Tuesday, January 31, 2017

ምንትኑ ውእቱ ሰብእ ከመ ትዝክሮ /ታስበው ዘንድ ሰው ምንድን ነው?/ መዝ 8÷4




© መልካሙ በየነ
ጥር 19/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT, LIKE ያድርጉ፡-
==============================================
ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “ምንትኑ ውእቱ ሰብእ ከመ ትዝክሮ፤ታስበው ዘንድ ሰው ምንድን ነው?” ይላል፡፡ እግዚአብሔር መፍጠር የጀመረው መጋቢት 29 በዕለተ ሰንበት እንደሆነ ሁላችን እናውቃለን፡፡ በሥነ ፍጥረት ትምህርታችን በዕለተ ሰንበት መላእክት እንደተፈጠሩ እንናገራለን፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ እግዚአብሔር ከሰው ልጅ ጋር ያለውን የጠበቀ ግንኙነት ማሳየት ስለሆነ ወደ ሥነ ፍጥረቱ ዝርዝር ጉዳይ አንገባም፡፡ ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የሚገባውን ሁሉ ከፈጠረ በኋላ በመጨረሻዋ ዕለት ዐርብ ሚያዝያ 4 ቀን አዳምን ፈጠረው፡፡ እግዚአብሔርን ስለመውደዴ አንዲት ቃል ልናገር እርሷም “እግዚአብሔር ለእኛ ለሰው ልጆች አድልቶልናል” የምትል ናት፡፡ በእውነት እግዚአብሔር የሚመሰገነው በፍጥረቱ ነው እኛም እናመሰግነዋለን መላእክትም ያመሰግኑታል ውኆች ድንጋዮች ሰማይና ምድርም ሁሉ ያመሰግኑታል፡፡ ነገር ግን ለእኛ ያደረገልንን ውለታ ለማንም አላደረገለትም ለዚህም ነው “እግዚአብሔር ለእኛ ለሰው ልጆች አድልቶልናል” ማለቴ፡፡

እግዚአብሔር በመጀመሪያ ሰማይና ምድርን ፈጠረ ይላል፡፡ ከዚያም ብርሃን ይሁን አለ ብርሃን ሆነ፡፡ ጠፈር ይሁን አለ ጠፈር ሆነ፡፡ ከሰማይ በታች ያለው ውኃ በአንድ ይሰብሰብ የብሱም ይገለጥ አለ እንዲሁም ሆነ ወዘተ እያለ ይቀጥልና ሰው ላይ ሲደርስ ግን ሰው ይሁን አለ ሰው ሆነ አላለም፡፡ እግዚአብሔርም አለ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር ይላል፡፡ አያችሁ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የሰጠው ትልቅ ክብር፡፡ ሰው በእግዚአብሔር መልክ እና ምሳሌ የተፈጠረ ድንቅ ፍጥረት ነው፡፡ የእግዚአብሔር መልኩ እና ምሳሌው የተገለጠው ገና በሥነ ፍጥረት አዳምን ፈጥሮ በገነት ባኖረው ጊዜ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የሰጠውን ክብር ለመላእክት እንኳን አልሰጣቸውም፡፡ ልብ በሉ ሳጥናኤል መጋቢት 29 እሁድ ተፈጥረ ሚያዝያ 2 ረቡዕ ቀን ነው አምላክ ነኝ ብሎ በእግዚአብሔር ላይ ስላመጸ አዳም ሳይፈጠር ነበር ሳጥናኤል የወደቀው፡፡ ሳጥናኤል ከመላእክት ዓለም እስኪባረር ድረስ የቆየባቸው ዕለታት ከእሁድ እስከ ረቡዕ ድረስ ያሉት ብቻ ናቸው፡፡ በቀን ደረጃ ስንቆጥራቸው 3 ቀናትን ማለት ነው፡፡ አዳም ሚያዝያ ዐራት ተፈጥሮ 7 ዓመት ከ1 ወር ከ17 ቀናትን ቆይቶ ነበር ከገነት የተባረረው፡፡ ሳጥናኤል በ3 ቀኑ ሲስት አምላክ ተሰቅሎ ሞቶ ተነሥቶ ወደ ቀደመ ክብሩ አልመለሰውም፡፡ አዳምን ግን በደሉን ተሸክሞ ቁስሉን ቆስሎ ህማሙን ተቀብሎ ተሰቅሎ ሞቶ ተነሥቶ ወደ ቀደመ ክብሩ መልሶታል፡፡ በርግጥ ሳጥናኤል ንስሐ አልገባም አዳም ግን ንስሐ ገብቷል ዋናው ቁልፍ ነገር ይህ ነው፡፡  ቢሆንም ግን አምላክ ሰማይና ምድርን በቃሉ ፈጥሮ አዳምን በቃሉ ወደቀደመ ክብሩ መመለስ ሲቻለው ይህንን ያህል መከራ የተቀበለው አብዝቶ ስለሚሳሳልን እንደሆነ እረዳለሁ፡፡ “እግዚአብሔር ለእኛ ለሰው ልጆች አድልቶልናል” ማለት የጀመርሁትም ይህንን ልዩ ፍቅሩን ከተመለከትሁ በኋላ ነው፡፡

ሌላው አምላክ ከሰው ልጅ መወለዱን ከመላእክት ዘንድ አለመወለዱን ሳስበው “እግዚአብሔር ለእኛ ለሰው ልጆች አድልቶልናል” እላለሁ፡፡ እግዚአብሔር ከድንግል ማርያም ተወልዶ አዳም ከባርነት ቀንበር ነጻ እንደሚወጣ አዳም ቀድሞውኑ ያውቅ ነበር፡፡ ነገር ግን መላእክትም በመወለዱ ደስ እንዲላቸው ብሥራቱን በመላእክት አደረገ፡፡ ከመላእክት መካከል ስሙ ቅዱስ ገብርኤል የተባለውን ወደ ድንግል ዘንድ የመጽነሷን ዜና ያበሥራት ዘንድ ላከው፡፡ ብሥራቱን በመላእክት ዘንድ አደረገ እነርሱም በመወለዱ ደስ የሚሰኙ ናቸውና፡፡ አንድም ሰውና መላእክት በልደቱ አብረው ይዘምሩ ያመሰግኑ ዘንድ በብሥራቱ አስታረቀን፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን አሁን ከድንግል ማርያም  ተወልዷል፡፡ በመወለዱም ሰውና መላእክት አብረው አመስግነዋል፡፡  እንግዲህ 30 ዘመን ሲሞላው ወደ መጥምቁ ዮሐንስ ዘንድ ሄደ፡፡ ለምን ሄደ ብንል ይጠመቅ ዘንድ ነው፡፡ አያችሁ ጥምቀቱንም በሰው እጅ አደረገ፡፡ በመላእክት እጅ አላደረገውም፡፡ ምክንያቱም “እግዚአብሔር ለእኛ ለሰው ልጆች አድልቶልናልና ነው”፡፡

እንደተጠመቀ ሳይውል ሳያድር ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ገብቶ 40 መዓልት 40 ሌሊት ጾመ፡፡ መጾሙም ለእኛ ነው ለመላእክት አይደለም፡፡ ጾሞ ጹሙ ያለን እኛን እንጅ መላእክትን አይደለም ወይም ሌሎች ፍጥረታትን አይደለም፡፡ ከዚያም ወደ ምኩራብ ገብቶ አስተማረ ማስተማሩም እኛን ነው፡፡ ከዚያም ተሰቀለ ሞተ መሞቱም ስለእኛ በእኛ መሰቀሉም ስለእኛ በእኛ ነው፡፡ የተሰቀለልን ለእኛ ነው የተሰቀለውም በእኛ እጅ ነው፡፡ የሞተልን ስለእኛ ነው የሞተውም በእኛ እጅ ነው፡፡ ከዚያም ተቀበረ፡፡ የተገነዘውም የተቀበረውም በሰው እጅ ነው፡፡ እንግዲህ ሁሉንም ነገር ለሰው ልጆች ነው ያደረገው፡፡ ምክንያቱም አብዝቶ ስለሚወደን ነው፡፡ ከዚያም በሦስተኛው ቀን ተነሣ ሲነሣም የማንንም እርዳታ አልፈለገም ምክንያቱም አምላክ ነውና፡፡ በልደቱ ሰውና መላእክትን እንዳገናኘ ሁሉ ፤ ዛሬ በትንሣኤውም እንዲሁ አገናኛቸው፡፡
የሚገርመኝ ነገር የሰው ልጅ ከመላእክት እንኳ በልጦ መገኘቱ ነው፡፡ ከሰው በዘር በሩካቤ የተወለደችው ድንግል ማርያም ከፍጡራን ሁሉ በላይ ናት፡፡ እዚህ ላይ ዮሐንስ አፈወርቅ ያደረገውን ድንቅ ሥራ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ንጉሥ አርቃድዮስና ንግሥት አውዶክስያ ልጅ እየሞተ አላድግላቸው ይላል፡፡ አሁንም ሴት ልጅ ይወልዳሉ እንዳትሞትባቸው ደግ ሰው ክርስትና እንዲያነሣላቸው በዘመኑ የነበረውን ደግ መምህር ዮሐንስ አፈወርቅን ክርስትና አንሣልን ይሉታል፡፡ እርሱም ጥሪውን አክብሮ ሲሄድ ረቂቁ መልአከ ሞት ልጅቷን ሊገድል ሲሄድ ያገኘዋል፡፡ ዮሐንስ አፈወርቅም የት ትሄዳለህ ይለዋል እርሱም አንተ ክርስትና ልታነሣት የምትሄድባትን ልጅ ልገድል ነው ይለዋል፡፡ ዮሐንስ አፈወርቅም “ልጅቷ ክርስትና እስክትነሣ ድረስ እንዳትገድላት እዚሁ ቆመህ ቆየኝ” ብሎት ይሄድና ክርስትና ያነሣታል፡፡ ልጅቷ ዐሥር ዓመት ሲሞላት ለባል ትታጭና ዮሐንስ አፈወርቅ ባርኮ እንዲሰድዳት ይጠሩታል፡፡ እርሱም ጥሪውን አክብሮ ሲመጣ መልአከ ሞትን ቆሞ ያገኘዋል፡፡ ዮሐንስ አፈወርቅም “ምነው ከዚህ ቆመሃል” ይለዋል፡፡ መልአኩም “የካህናት ማዕርጋቸው መቼ ያንቀሳቅሳል፡፡ ቃልህን አክብሬ ቆመህ ቆየኝ ካልከኝ ጊዜ ጀምሮ ወዲያ ወዲህ አላልኩም” ይላል፡፡ ዮሐንስ አፈወርቅም ይህን በመዘንጋቱ ራሱን ወቅሶ ሂድና የታዘዝከውን ፈጽም ብሎ ያሰናብተዋል እርሱም ሄዶ ልጅቷን ይገድላል፡፡ እዚህ ላይ ለሰው ልጅ የተሰጠው ማዕርግ ከመላእክት እንኳ ከፍ ያለ እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡ ሥጋና ደሙን መላእክት በበረሃ ላሉት ፈርተው በጉጠት ነው የሚያቀብሉት፡፡ ካህናት ግን በእጃቸው ይዳስሱታል፡፡ ለመላእክት እንኳ ያልተሰጠ ክብር ለሰው ልጅ ተሰጥቶታል፡፡ ነገር ግን ይህን ሁሉ ክብር ያድለው ዘንድ የሰው ልጅ ምንድን ነው? ዳዊት በመዝሙሩ “ምንትኑ ውእቱ ሰብእ ከመ ትዝክሮ ፤ታስበው ዘንድ ሰው ምንድን ነው? መዝ 8÷4 ማለቱ ከዚህ የተነሣ ነው፡፡