Thursday, April 27, 2017

የሃይማኖት መሠረት ክፍል ፪

© መልካሙ በየነ

ሚያዝያ 18/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

በጎ ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦች
በክፍል ፩ በርካታ አስተሳሰቦች እና ሃይማኖቶች እንዳሉ ተመልክተናል፡፡ እነዚህ በርካታ ሃይማኖቶች ደግሞ የየራሳቸው የሆነ አንዱ ከሌላው ልዩ የሚሆንበት አስተሳሰብ አላቸው፡፡ የአስተሳሰብ ዓይነቶችን አስቀድመን የተመለከትነው ለዚሁ ነው፡፡ እነዚያን አስተሳሰቦች ሃይማኖታዊ መሠረት አስይዘን የምንጠቀምባቸው አይደሉም ሊሆኑም አይችሉም፡፡ ሐዋርያው ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ 1ኛ ቆሮ 10÷23 ላይ “ሁሉ ተፈቅዶልኛል ሁሉ ግን የሚጠቅም አይደለም ሁሉ ተፈቅዶልኛል ነገር ግን ሁሉ የሚያንጽ አይደለም” ብሏል፡፡ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ማለት ይህ ነው፡፡ አያችሁት! “ሁሉ ተፈቅዶልኛል” ብሏል፡፡ ሁሉም ዓይነት አስተሳሰብ ተፈቅዶልኛል ነጻ ፈቃዴን ፈጣሪየ አጎናጽፎኛል ማለቱ ነው፡፡  እበላ፣ እጠጣ፣ እሰክር፣ እጨፍር፣ እዘሙት፣ እገድል፣ እሰርቅ እና እደበድብ ዘንድ “ሁሉ ተፈቅዶልኛል” ማለቱ ነው፡፡ በሥጋዊ አስተሳሰብ ውስጥ  ለታጠረ ሰው ይህ ጥቅስ የሃይማኖት መሠረቱ ነው፡፡ “ሁሉ ተፈቅዶልኛል” የሚለውን ጥቅስ እንዳነበበ መጽሐፉን የከደነ ሰው ሃይማኖቱ እንደዚህ ባለ በከንቱ ሥጋዊ ፍልስፍና እና በሥጋዊ ፈቃዱ ባህር ብቻ የሚዋኝ ከንቱ ዓሣን ይሆናል፡፡ ይህን የሃይማኖታቸው መሠረት ያደረጉ እንደ ፕሮቴስታንት እንደ እስልምና የመሳሰሉ ሃይማኖቶች አሉ፡፡ ፕሮቴስታንቶች ጭፈራ፣ ዳንስ፣ ዝሙትን ህጋዊ ሃይማኖታዊ ሽፋን በመስጠት ወጣቱን በጭፈራ እና በዝሙት ሽማግሌውንም በማብላት እና በማጠጣት እንዲሁም በቁሳዊ አስተሳሰብ በመጥመድ በገንዘብ እና በልዩ ልዩ አላቂ እና ድቃቂ በሆነ ነገር ሁሉ አፍነው ይዘውታል፡፡ ጭፈራውን በመንፈሳዊ መዝሙር ስም፤ እንደ ጠገበች አህያ መንከባለልን ደግሞ ለኢየሱስ ያደረጉት ትልቅ ውለታ እንደሆነ ያስባሉ፡፡ ይህ አስተሳሰብ ሥጋዊነቱ እና ቁሳዊነቱ የጎላበት ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ነው፡፡ ጾምን ስታነሣባቸው “ወደ አፍ የሚገባ አያረክስም ከአፍ የሚወጣ እንጅ” ብለው ይጠቅሳሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ላለመጾም በራሳቸው ፈቃድ በሚተረጎሙ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅሶች ውስጥ ይሰገስጋሉ፡፡ “ወደ አፍ የሚገባ አያረክስም” ያለው ስለምንድን ነው ብለው አይመረምሩም፡፡ ወደ አፍ የሚገባ ነገር አያረክስም ከተባለማ ጥንተ ፍጥረት አዳም አትብላ የተባለውን ትእዛዝ አፍርሶ ዕጸ በለስን ወደ አፉ በማስገባቱ አልረከሰም ማለት ነዋ፡፡ ወደ አፍ የሚገባ አያረክስም እያለ የጻፈልን እጅን ታጥቦ ስለመብላት እና ስለአለመብላት እንጅ ስለመጾም እና ስለአለመጾም አይደለም፡፡ ነገር ግን ሆዳቸው ላይ ጅብ የታሰረ የሚመስላቸው ጾምን የሚፈሩ ሰዎች ይህን ጥቅስ ላለመጾማቸው ሃይማኖታዊ ሽፋን አድርገው ሲሰጡ ይስተዋላሉ፡፡ በዚህ ዓይነት አስተሳሰብ ውስጥ የተተበተቡ ሰዎች መጽሐፋቸውን የሚዘጉት ላነበቡት ቃል ማብራሪያ ከላይ አርእስቱን ከታችም ህዳጉን ሳይመለከቱ ነው፡፡ ጥቅስን አንጠልጥሎ የመሮጥ እና ያችን ሃይማኖታዊ ሽፋን የመስጠት አባዜ የተጠናወታቸው ናቸው፡፡ እስልምናውንም ስንመለከት መንፈሳዊ አስተሳሰብ የሚለው የተዘነጋበት ነው፡፡ ጾም አላቸው ነገር ግን ለዚህ ጾማቸው “ሁሉ ተፈቅዶልኛል” የሚለውን የቅዱስ ጳውሎስ መልእክት በትክክል ሲፈጽሙ የሚስተዋሉ ናቸው፡፡ ሥጋቸውን የሚያወፍሩት ደረታቸውን የሚያቀሉት በጾማቸው ወራት ነው፡፡ ጾማቸው ሊገባ ሲል በጾማቸው ጊዜ የሚመገቡትን ሥጋ፣ ቅቤ፣ሾርባ ወዘተ ቀድመው ያዘጋጃሉ፡፡ ይህን ካላደረጉ ማለትም ሥጋ፣ ቅቤ፣ ሾርባ ወዘተ ካልተመገቡ እስከ ምሽት መቆየት እንደማይችሉ ራሳቸውን አሳምነውታል፡፡ ሌሊት ዐሥራ አንድ ሰዓት ተቀስቅሰው ይህንን የላመ የጣመ ኃይል እና ሙቀት ብርታት እና ጽናት የሚሰጠውን በዓይነት በዓይነት የተዘጋጀውን ምግብ ይመገባሉ፡፡ ይህ እንስሳዊነትን ያጎላባቸዋል፡፡ ሌሊት መመገብ የተፈቀደው ለእንስሳት ብቻ ነውና፡፡ ከምሽት ሦስት ሰዓት በኋላ መመገብ ለሰው ልጅ የተፈቀደ አይደለም፡፡ እነርሱ ግን እስከ ምሽት አንድ ሰዓት ለመጾም ሌሊት ዐሥራ አንድ ሰዓት ሥጋውን ቅቤውን ወተቱን ሾርባውን እያማረጡ ለራሳቸው ይመገባሉ፡፡ ታዲያ ይህ ሃይማኖታዊ ሽፋን ካልተሰጠው በቀር እንስሳዊነት አይደለምን ቁሳዊነትስ አይደለምን፡፡ ሥጋ፣ ቅቤ ካልበላሁ ይደክመኛል ወተት ሾርባ ካልጠጣሁ መጾም አይሆንልኝም የሚልን ቁሳዊነት ከንቱ ሃይማኖታዊ ሽፋንን በማላበስ የሃይማኖት መሠረት ማድረግ ተገቢ አይደለም፡፡  ቁርስ በልቶ ጾም የለምና፡፡ ስለዚህ ነው እውነተኛው ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ “ሁሉ ተፈቅዶልኛል” ከሚለው ቃል ቀጥሎ የሚመጣውን ማንበብ እንደሚኖርብን የሚያስገድደን፡፡ ቀጥሎ የሚመጣው ይህንን አስተሳሰብ ውድቅ ያደረገ ነው እንዲህ ይላል፡፡ “ሁሉ ግን የሚጠቅም አይደለም” የሚል ነው፡፡ ሁሉ የተፈቀደው ለሥጋዊ፣ ለቁሳዊ፣ ለፖለቲካዊ፣ ለባህላዊ ወዘተ አይነት አስተሳሰቦች ነው፡፡ አሁን የጠቀስነው ቃል ወይም ቀጥሎ የመጣው ቃል  “ሁሉ ግን የሚጠቅም አይደለም” የሚለው ግን ለመንፈሳዊ እና ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦች የተነገረ ነው፡፡ በሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ውስጥ “ሁሉ ተፈቅዶልኛል” የሚለውን ቃል ብቻ አንብቦ መጽሐፉን አይዘጋም፡፡ “ሁሉ ተፈቅዶልኛል ሁሉ ግን የሚጠቅም አይደለም” እስከሚለው ድረስ አንብቦ ምሥጢሩን ይረዳ ዘንድ ደግሞ ከላይ አርእስቱን ከታችም ህዳጉን ይመለከታል እንጅ፡፡ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ምንም ይሁን ምን ከሞት በኋላ ያለው ሕይወት የሚያስጨንቀው መሆን አለበት፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በምድራዊ ሕይወቱ አስተማሪ ይሆን ዘንድ ግብረ ገብነትን የተላበሰ መሆን አለበት፡፡ ግብረ ገብነት ምግባር (መታመኛ ) ነው ከሞት በኋላ ስላለ ሕይወት መጨነቅ ደግሞ ሃይማኖት ነው፡፡ ሃይማኖቱን ከምግባር ምግባሩን ከሃይማኖት አንድ አድርጎ አስማምቶ የሚኖር መሆን አለበት ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ፡፡ ሃይማታዊ አስተሳሰብ ከነፍስና ከሥጋ ለተፈጠረ ሰው ሁለቱን አንድ አድርጎ አስማምቶ ይኖር ዘንድ መንገድን የሚመራ መሆን አለበት፡፡ ለሥጋዊ ነገር ብቻ ያደላ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ እንስሳዊነትን የሚከተል ስለሆነ ሃይማኖት አይባልም፡፡ ሥጋን ከነፍስ ጋር ማስማማት የሚችል አስተሳሰብ መሆን ይኖርበታል፡፡ ሰው ከነፍስና ከሥጋ እንደመሠራቱ መጠን  ኅሊናው ውስጥ ሥጋ ልብላ ነፍስ ልጹም የሚሉበት ተቃራንያን ሃሳቦች የሚመላለሱበት ነው፡፡ እነዚህን ማስታረቅ የሚገባው መሆን አለበት፡፡ የሥጋ ፍሬ አለ የመንፈስም ፍሬ እንዲሁ አለ ሰው ግን በሥጋው እየኖረ መንፈሳዊ ፍሬን ያፈራ ዘንድ ይመከራል፡፡ በሥጋው እየኖረ ስል ነፍስ ከሥጋ ተለይታ ሰው ተብሎ መኖር ስለማይገኝ ነው፡፡ ሰው ሰው ሆኖ የሚኖረው ነፍስና ሥጋው ሳይለያዩ ተዋሕደው አንድ ሆነው ከጸኑለት ብቻ ነውና፡፡ ስለዚህ ነው ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ እነዚህን አስማምቶ ከሞት በኋላ ስላለ ሕይወት ተጨንቆ ከቁሳዊ እና ከሥጋዊ አስተሳሰብ ርቆ ያለ ምጡቅ አስተሳሰብ ነው የምላችሁ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ አሁንም ጽሑፉን ቀጥሎበታል “ሁሉ ተፈቅዶልኛል ነገር ግን ሁሉ የሚያንጽ አይደለም” ይላል፡፡ የተፈቀደልን ሁሉ አይጠቅመንም ብሎ ነበር አሁን ደግሞ ጎላ አድርጎ የሚያንጽ አይደለም አለ፡፡ ሁሉ ቢፈቀድልን ሁሉን መሥራት ሁሉን ማወቅ ሁሉን መመርመር ሁሉን ማድረግ ቢፈቀድልንም ማለት ነጻ ፈቃድ ቢኖረንም ሲል ነው፡፡ ሁሉ ግን የሚያንጽ አይደለም አለ፡፡ ሁሉን ብንመረምር ሁሉን ብናደርግ ሁሉን ብንፈጽም ሁሉን ብንበላ ብንጠጣ ሁሉን ሳንመርጥ ብናደርግ መብታችን ነው ሁሉ ተፈቅዶልናልና ነገር ግን በሃይማታዊ አስተሳሰብ ውስጥ ላላችሁ ወገኖቸ ይህ የምታደርጉት ሁሉ የሚያንጻችሁ በሃይማኖታችሁ የሚያጸናችሁ ርስት መንግሥተ ሰማያትን የሚያወርሳችሁ አይደለም ሲለን ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ከእነዚህ ሥጋዊ ምኞቶች እና ሃሳቦች ሁሉ የራቀ መሆን አለበት፡፡
ይቆየን፡፡

ይቀጥላል፡፡

የሃይማኖት መሠረት ክፍል ፫

© መልካሙ በየነ

ሚያዝያ 19/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
…ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ግብረ ገብነትን ከእምነት ጋር አንድ ያደረገ መሆን አለበት፡፡ ምንም ይሁን ምን ሰውን ግደሉ የሚል ሃይማኖት ያለው ሰው እርሱ ከንቱ ሃይማኖት ነው፡፡ ሰውን ከፍ ዝቅ በማድረግ በማበላለጥ ላይ የተመሠረተ ሃይማኖት እርሱ ግብረ ገብነት የለውም፡፡ አስተምረኝ ሳይባል ላስተምርህ የሚል ሃይማኖት እንደ ሰዳቢ እና ተከራካሪ ይቆጠራል፡፡ ደረቴ ይቅላ ሆዴ ይሙላ የሚል አስተሳሰብ ውስጥ የተወሸቀ ሃይማኖት እንስሳዊነትን የሚያበረታታ ነው፡፡ ፈጣሪ  በመረጣቸው ላይ የስድብ አፍን የሚከፍት የሚዘልፍ አስተሳሰብ ያለው ሃይማኖት እርሱ የስድብ ማምረቻ ፋብሪካ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ግብረ ገብነት ነው፡፡ ግብረ ገብነት ካለ ምግባር መሥራት ትሩፋት መፈጸም በሃይማኖት መጽናት ይኖራል፡፡ አንዳንድ ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦች ግን ከዚህ የተለዩ ናቸው፡፡ ግብረ ገብነት የላቸውም፡፡ አንድን ክርስቲያን የገደለ “ገነትን ይወርሳል” የሚል አስተሳሰብ ያላቸው አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች “ኢትቅትል፤ አትግደል” የሚለውን የፈጣሪ ትእዛዝ በራሳቸው ፍልስፍና ላይ በተመሠረተ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ደብቀው እና ህጋዊ አድርገው ከፈጣሪ የተቸረንን ሰብአዊ ነጻነት የሚገፍፉ ውሉደ ቃየን  ናቸው፡፡ አንዳንዶች ደግሞ በወንጌል “መንፈስም ከምድር ጣለው ተንፈራገጠም” እያለ ርኲሳን መናፍስት ሰውን እንደሚጥሉ እና እንደሚያንፈራግጡ እያወቁ ነገር ግን እነርሱ ስለወደቁ እና ስለተንፈራገጡ መንፈስ ቅዱስ የጣላቸው የሚመስላቸው የዋሐን አሉ፡፡ የሚጥል የሚያንፈራግጥ መንፈስ ቅዱስ አይደለም ርኲሳን መናፍስት ናቸው የሚጥሉም የሚያንፈራግጡም፡፡ ነገር ግን ሃይማኖታዊ ሽፋን በመስጠት በመንፈስ ቅዱስ ሰክረው እና ተሞልተው እንደተንፈራገጡ ራሳቸውን በመንፈስ ቅዱስ የሰከሩ አድርገው ይናገራሉ፡፡ እንዲያውም ወድቀው ካልተንፈራገጡ እግዚአብሔር እንደጠላቸው አድርገው ያስባሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ ሃይማኖታዊ ሽፋን ለመስጠት እና ራስን ለማታለል ካልሆነ በቀር ምንም የሃይማኖታዊ አስተሳሰብ መሠረት የለውም፡፡ ሌላው ደግሞ ወጣቱን ለመያዝና እንደ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ የአማኙን ቁጥር ለመጨመር ብቻ ሲባል በተለያዩ ሙዚቃ መሣሪያዎች ልዩ ልዩ ዓይነት የሆኑ ዘፈኖችን እየዘፈኑ ዳንኪራ ሲረግጡ ይውላሉ፡፡ በዓለም ውስጥ በዘፈን ናላው የዞረን ወጣት በሃይማኖት ስም ስታቀርብለት እንደአዲስ መስማት ይጀምራል፡፡ ጎደሎየ ሞላ፣ ቤቴ ተባረከ፣ ጌታየ ነገሠብኝ፣ ዙፋኑን አጸናብኝ ወዘተ እያሉ ስለሥጋቸውና ስላገኙት ቁሳዊ ነገር ብቻ ያቀነቅናሉ፡፡ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ይህንን በጣም ይጠላል፡፡ ሥጋዊ እና ቁሳዊ አስተሳሰብ በሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ውስጥ ጎልተው ከወጡ ሃይማኖቱ ሃይማኖት አይባል፡፡ ምንም እንኳ የፈጣሪ ቃል የሚነገርበት ባይሆንም ይነገርበታል ብለው ካሰቡ ግን የፈጣሪ ቃል ከሚነገርበት ቦታ እርቃንን መግባት ከነጫማ ዘው ማለት የተፈቀደ አይደለም፡፡ ነገር ግን ቁሳዊ እና ሥጋዊ አስተሳሰቦች ጎልተው የወጡበት ሃይማኖት ጫት እስከመቃም ድረስ፣ መንፈስ ቅዱስ መርቶኛል በማለት ዝሙት እስከመፈጸም ድረስ የሚደርሱበት ተቋም አለ፡፡ ሥርዓት የሌለበት ሁሉም እየተነሣ የፈጣሪውን ያይደለ የራሱን ነገር ብቻ የሚናገርበት የሃይማኖት መፈጸሚ ቦታ ሞልቷል፡፡ ራሳቸውን እንደጸደቁ ዕለቱን ገነት መንግሥተ ሰማያት እንደገቡ አድርገው አውነተኛውን የጌታ ፍርድ እዚህ በራሳቸው አዳራሽ የሚፈርዱ የዋሐንን የሚያታልሉ የሐሰት አስተማሪዎች የሐሰት መስካሪዎች አሉ፡፡ ስለዚህ ራስን ወደ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ መመለስ ያስፈልጋል፡፡ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ከሁሉ ልዩ ሊያደርገው የሚገባ አስተሳሰብ መያዝ አለበት፡፡ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ማለት ከሥጋዊ የተወሰነውን፤ ከፖለቲካዊ የተወሰነውን፣ ከቁሳዊ የተወሰነውን፣ ከባሕላዊ የተወሰነውን አስተሳሰብ ወስዶ እነዚያን ቀላቅሎ ቀምሞ እና አስውቦ ሃይማኖታዊ ይዘት ሰጥቶ ብቅ ማለት አይደለም፡፡ ስለዚህ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ቢያንስ በዋናነት የሚከተሉትን ነገሮች መያዝ አለበት ብየ በግሌ አምናለሁ፡፡
ü  ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት አብዝቶ የሚጨነቅ፡፡
ü  ሥጋዊ እና ቁሳዊ አስተሳሰቦችን የሚነቅፍ፡፡
ü  ከዓለም አመለካከት የራቀ መሆን አለበት፡፡
ü  ግብረ ገብነትን የሚያስተምር፡፡
ü  ሥጋውን ለነፍሱ ማቆያ ብቻ እንድትሆን ማድረግ፡፡
ü  ፈጣሪውን በመፍራት ለፈጠራቸው ሥነ ፍጥረታት አድኖቆት ያለው፡፡
ü  ሁሉ ተፈቅዶልኛል እያለ ፈጣሪውን የማያሳዝን፡፡
ወዘተ እና ይህን የመሳሰለው ሁሉ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ውስጥ መኖር አለበት እላለሁ፡፡ በዚህ መስፈርት ሁሉንም ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦችን ብንመለከታቸው ጉድለት እናገኝባቸው ይሆናል፡፡ ነገር ግን ጉድለቱን ራሳችሁ መርምሩት እና የትኛው የተሻለ እንደሆነ ወስኑ፡፡ እኔ የምመለከተው እንደ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የሃይማኖት አስተሳሰብ ውስጥ ነው፡፡ ይህን እምነት ያገኘሁት ደግሞ እኔ ወደጄ ሳይሆን ፈጣሪየ ፈቅዶልኝ ነው፡፡ ፈጣሪየን ከማመሰግንበት መካከል አንዱ እኔ ሳልመርጠው እኔ ሳልፈልገው እርሱ ፈቅዶ እርሱ መርጦ “የተዋሕዶ ልጅ” ስላደረገኝ ነው፡፡ ምናልባትም ወላጆቼ ይህን እምነት ባያወርሱኝ ባያሳዩኝ ኖሮ ዛሬ እንደ አብርሃም ተመራምሬ ፈጣሪየን ለማግኘት እና ይህችን ቀጥተኛ እና እውነተኛ ጥንታዊት የሆነችን የምኮራባትን የማጌጥባትን የምከብርባትን የሐዋርያት እምነት የማግኘት ዕድሌ ሰፊ ላይሆን ይችል ነበር፡፡ ምክንያቱም ወርቅ ሳይሆኑ ወርቅ ነን ብለው የተነሡ ብዙ ሃይማኖቶች ስላሉ ፈጣሪ ሲረዳ ነው እንጅ ከእነዚያ መካከል የመምረጥ አቅሜ ደካማ በሆነ ነበር፡፡ ነገር ግን እውነተኛዋ መንገድ ላይ ቆምሁ፡፡ ስለዚህ እውነቱን ከሐሰቱ እምነቱን ከክህደቱ የመለየት አቅማችንን እየገመገምን ወደ እውነት መምጣት አለብን፡፡ ሁሉም የእኔ የበላይ ነው የእኔ ጥሩ እምነት ነው ይል ይሆናል ነገር ግን፡፡
1.  የሃይማኖቱ መሥራች ማን እንደሆነ መርምሩ ፈጣሪ ወይስ ፍጡር፡፡
2.  ሃይማኖቱ መቸ ተመሠረተ ዕድሜው ይታይ፡፡
3.  ሃይማኖታዊ አስተሳሰቡ ይመዘን ይለካ፡፡
4.  አስተሳሰቡ ቁሳዊነት ሥጋዊነት ፖለቲካዊነት ባህላዊነት ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠረው ነውን የሚለው ጥያቄ ይመለስ፡፡
ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ እውነቱን ወደማወቅ የምትደርሱ፡፡ በልቶ ጠጥቶ ሰውን መግደል፤ ሀብት ንብረት ዘርፎ ማሳዘን፤ መጨፈር ፣መዝፈን፣ መግደል፤ አውቅልሃለሁ አውቅልሻለሁ እያሉ ማታለል፤ መንፈስ ቅዱስ ወረደልኝ ብርሃን በራልኝ እያሉ ጨለማን ከብርሃን መቀላቀል፤ እንደ ፍየል ቅጠል እያመነዠኩ ፈጣሪን መለመን ወዘተ ይህ ሁሉ ብላሽ ነው፡፡
ፈጣሪያችን ዓይነ ልቡናችንን ከፍቶ እውነተኛውን መንገድ ወደ ማዎቅ ይምራን፡፡
“አንዲት ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት አንድ ጌታ” እንደሆነ እናምናለን፡፡ እውነተኛውን ለማወቅ ግን አብርሃምን በምግባር በሃይማኖት ምሰሉት፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ፈጸምኩ፡፡

Tuesday, April 25, 2017

የሃይማኖት መሠረት ክፍል ፩


© መልካሙ በየነ
ሚያዝያ 17/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም በፍቅር በአንድነት አደረሰን አደረሳችሁ!
ፍጡራን በተለይም ሰውና መላእክት ነጻ ፈቃዳቸው ፈጣሪን እስከ መካድ ብቻ ሳይሆን ፈጣሪ ነን እስከማለት የደረሰ ነው፡፡ ይህም ሊታወቅ እግዚአብሔር ሥነ ፍጥረትን መፍጠር በጀመረበት ቀን የፈጠረው መልአክ ሳጥናኤል አኃዜ መንጦላእት አቅራቤ ስብሐት ሆኖ ከሁሉ ልቆ ቢፈጠር ፈጣሪውን ረስቶ በዝንጋዔ ኅሊና ታውሮ አነ ፈጣሪሆሙ ለእሉ ፍጡራን፤ የእነዚህ በክብር ከእኔ በታች በማዕረግ የምልቃቸውን መላእክት እኔ ፈጠርኋቸው ፈጣሪያቸው እኔ ነኝ አለ፡፡ እንግዲህ እዚህ ላይ ለሳጥናኤል የተሰጠው ነጻ ፈቃድ ፈጣሪውን መካድ ብቻ አይደለም ፈጣሪ ነኝ እስከማለት የደረሰ ድፍረት ነው እንጅ፡፡ ይህን ነጻ ፈቃድ ያገኘው ደግሞ ከፈጣሪው ከእግዚአብሔር ነው ከሌላ ከማንም አይደለም፡፡ ነጻ ፈቃዱን እንዴት አገኘው ቢሉ እግዚአብሔር መላእክትን ፈጥሮ በኅሊናቸው አስተውለው በሰጣቸው አእምሮ ተመራምረው ይደርሱበት ዘንድ ተሠወረባቸው፡፡ መሠወሩም መላእክት ሁሉ ፈቃዳቸውን እንዲከተሉ አእምሯቸውን እንዲጠቀሙ ነው፡፡ ፈጥሮ ባይሠወራቸው ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ነው ብለው ሳይወዱ በግድ ባመሰገኑት እና በተከተሉት ነበረ፡፡ ስለተሠወራቸው ግን ሳጥናኤል እኔ ፈጣሪ ነኝ እስከማለት የደረሰ ነጻነትን አገኘ፡፡ ቅዱስ ገብርኤልም ንቁም በበሕላዌነ እስከ ንረክቦ ለአምላክነ፤ አምላካችንን ፈጣሪያችንን እስከምናገኘው ድረስ በያለንበት እንጽና ሳጥናኤል አምላክ ነኝ ቢላችሁ አትሸበሩ እኛ ከእርሱ በማዕረግ ስላነስን ፈጠርኋችሁ አለን፡፡ ነገር ግን ከእኛ በማዕርግ የምታንሱ አላችሁ እኛ እናንተን መፍጠር አንችልም ስለዚህ ፈጣሪያችንን እስከምናገኘው ድረስ እንጽና ብሎ በመላእክት ዓለም የተፈጠረውን ግርግር አረጋግቶታል፡፡ ይህ ሁሉ ነጻ ፈቃድ ነው፡፡
ዛሬም በዓለማችን የሃይማኖት ቁጥሩ ብዙ ነው፡፡ ይህ ቢሆንም ቅሉ ሃይማኖት ግን አንዲት ናት ምክንያቱም ዓለምን ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣ እኛን ሁሉ ሌሎች ፍጡራንንም ሁሉ በየመልካቸው በየወገናቸው የፈጠረ አንድ ፈጣሪ እንደሆነ ስለምናውቅ፡፡ ሆኖም ግን ፈጣሪ ለመላእክት የሰጣቸውን ነጻነት ለእኛም ሰጥቶናልና ሀሰቱን ከእውነት ከክህደቱን ከእምነት አጣርተን እንድንለይበት በሰጠን አእምሮ እየተመራን የመሰለንን ሁሉ እንድንከተል ትቶናል፡፡ ለዚህም ነው ሰው የመሰለውን ሁሉ እያመለከ የሚኖረው፡፡ ያ ሰው የሚያመልከው የሚሰግድለት የሚንበረከክለት ሁሉ ግን ፈጣሪ አይደለም ምክንያቱም ፈጣሪያችን አንድ እንደሆነ የታወቀ ስለሆነ፡፡ ምንም እንኳ የሃይማኖት ቁጥሩ ብዙ የብዙ ይሁን እንጅ ፈጣሪ ግን አንድ ነው፡፡ ይህ ብዙው የብዙ ብዙው ሃይማኖት ሁሉ ግን የሚያመልከው ይህን አንዱን ፈጣሪ ብቻ አይደለም፡፡ ለየራሱ የሆነ ፈጣሪ አለው እንጅ፡፡ ስለዚህ ወደ እውነተኛው ሃይማኖት ወደ ትክክለኛው የቀና መንገድ ለመሄድና የዘላለም ርስትን ለመውረስ አንድ ሃይማኖት እንደ ሃይማኖትነቱ መያዝ ያለበት ጉዳይ መኖር አለበት፡፡ በዚህም እየተመዘነ ማለፍ እና መውደቅ መመረጥ እና መደነቅ አለበት፡፡ በዓለም ዘንድ የተለያዩ ዓይነት አስተሳሰቦች አሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል ፖለቲካዊ፣ ቁሳዊ፣ ባህላዊ፣ ሥጋዊ፣ መንፈሳዊ፣ ሃይማኖታዊ ወዘተ አስተሳሰቦች አሉ፡፡ ከእነዚህ አስተሳሰቦች መካከል ግን ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ከሁሉ በላይ የላቀ መሆን ይኖርበታል፡፡ እስኪ ለግንዛቤ ያህል ስለእያንዳንዱ አስተሳሰብ ጥቂት ጥቂት እንጻፍ፡፡
v  ፖለቲካዊ አስተሳሰብ፡- ይህ አስተሳሰብ ፈጣሪ ከመኖሩ ካለመኖሩ ጋር የሚገናኝበት ነገር የለውም፡፡ ይህ አስተሳሰብ ራስን ከሌሎች የተሻለ በማስመሰል ማቅረብን ያበረታታል፡፡ በትህትና ራስን ዝቅ በማድረግ ከእኔ የተሻሉ መሪዎች ስላሉ እኔ ልመራችሁ ላስተዳድራችሁ አልችልም ብሎ ለሌላ አሳልፎ የሚሰጥበት አመለካከት የለውም፡፡ በዚህ አስተሳሰብ ውስጥ ብዙ ተከታይ ለማፍራት ብቻ የማያደርገውን አደርጋለሁ እያሉ መናገርን ይደግፋል፤ ያልተደረገውንም ተደርጓል እያሉ ማውራትን ያበረታታል፡፡ አበርክቶ የሚመግብ በጥበቡ የሚያስተዳድር መስሎ እንዲታይ ራሱን ከማማ ላይ የሚሰቅል ዓይነት አስተሳሰብ  ነው፡፡ የምታየውን እንዳላየህ የምትሰማውን እንዳልሰማህ የምትዳስሰውን እንዳልዳሰስህ አድርጎ በቃላት አቀናብሮ የማቅረብ ብቃት አለው፡፡ በአፉ ሲናገር ስለአንተ የሚጨነቅ የሚያስብ ይመስላል ነገር ግን ለራሱ ብቻ የሚኖር ምቾትን ተድላ ደስታን ለራሱ ብቻ ጠቅልሎ የሚሰበስብ ነው፡፡ የተከታዩን ቁጥር በማብዛት ብቻ እርካታን ያገኘ የሚመስለው ነው፡፡ ምናልባትም ሲበላ የሚነጥበው ፍርፋሪ ሰብስቦ ሌሎችን ይመግብ ይሆናል፡፡ ከእርሱ ሥራ ውጭ ሌላው ሥራ ሁሉ ብላሽ ከንቱ እና ርኩስ ነው ብሎ ያስባል፡፡ የእርሱ ሥራ ግን ሁሉ እውነት፣ ሁሉ ጽድቅ እንደሆነ ያስባል፡፡ ይህ አስተሳሰብ ሕልውናው በዚህ በምድር ብቻ የተወሰነ ነው፡፡ ሰማያዊ አስተሳሰብ ሰማያዊ አመለካከት የለውም ሕይወት ከምድር ሕልፈት በኋላ ስላላት ዘላለማዊ ኑሮ አያስብም አይጨነቅምም፡፡
v  ቁሳዊ አስተሳስብ፡- ይህ አስተሳሰብ ካልዳሰስሁ አላምንም ካልጨበጥሁ አልከተልም የሚል ነው፡፡ ሕልውናው በሚዳሰስ በሚጨበጥ ነገር ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ረቂቅ ነገሮችን ምሥጢራትን ሁሉ አይቀበልም፡፡ ሁሉ ነገሩ ከሚጨበጥ እና ከሚዳሰስ ከሚነካካ ጉዳይ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ካላየሁ አላምንም ካልጨበጥሁ ካልዘገንሁ አልቀበልም በሚል ደዌ የተያዘ ነው፡፡ ገንዘብ ይጨበጣል ይዳሰሳል ስለዚህም ሁሉ ነገሩን ለገንዘብ አሳልፎ ይሰጣል፡፡ ምግብ ይጨበጣል ይዳሰሳል ይዘገናል ስለዚህም ስለምግብ ሁሉን ነገሩን አሳልፎ ይሰጣል፡፡ ሃብት ንብረት ይዳሰሳል ይጨበጣል ስለዚህም ሃብት እና ንብረት አወርስሃለሁ ብትለው ሁሉ ነገሩን ገልጦ ያሳይሃል፡፡ ፈጣሪየ የሚለው በእጁ የሚዳስሰውን በበቤተ ሙከራ ያረጋገጠውን ቁሳዊ ነገር ነው፡፡ እውነተኛውን ፈጣሪ ቢያገኝ እንኳ ስለቁሳዊ ነገር እንደ ይሁዳ አሳልፎ ይሰጣል እንጅ ጸንቶ አይቆምም፡፡
v  ባህላዊ አስተሳሰብ፡- ይህ አስተሳሰብ ስለ ሰፈሩ ባህል ብቻ የሚጨነቅ ነው፡፡ ያ ባህል ምን እንደሆነ፤ ከየት እንደመጣ፤ መነሻው ምን እንደሆነ  የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ ልማዳዊ ነውን ሃይማኖታዊ ነውን ትውፊታዊ ነውን የሚለውን ነገር አይመልስም፡፡ የራሱን የበላይነት ለማሳየት ብቻ የሚጥር ነው፡፡ የሌሎችን የሚነቅፍ የሌሎችን የማያከብር ነው፡፡ አስተሳሰቡ በሰፈር ውስጥ የታጠረ ነው፡፡ ሌሎች አማራጮችን አይመለከትም፡፡ የባህሉን የትመጣነት ከማሰብ ከመመርመር ይልቅ ስለሌሎች ባህል ከንቱነት ሌሊት ከቀን ያወራል፡፡ ባህሉ ጠቃሚ ይሁን ጎጅ ይሁን ማመዛዘን አይፈልግም፡፡ በዚህም የተነሣ ፈጣሪውን ከማወቅ ይልቅ በልማዳዊ ባህሎች ተተብትቦ ይኖራል፡፡ ለበሽታው መድኃኒቱ ባህሉ ነው፣ ለዘላለም ሕይወት የሚያበቃው ባህሉ ነው፣ ፈጣሪው ባህሉ ነው፡፡ በአለባበስ ባህሉ ይመካል፣ በአመጋገብ ባህሉ ይመካል፣ በአነጋገር ባህሉ ይመካል፣ በአረማመድ ባህሉ ይመካል፣ በጋብቻ በቀብር ባህሉ ይመካል፣ በሁሉ ነገሩ ባህሉን ያስቀድማል፡፡ ዋና ሥራው ባህሉን የመጠበቅ የማስጠበቅ አይደለም በባህሉ ስም አምልኮትን መፈጸም እንጅ፡፡ አምላኩ ባህሉ ነው፡፡
v  ሥጋዊ አስተሳሰብ፡- ይህ አስተሳሰብ እንስሳዊ አስተሳሰብ ነው፡፡ ሰው ሥጋውን ብቻ ካሰበ እንስሳዊነቱ ገዝፎበታል ማለት ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ ስለ ሥጋው መድለብ ስለደረቱ መቅላት ስለ ውበቱ ማማር ብቻ የሚጨነቅ ነው፡፡ ሁሉን ነገር የሚያደርገው ለሥጋው ብቻ ነው፡፡ በዚህ አስተሳሰብ ውስጥ ለሚኖር ሰው ሕይወት ማለት በምድር ላይ የሚፈጸም ነው፡፡ ከሞት ባሻገር ስላለ ሕይወት አያስብም አለ ብሎም አይቀበልም፡፡ ገነት እና ሲዖል የሚባሉ ዓለማት እንደሌሉ ይመሠክራል፡፡ ሕይወት ማለት መብላት መጠጣት መዝፈን መጨፈር መስከር ዝሙት መፈጸም ወዘተ ነው፡፡ ለሥጋ የተፈቀዱትን ሁሉ አንድ ሳያስቀሩ መጠቀም እንደሚያሸልም ያስባል፡፡ ስለዚህም ጫት በመቃም ሲጋራ በማብነን በመዳራት በመስከር እና በመጨፈር ኅሊናውን ያሳረፈ ይመስለዋል፡፡ ብልጭልጭ ዓለም በአሸንክታቧ መረብ ከምታጠምዳቸው ዓሣዎች መካከል አንዱ የዚህ አስተሳሰብ አራማጅ ነው፡፡ ዛሬን ብላ ጠጣ ነገን አታውቀውምና በሚል ፍልስፍና የሚመራ አስተሳሰብ ነው፡፡ የሥጋ ሥራዎችን ሁሉ ሥጋ በማረው እና በፈለገው ጊዜ ያለምንም ገደብ ያለምንም ቅድመሁኔታ መፈጸም ያስፈልጋል ባይ ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ እንስሳዊነት ጠባይእ ገዝፎ የሚታይበት  ምክንያትም ለዚሁ ነው፡፡
v  መንፈሳዊ አስተሳሰብ፡- ይህ አስተሳሰብ የቁሳዊ አስተሳሰብ እና የሥጋዊ አስተሳሰብ ተቃራኒ ነው፡፡ ረቂቅ በሆኑ ምሥጢራት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ካልዳሰስሁ አላምንም ለሚል አስተሳሰብ ሳያዩ የሚያምኑ ብጹአን ናቸው ይልብሃል የሚል አስተሳሰብ ነው፡፡ አስተሳሰቡ ሙሉ በሙሉ መንፈሳዊ የሆነ ሰው መላእክትን ይመስላቸዋል፡፡ ይህ አስተሳሰብ ስለነፍስ ብቻ የሚጨነቅ ነው፡፡ ነፍሱ የምትደሰትበትን እንጅ ሥጋው የምትደሰትበትን ነገር አይሻም፡፡ ነፍሱ በመራችው መንገድ ሁሉ ይጓዛል፡፡ መብላት መጠጣትን መስከር መጨፈርን ዝሙት መዳራትን ወዘተ አብዝቶ ይጠላል፡፡ እነዚህን የሥጋ ሥራዎች ሁሉ ኃጢአት ይሁኑም አይሁኑም አይወዳቸውም፡፡ ሥጋው በመራችው ሳይሆን ነፍሱ ባሳየችው የሚሄድ ሰው ነው፡፡
v  ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ፡- ይህ አስተሳሰብ ሁሉን የሚመረምር ከሁሉም አቅጣጫ የሚጠቅመውን ብቻ በመምረጥ የሚከተል ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ ከሌሎች የተለየ መሆን ይኖርበታል፡፡ ከላይ ያየናቸው አስተሳሰቦች አሉ፡፡ እነዚያ አስተሳሰቦች በሙሉ የፈጣሪን መንገድ በትክክል የሚመሩ ናቸው ብለን አናምንም፡፡ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ከሥጋ እና ከነፍስ አንድ ሆኖ የተፈጠረን ሰው በባሕርይ ልዩ ልዩ የሆኑትን ሥጋ እና ነፍስ አስማምቶ ስለሚኖርበት የሚያስብ ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ በዋናነት መንፈሳዊ አስተሳሰብን እና ሥጋዊ አስተሳሰብን በአንድነት አጣምሮ ለዘላለም መንግሥት ስለሚበቃበት ሁኔታ የሚያስብ ነው፡፡ ሌሎችን አስተሳሰቦችንም እንደአመጣጠቸው በተገቢው ሁኔታ የሚያስተናግድ ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ ነው እንግዲህ እልፍ አእላፋት ሃይማኖቶች እንዲፈጠሩ ያደረገው፡፡ ሆኖም ግን በመልኩ በቅርጹ ያማረ ፍሬ ሁሉ እንደማይገመጥ እነዚህ በልዩ ልዩ መልክእ እና ጠባይእ የተመሠረቱትን እምነቶች ሁሉ አዎን በጎ ናቸው ብሎ መቀበል አይቻልም፡፡ አንድ ሰው ያድነኛል ይጠቅመኛል ለዘላለም መንግሥት እበቃበታለሁ ያለውን ሃይማኖቱን መርጦ በመያዝ መማር ማስተማር ይኖርበታል እንጅ ከዚያ እዚያ ከዛፍ ዛፍ እንደሚበር ወፍ ለፌ ወለፌ ማለት አይበጅም፡፡ ይህን ሃይማኖት መርጦ እንዲከተል ግን መንፈሳዊነትን (ስለ ነፍስ ማሰብን) እንዲረዳ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህም ይህንን ነገር በጎ ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦች በሚል እንደሚከተለው እጽፋለሁ፡፡

Sunday, April 9, 2017

ፍኖተ እግዚአብሔር--- ክፍል አንድ



የሊቁ አለቃ ኅሩይ ፈንታ አጭር መግለጫ

በመምህር ልዑለቃል አካሉ
መቅድመ ቃል
ይህ በታላቁ ሊቅ በአለቃ ኅሩይ የተዘጋጀው “ፍኖተ እግዚአብሔር” የተሰኘው ትምህርተ ሃይማኖት አሥራ አምስት አናቅጽ (መክፈያ ክፍሎች) ያሉት፤ የራሱ የሆነ መግቢያ እና መቅድም ኖሮት እንደ አስፈላጊነቱ እና እንደ አንቀጹ ስፋትና መጠን አልፎ አልፎ አንቀጾችን የሚከፍሉ ክፍላት(ክፍሎች) ያሉት ሆኖ የተዘጋጀ በጣም ጠቃሚ የሆነ መድበል ወይም ምዕላድ ነው:: መጽሐፉ በገጽ ብዙም ባይሆን ከፍተኛ የሆነ ትምህርተ መለኮት በከፍተኛ ደረጃ የተገለጸበት፤ የቀደሙትን ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት አስተምህሮ እና የሃይማኖት ርቃቄ የሚያሳይ ነው:: ሊቁ አለቃ ኅሩይ እንዳሉት “በቅጥነተ ሕሊና” የሚታየውን ትምህርተ ሥላሴ የሚያራቅቅ፣ ከመናፍቃን ኑፋቄ የሚጠብቅ ትምህርት ይዟል:: መጽሐፉ ከቅዱስ መጽሐፍ ቅዱስ እና ከልዩ ልዩ መጻሕፍተ ሊቃውንት መረጃዎችን በመጥቀስ በመረጃ የታገዘ ብስል መጽሐፍ ነው:: የመጽሐፉ ዋና ዓላማ ምሥጢረ ሥላሴን መግለጽ ነው:: ስለ “ስመ አካል”፣ ስለ “ስመ ኲነት”፣ ስለ “ስመ ግብር” በግልጽ ያስተምራል:: ይህ መጽሐፍ “”ወላዲ መለኮት” ፤ “ተወላዲ መለኮት”፤ “ሠራጺ መለኮት” ማለት እንደማይገባ ይናገራል:: (አንቀጽ አንድ) በአንድ መለኮት ሦስት ኲነት እንዳለ ይናገራል:: የመለኮት አንድነት አካላትን እንደማይጠቀልል የአካላትም ሦስትነት መለኮትን እንደማይከፍል ያስረዳል:: ይህ መጽሐፍ ሥላሴ በመለኮት አንድ የሚሆኑበትን ምሥጢር ያሳያል:: ከዚህም በተጨማሪ ሥላሴ በግብር በአካል በባሕርይ የሚጠሩበትን ስም ለይቶ ያሳያል:: ስለ ስመ ተረክቦ እግዚአብሔርም ማለት መለኮት ከማለት ጋር አንድ ሲሆን ልዩነት እንዳለው ይናገራል:: እንዲሁም የሥላሴ መንግሥት በአካል ከሦስት የማይከፈል አንድ መሆኑን ይናገራል:: “አብ” ማለት እና “ወላዲ” ማለት “ወልድ” ማለት እና “ተወላዲ” ማለት “መንፈስ ቅዱስ” ማለትና “ሠራጺ” ማለት ልዩ ልዩ እንደሆነ ይናገራል:: ወልድ ከሦስቱ አካላት አንዱ ሲሆን በተለየ አካሉ ሰው የሆነበትን ምሥጢር ያሳያል:: መለኮት የሚለውን ቃል በልዩ ልዩ ሥልት ተርጉሞ ያሳያል:: “ኃይል” “ክሂል” “ሥልጣንም” በአካል ከሦስት የማይከፈሉ መሆናቸውን ያስተምራል:: በአጠቃላይ ይህ መጽሐፍ ለትምህርተ መለኮት ደቀ መዛሙርት እና በሃይማኖት ለማደግ በትምህርተ ሥላሴ ለመራቀቅ በሃይማኖት ትምህርት ለመላቅ ለሚፈልጉ ሁሉ ግሩምና ድንቅ መልዕክት የያዘ መጽሐፍ ነው:: እኔም ይህን ጽሑፍ ለማንበብ ባገኘሁት ጊዜ ለንባብ በሚያዳግት ታይፕ ተጽፎ አንድ መቶ ገጽ ያለው ሆኖ አገኘሁት:: በአነበብኩት ጊዜ በጣም የበሰለ “ትምህርተ መለኮት” የተገለጠበት ትምህርተ ሊቃውንት ሆኖ አገኘሁት:: በመሆኑም የቀደሙት ሊቃውንት አስተምህሮ ለትውልድ እንዲተላለፍ በማድረግ የበኩሌን አስተዋጽኦ ለማድረግ እንደገና አቅንቼ ጽፌ ለአንባቢ በሚመች መንገድ አቅርቤዋለሁ:: ሊቁ የጠቀሧቸው መጻሕፍት ከታተሙት መጻሕፍት ጋር በምዕራፍ እና በቁጥር ስለማይገናኙ ከታተሙት መጻሕፍት ኃይለ ቃሉ የሚገኝበትን አብዛኛውን ምዕራፍ እና ቁጥር በመፈለግ ለማዛመድ ሞክሬአለሁ። የዚህን ጽሑፍ ባለቤት የጌታውን የታላቁ አለቃ ኅሩይ ታሪክም ከልዩ ልዩ ጽሑፎች አፈላልጌ በማግኘቴ አብሬ አሰባስቤ አሳትሜዋለሁ:: የቀደሙትን ሊቃውንት ትምህርት ለማግኘት ዕድል ያጋጠማቸው ደቀ መዛሙርት በየእጃቸው የሚያገኙትን ጹሑፎች በማሳተም ከአበው አስተምህሮ ትውልዱ እንዲሳተፍ እንዲያደርጉ ትልቅ ምሳሌ ይሆናል ብዬ እገምታለሁ:: ከዚህም ጋር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን የአስተምህሮ ሂደትና ስልት እንዲሁም የአስተምህሮ ምንጮችን ለመግለጽ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ትናንት እና ዛሬ” በሚል ርዕስ ጠቅላላ መግቢያ ሠርቸለታለሁ:: ይህም ወደፊት ለሚታተሙት መድበሎች ሁሉ ተቀዳሚ እንደ እሸት የሚቆጠር ሥራና ታላቅ ምሳሌ ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ::
 ========================================================
የአለቃ ኅሩይ ታሪክ
ልደት :- ከ፲፰፻፶፭-፲፱፻፵፰ (1855-1948) አለቃ ኅሩይ ፈንታ በጎንደር ክፍለ ሀገር በበጌምድር የሊቃውንት ምንጭ የድጓ ማስመስከሪያ የሊቃውንት መነሃሪያ በሆነችው በቤተልሔም ተወለዱ:: የተወለዱት በ፲፰፶፭ ዓ.ም መስከረም ፲፮ ነበር:: አባታቸው የተማሩ ሊቅ ከመሆናቸውም ባሻገር የቤተልሔምና የአካባቢዋ ሊቀ ካህናት ነበሩ:: ስማቸውም ሊቀ ካህናት ፈንታ ይባል ነበር:: እናታቸው ወይዘሮ ብሪቱ ይባሉ ነበር:: የአለቃ ኅሩይ ወላጆች ብዑላነ ጸጋ (ባለጸጎች) እንደነበሩ ይነገርላቸዋል:: ታላቁ የቤተ ክርስቲያን ሊቅ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ ስለ ጌታው አለቃ ኅሩይ በጻፉት አጭር የሕይወት ታሪክ ላይ “አባታቸው የወይን ጠጅ ድረስ የሚያጠጡ ባለጸጋ ነበሩ” ብለው በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ ከታደሉ ቅዱሳን ሰዎች መገኘታቸውን ተናግረዋል:: መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ዝክረ ሊቃውን ት ፲፱፻፷፫ ዓ.ም

ዕድገት :- የአለቃ ኅሩይ አባት የሊቀ ካህናት ፈንታ ድንገተኛ ሞትና የእናታቸው የወ/ሮ ብሪቱ ትጋት የአለቃ ኅሩይ ዕድገት፦ ሊቀ ካህናቱ አባታቸው በድንገት ስላረፉ በሕፃንነታቸው አባታቸውን ያጡትን ሕፃን በመልካም አስተዳደግ ለማሳደግና ለቁም ነገር ለማብቃት ወ/ሮ ብሪቱ በትጋት መሥራት ጀመሩ:: እንደ አባት እንደ እናት ሆነው በቁም ነገር በሥርዓት አሳድገው ትምህርት ቤት አስገቧቸው:: ብሩህ አእምሮ የነበራቸው የቀለም ሰው ስለነበሩ በአጭር ቀን ውስጥ ከንባብ እስከ ዜማ ያለውን ትምህርት አጠናቀቁ:: መልአከ ብርሃን ይህን ሁኔታ “አእምሮአቸው እንደተዳመጠ ብራና ቀለም የሚቀበል ስለሆነ ከንባብ እስከ ዜማ ያለውን ትምህርት በትንሽ ቀን አጥንተው በዚያው ወራት ቅጽል ከባለቤት ለይተው ዘርፍ ከባለቤት አስማምተው ተነሽና ወዳቂ ጠንቅቀው ሲያነቡ ዕጨጌ ቴዎፍሎስ ሰምተው ይህ ልጅ ታላቅ መምህር ይሆናል ብለው ትንቢት ተናግረውላቸዋል” በማለት ነበር የሊቁን የቀለም ሰውነት የሃይማኖት ዐምድ እንዲሆኑ ከእግዚአብሔር በተፈጥሮ ለእውቀት የታደሉ እንደነበሩ የገለጹት:: ክብርት እናታቸው ወ/ሮ ብሪቱም በልጅነቱ አባቱን ያጣው ሕፃን ረዳት አጥቶ በችግር ተፈቶ ትምህርቱን ትቶ የእናቱን ቤት ተመኝቶ ወደ ኋላ እንዳይመለስ ለትምህርት ጎጃም ሲሄዱ ጎጃም ድረስ ወደ ጎንደር ከተማም ሲሄዱ ጎንደር ከተማው ድረስ በበቅሎ በአህያ ስንቅ እያስጫኑ “ተማር የአባትህን ስም እንድታስጠራ ለቤተክርስቲያን ብርሃን እንድትሆን እኔ እናትህ እያለሁ ምንም የሚቸግርህ ነገር የለም” እያሉ እያበረታቱ በትምህርታቸው እንዲገፉበት ለዚህም ማዕረግ እንዲበቁ አደረጉአቸው:: ከዚህ የተነሳ አለቃ ኅሩይ ምንም እንኳ ሰው የተባለውን (የሆነውን) ሁሉ የሚወዱ ፍቅረ ቢጽ የተሰጣቸው ለሁሉም አክብሮትና ፍቅር ያላቸው የፍቅር ሐዋርያ ቢሆኑም ለእናታቸው ያላቸው ፍቅር የተለየ ነበር:: ይኸውም ሊታወቅ ጌታው አለቃ ኀሩይ አዲስ አበባ ቅድስት ሥላሴ አጠገብ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ በሰጧቸው ማረፊያ ቤት እያሉ የዕድሜ ባለጸጋ የሆኑት ታላቅ ወንድማቸው ሊጠይቋቸው ከቤተልሔም ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ:: አለቃ ኅሩይ “ሁሉን ልትነግረኝ ትችላለህ እናቴን ግን ሞተች ብለህ እንዳትነግረኝ:: የእናቴን ሞት ሳልሰማ እኔ መሞት እፈልጋለሁ” ስላሏቸው የእናታቸውን ሞት ሊያረዱ የመጡት ወንድማቸው ሳይነግሯቸው ተመልሰው ሄዱ:: ሌላም ጊዜ ሲመጡ ተመሳሳይ ነገር ስለተናገሯቸው ታላቅ ወንድማቸው አዝነው “እኔ እንዲህ ሸምግዬ እያየ እንዴት እናታችን በሕይወት ትኖራለች ብሎ ይገምታል” ብለው አዝነው ተመልሰው ሄደዋል:: እንዲህ እያሉ የመጣውን ሰው ሁሉ እየመለሱ የእናታቸውን መሞት ሳይሰሙ እርሳቸው አርፈዋል:: ይህም ለእናታቸው የነበራቸውን ፍጹም ፍቅር ያስታውሰናል:: ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ በቃል የነገሩኝ 1999 ዓ.ም፡፡

ትምህርት ቤት
ዕጨጌ ቴዎፍሎስና አለቃ ኅሩይ:- ከላይ እንዳየነው ዕጨጌ ቴዎፍሎስ የአለቃ ኅሩይን የተፈጥሮ ጸጋ ከተረዱ በኋላ በመንፈሳዊ አባትነታቸው አስበው የሊቀ ካህናቱን የአባታቸውን መሞት አውቀው ስለነበር ከእናታቸው ድጋፍ በተጨማሪ በችግር ምክንያት ትምህርታቸው እንዳይቋረጥ በማሰብ ቀለብ አዘውላቸው ነበር:: በወቅቱ የድጓ ምስክር ከነበሩት ከመምህር ደርሶ "ዜማ" እንዲማሩ ያደረጓቸው ዕጨጌ ቴዎፍሎስ ናቸው:: የአለቃ ኅሩይን የትምህርት ቤት ሕይወት ስለ አለቃ ኅሩይ ታሪክ ከጻፉት ሊቃውንት መካከል ጥሩ አድርገው የጻፉት “ዘወትር ከጉባኤያቸው እየተገኙ የተሰወረውን ምሥጢር የምሥጢር ባለቤት ከሆኑት ከአለቃ ኀሩይ ይረዱ ነበር” ብለው ሊቀ ሊቃውንት መሐሪ ትርፌ (አቡነ ጴጥሮስ ሊቀ ጳጳስ ዘጎንደር) ስለአለቃ ኅሩይ ታሪክ ሲጽፉ የጠቀሷቸው የዲማው ሊቅ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ ናቸው:: መልአከ ብርሃን አድማሱ “ዕጨጌ ቴዎፍሎስ ቀለብ ሰጥተው የድጓ ምስክር ከነበሩት ከመምህር ደርሶ ዜማ እንዲማሩ አድርገዋቸዋል:: እሳቸውም (አለቃ ኅሩይ) በዚህ ትምህርት ቤት ድጓ አንድ ጊዜ ከዘለቁ በኋላ ተድባበ ማርያም ሂደው አለቃ ወረደ ቃል ከሚባሉት መምህር ቅኔ ተምረው ተቀኝተው እንደገና ጎጃም ተሻግረው አጋሜና ቢሰውር ከሚባሉት ስመ ጥር መምህራን ቅኔውን አስፍተው እስከ አገባቡ ጠንቅቀው አውቀው ወደ ሀገራቸው ተመልሰው እንደገና ድጓውን መላልሰው አጥንተው ለምስክርነት ተመርቀዋል:: መምህር ደርሶም በእኔ እግር ተተክቶ የድጓ ምስክር ይሆናል እያሉ ሲያስቡ ልቦናቸው ወደ መጻሕፍት ትምህርት ስላዘነበለ ጎጃም ተሻግረው ደብረ ጽላሎ ከአለቃ እንግዳ ብሉያትን አጠኑ:: ከዚያም ጎንደር ሂደው ከታላቁ መምህር ከወልደ አብ ወልደ ሚካኤል በጥቂት ቀን የሐዲሳትን ትርጓሜ አጥንተዋል:: በዚያው ጊዜ (ጎንደር ሳሉ) አዕምሮ ከሚባሉ የአቋቋም መምህር አቋቋም ተምረዋል:: ድምፃቸው በተፈጥሮ መልካም ከመሆኑም በላይ ዜማ ያሸው ስለሆነ በጎንደር ባህል ሲዘሙ ሲመረግዱ ዚቅ ሲያወርዱ መልስ ሲመልሱ “እንስማው የሚባሉ እጅግ የተመሰገኑ ነበሩ” ብለው ጽፈውላቸዋል::  ዝኒ ከማሁ አድማሱ ጀምበሬ (መልአከ ብርሃን) ዝክረ ሊቃውንት በ፲፱፻፷፫ ዓ.ም፡፡ ጎንደርን ድርቡሽ እንዳጠፋው ሊቃውንት እንደተሰደዱ ለብዙ ዘመናት የኢትዮጵያ ሥጋዊና መንፈሳዊ ሥልጣኔ፣ አስተዳደር፣ ዕውቀት ማዕከል፣ የሊቃውንት መንደር፣ የመላው የኢትዮዽያ መናገሻ ማዕከል ሆና ትኖር የነበረችውን ጎንደርን የእስላም ኃይል ገብቶ ባቃጠላት ጊዜ ሊቃውንቱ እያዘኑ እያለቀሱ ከእሳትና ስለት የቀሩት ለዘር ይተርፉ ዘንድ ተሰደዱ:: እነ መምህር ወልደ አብ ወልደሚካኤልን ጨምሮ ብዙ ሊቃውንት በእስላሞች ሰይፍ ታረዱ:: ከሞት የተረፉትም ብሶታቸውንና የሀገራቸውን ጥፋት በቅኔያቸው እያስታወሱ እያለቀሱ ተሰደዱ:: በ፲፰፻፹፰ (1888) ዓ.ም ጎንደርን ድርቡሽ ባቃጠላት ጊዜ ከአንድ ሊቅ የተደረሰ የሐዘን እና የጸጸት መወድስ ቅኔ እነሆ:-
ሠናይተ ሡራሬ ጎንደር ተስፋ ነዳያን
ወተስፋ መኳንንት ጎንደር እንበለ መሥፈርት ወአቅም::
ርግበ ዮሐንስ ጎንደር ርኅርኅተ ልብ እም::
ጎንደር ዘበላዕሌሃ ኢሀሎ ሕማም::
ጎንደር እድምተ ስም::
መካነ ተድላ ጎንደር ወመካነ መብልእ ጥዑም::
ጎንደር ቤተ ኢያሱ ወቤተ በካፋ ግሩም::
ጎንደር ዘትሤንያ ለሀገረ ዳዊት ምድረ ሰላም::
መሐድምተ ትኩን እስከ ለዓለም::
እፎኑ ተመዝብረት እንበለ ፍዳሃ ከመ ሶዶም:: አድማሱ ጀምበሬ (መልአከ ብርሃን) ዝክረ ሊቃውንት ፲፱፻፷፫ ዓ.ም
 ================================================
በዚህ ክፉ ዘመን ከተሰደዱት መካከል አንዱ አለቃ ኅሩይ ከመምህር ወልደ ጊዮርጊስ ጋራ ወደ ቤተልሔም ወደ መካነ ትውልዳቸው ተመለሱ:: “ቤተልሔም ጥቂት ቀን ከቆዩ በኋላ ወደ ግሸን ሄደው የሐዲስ ኪዳን ትርጓሜና አቋቋም ሲያስተምሩ ቆይተው ወደ ደብረ ሊባኖስም በመሔድ ጉባኤ ዘርግተው ሲያስተምሩ ነበር:: በዚህ ጊዜ ነበር ራስ ዳርጌ የሊቁን ብቃት በመመልከት የሥሬ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አለቃ እንዲሆኑ የጠየቁአቸው:: እርሳቸው ግን መናኝ በመሆናቸው መጽሐፍ በመመልከት ዘመናቸውን እንዲፈጽሙ ስለወሰኑ ሹመቱን አልፈልግም ብለው ትተውት ወደ አዲስ አበባ መጥተው መዝሙር ካሣ ከሚባሉት ከጎንደሩ ሊቅ መጽሕፍተ ሊቃውንትን አጠኑ:: ከዚያም ደብረ በግዕ ወርደው ከአለቃ ወልደ ማርያም ሊቃውንትን አደረሱ።” (አስመሰከሩ) በማለት መልአከ ብርሃን አድማሱ የአለቃን ታሪክ በጻፉበት አምዳቸው ዘግበዋል:: ከዚህ በመቀጠል የታላቁን ሊቅ የጌታው አለቃ ኅሩይን ትጋትና ምሥጢር ለማደላደል ለማራቀቅ ነገረ እግዚአብሔርን ያውቁ ከነበሩት ሊቃውንት ጋር በመወያየት የልቦና ደስታ ያገኙበት እንደነበር፣ ዕለት ከዕለት ከኃይል ወደ ኃይል ይራመዱበት፣ መጻሕፍትን ማንበብ ዋና የዕለት ተለት ተግባራቸው ሁኖ ይኖሩ እንደነበር ሲያስገነዝቡ “ከዚህ በኃላ ወደ ጎጃም ተሻገሩ:: በዚያን ጊዜ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ነበሩና አክብረው ተቀብለዋቸዋል:: እርሳቸው ግን በመጻሕፍት ፍቅር ብቻ የተወሰኑ ስለሆኑ ደጅ ልጥና ልሾም ልሸለም ሳይሉ ብሉያትን ከብሉይ መምህራን ከነ መምህር ሰውአገኘሁ፣ ከእነ መምህር ጸበሉ፣ ከእነ አለቃ ገብረ ኤልያስ፣ መጻሕፍተ ሊቃውንትን ከእነ አለቃ ተስፋ፣ ከእነ ሊቀ ጠበብት ወልደ ሥላሴ፣ ከእነ መልአከ ሰላም ገብረ ማርያም፣ ከእነ መምህር እንግዳ እሸት ጋራ እየተጨዋወቱ ሐሳብ ለሐሳብ ከተለዋወጡ በኋላ አዋልድ መጻሕፍት በያይነቱ ከሚገኙባቸው ደሴቶችና ገዳማት በነዘጌ፣ በነክብራን፣ በጣና ቂርቆስና በዲማ እየተዘዋወሩ ተመለከቱ:: ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ብዙ ተማሪ ይከተላቸው ነበርና አንድም ቀን ጉባኤ ፈትተው አያውቁም” በማለት መልአከ ብርሃን የጌታው አለቃ ኅሩይን የቀለም ሰውነት፣ አንባቢ ተመራማሪ የትርጓሜ ሰው እንደነበሩ መስክረዋል:: መልአከ ብርሃን አድማሱ በጉባኤያቸው እየተገኙ ማወቅ የሚፈልጉትን ምሥጢር ለመጠየቅ ከአለቃ ኅሩይ ጉባኤ ቤት ይገኙ ስለነበር በዓይናቸው ያዩትን በጀሮአቸው የሰሙትን የታላቁን ሊቅ የጌታው አለቃ ኅሩይን የዕውቀት ብቃት፣ የአእምሮ ምጥቀት፣ የአስተሳሰብ ብስለት፣ የትርጓሜ ስልት ባለቤትነት፣ የጠፋ መገኛ የተሰወረ መገለጫ፣ አንቀጸ መጻሕፍት መሆናቸውን ሲገልጹ “የተፈጥሮ እውቀታቸውን በትምህርት ስላስፋፉት ትምህርታቸውንም መጽሐፍ በመመልከት ስላደረጁት የጠፋ ንባብ የተሰወረ ምሥጢር ከእርሳቸው ይገኝ ነበር:: አለቃ ኅሩይንም ጠይቆ ሳይረዳ የሚሄድ አልነበርም” በማለት ሊቁ መልአከ ብርሃን ያዩትን መስክረዋል:: አለቃ ኅሩይ በ፲፱፻፬ (1904) ዓ.ም ከጎጃም ወደ ጎንደር ሄደው ነበር:: በወቅቱ የነበሩት ንጉሥ ወልደ ጊዮርጊስም አክብረው ተቀብለው ጸዳ እግዚአብሔር አብን ልቅና ልስጠዎት ይሾሙ ቢሉአቸው አይሆንም ስላሉአቸው የሹመት ፍላጎት የጠፋላቸው ቅዱስ ሰው መሆናቸውን አውቀው ሸልመው ከእነ ተማሪያቸው የሚመገቡትን ቀለብ ሰጥተዋቸው በጎንደር ለሦስት ዓመታት ጉባኤ ዘርግተው አስተምረዋል::
==============================================
የኢየሩሳሌም ጉዞ
ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌምን ለመሳለም ከጎንደር ወደ አዲስ አበባ በ፲፱፻፲፮ ዓ.ም መጥተው ኢየሩሳሌምን እጅ ነሥተው ተመልሰዋል:: ከዚህ በኋላ ደብረ ሊባኖስ ገብተው ጉባኤ ዘርግተው ሲያስተምሩ ቆይተዋል:: ከዚያም በኋላ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አልጋ ወራሽ በነበሩበት ጊዜ ቅዱሳት መጻሕፍት እየተተረጎሙ ሲታተሙ ተጠርተው መጥተው ከሌሎች ሊቃውንት ጋር ሆነው ወንጌልን ተርጉመው አሳትመዋል:: መልአከ ብርሃን እንደገለጹት ከመጻሕፍተ ሊቃውንትም ቄርሎስን ንባቡን ከነትርጓሜው አዘጋጅተው አስረክበዋል:: ከዚህ በተጨማሪ "የቤተ ክርስቲያን ጸሎት" በሚል ርዕስ ተዘጋጅቶ የቀረበው በስደት ዘመን ቤተ ክርስቲያን ትጠቀምበት የነበረው መጽሐፍ አዘጋጆች ከሆኑት አንዱ አለቃ ኅሩይ ነበሩ:: ሊቀሥልጣናት ሀብተ ማርያም ወርቅነህም “ጥንታዊ የኢትዮጵያ ትምህርት” በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጻሕፋቸው “ሐዲስ ኪዳንን የተረጎሙት ንቡረ ዕድ ተክሌ (ሐዲስ ተክሌ)፣ አለቃ ኅሩይ ዘጎንደር፣ አለቃ ለማ ዘመካነ ሥላሴ፣ አለቃ ቀጸላ ዘእንጦጦ ማርያም፣ እንደ አንድ ልብ መካሪ ሆነው በየክፍላቸው በቅንነት ሠርተው ያበረከቱ ናቸው:: ሥራቸውም ቋሚና ዘላቂ ሆኖ እነርሱንና ንጉሠ ነገሠቱን ሲያስታውስ ይገኛል” ብለው ለቤተክርስቲያን መጻሕፍትን በመተርጎም ታላቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ዕውቅና ታላቅ ሊቅ እንደነበሩ ከላይ የተመለከትናቸው መልአከ ብርሃንና ሊቀ ሥልጣናቱ ቋሚ ምስክሮች በመሆን ሊቁን በሥራቸው እንድናውቃቸው አድርገዋል:: (ሊቀ ሥልጣናት ሀብተ ማርያም ወርቅነህ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ትምህ ርት) ነገር ግን ባልታወቀ ምክንያት የደከሙባቸው መጻሕፍት ለኅትመት አልበቁም:: አለቃ ኅሩይ አበ ብዙኀን ናቸው:: “ዕድለ መልካም ሊቅ ስለነበሩ በጉባኤ የወለዷቸው ደቀ መዛሙርት እጅግ ብዙዎች ናቸው” ዛሬ በመላው ኢትዮጵያ ሊቃውንትን የሚያፈሩ ሊቃውንት የሳቸው የቀለም ልጆችና የልጅ ልጆች ናቸው:: ደቀ መዝሙራቸው የነበሩት አቡነ ጴጥሮስ ስለ አለቃ ኅሩይ ሲጽፉ “ታላቁ ሊቅ አለቃ ኅሩይ መጻሕፍተ ሐዲሳትንና መጻሕፍተ ሊቃውንትን የዕለት ተግባራቸው አድርገው በጉባኤ ሲያስተምሩ አርባ ዘመን ያህል ቆይተዋል:: መጻሕፍተ ሐዲሳትን በማስተማርእስከ ዕለተ መቃብር ቆይተዋል:: በዚህ ድካማቸው ጊዜ ብዙ ደቀ መዛሙርትን ተክተዋል” ካሉ በኋላ ለምሳሌ ያህል የስምንት ሊቃውንትን ስም ዘርዝረዋል:: ታላቁን ሊቅ ጌታው ዶክተር አለቃ አየለን ጨምሮ ሊቀ ሊቃውንት መኀሪ ትርፌ (ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሊቀ ጳጳስ ዘጎንደር) ፣ አባ ዘካርያስ ንቡረ ዕድ መኩሪያ፣ መምህር ወንድም አገኘሁ፣ አባ ጌድዮን፣ አለቃ ገ/መድኅን፣ አባ ገ/አምላክ ከደቀ መዛሙርቶቻቸው መካከል እንደ ምሳሌ የሚጠቀሱ ናቸው:: አለቃ ኅሩይ ፍፁም መናኝ ነበሩ:: “አለቃ ኅሩይ ከዚህ ዓለም ክብር የራቁ በመሆናቸው ከቶ አንድ ጥሪት አልነበራቸውም” ካሉ በኋላ ሊቀ ሊቃውንት መሐሪ ትርፌ ከአፄ ኃ/ሥላሴ ጋር ስለነበራቸው ቀረቤታና በጉባኤያቸው ተገኝተው የከበዳቸውን ምሥጢር ይጠይቁ ስለነበሩ ሊቃውንት፣ ስለተሰጣቸው ዕሤተ አንብዕ፣ ከብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ጋራ ስለነበራቸው ጽኑ ፍቅር እና ስለመጨረሻው ዕረፍታችው የሚከተለውን ጽፈዋል:: አለቃ ኅሩይ የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ የጠበቁ እውነተኛ መምህር ስለነበሩ ግርማዊነታቸው ከዕልፍኛቸው አስቀምጠው በሚያስፈልጋቸው ሁሉ እየረዱ በየዕለቱ ይጎበኟቸው ነበር:: አለቃ ኅሩይ ግርማዊነታቸውን በሚያዩበት ጊዜ ሁሉ ከፍቅራቸው ጽንዓት የተነሳ ደዌያቸውን ሁሉ ይዘነጉት ነበር:: አለቃ ኅሩይ ዕሤተ አንብዕ የተሰጣቸው ስለነበሩ በቅድስት ሥላሴ አጠገብ ግርማዊነታቸው በሰጧቸው ቤት ሳሉ ትሕትና ገንዘባቸው የሚሆን ግርማዊነታቸው ሊጠይቋቸው ሲሄዱ ለማናገር በሩ በተከፈተ ጊዜ ዕንባቸው በሚጸልዩበት አርጋኖን ላይ ሲንጠባጠብ ታይቷል... ሊቃውንቱን የሚንከባከቡ ግርማዊነታቸው እኒህን ሊቅ እንደ ዐይናቸው ብሌን ይንከባከቧቸው ስለነበረ አስታመው አማውተው እስከ መቃብር ሸኝተው ተመልሰዋል:: ...የአለቃ ኅሩይ ሞት ሞት አይባልም ከልባቸው ፈልቆ የአርድእትን ልቡና ያረካው ትርጓሜያቸው አካል ገዝቶ ስለተገኘላቸው:: አለቃ ኅሩይ ከትዕግሥታቸው ብዛት የተነሳ የሐረሩ ሊቅ አለቃ ገብረ አብ ዲያብሎስ ቅሉ ድል ሊነሣቸው አይችልም ብለው የተናገሩት ነገር ሲነገር ይኖራል:: አለቃ ኅሩይ በነበሩበት ጊዜ በአዲስ ዓለም ማርያም የነበሩት ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ በዕየለቱ ሊጠይቋቸው ሲመጡ የነበረ ፍቅር ልክ አልነበረውም:: ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ እንደ አረፉ በሰሙ ጊዜ ጉባኤውን አጥፈው በኀዘን ቆይተው የፍቅራቸው ብዛት ሊታወቅ ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ በዐረፉ በአርባ ቀን አለቃ ኅሩይ ዐርፈው በደብረ ሊባኖስ ተቀበሩ:: የሐረር ሥላሴ አለቃ፣ አለቃ ለማም ከአለቃ አየለ ሃይማኖተ አበውን ለመስማት ዘወትር ከአለቃ ኅሩይ ጉባኤ ይገኙ ነበር:: የዲማው ሊቅ መልአከ ብርሃን አድማሱም ዘወትር ከጉባኤያቸው እየተገኙ የተሰወረውን ምሥጢር የምሥጢር ባለቤት ከሆኑት ከአለቃ ኅሩይ ይረዱ ነበር:: የአለቃ ኅሩይ ታሪክ ብዙ ነበር:: ከብዙ በጥቂቱ በዚህ መጽሐፍ ገልጸነዋል። (ሠለስቱ ሐዲሳት ገጽ ፬፻፹፭) በማለት ነው አባታችን ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ቋሚ ምስክርነታቸውን የተውልን:: በተመሳሳይ መንገድ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬም የአለቃ ኅሩይን አጭር የሕይወት ታሪክ ሲያጠቃልሉ “በእንደዚህ ያለ አኳኋን ከቆዩ በኋላ እርጅና ከደዌ ጋር ተጭኗቸው ከቤት በዋሉ ጊዜ የሰው ውለታ የማይቀርባቸው ግ/ቀ/ኃ/ሥላሴ በቤተ መንግሥታቸው ውስጥ የተሰናዳ ማረፊያ ቦታ ሰጥተው እጅግ በተመቻቸ አያያዝ ሲረዱ ቆይተው በ፺፰ ዓመታቸው በ፲፱፻፵፰ ዓ.ም ሐምሌ ፲፮ ቀን ዐርፈው በደብረ ሊባኖስ ተቀብረዋል” ብለዋል:: በሃይማኖት ወደ ሚናፍቋት በቃለ መጻሕፍት ወደ ለመዷት ወደ ርስተ ቅዱሳን ወደ ሕጽነ አብርሃም ወደ ማታልፈው መንግሥተ እግዚአብሔር ሄደዋል:: ይህንንም በተመለከተ መምህር አባ ዓለሙ በላይ የብፁዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስ ባልንጀራ በቃል ከብፁዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስ የሰሙትን ታሕሣስ 18፤ 2001 ዓ.ም እንደሚከተለው አጫውተውኝ ነበር፤ “አለቃ ኅሩይ ማክሰኞ ሊያርፉ እሁድ ቀን መምህር ያሬድ (አቡነ መርሐ ክርስቶስ) ምሥጢር እየጠየቁ ሳለ “እኽ ሳላመልጥህ ጠይቅ፤ ላመልጥህ ነው ጠይቀኝ” አሏቸው አለቃ፤ አቡነ መርሐም ጌታው እድሜዎ ሰፊ ነው፤ ይበቃዎታል ግን እኔ የሃይማኖተ አበውን ምሥጢሩን ሳልረዳው የተማርኩትን ከፊትዎ አንብቤ ሳልዘልቀው በመሞትዎ ብቻ ነው የማዝነው አሏቸው፤ “አዎ እኔም ለብዙ አስቤህ ነበር ግን ሐዲሳቱን አውቀኸዋል፤ ከሐዲሳቱ የወጣ ምሥጢር በሃይማኖተ አበው የለም፤ ያንኑ ምሥጢሩን በምሳሌ ማብዛት መግለጽ ነው እንጂ፤ ለሁሉም ምዕላዱን አንብበው፤ ነገር ያለበትን እና ኃይለ ቃሉን በምዕላዱ ላይ አውጥቼዋለሁ” አሏቸው፤ ሰኞ አንደበታቸው ተያዘ፤ ማክሰኞ አረፉ፤ ቀደም ብለው ራሳ ካሳ መጥተው “ቀብርዎት የት ቢሆን ይወዳሉ ቅድስት ሥላሴ ይሁን ወይስ ደብረ ሊባኖስ ነው የሚፈቅዱት” አሏቸው፤ አለቃም “ፈቃዴ ደብረ ሊባኖስ ቢሆን ነው፤ ግን ፈራሽ ሥጋ ተሸከሙ አልልም፤ እግዚአብሔር ከፈቀደው ይውደቅ” አሉ፤ ከዚህ በኋላ ሲያርፉ የቤተ ክርስቲያኑ ደወል ተደወለ፤ ቅድስት ሥላሴ ከቤተልሄሙ መቃብር ተቆፍሮ ነበር፤ ነገር ግን ራስ ካሳ በኋላ ደረሱና “የለም አይሆንም ደብረ ሊባኖስ ነው የሚሄዱ” ብለው ደብረ ሊባኖስ ወስደው ቀበሩአቸው፤ አጼ ኃይለ ሥላሴም ደብረ ጽጌ ድረስ ሸኝተው ተመልሰዋል” ብለውኛል። ቅዱስ ያሬድ የጥናት እና የተራድኦ ማዕከል የቀደሙትን አባቶቻችንን ትምህርት፣ ጥበብ፣ ታሪክ ለትውልድ ለማስተዋወቅ ለማቆየት የጀመረው የሥራ ፍሬ በታላቁ ሊቅ በጌታው አለቃ ኅሩይ ታሪክ እና ትምህርተ ሃይማኖት በመጀመሩ ታላቅ ደስታ ይሰማዋል። በረከተ አበው መምህራን አይለየን!
=================================================
ቅኔዎች
ለመታሰቢያ ከቀረቡት ከአለቃ ኀሩይ ቅኔዎች ጥቂቶቹ
መወድስ ፩
ሰብዓ አዝማነ አርድተ ብካይ እም ሕዝበ ዘመኑ ዮሐንስ ለስብከተ ሐዘን ሐረየ፤
ወማዕከለ ኀዘን ፍኖቱ ለእመ ጸምአ ብካየ፤
አምነ ሳምራዊት ሰአለ ዐይነ ወንጌላዊ ከመ ይስተይ ማየ፤
ሕዋሳቲሁ ሐዋርያት እስመ ሀገረ ሞት ቦኡ ለተሳይጦ ሲሳየ፤
ተጋብኡሂ ገጻቲሁ ማዕከለ አዕይት ዝየ፤
ላዕለ ዕፅ ከመ ይሰቅሉ ህሊና ዘኢጌገየ፤
ወውስተ ካልዑ መብልዕ ሐሞተ ምሳሌ ወደየ፤
በሕለተ ወይን ትርጉሜሁ ስታየ ስሙ እስመ ዐበየ፤
መወድስ ፪
ሞተ ፍጡራን ተምህረ ገቢረ ትሕትና አንቃዕዲዮ ኢይርአይ ገጸ አረጋዊ በዐይኑ፤
ባህቱ ይብለነ ዉስተ ደብረ ዳሞ መካኑ፤
እንበለ ውእቱ አረጋዊ ሥጋ ሰብእ ለቢሶ ዘሞአኒ መኑ፤
ንንግር ወንዜኑ፤
ከመ ከመ ሊቁ ኤልያስ ለአረጋዊ መጠኑ፤
ለሕያዉኒ ገብረ ክርስቶስ ላዕካነ ምሥጢር ይኩኑ፤
ካህናተ ሰማይ ሕማማት መንበረ ሥጋሁ ዘየትጥኑ፤
ወእም ሐዋርያት ገድላት እለ ተአመኑ ዮሐንስ ዐፄ ሥጋ ዘረፈቀ ውስተ ሕፅኑ፤ (የግዕዝ ቅኔያት የሥነ -ጥበብ ቅርስ ንባብና ትርጓሜው ከኢትዮጽያ ቋን ቋዎች አካዳሚ 1980)
መወድስ ፫
አሣዕነ ገባዖን ነሥአ ውስተ ደብረ ዘይት መከልአ ምድያም ቃል መግቦተ ርእሱ ኀበ አእመረ፤
ወበአልባሰ ብርት ገባዖን ዕርቃነ መልአክ ሰወረ፤
ለኢየሩሳሌም እንዘ ቅርብት መላክ በጊዜ ነገደ ርህቅተ ምድረ፤
ኢያሱ እሰከ ሰአለ ለማዕረረ ቃሉ ድንግል ከመ ይፈኑ ገባረ፤
ወገባዖን ቀዳማዊ ድኅረ በምሳሌ አንጸረ፤
ጸወርተ ዕፀው ከመ ይኩኑ ለቤተመቅደስ ዘተመዝበረ፤
ሥጋ ወቃል ተሰናዕዎ ዕፅ አንበረ፤
እብነ ዘለፋ መልዕልተ ወርቅ ብልጣሶር ዘአንበረ፤ ( አድማሱ ጀንበሬ:: መጽሐፈ ቅኔ በ ፲፱፻፷፫ ዓ.ም)
===================================