Tuesday, March 8, 2016

ፍትሐ ነገሥት እና ጾም

© በመልካሙ በየነ
የካቲት 28/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
አባቶቻችን ለእያንዳንዱ ሥራዎች ሥርዓትን ሠርተውልናል፡፡ ይህንን በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ለኛ የሠሩልንን ሕግ ደግሞ ማዎቅና ተግባራዊ ማድረግ ሕይወትን የሚያሰጥ በረከትን ያሚያድል መሆኑ የተረዳ ነው፡፡ በመሆኑም አሁን በያዝነው ጾም ውስጥ ምን ማድረግ ይጠበቅብናል የሚለውን ከፍትሐ ነገሥቱ ቃል በቃል እንመልከት፡፡
ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 15 (በእንተ ኵሎሙ አጽዋም፤ ስለጾሞች ሁሉ)
ቁጥር 564፡ ጾምስ በሕግ ውስጥ በታወቀው ጊዜ የሰው ከምግብ መከልከል ነው በደሉን ለማስተሥረይ ዋጋውን ለማብዛት እርሱን ወዶ ሕግን ለሠራለት እየታዘዘ የፈቲውን ኃይል ያደክም ዘንድ ለነባቢት ነፍስም ትታዘዝ ዘንድ፡፡
ቁጥር 565፡ ለክርስቲያን ሁሉ የታዘዘውም ጾም ክብር ምስጋና ይግባውና ክርስቶስ የጾመው ጾመ አርባ ነው፡፡ ፍጻሜዋ ከፍሥህ (የአይሁድ ፋሲካ) በፊት ባለው ዓርብ የሚሆን ነው፡፡ ከዚህም ቀጥሎ የስቅለት ሳምንት ነው፡፡ እነዚህን እስከ አሥራ ሁለት ሰዓት ድረስ ይጾማሉ ደም የሚወጣው እንስሳ ከእንስሳትም የሚገኘው አይበላባቸውም፡፡
ቁጥር 566፡ ዳግመኛም በእየሳምንቱ ሁሉ ዓርብና ረቡዕን መጾም ነው፡፡ በዓለ ሃምሳ የልደትና የጥምቀት በዓል የተባበሩባቸው ጊዜ ካልሆነ በቀር እንደተጻፈው እስከ 9 ሰዓት ድረስ ይጹሟቸው፡፡
ቁጥር 567፡ በዚህ ላይ የተጨመሩ ሌሎች ጾሞች ግን በግብጽ ቤተክርስቲያን ተጽፈዋል፡፡ ከእነርሱም እንደ ዐቢይ ጾም በመጠንቀቅ የሚሆን አለ፡፡ ይህችውም ከዐቢይ ጾም አስቀድማ የምትሆን የሕርቃል ጾም ናት፡፡ የነነዌ ሰዎች ጾም 3 ቀን የልደትና የጥምቀት ዋዜማ ጾም (ገሀድ)፡፡
ቁጥር 568፡ ከእነርሱም የሚያንስ እንደ ረቡዕና እንደ ዓርብ የሚሆን አለ፡፡ ይኸውም ከልደት አስቀድሞ የሚጾም ጾም ነው፡፡ መጀመሪያው የኅዳር እኩሌታ ፋሲካው የገና በዓል ነው፡፡
ቁጥር 569፡ ከዚህም ቀጥሎ ከበዓለ ሃምሳ ቀጥሎ ያለ የሐዋርያት ጾም ነው፡፡ ፋሲካው በጴጥሮስና በጳውሎስ በዓል ሐምሌ 5 ቀን ነው፡፡
ቁጥር 570፡ እነዚህን ጾሞች ሕጎቻቸውን ከተቀበሏቸው በኋላ ከጥቂቶቹ ውሳኔዎች ቁጥራቸው ከሚበዙ ሊቃነ ጳጳሳት ወገን ከተቆጠሩት ጋር ሕዝቡ እነሆ ጾመዋቸዋል፡፡ ያለሕጸጽም ሊጠብቋቸው ይገባል፡፡
ቁጥር 571፡ ከእነዚህም ሌላ ብዙ ሰዎች ጠብቀው የሚጾሙት አለ፡፡ ይኸውም ጾም ስለእመቤታችን በዓል ነው፡፡ ይልቁንም መናኒዎች መነኮሳት የሚጾሙት መጀመሪያው ነሐሴ አንድ ቀን ፋሲካው የእመቤታችን በዓል ነው፡፡
ቁጥር 572፡ በእነዚህ በታዘዙት ጾሞች ከቀኑ እስከ 9 ሰዓት ድረስ ይጹሙ ከዓሣ በቀር ሥጋ አይብሉባቸው፡፡ (እዚህ ጋር ግን ዓሣ ይበላል ማለት አይደለም ዓሣም ቢሆን ለማለት ነው)፡፡ ከዚህ ከታዘዘው አብልጦ የጾመ ግን ዋጋው ይበዛለታል ከጥሉላት በቀር እሁድና ቅዳሜ አይጹሙ፡፡
ቁጥር 573፡ ጾምስ የሥጋ ግብር ነው ምጽዋት የገንዘብ ግብር እንደሆነ፡፡ ሕግ ጾምን ያስወደደው የፈቲው ጾር ትደክም ዘንድ ለነባቢት ነፍስም ትታዘዝ ዘንድ ነው፡፡ ጸሎትን ያሻው ፈቃድ ለልብ የቁጣ ኃይል እንድትታዘዝ እንደሆነ፡፡
ቁጥር 574፡ ጾም ይረባናል ብለን ከመጾማችን የተነሣ መንፈሳውያንን እንመስላለን ከመሰልናቸውም የሚመስሉትን ለመምሰል ይቻላል፡፡ ዳግመኛም ጿሚው የረኃብን ችግር ያውቅ ዘንድ ለተራቡትና ለሚለምኑት ይራራላቸው፡፡ ዳግመኛም በፅኑዕ ፈቃድ ሁኖ ሊመገበው ሥጋውንና ደሙን ይቀበል ዘንድ ነው መቀበሉም በሥጋዊና በነፍሳዊ ትጋት ይሁን ዳግመኛም ከእንስሳዊ ባሕርይ ተለይቶ የጾምን ሥርዓት ጠብቆ ከሰው ወገን ደግሞ በጸሎት የተለየ ሁኖ ስለአጽዋም በተሠሩት ሕጎች የፀና ሁኖ በሁለንተናው እግዚአብሔርን ያምልከው፡፡
ቁጥር 575፡ ጾመ አርባ በእናንተ ዘንድ የከበረ ይሁን መጀመሪያውም ከሰንበቶቹ ሁለተኛ የሆነው ሰኞ ነው፡፡ መጨረሻውም ከፍሥህ አስቀድሞ ባለው በዕለተ ዓርብ ነው፡፡ ይህም ከፍሥህ ሱባዔ በኋላ ያለ ሱባዔ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ ከዐቢይ ጾም በኋላ የከበረ ሰሙነ ሕማማትን ትፈጽሙ ዘንድ ትጉ፡፡
ቁጥር 576፡ ከእርሷ በኋላ የፋሲካ ሳምንት የሚሆን ሰሙነ ፍሥህ (የአይሁድ ፋሲካ) እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እንደዚሁም እነዚህን ስድስቱን ቀኖች እንጾም ዘንድ አዘዙን፡፡ በየሳምንቱም ረቡዕንና ዓርብን እንጾም ዘንድ አዘዙን፡፡ ይኸውም ምክር የተፈጸመበት ነውና፡፡ ይኸኛውም መድኃኒታችን ፈቃዱን ስለፈጸመበት ነውና፡፡ በሰባተኛው ቀን ዶሮ በጮኸ ጊዜ ከጾም ይረፉ፡፡
ቁጥር 577፡ ዘወትር በዕለተ ሰንበት መጾም አይገባም እግዚአብሔር ከሥራው ሁሉ አርፎበታልና ቅዳሜ ስዑርን ብቻ ሊጾሙ ይገባል እንጅ፡፡ የፍጥረታቱ ሁሉ ፈጣሪ በመቃብር ውስጥ አድሮበታልና፡፡
ቁጥር 578፡ በሊህ በስድስቱ ቀኖች ከቂጣ ከጨው ከውኃ ብቻ በቀር አይብሉባቸው፡፡ በሊህ ቀኖች ከወይን ከሥጋ ተለዩ የኀዘን ቀኖች ናቸውና የደስታ ቀኖች አይደሉም፡፡ዓርብንና ቅዳሜን ግን ሁለቱንም በአንድነት ጹሟቸው፡፡ የሚችል እስከ ሌሊቱ ዶሮ ጩኸት ጊዜ ድረስ ምንም ምን አይቅመስባቸው ሰውየውም ሁለቱን ቀኖች በአንድነት መጾም ባይቻለው ግን የቅዳሜን ጾም ይጹም፡፡
ቁጥር 579፡ ጌታ ስለ ራሱ እንዲህ አለ “ሙሽራውን ከእነርሱ ለይተው በወሰዱት ጊዜ ያንጊዜ ይጾማሉ” እናንተም በእነዚህ ቀኖች እስከ ሌሊት ድረስ ጹሙ ሙሽራውን ከእኛ ለይተው በወሰዱት ጊዜ እኛ እንደ ጾምን፡፡
ቁጥር 580፡ በዓለ ሃምሳን ከጨረሳችሁ በኋላ ዳግመኛ ሰባት ቀን ሌላ በዓል አድርጉ ከዚህም ቀጥሎ ከአረፋችሁ በኋላ ቱሙ፡፡ ዳግመኛም ረቡዕንና ዓርብን ዘወትር ትጾሙ ዘንድ እናዝዛችኋለን የሚቻላችሁስ ከሆነ ከእህል ከዚህ አብልጣችሁ ጹሙ ለድሆችም ምጽዋት ስጡ፡፡
ቁጥር 581፡ እግዚአብሔር ይቅር ይበለውና ይህን መጽሐፍ ከሰበሰበው ተመረጠ ከሆነው መምህር ቃል የተገኘ ነው፡፡ የዚህ ሳምንት ምልክት ግን ልንበላበት እንደማይገባ እነሆ ረቡዕንና ዓርብን እንድንጾም ያዘዘበት አንቀጽ አለ ዳግመኛም በዓለ ሃምሳ ልደት ጥምቀት ቢውልባቸው አትጹሙ ብሎ ያዘዘበት አንቀጽ አለ፡፡ ስለዚህ ሳምንት ግን አልተናገረም፡፡ ቢበሉባቸው በሚገባ ቀኖች ውስጥ ሊጾሙባቸው የማይገባ ቢሆን ኖሮ እንደነዚያ መልሶ በተናገረ ነበር፡፡
ቁጥር 582፡ ዳግመኛም እንድንጾምባቸው እንድንሰግድባቸው የታዘዝንባቸው ቀኖች እንደ እሁድ እንደ ሰንበት እንደ ጌታ በዓላት ያሉ ቀኖች አሉና ከእነርሱ ጋር ይህን ሳምንት አልተናገረም፡፡ ዳግመኛም የሰሙነ ሕማማትን ሥራ ሳይሠራ ላለፈበት ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ስለርሷ መጾም መስገድ ይገባ ዘንድ ታዘዘ፡፡ ከበዓለ ሃምሳ በኋላ የሚውለው ሳምንት ይህ ቢሆን ኖሮ ከሃምሳ ቀኖች በኋላ ይበሉበት ዘንድ የሚገባ ቢሆን እንደገና ብሉበት በተባለ ነበር፡፡ በዓል አድርጉ ከማለቱ በቀር ብሉበት አላለምና፡፡
ቁጥር 583፡ ይህስ በውስጡ ያሉትን የዓርብንና የረቡዕን ጾም ያስረዳል፡፡ እነርሱንም ይፈጽሟቸው ዘንድ አያስረዳም እነሆ ባስልዮስና አፈወርቅ እንዲህ አሉ፡፡ በዓል ማክበር በመብል አይደለምና ዳግመኛም በጾም በዓል ማክበር እንዲገባ የታወቀ ነው፡፡ ይኸውም ለበዓሉ የሚስማማው እንዲነበብ ነው እንጅ ሊበሉበት አይደለም፡፡ ኤጲስ ቆጶስ በተሾመ ጊዜ 3 ቀን እንድናከብር እነሆ ቀኖና አዘዘችን፡፡ በጾም ቀን እንኳ ቢሆን በእነዚህ በ3 ቀኖች እንዳንበላ የታወቀ ነው በዓል ማክበር በመብል አይደለም፡፡  
ቁጥር 584፡ ዳግመኛም ቢቻላችሁ ከዚህ አብዝታችሁ ጹሙ በማለታቸው ይህን ሕግ እነሆ ወሰኑ በጾሙ ምክንያት ጠብ ክርክር ቢሆን መጾም ይገባል፡፡ ከመብላት በጣም ይሻላል፡፡
ቁጥር 585፡ ዳግመኛም ከተሰበሰቡት ወገን ቁጥራቸው ኸያ የሚሆኑት ጹመውታልና ከእስክንድርያ ሊቃነ ጳጳሳት ወገን ከዚህ ቁጥር ቁጥራቸው እስከበዙት ሊቃነ ጳጳሳት ድረስ በዚህ ሳምንት እነሆ ይህን ጾም ጾምን፡፡ የማኅበሩን ትእዛዝ ብንተላለፍ ይህን ማኅበር እንዲነቀፍ ብናደርግ ደግ አይደለም፡፡ ይልቁንም የሕጋችንን ትሩፋት በተቃወመ ጊዜ፡፡ ይኸውም ስለመብል ስስትን በመግለጽ የሚደረግ ክፋት ነው፡፡
ቁጥር 586፡ ዳግመኛም ስለ ሃምሳኛው ቀን አከባበር ሙሴ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቀበለውን ሕገ ኦሪት ለሕዝቡ ከማስተማር በፊት እንደጾመ ጌታችንም በርሱ ላይ መንፈስ ቅዱስ ከወረደ በኋላ የርሱን ሕግ ለሕዝብ ከማስተማሩ አስቀድሞ እንደዚሁ ጾመ፡፡ ሐዋርያትም በበዓለ ሃምሳ መንፈስ ቅዱስ በወረደላቸው ጊዜ ሕገ ወንጌልን ለሕዝብ ከማስተማራቸው አስቀድሞ እንደዚሁ ጾሙ፡፡ እኛም በዚህ በእነርሱ ተመራን፡፡
ቁጥር 587፡ ልደት በጾም ቀኖች ረቡዕና ዓርብ ቢውል ይጸልዩ፡፡ ሥጋውንና ደሙንም ይቀበሉ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ጹሙ ብለው አይፍረዱ፡፡
ቁጥር 588፡ አንድ ሰው በባሕር ቢኖር ሰሙነ ሕማማትን ባያውቅ ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ይጹም፡፡ ይኸውም ሰሙነ ሕማማትን የሚጠብቅ አይደለም፡፡ ምሳሌውን ብቻ ነው እንጅ ስለእርሱ መጾም ይገባዋል፡፡
ቁጥር 589፡ ዐቢይ ጾምንና ዓርብን ረቡዕን የማጾም የታወቀ ደዌ ያለበት ካልሆነ በቀር ካህን ከሆነ ይሻር ሕዝባዊ ቢሆንም ይለይ፡፡
ቁጥር 590፡ ካህን ሰሙነ ሕማማትን ቀንና ሌሊቱን ሳያስተካክል አስቀድሞ ቢያውል ይሻር፡፡ ከሕማማት ቀጥላ ከምትሆን ከቅዳሜ ስዑር በቀር እሑድንና ቅዳሜን የጾመ ካህን ቢኖር ሻር፡፡
ቁጥር 591፡ በዐቢይ ጾም የሰማዕታትን በዓል ልናከብር አይገባንም፡፡ የሰማዕታት መታሰቢያ በእሁድ በቅዳሜ ይሁን እንጅ፡፡
ቁጥር 592፡ በአርባ ጾም ሠርግ ማድረግ አይገባም ሴትም በወለደች ጊዜ ሰውን ወደ መጠጥ ቤት መጥራት አይገባም፡፡
ቁጥር፡ 593፡ ከካህናት ወገን ማንም ቢሆን በአርባ ጾም በዓርብና በረቡዕም ጾም ወይን መጠጣት አይገባውም ወደ መዋት (ውሽባ ቤት) አይግባ፡፡ በዐቢይ ጾም ወራት ሰው ከሚስቱ ጋር አይተኛ፡፡
ቁጥር፡ 594 የሰማዕታት በዓል ከጾም ላይ ቢውል ስለሰማዕታት ሞት ምክንያት ኤጲስ ቆጶሱ ወይም ቄሱ ለሕዝቡ በመብል በዓል ቢያከብር ይሻር፡፡ እርሱ ለብዙዎች ሰዎች የኃጢአት ምክንያት ሆኗልና እነርሱ በፈቃዳቸው ቢበሉ ግን ኤጲስ ቆጶሱ ወይም ቄሱ ይለያቸው፡፡ በጾም ወራት ከሆነ በሰማዕታት በዓል ቀን በመብል በመጠጥ ማክበር አይገባቸውምና፡፡ እነዚህ ሰማዕታት እየተራቡ እየተጠሙ በእሳት ተቃጥለው ሞተዋልና፡፡
ቁጥር 595፡ ስለ ልደትና ስለ ጥምቀት ግን በዚያ ዘመን በኒቅያ የተሰበሰቡ ሊቃውንት ቅዳሴው በሌሊት ይሆን ዘንድ አዘዙ፡፡ ዳግመኛም በበዓለ ሃምሳ እንደዚሁ ነው፡፡
ቁጥር 596፡ ክብርት በምትሆን በአርባ ጾም በመጀመሪያው ሱባዔ ፀሐይ እስኪገባ ድረስ ይጹሙ፡፡ የመጀመሪያው ሱባዔ ካለፈ በኋላ እስከ 11 ሰዓት ድረስ ይጹሙ፡፡ በሰሙነ ሕማማት ግን ኮከብ እስኪወጣ ድረስ ይጹሙ፡፡ በእነዚህም ወራቶች አያጊጡ፡፡
ቁጥር 597፡ ሴቶችም ጌጣቸውን ይተው፡፡ ሁሉም ለእያንዳንዱ በአርባ ጾምና በሰሙነ ሕማማት መጠበቅ ይገባዋል ድኅነታችንና የኃጢአታችን ሥርየት በእነርሱ ነውና፡፡ ይኸውም ሥራ አንዱስ እንኳ በአርባ ጾም ወራት በምንጣፍ ፈጽሞ እንዳይገናኝ ከጋብቻ ሕግ የወጣ ነው፡፡ ክብርት በምትሆን በሕማማት ወራት ይህችን ኃጢአት የሚሠራት ሰው ወዮለት፡፡ በአርባ ጾም በተድላ በደስታ ፈቃዳችንን ካደረግን ትንሣኤውን ባየን ጊዜ ተድላ ደስታችን ወዴት አለ?
ቁጥር፡ 598 ጾም ከእህል ከውኃ መከልከል አይደለም ከእግዚአብሔር ፊት የሚደርስ ጾምስ የልብ ንጽሕና ነው፡፡ ሥጋ ቢራብ ቢጠማ ነፍስ ግን ፈቃዷን ብትፈጽም ልብም ከጣዕሙ የተነሣ ደስ ቢለው የጾምህ ጥቅሙ ምንድን ነው?
ቁጥር 599፡ በተባሕትዎ በትሕትና አርባ ቀን ጾምን ይጹሙ፡፡ ከጥሉላት መከልከል ይገባል፡፡ አያግቡም፡፡
ቁጥር 600፡ በሰሙነ ሕማማት ክርስትና ማንሣት ክህነት መስጠት ለሞቱ ሰዎች መጸለይ አይገባም፡፡ በእነዚህም ቀኖች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ፈጽሞ ማገልገል ይገባል እንጅ፡፡ በሰሙነ ሕማማት ስለሚሞቱት ሰዎች የሙታን ግንዘትና የሐዋርያት ሥራ ወንጌላት የሙታን ፍትሐት በሆሣዕና በዓል ቀን ይነበብ እንጅ፡፡
ቁጥር 601፡ በጸሎተ ሐሙስ ጸሎተ ተአምኆ እግዚአ ሕያዋን የቡራኬ ጸሎት አይባልም (አይጸለይም)፡፡ ቅዳሜ ግን እግዚአ ሕያዋን ይባላል ፍትሐት ይፈታል፡፡ ከመሳለም በቀር ጸሎተ ዕጣንም ይጸለያል፡፡ በዕለተ እሑድ ግንዘት ማድረግ በፋሲካ ቀንም ማልቀስ አይገባም፡፡ ዳግመኛም በውስጧ በአርባ ጾም ከተድላ ከደስታ ወገን ምንም ማድረግ አይገባም፡፡ መጋባት ክህነት መስጠት ክርስትና ማንሣት ከሹመትም ወገን ስለሚሞቱት ከመጸለይ በቀር ምንም ማድረግ አይገባም፡፡ ይሞታል ተብሎ ለሚያስፈራው ግን ጥምቀተ ክርስትና ይደረግለታል፡፡
ቁጥር 602፡ ዐቢይ ጾም ስምንት ሱባዔ እንደሆነ በነገሥታት መጽሐፍ ተጻፈ፡፡ መጀመሪያው የክረምት መጨረሻ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ክረምት እንዳይደለ ይታወቃል መጨረሻው የበጋ መጀመሪያ ነው በየሳምንቱ አምስት ቀን መጾም ይገባል፡፡
ቁጥር 603፡ በብሉይ ሕግ በዓል በቅዳሜ በሐዲስ ሕግ በዓል በእሁድ ይብሉ ቅመማት የበዛበትን አይብሉ፡፡ የዓርብንና የረቡዕን ጾም ግን ከልደት ከጥምቀት ከበዓለ ሃምሳ በቀር ዘወትር ይጹሙ፡፡
ቁጥር 604፡ ከእሁድና ከቅዳሜ በቀር ለእግዚአብሔር የሚታዘዙ ሰዎች ከበዓለ ሃምሳ በኋላ የሐዋርያት ጾም መጾም ይገባቸዋል፡፡

===============================================================

No comments:

Post a Comment