Friday, March 10, 2017

ዓለም አቀፍ የቤተክርስቲያን ጉባኤያት---ክፍል ፩



© መልካሙ በየነ
መጋቢት 1/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT, LIKE ያድርጉ፡-
=============================================
ከዛሬ ጀምረን እግዚአብሔር እስከ ፈቀደው ድረስ በጉባኤያት ዙሪያ እና በእነዚህ ጉባዔያት የተወገዘው ትምህርተ ምንፍቅና ወደ አገራችን እንዴት እንደ ገባ በሰፊው በማብራሪያ አስደግፈን እንመለከታለን፡፡ ምናልባትም ከ፲፭ ክፍል ያላነሰ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ ስለዚህ ሁሉንም ክፍሎች እንድትከታተሉ ከወዲሁ በእግዚአብሔር ስም አሳስባችኋለሁ፡፡
የቀደሙ አባቶቻችን በየዘመኑ ለሚነሡ ከሐድያን ፣ መናፍቃን፣ ዐላውያን እና አረማውያን ሁሉ እጃቸውን ባለመስጠት የምንፍቅና ትምህርታቸውን በማውገዝ ርትዕት በሆነች ተዋሕዶ ሃይማኖት ኖረዋል፡፡ በቤተክርስቲያን ላይ ቀስታቸውን ለሚወረውሩ መናፍቃን ሁሉ ተገቢውን ክርስቲያናዊ ምላሽ በማቅረብ የምእመናንን ነፍስ ከመናፍቃን ቀስት ታድገዋል፡፡ በቤተክርስቲያናችን ላይ በርካታ መናፍቃን የክህደት ትምህርታቸውን ወደ ውስጥ ለማስገባት ሲጥሩ እንደነበር ታሪክ መዝግቦት እናገኛለን፡፡ ለቤተክርስቲያናችን በጣም ስጋት የነበረው ግን ከውጭ ያሉ መናፍቃን የሚወረውሩት ቀስት ሳይሆን ከውስጥ ሆነው ምንፍቅናቸውን በተለያዩ አጋጣሚዎች ያስተላልፉ የነበሩ ሰዎች ናቸው፡፡ በዚህ መልኩ ተደራጅተው ከውጭ ያሉ መናፍቃንን አስተምህሮ ከውስጥ ሆነው ያስተምሩ የነበሩትን መናፍቃን አባቶቻችን ትምህርታቸውን ማውገዝና መናፍቃኑንም ከቤተክርስቲያን አንድነት በመለየት ተዋሕዶ እምነትን አሁን ላለን ክርስቲያኖች አቆይተውናል፡፡ በእነዚህ በርካታ መናፍቃን መነሣት ምክንያት አባቶቻችን ትምህርታቸውን ለማውገዝና መናፍቃኑን ለመለየት ዓለም አቀፋዊ ጉባኤዎችን አካሂደዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የምትቀበላቸው ዓለም አቀፍ የቤተ ክርስቲያን ጉባኤዎችም ሦስት ናቸው፡፡ እነዚህም፡-
1.  ጉባኤ ኒቅያ በ325 ዓ.ም በ318ቱ ሊቃውንት የተካሄደው
2.  ጉባኤ ቁስጥንጥንያ በ381 ዓ.ም በ150 ሊቃውንት የተካሄደው እና
3.  ጉባኤ ኤፌሶን በ431 ዓ.ም በ200 ሊቃውንት የተካሄደው ናቸው፡፡
ለእነዚህ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች መካሄድ ምክንያት የሆነው ከላይ አስቀድመን እንደተናገርነው በየዘመናት አስተምህሯቸውን እየቀያየሩ የተነሡ መናፍቃን ናቸው፡፡ በእነዚህ ጉባኤዎች መጨረሻ ላይም ሊቃውንተ ቤተክርስቲያኑ የተስማሙበትን የቀና እና በጎላ በተረዳ የታወቀውን ትምህርት ይጽፉ እና ለመላው ዓለም ያሰራጩ ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለጉባኤው ምክንያት የሆነውን የምንፍቅና ትምህርት ያወግዙ እና ይህን ምንፍቅና ያራምድ የነበረውንም መናፍቅ ከምእመናን አንድነት ይለዩ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት በዚህ ምእራፍ በዋናነት የምንመለከተው የሚሆነው በእያንዳንዱ ጉባኤያት የተወገዘውን ትምህርት እና ከምእመናን አንድነት የተለየውን መናፍቅ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም ሊቃውንት አበው የደረሱበትን የቀና ትምህርትም እንዲሁ እንመለከታለን፡፡
፩.ጉባኤ ኒቅያ
ይህ ጉባኤ የመጀመሪያው ጉባኤ ሲሆን የተካሄደውም ህዳር 9 ቀን 325 ዓ.ም ሲሆን የጉባኤው ተሳታፊ የነበሩት ሊቃውንትም 318 ነበሩ፡፡ ኒቅያ በጥቁር ባሕር ወደብ አካባቢ የምትገኝ ከተማ ስትሆን የተመሠረተችውም በዲዮናስዮስ ነው፡፡
፩.፩ ጉባኤው ለምን አስፈለገ?
ለዚህ ጉባኤ መጠራት ዋና ምክንያት የሆነው በዋናነት “ወልድ ፍጡር” የሚለው የአርዮስ የክህደት ትምህርት ነበር፡፡ ነገር ግን ሌሎችም የምንፍቅና ትምህርቶች በጉባኤው ታይተዋል፡፡ ሃይማኖተ አበው ዘሠለስቱ ምዕት ምእራፍ 18 ቁጥር 1 ላይ  ይህንን የመሰብሰባቸውን ምክንያት ሲገልጹ “የመሰብሰባቸው ምክንያትም የእግዚአብሔር ልጅ ፍጡር ነው ያለ አርዮስን መናፍቃንንም ሁሉ ፎጢኖስን ደኃራዊ ስላለ፣ ጳውሎስ ሳምሳጢን ኅድረት ስላለ፣ ዋሊጦንና ማኒን ምትሐት ስላሉ፣ መርቅያንን ዝርው ስላለ ሐዋርያት የሰበሰቡዋት የከበረች ቤተክርስቲያንን ይወሯት ዘንድ የተነሡ መናፍቃንን ሁሉ ስለማውገዝ ነው” በማለት ይገልጻሉ፡፡ ከዚህ እንደምንረዳው በኒቅያው ጉባኤ ላይ የተሳተፉ 318ቱ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን የሚከተሉትን ነጥቦች ዓይተዋል ማለት ነው፡፡
v  ወልድ ፍጡር ነው በማለት ኑፋቄውን በልዩ ልዩ መንገዶች ያሰራጭ የነበረውን አርዮስን እና ትምህርቱን፣
v  ቃል የታወቀው ከድንግል ማርያም ከተወለደ በኋላ ነው ስለዚህም ወልድ አብና መንፈስ ቅዱስ ከኖሩበት ዘመን በኋላ የመጣ ደኃራዊ ነው በማለት ያስተምር የነበረውን ፎጢኖስን እና ትምህርቱን፣
v  ወልድ ከድንግል ማርያም ሥጋን የተዋሐደው መንፈስ ቅዱስ በቅዱሳን እንደሚያድረው ባለ ኅድረት ነው በማለት ያስተምር የነበረውን ጳውሎስ ሳምሳጢን እና ትምህርቱን፣
v  ወልድ የተዋሐደው ሥጋ በምትሐት ነው እንጅ የድንግል ማርያም ሥጋ አይደለም በማለት ያስተምሩ የነበሩትን ዋሊጦንና ማኒን እና ትምህርታቸውን፣
v  ቃልን አካል የለውም ዝርው ነው በማለት ያስተምር የነበረውን መርቅያንን እና ትምህርቱን፣
ሆኖም ግን በዚህ ጉባኤ በዋናነት ጎልቶ የወጣው ትምህርት የአርዮስ ስለነበረ ይህ ጉባኤ በዋናነት ለአርዮስ የክህደት ትምህርት ተገቢውን ምላሽ የሰጠ ነበር፡፡ በአርዮስ ጉዳይ በዋናነት ጉባኤው የተመለከታቸው ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው፡፡
v  አርዮስ  “ወልድ ፍጡር” የሚለውን ትምህርቱን ይደግፋሉ ብሎ ያቀረባቸውን ሁሉንም ጥቅሶች መርምረዋል፤
v  የኑፋቄው መነሻ የነበረውን “ጥበብ” የሚለውን ቃል አርዮስ እንዴት እንደተረጎመው ተመልክተዋል፤
v  አርዮስ እንዳለው ወልድ በባሕርይው ፍጡር ነው ከተባለ የማዳን ሥራው እንዴት እንደተከናወነ ተወያይተዋል፣
v  በአባቱ ፈቃድ በእርሱም ፈቃድ በመንፈስ ቅዱስም ፈቃድ ለሰው ልጆች ድኅነት ሲል ክቡር አምላክ ክቡር ካልሆነ ሥጋ ጋር ቢዋሐድ በባሕርዩ ተወራጅ ስለሆነ ነው በማለት ያስተምር በነበረው የአርዮስ ክህደት ላይ ተነጋግረዋል፣
v  ወልድ በባሕርይው ፍጡር ሲሆን እንደሌሎች ፍጡራን ሁሉ በገድል በትሩፋት የአምላክነት ክብርን አገኘ በማለት አርዮስ ያስተምረው በነበረው ክህደቱ ላይ በጥልቀት ተወያይተዋል፣

No comments:

Post a Comment