Thursday, June 30, 2016

“የቅብአት ምንፍቅና መደበቂያ ካባዎች” ክፍል 8


© መልካሙ በየነ
ሰኔ 23/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

በክፍል 7 “በቅብአት የባሕርይ ልጅ ሆነ ማለት” ክህደት እንደሆነ በሚገባ ተመልክተናል በዚህ ክፍልም የዚህን ተከታይ መጽሐፋቸው “ወልደ አብ” ላይ ያለውን መነሻ አድርገን እንመለከታለን፡፡
በመጀመሪያ የመጽሐፉ ርእስ “ወልደ አብ” የተባለበትን ምሥጢር ግን ሁላችን ልንረዳው ይገባል፡፡ “ወልደ አብ” ብለው መሰየማቸው አብ በመለኮትና በሰውነት ሁለት ጊዜ ወልዶታል ብለው ስለሚያስቡ ነው “ወልደ ማርያም” ከሚለው ስሙ ይበልጣል ብለው ስለሚያምኑ ነው፡፡ ለማንኛውም እምነታቸው የራሳቸው ስለሆነ ባይመለከተንም በአንድ ገዳማችን ስም ስለጻፉት ግን የእኛ አስተምህሮ እንዳልሆነ እንገልጽ ዘንድ እንገደዳለን፡፡ ስለዚህም ዝም አንልም!!!
ወልደ አብ ገጽ 219 ላይ ነኝ ዛሬ “ይህ የጸጋ ልጅነት የሌለው ባእድ ሥጋ እምቅድመ ዓለም የባሕርይ ልጅነት ካለው መለኮት ጋራ ቢዋሐድ የቃልን ገንዘብ ተቀብሎ ወልደአብ ቃለ አብ ቃለ መንፈስ ቅዱስ ሆነ ልጅነት አገኘ፡፡ ይህ ልጅነት ያለው ቃል ልጅነት ከሌለው ሥጋ ጋራ ቢዋሐድ በሥጋ ርስት ልጅነትን የሚሻ ሆነ፡፡ እንዘ ባዕል ውእቱ በኩሉ አንደየ ርእሶ እን ጳውሎስ ፪ኛ ቆሮ ም፰ ቁ፱ ስለዚህ ከእምቅድመ ዓለም ልደቱ ፩ድ ለማድረግ በሰውነቱ የባሕርይ ህይወቱን በመላ ተቀብሎ ከአብ ተወለደ እንጅ የቀደመ ልጅነቱስ አልተነሣውም፡፡ ወልድስ በሰውነቱ መንፈስ ቅዱስን ከአብ ተቀብሎ ባይወለድ ወልድ በሰውነቱ እንደ አብ ባልገዛም አብም ለወልድ በሰውነቱ አገዛዙን ክብሩን በመላ በሰፋ ባልሰጠውም ነበር ኢይሁብ ክብርየ ለባዕድ ለተሳትፎ ወስብሐትየ ለግልፎ እን ኢሳ ም፵፪ ቁ፰ መንፈስ ቅዱስን ከአብ ተቀብሎ ቢወለድ ግን እንደአብ ገዛ አዘዘ፡፡ አብም ለወልድ በሰውነቱ አገዛዙን ክብሩን ሰጠው አኮ ዘይሁብ እግዚአብሔር አብ መንፈሶ በመስፈርት አላ አብሰ ያፈቅር ወልዶ ወኲሎ ኲነኔሁ አወፈዮ ለወልዱ ውስተ እዴሁ እን ወን ዮ ም፫ ቁ፴፬፡፡ ወረሰዮ ወራሴ ለኲሉ እን ጳው ዕብ ም፩ ቁ፪” እያለ ክህደት እንደ ጉድ ይጎርፋል፡፡ ቃል በቃል እንመልከት፡፡
“ይህ የጸጋ ልጅነት የሌለው ባእድ ሥጋ እምቅድመ ዓለም የባሕርይ ልጅነት ካለው መለኮት ጋራ ቢዋሐድ የቃልን ገንዘብ ተቀብሎ ወልደአብ ቃለ አብ ቃለ መንፈስ ቅዱስ ሆነ ልጅነት አገኘ” ሥጋ ከፈጣሪው የጸጋ ልጅነትም የለውም ነበር ማለታቸው አዳም ስለበደለ እና ጸጋ እግዚአብሔር ስለተገፈፈበት ነው፡፡ ሆኖም ግን እምቅድመዓለም የባሕርይ ልጅነት ያለው መለኮት ሲዋሐደው የቃልን ገንዘብ ገንዘቡ አደረገ እና ወልደ አብ ቃለ አብ ቃለ መንፈስ ቅዱስ ሆነ ልጅነትንም አገኘ ብለው ይደመድማሉ፡፡ በጣም ጥሩ ነው አሁን ላይ መለኮት ሲዋሐደው ሥጋ አምላክ ሆነ ክቡር ሆነ የቃል ገንዘብ ገንዘቡ ሆነ እና ወልደ አብ ቃለ አብ ቃለ መንፈስ ቅዱስ ሆነ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ቀጥለው ይህንን ይጣረሱታል፡፡ “ይህ ልጅነት ያለው ቃል ልጅነት ከሌለው ሥጋ ጋራ ቢዋሐድ በሥጋ ርስት ልጅነትን የሚሻ ሆነ” ከላይ “የቃልን ገንዘብ ተቀብሎ ወልደአብ ቃለ አብ ቃለ መንፈስ ቅዱስ ሆነ ልጅነት አገኘ” ብለው ነበር አሁን ደግሞ እንደገና ተመልሰው “በሥጋ ርስት ልጅነትን የሚሻ ሆነ” ብለው የሚጋጭ ሃሳብ አስፍረዋል፡፡ ለዚህ ሃሳባቸውም የሚደግፍ ማስረጃ ብለው ሰውን ለማደናገር ግዕዙን ብቻ ጠቅሰው አማርኛውን ሳያስቀምጡት አለፉ፡፡ አብዛኛው ሕዝብ ግእዝን እንደማይችል ስለሚያውቁ እንዲህ ይላልሳ እያሉ ያወናብዳሉ እንዘ ባዕል ውእቱ በኩሉ አንደየ ርእሶ እን ጳውሎስ ፪ኛ ቆሮ ም፰ ቁ፱ ፍችውም “ሃብታም ሲሆን እናንተ በርሱ ድህነት ባለጠጋዎች ትሆኑ ዘንድ ስለእናንተ ደሃ ሆነ” የሚል ነው፡፡ እነርሱ ግን ሙሉውን ሳይጠቅሱ ቆርጠውታል፡፡ ሆኖም ይህ ጥቅስ “ቃል በሥጋ ርስት ልጅነትን የሚሻ” ለመሆኑ ምንም ማረጋገጫ የለውም፡፡ ስለዚህም ማስረጃነቱን ለማወናበድ ካልተጠቀሙበት በቀር ምንም ማረጃነት የለውም፡፡ ማስረጃ ሊሆን የማይችለውም ነድየ የሚለው የሚስማማው ለሥጋ ነው እንጅ ለመለኮት አይደለምና ቃል ከሥጋ ጋር በተዋሐደ ጊዜ የሥጋ ንድየት በቃል ባዕልነት ተወግዷል፡፡ ስለዚህ የዚህ ማስረጃነት ተቀባይነት የለውም፡፡ ቀጥለውም  “ስለዚህ ከእምቅድመ ዓለም ልደቱ ፩ድ ለማድረግ በሰውነቱ የባሕርይ ህይወቱን በመላ ተቀብሎ ከአብ ተወለደ እንጅ የቀደመ ልጅነቱስ አልተነሣውም” ይላሉ፡፡ በክፍል 7  ዳግመኛ “ከአብ በማኅጸነ ማርያም ተወለደ” የሚለውን ክህደት ተመልክተናል ስለዚህ እዚህ ላይ አልደግመውም፡፡  በመቀጠልም “ወልድስ በሰውነቱ መንፈስ ቅዱስን ከአብ ተቀብሎ ባይወለድ ወልድ በሰውነቱ እንደ አብ ባልገዛም አብም ለወልድ በሰውነቱ አገዛዙን ክብሩን በመላ በሰፋ ባልሰጠውም ነበር” ብለው ወልድን ከአብ ያሳንሳሉ፡፡ አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ በመግዛት አንድ ናቸው፡፡ ይህ ምሥጢረ ሥላሴ ነው፡፡ ይህ የመግዛት አንድነት ወልድ ሥጋን በለበሰ ጊዜ አልተቋረጠም፡፡ ስለዚህ ወልድ የመግዛት አንድነቱን ይዞ ከአብ እና ከመንፈስ ቅዱስ ሳይለይ ሥጋን ቢዋሐድ ሥጋ የመግዛት ሥልጣንን ከወልድ ያገኛል እንጅ ከአብ አያገኝም፡፡ አስቀድመን እንደተናገርነው ወልድ ባለበት አብና መንፈስ ቅዱስ አሉና አብ ለወልድ የመግዛት ስልጣንን የሚሰጠው ወልድም የመግዛት ስልጣንን የሚቀበል አይደለም፡፡ ምክንያቱም ከመግዛት አንድነቱ የጠለየበት ጊዜ ስለሌለ፡፡ ምናልባት በግልጽ አልጻፈላቸው ይሆናል እንጅ ጸሐፊው “ገብረ መድኅን እንዳለው” ወልድ አምላክነቱን ለዓይን ጥቅሻ ታህል አጥቷል ብሎ ያምናል፡፡ ሎቱ ስብሐት!
አሁንም በግእዝ ጠቅሰው ለማወናበድ “ኢይሁብ ክብርየ ለባዕድ ለተሳትፎ ወስብሐትየ ለግልፎ እን ኢሳ ም፵፪ ቁ፰” ይላሉ ትርጉሙን እንመልከት፡- “እኔ እግዚአብሔር ነኝ ፡- ክብሬን ለሌላ ምስጋናየንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም” የሚል ነው ቆርጠው ስላስቀሩት ነው እንጅ፡፡ እስኪ አስተውሉ ወገኖቼ! “ወልድስ በሰውነቱ መንፈስ ቅዱስን ከአብ ተቀብሎ ባይወለድ ወልድ በሰውነቱ እንደ አብ ባልገዛም አብም ለወልድ በሰውነቱ አገዛዙን ክብሩን በመላ በሰፋ ባልሰጠውም ነበር” ለሚለው “ክብሬን ለሌላ ምስጋናየንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም” ማስረጃ ሊሆን የሚችለው በምን ሂሳብ ነው፡፡ ወይስ ደግሞ ግእዝ ስለሆነ የተጠቀሰው ሁሉ ማስረጃ ይሆናል ማለት ነው፡፡ “ገብረ መድኅን እንዳለው” በእውነት የመጽሐፍ ሊቅ አይደለም ማለት ነው እንጅ እንዲህ ባላለም ነበር፡፡ ከመጻሕፍት ሊቃውንት የወሰዳቸው ቃላት “እንዲል” “አንድም” የሚሉትን ብቻ ነው እንጅ እውቀቱን ትምህርቱን አልወሰደም፡፡ በራሱ ደስ እንዳለው የሚጽፍ የልብወለድና የፈጠራ ጸሐፊ ነው፡፡ በመቀጠልም “መንፈስ ቅዱስን ከአብ ተቀብሎ ቢወለድ ግን እንደአብ ገዛ አዘዘ፡፡ አብም ለወልድ በሰውነቱ አገዛዙን ክብሩን ሰጠው” ይላሉ፡፡ አብን ሰጭ ወልድን ተቀባይ ልናደርገው እንዴት እንደፍራለን፡፡ ወልድስ ለመግዛት አብን እያስፈቀደ ነው ልንል እንዴት እንደፍራለን፡፡ ወልድ መንፈስ ቅዱስን ዳግመኛ መቀበል ያስፈለገውስ እምቅድመዓለም የባሕርይ ሕይወቱ የሆነው መንፈስ ቅዱስ አልቆበት ነው ልንል ነውን? ወይስ ዳግመኛ መንፈስ ቅዱስን ሊያድስ ነው ልንል ይሆን? ለዚህም ማስረጃቸው ያው የተለመደው ግእዝ ብቻ ነው፡፡ “አኮ ዘይሁብ እግዚአብሔር አብ መንፈሶ በመስፈርት አላ አብሰ ያፈቅር ወልዶ ወኲሎ ኲነኔሁ አወፈዮ ለወልዱ ውስተ እዴሁ እን ወን ዮ ም፫ ቁ፴፬፡፡ ትርጉሙም “እግዚአብሔር የላከው የእግዚአብሔርን ቃል ይናገራልና እግዚአብሔር መንፈሱን ሰፍሮ አይሰጥምና አባት ልጁን ይወዳል ሁሉንም በእጁ ሰጥቶታል” የሚል ነው፡፡ አንድምታውን ስትመለከቱ “ከእግዚአብሔር አካል ዘእምአካል ባሕርይ ዘእምባሕርይ ተወልዶ የመጣ እሱን እግዚአብሔርነቱን ያስተምራል፡፡ ሀብተ መንፈስን በልክ የሚሰጥ አይደለምና” ይላል ተመልከቱት ሁላችሁም፡፡ ሌላው የጠቀሱት “ወረሰዮ ወራሴ ለኲሉ እን ጳው ዕብ ም፩ ቁ፪” የሚል ነው ትርሙም “ሁሉን ወራሽ ባደረገው” ማለት ነው፡፡ እንግዲህ እዚህ ላይ ሁለቱም ቦታዎች ላይ ያስቀመጧቸው ጥቅሶች “ወልድ መንፈስ ቅዱስን ከአብ ተቀብሎ ቢወለድ ግን እንደአብ ገዛ አዘዘ፡፡ አብም ለወልድ በሰውነቱ አገዛዙን ክብሩን ሰጠው” የሚል አይደለም፡፡ ስለዚህ ማስረጃ ተብለው የተቀመጡት ሁሉ ማስረጃነት የሌላቸው የመጽሐፉን ገጽ ብቻ ለመጨመር የተጻፉ እንደሆኑ ልብ ይሏል፡፡

ይቀጥላል…

Wednesday, June 29, 2016

“የቅብአት ምንፍቅና መደበቂያ ካባዎች” ክፍል 7

© መልካሙ በየነ
ሰኔ 22/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ


በክፍል 6 የተዋሕዶን ምሳሌ በጋለ ብረት መስለን ተመልክተናል፡፡ ስለዚህ ወልድ ከድንግል ማርያም ሥጋን ለመሐድ የመንፈስ ቅዱስን ቅባትነት እንደማይሻ ተረድተናል፡፡ ምክንያታችንም እንደእንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ አይደለም ጥንትም ያለ ነው እንጅ፡፡ ጥንትነቱም መንፈስ ቅዱስ የባሕርይ ሕይወቱ የሆነው ከዓለም መፈጠር አስቀድሞ የሰው ኅሊና በማይደርስበት ረቂቅ ምሥጢር ነው አንጅ ዛሬ ሥጋን ሲዋሐድ አይደለምና ነው፡፡ ያ የቀድሞ የባሕርይ ሕይወቱ ለቅጽበት ታህል እንኳ የተለየበት ጊዜ ሰለሌለ ሥጋን በተዋሐደ ጊዜ ዳግመኛ መንፈስ ቅዱስን የባሕርይ ሕይወቱ ያደርገው ዘንድ ወልድ አይሻም፡፡ በዚህ ክፍል የምንመለከተው በዚሁ ዙሪያ ነው፡፡
ወልደ አብ ገጽ 212 ላይ ያለውን ክህደት መነሻ አድርገን እንጽፋለን፡፡ “በቅብአት የባሕርይ ልጅ ሆነ ማለት ምሥጢሩ ምንድን ነው ቢሉ ወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ ከአብ የባሕርይ ልደት ተወለደ ማለት ነው፡፡ ምነው ይህስ ቢሆን ወልድ በአብ ያልተወለደ በራሱ ያልተወለደ ስለምን በመንፈስ ቅዱስ ተወለደ ቢሉ ይህስ ወላዲ በሚመስለው ሕይወት ይወልዳል እንጅ በማይመስለው አይወልድም፡፡ ለዚህም ምሳሌ ያስረዳል እነሆ ዛሬ በደመ ነፍስ ሕያዋን የሆኑ እንስሳ ከእንስሳ ይወለዳሉ በነባቢትም ነፍስ ሕያው የሆነ ሰው ከሰው ይወለዳል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ለአብ ሕይወቱ ነው በደመ ነፍስ ሕያው ያልሆነ ከእንስሳ በነባቢት ነፍስ ሕያው ያልሆነ ከሰው እንዳይወለድ፡፡ እንደዚህም ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ሕያው ያልሆነ ከአብ አይወለድምና ወልድ በመንፈስ ቅዱስ ከአብ ተወለደ” ይላል፡፡ እስኪ ቃል በቃል እንመልከተው፡፡

v “በቅብአት የባሕርይ ልጅ ሆነ ማለት ምሥጢሩ ምንድን ነው ቢሉ ወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ ከአብ የባሕርይ ልደት ተወለደ ማለት ነው”
ሁላችን እንደምናውቀው በከዊን አብን “ልብ” ወልድን “ቃል” መንፈስ ቅዱስን “እስትንፋስ” እንላለን፡፡ የአብ “ልብነት” ከወልድ “ቃልነት” ከመንፈስ ቅዱስም ሕይወትነት (እስትንፋስነት) አይቀድምም አይከተልምም፡፡ በተመሳሳይ የወልድ “ቃልነት” ከአብ “ልብነት” እና ከመንፈስ ቅዱስ “እስትንፋስነት” አይይቀድምም አይከተልምም፡፡ የመንፈስ ቅዱስም “ሕይወትነት” (እስትንፋስነት) ከአብ “ልብነት” ከወልድ “ቃልነት” አይቀድምም አይከተልምም፡፡ ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ ለአብ እና ለወልድ እስትንፋሳቸው ነው ማለት የባሕርይ ሕይወታቸው ነው ማለት ነው፡፡ በቅብአት እምነት ውስጥ ግን “ወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ”  ይላሉ፡፡ እንግዲህ “ወልድ” ማለት ልጅ ማለት እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ልጅነቱም ከአብ የባሕርይ ልጅነት ነው፡፡ ይህ “ወልድ” የሚለው ስም አብ “አብ” ከተባለበት መንፈስ ቅዱስም “መንፈስ ቅዱስ” ከተባለበት ስሙ አይቀድምም አይከተልምም፡፡ ስለዚህ “ወልድ” የሚለው ስም የተገባው የሆነ ከድንግል ማርያም በተወለደ ጊዜ አይደለም፡፡ ከድንግል ማርያም በተወለደ ጊዜስ “አማኑኤል” “ኢየሱስ” ተባለ እንጅ ወልድ የተባለውስ ከዓለም መፈጠር አስቀድሞ “ባሕርይ ዘእምባሕርይ አካል ዘእምአካል” ከአብ በተወለደ ጊዜ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ “ወልድ” የመንፈስ ቅዱስን ሕይወትነት ያገኘው ዛሬ ከድንግል ማርያም በተወለደ ጊዜ ሳይሆን ጥንት ከአብ ተወልዶ “ወልድ” ተብሎ በተጠራበት ጊዜ ነው፡፡ ስለዚህ “ወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ”  ቢባል ክህደት ነው አንጅ እምነት አይባልም፡፡ ምክንያቱም “አብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ህልው ነውና፤ ወልድም በአብና በመንፈስ ቅዱስ ህልው ነውና፤ መንፈስ ቅዱስም በአብና በወልድ ህልው ነውና” እንዳሉ የቀደሙ አባቶቻችን በሃይማተ አበው ዘዲዮናስዮስ ምእ 101 ቁጥር10 ላይ፡፡ ስለዚህ ይህ ህልውና ቀድሞ ከዓለም መፈጠር አስቀድሞ ያለ በመሆኑ እና ወልድ ከዚህ ህልውናው የተለየበት ጊዜ ስለሌለ  “ወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ”  ቢባል ክህደት ነው፡፡ “በቅብአት የባሕርይ ልጅ ሆነ ማለት ምሥጢሩ ምንድን ነው ቢሉ ወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ ከአብ የባሕርይ ልደት ተወለደ ማለት ነው”  ማለትን ከማን እንደተማሩት አይታወቅም፡፡ አብ በመለኮቱ ቅድመ ዓለም ያለ እናት ወለደው እንጅ ድህረ ዓለምም ዳግመኛ በሰውነቱ ከእናት አልወለደውም፡፡ በሰውነቱስ ከአብ ዳግመኛ ተወልዶ ቢሆን ኖሮ “ወልደ አብ” መባል “ወልደ ማርያም” ከመባል በበለጠበት ነበር፡፡ ነገር ግን ቅድመ ዓለም “ወልደ አብ” የተባለው ድኅረ ዓለም “ወልደ ማርያም” ቢባል እኩል ነው አንጅ አይበላለጥም፡፡ እንዲያውም ሊቃውንቱ ሲያመሰጥሩ “ቀዳማዊ ልደቱ በደኃራዊ ልደቱ ታወቀ” ይላሉ፡፡ ይህ ማለት “ወልደ አብ” መባሉ “ወልደ ማርያም” በመባሉ ታወቀ ተገለጠ ማለት ነው፡፡ ሃይማኖተ አበው ዘቴዎዶጦስ ምእ 53 ቁ 13 ላይ “ወልድ ዋሕድ ከአብ መወለዱ እንዴት እንደሆነ ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱ እንዴት እንደሆነ አትጠይቀኝ፡፡ እርሱ በባሕርዩ ከአብ ተወልዷልና ለራሱ በአደረገው ተዋሕዶም ከድንግል ማርያም ተወልዷልና አምላክ ነው ሰውም ነው” ይላል፡፡ ሊቁ “ለራሱ በአደረገው ተዋሕዶም ከድንግል ማርያም ተወልዷልና አምላክ ነው ሰውም ነው” አለ እንጅ የቅብአት ምንፍቅና አራማጆች እንደሚሉት “ወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ ከአብ የባሕርይ ልደት ተወለደ ማለት ነው”  አላለም፡፡
v “ምነው ይህስ ቢሆን ወልድ በአብ ያልተወለደ በራሱ ያልተወለደ ስለምን በመንፈስ ቅዱስ ተወለደ ቢሉ ይህስ ወላዲ በሚመስለው ሕይወት ይወልዳል እንጅ በማይመስለው አይወልድም ”
ይኼኛው ከመጀመሪያ ሃሳባቸው ጋር ይጋጫል፡፡ ምክንያቱም ቅድም “ወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ ከአብ የባሕርይ ልደት ተወለደ ማለት ነው”  ብለው ነበር አሁን ግን “ምነው ይህስ ቢሆን ወልድ በአብ ያልተወለደ” ብለው ሃሳባቸውን ራሳቸው ያጣሉታል፡፡ በእርግጥ መጽሐፋቸው ሙሉውን እንደዚህ እርስ በእርሱ የተጣረሰ ሃሳብ የሰፈረበት ነውና አይገርመኝም፡፡ እሽ ይሁን ብለን ብንቀበለው እንኳ “ወላዲ በሚመስለው ሕይወት ይወልዳል እንጅ በማይመስለው አይወልድም ” ስላሉ መንፈስ ቅዱስን “ወላዲ” ያሰኛልና አንቀበለውም፡፡ አብን “ወላዲ” ፣ ወልድን “ተወላዲ”፣ መንፈስ ቅዱስን “ሰራጺ” ብንል እንጅ መንፈስ ቅዱስን “ወላዲ” እንዳንል እነሆ የታወቀ የተረዳ ነው፡፡ “ወላዲ በሚመስለው ሕይወት ይወልዳል”  አልን እንጅ መቼ “ወላዲ” ነው አልን ቢሉም ወላጅ የሚመስል ሕይወት የለም ብለን እንመልሳለን፡፡
v  “ለዚህም ምሳሌ ያስረዳል እነሆ ዛሬ በደመ ነፍስ ሕያዋን የሆኑ እንስሳ ከእንስሳ ይወለዳሉ በነባቢትም ነፍስ ሕያው የሆነ ሰው ከሰው ይወለዳል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ለአብ ሕይወቱ ነው በደመ ነፍስ ሕያው ያልሆነ ከእንስሳ በነባቢት ነፍስ ሕያው ያልሆነ ከሰው እንዳይወለድ፡፡ እንደዚህም ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ሕያው ያልሆነ ከአብ አይወለድምና ወልድ በመንፈስ ቅዱስ ከአብ ተወለደ”
በመጀመሪያ የእግዚአብሔርን ረቂቅ ልደት በእንስሳት እና በሰው ልጅ ልደት ልንመስለው እንዴት እንችላለን? ሰው ቢወለድ ከእናት እና ከአባቱ ዘር ነው እንጅ በድንግልና አይደለም፡፡ እንስሳትም ከእንስሳት ቢወለዱ እንዲሁ በተራክቦ ነው እንጅ በድንግልና አይደለም፡፡ የወልድስ ከድንግል ማርያም መወለድ በማክሰኞ ቀን ኅቱም ምድር ለታብቁል ባለው ቃል አብቅላ አፍርታ እንደተገኘች ያለ ነው፡፡ ሰው ከሰው የተለየ እንስሳን፤ እንስሳም ከእንስሳ የተለየ ሰውን ይወልዱ ዘንድ ፈጣሪ ተአምሩን ከገለጸ ይወልዳሉ፡፡ ይህንንም በተለያዩ ዜናዎች እየሰማን እና እየተመለከትን ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ምሳሌ “ወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ ከአብ የባሕርይ ልደት ተወለደ ማለት ነው”  ለሚለው ክህደት ማስረጃ ሊሆን አይችልም፡፡ “እንደዚህም ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ሕያው ያልሆነ ከአብ አይወለድምና ወልድ በመንፈስ ቅዱስ ከአብ ተወለደ”  ብለው ክህደታቸውን በአራት ነጥብ ይቆልፉታል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ሕያው ያልሆነ ከአብ ካልተወለደ በቀዳማዊ ልደቱ አብ ወልድን የወለደው የባሕርይ ሕይወቱ ከሆነው መንፈስ ቅዱስ ሕያው ከሆነ በኋላ ነውን ቢሏቸው መልስ የላቸውም፡፡ ይህ ክህደታቸው ሌላ ክህደትን ይፈጥርባቸዋል፡፡ “በመንፈስ ቅዱስ ሕያው ያልሆነ ከአብ አይወለድምና ወልድ በመንፈስ ቅዱስ ከአብ ተወለደ”  የሚለውን ስንመለከት ወልድ ከአብ ለመወለድ በመንፈስ ቅዱስ ህያው መሆን አለበት ከተባለ የአብን ልብነትስ መቼ ገንዘቡ ሊያደርግ ነው ቢባሉ መልስ የላቸውም፡፡
ጠቅለል ሲል እኛ አባቶቻችን ያስተማሩንን ትምህርተ ተዋሕዶ እንማራለን እናስተምራለን እንጅ አሁን በመጣ እንግዳ ትምህርት አንታለልም አንነጠቅምም፡፡

ይቀጥላል…

Tuesday, June 28, 2016

“የቅብአት ምንፍቅና መደበቂያ ካባዎች” ክፍል 6

© መልካሙ በየነ
ሰኔ 21/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

በክፍል 5 ተዋሕዶ የሚለው ቃል በቅብአት መናፍቃን አንደበትና በእኛ አንደበት የተለያየ ትርጉም እንደሚሰጠው ተመልክተናል፡፡ በዚህም ክፍል እንዲሁ ከአባቶቻችን ምሳሌ አንዱን እንመለከታለን፡፡
በክፍል 5 ላይ የሰጠኋችሁ የተዋሕዶ ምሳሌ “የሃይድሮጅንና የኦክስጅን” ውህደትን ነበር፡፡ እሱ ምሳሌ ትንሽ ፍንጭ ይሰጣችሁ ዘንድ ነው እንጅ አባቶቻችን ከቀድሞው ዘመን ጀምረው ቅብአትን የሚረቱበት ምሳሌ አላቸው፡፡ እኛም እንዲሁ እሱን እንነግራችኋለን፡፡
የቅብአት ምንፍቅና ያነሆለላቸው ጥቂት የሚባሉ በተለይም ደግሞ አሁን በዩኒቨርሲቲ ተማሪነት ደረጃ ላይ ያሉ ለጋ ወጣቶች  ተዋሕዶን “ወርቅ ከብር ጋር ተቀላቅሎ ክብር እንደሚሆነው ሁሉ በተዋሕዶም ወቅት መለኮት ለሥጋ ክብር ሆነው ትላላችሁ” ብለው ነገርን ያጣምማሉ፡፡ እኛስ አባቶቻችንም እንዲህ ያለውን የክህደት ምሳሌ አላስተማሩንም አልጻፉልንምም አልመሰሉልንምም፡፡ እነዚህ የቅብአት በሽታ የተጠናወታቸው መናፍቃን ግን እኛ ያላልነውን ብለው እኛ ያልጻፍነውን አንብበው እንዲህ አሉ ብለው ይናገራሉ፡፡ ወርቅ ከብር ጋር ቢቀላቀል እንጅ እንዴት ሆኖ ሊዋሐድ ይቻለዋል? እኛ የምንለው ያለመጨመር፣ ያለመቀላቀል፣ ያለመደባለቅ፣ ያለ ማደር፣ ያለ መጎራበት፣ ያለመለወጥ በፍጹም ተዋሕዶ  አካለ ሥጋ ከአካለ ቃል ጋራ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆኑ ነው፡፡ ወርቅና ብር ደግሞ በምንም ተአምር አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሊሆኑ አይችሉም ምክንያቱም መዋሐድ ስለማይችሉ፡፡ ይህንን ደግሞ የኬሚስትሪ ባለሙያዎችን አማክሩ፡፡ አለቀ፡፡
እኛ ግን ተዋሕዶን አባታችን ቄርሎስ በመሰለልን የጋለ ብረት እንመስለዋለን፡፡ ብረት የሚስማማው ባህርይ እሳት ከሚስማማው ባህርይ ጋር ፈጽሞ የተለያየ ነው፡፡ ብረት እና እሳት ሁለት የተለያዩ አካላት ናቸው፡፡ ደህና ብረት ሰሪ ያገኘው እንደሆነ ከእሳት አግብቶ ያግለዋል፡፡ ከዚያም የጋለውን ብረት አውጥቶ የፈለገውን ዓይነት ቅርጽ ሰጥቶ ይሰራዋል፡፡ እዚህ ላይ የምንመለከተው ቅድመ ግለት፤ ጊዜ ግለት እና ድኅረ ግለትን ነው፡፡ ቅድመ ግለት ሁለት አካላት ሁለት ባሕርያትን እንመለከታለን፡፡ እሳት አንድ አካል ነው አንድ ባሕርይ ነው ብረትም እንዲሁ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ነው፡፡ እሳትና ብረት የራሳቸው የሆነ አካልና ባሕርይ አላቸው፡፡ በጊዜ ግለት ግን እሳት የብረትን ብረትም የእሳትን ባሕርይ ገንዘባቸው ያደርጋሉ፡፡ ለዚህም ነው እሳቱ የብረቱን ቅርጽ ብረቱም የእሳቱን መልክእ ይዞ መገኘቱ፡፡ በጊዜ ግለት ጥቁር የነበረው ብረት የእሳትን ቀይነት መልክእ ገንዘቡ አድርጎ ቀይ እንደሚሆን ሁሉ ጎንና ዳር የሌለው የማይጨበጠው ረቂቅ እሳትም ግዙፍ የሆነውን የብረት ቅርጽና ግዘፍነት ገንዘቡ አድርጎ የብረቱን ቅርጽ የብረቱን ግዘፍነት ይዞ ይገኛል፡፡ ትክክለኛው የተዋሕዶ ምሳሌ እንግዲህ ይህ ነው፡፡ ብረቱ የሥጋ እሳቱ የመለኮት ግለቱ የተዋሕዶ ምሳሌ ነው፡፡  በቅድመ ተዋሕዶ ሥጋ እና መለኮት የተለያዩ ባሕርያት የተለያዩ አካላት ናቸው፡፡ ሥጋ የራሱ ገንዘብ የራሱ አካል አለው መለኮትም የራሱ ባሕርይ የራሱ አካል አለው፡፡ በጊዜ ተዋሕዶ ግን ሁለት አካላት አንድ አካል ሁለቱ ባሕርያት አንድ ባሕርይ ሆነዋል፡፡ መለኮት የሥጋን ግዘፍነት ጠባብነት ውስንነት ደካማነት ገንዘቡ እንዳደረገ ሁሉ ሥጋም የመለኮትን ረቂቅነት አምላክነት ፈጣሪነት ምሉዕነት ፈታሒነት ገንዘቡ አደረገ፡፡ ሥጋ የመለኮትን ገንዘብ ገንዘቡ ለማድረግ መለኮትም የሥጋን ገንዘብ ገንዘቡ ለማድረግ ሌላ አካልን አይሹም፡፡ ቃል መለኮት ነው ይህ መለኮት የራሱ የተለየ አካል የተለየ ገጽ አለው ከሥጋ ጋርም የተዋሐደው በራሱ አካል ነው፡፡ ይህ ማለት እጅ ከሰውነት አካላት ሳይለይ ዕቃን እንዲያነሣ ቃልም ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ አንድነት ሳይለይ የጠፋ በግ አዳምን ይፈልግ ዘንድ በማኅጸነ ማርያም በሥጋ ማርያም በፍጹም ተዋሕዶ ተገልጧል ማለት ነው እንጅ ከባሕርይ አባቱ ከአብና ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ አንድነቱ ተለይቶ ተዋሕዷል ማለት አይደለም፡፡ ስለዚህ በጊዜ ተዋሕዶ መንፈስ ቅዱስን አይሻም ማለት ስለዚህ ነው፡፡ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ሳይለይ በማኅጸነ ማርያም አድሯልና ቅብአቶች እንደሚሉት ለተዋሕዶ መንፈስ ቅዱስን የሚሻ አይደለም፡፡ ከዚህ ከተዋሕዶ በኋላ ሥጋና መለኮት አንድ አካል አንድ ባሕርይ ናቸው እንጅ ሁለት አካላት ሁለት ባሕርያት አይደሉም፡፡ ቅብአቶች እንደሚሉት ተዋሕዶ ሁለትነትን አጥፍቶ አንድነትን ለማምጣት ብቻ የተደረገ እንዳልሆነ በጋለው ብረት ምሳሌ ለመረዳት እንችላለን፡፡ ብረት ከእሳት ጋር ሲዋሐድ የየግል ገንዘቦቻቸውን የጋራ ገንዘቦቻቸው አድርገው ነው፡፡ ለዚያም ነው የማይቀጠቀጠው እሳት ከብረት ጋራ ስለተዋሐደ በመዶሻ የሚቀጠቀጠው ሆኖም ግን መቀጥቀጡ በብረቱ እንጅ በእሳቱ ላይ አይደርስበትም፡፡ ቅብአቶች  “ህማሙ ግርፋቱ በመለኮቱ ደርሶበታል ልትሉን ነውን” ይሉናል፡፡ እኛ ግን የሥጋው ሕማም ወደ መለኮቱ የሥጋው ረሃብ ወደ መለኮቱ የሥጋው ግርፋት ወደ መለኮቱ ያልፋል አንልም፡፡ የጋለን ብረት ቢቀጠቅጡት እሳት ላይ እንደማይደርስ ሁሉ የሥጋና የመለኮትም እንዲሁ ነውና፡፡ ፀሐይ ያረፈችበትን ግንድ ቢቀጠቅጡት ግንዱ ይቀጠቀጣል እንጅ ፀሐይ አትቀጠቀጥም እንደዚህም ሁሉ መለኮት የተዋሐደው ሥጋ በሥጋው ቢገረፍ ቢጠማ ቢራብ ቢቸነከር ቢቀበር በመለኮቱ አይደርሱበትም፡፡ ይህ ማለት ግን መለኮት የተለየው ሥጋ ተቀበረ፣ መለኮት የተለየው ሥጋ ተገረፈ፣ መለኮት የተለየው ሥጋ ተቀበረ፣ መለኮት የተለየው ሥጋ ተራበ ተጠማ ማለት አይደለም፡፡ አባቶቻችን እንዳስተማሩን ሥጋ ከመለኮቱ ባለመለየት ታመመ ሞተ ተራበ ተጠማ ተሰቀለ እንላለን አንጅ፡፡

ይቀጥላል…

Monday, June 27, 2016

“የቅብአት ምንፍቅና መደበቂያ ካባዎች” ክፍል 5

© መልካሙ በየነ
ሰኔ 20/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

በክፍል 4 ትምህርታችን መክበር የሚስማማው ሥጋ እንጅ መለኮት እንዳይደለ ተመልክተናል፡፡ በዚህ የማይስማሙት የቅብአት ምንፍቅና ተከታዮች ግን አሁንም ስድባቸውን ቀጥለዋል፡፡ እውነቱን የሚገልጥባቸውን አይፈልጉም እኛ ግን እውነታውን እንናገራለን ምሥጢረ ተዋሕዶንም እንመሰክራለን፡፡ “ወልድ በሰውነቱ ፍጡር ይባላል፡፡ ወልድንማ ፍጡር ብንለው እንደአርዮስ ክህደት አይሆንብንም ቢሉ አርዮስ በመለኮቱ ፍጡር ቢለው ክህደት ሆነበት እንጅ በሰውነቱ ፍጡር ቢለው ክህደት ባልሆነበትም ነበር፡፡ ነገር ግን በመለኮቱ ፍጡር ቢለው ክህደት ሆነበት” ወልደ አብ ገጽ 130-131 የሚለውን ጽሑፋቸውን እና “እንደ ዘርአ ብእሲ የሆነው ወልድ ነው ማለት እንዴት ነው ቢሉ፡፡ ከአባት ዘር ከእናት ደም ተከፍሎ ተዋሕዶ እንዲፈጠር ወልድም ከእግዝእትነ ማርያም በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከተከፈለ ደመ ድንግልና ጋራ ተዋሕዶ ተፈጥሯልና” ወልደ አብ ገጽ 127 የሚለውን ክህደት አሁንም ድረስ ይከራከሩበታል፡፡ “በሥጋው ፍጡር ካላልነውማ በመለኮቱ ታመመ በመለኮቱ ሞተ ትላላችሁ ማለት ነዋ!” ብለው ያልተጻፈውን ያነብባሉ፡፡ እኛስ አባቶቻችን እንዳስተማሩን እንዲህ እንላለን “ሰው ስለሆነ ተፈጠረ ሰው በመሆኑም ዓለምን ለማዳን ታመመ ቢባልም እርሱስ የአብ አንድ ልጁ ነው ፍጡርም አይባልም” ሃ.አበ ዘቄርሎስ ምእራፍ 76 ክፍል 35 ቁጥር 2 ስለዚህም ሥጋን የተዋሐደ አምላክ እንለዋለን እንጅ እኛስ ከተዋሐደ በኋላ ሥጋንና መለኮትን ከፋፍለን  በሥጋው ፍጡር ነው አንለውም፡፡ መታመሙ መሞቱ በሥጋው ነው ስንል በመለኮቱ ታመመ በመለኮቱ ሞተ ማለታችን አይደለም፡፡ መለኮትን የተዋሐደ ሥጋ ሞተ እንላለን እንጅ፡፡ መለኮት የተለየው ሥጋ አልተሰቀለም መለኮት የተለየው ሥጋ ወደ መቃብር አልወረደም መለኮት የተለየው ነፍስ ወደ ሲዖል ወርዶ ነፍሳትን አላወጣም መለኮት የተዋሐደው ነው እንጅ፡፡ ቃለ ግዘት ምእራፍ 120 ክፍል 3 ቁጥር 1 ላይ “እሱ ሰውን ፈጠረ ከዚህም በኋላ በእሱ በፍጡሩ እግዚአብሔር ቃል አደረበት የሚል ቢኖር ውጉዝ ይኹን” ይላል ሃይማኖተ አበው፡፡ ስለዚህም በዚህ ከላይ ባየናቸው ክህደቶቻቸው ለዘለዓለም የተወገዙ ናቸው፡፡ እነርሱ ግን የተዋሕዶ ትርጉም አልገባቸው ማለቱን የተረዳሁት ወልደ አብ ገጽ 232 ላይ የጻፉትን ድፍረት ስመለከት ነው፡፡ “ተዋሕዶ ክብር የሚያሳልፍ ንዴትን የሚያጠፋ መስሏቸው የቃልን ክብር ለሥጋ ካሳለፍን ብለው ለመንፈስ ቅዱስ ቦታ ቢያጡለት በተዋሕዶ ከበረ ቅብአት አልረባውም ብለው ተነሥተዋል፡፡ ለሊህ ምን ይመልሷል ቢሉ ተዋሕዶማ ሁለትነትን አጠፋ አንድነትን አጸና እንጅ ንዴትን አላጠፋም ክብርን አላሳለፈም” ይሉናል፡፡ ወገኖቼ አስቡት ይህንን ድፍረት ምሥጢረ ስላሴንና ምስጢረ ሥጋዌን ያልተማረ ሰው ካልሆነ በቀር እንዲህ የሚለውን ክህደት ባልሞከረውም ነበር፡፡ “የቃልን ክብር ለሥጋ ካሳለፍን ብለው ለመንፈስ ቅዱስ ቦታ ቢያጡለት” የሚለውን እንውሰደው እንግዲህ፡፡ በመጀመሪያ ለመንፈስ ቅዱስ ቦታ ቢያጡለት ማለት ምን ማለት ነው? ምን ዓይነት ቦታ ነው ለመንፈስ ቅዱስ ያጣንለት? በመቀጠል የቃል ክብር ከመንፈስ ቅዱስ ክብር ይለያልን ብንላቸው ምን ይሉን ይሆን? እነርሱ እንደሚሉት ከሆነ የቃል ክብር ከመንፈስ ቅዱስ ክብር የተለየ ነው፡፡ ለዚህም ነው “ለመንፈስ ቅዱስ ቦታ ቢያጡለት” ማለታቸው፡፡ ቃል ባለበት መንፈስ ቅዱስ የለም ማለት ክህደት ነው፡፡ ቃል ሥጋን የተዋሐደው ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ተለይቶ አይደለም፡፡ በቃል ሕልው ሆኖ የሚኖረው መንፈስ ቅዱስ በጊዜ ተዋሕዶም ሕልውናውን አላጣም፡፡ ስለዚህ የቃል ተዋሕዶ ከመንፈስ ቅዱስ ባለመለየት እንደሆነ እንናገራለን፡፡ ተዋሕዶ የቃልን ክብር ወደ ሥጋ ማሳለፍ ብቻ አይደለም ተዋሕዶ ማለት “የቃልን ገንዘብ ለሥጋ የሥጋንም ገንዘብ ለቃል ማድረግ” ነው፡፡ ቀጥለው “ለሊህ ምን ይመልሷል ቢሉ ተዋሕዶማ ሁለትነትን አጠፋ አንድነትን አጸና እንጅ ንዴትን አላጠፋም ክብርን አላሳለፈም” ይላሉ፡፡ ተዋሕዶ ሁለትነትን ለማጥፋት አንድነትን ለማጽናት ብቻ የተደረገ አይደለም፡፡ ሁለትነትን ለማጥፋትማ መዋሐድም ላያስፈልግ ይችል ነበር፡፡ ምክንያቱም በመቀላቀል በመደባለቅ ሁለትንትን አጥፍቶ አንድነትን አጽንቶ መኖር ይቻላልና፡፡ ምናልባት ጸሐፊው ዘመናዊውን ትምህርት ያልተማረ ይሆናል እንጅ ይኼ 1ኛ ክፍል ጀምሮ የሚሰጥ የአካባቢ ሳይንስ ትምህርት ነው፡፡ ልብ በሉ እንግዲህ ቀላል ምሳሌ ልስጣችሁ “አየር የምንለው ኦክስጅን፣ ናይትሮጅን፣ ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ… የመሳሰሉት በባሕርይ የተለያዩ የሆኑ ጋዞች ተቀላቅለው የሚገኙበት ነው፡፡ እነዚህ ከሦስት በላይ የሆኑ ጋዞች አንድነትን አጽንተው አየር የሚል ስም የተሰጣቸው በመዋሐድ ሳይሆን በመቀላቀል ነው፡፡ ያልተዋሐዱ በመሆናቸውም የኦክስጅን ገንዘብ ለናይትሮጅን የናይትሮጅንም ገንዘብም ለካርቦን ዳይ ኦክሳይድ ሊሆን አይችልም፡፡ የአንዱን ገንዘብ ለሌላው ገንዘቡ ለማድረግ የግድ መዋሐድ ያስፈልጋቸዋል” ስለዚህ ተዋሕዶ ያስፈለገው ሁለትነትን አጥፍቶ አንድነትን ለማጽናት ብቻ አይደለም፡፡ ተዋሕዶ ያስፈለገው የሥጋን ገንዘብ ለቃል የቃልንም ገንዘብ ለሥጋ ለማድረግ ነው፡፡ ሥጋ ክብርን የሚያገኘውም ከቃል ጋር ሲዋሐድ ብቻ ነው፡፡ ከተዋሕዶ በኋላ ይህ የሥጋ ነው ይህ የመለኮት ነው በማለት ልንለያየው አንችልም፡፡ ይህንንም ቀላል ምሳሌ ልስጣችሁ “ኦክስጅንና ሄድሮጅን ተዋሕደው ውኃን ይሰጣሉ፡፡ ከዚህ ከተዋሐዱ በኋላ ይህ ሃይድሮጅን ነው ይህ ደግሞ ኦክስጅን ነው ብለን መክፈል አንችልም፡፡ ምክንያቱም የሃይድሮጅን ገንዘቦች በሙሉ ለኦክስጅን የኦክጅንም ገንዘቦች በሙሉ ለሃይድሮጅን ሆነዋልና ” ይህ ለተማሩት ማስረጃ የሚሆን ቀላል ምሳሌ ነው፡፡ በእርግጥ ምሳሌዎች ሁሉ የመለኮትና የሥጋን ተዋሕዶ ያስረዳሉ ማለት አይደለም ትንሽ ፍንጭ ይሰጣሉ ለማለት ነው እንጅ፡፡ እንግዲህ የመለኮት ከሥጋ ጋር መዋሐድ ሁለትነትን ብቻ ለማጥፋት እንዳልሆነ በዚህ ተረዱ፡፡ አስቀድመን እንደተመለከትነው ሁለትነትን ብቻ ለማጥፋት ቢሆን ኖሮ መቀላቀልም ይችል ነበርና ነገር ግን በመቀላቀል ጊዜ  የአንዱ ገንዘብ ለሌላው አይሆንምና የሥጋን ገንዘብ ለቃል የቃልንም ገንዘብ ለሥጋ አድርጎ ሥጋን አምላክ ለማድረግ ተዋሐደ፡፡ ይህንንም ሃይማኖተ አበው ዘቄርሎስ ምእራፍ 78 ክፍል 48 ቁጥር 3 ላይ እንዲህ ይጽፍልናል “ካልተዋሐደስ እርስ በእርሱ በተካከለ ሥራ አንድ ሆኖ ባሕርዩ በመለኮት ላይ ተጨመረ እንዳልን ይቆጠራል፡፡ ሥጋ የመለኮትን ባሕርይ ወደ መሆን እንደተለወጠ ቃልም የሥጋን ባሕርይ ወደ መሆን እንደተለወጠ አይነገርም መለኮት ባሕርዩን ሊለቅ ሊለውጥ እንዳይቻል እንዲሁ ከፍጡራንም ወገን ማንኛውም የመለኮትን ባሕርይ ወደመሆን ሊለወጥ አይቻልም ሥጋ ፍጡር ግቡር ነውና” ይለናል፡፡ ስለዚህ ለሥጋ የጠቀመው የረባው እንዲከብር ያደረገው የቃል ከሥጋ ጋር መዋሐድ ነው፡፡ ሥጋ ከቃል ጋር በመዋሐዱ ነው ግዙፍ ሲሆን ረቂቅ አምላክ ሲሆን ሰው ምሉዕ ሲሆን ጠባብ መሆኑ እና መባሉ፡፡

ይቀጥላል… 

Thursday, June 23, 2016

“የቅብአት ምንፍቅና መደበቂያ ካባዎች” ክፍል 4

© መልካሙ በየነ
ሰኔ 16/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ባለፉት ክፍሎች የቅብአት ክህደት ለዓለም ሁሉ ተገልጦ ሕዝበ ክርስቲያኑ በግልጥ ክህደታቸውን እንዳይረዳ በሥውር ክህደታቸውን ለማስፋፋት ያመቻቸው ዘንድ ክህደታቸውን የደበቁባቸውን ካባዎች ተመልክተናል፡፡ በእነዚያ ተከታታይ ክፍሎች ላይም የ “ቅብአት” ምንፍቅና ቅልጥ ያደረጋቸው እህቶችና ወንድሞች ከተጻፈው ጽሑፍ ጋር የማይገናኙ የተለያዩ አስተያየቶችን በስድብ አጅበው ሰጥተዋል፡፡ እኛ ግን ግልጹን እንንገራችሁ ስለተዋሕዶ ዝም አንልም፡፡ ገና ብዙ እንላለን ገና ምኑን አይታችሁት፡፡ እናንተም ስደቡን እኛም እንሰደባለን!
በዚህ ክፍል የምናየው በ “ቅብአት” የከበረው ማን ነው? የሚል ይሆናል፡፡ እንግዲህ ባለፉት ክፍሎችም እንደተመለከትነው “ቀባ” የሚለው ቃል አንድ ዓይነት ፍቺ የለውም፡፡ “ቀባ” አከበረ ከፍ ከፍ አደረገ የሚለውን እንውሰድና እንመልከት፡፡ በ “ቅብአት” እምነት ውስጥ “ቀባ” የሚለው ቃል ከዚህ የዘለለ ትርጉም አይሰጠውም፡፡ “ቀባ” ብሎ አከበረ ከፍከፍ አደረገ የሚል ብቻ ነው ትርጉማቸው፡፡ እሽ እናንተ በተሰፋችሁበት ልክ እንሰፋ እና እንነጋገር፡፡ “ቀባ” ማለት አከበረ ከፍከፍ አደረገ ማለት ብቻ ነው ብለን እንከተላችሁ፡፡ ማን ነው የተቀባው? ማለትም ማነው ከፍ ከፍ ያለው?  ማነው የከበረው? የሚለውን ጥያቄ ግን እንድትመልሱልን እንጠይቃለን፡፡ ጥያቄየን ግን ተውኩት የጥያቄውን መልስ “ወልደ አብ” ከተሰኘው የምንፍቅና መጽሐፋችሁ ገጽ 233 ላይ አገኘሁት፡፡ “ቅብአቱስ እንደረባው ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እንዳስተካከለው” ብላችሁ የከበረው ከፍ ከፍ ያለው ወልድ (ቃል) እንደሆነ በክህደት በተሞላ ጽሑፋችሁ ጽፋችሁልናል፡፡  ቆዩ እንጅ ትንሽ ግን አይዘገንናችሁም? “ወልድ” ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ ለመስተካከል ነውን መወለድ ያስፈለገው? “ወልድ” በመጀመሪያ እግዚአብሔር አልነበረምን? በእውነት ኅሊና ላለው ሰው መክበርን ከፍ ከፍ ማለትን መስተካከልን ለመለኮት ቀጽሎ ይናገራልን? እንደፈለጋችሁት ማተም የሚችል ሰው ስላገኛችሁ ብቻ ይሆንን እንዲህ ያለውን ክህደት ለትውልዱ ያስቀመጣችሁት? ፈጣሪ ይቅር ይበላችሁ በፈሰሰው ደሙ በተወጋው ጎኑ ይቅር ይበላችሁ፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ስም ያውም በአንዲት ገዳማችን ስም እንዲህ ያለውን ምንፍቅና ለመጻፍ ያስደፈራችሁ አይዟችሁ ባይ በማግኘታችሁ ሳይሆን አልቀረም፡፡ የሆነው ሆነና “ወልድ” በቅብአት ከበረ ከፍ ከፍ አለ ስትሉ እንዴት አታፍሩም? መቼም ይህንን በመጽሐፋችሁ ያሰፈራችሁትን አትክዱም፡፡ በዚህ ብቻ አያልቅም ወገኖቼ የከበረው ወልድ እንደሆነ ቁልጭ እያደረጉ ነው የጻፉት፡፡ መስማት ካልከበዳችሁ ስሙት ያሉትን “እንደ ዘርአ ብእሲ የሆነው ወልድ ነው ማለት እንዴት ነው ቢሉ፡፡ ከአባት ዘር ከእናት ደም ተከፍሎ ተዋሕዶ እንዲፈጠር ወልድም ከእግዝእትነ ማርያም በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከተከፈለ ደመ ድንግልና ጋራ ተዋሕዶ ተፈጥሯልና፡፡ እንደ ዘርአ ብእሲ የሆነ ወልድ ነው ማለት ስለዚህ ነው” ወልደ አብ ገጽ 127፡፡  “ወልድ” እዚህ ላይ ፍጡር ሆኗል ማለት ነው ምንም ክርክር የሌለው ነጥብ ነው፡፡ እንግዲህ “ወልድ” ከእግዝእትነ ማርያም በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከተከፈለ ደመ ድንግልና ጋራ ተዋሕዶ ከተፈጠረ በኋላ አምላክ ለመሆን ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ ለመስተካከል “ቅብአተ መንፈስ ቅዱስ” አስፈለገው ክህደት ማለት ይቺ ነች እንግዲህ፡፡ አያችሁ ወገኖቻችን ሚጠት የሚባለው ክህደት ይኼ ነው እንግዲህ፡፡ ሚጠት ማለት መመለስ ማለት ነው፡፡ ወልድ አስቀድሞ አምላክ ነበረ ከድንግል ማርያም ሥጋን በተዋሐደ ጊዜ ተፈጠረ (ሰው ሆነ)  ከዚያም በቅብአተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ እና አምላክ ሆነ ወደ ቀደመው አምላክነቱ ተመለሰ ይሉናል፡፡ የቅብአት ክህደት እንግዲህ በዚህ ይጀምራል፡፡ ይህ ማለት እንደ በትረ ሙሴ ማለት ነው፡፡ የሙሴ በትር በእጁ ሲይዛት በትር ሲጥላት እባብ ሲያነሣት ተመልሳ እንደቀድሞው በትር ሆናለች በዚያ ምሣሌ ቅብአቶችም አምላክን እንደዛ አደረጉት፡፡ ቅብአቱ ረባው ጠቀመው ማለታቸውም ቅሉ ከአምላክ ጋራ (ከአብ እና ከመንፈስ ቅዱስ) ጋራ አስተካከለው ማለታቸው ነው፡፡ ሎቱ ስብሐት!
በዚህ ይቀጥሉና አርዮስን ጥሩ ዘመዳቸው ያደርጉታል፡፡ በእርግጥ እንዲህ አድርገህ ብትክድ ኖሮ እኮ እኛን ትመስለን ነበር ነው ለማለት የፈለጉት፡፡ ትንሽ የዝምድና መራራቅ ሊኖር ይችል ይሆናል በሰማይ ቤት ግን ለዘለዓለም መዛመዳቸው አይቀርምና ያው ዘመዳሞች ናቸው እንበል፡፡ “ወልድ በሰውነቱ ፍጡር ይባላል፡፡ ወልድንማ ፍጡር ብንለው እንደአርዮስ ክህደት አይሆንብንም ቢሉ አርዮስ በመለኮቱ ፍጡር ቢለው ክህደት ሆነበት እንጅ በሰውነቱ ፍጡር ቢለው ክህደት ባልሆነበትም ነበር፡፡ ነገር ግን በመለኮቱ ፍጡር ቢለው ክህደት ሆነበት” ወልደ አብ ገጽ 130-131 ይላሉ፡፡ አርዮስ እናንተን ሳያገኝ በመሞቱ ሳይሰማው አይቀርም ምክንያቱም ክህደቱን በሌላ ክህደት ታስተካክሉለት ነበርና፡፡ እኔን የገረመኝ ነገር እንዲህ እንደፈለጋችሁ ስትፈነጩ ዝም የተባላችሁበት ነገር ነው፡፡ ምን ዓይነት አዚም እንደለቀቃችሁብንም አይገባኝም፡፡ ጠቅለል ሲል መክበር ከፍ ከፍ ማለት የሚስማማው “ቃል” ሳይሆን ሥጋ ነው፡፡ ሥጋን የሚያከብረው ደግሞ ራሱ እከብር አይል ክቡር የሆነው “ቃል” ነው፡፡ ምክንያቱም ቃል እግዚአብሔር ነውና! ዮሐ 1÷1
ለዛሬ በዚሁ ልቋጨው እንደተለመደው መጽሐፉን እያነበባችሁ ጠብቁኝ፡፡
ይቀጥላል፡፡

Wednesday, June 22, 2016

“የቅብአት ምንፍቅና መደበቂያ ካባዎች” ክፍል 3

© መልካሙ በየነ
ሰኔ 15/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ባለፉት 2 ክፍሎች በቅብአት ምንፍቅና የተጠመዱ ሰዎች ህዝበ ክርስቲያኑን ለማታለል የተደበቁባቸውን ሶስት ካባዎች ተመልክተናል፡፡ የመጀመሪያው የጌታችን የልደት ቀን በዓል አከባበር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የጾመ ነቢያትና የጾመሐዋርያት መግቢያ ቀናትን ነው፡፡ በመጨረሻ የተመለከትነው የመደበቂያ ካባ ደግሞ “ቀባ” እና ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ቃላትን ነው፡፡ ከዚህ ጋርም በተያያዘ ከመጻሕፍት ላይ እነዚህን ቃላት በመፈለግ እዚህ ቦታ ላይ እንዲህ ይላል” ማለታቸውን እንዲሁም ጥንታዊ እምነት ቅብአት ነው ለማለት “በብራና መጻሕፍት ላይ እንዲህ ተጽፏል” እያሉ ህዝቡን ለማደናገር  መሞከራቸውን ተመልክተናል፡፡ በዚህ ክፍል የምንመለከተው “ቅብአት” የሚል ቃል በመጻሕፍቶቻችን ውስጥ ይገኛልን? የቃሉ ትርጉምስ እነርሱ እንደሚሉት ነውን? የሚለውን ነው፡፡
በአሥራው መጻሕፍቶቻችን እንዲሁም በአዋልድ መጻሕፍቶቻችን የ”ቅብአት” ነገር ብዙ ጊዜ ተጽፏል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ በተለያዩ ቦታዎች በመጻሕፍተ ሊቃውንትም እንዲሁ በተለያዩ ሊቃውንት ጽሑፎች ላይ “ቅብአትን” ያነሣሉ፡፡ ይህ ቅብአት ምንድን ነው? ስትሉ ግን እምነት አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኙ ቃላት እንደቃላቸው በቀጥታ አይፈቱም አይተረጎሙም፡፡ “ቅብአት” ን በተለያየ መልኩ ሊቃውንቱ መተርጉማኑ ይፈቱታል ይተረጉሙታል፡፡ “ቀባ” ብለው አከበረ ከፍ ከፍ አደረገ፤ “ቀባ” ብለው አነገሠ ሾመ ሥልጣን ሰጠ፣ “ቀባ” ብለው አዋሐደ እያሉ ይተረጉሙታል ይፈቱታል፡፡ የቅብአት እምነት ተከታዮች ደግሞ “ቅብአት” የሚለውን ቃል ወስደው “አብ ወልድን በመንፈስ ቅዱስ ቅብአትነት አከበረው” ብለው ይተረጉሙታል ውድቀቱ ከዚህ ይጀምራል፡፡ ወገኖቼ ግልጽ ይሁንላችሁ በደንብ ተረዱት፡፡ ወደሌላ ምሥጢር ሰደደኝ እንጅ ለዚህ ሁሉ እምነት መፈልፈል ምክንያቱ የኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ መልበስ ነው፡፡ ዘመኑ ቅርብ ቢሆንም ቢሆንም ቅሉ ቅብአት ከሳጥናኤል ቀጥሎ የሚመጣ ክህደት ነው፡፡ በመጀመሪያ ሳጥናኤል እኔ ፈጣሪ ነኝ አለ፡፡ በመቀጠል በኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ መልበስ ምክንያት ከተሰናከሉት(ክህደት ካፈለቁት) ወገኖች ግንባር ቀደም የሚሆኑት “ቅብአቶች” ናቸው፡፡ እስላሞች በዕለተ ስቅለት ጊዜ የተሰቀለው ነቢይ ነው በማለታቸው አምላክነቱን በመካዳቸው እስላም እንደተባሉ ሕማማተ መስቀል ያስነብበናል፡፡ ፕሮቴስታንቶችም የተሰቀለው በደሙ ያዳነን ኢየሱስ ክርስቶስ አማላጅ ነው ብለው በማመናቸውን ክህደትን ጀምረዋል፡፡ ጸጋዎችም በተጠመቀ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ አደረበትና አምላክ ሆነ ብለው በማመን ክህደታቸውን ጀምረዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስ ከተወለደ በኋላ የካዱ ናቸው ቅብአቶች ግን ሲወለድ ጀምረው ክህደት ጀምረዋል፡፡ ምን ይላሉ “ኢየሱስ ክርስቶስ በማኅጸን በሰውነቱ ከአብ በቅብአተ መንፈስ ቅዱስ ተወለደ” ወልደአብ ገጽ 216 ቅብአቱ ምን እንዳደረገው ሲገልጹ “ቅብአቱስ እንደረባው ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እንዳስተካከለው” ብለው ክደዋል ወልደ አብ ገጽ 233፡፡ ስለዚህ የቅብአት ክህደት የሚጀምረው ገና ከማኅጸነ ማርያም ሲወጣ ጀምሮ ነው ማለት ነው፡፡ በእውነት ልብ በሉ ወገኖቸ ቃለ እግዚአብሔር ወልድ እግዚአብሔር አይደለምን? ዮሐንስ ወንጌላዊ ለመናፍቃን መዶሻ በሆነው መለኮትን በረቀቀ መልኩ በገለጸበት ወንጌሉ ምእራፍ 1 ቁጥር 1 ላይ “በመጀመሪያ ቃል ነበረ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ” ብሎ ይደመድመዋል፡፡ ስለዚህ ቃል ራሱ የባሕርይ አምላክ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ የተካከለ አምላክ ነው፡፡ ቃል ራሱ እግዚአብሔር ነውና፡፡ እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ እነርሱ ግን ከአምላክነት ዝቅ አድርገውት “ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ የተካከለው በቅብአተ መንፈስ ቅዱስ ነው” ብለው ክህደታቸውን በዚህ ጀምረዋል፡፡
ወደቀደመ ነገራችን እንመለስና “ቀባ” የሚለው ቃል ትርጉሙ አንድ ብቻ አይደለም፡፡ በተለምዶ የምናውቀውን መቅባት የሚያስረዳ ብቻ አይደለም፡፡ ነገሥታትን አነገሠ ሲል ቀባ ይላል፡፡ ሥጋን አከበረ ሲል ቀባ ይላል፡፡ ሥጋን ተዋሐደ ሲል ቀባ ይላል፡፡ ሥጋን ከፍ ከፍ አደረገ የባሕርይ አምላክ የባሕርይ ገዥ አደረገ ሲል ቀባ ይላል፡፡ ይህ ሁሉ የየራሱ የትርጉም ቦታና ጊዜ አለው፡፡ ቀላል ምሳሌ ልስጣችሁ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ጽዮን” ፣ “መማለድ” የሚሉ ቃላትን ብዙ ቦታ እናገኛቸዋለን፡፡ ጽዮን አንዳንድ ቦታ ከተማ አንዳንድ ቦታ ተራራ አንዳንድ ቦታ ድንግል ማርያም አንዳንድ ቦታ ታቦት ሆኖ ይተረጎማል እንጅ “ጽዮን” የሚለውን ቃል በሙሉ ለተራራ ብቻ አልያም ለከተማ ብቻ አልያም ለድንግል ማርያም ብቻ አልያም ለታቦት ብቻ ተሰጥቶ አይተረጎምም አይፈታምም፡፡ “መማለድ” የሚለው ቃልም እንዲሁ ተመሣሣይ አፈታት አለው፡፡ ነገር ግን አፈታቱ አተረጓጎሙ አንድ ብቻ ነው ካልን ሮሜ 8÷34 ን ወስደን ወልድ ይማልድልናል፤ ሮሜ 8÷26 ን ወስደን ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ይማልድልናል ኤር 7÷25 ን ይዘን ደግሞ እግዚአብሔር ይማልዳል ልንል ነው ማለት ነው፡፡ ታዲያ አምላካችን ማን ሊሆን ነው? ስለዚህ በተመሳሳይ መልኩ ከ“ቅብአት” ጋራ ተያይዞ የተገለጹት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃላትም በሙሉ የየራሳቸው የአተረጓጎም ስልት አላቸው የሚተረጎሙትም በተለያየ ቦታ የተለያየ ፍችን ወስደው ነው፡፡ ዳዊትና ሳኦል ተቀቡ ሲል መቸም የባሕርይ አምላክ ሆኑ ተብሎ አይፈታም፡፡ በሀገራችንም እንደ ላሊበላ እንደ ቴዎድሮስ እንደ ምኒልክ እንደ ኃይለ ሥላሴ ያሉ ነገሥታት ተቀብተዋል ስንል የባሕርይ አምላክ ሆነዋል ማለታችን እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ እኛም እንዲሁ በ40 በ80 ቀናችን ተቀብተናል ማለት ልጅነትን አግኝተናል ማለት እንጅ የባሕርይ አምላክ ሆነናል ማለት አይደለም፡፡ ስለዚህ አፈታቱና አተረጓጎሙ ይለያያል፡፡ ሊቃውንቱ “ቀባ” የሚለውን ቃል “ሥጋን አከበረ ሥጋን ከፍከፍ አደረገ ሥጋን ተዋሐደ” ብለው አርቅቀው አመስጥረው አብራርተው አስረድተው ይተረጉሙታል፡፡ ስለዚህ “ቀባ” ማለት ቅብአትን አፍስሶ ወልድን ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ማስተካከል ማለት አይደለም፡፡
ወደ ክህደት መጽሐፋቸው ልገባ ስለሆነ እንደተለመደው “ወልደ አብ” ን እያነበባችሁ ጠብቁኝ፡፡
ይቀጥላል...

Tuesday, June 21, 2016

“የቅብአት ምንፍቅና መደበቂያ ካባዎች” ክፍል 2

© መልካሙ በየነ
ሰኔ 14/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

በክፍል 1 የቅብአት ምንፍቅና የተደበቀባቸውን ሁለት ጉዳዮች አንሥተን ተመልክተናል፡፡ የጌታችን የልደት ቀን በዓል አከባበርና የአጽዋማት መግቢያ ላይ በሰፊው ለማየት ሞክረናል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ቀኖና በመሆናቸው የቀደሙ አባቶቻችን በሰሩልን በቀየሱልን በሄዱበት በተመሩበት መንገድ ብቻ መጓዝ እንደሚገባን ተገንዝበናል፡፡ ይህንን ማንሣት ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት ልዩነታችንን የቀኖና ብቻ በማስመሰል ህዝበ ክርስቲያኑን በማታለል ላይ በመሆናቸው ነው፡፡ ስለዚህ በቀኖና ጉዳይ ላይ በቤተክርስቲያናችን የሥልጣን እርከን የበላይ የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ የቀደሙ አባቶቻችን ባቆዩን መልኩ እንድንቀጥል በወሰነልን መንገድ እንሄዳለን፡፡ በመሆኑም ቀድሞ በነበረው ሥርዓት ወደፊትም እንቀጥላለን ማለት ነው፡፡ በዚህ ክፍል የምንመለከተው መጻሕፍትን አብነት አድርገን እንከራከራለን በሚሉት የቅብአት ምንፍቅና አራማጆች ዙሪያ ነው፡፡ መጻሕፍትን እንደፈለግነው መተርጎም አንችልም፡፡ ስለዚህ እንደ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ “የሚመራኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል?” የሐዋ 8÷31 ማለት ያስፈልገናል፡፡ ጃንደረባው ፊደል ያልተማረ ሆኖ አይደለም ተምሯል የሚያነበው የመጽሐፍ ምሥጢር ግን ፊደላትን ከማዎቅ በላይ ነውና ይህንን ቃል ተናገረ፡፡ ስለዚህ ዝም ብለን እንዴት እንደሚተረጎም ሳንረዳ ምክንያተ ጽሕፈቱን ሳናውቅ የመጻሕፍት ቃላትን እንዲህ ማለት ነው ብለን መተርጎም አንችልም፡፡
የቅብአት እምነት አራማጆች ሙሉ ጊዜያቸውን ያቃጠሉት ጉባኤ ቤት በመማር አልያም ሊቃውንቱን በመጠየቅ ወይም ትርጓሜውን በማመስጠር አይደለም ፕሮቴስታንቶች ኢየሱስ ክርስቶስን አማላጅ ለማለት “አማለደ”፤ “ለመነ” ፣“አስታረቀ” ወዘተ የሚሉትን ቃላት ፍለጋ እንደደከሙ ሁሉ የቅብአት እምነት አራማጆችም “ቅብአት”፣ “ተቀባ”፤ “ቀባ”፣ “ቀባው”፣ “አስቀባው” ወዘተ እና የመሳሰሉትን ከ “ቀ” እና ከ “በ” ፊደላት የተጣመሩ ቃላትን ፍለጋ ብቻ ነው፡፡  ለዚህም ነው የቃሉን ትርጉም ሳይመለከቱ “እዚህ ቦታ ላይ ቀባው ይላል” ፣ “እዚህ ቦታ ላይ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ቀባው ይላል” ወዘተ እያሉ ራሳቸውን እያታለሉ የሚገኙት፡፡ የሚጠቅሱት ጥቅስ ደግሞ ከ “አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ የግእዝ መዝገበ ቃላት” ወይም ደግሞ ከ “ገብረ መድኅን እንዳለውን የኑፋቄ መጽሐፍ ወልደ አብ” ብቻ ነው፡፡ አንድምታቸው “ወልደ አብ” ማብራሪያቸው ደግሞ “መዝገበ ቃላት” ነው፡፡ በእውነት እንደ ሰው ማሰብ ከቻልን ለመሠረተ እምነት የአንድ ሰው መጽሐፍ ያውም የቋንቋ ማስተማሪያ መዝገበ ቃላት ሊጠቀስ እንዴት ይችላል? እሱንም እሽ እንቀበላችሁ ጥቀሱት፡፡ “ወልደ አብ” እንዴት ማስረጃ ሆኖ ይጠቀሳል? ምክንያቱም “ወልደ አብ” የታተመው ትናንትና ነውና፡፡ ስንት ቀደምት መጻሕፍት እያሉ የትናንትናውን የ “ገብረመድኅን እንዳለው” ን ተረት እንደማጣቀሻ መጠቀም ጅልነት ካልሆነ በቀር ምን ሊባል ይችላል?
በእርግጥ ሌሎችም የሚጠቃቅሷቸው መጻሕፍት አሉ ያውም የብራና ናቸው አሉ፡፡ ህዝቡን ለመሸወድ “የብራና መጽሐፍ ገጽ እዚህ ላይ እንዲህ ይላል” ይላሉ፡፡ ሕዝቡ የሚረዳው አንድ ነገር አለ እሱም ምንድን ነው “የብራና መጽሐፍ ማለት ቀደምት መጽሐፍ ነው” የሚል ነው፡፡ ይህን አስተሳሰብ ስለሚያውቁ ነው እንግዲህ በድክመታችን ገብተው የራሳቸውን ምንፍቅና ለመዝራት የብራና መጽሐፍ ወዘተ የሚሉት፡፡ ወገኖቼ በዚህ እንዳትሸወዱ የብራና መጻሕፍት የሚጻፉት ከፍየል ቆዳ ነው ዛሬ ድረስ ፍየሎች አሉ ቆዳቸውም አለ፡፡ ስለዚህ ዛሬም መጻፍ እንችላለንና ይህ ቀደምትነትን ያሳያል ብላችሁ እንዳትሸወዱ፡፡ እነርሱ የሚጠቅሷቸው መጻሕፍት ቀደምት ላለመሆናቸው ማስረጃው “ደብረ ወርቅ ማርያም” እና “ቆጋ ኪዳነ ምሕረት” ብቻ የሚገኙ መሆናቸው ነው፡፡ ብራና ላይ የተጻፈውን ሁሉ ወረቀት ላይ ማስፈር ይቻላል፡፡ ወረቀት ላይ ያለውንም ሁሉ እንዲሁ ብራና ላይ ማስፈር ይቻላል፡፡ ስለዚህ ቁምነገሩ የብራና የወረቀት መሆኑ ላይ አይደለም፡፡ ምክንያቱም “ድንግል ማርያም አታማልድም” ብሎ ብራና ላይ መጻፍ ይቻላል፡፡ በመሆኑም ብራና ላይ ስለተጻፈ ብለን  የዓለም እናትን ወላዲተ አምላክ እመብርሃንን የጭንቅ ቀን ደራሽ እናታችንን አታማልድም ብለን አንናገርም፡፡ “ወልደ አብ” የተሰኘውን መጽሐፋቸውንስ በብራና ጽፈው ቀደምት ነው እያሉ ስላለመሆናቸው ምን ማረጋገጫ አለን? ስለዚህ ብራና ኑፋቄን አይቀበልም ብለን ስለማናምን እውነተኛ መጻሕፍት ላይ ብቻ እናተኩራለን፡፡ አሁን እንደመግቢያ ይህን የምጽፍላችሁ ወደ ዋናው ጉዳያችን ስንገባ እነዚህን ጉዳዮች ልብ እንድታደርጉ ስለምፈልግ ነው፡፡ “ወልደ አብ” የተሰኘውን የኑፋቄ መጽሐፋቸውን እስከዛው ድረስ እያነበባችሁ እንድትቆዩኝ አሁንም አሳስባችኋለሁ፡፡ የቅብአት እምነት ተከራካሪ ወገኖችም በትህትና ያለመሰዳደብ እውነቱ ላይ ብቻ አተኩረን እንድንነጋገር አሳስባችኋለሁ፡፡
ይቀጥላል…

Monday, June 20, 2016

“የቅብአት ምንፍቅና መደበቂያ ካባዎች” ክፍል 1

© መልካሙ በየነ
ሰኔ 13/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

እንኳን ለጾመ ሐዋርያት በሰላም እና በፍቅር አደረሳችሁ አደረሰን!

ዛሬ ዛሬ ማንነታቸውን ይፋ ማድረግ ጀምረዋል፡፡ ትምህርታቸውንም ከኩሽና ቤት ወደ አደባባይ አውጥተውታል፡፡ በግልጽ ማስተማር መከራከር ጀምረዋል፡፡ አልፎ ተርፎም ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን መሳደብ መንቀፍ ጀምረዋል፡፡ መናፍቃኑ!
እነዚህን ልዩ የሚያደርጋቸው በቤተክርስቲያናችን ጥላ ሥር ተጠልለው ከበላነው በልተው ከጠጣነው ጠጥተው እኛ በሠራነው ሥርዓት ተሠርተው ለእኛ በተሾመልን ጳጳስ ደቁነው ቀስሰው ጰጵሰው የሚገኙ መሆናቸው ነው፡፡ በብዛት ሰፍረው የሚገኙት ደግሞ በጎጃም ጥቂት አካባቢዎች ውስጥ ነው፡፡ ከዚህ በፊት አስተምህሯቸው በግልጽ አይታወቅም ነበር፡፡ ተከታዮቹም የእናት እና የአባቴ እምነት ነው ብለው ክርር ከማለት ባለፈ ምሥጢራትን አያውቁም ነበር፡፡ የየዋሃኑም መከራከሪያ ሆኖ የቆየው የጌታችን የልደት በዓል ቀን በ28 እና በ29 ይከበራል ወይስ ደግሞ በ29 ብቻ ይከበራል የሚለው የመከራከሪያ ነጥብ ስለነበር ለብዙዎቹ ልዩነት ያለን በ4 ዓመት አንድ ቀን ብቻ ይመስላቸው ነበር፡፡ ስለአጽዋማት የሚያውቁት ደግሞ በጾመ ነቢያት እና በጾመ ሐዋርያት መግቢያ ላይ ብቻ ያለ ልዩነት  አድርገው ይቆጥሩት ስለነበር በዓመት ሁለት ጊዜ ብቻ የሚፈጠር የአጿጿም ችግር ይመስላቸው ነበር፡፡ ዛሬ ግን ሊደበቅ የማይችል በምንም በማንም ሊሸፈንና ሊከለል የማይችል አደባባይ ላይ የወጣ ምንፍቅና  ቅ--ብ---አ---ት፡፡
ዛሬ ላይ በልደት በዓልና በአጽዋማት መግቢያ ላይ የምንከራከርብት ጊዜ ላይ አይደለንም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ጉዳዮች ቀኖና ቤተክርስቲያን ናቸው፡፡ አድርጉ ፈጽሙ በተባልንበት ቀን የምናደርጋቸው በተከለከልንባቸው ቀናት ደግሞ የምንቆጠብባቸው የምንታቀብባቸው ናቸው፡፡ ይህንን ደግሞ እንድናደርግ ወይም እንዳናደርግ ቤተክርስቲያናችን ስልጣንና ኃላፊነት የሰጠችው አካል አለ እርሱም ቅዱስ ሲኖዶስ ብቻ ነው፡፡ ልደትን በታህሳስ 28 ማክበራችን አያጣላንም ምክንያቱም እንኳን ምሥጢር እያለው ይቅርና መስከረም 1 ወይም ጥቅምት 30 ወይም ደግሞ ሰኔ 24 ወይም ሚያዝያ 7 ወይም ደስ ያላችሁን ቀን መርጣችሁ የጌታችንን ልደት አክብሩ ብንባል ኖሮም እናደርገው ነበር እናከብረውም ነበር፡፡ ጌታችን በየዓመቱ የሚወለድ ሆኖ ነው እንዴ እያከበርነው ያለነው? አይደለም፡፡ የአጽዋማት መግቢያም እንዲሁ ነው፡፡ የነቢያት ጾም በህዳር 15 የሐዋርያት ጾም ደግሞ ከበዓለ ጰራቅሊጦስ በነጋታው ሰኞ እንድንጀምር ሥርዓት ተሠራልን በዚያ ሥርዓት እንመራለን እንተዳደራለን፡፡ አለቀ ይህ ምንም አያከራክርም ምክንያቱም ቀኖና ስለሆነ፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ከቀደሙ አባቶቻችን እና ከመጽሐፎቻቸው ጋር በማይጣላ መልኩ አድርገው በወሰኑልን ውሳኔ የምንፈጽመው ነው፡፡ እነዚህ የቅብአት ምንፍቅና አራማጆች የሚጠቅሱት ነገር አለ “ልደት በዘመነ ዮሐንስ አንድ ቀን ወደ ኋላ ከተመለሰ ጥምቀት ግዝረት ለምን አንድ ቀን ወደኋላ አይመለሱም” የሚል ነው፡፡ የእነርሱ ደጋፊ የሆኑት ጳጳስም “ልደት በዘመነ ዮሐንስ አንድ ቀን ቀንሶ በታህሳስ 28  ይከበር የምትሉ እናንተ ልደታችሁን ስታከብሩ አንድ ቀን ቀንሳችሁ ነውን? ታህሳስ 29 የተወለደ ሰው በዘመነ ዮሐንስ ልደቱን ታህሳስ 28 ያከብራልን?” ብለዋል፡፡ መልካም ነው! እኔ ግን ግርም ድንቅ የሚለኝ ነገር አለ፡፡ አሰቀድሜ እንደተናገርኩት ይህ የቀኖና ጉዳይ ነው ይህን መፍታት የሚችል ራሱን የቻለ አካል አለው፡፡ አይደለም ታህሳስ 28 ከ365ቱ ቀናት መካከል አንዱን ቀን መርጠው የጌታችን ልደት በዚህ ቀን ይከበር ብለው ካሉን ግዴታችን ነውና እናከብረዋለን፡፡ ምክንያቱም የጌታችን ስቅለት፤ ትንሣኤ እና ዕርገት  በጥንተ ስቅለት፣ በጥንተ ትንሣኤ እና በጥንተ ዕርገት እያከበርናቸው ስላልሆነ ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ የ2008 ዓ.ምን ስቅለት፣ ትንሣኤና ዕርገት ቀን አስቡት፡፡ ጥንተ ስቅለቱ መጋቢት 27 ጥንተ ትንሣኤው መጋቢት 29 ጥንተ ዕርገቱ ግንቦት 8 ነው እኛ ግን ስቅለቱን ሚያዝያ 21 ትንሣኤውን ሚያዝያ 23 እንዲሁም ዕርገቱን ሰኔ 2 ቀን አከበርን ለምን? ቀኖና ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ ወደኋላ መለስ ብላችሁ በየዓመቱ እነዚህን በዓላት መቼ መቼ እንዳከበርናቸው ተመልከቱ፡፡ በየዓመቱ ይለያያሉ ዕለታቸው አይቀየርም እንጅ ቀናቸው ይቀያየራል፡፡ ታዲያ በአንድ የልደት ቀን አከባበር ላይ ከምንነታረክ ለምን እነዚህንስ አንከራከርባቸውም፡፡ ስለዚህ በልደት በዓል አከባበርና በአጽዋማት መግቢያ ላይ ምንም መከራከሪያ ልናነሣ አይገባንም፡፡ ምክንያቱም እኛ ታዛዦች እንጅ አዛዦች አይደለንምና አድርጉ በተባልነው ቀን ማድረግ ብቻ ነው ሥራችን፡፡ ስለዚህ እነዚህ ነገሮች ለቅብአት ምንፍቅና የመደበቂያ ካባዎች እንጅ መሠረታዊ ነጥቦች አይደሉም፡፡ ህዝበ ክርስቲያኑም ማስተዋል የሚገባው ይህንን ጉዳይ ነው፡፡ ዋናው ጉዳያችን መሆን ያለበት አስተምህሮ ላይ ወይም ዶግማ ላይ ነው፡፡ ዶግማን ማሻሻል የሚችል አካል የለም፡፡ ምክንያቱም ስታምን የምትቆይበት ካላመንክ ደግሞ ተለይተህ የምትወጣበት መሠረተ እምነት ነውና፡፡ ለሲኖዶስ ቀኖናን የማሻሻልም የመለወጥም የመቀየርም ስልጣን አለው ለዶግማ ግን ማንም ቅንጣት ታህል የማሻሻል የመለወጥ የመቀየር ሥልጣን አልተሰጠውም፡፡ ስለዚህ መሠረታዊ ነጥቦቻችን መከራከሪያዎቻችን መሆን ያለባቸው አስተምህሮ ላይ ነው፡፡ አስተምህሯቸውን ደግሞ በራሳቸው ባሳተሙት መጽሐፋቸው ላይ እናገኘዋለን፡፡ ያ አስተምህሮ በእውነት እኛ የተዋሕዶ አማኞች የምንከተለው ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ወደፊት በዝርዝር የምንመለከተው ስለሚሆን ከላይ በጠቀስኳቸው ጉዳዮች ላይ እንደመከራከሪያ አድርጋችሁ ጊዜ እንዳታጠፉ እጠይቃለሁ፡፡ የቅብአት ምንፍቅና አራማጆችም ሳትቸኩሉ በማስተዋል ለስድብ ሳትፈጥኑ ራሳችሁን በመመርመር ስህተቶቻችንን እየተማማርን እንድንቀጥል አሳስባችኋለሁ፡፡ እስከዚያ ድረስ ግን “ወልደ አብ” የተሰኘውን መጽሐፋቸውን እያነበባችሁ ጠብቁኝ፡፡
ይቀጥላል…

Monday, June 13, 2016

ጾመ ሐዋርያት

© በመልካሙ በየነ
ሰኔ 06/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

ጾመ ሐዋርያት ከሰባቱ አጽዋማት መካከል አንዱ ነው። ይህ ጾም ሐዋርያት መንፈስቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ለትምህርት ወደ ዓለም ከመሄዳቸው አስቀድመው ለሥራቸው ሁሉ መጀመሪያ አድርገው የጾሙት ነው። ይህንን ሲገልጽ ፍትሐነገሥት አንቀጽ 15 ቁጥር 586 ላይ "ዳግመኛም ስለ ሃምሳኛው ቀን አከባበር ሙሴ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቀበለውን ሕገ ኦሪት ለሕዝቡ ከማስተማር በፊት እንደጾመ ጌታችንም በርሱ ላይ መንፈስ ቅዱስ ከወረደ በኋላ የርሱን ሕግ ለሕዝብ ከማስተማሩ አስቀድሞ እንደዚሁ ጾመ፡፡ ሐዋርያትም በበዓለ ሃምሳ መንፈስ ቅዱስ በወረደላቸው ጊዜ ሕገ ወንጌልን ለሕዝብ ከማስተማራቸው አስቀድሞ እንደዚሁ ጾሙ፡፡ እኛም በዚህ በእነርሱ ተመራን" ይላል። በበዓለ ሃምሳ ጾምና ስግደት የለም ይኼውም ማቴዎስ ወንጌል ምእራፍ 9 ቁጥር 15 ላይ እንደተጻፈው ነው።  ፍትሐ ነገሥቱም ይህንን ቃል ወስዶ አንቀጽ 15 ቁጥር 579 ላይ እንዲህ ብሏል። ጌታ ስለ ራሱ እንዲህ አለ “ሙሽራውን ከእነርሱ ለይተው በወሰዱት ጊዜ ያንጊዜ ይጾማሉ”። በዚህም መሠረት ጾም መጾም ተገቢ እንደሆነ እነሆ ተነገረ። የጾምን አስፈላጊነት አበው እንዲህ ይገልጹታል ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 15 ቁጥር 564 ላይ "ጾምስ በሕግ ውስጥ በታወቀው ጊዜ የሰው ከምግብ መከልከል ነው በደሉን ለማስተሥረይ ዋጋውን ለማብዛት እርሱን ወዶ ሕግን ለሠራለት እየታዘዘ የፈቲውን ኃይል ያደክም ዘንድ ለነባቢት ነፍስም ትታዘዝ ዘንድ" በተጨማሪም ቁጥር 573 "ጾምስ የሥጋ ግብር ነው ምጽዋት የገንዘብ ግብር እንደሆነ፡፡ ሕግ ጾምን ያስወደደው የፈቲው ጾር ትደክም ዘንድ ለነባቢት ነፍስም ትታዘዝ ዘንድ ነው፡፡ ጸሎትን ያሻው ፈቃድ ለልብ የቁጣ ኃይል እንድትታዘዝ እንደሆነ" ቁጥር 574 ላይም "ጾም ይረባናል ብለን ከመጾማችን የተነሣ መንፈሳውያንን እንመስላለን ከመሰልናቸውም የሚመስሉትን ለመምሰል ይቻላል፡፡ ዳግመኛም ጿሚው የረኃብን ችግር ያውቅ ዘንድ ለተራቡትና ለሚለምኑት ይራራላቸው፡፡ ዳግመኛም በፅኑዕ ፈቃድ ሁኖ ሊመገበው ሥጋውንና ደሙን ይቀበል ዘንድ ነው መቀበሉም በሥጋዊና በነፍሳዊ ትጋት ይሁን ዳግመኛም ከእንስሳዊ ባሕርይ ተለይቶ የጾምን ሥርዓት ጠብቆ ከሰው ወገን ደግሞ በጸሎት የተለየ ሁኖ ስለአጽዋም በተሠሩት ሕጎች የፀና ሁኖ በሁለንተናው እግዚአብሔርን ያምልከው"ይላል። በዚህም መሠረት ለክርስቲያኖች 7 አጽዋማት ታዘዙ። ከእነዚህ መካካል አንዱ ጾመ ሐዋርያት ወይም የሰኔ ጾም ብለን የምንጠራው ነው። ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 15 ቁጥር 569 ላይ "ከዚህም ቀጥሎ ከበዓለ ሃምሳ ቀጥሎ ያለ የሐዋርያት ጾም ነው፡፡ ፋሲካው በጴጥሮስና በጳውሎስ በዓል ሐምሌ 5 ቀን ነው" ተብሏል። አባቶቻችን እንደሰሩልን ሥርዓት መሠረት የዚህ ጾም መጀመሪያ በዓለሃምሳ እንደተፈጸመ የመጀመሪያው ሰኞ ነው። ይህም ማለት አጽናኝ መንፈስ ቅዱስ ከወረደበት ከጰራቅሊጦስ በዓል ቀጥሎ ባለው የመጀመሪያው ሰኞ ይጀመራል ማለት ነው። ነገር ግን አንዳንድ ወገኖች ለመብላት ካላቸው ልዩ ፍቅር የተነሣ የፍትሐ ነገሥቱን ትእዛዝ በሙሉ ሳያነቡ ለራሳቸው እንደሚገባ አድርገው ተርጉመው ከበዓለ ሃምሳ በኋላም ሌላ 7 ቀናትን ይበላሉ። ይህንንስ ከየት አግኝተውት ነው ቢሉ ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 15 ቁጥር 580 ላይ "በዓለ ሃምሳን ከጨረሳችሁ በኋላ ዳግመኛ ሰባት ቀን ሌላ በዓል አድርጉ ከዚህም ቀጥሎ ከአረፋችሁ በኋላ ጹሙ" የሚለውን ይዘው ነው። ነገር ግን በዓልን በማድረግ የሚጾሙ አጽዋማት አሉና በዓል አድርጉ አለ እንጅ ብሉበት አላለም። ለዚህም ሲያስረዳ ቁጥር 581ላይ  "እግዚአብሔር ይቅር ይበለውና ይህን መጽሐፍ ከሰበሰበው የተመረጠ ከሆነው መምህር ቃል የተገኘ ነው፡፡ የዚህ ሳምንት ምልክት ግን ልንበላበት እንደማይገባ እነሆ ረቡዕንና ዓርብን እንድንጾም ያዘዘበት አንቀጽ አለ ዳግመኛም በዓለ ሃምሳ ልደት ጥምቀት ቢውልባቸው አትጹሙ ብሎ ያዘዘበት አንቀጽ አለ፡፡ ስለዚህ ሳምንት ግን አልተናገረም፡፡ ሊበሉባቸው በሚገባ ቀኖች ውስጥ ሊጾሙባቸው የማይገባ ቢሆን ኖሮ እንደነዚያ መልሶ በተናገረ ነበር" ይላል። ረቡዕ እና አርብን ከዓመት እስከዓመት ጹሙ ነገር ግን ጥምቀት፣ በዓለ ልደት እና በዓለሃምሳ ካልዋሉባቸው በቀር ብሎ ተናግሮ ነበርና። ቁጥር 566 ላይ "ዳግመኛም በእየሳምንቱ ሁሉ ዓርብና ረቡዕን መጾም ነው፡፡ በዓለ ሃምሳ የልደትና የጥምቀት በዓል የተባበሩባቸው ጊዜ ካልሆነ በቀር እንደተጻፈው እስከ 9 ሰዓት ድረስ ይጹሟቸው" ብሎ አዘዘ። ከበዓለ ሃምሳ በኋላ በዓል አድርጉ አለ እንጅ ብሉበት አላለም። ብሉበት ቢል ኖሮ ግን በዚህ ቁጥር ላይ "በዓለ ሃምሳ እና ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ባሉት ሰባት ቀን" ባለ ነበር። በመጾም በዓል ማድረግ እንደሚገባ እዚሁ አንቀጽ ላይ  ቁጥር 582 ላይ "ዳግመኛም እንዳንጾምባቸው እንዳንሰግድባቸው የታዘዝንባቸው ቀኖች እንደ እሁድ እንደ ሰንበት እንደ ጌታ በዓላት ያሉ ቀኖች አሉና ከእነርሱ ጋር ይህን ሳምንት አልተናገረም፡፡ ዳግመኛም የሰሙነ ሕማማትን ሥራ ሳይሠራ ላለፈበት ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ስለርሷ መጾም መስገድ ይገባ ዘንድ ታዘዘ፡፡ ከበዓለ ሃምሳ በኋላ የሚውለው ሳምንት ይህ ቢሆን ኖሮ ከሃምሳ ቀኖች በኋላ ይበሉበት ዘንድ የሚገባ ቢሆን እንደገና ብሉበት በተባለ ነበር፡፡ በዓል አድርጉ ከማለቱ በቀር ብሉበት አላለምና" ይላል። እንደዚሁም ቁጥር 583 ላይ "ይህስ በውስጡ ያሉትን የዓርብንና የረቡዕን ጾም ያስረዳል፡፡ እነርሱንም ይፈጽሟቸው ዘንድ አያስረዳም እነሆ ባስልዮስና አፈወርቅ እንዲህ አሉ፡፡ በዓል ማክበር በመብል አይደለምና ዳግመኛም በጾም በዓል ማክበር እንዲገባ የታወቀ ነው፡፡ ይኸውም ለበዓሉ የሚስማማው እንዲነበብ ነው እንጅ ሊበሉበት አይደለም፡፡ ኤጲስ ቆጶስ በተሾመ ጊዜ 3 ቀን እንድናከብር እነሆ ቀኖና አዘዘችን፡፡ በጾም ቀን እንኳ ቢሆን በእነዚህ በ3 ቀኖች እንዳንበላ የታወቀ ነው በዓል ማክበር በመብል አይደለም"  በማለት እንድንጾም ያስረዳል። ነገርግን ለመብል ራሳቸውን የሰጡ ወገኖች ይህንን ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ያለውን 7 ቀን ይበሉበት ዘንድ በዓል አድርጉ ተብለናል ይላሉ። ከላይ እንደተመለከትነው በዓል የሚደረገው በመብል በመጠጥ ብቻ አይደለም በጾምም ጭምር ነው እንጅ። የሚበላበት ቢሆን ኖሮ  ቁጥር 588 ላይ "አንድ ሰው በባሕር ቢኖር ሰሙነ ሕማማትን ባያውቅ ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ይጹም፡፡ ይኸውም ሰሙነ ሕማማትን የሚጠብቅ አይደለም፡፡ ምሳሌውን ብቻ ነው እንጅ ስለእርሱ መጾም ይገባዋል" ብለው ባላዘዙም ነበር። ነገር ግን መጾም እንዲገባ ጹሙ ብለው አዘዙ እንጅ። አባቶቻችን ይህን ያዘዙን እነርሱ ሳይጾሙ አይደለም ጾመው ነው እንጅ ለዚህም  ቁጥር 585 ላይ "ዳግመኛም ከተሰበሰቡት ወገን ቁጥራቸው ኸያ የሚሆኑት ጹመውታልና ከእስክንድርያ ሊቃነ ጳጳሳት ወገን ከዚህ ቁጥር ቁጥራቸው እስከበዙት ሊቃነ ጳጳሳት ድረስ በዚህ ሳምንት እነሆ ይህን ጾም ጾምን፡፡ የማኅበሩን ትእዛዝ ብንተላለፍ ይህን ማኅበር እንዲነቀፍ ብናደርግ ደግ አይደለም፡፡ ይልቁንም የሕጋችንን ትሩፋት በተቃወመ ጊዜ፡፡ ይኸውም ስለመብል ስስትን በመግለጽ የሚደረግ ክፋት ነው" ብለዋል። ሰለዚህ ከአባቶቻችን አንበልጥምና በእነርሱ መንገድ እንጓዝ ዘንድ ይገባል። ይህን ሁሉ ብለው አልሰማ ላላቸው ግን ሁሉን ሊጠቀልል የሚችል ትእዛዝ እነሆ ሰጡን። ቁጥር 584 ላይ "ዳግመኛም ቢቻላችሁ ከዚህ አብዝታችሁ ጹሙ በማለታቸው ይህን ሕግ እነሆ ወሰኑ በጾሙ ምክንያት ጠብ ክርክር ቢሆን መጾም ይገባል፡፡ ከመብላት በጣም ይሻላል" ብለው አዘዙን። በጾም ወቅት ክርክር ከተፈጠረ ጹሙ ምክንያቱም ከመብላት በጣም ይሻላልና ብለው በአንድ አረፍተ ነገር አሠሩልን። ከዚህ ወዴት እንሸሻለን? እንብላበት እና እንጹምበት የሚሉ ሰዎች ቢከራከሩ እንጹምበት ያለው እንዲረታ እወቁ። ስለዚህ የጾመ ሐዋርያት መግቢያ ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ባለችው ሰኞ ነው ማለት ነው እንጅ ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ሌላ አንድ ሳምንት ከበላን በኋላ ባለችው ሰኞ ነው ማለት አይደለም።