመግደፍ ፣ ሐሰት በመናገር፣ በመስከር፣ በመስረቅ ወዘተ… ያሳዩን መንገድ ካለ ይህ ለእኛ የሚበጅ መንገድ አይደለምና ልንጓዝበት አይገባም፡፡ እንዲህ አይነቱን “አባት ያበጀው ለልጅ አይበጀው” ብንለው ይቀናል፡፡ ምክንያቱም እያሳዩን ያለ የኃጢአት መንገድ ብቻ ስለሆነ፡፡

ስለዚህ “አባት  ያበጀው ለልጅ ይበጀው” የሚለው በቃለ እግዚአብሔር የጸኑት፣ የኑሯቸው ፍሬ አስተማሪ የሆኑት፣ በእምነታቸው የጸኑት፣ በትምህርታቸው መናፍቃንን የረቱት ፣ በጸሎታቸው የሚጠብቁት አባቶች ያበጁት ሥርዓት በእነርሱ እግር ለተተካን ልጆቻቸው ይበጁናልና የቀደሙ አባቶች በሠሩልን ሥርዓት በከፈቱልን መንገድ ልንጓዝ ይገባናል፡፡

ትምህርት በምሳሌያዊ አነጋገር ክፍል አንድ

ትምህርት በምሳሌያዊ አነጋገር
“ብዙ ቢያወጉ ይዘነጉ፤ ብዙ ቢተቹ ይሰለቹ” እንዲሉ ኢትዮጵያውያን በጥቂት የቃላት ጥምርታ ብዙ ቁም ነገሮችን በማስተላለፍ የታወቁ ናቸው፡፡ ከንባብ መብዛት ይልቅ ለምሥጢር መብዛት ትኩረት የሚሰጡ ለመሆናቸው በርካታ አባባሎች ምስክርነታቸው ዛሬም ድረስ ይገኛል፡፡ እነዚህ አባባሎች በቀጥታው ካለው ትምህርታቸው በተጨማሪ በብዙ አቅጣጫ አስተማሪ የሆኑ ድብቅ ምሥጢሮችን የያዙ ናቸው፡፡ ከበርካታ አባባሎች ጥቂቶችን በጥቂት በጥቂቱ እንመልከት፡፡
ለልጅ ከሳቁለት…
ሰይጣን በነገሠበት በዚህ ዓለም ለምንኖር በሰይጣን የተሰረቀ ልቡናችንን የምንመልስበት ልቡናችን እናዳይሰረቅም የምንጠነቀቅበት ምሳሌያዊ አነጋገር ነው፡፡ ሥነ ቃሉ “ለልጅ ከሳቁለት ለውሻ ከሮጡለት”  የሚል ነው፡፡ በዚህ ምሳሌያዊ አነጋገር ውስጥ የተገለጹ ልጅና ውሻ ከሚስማሟቸው ባሕርያት ጋር ነው፡፡ ልጅ ከሳቁለት ሽንቴን ልሽናብህ፣ ሰገራዬን ልጸዳዳብህ፣ ንፍጤን ልነፈጥብህ፣ በዱላ ልደብድብህ ፣ ጭቃ ልቀባህ ወዘተ… በማለት የብልግና ሥራ ሊሠራብን ይወዳል፡፡ በተለይ ደግሞ ብዙ ጊዜ የሳቃችሁለት ከሆነ እነዚህን የብልግና ሥራዎች እንዳይሠራ ብትቆጡት ያለቅሳል፡፡ ውሻም ምንም ያህል እንኳ ፈሪ ቢሆን ከሮጣችሁለት ተከትሎ ማባረሩ አይቀርም፡፡ ጎንበስ ስትሉ ያየ እንደሆነ ግን ከተከተለበት በበለጠ ፍጥነት ወደ ኋላው ይሸሻል፡፡ ሰይጣን እንዲሁ ልጅ ሲስቁለት የብልግና ሥራ እንደሚሠራ ሁሉ ወድደውት ለሚስቁለት የሥጋ ሥራን አሠርቶ በኃጢአት ሊያቆሽሽ ይወዳል፡፡ ብዙ ጊዜ እንዲህ ሲስቁለት ኖረው በጾም፣ በጸሎት ፣ በስግደት ፣ በንስሓ ቢቆጡት እንደ ሕጻን አልቅሶ የሥጋ ሥራን ከማሠራት መታገሱ አይቀሬ ነው፡፡ ዳግመኛም ሰይጣን እንደ ውሻ ሲሮጡለት ከቤተክርስቲያን ፣ ከጸሎት ፣ ከጾም፣ ከስግደት ፣ ከበጎ ሥራ ወዘተ… ፈሪነቱን ደብቆ ደፋር መስሎ እየተከተለ ያባርራል፡፡ ይሁን እንጅ በእምነት፣ በጸሎት፣ በጾም፣ በትሕትና ወዘተ…  ጎንበስ ሲሉ ያየ እንደሆነ ከተከተለበት በበለጠ ፍጥነት አፍሮ ወደኋላው ይመለሳል፡፡ ስለዚህ ሰይጣንን እንደ ልጅ በመሳቅ እንደ ውሻ በመሮጥ ልንገዛለት አይገባም፡፡ ሰይጣን ማለት የተዋረደ፣ የወደቀ፣ ወራዳ፣ ውዳቂ፣ የከረፋ ማለት ስለሆነ ለተዋረደ፣ ለወደቀና ለከረፋ ደግሞ እጅ መስጠት በክርስትና ሕይወት ልማድ አይደለም፡፡  ሰይጣን ጸሎት እንዳትጸልዩ፣ ጾም እንዳትጾሙ፣ ስግደት እንዳትሰግዱ፣ በጎ ሥራ እንዳትሠሩ ወዘተ… በሰንሰለት ቢያስራችሁ ሰንሰለቱን ሊፈቱ ወደሚችሉት ካህናት መሄድ እንጅ የማሰርና የመፍታት ሥልጣን ወዳልተሰጠው ሰይጣን መገስገስ አይገባም፡፡
የራሷ እያረረባት…
ይህ ምሳሌያዊ አነጋገር ሁለት ጠቃሚ ትምህርቶች በውስጡ የያዘ ስለሆነ ባለሁለት ስለት ቢላዋ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሥነ ቃሉ “የራሷ እያረረባት የሰው ታማስላለች” የሚል ነው፡፡ ከዚህ ምሳሌያዊ አነጋገር የምናገኘው የመጀመሪያው ትምህርት ማቴ 7÷3በወንድምህም ዓይን ያለውን ጉድፍ ስለምን ታያለህ በዓይንህ ግን ያለውን ምሰሶ አትመለከትም” የሚለውን አምላካዊ ቃል የሚገልጽ ነው፡፡ ሰዎች በባሕርያችን ከእኛ ይልቅ በሌሎች ያለውን ለማየት እንፈጥናለን፡፡ ከእግዚአብሔር ርቀን፣ በኃጢአት ተዘፍቀን፣ የጽድቅ ፀሐይ ጨልሞብን በሥጋ ሥራ ተጨማልቀን ሳለ ስለሌሎች በኃጢአት መዘፈቅ፣ ከእግዚአብሔር መራቅ ስናወራ  በርካታ ጊዜያትን እናቃጥላለን፡፡ የራሳችን ሕይወት በኃጢአት እያረረ መሆኑን ሳንመለከት የሌሎችን ኃጢአት እናማስላለን፡፡ እኛ የምናማስለው የሌሎች ኃጢአት በንስሓ ጠፍቶ ይሁን አይሁን ምን ማረጋገጫ ኖሮን ነው በሌሎች ዓይን ያለውን ጉድፍ ስንመለከት ዓይናችን የሚፈዘው? የራስ የሆነውን አሳርሮ የሌሎችን ማማሰል ከንቱነት ነው፡፡ የሌሎችን ከማማሰል በፊት የራስን በአግባቡ ማማሰል ይቀድማል፡፡ ስለዚህ የሌሎችን ትንሽ ኃጢአት ከምናማስል የራሳችንን ትልቅ ኃጢአት በንስሓ አስወግደን በኃጢአት እሳት ለማረር የቀረበ ሕይወታችንን ልንታደግ ይገባናል፡፡

ሁለተኛው ትምህርት ከዚህ በተለየ መልኩ የጻድቃንን ደግነት የሚያሳይ ነው፡፡ ጻድቃን የዚችን ዓለም ጣዕም ንቀው፣በበረሐ ወድቀው፣ ድንጋይ ተንተርሰው፣ ጤዛ ልሰው፣ ዳባ ለብሰው፣ ፀብአ አጋንንትን ድምጸ አራዊትን ታግሰው፣ ተድላ ሥጋቸውን ጠልተው፣ ተድላ ነፍሳቸውን ፈልገው  ከሰው ርቀው ፣ ንጽሕ ጠብቀው ይኖራሉ፡፡ እንዲህ ለሥጋ በማይመች ኑሮ እየኖሩ በተድላ ሥጋ ለሚኖረው ዓለም ይጸልያሉ፡፡ ምክንያቱም ቅዱሳን ከራሳቸው ጥቅም ይልቅ የሌሎችን ጥቅም ያስቀድማሉና ነው፡፡ እነርሱ ነድደው ለሌሎች ብርሃን ይሆናሉ፡፡ ራሳቸውን ጎድተው ሌሎችን ይጠቅማሉ ፡፡ የራሳቸው ተድላ ሥጋ አርሮ ሳለ ለሌሎች ተድላ ሥጋ ይጸልያሉ፡፡ ስለዚህ የጻድቃንን ደግነት የራሷ እያረረባት የሰው ታማስላለች ብለን ልንገጸው እንችላለን ማለት ነው፡፡

Tuesday, September 16, 2014

ተሐድሶ መናፍቃን ክፍል ሦስት

ሌባ ለአመሉ…
“እገሌ ባዘጋጀው ልዩ የስብከት መርኀ ግብር ይህን ያህል ሽህ ብር ለቤተክርስቲያን ገቢ አደረገ፡፡ ስለዚህ እገሌ ተሐድሶ ሊባል እንዴት ይችላል በእኔ በኩል ግን ተሐድሶ መናፍቅ መባሉን አልደግፍም” የሚሉ አንዳንድ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች “ሌባ ለአመሉ ዳቦ ይልሳል” የሚለውን ምሳሌያዊ አነጋገር የዘነጉ ናቸው፡፡ እነርሱ እንደሚሉት ለቤተክርስቲያን የሰጠው ገንዘብ እንጅ ጥሩ ምእመን አይደለም እኮ ፡፡ ቤተክርስቲያን የምትፈልገው ደግሞ በሽህ የሚቆጠር ጥሩ ምእመንን ነው፡፡ ስለዚህ ገንዘብ መስጠት ብቻውን የተዋሕዶ ልጅ የሚያሰኝ ባለመሆኑ ትምህርቱን፣ ሥርዓት አጠባበቁን መመልከት ተገቢ ነው፡፡ 
የሚያስለቅስህ ፈልግ
ተሐድሶ መናፍቃን ስብከቶቻቸው በቀልድ በሳቅ የታጀቡ በመሆናቸው ለመሳቅ የሚከተላቸው እጅግ ብዙ ነው፡፡ አንድ ወጣት “እገሌ ሲሰብክ እየቀለደና እያሳቀ በጣም እያዝናና ስለሆነ ሁልጊዜ ከእርሱ ጋር ብውል ባድር እንዴት ደስ ይለኝ ነበር” እያለ ለአባቱ ይነግራቸዋል፡፡ አባቱም “ልጄ ከዛሬ ጀምረህ ኃጢአትህን እየነገረ ስለኃጢአትህ በንስሓ የሚያስለቅስህ ሰባኪ ፈልግ” አሉት፡፡ ስለዚህ የሚያስፈልገው ኃጢአታችንን እያሰብን ወደ ንስሓ የሚመራን ስብከት እንጅ የሚያስቅ የሚያዝናና አይደለም፡፡ ሳቅ ጨዋታማ በዓለምስ ሞልቶ ተርፎ የለም እንዴ? ቤተክርስቲያን መሄድ ያስፈለገው ለንስሓ ነው እንጅ፡፡
አገልግሎት ስብከት ብቻ
አንድ የተሐድሶ መናፍቅ ሰባኪ አርብና ረቡዕን በሌሊት ሲመገብ ቅር አይለውም፡፡ ለምን እንዲህ ታደርጋለህ? ሲሉትም እኔ አገልጋይ ስለሆንኩ እንዳይደክመኝ ነው ይላል፡፡ በእውነት አገልግሎት ስብከት ብቻ ነው? ጹሙ ለማለትስ መጾም አያስፈልግም? ያለ ምግብ ቃለ እግዚአብሔርን ማስተማርስ አይቻልም? እንዲህ አይነቱ የሰባኪነትን ክብር ማቃለል የሚፈልግ የዲያብሎስ የግብር ልጅ ነው፡፡ ሐዋርያት ሳንበላ ሳንጠጣ ወንጌልን አንናገርም ብለው ነበር እንዴ? ቅዱስ ጳውሎስ ዕለት ዕለት የሚያሳስበኝ የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ነገር ነው ያለው ከሆዱ መሙላት በኋላ መሰላችሁ እንዴ? አይደለም ብዙ መከራ እንደደረሰበት ዘርዝሮ ያንን ሁሉ ከምንም ሳልቆጥር የአብያተ ክርስቲያናት ጉዳይ ያሳስበኛል ነው እኮ ያለው፡፡
የሚደግፈው እንዳያጣ ነው
ብዙዎች “እገሌ በስብከቱ ውስጥ ድንግል ማርያምን የማይሰብከው ለምንድን ነው?” ይላሉ፡፡ ድንግል ማርያምን የማይሰብከውማ ድንግልን አምባ መጠጊያ እያደረገ በእናትነት ጥላዋ ሥር እየተጠለለ የሚኖር ትውልድ እንዳይፈጠር ነው፡፡ ትውልዱ ድንግል ማርያምን ከተጠጋ እርሱን የሚደግፈው ደጋፊ እንዳያጣ ስለሚሰጋ እርሱን ብቻ እንዲከተሉት ለማድረግ ሌሊት ከቀን የራሱን የማይጠቅም ታሪክ ሲዘረዝር ይኖራል፡፡ በተጨማሪም እመብርሃንን የካዱ ለሆዳቸው ያደሩ ስለሆኑ የእመቤታችንን ሥም ማንሣት አይፈልጉም፡፡
እውነትን ለማስጠላት
መናፍቃን ሻሽ ጠምጥመው መስቀል ጨብጠው ሰክረው ለመውደቅ ይንገዳገዳሉ፡፡ የምንኩስና ቆብ ገዝተው ይለብሱና ከሴት ጋር ተቃቅፈው መንገድ ለመንገድ ይዞራሉ፡፡ የሰውን ኅሊና ለመስረቅም ጀርባቸውን በብረት እየገረፉ እግዚአብሔር የላከን ነን እያሉ በየቦታው ይልከሰከሳሉ፡፡ ይህን የሚያደርጉት በርካታ ሕዝብ በሚገኙባቸው ቦታዎች መሆኑ አውነተኛ ካህናትን፣ መነኮሳትን ባሕታውያንን ለማስጠላት ነው፡፡ ወይ የዘመኑ ቄስ! ወይ የዘመኑ መነኩሴ! ወይ የዘመኑ ባሕታዊ! እያለ ያያቸው የተመለከታቸው ሁሉ አውነተኞቹን ይሰድባል፡፡ ቤተክርስቲያንም እንድትጠላ ጃንጥላ ዘቅዝቀው ሰሌን ዘርግተው ቅዱሳት ሥዕላትን አንግበው መስቀል ይዘው የቅዱሳንን ሥም እየጠሩ የዚህ ቤተክርስቲያን ማሰሪያ እጃችሁን ዘርጉ እያሉ የየዋሃንን ገንዘብ መስከሪያ የሚያደርጉ እየተበራከቱ ነውና ወገኔ መንቂያ ሰዓትህ  አሁን ነው እንቅልፍ ይብቃህ፡፡
ድፍረት
የተሐድሶ መናፍቃን ዋና መርኅ ድፍረት ነው፡፡ በትምህርታቸውና በመዝሙራቸው ውስጥ ይህን ድፍረታቸውን ለትውልዱ ሁሉ በማለማመድ ላይ ይገኛሉ፡፡ ዓለምን ተኝቶ የሚገዛ ፈጣሪ ነው የምናመልከውይላሉ፡፡ ይህን የድፍረት ቃል ማነው ያስተማራቸው? ከየትስ ነው ያነበቡት? በእውነት ዓለም የምትተዳደረው በሚያንቀላፋ አምላክ ነውን? እስራኤልን የሚጠብቅ አያንቀላፋም ሲባል ነው ከመምህራን የሰማነው ከመጻሕፍት ያነበብነው የዛሬ ደፋሮች ግን እግዚአብሔርን የሚያንቀላፋ እንቅልፍ የሚያሸንፈው አድርገው ያስተምራሉ፡፡የሳሎኑ ጽጌረዳበማለት ክርስቶስን ከሰው ሠራሹ የፕላስቲክ አበባ ጋር የሚደምሩም ድፍረትን በጥሩ ሁኔታ የለመዱ ደፋሮች አሉ፡፡ ዕድሜ ብቻ! ማቱሳላ ያን ያህል ዘመን ቢኖር ምን ሠራእያሉ ማቱሳላን የሚንቁ ሽማግሌዎችንም የሚሳደቡ ድፍረት ገንዘባቸው የሆኑ አፈ ጮሌዎችም አሉ፡፡ እነርሱ በተጠቀሙት ቃል እኛም ብንገልጸው ለጆሮ የሚያሳክክ ከባድ ኑፋቄ ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ከድፍረት ኃጢአት ራሳችንን ልንጠብቅ ይገባናል፡፡