Wednesday, October 24, 2018

የቅዱስ ፓትርያርኩ ነገር ግራ እየገባኝ ነው



===========================
[ፓትርያርኩ “ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር አልታረቅሁም፤ እስከምሞት እረግመዋለሁ” አሉ:: ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ ከማኅበረ ቅዱሳን ጋራ እንዳልታረቁና እስከሞት ድረስ እንደሚረግሙት ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተናገሩ]
ይህ ዜና አባ ማትያስ ላይ ያለንን የአባትነት ስሜት ክፉኛ የሚጎዳ ነው፡፡ አባ ማትያስ ከበፊት ጀምሮ ቃላቸው ኹለት ነው፡፡ አሜሪካ እያሉ ማኅበረ ቅዱሳንን እግዚአብሔር ያስነሣችሁ ለቤተክርስቲያን እጅግ የምታስፈልጉ ናችሁ እያሉ ሲያሰግኑ ነበር፡፡ ፓትርያርክ ኾነው አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ ግን ነገሮች እየተቀየሩ መጡ፡፡ እርሳቸውም ማኅበረ ቅዱሳንን እቃወመዋለሁ ቤተክርስቲያናችንን ቅኝ የገዛ ማኅበር ነው ብለው ተናገሩ፡፡
ስለሦስተኛው ፖትርያርክ አቡነ ተክለ ሃይማኖትም እንዲሁ ያለ ኹለት ምላስ የኾኑበት አጋጣሚ ነበር፡፡ በቪኦኤ ቃለ መጠይቅ ሲደረግላቸው አቡነ ተክለሃይማኖትን ፖለቲከኛ እንደኾኑ፣ አባትነታቸው ትክክል እንዳልኾነ፣ ቤተክርስቲያንን ማስተዳደር እንደማይችሉ ወዘተ ገልጸዋል፡፡ እንዲያውም በጣም ሰድበዋቸዋል፡፡ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ስለእርሳቸው ሲጠየቁ ግን የሰጡት ምላሽ በፍጹም እርሳቸውን አልተሳደብኩም፡፡ እንዲያውም እርሳቸው ደግ መናኝ ነበሩ ወዘተ ብለው መለሱ፡፡
ከዚህ ኹሉ የምንረዳቸው አቡነ ማትያስ አእምሯቸው ትክክል እንዳልኾነ ነው፡፡ ምናልባትም ሌት ከቀን ከጎናቸው ኾኖ አቋማቸውን ሳፋ ላይ እንዳለ ውኃ እንዲዋልል የሚያደርጋቸው ኃይል ያለ ይመስለኛል፡፡
ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር ታረቁ ተብሎ እርሳቸውም ታርቄያለሁ ብለው አቡነ ቀውስጦስም ይህንኑ አብሥረውን የቤተክርስቲያን ችግር ተፈታ እያልን ባለንበት ጊዜ በፍጹም አልታረቅሁም ማለት ምን ማለት ነው? የጤና ይመስላችኋል ግነ? እኔ የጤና አይመስለኝም፡፡ አንድ ፓትርያርክ እንዲህ በኹለት ምላስ ሲዋቀሩ ማየት ይከብዳል፡፡ እስከሞት ድረስ እረግመዋለሁ ማለታቸው እርቃቸውን ለታይታ ያደረጉ መኾናቸውን የሚጠቁም ነው፡፡
በዚህ ዓይነትማ ከውጩ ሲኖዶስ ጋርም አልታረቅሁም ማለታቸው አይቀርም እኮ፡፡ አሁን የሊቃነ ጳጳሳት ምደባ ሲጀመር እገሌ አይመደብም ከውጭ የመጣ ነውና ማለታቸው አይቀርም፡፡ አባታችን ምነው ታርቀን የለምን? ሲሏቸው ደግሞ እኔ ዶ.ር ዓቢይ ደስ እንዲለው ብየ እንጅ እስክሞት ድረስ አወግዛቸዋለሁ ማለታቸው አይቀርም፡፡
ምልዓተ ጉባዔው ግን የአባ ማትያስን ጉዳይ አይቶ ከፓትርያርክነት እስከማውረድ ድረስ መድረስ አይችልም ወይ? እርሳቸው እኮ የማይመከሩ የማይዘከሩ እየኾኑ ነው፡፡ በመንግሥት ተጽእኖ ፓትርያርክ የኾኑ እንደኾነ ፀሐይ የሞቀው ዓለም ያወቀው ጉዳይ ነው፡፡ ታዲያ ዛሬ ቤተክርስቲያን ነጻ ስትኾን አባ ማትያስን ማረም እንዴት ለምልዓተ ጉባዔው ከበደ?
ከውስጥ ያለው የዘረኝነት መንፈስ ግን ብዙ ሊቃነ ጳጳሳትን እያስለቀሰ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ የኦሮምያ ጠቅላይ ቤተክህነት፣ የአማራ ጠቅላይ ቤተክህነት፣ የትግራይ ጠቅላይ ቤተክህነት ብለው ለመከፋፈል እየሠሩ ያሉ ከፋፋዮችም አሉ፡፡ መንፈስ ቅዱስን አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ ብለው ሊከፋፍሉት ይታትራሉ አሉ፡፡ ለማንኛውም እግዚአብሔር አምላክ የጠላት ምክሩን ያፍርስልን፡፡
ትልቁን የቤተክርስቲያን ሸክም አባ ማርቆስን ካነሡልን በኋላ እያሰብን ያለነው ማን ይመደብልን ይኾን? የሚለውን ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ በመጀመሪያ የሃይማት ሕጸጽ ያለባቸውን ሊቃነ ጳጳሳት ለይቶ መምከር ማስተማር ካልተመለሱም አውግዞ መለየት ይኖርበታል፡፡ ለምሳሌ፡- ከውጭ ከመጡት መካከል አባ ወልደ ትንሣኤ የአሁኑ አባ በርናባስ፣ አባ ሀብተ ማርያም የአሁኑ አባ መልከጼዴቅ ወዘተ እነዚህን ሊቃነ ጳጳሳት በመጀመሪያ መምከር ያስፈልጋል፡፡ ወልድ አማላጅ ነው እያለ የሚሰብክን ሰው ሊቀ ጳጳስ አድርጎ መመደብ ችግሩን ያብሰዋል፡፡
ከሀገር ውስጥ ደግሞ እነ አባ ማርቆስ፣ እነ አባ ቶማስ ወዘተ መታየት አለባቸው፡፡ ምእመናን ከቅዱስ ሲኖዶስ በላይ እንዲኾኑ መጠበቅ የለባችሁም፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ልእልናውን ማስከበር አለበት፡፡
====================
ጥቅምት 14/2011 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ

Tuesday, October 23, 2018

‹‹ወነሰተ ምክሮ ለጸላዒ- የጠላት ምክሩን አፈረሰ›› የደርሶ መልስ ዘገባ!



=====================
የምሥራቅ ጎጃም የተዋሕዶ ልጆች ‹‹ዝ ሕዝብ አብ ወአኮ ጠቢብ - ይህ ሕዝብ ሰነፍ ነው ጥበበኛ አይደለም›› የተባለለት ሰነፍ ሳይኾን ጥበበኛ የኾነ ይህ ቃል ተገልብጦ የሚነገርለት ‹‹ዝ ሕዝብ ጠቢብ ወአኮ አብድ- ይህ ሕዝብ ጥበበኛ ነው ሰነፍ አይደለም›› ተብሎ የተመሰከረለት ጠቢበ ጠቢባን ነው፡፡ ከመነሻው እስከመድረሻው ድረስ ምን ማድረግ ምን መደረግ እንዳለበት የሚያውቅ ጥበበኛ ነው፡፡


አቡነ ማርቆስ ምሥራቅ ጎጃምን ከያዙበት ሕዳር 2004 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ 7 ዓመታት ተቆጥረዋል ወር ቢቀራቸውም፡፡ በእነዚህ ሰባት ዓመታት በትዕግሥትና በጽናት ለ12ኛ ጊዜ ቅዱስ ሲኖዶስ ላይ አቤት ያለ ታጋሽ ሕዝብ ነው፡፡ ምሥራቅ ጎጃም በጀግንነቱ በላይ ዘለቀ አለለት ልጀግን ካለ እንደ አባ ኮስትር በላይ ይጀግናል፡፡ ልታገስ ካለም እስከሞት ድረስ ራሱን አሳልፎ ይሰጣል፡፡ ለወደደው ማር ለጠላው ኮሶ ማለት ይኸው ነው፡፡ እንዲያውም ስንክሳር ዘጎጃም የሚባል አለ አሉ፡፡ ስንክሳሩ ወበዛቲ ዕለት አእረፈ አባ ኮስትር በላይ ይላል፡፡ ሲጨርስ ደግሞ ጀግንነቱ ወንድነቱ ይኅድር በላእሌነ ይላል አሉ፡፡ ይችን የጎጃም ስንክሳር የሰማኋት አባ ማርቆስ እንዲነሡልን ቅዱስ ሲኖዶስን ለመጠየቅ መንበረ ፓትርያርክ በተገኘሁበት ጥቅምት 11/2011 ዓ.ም ነው፡፡
የተመለከተን ኹሉ ‹‹ኦ ትእግሥት ዘመጠነዝ ትዕግሥት ኦ ትሕትና ዘመጠነዝ ትሕትና›› የተባለለትን ክርስቶስን መሰላችሁ እኮ ይለናል፡፡ እርሱ እኮ ሁሉን ማድረግ እየቻለ ኹሉን ነገር ሲያደርጉበት በመታገሱ ራሱን ዝቅ በማድረጉ ነው፡፡ እኛ እኮ ኹሉን ማድረግ ስለማንችል ማድረግ የምንችላትን ብቻ ማድረግ ስላለብን የተመላለስን ደካሞች ነን፡፡
ያም ኾነ ይህ ቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባውን በጸሎት ሲከፍት የምሥራቅ ጎጃም ምእመናን በጸሎት መርኃ ግብሩ መገኘት ልማድ ነው፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ ዝምታ የአቡነ ማርቆስ ወደ ልባቸው አለመመለስ የምእመናን አቤቱታ መብዛት ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አልሄደም፡፡ ብዙዎች ያላወቁት ነገር ያለ ይመስለኛል ይህንን ግልጽ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ‹‹ለአንድ መነኩሴ ዐሥራ ኹለት ጊዜ ለምን ትደክማላችሁ? ቅዱስ ሲኖዶስ መልስ ይሰጠናል ብላችሁ መጠበቃችሁ በራሱ ሞኝነት ነው›› የሚሉን አሉ፡፡ ታዲያ ምን ማድረግ ነበረብን? ብለን ስንጠይቃቸው የጎጃም ጀግንነት የት ገባ? ብለው መልሰው ይጠይቁናል፡፡ ለእኛ ጀግንነት ትእግስት ነው፤ ጀግንነት ትሕትና ነው፤ ጀግንነት ሥርዓትን ማክበር ሕግን መጠበቅ ነው፤ ጀግንነት የአባቶቻችንን ድምጽ መስማት ነው፡፡ ለዚህም ነው የቅዱስ ሲኖዶሱን ልእልና የአባ ማርቆስን ክብር ጠብቀን በ7 ዓመት ውስጥ 12 ጊዜ የተመላለስን የደከምን የወጣን የወረድን፡፡ አባ ማርቆስን ከመድረክ ጎትቶ ማውረድ ቀላል ነው፡፡ አባ ማርቆስን ጎጃምን እንዳይረግጧት ማድረግ ቀላል ነው፡፡ በእርሳቸው ላይ ጥቃት ማድረስም ቀላል ነው፡፡ ይህ ኹሉ ግን እምነታችን የሚፈቅደው አይደለምና ትዕግስትን እና ቻይነትን ተመልተን ይኸው ዛሬም የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔ በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን፡፡ በአንድ አቅጣጫ ማሰብ ጥሩ አይደለም፡፡ ዛሬ የምንሠራው ጥፋትም ልማትም የነገ ታሪክ ነው፡፡ ዛሬ ጎትተን ብናወርዳቸው ነገ ጥሩ አባት ቢመጡም በተቃራኒው ጎራ ያሉ ሰዎች ጎትተን እናውርድ ማለታቸው አይቀርም ምክንያቱም ታሪክ ኾኖ ይቀመጣልና፡፡ መንፈስ ቅዱስ ይመራዋል የምንለውን ሲኖዶስም ማሳዘን ማስቀየም አንፈልግም፡፡ ለበረከት ብለን መቅሰፍትንም አንሻም፡፡ አቡነ ማርቆስን ከመድረክ ጎትቶ ለማውረድ ብዙ ምቹ ጊዜ ነበረን ግን አላደረግነውም አናደርገውምም፡፡ ምንም ይኹኑ ምን የያዙት ስም የጨበጡት በትረ ሙሴ የደፉት ቆብ የተቀመጡበት መንበር ክብር አለው፡፡ እርሳቸው ግን ያንን ክብራቸውን አዋርደዋል፡፡ ያዋረዱት ሰው በመኾናቸው ነውና እርሳቸውን እንደሰውነታቸው ወድደን አፍቅረን እንደማዕርጋቸውም አባ አቡነ ብፁዕ ብለን ሥራቸውንና ተግባራቸውን የያዙትን የጥፋት መንገድ ግን እጅጉን እንቃወማቸዋለን፡፡ ደጋፊዎቻቸውም ያልገባቸው ይኸው ነው፡፡ እነርሱ ደጀን ላይ ግፍ ፈጽመዋል፡፡ ጌታቸው ተፈሪ የተባለውን ወንድማችንን መምህራችንን አፍነው ወስደው በፈላ ውኃ ሲገሽሩት በብርጭቆ ሲላጨጩት ውለዋል፡፡ ድግምት መተታቸውን መትተውበታል፡፡ በፀበል ቢድንም፡፡ ይህ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አይደለም፡፡ ንግባዕኬ ኀበ ጥንተ ነገር እንዳለ ወደ ጥንተ ነገራችን ተመልሰን የ12ኛውን ጉዟችንን እንናገር፡፡
ቀኑ 11 ዕለቱ እሁድ ሰዓቱ 9 ሰዓት ነበር ኩንትራት ወደ ተያዙት መኪኖች መግባት የጀመርነው፡፡ ኾኖም ግን ማኅሌት ያደሩ አባቶች ወንድሞች እህቶች ስለነበሩና ከሩቅም የሚመጡ ብዙዎች ስለኾኑ እነርሱን በመጠበቅ ሰዓታት አልፈዋል፡፡ ኹሉም አውቶቡሶች በተመሳሳይ ሰዓት እንዲነሡ ለማድረግ ሲባል መጠባበቅ ስለነበረብን ከደብረ ማርቆስ የተነሣነው ከ10 በኋላ ነበር፡፡ ከደጀን እና ከብቸናም እንደዚሁ ከዚህ ሰዓት በኋላ ተነሥተዋል፡፡ ከደብረ ማርቆስ 5 አገር አቋራጭ አውቶቡሶች እያንዳንዳቸው ከ60 ሰዎች በላይ ጭነው፣ ከደጀን አንድ ከብቸና ኹለት አይሱዙ ቅጥቅጦች በተጨማሪነት አብረው ተጉዘዋል፡፡ ጉዟችን የቤተክርስቲያንን ችግሮች እንዲፈቱልን ለመጠየቅ የተደረገ እንደመኾኑ መጠን የጉዟችን መጀመሪያ የነበረው ጸሎት ነበር፡፡ ጸሎት አድርገን ጉዟችንን ጀመርነው፡፡
የአቡኑ ደጋፊዎች ደግሞ በሚኒ ባስ ተጭነው በረዋል፡፡ የደብረ ማርቆስ አካባቢ ደጋፊዎች ደግሞ በአንድ አይሱዙ ቅጥቅጥ ተጭነዋል፡፡ የጎንቻዎቹ በሚኒባስ ናቸው፡፡ ደጀን ላይ ኹላችንም ከትመናል፡፡ ኹሉም መኪኖቻችን ቆመዋል፡፡ ምክንያቱ ምንድን ነው? ለምን አንሄድም? ረፈደብን እኮ የሚሉ ድምጾች ተስተጋቡ፡፡ የቆምንበትን ምክንያት ግን የተረዳ አልነበረም፡፡ አንዳንዶች ከዐሥራ ኹለት ሰዓት በፊት መሄድ ስለማይቻል ነው የቀረን አምስት ደቂቃ ነው እንንቀሳቀሳለን ይላሉ፡፡ አንዳንዶች ኬላ ላይ ፍተሻ ስላለ ነው ፍተሻው ሲያልቅ እንሄዳለን ይላሉ፡፡ እኛም ጠበቅን ወዲያውኑ የአባ ማርቆስ ደጋፊዎች ሚኒባሳቸውን ወደ ከተማ አዙረው መብረር ጀመሩ፡፡ ምንድን ናቸው? ምንድን ናቸው? ያዛቸው ያዛቸው የሚል ድምጽ ከየአቅጣጫው ተሰማ፡፡ ያኔ ነበር የአባ ማርቆስ ደጋፊዎች መኾናቸውን የተረዳነው፡፡ 6ቱም ሚኒባሶች ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንዲገቡ ተደረጉ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሕገ ወጥ ናችሁ በሚል ነው፡፡ ሚኒባሶች ከጎንቻ ሲነሡ መውጫ አልቆረጡም ነበር፡፡ ደጀን ላይ ተይዘው መውጫ አምጡ ሲባሉ የላቸውም፡፡ ከሌላችሁ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ዙሩ ተብለው እያንዳንዳቸው 5ሽህ 5ሽህ ብር ተቀጥተው ተለቀቁ፡፡ በጠቅላላው 30ሺህ ብር መኾኑ ነው ቅጣታቸው ብቻ፡፡ ከደብረ ማርቆስ የተነሣው የአይሱዙ ቅጥቅጥ ግን አልተቀጣባቸውም፡፡ ኹላችንም ደጀን ኬላ ላይ ያለውን ማንኛውንም ምርመራ አልፈን የዓባይን በረኃ አሐዱ ብለን ተያያዝነው፡፡
ስንቀድም ስንቀደም ስንከተል ስናስከትል ቆይተን ቁርስ ለመብላት እንጦጦ ጫካ ላይ ሰፈርን፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በ5 እንጀራ እና በ2 ዓሣ 5ሺህ ሕዝብ ሲመግብ ያስቀመጣቸው ለምለም ሣር ካለበት ቦታ ነበር፡፡ እኛም ልክ ያንን መስሎ እስኪታየን ድረስ ኹሉም ተጓዦች ቁርሳቸውን ቀመሱ፡፡ ውኃ ታደሉ፡፡ ከምሳ በኋላ አሁንም ጉዟችንን ቀጠልን፡፡ በዚህ ምክንያት የደጋፊዎች መኪና ደጀን ላይ ከተያዙት ሕገወጥ ሚኒባሶች በስተቀር ሌሎች ቀድመውናል፡፡
እንጦጦ ኬላ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረግ ስለነበር በመኪና ከመሄድ ይልቅ በእግር መጓዝ የተሻለ ፍጥነት ነበረው፡፡ አንድ ነገር ትዝ ብሎኛል ምን መሰላችሁ አንድ ሰው ዓባይ በረሃ ላይ ኮንቴነር የጫነ መኪናን ወደ ደጀን ውሰደኝ ብሎ ይለምነዋል፡፡ ከዚያ ሹፌሩም ሰውየው ስላሳዘነው ይጭነዋል፡፡ ከዚያ መጓዝ ይጀምራል፡፡ ደጀን እገባበታለሁ ብሎ ያሰበው ሰዓት እና የመኪናው ፍጥነት አልመጣጠንለት ይላል፡፡ ከዚያ ሰውየው ሹፌሩን ጋሸ አመሰግናለሁ በጣም ስለምቸኩል አውርደኝና በእግሬ ልሂድ አለው ይባላል፡፡ እንጦጦ ላይ የገጠመን ነገር ልክ እንደዚያ ነው የኾነብን፡፡
የደጋፊዎች አንድ ሚኒባስና አይሱዙ ቅጥቅጥ ቦታ ይዘው ቆመዋል፡፡ የእኛ አውቶቡሶችም እንዲሁ ማለፍ አትችሉም ተብለው ተሰልፈዋል፡፡ አዊዎችም በአንድ አገር አቋራጭ አውቶቡስ አለፍ ብለው ቆመዋል፡፡ ፖሊሶች በመገናኛቸው በፍጥነት በፍጥነት ይነጋገራሉ፡፡ ከዚያ ተወካዮች ከየመኪኖች ውረዱ እንነጋገር ተባለ፡፡ እኛ እስከዛሬ ድረስ ተመላልሰናል ደብዳቤ ካላጻፋችሁ አትገቡም ተብለን አናውቅም አሉ ተወካዮቻችን፡፡ ፖሊስም አሁን ያለው የአዲስ አበባ የጸጥታ ጉዳይ ከባድ ስለኾነ ችግር ልትፈጥሩ ትችላላችሁና የመጣችሁበት ቦታ ደብዳቤ መጻፍ ነበረበት አለ፡፡ መፍትሔው ምንድን ነው ሲባል መኪናችሁን አዙራችሁ ወደ መጣችሁበት ተመለሱ የሚል ኾነ፡፡ በዚህ ውሳኔ አባ ማርቆስ ደጋፊዎች የተሰማቸው ከልክ ያለፈ ደስታ የሳቅ ሲቃ ኾናቸው፡፡ ልባቸው ሐሴትን ተመላች፡፡ ምክንያቱም በዚያ ሰዓት ከደጋፊዎቻቸው መካከል አንድ ሚኒባስና አንድ አይሱዙ ቅጥቅጥ ብቻ ነበሩና፡፡ ሌሎች ደጀን ላይ በነበረው ኹኔታ ገና ዓባይ በረሃ ውስጥ ነበሩ፡፡ የእነርሱ መመለስ ሳይኾን የእኛ አውቶቡሶች መመለሳቸውና ገንዘባችን በከንቱ መባከኑ ነበር ያስደሰታቸው፡፡ እነርሱ በአንድ ብጣሽ ወረቀት 50 ሺህ ብር አውጥተው ነውና የሚጓዙት ቢመለሱም የሚከስረው የወረዳ ቤተክህነቱ ገንዘብ እንጅ የእነርሱ ስላልነበር ደስታቸው እጅግ ትልቅ ነበር፡፡
አንድ ከእኛ ጋር የነበረች እና ወርዳ ከፖሊሱ ላይ ጮኸችበት፡፡ ይች እናት በአባ ማርቆስ ዘንድ እብድ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ውድ ናት፡፡ ለሃይማኖቷ አእምሮዋን ትስታለች፡፡ ጣቷን ወደ ላይ አቅንታ እግዚአብሔር ኾይ ፍረድ ብላ አለቀሰች፡፡ ፖሊሱ ልቡ ራራ በጣም በርኅራኄ ዓይን ተመለከታት፡፡ እኛ እኮ ስለሃይማኖታችን ነው እንዲህ የምንኾነው ለኦርቶዶክስ ተዋህዶ ግን መቼ ነው ነጻነት የሚሰጣት ብላ ማተቧን አሳየችው፡፡ እንባዋን ስታፈስ ፖሊሱ ትኩረቱ እርሷ ላይ ኾነ፡፡ ከዚያም አማራጭ ተፈለገ፡፡ ክልሉንም ዞኑንም ቢጠይቁ እነርሱ ሰላምን ለማውረድ የመጡ ናቸው፡፡ ይለፉ ተባለ በዚህ ተፈቀደልን፡፡ ከዚያም ጉዟችንን ከሰዓታት መንገላታት በኋላ ጀመርነው፡፡
ፖሊሶቹ ያሰቡት ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች አንድ መድረክ ላይ ሲገናኙ ጠብ ይፈጥራሉ የሚል ነው፡፡ እኛ ደግሞ ለሰላም ነው እንጅ ለጠብ ከጎጃም ድረስ መጥተን አዲስ አበባ እንዴት እንጣላለን የሚል ነው፡፡ ሰው ለመጣላት አዲስ አበባን አይመርጥም፡፡ ጎረቤታሞች ኾነን በሰላም እየኖርን ያለን ሰዎች ዕለት ዕለት የምንገናኝ ሰዎች እንዴት አዲስ አበባን ለጥል እንመርጣታለን፡፡ ለመጣላት ለመጣላትማ ማርቆስ ምን አለን፡፡ ለጥል ለጥላቻማ ከኾነ ይህን ያህል ብር ከምናወጣ ለአንድ ወንበዴ ሽፍታ መወዳጀት ይበቃ አልነበረምን?
አሁንም ሄድን ተጓዝን ከተማ ውስጥ ገባን፡፡ ኬላ ላይ አስቁመውን የነበሩ ፖሊሶች አራዳ ክፍለ ከተማ ስንደርስ ደግሞ አስቆሙን፡፡ ፍተሻ ሳናደርግ ስላሳለፍናችሁ ልንፈትሻችሁ ነው አሉ ፈትሹን አልን፡፡ እነርሱም እርስ በርሳችሁ ተፈታተሹ አሉ፡፡ እርስ በእርሳችን ተፈታተሽን፡፡ ጨረሳችሁ? አለን፡፡ አዎ ጨረስን አልነው፡፡ ምን አገኛችሁ? አለን፡፡ ምንም አላገኘንም አልነው፡፡ መስቀልም አላገኛችሁም? መስቀል ኃይላችን ነው አለና በሰላም ግቡ ብሎ ወጣ፡፡ እኛም ወደ መንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም አመራን፡፡ ከመኪናችን ወርደን ወደ ቤተክርስቲያን ስንገባ የአርሲ ሀገረ ስብከት፣ የአዊ ሀገረ ስብከት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በተለይ የሰአሊተ ምሕረት የተዋሕዶ ልጆች ባነራቸውን ይዘው አገኘናቸው፡፡ እኛ በተለያዩ ቦታዎች ላይ በነበረው ፈተና ተቀድመናል፡፡ የአባ ማርቆስ ደጋፊዎችም ቦታቸውን ይዘው ቆመዋል፡፡ እኛም ገባንና ቦታችንን ይዘን ቆምን፡፡ እነርሱ ለጥፋት እኛ ለቤተክርስቲያን ሰላም ስንል በአንድ ቦታ ከተምን፡፡ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ከምሥራቅ ጎጃም ይነሡልን የምትለዋ ወረቀት ከአባ ማርቆስ ደጋፊዎች በስተቀር ኹሉም ከፍ አድርጎ አነሣት፡፡ አዊዎችም፣ አርሲዎችም፣ ሰአሊተ ምሕረቶችም እኛም ከፍ አድርገን አነሣናት፡፡ ሞንታርቮ ይዘን ስለነበር፡፡ በሞንታርቮ አባ ማርቆስ ይነሡልን፣ ቅዱስ ሲኖዶስ የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከትን ችግር ይፍታልን፤ ቅብዓት ይወገድልን ወዘተ የሚል ድምጽ በቅብብል ተዜመ፡፡ ቅብዓቶች ደግሞ በተራቸው ማኅበረ ቅዱሳን ይወገዝልን፣ በአባ ማርቆስ ስብከት የሚደነግጠው ሰይጣን ብቻ ነው ወዘተ እያሉ መጮኽ ጀመሩ፡፡ ቅባቶች በብዛት ከአዲስ አበባ የመጡ እግር መንገደኞች ናቸው፡፡ ከዚህ ከጎንቻና ከደብረ ማርቆስ አካባቢ የመጡት ደግሞ አበል ስላላቸው አበሉን ፈልገው የሄዱ ናቸው፡፡ ሻሽ አስጠምጥመው ካህን አስመስለው ከኋላቸው አስቁመዋል፡፡ ካህን ያልኾኑ ካህናትን ሰብስበዋል፡፡ እንዲያውም ትምህርታቸውን እውቀታቸውን ማንነታቸውን የሚያውቁ መጋቤ አእላፍ ጥበቡ የእኛ ስህተት አንድ ጣቃ ሻሽ ገዝተን ይህን ኹሉ ሕዝብ ሻሽ አለማስጠምጠማችን ነው፡፡ እነርሱ ላይ እኮ ሻሽ የጠመጠሙት ሰዎች ምንም ያልተማሩ ናቸው ብለዋል፡፡ በጥቅም ተሳስረው በዓላማ እና በሃይማኖት አንድ ኾነው ቅብዓትን ለማስፋፋት የሚታትሩ የአበል ተጓዦች በዋናነት ከጎንቻ 6 ሚኒባሶች እና ከደብረ ማርቆስ 1 አይሱዙ ቅጥቅጥ ነው፡፡ ከዚያ ውጭ ያለው ኹሉ ከመንገድ ተለቅሞ የገባ ነው፡፡
በዚህም መሠረት፡-
ከደብረ ማርቆስ አካባቢ
1ኛ. ለዓለም… የደ/ማ ወ/ቤ/ክ ሥራ አስኪጅ፡፡ ይህ ሰው በአይሱዙ ቅጥቅጥ ከየመንገዱ ለቅሞ ያስገባቸውን ሰዎች ሙሉ ወጭ ከወረዳ ቤተክህነቱ ወጭ አድርጎ የከፈለ ነው፡፡ የተከፈለው ገንዘብ መጠን በትክክል ባይታወቅም ከ20 እስከ 50 ሽህ ብር ባለው መካከል ሊኾን እንደሚችል ጉዳዩን የያዙት የሀገረ ስብከቱ ኦዲተር አረጋግጠውልናል፡፡
2ኛ. ተስፋ (ንዑስ)… ይህ ሰው ጎንቻ እያለ የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ የነበረ እና ፎቶ በማንሣት ይተዳደር የነበረ ነው፡፡ ቅብዓትን እቃወማለሁ የሚል ነገር ግን ቅብዓትን ደግፎ አዲስ አበባ ድረስ የሄደ ነው፡፡
3ኛ. መምህር ጳውሎስ…ከወደ ረቡዕ ገበያ አምጥተው የሾሙት ነው፡፡ ሰንበት ትምህርት ቤትን ለመበተን በጣም የሚሠራ ነው፡፡
4ኛ. መምህር ዓምደ ወርቅ--- አሁን የሚገኘው ቁይ ሲሆን ትምህርቱን የተማረው ግን ዲማ ነው፡፡ የዲማ አረም ማለት ይኸው ነው፡፡ ከመንገድ ተጠብቆ አብሮ ተጭኖ የሄደ ሰው ነው፡፡
ከብቸና አካባቢ ደግፈው የሄዱ ደግሞ
1ኛ. መልአከ ምህረት ድረስ አሰፋ… የወረዳ ቤተክህነቱ ሥራ አስኪያጅ
2ኛ. ሊቀ ጠበብት አብርሃም ካሰ
3ኛ. ቄስ ደምሴ ይድነቃቸው
4ኛ. ቄስ ውበቴ ወንድሜነህ
6ኛ. መ/ር ናሁ ሠናይ ውበት
7ኛ. ቄስ ይዘንጋው ደጀን
8ኛ. ቄስ ላመስግን ጌቴ
9ኛ. ቄስ ደባስ ተረፈ
10ኛ. መ/ጌታ አመናረ ዋለ
11ኛ. ላእከማርያም መኩሪያው ናቸው፡፡
እነዚህ ሰዎች መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ አለቃ አያሌው ታምሩ መምህር ዘሚካኤል ይኹኔ በኖሩበት ቦታ የሚኖሩ ዲማን መጫወቻቸው ያደረጉ ሰዎች ናቸው፡፡ በተለይ ላእከ ማርያም በሕይወቴ የማፍርበት ሰው እርሱ ነው፡፡ መምህር ዘሚካኤል ይኹኔ ያስተማሩት በእርሳቸው ወንበር ላይም እንዲቀመጥ ተመድቦ የነበረ እርሱ ግን የመምህሩን ሚስት የደፈረ ነውረኛ ነው፡፡ ዲማ ላይ ተመድቦ ዲማን እንደ ዓሣ መቁሎ ማመስ የሚፈልግ ነው፡፡ አባ ማርቆስ ደብዳቤ ጽፈው የመደቡት ቢኾንም ከፍተኛ ችግር በመፈጠሩ እንዲነሣ የተደረገ ነው፡፡ ከእርሱ ጋር የተማሩት እን መጋቤ ብሉይ አእምሮ ዘውዴ፣ እነ ሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክ የት እንዳሉ ቢረዳ በተሻለው ነበር፡፡
እነዚህ ሰዎች ናቸው በአይሱዙ ቅጥቅጥ ተጭነው ወልደ አብ ለምን ተወገዘ? ማኅበረ ቅዱሳን ይወገዝልን እያሉ ሲጮኹ የነበረው፡፡
ጎንቻዎች ከየአጥቢያው ጥቅመኞች እና ሃይማኖታቸው ቅብዓት እንደኾነ የተረጋገጠላቸው ሰዎች ናቸው ሌሎች ደጋፊዎች፡፡ ዲማ የተማሩ ሰዎች ወልድ ፍጡር ከሚሉ ሰዎች ጋር ኅብረት መፍጠራቸው በእውነቱ አርዮሳዊነታቸውን አጉልቶ ከሚያሳይባቸው በቀር ሌላ ምን ሊኾን ይችላል?
የኾነው ኾኖ እነርሱም እኛም ተሰልፈናል፡፡ እኛ ይነሡልን እነርሱ አይነሡብን፣ እኛ ተዋሕዶ ሃይማኖታችን ትጽናለን እነርሱ ቅብዓት ይጽናልን፤ እኛ እውነትን እነርሱ ሐሰትን ይዘን በየምቅዋማችን ቆመናል፡፡ አጠገባቸው ሆነን አባ ማርቆስ ይነሡልን የምትለዋን ወረቀት እያሳየን ስናቃጥላቸው እንደነበር ፊታቸው ላይ የሚነበበው ነገር ያረጋግጥልናል፡፡ አጠገባቸው ቆሜ ሳለሁ በአባ ማርቆስ ስብከት የሚደነግጠው ሰይጣን ብቻ ነው የሚለውን ባነር አነበብኩና ሰኔ ጎልጎታን ልብ ወለድ ነው የሚሉ ሰው በእውነት የሚያስደነግጡት በየትኛው ወንጌላቸው ነው? አልኩ፡፡ አንዱ ያልሰማ በእውነት እንደዚህ ብለዋል አለ፡፡ አዎ አልኩት፡፡ የተቀረጸ አለ? አለኝ አዎ ራሳችን የቀረጽነው ቪዲዮ አለ አልኩት፡፡ በጣም ያሳዝናል ብሎ የሀዘን ፊት አሳየኝ፡፡ አንዱ ደጋፊያቸው ጠጋ ብሎ ዝም ብሎ ነው ፌስቡክ ላይ ያለውን አይቶ ነው እንጅ አለ፡፡ እርሱን ተወው አልኩት፡፡
አንዱ ከሉማሜ አካባቢ የሄደ ጥቁር ልጅ ሱፍ የለበሰ ነው፡፡  ማኅበረ ቅዱሳንማ ወወገዝ አለበት አለ፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ወልደ አብ መሰለህ እንዴ የሚወገዘው አልኩት፡፡ ጎጃምን ዳግም እያጠመቀ መወገዝ አለበት አለኝ፡፡ ጎጃምን ማን ዳግም ተጠመቅ አለ ቅብዓትን እንጂ አልኩት፡፡ እርሱን ተወው ቅብዓት ተዋሕዶ ብሎ ማንሣት አይገባም ቅብዓት የሚባል ነገር አናውቅም አለ፡፡ አንተ ራስህ ቅብዓት ኾነህ እኮ ነው ደግፈህ የመጣህ አልኩት፡፡ ቅብዓት የሚባል ነገር የለም አለ፡፡ ታዲያ ወልደ አብ የተባለውን መጽሐፍ ማን ጻፈው እኛ የጻፍነው ይመስልሃልን? አልኩት፡፡ እንግዲያውስ ግባና ቀድስ አለኝ፡፡ ታዲያ እንዴት የማልቀድስ እኔም እኮ ዲያቆን ነኝ መቀደስን ማን ይከለክለኛል አልኩት፡፡ ኤዲያ ዝም ብላችሁ ነው አለኝ፡፡ እንፈተን እና ቢያንስ እንዳንተ ካልመለስኩ ልወቀስ አልኩት፡፡ ዝም አለ፡፡ እኔም ትቼው አባ ማርቆስ ይነሡልን የምትለዋን ወረቀቴን ከፍ አደረግኋት፡፡
ከ50 የማይበልጡ ደጋፊዎች ቢጮኹ ቢጮኹ አልሰማ ስላሉ ባነራቸውን ከፍ አድርገው ለዝናብ መከላከያ ብለው በያዙት ጥላ አንጠለጠሉት፡፡ ነፋስ አላዘረጋ አላሲዝ አላቸው፡፡ ከዚያ ከዛፍ ላይ አሰሩት፡፡
ሊቃነ ጳጳሳት ወደ ቤተክርቲያን እየገቡ ነው፡፡ የምሥራቅ ጎጃም ካህናትና ምእመናን በመዝሙር ወረቀታቸውን ከፍ እያደረጉ ፈጣሪን መለመን ጀመሩ፡፡ አባቶች ገብተው ሲጨርሱ ጸሎቱ ተጀመረ፡፡ ቅዱስ ፓትርያርኩ በሚመሩት በዚህ ጸሎት ላይ የምሥራቅ ጎጃም ካህናት ተሰጥዎውን በመቀበል ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ፈጣሪን ተማጸኑ፡፡ ከአባ ማርቆስ ደጋፊዎች በኩል አንድም ተሰጥዎ የሚቀበል ሰው አልሰማሁም፡፡ ምናልባት ምን ይባል እንደነበር ስላልሰሙት ካልኾነ በቀር ሻሽ የጠመጠሙ ብዙ ሰዎችን ይዘው ነበር፡፡
ጸሎቱ አለቀ፡፡ በእንባቸው የሚታወቁት አቡነ ቀውስጦስ ትምህርት እንዲሰጡ ተጋበዙ፡፡ አቡነ ቅስጦስ በእንባ የኹለቱን ቅዱስ ሲኖዶስ አንድ መኾን ተናገሩ፡፡ ድንቅ ታሪክ በመሠራቱም ፈጣሪን አመሰገኑ፡፡ ጊዜው አልኾን ብሎ ስለነበር ነው እንጅ ጥጃ ከእናቱ ሰይፍ ከፎቱ መገናኘቱ አይቀርም፡፡ ለዚህ ነው ከ27 ዓመታት በኋላ በአንድነት በእናታችን ቤት የተገናኘን አሉ፡፡ የማኅበረ ቅዱሳን ልጆቻችን ሲያለቅሱ ሲያዝኑ እንባቸውን ሲያፈሱ ኖረዋል፡፡ አሁን ግን ከቅዱስ ፓትርያኩ ጋር ተስማምተው ስለአንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን ሊሠሩ አንድ ኾነዋል አሉ፡፡ በዚህ ጊዜ በሙሉ አጨበጨበ፡፡ ለማጨብጨብ እጃቸው የታሠረው ግን የአባ ማርቆስ ደጋፊዎች ብቻ ነበሩ፡፡ በደጋፊዎች በኩል ከነበሩት ጥቂት ወንድሞችና አባቶች በቀር ያጨበጨበ አልነበረም፡፡ እነዚህም ያጨበጨቡ ምናልባትም ሌላው ሲያጨበጭብ ስለሰሙ ሊኾን ይችላል፡፡
አቡነ ቀውስጦስ እንባቸውን እያፈሰሱ ያስተማሩትን ትምህርት ጨረሱ፡፡ አቡነ ማትያስም ቃለ ምእዳን ሰጥተው ከቤተክርቲያኑ ወደ መድረክ መጡ፡፡ አቡነ ዲዎስቆሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ሥራ አስኪያጅ፣ አቡነ ሳዊሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ፀሐፊ እና ሌሎች ሊቃነ ጳጰሳት አሉ፡፡ የአዊ ሀገረ ስብከት ተወካዮች ጥያቄያቸውን በንባብ አሰሙ፡፡ አቡነ ዲዎስቆሮስ ይበቃናል፡፡ የጻፋችሁትን ለቅዱስ ሲኖዶስ ፀሐፊ ስጡ እኛ እንወያይበታለን አሉ፡፡ አቤቱታ አቅራቢዎች ግን ኹሉም ይነበብ አለ፡፡ ኾኖም ግን አቡነ ዲዎስቆሮስ ከፈለጋችሁ የተወሰኑ ተወካዮችን ስብሰባ ስንጀምር እንዲያስረዱ መወከል ትችላላችሁ፡፡ ጥያቄያችሁን እንመለከተዋለን አሉ፡፡ በዚህ ተስማምተን እሺ ብለን የተጻፈውን ወረቀት አስገባን፡፡ ይህ ኹሉ ሲኾን አቡነ ማርቆስን ማዬት አልቻልኩም ነበር፡፡ ብዙ ፈልጌ አገኘኋቸው፡፡ ከመድረኩ ወርደው ከሊቃነ ጳጳሳት ተለይተው ለብቻቸው ከታች ቆመዋል፡፡ በቆባቸው ላይ ጥቁሩን ፎጣቸውን ከላይ ደርበው ተሸፋፍነዋል፡፡ ይህ አብውነቱ መሸማቀቅ ካልኾነ በቀር ምን ሊባል ይችላል? ዐሥራ ኹለት ጊዜ ሙሉ ተሸማቀው ለእርሳቸውስ ጥሩ ይኾናል ወይ?
የዘንድሮው ጉዟችን ልዩ የሚያደርገው የመጀመሪያው ደጋፊዎችም አብረውን የሄዱ መኾኑ ነው፡፡ ኹለተኛው ደግሞ የመጨረሻችን ይኾናል ብለን ተስፋ የምናደርገው መኾኑ ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ አቡነ ማትያስም ከፖለቲካው እሥራት የተፈቱ መኾናቸው ነው፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች ልዩ ያደርገዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ሊቃነ ጳጳሳት ወደመኖሪያ ቤታቸው አቀኑ፡፡ እኛም በጭብጨባና በእልልታ ሸነናቸው፡፡
የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች በመዝሙር እግዚአብሔርን ማመስገን ጀመሩ፡፡ በዚህ ሰዓት ቅብዓቶች ደግሞ ለብቻቸው ቆመው ማኅበረ ቅዱሳን ይወገዝልን በማለት መጮኽ ጀመሩ፡፡ አንድ ሽማግሌ አባት ሰሟቸውና በጣም ተናደዱ፡፡ ደንቆሮዎች አቡነ ቀውስጦስ ቅድም ሲያስተምሩ አልሰማችሁም እንዴ? ማኅበረ ቅዱሳን እኮ ከፓትርያርኩ ጋር ተስማምተዋል፡፡ አትጩኹ አሏቸው፡፡
ከዚህ በኋላ ወደ ውጭ በሰላም መውጣት ዓላማችን ስለነበር መውጣት ጀመርን፡፡ ደጋፊዎች ግን ከሊቃነ ጳጳሳት መኖሪያ ቤት መግቢያ ላይ ቆመው መጮኽ ጀመሩ፡፡ በዚያ ሄደው መጮኽ ያስፈለጋቸው በፊት ድምጻቸው ተውጦ የቆየ ስለነበር ነው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ይወገዝልን ይላሉ አሁንም፡፡ አቡነ ማርቆስ አይነሡብን ይላሉ አሁንም፡፡ ግን ማንም አይሰማቸውም ነበር፡፡ ጠብ ለመፍጠርም የሞከሩ ነበሩ ኾኖም ግን በትእግስት አልፈነዋል፡፡
እኛም ወጥተን ወደ መኪኖቻችን አቀናን፡፡ ቀኑን ሙሉ አቤቱታ ለማሰማት ቆመው የዋሉት ሰአሊተ ምሕረቶች ማረፊያ ቦታ አዘጋጅተንላችኋልና ወደዚያ እንሂድ አሉን፡፡ የቤተክርቲያን አንድነት ማለት ይኸው ነው፡፡ ከማርቆስ የመጡ አውቶቡሶች በሙሉ ጉዟቸውን ወደ ሰአሊተ ምሕረት አደረጉ፡፡ ከብቸና እና ከደጀን የመጡት አውቶቡሶች ደግሞ ጉዟቸውን ወደ ጎጃም አድርገዋል፡፡ የአዊዎች ጉዳይ ግን እንዴት እንደነበር ሳላረጋግጥ መቅረቴ ያሳዝነኛል፡፡ ደጀኖች ሌሊት 7 ሰዓት ብቸናዎች ደግሞ ሌሊት 9 ሰዓት ወደ ቤታቸው በሰላም ገቡ፡፡ እኛ ደግሞ በተጨናነቀው የትራፊክ እንቅስቃሴ ታጅበን ወደ ሰአሊተ ምሕረት ገባን፡፡
ሰአሊተ ምሕረት በምእመናን የምትጠበቅ አስተዳዳሪ የሌላት ቤተክርቲያን ናት፡፡ የሙስና ሰዎች ሲመሯት ስለነበር እስከ ሞት ድረስ ጸንተው ቤተክርስቲያናቸውን ነጻ ያደረጉ የተዋሕዶ አናብስት ያሉባት ቦታ ናት፡፡ አቡነ ማትያስ ፈቅደው በአባ ኃይለማርም በአሁኑ አቡነ አረጋዊ ቀቢነትና ተቀቢነት ከፕሮቴስታንቶች ጋር የተቀባቡባትም ቦታ ናት፡፡ በዚህም የተነሣ ምእመናን እጅጉን ተቆጥተው ቤተክርስቲያናቸውን ከሌቦች እና ከወንበዴዎች መንጋጋ የታደጉ ናቸው፡፡ ዛሬም አብረውን አቤቱታቸውን ሲያሰሙ የዋሉ ናቸው፡፡
ሰአሊተ ምሕረት ደረስን፡፡ ድንኳን ተጥሏል፡፡ የእግር መታጠቢያ ውኃ እና ሳፋ ተዘጋጅቷል፡፡ ከጎጃም ሄደን እንግዳ መቀበልን ከአዲስ አበባ የተማርንበት ነው፡፡ እንግዳ ተቀብለን እናውቅ ይኾናል፤ የተራበን አብልተን የተጠማንም አጠጥተን እናውቅ ይኾናል እንደ ሰአሊተ ምሕረቶች ያለ እንግዳ አቀባበል ግን አላየሁም፡፡ ቤተክርስቲያን ሄደን አቡነ ብለን ተመለስን፡፡
ወንድሞቼ ኑ እግራችሁን እንጠባችሁ ተባልን፡፡ እንግዳ አይደለን መቼስ እንግዳ ባናጥብም እኛ ግን እንግዶች ነንና እንድንታጠብ ተቀመጥን፡፡ ታጠብን፡፡ አመስግነን ወደ ድንኳናችን ገባን፡፡ በዚያች ድንኳን ውስጥ ኹላችንም ተቀመጥን፡፡ ምግብ መጣ፡፡ የፍስኩም የጾሙም ምግብ በየዓይነቱ ቀረበልን፡፡ ለሚጾመው ምስር ወጥ ለማይጾመው ደግሞ ቀይ ወጥ ሥጋ ፍርፍር ወዘተ ቀረበ፡፡ ዳቦ ተጨመረ፡፡ በላን፤ ውኃ ቀረበልን ጠጣን፡፡ ከሚገባው በላይ ተስተናገድን፡፡ ስንጨርስም ስብሐት ተባለ አባቶችም መረቁ፡፡ አስተናጋጆቻችንም ቆመው ምረቃውን ተቀበሉ፡፡ ከዚያ ስለማደሪያችን ገለጻ አደረጉልንና ወደ አዳራሹ አቀናን፡፡ ለአባቶች ለእህቶች ለምእመናን ቦታዎች ተለይተው ተዘጋጅተዋል፡፡ በዚያ ከተንጣለለው አዳራሽ ላይ በቀይ ምንጣፍ ላይ በሰላም አሳድረን ብለን ጎናችንን አሳረፍን፡፡ ስለአጠቃላይ ውሏችን አጭር ውይይት አድርገን ሌሊት 9 ሰዓት እንደምንነሣ ማሳሰቢያ ተሰጥቶ ተኛን፡፡ ሽንት ቤት አጠቃቀማችን፣ ድንኳን ውስጥ በነበረው መስተንግዶ ጮኸንባችሁ አስቀይመናችሁ፤ እግር ስታጥቡን ትሕትናን አላሳያችሁ ብለን ከኾነ፣ ማደሪያችን ላይ ጥፋት ሠርተን ከኾነ ይቅርታ እንጠይቃችኋለን፡፡ ኹላችንም ጥሩ ልንኾን አንችልምና ጥፋት ፈጽመን ሊኾን ስለሚችል፡፡
ሌሊት 8፡30 አካባቢ ተነሣን፡፡ ጸሎት የሚያደርሰው ጸሎቱን አደረሰ፡፡ ወደ ቤተክርስቲያን አምርተን አቡነ አልንና ወደ መኪናችን አቀናን፡፡ ሌሊት 9 ሰዓት ኾኗል፡፡ መኪናችን መንቀሳቀስ ጀመረ:: የማይቀረውን ጉዟችንን ተያያዝነው፡፡ ደጀን ስንደርስ እረፍት አደረግን፡፡ ከዚያም አምበርን ለውይይት መርጠን እዚያ እንድንቆም ተነጋግረን ሄድን፡፡ ነገር ግን ቦታውን አልፎ የቆመ መኪና ስለነበር ደብረ ማርቆስ ልንገባ ስንል እንነጋገራለን ብለን ወደዚያው አመራን፡፡
ከዚያም ስለነበረን አጠቃላይ ኹኔታ ተነጋገርን፡፡ ወደፊት ምን ማድረግ ይገባናል? ስለሚለውም ተነጋገርን፡፡ በዚህም ውይይት ጎልቶ የተሰማው የደብረ ማርቆስ ወረዳ ቤተክህነት ለአንድ አይሱዙ ቅጥቅጥ የኮንትራት ክፍያ ወጭ አድርጎ የከፈለ ስለኾነ ተጣርቶ ክስ እስኪመሠረት ድረስ ጽ/ቤቱ መታሸግ አለበት የሚለው ነበር፡፡ መረጃ እንዳያሸሹ መታሸግ እንዳለበት ተስማማን፡፡ ስናሽግ ግን የመንግሥት አካላትም ማወቅ አለባቸውና እነርሱንም እናሳውቅ በሚለው ስምምነት ላይ ደርሰን፡፡ ቃለ ጉባዔ ይዘን ኹሉንም ፊርማ እንዲፈርሙ አድርገን ወደ ደብረ ማርቆስ አመራን፡፡ ተክለ ሃይማኖት አደባባ አባ ማርቆስ ይነሡልን የሚል ወረቀት የተለጠፈባቸው አውቶቡሶች ከባጃጆች መካከል ከፍ ብለው ቆሙ፡፡ ሰው ኹሉ ዓይኑን ወደእነዚህ አውቶቡሶች አደረገ፡፡ ተወካዮች የመንግሥት አካላትን ለማሳወቅ ሄዱ፡፡ እኛም ወረዳ ቤተክህነቱ ወደሚገኝበት ወደ ቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስቲያን አቀናን፡፡ ሰዓቱ 8 ሰዓት አካባቢ ኾኖ ነበር፡፡ ተወካዮች ለመንግሥት አካላት አሳውቀው እስኪመጡ ድረስ በትዕግሥት ፀሐይ ላይ ቆመን ጠበቅን፡፡ በመጨረሻም ተወካዮቻችን አሳውቀው መጡ፡፡ ከዚያም ኹሉም ጉዟችንን ወደ ወረዳ ቤተክህነቱ አደረግን፡፡ የደብረ ማርቆስ ወረዳ ቤተክህነት ከምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ግቢ ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡ ወደዚያ ስንገባ ሥራ አስኪጁም ሌሎችም ሠራተኞች የሉም፡፡ ሥራ አስኪያጁ 7፡33 አካባቢ ከቢሮ ወጥተው ሲመለሱ ዓይተናል፡፡ ከቢሮ የወጡት ሊታሸግ እንደኾነ የነገራቸው አብሮን የነበረ ሰው ስላለ ነው፡፡ ወደ ቢሮው ስናቀና በሙሉ ዝግ ነው፡፡ የሀገረ ስብከቱ አስተዳድር ጉባዔ አባላት የተወሰኑት 4 የሚኾኑት ቢሯቸውን ከፍተው በመሥራት ላይ ነበሩ፡፡ አራቱም እንዲወጡና እንዲያናግሩን አደረግን፡፡ እኛ ሥራ አስኪያጁን ነው የምንጠብቅ፡፡ ኦዲተሩም ተናገሩ፡፡ ወረዳ ቤተክህነቱ በትክክል ገንዘብ አውጥቷል፡፡ ከዚህ ወጭ በተደረገ ገንዘብ  ከብቸና ከቁይ ከሉማሜ ከደብረ ማርቆስ አካባቢ ያሉ ሰዎችን ሰብስቦ ሄዷል፡፡ እናንተ ይነሡልን ብላችሁ ሄዳችሁ እርሱ ደግሞ ከእናንተ በተሰበሰበ ገንዘብ ጠላት ኾኖ ሄዷል አሉ፡፡ ስለዚህ ማሸግ ትችላላችሁ፡፡ የገንዘብ እንቅስቃሴም እንዳይደረግ ሥራ አስኪጁ ከመጡልን ደብዳቤ ጽፈን የሂሳብ ደብተሩን እናስቆመዋለን ብለዋል፡፡ የወጣው ገንዘብ መጠን ግን በወሬ ደረጃ 20ም 30ም 50ም ሺህ ነው ይላሉ እኛ እያረጋገጥን ነው ብለውናል፡፡ እኛም ጽ/ቤቱን አሽገን ለሀገረ ስብከቱ ዘበኞች እና ለአስተዳድር ጉባዔ አባላት አስጠብቀን ወጣን፡፡ ችግር የሚፈጥሩ ከኾነ አሳውቁን ብለን ወደየቤታችን አመራን፡፡
አባ ማርቆስ ይነሡልን የምንለው፡-
. ከምሥራቅ ጎጃም ሐገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስነት
. ከስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ መምሪያ ኃላፊነት
. ከቴሌቪዥን የቦርድ ሰብሳቢነት ጭምር ነው፡፡
ይህን የምንለውም እምነታቸው ትምህርታቸው ችግር ስላለበት ነው፡፡ ከእነዚህ የስህተት ትምህርቶቻቸው እና ከሠሩት በደል መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡
. ሰኔ ጎልጎታን ልብ ወለድ ነው ያሉ፡፡
. ተዝካርን ምዋርት ነው ያሉ፡፡
. በዘመነ ዮሐንስ ልደት ታኅሣሥ 28 መከበር የለበትም ያሉ፡፡
. ተዋሕዶ፣ ቅባት፣ ካራ፣ ጸጋ የሚባል ነገር የለም ያሉ፡፡
. ሐገረ ስብከቱን ለቅብዓትና ለተሐድሶ አሳልፈው የሰጡ፡፡
. ደመወዛቸውን ከ10ሺህ ወደ 17 ሺህ በር ያሳደጉ፡፡
. ድጓ፣ ቅኔ ተምረህ ሰው አትኾንም ያሉ፡፡
. የጽጌ ጾምን ያመጣብን ሰንበት ትምህርት ቤት ነው ያሉ፡፡
. የከሳ የሚወፍረው በጽጌ ጾም ነው ሥጋና ቅቤ ስለሚበላ ያሉ፡፡
የአባ ማርቆስ ደጋፊዎች እነዚህን ትምህርቶች የሚቀበሉ ናቸው፡፡ ለዚህም ነው የጥፋት ተባባሪዎች ናችሁና አንፈልጋችሁም ተብለው በመባረር ላይ የሚገኙት፡፡ ከዚህ በኋላ ለዓለም፣ ተስፋ(ንዑስ)፤ ጳውሎስ እና ሌሎችም ተባባሪዎች አባ ማርቆስ በሰጧቸው ሥራ አይቀጥሉም፡፡ የሚከፈላቸው የሕዝብ እንጅ የአባ ማርቆስ ገንዘብ አይደለምና ደመወዝ ለጠላት አንከፍልም ይህ የምእመናን ውሳኔ ነው፡፡
እነዚህ ደጋፊዎች ከማርቆስ የተነሡት ሌሊት ሲጓዙ አድረው ማርቆስ የገቡትም ሌሊት ነው፡፡ የተወሰኑት ከጎንቻ የሄዱት የቅርብ ዘመዶቻቸው ግን ጠቅላይ ቤተክህነት በሰጣቸው ቤታቸው ላይ አሳድረዋቸዋል፡፡ ማታ አካባቢ ያገኟቸው አንድ ካህን አብደዋል እርሳቸው በጣም ተናደዋል አሉኝ፡፡ በተዋሕዶ ሃይማኖት ላይ ጦርን ለመስበቅ ሲመክሩ እንዳደሩ ይታወቃል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ እንዲያውቅልን የምንፈልገው ነገር እነዚህ አባ ማርቆስ ደጋፊዎች በብዛት ቅብዐቶች መኾናቸውን ነው፡፡ ወልደ አብ አይወገዝ ብለው ጮኸዋል ተብሏል፡፡ ይህ እውነት ከኾነ ቅዱስ ሲኖዶስ አይቶ ያወገዘውን መጽሐፍ አይወገዝ ብሎ ቅዱስ ሲኖዶስን የሚሞግት የእርሳቸው ደጋፊ ከኾነ እርሳቸው ማን እንደኾኑ ለመረዳት ቀላል ነው፡፡ ‹‹ማኅበረ መሢሕ›› በሚል የመሠረቱት ማኅበር በጀቱ ማን ነው እርሳቸው አይደሉምን? ምሥራቅ ጎጃም ላይ ያለው ሁኔታ ጥሩ አይደለም፡፡ ምእመናን ደም ከመፋሰሳቸው በፊት ካህናት ከመተራረዳቸው በፊት ቅዱስ ሲኖዶስ መላ ሊያበጅለት ይገባል፡፡ ቅብዓቶች በግልጽ እንለይ እያሉ ያሉበት ጊዜ ነው፡፡ ጉዳዩን ሸፋፍነን ደባብቀን ማለፍ አይገባንም፡፡ ነገ እኮ ይህ የእኔ ነው ይህ የእኔ ነው ብለው ቤተክርስቲያናችንንም ሊከፍሏት ነው፡፡ በወልደ አብ መናፍቅ አፈረ፣ እናምናለን ምስጢረ ቅብዓትን ወዘተ የሚሉ ዘማርያንን እኮ ናቸው ትናንትና አባ ማርቆስ አይነሡብን ብለው የቆሙት፡፡ ታዲያ ቅዱስ ሲኖዶስ እርምጃ ለመውሰድ እርሳቸውንም እምነታቸውን ጠይቆ ለምን አይለያቸውም? ራሳችን ገንዘባችንን እየከፈልን እስከ መቼ ነው ምንፍቅና ሲያሳትሙ ዝም የምንላቸው፡፡ አባ ማርቆስ ደጋፊዎቻቸውን በቤታቸው አሳረው ጠዋት ላይ ሸኝተዋቸዋል፡፡ ደጀን ሲደርሱ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ቀርበው የከፈልነው ገንዘብ ይመለስልን ተገቢ አይደለም ብለው ከቢሮ ቢሮ ተንከራትተዋል፡፡ ፖሊሶች ግን ምንም እንደማያገኙ ነግረዋቸዋል፡፡ ይህንንም አምነውበት ተቀብለው ወደ ጎንቻ አምርተዋል፡፡ ጎንቻዎች መኪና ውስጥ ተከፋፍለው ሊደባደቡም እንደነበር ሰምተናል፡፡ ከዚህ በፊት መኪናቸው እየተጋጨ መኪናቸው እየተገለበጠ ተአምር ሲያዩ ኖረዋል፡፡ ዘንድሮ ግን መጨረሻቸው ስለኾነ ከጠብ እና ከቅጣት ውጭ ሌላ ነገር አልገጠማቸውም፡፡ የጠባቸው ምክንያት መረጃ የምትሰጡ ሰዎች አላችሁ በሚል እንደኾነ ለማወቅ ችለናል፡፡ መረጃችን አቡነ ማርቆስ ናቸው፡፡ እርሳቸው ጋር ደውለን ኹሉን ነገር ማረጋገጥ እንችላለን፡፡
‹‹ወነሰተ ምክሮ ለጸላዒ›› ማለት ይኸው ነው፡፡ ጎንቻዎች ለቅጣት 30 ሺህ ብር እና ለመኪኖች የትራንስፖርት ክፍያ የፈጸሙት ከአጥቢያዎች እንደኾነ ሰምተናል፡፡ ይህንን አረጋግጣችሁ መረጃውን ላኩልን ያለምንም ድርድር ውሳኔ እንዲሰጥ እናስደርጋለን፡፡ ገንዘባችንን ለጠላት መስጠት ስለማንሻ፡፡
==========
ጥቅምት 13/2011 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

ለ12ኛ ጊዜ የተጓዘው የምሥራቅ ጎጃም የተዋሕዶ ልጆች አቤቱታ!



================================
ጥቅምት 10/2011 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ቀን፡- 11/02/2011 ዓ.ም
ለኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን ቅ/ሲኖዶስ
አ/አበባ 
=============================== 
ጉዳዩ፡- በምሥ/ጎጃም ሃ/ስብከት እየተፈፀመ ያለውን ሃይማኖታዊና አስተዳደራዊ በደል በተመለከተ ለዐሥራ ኹለተኛ /12/ ጊዜ አቤቱታ ማቅረብ ይሆናል፡፡
============================
እኛ በምሥ/ጎጃም ሃ/ስብከት የምንኖር ምእመናን ፣ማኅበረ ካህናት እና የሰ/ት/ቤት ወጣቶች በሃገረ ስብከታችን እየደረሰ ያለውን ሃይማኖታዊ እና አስተዳደራዊ በደል አስመልክቶ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት ማለትም ለቅ/ሲኖዶስ፣ ለጠ/ቤተ ክህነት፣ ለምሥ/ጎጃም ዞን አስተዳድር፣ ለደ/ማ ከተማ አስተዳድር እንዲሁም ለአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በተደጋጋሚ ያሳወቅን መሆኑ ይታወቃል፡፡
ነገር ግን የሕዝቡ አቤቱታ እና በደል ሳይሰማ እና ሳይደመጥ በመቅረቱ ችግሩ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ከመሄዱ ጋር ተያይዞ የምሥ/ጎጃም ሃገረ ስብከት ለምሥ/ጎጃም ዞን ብሎም ለአማራ ክልል ከፍተኛ የስጋት ምንጭ በመሆኑ የምሥ/ጎጃም ዞን አስተዳድር ፣ የደ/ማ/ከተማ አስተዳድር እንዲሁም የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መስተዳድር ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ለክልላችን የሰላም ስጋት መኾናቸውን በመግለፅ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ቤተክህነት እንዲሁም ለቅዱስ ፓትርያርኩ ደብዳቤ ማስገባታቸው ይታወቃል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ አሁንም በቅ/ሲኖዶስ ተስፋ የማንቆርጥ በመኾናችን የብፁዕ አቡነ ማርቆስን ችግሮች ለዐሥራ ሁለተኛ /12 / ጊዜ እንደሚከተለው ለማቅረብ ተገደናል፡፡


ቅዱስ አባታችን
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት
ከኹሉም በፊት የሃገረ ስብከቱን ካህናት እና ምእመናን አቤቱታ ለመስማት በመፍቀዳችሁ በእግዚአብሔር ስም እያመሰገንን በብፁዕ አቡነ ማርቆስ እየደረሰብን ያለውን ግፍ በዝርዝር እናሳያለን ፡፡
1.  የሃይማኖታዊ ችግር
2.  አስተዳደራዊ ችግር
3.  የፋይናስ ችግር
4.  የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ አለማስከበር ብሎም መጣስ
5.  የሰላም ስጋት
1.ሃይማኖታዊ ችግር፡-
ምሥራቅ ጎጃም በመጽሐፍም በቃልም መናፍቃንን ያሳፈሩ የብዙ ሊቃውንት  መፍለቂያ ምንጭ ማለትም የእነ ቅዱስ ወሰማዕት አቡነ ቴዎፍሎስ፤ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ፣ አለቃ አያሌው ታምሩ፣ አራት ዓይና ጎሹ እና የእነ ክቡር ዶክተር ሐዲስ አለማየሁ፣ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ  መገኛ የሆነችውን ሀገረስብከት ብጹዕ አባታችን አቡነ ማርቆስ ግን ብዙ ሃይማኖታዊ ግድፈቶችን በየጊዜው የተናገሩ ሲሆን  ለአብነት ያክል፡-
ሀ. ማንኛውም ሰው ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ውጪ ቢሆንም በክርስቶስ ስም ከተጠመቀ ወደ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ሲመጣ ዳግም ጥምቀት ስለሚሆንበት አይጠመቅም ብለው ታላቁ የቤተ ክርስቲያንን መጽሐፍ በፍትሐ ነገሥት ላይ የተጻፈውን “ለዘተጠምቀ እም አላውያን ያጠምቅዎ ዳግመ” ትርጉሙም ከአላውያን ወገን የተጠመቀ ቢኖር ዳግም ያጥምቁት “ለዘተወልደ እም ጳውላኒ ዳግመ ያጥምቅዎ ፤ ከሳምሳጢ ጳውሎስ ከአርዮስ ከንስጥሮስ ወገን የተጠመቁ ቢኖሩ ይጠመቁ” እያለ መጽሐፍ እየተናገረ ይህ ልክ አይደለም በሚል መልኩ ያጠመቁ ካህናትን ዳግም ጥምቀት ታጠምቃላችሁ እያሉ እያወገዙ መገኘታቸው፡፡ 
ለ. በእርሳቸው ትውልድ ቦታ በጎንቻ ሲሶ እነሴ ወረዳ ቤተ ክህነት ውስጥ በምትገኝ ምስካበ ቅዱሳን ቆጋ ኪዳነ ምሕረት አንድነት ገዳምና  በመምህር ገብረ መድኅን እንዳለው ስም  የታተመውን ‘’ወልደ አብ’’ የሚባለውን መጽሐፍ ቅዱስ ሲኖዶስ በሊቃውንት ጉባኤ ካስመረመረ በኋላ በጥቅምት ወር 2010 ዓ.ም ባደረገው ጉባኤ አውግዞ ከቤተ ክርስቲያን መጽሐፍነት ለይቶና በዚህ መጽሐፉ በታተመበት አካባቢ ሥልጠና እንዲሰጥ ቢወስንም አቡነ ማርቆስ ግን በግልባጩ በዚህ ገዳም ያሉትን ሰዎች ስማቸውን በየመድረኩ እየጠሩ ማሞገስና የቅዱስ ሲኖዶስንም ውሳኔ ከምንም አለመቁጠርና ማንም መጽሐፍትን ሊያነብ ቢወድ ከዚሁ ገዳም ሄዶ ያንብ በማለት የተወገዘውን መጻሕፍ መጋበዝና ማስተዋወቅ ፤ ይኸው ‘’ወልደ አብ’’ የተባለው መጽሐፍ የተወገዘው በስህተት ነው የሚል ቡድን አቋቁመው ውሳኔውን ለማስቀልበስ በእንቅስቃሴ ላይ መሆናቸው፤
ሐ. አቡነ ማርቆስ በዓመታዊ በዓላት ይኹን በአንዳንድ ቦታዎች በሚያስተምሩበት ወቅት ተዋሕዶ የሚለውን ቃል ካለመጥራታቸው በተጨማሪ ሃይማኖታዊ ግድፈቶችን መናገራቸው፤ ለአብነትም ያህል
  ‘’ሰኔ ጎልጎታ ልብ ወለድ ነው’’ በዚህ የተጸለየ ጸሎት ጫካ ውስጥ የተዘራ ዘር ማለት ነው ፤
  ‘’ተዝካር ሟርት ነው’’
  ድጓ ተምረህ ሰው ልትሆን -----እያሉ ማስተማራቸውና ሕዝበ ክርስቲያኑን ግራ ማጋባታቸው፤
  ብጹእነታቸው ነገረ ቅዱሳንን በተመለከተ ግራ የሚያጋባ አቋም ያላቸው ሲሆን በአንድ ወቅት  ሰባክያነ ወንጌልን በመሰብሰብ እሙሐይ አባሆይ እያላችሁ አትስበኩ በማለት ትእዛዝ መሰል መልእክት ማስተላለፋቸው
  ኪዳንንና ቅዳሴን በማይነካ ሁኔታ በዐቢይ ጾም ጊዜ ሰንበት ት/ቤቶች ተሰባስበው የሚጸልዩትን ጸሎት ማስቆምና ጸሎቱን አድርሰው ወደ ቅዳሴ ለማስቀደስ የሚገባው ሰንበት ተማሪ ተስፋ ቆርጦ ከቤቱ እንዲቀር ማድረግ
መ. ተሐድሶ የሚባለውን የቤተ ክርስቲያን ጠላት የሆኑትን አቅፈውና ተንከባክበው መያዝ ለዚህም ማሳያ በሀገረ ስብከታችን ከመምሪያው አስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን  በግልጽም ይሁን በድብቅ ተሰግስገው መገኘታቸውና እንዲሁም የሰላም እጦት ምክንያት መሆናቸው
2. የፋይናንስና አስተዳደር ችግር
  አቡነ ማርቆስ ቤተክርስቲያን ሊባርኩ ወደ ገጠር ቤተ ክርስቲያን በሚሄዱበት ጊዜ ለጧፍ ፣ ለእጣን እንዲሁም ለማስቀደሻ ፍሬ ግብርና አልባሳት ያጣች ቤተ ክርስቲያን ብጹእነታቸው ከነቤተሰቦቻቸው ሄደው የሚጠይቁት ገንዘብ ከፍተኛ መሆንና ይህም ያለምንም ሕጋዊ ደረሰኝና አሰራር ውጭ መውሰዳቸው፡፡
  ገንዘብን ሕጋዊ አድርጎ ለመብላት የቁጥጥርና የሒሳብ ሹም መደቦችን የሚያስይዙት በሙያ ብቃት ሳይሆን በቤተሰብ ከዚያም ከራቀ ለሆድ አደሮች በመስጠት ሕጋዊ ሌብነትን መፈጸም፤
  ከሕዝብ ጋር በመሆን አንዳንድ ፕሮጀክት እንድንሰራ ተስማምተን እርሳቸውም ኮሚቴ አቋቋመው ሥራውን ለመጀመር ጠቀም ያለ ገንዘብ ከተሰበሰበ በኋላ ገንዘቡን ለማባከንና ለመበዝበዝ ጠንካራ የኮሚቴ አባላትን ያለ ምንም ጥፋትና ግምገማ ከኮሚቴው ማባረር ብሎም ኮሚቴውን ማፈራረስና ለምዝበራ የሚመች ኮሚቴ ማቋቋም፤
ለምሳሌ፡-  የሀገረ ስብከቱ ህንጻ አሰሪ ኮሚቴና የባሕረ ጥምቀቱ ኮሚቴ ለዚህ ማሳያዎች ናቸው፡፡   
3. አስተዳደራዊ ችግር፡-
3.1 የአቡነ ማርቆስ ጠባይ በራሱ ከአንድ አባት የማይጠበቅ ከመሆኑም በላይ ምንም እንኳን ሀገረ ስብከታቸው ባይቀመጡም አንዳንድ ቀን ይመጡና ዐውደምህረት በሚቆሙበት ሰዓት ታላቁን የጎጃም ሕዝብ ማዋረድና እንደ ሰው አለመቁጠር ለምሳሌ የጎጃም ሕዝብ ምንም አያመጣም ትንኝ ነው ፣ ብዙ ሊቃውት የወለዱትን አናቶችንና እህቶችን ወደ መድረክ ያወጡና ‘’አንቺ የባሏ እዳ’’ በማለት በሕዝበ ክርስቲያኑ ፊት ማዋረድና ባልና ሚስት እንዲጠራጠሩ ማድረግና በበዓሉ ምክንያት የተሰበሰበውን ሕዝበ ክርስቲያን የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል እንዳይሰማ ጊዜ ማባከን ፣ ሌላውን ስድብና ንቀት ለጉባኤው ስለማይመጥን ትተነዋል፡፡
3.2 አቡነ ማርቆስ ፈታኝ የሆነ ችግር ሲመጣና የአጿማት ጊዜያት ሲገቡ ወይም ሲያዙ  ከሕዝበ ክርስቲያኑ ጋር ተቀራርቦ ችግርን ከመፍታትና ጾም ጸሎት ከመያዝ ይልቅ ለጉብኝትም ይሁን ገንዘብ ለመሰብሰብ ወደ አሜሪካ ሄዶ ሦስት አራት ወር መቆየት የተለመደ ተግባራቸው ከመሆኑም በላይ በመጡ ሰዓት ደግሞ ችግሩን ተቋቁመው ከሕዝቡ ጋር ስለ ቤተ ክርስቲያንና ስለ ሰላም ሲወጡ ሲወርዱ የቆዩትን የሀገረ ስብከቱ አገልጋዮችም ሆነ ወረድ ብለውም ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች ጀምሮ አስከ አቃቢት ድረስ ማፈናቀል፤ ለዚህም ማሳያ
ሀ. የቤተሰብ ቅጥር፡-
የሀገረ ስብከታችን ሥራ አስኪያጅ አስተዳድር ጉባኤውን በመያዝ  ሕዝበ ክርስቲያኑ በጠየቃቸውና ሕገ ቤተ ክርስቲያን በጠበቀ ሁኔታ ቦታውን በእውቀትም ሆነ በሥነ ምግባር የማይመጥኑ አገልጋዮችን ዝቅ አድሮጎ እንዲመድቡና በአንጻሩ ደግሞ የእውቀት ምንጭ የሆኑትን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን በቦታው እንዲተኩ አንዲሁም በቤተሰብ የተያዘችውን ሀገረ ስብከት ነጻ እንዲያወጧት በመጠየቁና ይህ ካልሆነ ደግሞ ሕዝበ ክርስቲያኑ የራሳችንን እርምጃ እንወስዳለን በማለቱ የተከበሩ የሀገረ ስብከታችን ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ብርሃናት ከሀሊ በቃሉ የሕዝበ ክርስቲያኑን ችግር በማዳመጥና በኋላም የአስተዳደር ጉባኤውን በመሰብሰብና አገልጋዮችንም የሚመጥናቸውን ቦታ ራሳቸው እንዲያመለክቱ በማድረግ ምንም እንኳን የቀድሞው አመዳደባቸው ትክክል ባይሆንምና የደመወዛቸው መጠን ከፍተኛ ቢሆንም ደመወዛቸውን እንደያዙ ከአካባቢው ሳይለቁ ወረድ ብለው ተመድበዋል፡፡ ይህን በማድረጉም የአስተዳደር ጉባኤው ሕዝበ ክርስቲየኑን ከስህተት፤ ቤተክርስቲያንን ደግሞ ከቤተሰባዊ ቅጥር አሰራር ነጻ ወጣች ባንልም ነጻ በመውጣት ላይ ይገኛል፡፡ ቤተሰባቸው በመነካታቸው አቡነ ማርቆስ የቁጭት ብቀላ ጀምረዋል፡፡
ለ. ሕገ ወጥ ማሕተም ማስቀረጽና ሕገ ወጥ እገዳ፡-
ሌላው የሕዝበ ክርስቲያኑ ጥያቄ የፋይናንስ አስተዳደር ጉዳይ ስለነበር ሊቀ ብርሃናትና የአስተዳደር ጉባኤውም ሀገረ ስብከቱ ኦዲት እንዲደረግ  ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጋር በመነጋገር ለዚህ በጎ ተግባርም  ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ሦስት ኦዲተሮችን ስለላከ የሚያስመሰግነው ተግባር ነው፡፡ ክቡር የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅም በዚህ ባልተረጋጋና በለውጥ ዘመን ሀገረ ስብከታችንን ከችግር በመታደጋቸው ከአስተዳደር ጉባኤው ጋር ምስጋና ሲገባቸው ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ከእረፍታቸው መልስ ሕዝቡ ሲረጋጋና ሦስት ወር በሰላም ኑሮውን ሲቀጥል ሰላም የማያስደስታቸው ብፁዕነታቸው በክቡር ሥራ አስኪያጁ ቀሲስ ከሀሊ በቃሉና በሀገረ ስብከቱ ጸሐፊ  መልአከ ብርሃን አባ ወልደ ትንሣኤ ላይ የሥራ እገዳ ደብዳቤ ጽፈውባቸዋል፡፡  ‘’ብር ላበደረ ጠጠር’’ እንዲሉ በዚያ በጭንቅ ሰዓት ሀገረ ስብከቱን ከጥፋት ታድገው በመቆየታቸው፤ ሊመሰገኑ ሲገባ  ሕገወጥ የእገዳ ደብዳቤ መሰጠቱ አግባብነት የሌለው ከመሆኑም በላይ በጣም የሚያስገርመውና ቤተ ክርስቲያንን አንገት የሚያስደፋው ጉዳይ ለእገዳው የተጻፈው ደብዳቤና ማህተም ሕጋዊነት ሁኔታ ነው፡፡ ይኸውም ሕዝበ ክርስቲያኑ ብጹነታቸው ቢመጡ እርምጃ እንወስዳለን ስላለና ወደ ሀገረ ስብከቱ መምጣት ሳይችሉ ሲቀሩ የሀገረስብከቱ ሕጋዊና ነባር ማህተም እያለ ኹለተኛ ሕገ ወጥ ማህተም በማስቀረጽ በፕሮቶኮል ተመዝግቦ ያልወጣ ደብዳቤ ወደ ሃገረ ስብከታችን መላካቸው፡፡
ሐ. ሹም ሽርና ያልተገባ ዝውውር    ፡-
ብጹዕ አቡነ ማርቆስ የእርሳቸው ቤተሰብ ካልሆነ በቀር ሌሎች ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ተረጋግተውና ከቤተሰብ ጋር እንዳይኖሩ በየሦስት ወሩ መቀያየርና አንዳንዶቹን ደግሞ ከሥራ ማባረር ለዚህም በዓመት ውስጥ የአንድ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ እስከ ሦስትና ከዚያ በላይ ጊዜ መቀያየር በቂ ማሳያ ነው፡፡
ሐ. የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አባላትን ማገድ፡-
ሕዝብ የመረጣቸውንና የሚወዳቸውን እንዲሁም ሥራቸውን አውቀው በጥሩ ሁኔታ ቤተ ክርስቲያንን የሚያለሙትንና ሌብነትንና ዘረኝነትን የሚከላከሉትን የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አባላት ከሥራ ማባረርና ሲመች ዘመዳቸውንና ሆድ አደሮችን ማስገባት ካልተቻለም አጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑ ያለ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ማስቀረት፣ ለአብነት ያህልም የገዳመ ሕያዋን ዋሻው ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ያለ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ከዓመት በላይ መቆየቱን መጥቀስ በቂ ማስረጃ ነው፡፡
መ. የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ማሳሰርና ማስደብደብ፡-
የነገዪቱ ቤተ ክርስቲያን ተተኪ የሆኑትንና ተሐድሶ መናፍቃንን በማስተማር፣ ወደ አባቶቻችንም በመውሰድና በማስመከር እንዲሁም ስውር ሴራቸውን በማጋለጥ ለቤተ ክርስቲያን የጀርባ አጥንት የሆኑትን የሰንበት ት/ቤት አባላትን ለእስር ጋብዘዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በፌሮ፣ በመቋሚያና በምንባረክበትና የሰላማችን ምልክት በሆነው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ደሙ እንደፈሰሰው እንደ ሊቀ ካህኑ ዘካርያስ የሰንበት ተማሪዎች አንድ ቀን አይደለም ሁለት ሦስት ጊዜ ደማቸው ፈሷል፡፡
4. የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔና የጠቅላይ በተ ክህነቱን ትዕዛዝ አለማክበርና አለማስከበር ብሎም መጣስ
ብጹእ አቡነ ማርቆስ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ቢሆኑም ቅዱስ ሲኖዶስ የሚወስናቸውን ውሳኔዎች አያከብሩም፤ አያስከብሩም፡፡ ለዚህም ማሳያዎች፡-
4.1. በሀገረ ስብከቱ ጸረ ተሐድሶ ኮሚቴ አለማቋቋም፡-
ቅዱስ ሲኖዶስ በ2007 ዓ.ም ባደረገው ጉባኤ ተሐድሶ በቤተክርስቲያናችን እያደረሰው ያለውን ግፍና በደል ከተመለከተ በኋላ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጀምሮ አስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ጸረ ተሐድሶ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሥራውን እንዲሰራ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥብቅ ውሳኔ መመሪያ ቢያስተላልፍም ብጹእ አቡነ ማርቆስ የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ ወደ ጎን በመተው ኮሚቴም ሳያቋቁሙ መቅረታቸውና እንዲያውም እርሳቸውን የሚያማክሯቸው ጨለማን ተገን አድርገው ለጥፋት የተፋጠኑ ስውር ጥቅመኛ የሆኑ በተሐድሶ መናፍቃን የሚጠረጥሩ ግለሰቦች መሆናቸው
4.2 ከአራት ዓመት አንድ ጊዜ በዘመነ ዮሐንስ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ጊዜ አቡነ ማርቆስ አንዳንድ ጊዜ ልደት በ28 ቀን ከተከበረ ግዝረትም በአምስት ጥምቀትም በአስር ቀን መሆን አለበት ይላሉ፤ ስለዚህ በዓሉ በታህሳስ 29 ቀን መከበር አለበት በማለት የቅዱስ ሲኖዶስን ቀኖና ከመጣሳቸውም በላይ ለእርስ በእርስ ግጭት አይነተኛ መንስኤ ሆነዋል፤ ይህንም በኅቡእ “ማኅበረ መሲህ” የሚባል ማኅበር በመመስረት እየተንቀሳቀሱና ሥልጠና በማሰጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ እንዲሁም በአንድ ሲኖዶስ ውስጥ ‘’በዶግማ አንድ ነን በቀኖና ግን እንለያያለን’’ እየተባለ ይገኛል፡፡  ጠበቅ ያለ ጥያቄ ሲቀርብባቸው ደግሞ አንዱን በ28 ሌላውን በ29 ቀን መከበርና መቀደስ አለበት በማለት ከግጭቱም በተጨማሪ በአንድ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሁለቱም ቀን በዓሉ ይከበራል ይቀደሳል፡፡



4.3 የጠቅላይ ቤተ ክህነት ትእዛዝ አለመፈጸም፡-
የጠቅላይ ቤተ ክህነት ትእዛዝ ከሰኔ 4- ሰኔ 6/2010 ዓ.ም ስለ ስብከተ ወንጌል፣ ስለ ሰበካ ጉባኤና ስለ ተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ ስልጠና እንዲሰጥ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ልኡክ ቢልክም የሰንበት ተማሪዎች ስልጠናውን ከጀመሩ በኋላ ስለ ስብከተ ወንጌል አሰጣጥና ስለመናፍቃን ጥያቄ በመጠየቃቸው የሰንበት ተማሪዎች ከስልጠናው ተባረዋል፤ በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰ/ት/ቤቶች የመምሪያ ኃላፊው መምህር እንቁባሕርይ በአሉበት መሆኑ ነው፡፡
4.4 የተወገዘን መጽሐፍ በድብቅም ይሁን በግልጽ አንዲሸጥ መፍቀድ፡-
በጥቅምት 2010 ዓ.ም ቅዱስ ሲኖዶስ ባደረገው ጉባኤ ላይ ‘’ወልደ አብ’’ የሚለው መጽሐፍ ተወግዞ እያለና በሀገረ ስብከቱ ውስጥ ስልጠና እንዲሰጥ መወሰኑ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን በብጹዕነታቸው ሀገረ ስብከት ወልደ አብ መወገዙ ስህተት ነው፤ ስለዚህ ‘’ወልደ አብ’’ መወገዙን እናስመልሳለን የሚል የጨለማ ቡድን እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፤ ለዚህም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የብጹነታቸው ድጋፍ መኖሩና ይህ ደግሞ የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ አለመቀበል ነው፤ እያደገ ሲመጣ ምን ሊሆን እንደሚችል ለመተንበይ ነብይ መሆን አያስፈልግም፡፡   
5. የሰላም ስጋት መሆናቸው
5.1 ሕዝበ ክርስቲያኑን በቡድን መከፋፈል፡-
አቡነ ማርቆስ ሁለትና ሦስት ወረዳዎችን ማለትም በተወለዱበት አካባቢ ያሉትን አባቶቻችንን፣ እናቶቻችንን፣ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን በመከፋፈልና ሃይማኖትህን ሊያስክድህ መጣልህ ተነሥ በማለት ሕዝብን ከሕዝብ ማጋጨት ለአብነትም ያክል በጎንቻ ሲሶ እነሴ ወረዳ ቤተ ክህነት ጉንደ ወይን ከተማ በቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ላይ ራሳቸው የቀጠሩትን ሰባኬ ወንጌል ዲማ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሄደሃል ተብሎ ቤተ ክርስቲያን ላይ ሕዝቡ እንዲወግረው በማይክራፎን ከቀሰቀሱ በኋላ በአንዳንድ አስተዋይ ግለሰቦችና በመንግስት ጥረት መምህሩ ሊተርፉ ችለዋል፡፡

5.2 የጾም ሥርዓትና ቀኖናን በማዘበራረቅ፡-
በዘመነ ዮሐንስ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ታህሳስ 28 ቀን ቢወሰንም በእኛ ሀገረ ስብከት በአንዲት አጥቢያ ቤተ ክርስቲን ውስጥ በ28ትም በ29ኝም ቀን የሚያከብሩና የሚቀድሱ አጥቢያዎች አሉ፡፡ አሁንም ይህ ጉዳይ ሃይማኖታዊ ብቻ ሳይሆን ለሰላምም ጠንቅ ስለሆነና ብጹእነታቸውም ሕዝብን ከሕዝብ የሚከፋፍሉበት ስልት ስለሆነ ቅዱስ ሲኖዶስ አፋጣኝ እልባት ሊሰጠው ይገባል፡፡ በአጠቃላይ ብጹእ አቡነ ማርቆስ ለምን ይህን አደረጉ ብለው ሲጠየቁ አንድ ለየዋህን እውነት የመሰለ ነገር ግን ሀሰት የሆነ መደበቂያ ዋሻ አላቸው ይኸውም ይህን ሁሉ ያደረገኝ ማኅበረ ቅዱሳን ነው ይላሉ  ነገር ግን ማን ያርዳ የቀበረ ማን ይናገር የነበረ ነውና እኛስ ማኅበረ ቅዱሳንን የምናውቃቸው የተዘጋ ቤተ ክርስቲያን ሲያስከፍቱ፣ አብነት ት/ቤቶችንና መምህራንን ሲደግፉ፣ ጧፍ እጣን ያጡትን አብያተ ክርስቲያናት ሲረዳና ወጣቱ ሃይማኖቱንና ባህሉን እንዳይለቅ ሲያስተማሩ ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ብጹእ አቡነ ማርቆስ ስለእውነት ደፍሮ የሚናገራቸውን የመንግሥት አካላትም ይሁን ነጋዴ ወይም ምእመን ይህ ማኅበረ ቅዱሳን ነው በማለት ስምና ተቀጽላ ታርጋ ከነግብርአበሮቻቸው ይለጥፉበትና የስም ማጥፋት ዘመቻ ይከፍታሉ፤ ሲፈልጉም ኲላዊት የሆነች ቤተ ክርስቲያንን በወንዝ ይከፍሉና የሽዋ ማኅበር ነው ይላሉ፡፡ ይህ ስብስብ ማኅበረ ቅዱሳን እንዳልሆነ ለዚህ ማስረጃ የሚሆነው የዛሬውን አቤቱታ አቅራቢ የመነኮሳት፣ የካህናት፣ የሽማግሌዎችና ሰ/ት/ቤቶች ስብጥርን ያየ ዓይን  ራሱ ምስክር ነው፡፡ 
ስለዚህ እኛ የምንፈልገው፡-
1.  ደም ሳይፋስ አቡነ ማርቆስ በዚህ ሲኖዶስ ጉባኤ ከምሥ/ጎጃም ሃ/ስብከት እንዲነሡልን፡፡
2.  የተከበሩ ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ብርሃናት ከሀሊ በቃሉና የተከበሩ የሀገረ ስብከቱ ጸሐፊ አባ ወልደ ትንሣኤ በሕገ ወጥ ደብዳቤ የታገዱበት እንዲነሣላቸው፤
በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ሰላማችንን እየነሱን እና እያበጣበጡን አቤቱታ ስናቀርብ ከሳሼ ማኅበረ ቅዱሳን ነው በማለት ቅ/ሲኖዶስን እንኳ ሳይቀር ሲያታልሉ የቆዩ ቢሆንም የምሥ/ጎጃም ዞን አስተዳደር፤የደ/ማርቆስ ከተማ አስተዳደር እንዲሁም የደ/ማ ከተማ ፖሊስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የምሥራቅ ጎጃም የሰላም ስጋት መሆናቸውን በአካልም በጽሑፍም ለቅዱስነታቸው፣ ለብፁዕ ሥራ አስኪያጁ እና ለብፁዕ የቅ/ሲኖዶስ ዋና ፀሃፊ እውነታውን ማቅረባቸው ይታወቃል፡፡ አሁንም ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ዘመዶቻቸውን ፤ጥቅመኞችን እና እንባረራለን ብለው የፈሩ ካህናትን ለአቤቱታ ወደ አዲስ አበባ ይዘው መጥተዋል፡፡
ስለዚህ ቅዱስ አባታችን፣ ብፁአን አባቶቻችን ይህን ሁሉ አቤቱታ ሰምታችሁ ብፁዕ አቡነ ማርቆስን ከሃ/ስብከታችን የማታነሡልን ከሆነ በማንኛውም መንገድ ቤተክርስቲያናችንን የመጠበቅ ግዴታ ያለብን በመሆኑ ይህን ተከትሎ ለሚፈጠረው ችግር ኃላፊነቱን የምትወስዱ መሆኑን ለመግለፅ እንወዳለን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ግልባጭ፡-
-   ለሰላም ሚንስቴር
አዲስ አበባ
-   ለአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር
ባህር ዳር
-   ለምስ/ጎጃም ዞን መስተዳድር
-   ለደ/ማርቆስ ከተማ አስተዳደር
ደ/ማርቆስ