በትንሽ
ከተማ በኪራይ ቤት የሚኖር አንድ ሰው ነበር፡፡ ይህ ሰው የተከራየው ትልቅ መኖሪያ ቤት ነው፡፡ በዚህ ቤት ባለቤቱን፣ ልጆቹን፣
ከብቶቹን ይዞ ነበር የሚኖረው፡፡ ሰው ግን እጅግ አብዝቶ ያስመርረዋል፡፡ ሰውየው ማንበብና መጻፍ አይችልም፡፡ ማንበብ እና መጻፍ
አለመቻሉ ነው ለዚህ ሁሉ ስቃይ የዳረገው፡፡ ኪራይ የሚፈልግ ሰው ሁሉ የተከራየውን ቤት እያንኳኳ “ስንት ነው የሚከራየው” ይለዋል፡፡
ሰውየው ይህንን ጥያቄ እጅግ በጣም ሰልችቶታል፡፡ ነጋ ጠባ ሰው ሁሉ እያንኳኳ “ስንት ነው ኪራዩ” ይለዋል፡፡ እርሱም በጣም ሰለቸና
አንድ ቀን “እንዴ ሰው ሁሉ ምን ነካው? እኔ ተከራይቼ እያያችሁ
እንዴት አይነት ጥያቄ ነው የምትጠይቁኝ? ቤቱ እኮ የእኔ አይደለም የተከራየሁት እንጅ፡፡ ቆዩ ግን ለምንድን ነው እንዲህ በላየ
ላይ ኪራይ ምናምን የምትሉት? ሰው እንደው ትንሽ ይሉኝታ የሚባል ነገር የለውም ልበል ሆ ወይ ጉድ ነገር፡፡ ግሩም እኮ ነው የእናንተ
ደግሞ! እሽ ግን ይከራያል ብላችሁ ልትደረቡብኝ ነው እንዴ?” አለ በቁጣ ገንፍሎ፡፡ ሰውየው ቤቱን ሲከራይ አብሮ የተከራየውን ጽሑፍ
አላወቀም፡፡ አላፊ አግዳሚው ግን ያንን ጽሑፍ እየተመለከተ ነበር “ኪራይ ስንት ነው?” የሚለው፡፡ከቤት በር ላይ የቤቱ ባለቤት
ቤቱ ከመከራየቱ በፊት “ይከራያል” ብሎ በቆርቆሮ ቀለም በጉልህ ጽፎበት ነበር፡፡ ሰውየው ይህንን ቤት ሲከራይ ይህንን ጽሑፍ አላነበበውም
ምክንያቱም ማንበብ ስለማይችል፤ የቤቱ ባለቤትም ቤቱ ከተከራየ በኋላ የተጻፈውን አላጠፋውም፡፡ ለዚህ ነው ሰው ሁሉ ቤቱን እያንኳኳ
“ስንት ነው ኪራይ” በማለት ሰውየውን ልቡን ያወለቀው፡፡ ቤቱን ከነጽሑፉ ስለተከራየው ይህ ሰው በጣም ተቸገረ፡፡
ዛሬ
ዛሬ ከዚህ ሰው በከፋ ችግር ውስጥ ያለን በርካታ ሰዎች አለን፡፡ ከግለሰብ እስከ ቡድን፣ ከነጠላ እስከ ማኅበራት፣ከተማሪ እሰከ አስተማሪ፣ ከቀበሌ እስከ ፌዴራል፣ ከክልል እስከ አገር ድረስ ሳናውቅ በምንከራያቸው
ነገሮች በጣም ስቃይ ጸንቶብናል፡፡ አንድ ሰው ባለማዎቅ ከልብሱ ጋር በሚገዛው ጽሑፍ ይሸማቀቃል፡፡ አንዲት እርጉዝ ሴት “I
AM VIRGIN” የሚል ልብስ ለብሳ ስትሄድ ሰው ቢስቅባት ሳቁን ከማስተናገድ ውጭ የለበሰችው ልብስ ላይ የተጻፈውን ነገር አትረዳውም፡፡
አንዱ ደግሞ ያገኘው ሰው ሁሉ ባገኘው ነገር ይመታዋል፡፡ ለምን እንደሚመቱት ግን አያውቅም፡፡ ለካስ “KICK ME” የሚል ጽሑፍ
ከልብሱ ላይ ተጽፏል፡፡ ሳናውቅ በምንሰራቸው ሥራ፤ ሳንረዳ በምንገለብጠው ነገር ሁሉ ተጠቂዎች ራሳችን ነን፡፡ ቆዩ እንጅ ግን የማናውቀውን
የምንሠራ እና የምንገለብጥ እኛ ኢትዮጵያውያን ብቻ ነን እንዴ? ሰው የማያውቀውን እያደረገ በመከራ ይኖራል፤ መንግሥት የማያውቀውን
ሕግ እየገለበጠ አገዛዝ ያከፋብናል፡፡ ተማሪው መልስ መሆን አለመሆኑን ሳይረዳ ከጓደኛው ይኮርጃል (ይሰርቃል)፤ አረ አንዳንዱስ
ከነ ስሙም የሚኮርጅ አለ አሉ፡፡ የማናውቀውን ስንሠራ ትንሽ ኃፍረት የማይሰማን ግን ለምንድን ነው? አገርን ያህል ነገር በተቀዳ
ፖሊሲ፣ በተኮረጀ እቅድ፣ ይጥቀም አይጥቀም በማይታወቅ አስተሳሰብ ስናስተዳድር ትንሽ አይሰቀጥጠንም፡፡ አይጥና ዝንጀሮ ለላብራቶሪ
ምርመራ እንደሚጠቀሙባቸው ሁሉ እኛን ኢትዮጵያውያንንም የፖሊሲ፣ የስታራቴጅ፣ የአመለካከት፣ የአስተሳሰብ መፈተኛ ቤተሙከራዎች ያደረጉን
በርካቶች ናቸው፡፡ ለማንኛውም ቢያንስ በራሳችን መፍታት የምንችላቸውን ቀላል ነገሮች መፍታት የተሻለ ስለሆነ ሥራን ከመስራታችን
በፊት ጥቅሙን፣ ለምን እንደምንሰራው፣ መቼ እንደምንሠራው፣ እንዴት እንደምንሠራው ማወቅ ያስፈልጋል፡፡
des yilal
ReplyDeletedes yilal
ReplyDelete