©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ሰላምና ጤናን የምመኝላችሁ ውድ
ጓደኞቼ ቸርነት የማያልቅበት ባለፀጋ ሁሉን የፈጠረ አምላክ እንኳን ከዘመነ ሉቃስ ወደ ዘመነ ዮሐንስ አሸጋገራችሁ፡፡ አዲሱ ዓመት
ከጥል ወደ ፍቅር፣ ከኃጢአት ወደ ጽድቅ፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከባርነት ወደ ልጅነት፣ ከቂም ከበቀል ወደ ይቅር ባይነት፣ ከበደል
ከርኩሰት ወደ ንስሐ የምንመለስበት እንዲያደርግልን አምላካችንን ዘወትር በመትጋት እንለምን፡፡ በዚህ ዘመን የምንሰማውና የምናየው
ነገር ሁሉ አስፈሪ ነው፡፡ ፍቅር ከሰው ልጆች እጅግ ርቃ የሄደችበት ዝርፊያ፣ ውንብድና፣ ስርቆት፣ መግደል የበረታበት ጊዜ ነው፡፡
ልማድ ሆኖብኝ ነው እኔም አንኳን አደረሳችሁ ያልኳችሁ እንጅ ለዚህ ዘመን ከመድረስስ አለመድረስ በተሻለ ነበር፡፡ ኃጢአት በአብዝተን
ከፈጣሪያችን ጋር በዓይነ ቁራኛ የምንተያይበት የሰይጣን ባለሟልነት የበረከተበት ዘመን ነው፡፡ በእውነት የጥፋት ውኃ ቢኖርማ መጥፋት
የነበረብን እኛ የዛሬዎቹ ነበርን ግን ቸርነቱ ምጡቅ የሆነ ፈጣሪ አለንና ትእግሥቱ ከለከለው፡፡ አቤት… ጉዳችን!!! አቤት… ኃጢአታችን!!!
አቤት … ውርደታችን!!!
እኔ ለኃጢአት እጄን ከሰጠሁ ሰነባበትሁ
ለዛም ነው አምላክ እንድጓዝበት ከሰጠኝ መንገድ ይልቅ የተሻለ የመሰለኝን ሰፊ መንገድ መርጨ መድረሻው በውል በማይታወቀው ጉዞ የምባክነው፡፡
ኃጢአትን ልትሰራት ስታስብ አቤት ያላት ጣፋጭነት አቤት ያላት ሰላም፡፡ ኃጢአትን ከመሥራትህ በፊት የሚፈጥርልህን ደስታ ከሰራኸው
በኋላ አታገኘውም፡፡ ሰይጣን በጎ አስመስሎ የሚያሳየኝን ኃጢአት ስዳስስ ብዙ ባክኛለሁ እንዲያውም ኃጢአትን ከመሥራት
ባለፈ መጠሪያዬም ሆኗል፡፡ ለኃጢአት እጄን አንሥቼ ምርኮኛነቴን አረጋግጫለሁ፡፡ በዚህ ብርሃናዊ
በመሰለው የኃጢአት ዘመን ሁሉ የማይታሰበኝ ጽድቅ እጅግ ርቆኛል፡፡ ቅዳሴው፣ ኪዳኑ፣ የዕጣኑ ሽታ፣ የእመቤታችን ተአምር፣ የእነ
እማሆይ መክፈልት… ሁሉንም ከመናፈቅ ባለፈ አይቻቸውም፣ ሰምቻቸውም፣ ቀምሻቸውም አላውቅም፡፡ ዘመኑ ዘመንን እየወለደ ይከንፋል እኔም
በዕድሜዬ ላይ ዕድሜን እየጨመርሁ እኖራለሁ የልደት ዘመኔን አከብራለሁ ለካ ሞትን እየቀረብሁት እንጅ እየራቅሁት አይደለም፡፡ ጉዞዬ
ወደ ሞት እየተቃረበ መሆኑን ግን እንዳላስብ ሰይጣን የማስብበትን ኅሊና ሰውሮብኛል፡፡ መተኛት፣ መነሣት፣ መብላትና መጠጣት መሳቅና
መጫወት፣ መዝፈንና መጨፈር ብቻ ነው የዕለት ከዕለት ተግባሬ፡፡ ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደት፣ ምጽዋት የሚባሉት ምግባራት በስም ለመጥራት
እንኳ ሳልረሳቸው አልቀረሁም፡፡
መጾም ሲሰለቸኝ መብላትን እመርጣለሁ፣
መመጽወት አልችል ስል እንዲያውም መስረቅን ገንዘቤ አደረግሁት ከዚህ የኃጢአት ሸክሜ ጋር ደግሞ እምነት አለኝ እላለሁ፡፡ መጾም
ባትችልም እምነትህን አትለውጥ፣ መስገድ ባትችልም እምነትህን አትለውጥ፣ መመጽወት ባትችልም እምነትህን አትለውጥ እያሉ ያስተማሩኝ
መምህር ትዝ ይሉኛል፡፡ ለመብላት፣ ለመጠጣት፣ ለመዝፈን ለመደነስ፣ ለመጨፈር ሲሉ ከተዋሕዶ እምነት የወጡ ወገኖቼ ትዝ ይሉኛል፡፡
ጹም፣ ጸልይ፣ መጽውት፣ ስገድ ከምትለዋ እምነታችን አፈንግጠው እንዲህ ወደማይለው ምንፍቅና የተሰገሰጉ ብዙዎች ናቸው፡፡ እኔ ግን
ኃጢአቴን እንደያዝኩ በኃጢአት እንደተጨማለቅሁ፣ በኃጢአት ሸክም እንደጎበጥሁ እምነቴን ይዤ ተቀምጫለሁ፡፡ ከእምነት ሕጸጽ ይልቅ
የምግባር ሕጸጽ ይበጅሃል ያሉኝን መምህር በተለየ ሁኔታ እወዳቸዋለሁ፡፡ ጻድቅ ሰባት ጊዜ ይወድቃል ሰባት ጊዜም ይነሣል እያሉ ያጽናኑኝ
አንድ አባት ደግሞ የሁልጊዜ ትዝታዬ ናቸው፡፡
ታዲያ በዚህ የኃጢአት ዘመኔ አምላኬ
ቢጠራኝስ? ከባዱ ችግር ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡ እኔ አሁን ላይ ሆኘ ሳስበው ኃጢአት መራራ ሆኖብኛል ስለዚህ ልተፋው እወዳለሁ፡፡
አዲስ ሰው እንድሆንም አፍርሳችሁ ልትሠሩኝ አደራው የናንተ ነው፡፡ ከወሬ ያለፈ የተግባር ሰው እንድሆን ደግሞ የናንተን ድጋፍ አሻለሁ፡፡
የምታፈርሱት በኃጢአት የቆሸሸ ኅሊናዬን ነው፡፡ አንተ ለእኔ መጥፋት ተጠያቂ እንዳትሆን እኔን ማትረፍ አለብህ፡፡ እኔም እንዲሁ
ላንተ መጥፋት ተጠያቂ እንዳልሆን አንተን ማትረፍ አለብኝ፡፡ አንተ ለእኔ እኔም ለአንተ መዳን ምክንያቶች ነን፡፡ የመዳን ቀን ደግሞ
ዛሬ ነው ነገ ሌላ ቀን ስለሆነ የነገንም መኖር ስለማናውቅ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ ሁሉ የኃጢአት ሸክም ለመገላገል አፍርሳችሁ
ልትሰሩኝ ይገባል፡፡ ካህናት አባቶቼ የተሰጣችሁ ሥልጣን በእውነት ግሩም ነው እኮን፡፡ እናንተን ለእኔ ባይሰጠኝ ኖሮ በኃጢአት እንደጨቀየሁ
ወደ ገሐነመ እሳት እጣል ነበር ነገር ግን እናንተን ስለሰጠኝ አፍርሳችሁ ትሠሩኛላችሁ፡፡ የተሸከምኩትን ከባድ ሸክም አራግፋችሁ
ቀና ብየ እንድሄድም ታደርጉኛላችሁ፡፡ የኃጢአቴን እድፍና ቆሻሻ በንስሐ ሳሙና ታጥቡልኛላችሁ፡፡ እኔ ራሴን ለእናንተ አሳያለሁ የውስጤንም
ማንነት እገልጥላችኋለሁ እናንተ ደግሞ አዲስ ሰው እንድታደርጉኝ አፍርሳችሁ ልትሰሩኝ የአምላክ ትእዛዝ አለባችሁ፡፡ ስለዚህም በኃጢአት
የተገነባውን ማንነቴን በንስሐ አፍርሳችሁ እንድትሰሩኝ እማጸናችኋለሁ፡፡