Monday, February 8, 2016

የዔሊ ቸልተኝነት

© በመልካሙ በየነ
ጥር 30/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ካህኑ ዔሊ አፍኒንና ፊንሐስ የሚባሉ ሁለት ምናምንቴ ልጆች ነበሩት፡፡ ዔሊ ክህነት ከምስፍና ጋር አስተባብሮ ለ40 ዘመን አስተዳድሮ ስለደከመ እነዚህን ልጆቹን ከበታቹ ሾማቸው፡፡ እነዚህ የዔሊ ልጆች ግን ሦስት ዐበይት ኃጣውእ ሠሩ፡፡
1.  ሙሴና አሮን በሠሩት ሥርዓት መሠረት በቀዳማይ ሰዓተ ሌሊት በርቶ በቀዳማይ ሰዓተ መዓልት ይጠፋ የነበረውን ፋና ከባዶ ቤት ሲበራ ቢያድር ምን ይጠቅማል? ብለው አስቀሩ፣
2.  እስራኤላውያን መሥዋዕት በሚሠዉ ጊዜ ገና ስቡ ሳይጤስ የወደዱትን ሥጋ እየነጠቁ ይበሉ ነበር፣
3.  ሴቶችን በቤተመቅደስ ውስጥ ያስነውሩ ነበር፡፡

ካህኑ ዔሊ ልጆቹ ይህን ሁሉ ሥራ እንደሚሠሩ ሲያውቅ ልጆቼ ሆይ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ኃጢአተኛ በማድረጋችሁ ስለእናንተ የደረሰኝ ወሬ መልካም አይደለምና ይህ አይሆንም፡፡ ሰውስ ሰውን ቢበድል እግዚአብሔር ይፈርድለታል ሰው ግን እግዚአብሔርን ቢበድል ስለእርሱ የሚለምን ማን ነው? አላቸው፡፡ ነገር ግን ምክሩ ቸልተኛ ምክር ነበር፡፡ እንደዚያ ያለ የከፋ ኃጢአት እየሠሩ እያለ ከስልጣን ልሻራቸው አለማለቱ ቸልተኝነቱን ያሳያል፡፡ካህኑ ምክሩ ከእኔ ይውጣልኝ እንጅ ቢመለሱ ባይመለሱ የሚል የቸልተኝነት አስተሳሰብ ተጠቂ ነው፡፡ ከላይ የተጠቀሱትን ሦስት ዐበይት ኃጣውእ ልጆቹ ማድረጋቸውን (መሥራታቸውን) እያወቀ ከእግዚአብሔር ይልቅ ለልጆቹ አድልቶ ከበታቹ እንደሾማቸው ልሻራቸው ሳይል ቀረ፡፡ እነርሱም አባታቸው በቸልተኝነት የመከራቸውን ምክር ቸል አሉት አልተቀበሉትም፡፡ የቸልተኛ ልጆች ናቸውና እንደአባታቸው እነርሱም ቸልተኞች ሆኑ፡፡ እግዚአብሔር ሊገድላቸው ወዷልና የአባታቸውን ቃል አልሰሙም እንዲል፡፡ በዚያን ጊዜ ታቦተ ጽዮንን ያገለግል የነበረው ብላቴናው ሳሙኤል ተኝቶ ሳለ “ሳሙኤል ሳሙኤል!” ብሎ ጠራው፡፡ ሳሙኤል ግን ካህኑ ኤሊ የጠራው መስሎት ወደ ዔሊ ሄዶ “እነሆኝ የጠራኸኝ” አለ፡፡ዔሊም “”ሂድና ተኛ እኔ አልጠራሁህም” አለው፡፡ አሁንም ለሁለተኛ ጊዜ እንዲሁ ሆነ ዔሊም “ሦስተኛ የሚጠራህ ከሆነ ተናገር ባሪያህ ይሰማል በል” አለው፡፡ሳሙኤልም ለሦስተኛ ጊዜ እግዚአብሔር ሲጠራው ዔሊ እንዳዘዘው አደረገ፡፡ እግዚአብሔርም ለሳሙኤል “ልጆቹን አፍኒንና ፊንሐስን ከበደል አልከለከላቸውምና እንድፈርድበት የነገርኹትን በዔሊ ላይ እፈጽምበታለሁ” አለው፡፡ በተጨማሪም የእስራኤልን መሸነፍ (መመታት)፣ የታቦተ ጽዮንን መማረክ፣ የአፍኒንና ፊንሐስን የዔሊንም ሞት ነገረው፡፡ ሲነጋ ዔሊ እግዚአብሔር የነገረህን አንዲት ሳታስቀር ንገረኝ ብሎ ሳሙኤልን ጠየቀው፡፡ ሳሙኤልም አንዲት ሳያስቀር ነገረው፡፡ ዔሊ ግን እርሱ እግዚአብሔር ነውና የወደደውን ያድርግ አለ፡፡ አሁንም ይመጣብሃል የተባለውን መቅሰፍት በቸልታ ተመለከተው፡፡ ከመመለስ ይልቅ ቸልተኝነትን መረጠ፡፡ የወደደውን ያድርግ እንጅ እኔ አልመለስም ልጆቼንም አልሽራቸውም አለ፡፡እግዚአብሔርም እንደተናገረው እስራኤላውያን በፍልስጥኤማውያን ተመቱ 4 ሽህ የሚያህሉ ሰዎችም ተገደሉባቸው፡፡ ይህ የሆነብን ታቦተ ጽዮንን ስላልያዝን ነው ብለው ታቦተ ጽዮንን እንዲልክላቸው ወደ ካህኑ ዔሊ መልእክተኛ ላኩ፡፡ የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ ታቦተ ጽዮንን ይዘው መጡላቸው፡፡ እስራኤላውያን ታላቅ ደስታ አደረጉ እልልታቸውም ደመቀ፡፡ ፍልስጥኤማውያንም እስራኤላውያን የሚደሰቱት በታቦተ ጽዮን መምጣት ምክንያት መሆኑን ሲያውቁ ወዮልን ወዮታ አለብን አሉ በግብጽ የሠራችውን ተአምር ያውቃሉና፡፡ ነገር ግን ተጽናንተው አስራኤላውያንን ገጠሙ አሸነፉም፡፡ አፍኒንና ፊንሐስን ገደሉ ታቦተ ጽዮንን ማረኩ፡፡ አንድ ብንያማዊ ልብሱን ቀድዶ አመድ ነስንሶ ወደ ከተማ ተመልሶ የሆነውን ሁሉ ለዔሊ ነገረው፡፡ ዔሊም የዘጠና ዓመት ሽማግሌ ነበርና ደንግጦ ከመንበሩ ወድቆ አንገቱ ተሰብሮ ሞተ፡፡ /1ኛ ሳሙ4÷1-18/ ለዚህ ሁሉ ከባድ ችግር ዋናው ምክንያት የዔሊ ቸልተኝነት ነበር፡፡ እግዚአብሔር በግልጥ እየነገረው ቃሉን ቸል ማለቱ ይህን መቅሰፍት አምጥቷል፡፡ እግዚአብሔር እንድትሠራው ያዘዘህን አለመሥራት አትሥራ ያለህንም መሥራት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ተመልከት፡፡ ስለዚህም እንዲህ አይነቱን የዔሊን መሰል ቸልተኝነት ልታስወግደው ይገባል፡፡ ከዚያ ውጭ ግን በአንድም በሌላም ነገር ተመክረህ ካልሰማህ ተዝቆ የማያልቀውን መከራ እግዚአብሔር ያሸክምሃል፡፡