Thursday, March 16, 2017

ዓለም አቀፍ የቤተክርስቲያን ጉባኤያት---ክፍል ፮


© መልካሙ በየነ
መጋቢት 7/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

ጉባኤ ኤፌሶን
የመቅዶንዮስን እና የሌሎችንም የእርሱን መሰል ምንፍቅና አራማጆች በጉባኤ ቁስጥንጥንያ ከተወገዙ እና ከተለዩ ከ50 ዓመታት በኋላ ከወደ ግሪክ ሌላ ክህደት የያዘ ሰው ስለተገኘ ሌላ ጉባኤ ተጠርቷል፡፡ ይህ ጉባኤ የተጠራው በ431 ዓ.ም ሲሆን በዚህ ጉባኤ ተሳታፊ የሆኑ ሊቃውንት ቁጥርም 200 ነበር፡፡ ለዚህ ጉባኤ መጠራት ምክንያት የሆነው በግሪክ ባለ አንድ ገዳም ውስጥ ይኖር የነበረው የንስጥሮስ ክህደት ነው፡፡ ይህ ንስጥሮስ ሁለት መሠረታዊ ክህደቶች አሉበት፡፡ እነዚህም፡-
v  ከተዋሕዶ በኋላ መለያየት እንዳለ ያምን የነበረውን ዲያድርስ የሚባለውን መናፍቅ አስተምህሮ ያምን ነበር፡፡ የዚህ መሠረታዊው ክህደት ሁለት ባሕርይ የሚል ነው፡፡ በዚህም መሠረት ከተዋሕዶ በኋላ አንዱን ወልደ ዳዊት አንዱን ደግሞ ወልደ እግዚአብሔር ነው በማለት ያምን ነበር፡፡
v  ሁለት ባሕርይ የሚል እምነት ስለነበረው ከእግዚአብሔር አብ የተወለደው ወልደ እግዚአብሔር ከድንግል ማርያም የተወለደው ደግሞ ወልደ ዳዊት ነው ብሎ ያምን ስለነበር እመቤታችን የወለደችልን እሩቅ ብእሲ ሰውን ነው እንጅ አምላክን አይደለም ይል ነበር፡፡ በዚህም ድንግል ማርያምን “ወላዲተ ሰብእ” በማለት ክህደቱን ጀምሯል፡፡
እነዚህን ክህደቶቹን በአደባባይ በማስተማር እርሱን መሰሎችን መሰብሰብ ጀመረ፡፡ ለዚህ ክህደቱም ይደግፋል ብሎ ይጠቅስ የነበረው “ቃል ሥጋ ሆነ” ዮሐ1÷14 የሚለውን ቃል ነበር፡፡ ይህንን ቃል ለራሱ እንዲመች አድርጎ መለወጥ አለበት በማለት ኑፋቄውን ቀጥሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ፊል 2÷5-6 ላይ “በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ ዐሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይኹን እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቆጠረውም” የሚለውን ቃል ይዞ በራሱ ለራሱ እንዲመች አድርጎ በመተርጎም ቃል በሥጋ አደረ ብሎ ኅድረትን ደግፎ ያስተምር ነበር፡፡ ስለዚህ ይህ ንስጥሮስ በውስጡ ብዙ ምንፍቅናዎችን የያዘ ትምህርት በዐደባባይ ያስተምር ነበር፡፡ ይህንን የክህደት ትምህርቱን የሰሙ ሊቃውንት በተለያዩ ጊዜያት ተገቢውን መልስ እየሰጡ ይመክሩት ነበር፡፡ ለዚህ ለንስጥሮስ ክህደት ተገቢውን ምላሽ ከሰጡት አባቶች መካከል በእስክንድርያ 24ኛ ፓትርያርክ የተሾመው ቅዱስ ቄርሎስ ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ ይህ ታላቅ አባት የቃልና የሥጋን ተዋሕዶ በሚገባ ከምሳሌ ጋር በማስረዳት ውላጤ እና ኅድረት የሚሉትን የንስጥሮስ ክህደቶች በሚገባ አጋልጧል፡፡
የጉባኤ ኤፌሶን መጀመር
ይህ ጉባኤ በዋናነት የንስጥሮስን ክህደት በሚገባ መርምሯል፡፡ ጉባኤው በኤፌሶን እንዲደረግ ዐዋጅ ያወጀው ንጉሥ ቴዎዶስዮስ ዘይንዕስ ነው፡፡ በዚህም የጌታን አምላክነት የድንግል ማርያምን ወላዲተ አምላክነት ነቅፎ ያስተምር የነበረው ንስጥሮስ በቅዱስ ቄርሎስ አፈጉባኤነት በተመራው ጉባኤበ200 ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ተወግዞ ተለይቷል፡፡ በዚህ ጉባኤ ላይ ታላቁ አባት ቅዱስ ቄርሎስ ምሥጢረ ተዋሕዶን በጋለ ብረት መስሎ በሚገባ አስረድቷል፡፡ ብረት የሚስማማው ባህርይ እሳት ከሚስማማው ባህርይ ጋር ፈጽሞ የተለያየ ነው፡፡ ብረት እና እሳት ሁለት የተለያዩ አካላት የተለያዩ ባሕርያት ናቸው፡፡ እሳት አንድ አካል ነው አንድ ባሕርይ ነው ብረትም እንዲሁ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ነው፡፡ እሳትና ብረት የራሳቸው የሆነ አካልና ባሕርይ አላቸው፡፡ በጊዜ ግለት ግን እሳት የብረትን ብረትም የእሳትን ባሕርይ ገንዘባቸው ያደርጋሉ፡፡ በጊዜ ግለት ጥቁር የነበረው ብረት የእሳትን ቀይነት፣ሙቀት፣ መልክእ ገንዘቡ አድርጎ ቀይ፣ሞቃት እንደሚሆን ሁሉ ጎንና ዳር የሌለው የማይጨበጠው ረቂቅ እሳትም ግዙፍ የሆነውን የብረት ቅርጽና ግዘፍነት ገንዘቡ አድርጎ የብረቱን ቅርጽ የብረቱን ግዘፍነት ይዞ ይገኛል፡፡ በዚህም አንድ አካል አንድ ባሕርይ ይሆናል፡፡ የመለኮትና የሥጋ ተዋሕዶም እንደዚሁ ያለ ነው፡፡ መለኮት ከሥጋ ጋር በተዋሐደ ጊዜ መለኮት የሥጋን፣ ሥጋም የመለኮትን ገንዘብ ገንዘቡ በማድረግ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆነ በማለት ለንስጥሮስ በዚህ ምሳሌ አስረድቷል፡፡ የንስጥሮስንም ምንፍቅና ለሁሉ አጋልጧል፡፡ በዚህም መሠረት የንስጥሮስ ክህደት ተወግዞ ተለይቷል፡፡በዚህ ጉባኤም አባቶቻችን የጨመሩልን አንቀጸ ሃይማኖት “በአማን ወላዲተ አምላክ፤ በእውነት አምላክን የወለደች” የሚል ነው፡፡ ንስጥሮስ “ሕስወኬ ትሰመይ ቅድስት ድንግል ወላዲተ አምላክ ወአማነ ትሰመይ  ወላዲተ ሰብእ” በማለት ክዶ ነበርና ሊቃውንቱ እርሱን አውግዘው “በአማን ወላዲተ አምላክ፤ በእውነት አምላክን የወለደች” ናት በማለት ድንግል ማርያምን ወላዲተ አምላክ ብለው አንቀጸ ሃይማኖት ጽፈውልናል፡፡
ንስጥሮስ ከጉባኤ ኤፌሶን በኋላ
ንስጥሮስ በክህደቱ ተወግዞ ከተለየ በኋላ ላዕላይ ግብጽ ይኖር ነበር፡፡ በዚህ ኑፋቄውም ጸንቶ ስለነበር ቅዱስ ቄርሎስ ዝም ብሎ አልተወውም ነበር፡፡ ንስጥሮስ ካለበት ዘንድ ሄዶ ወንደሜ ጌታን አምላክ ድንግል ማርያምን ወላዲተ አምላክ ብለህ እመን አለው፡፡ ንስጥሮስ ግን እኔስ አንተ እንደምትለው አልልም ጌታን እሩቅ ብእሲ ድንግል ማርያምን ወላዲተ ሰብእ እላለሁ እንጅ በማለት አሻፈረኝ አለ፡፡ ቅዱስ ቄርሎስም እመቤቴን ላዋርድ ብለህ እንዲህ እንዳልክና እኔንም አልታዘዝም እንዳልክ ላንተም አንደበትህ አይታዘዝልህ ብሎ ረገመው፡፡ በዚህም የተነሣምላሱ ተጎልጉሎ ከደረቱ ተንጠልጥሎ ደምና መግል እየተፋ በከፋ አሟሟት ሞቷል፡፡
በአጠቃለይ እነዚህ ሦስቱ ዓለም አቀፍ የቤተ ክርስቲያን ጉባኤዎች በየዘመናቱ ለተነሡት መናፍቃን እና የኑፋቄ ትምህርቶቻቸው ተገቢውን ውሳኔ በመስጠት እና ቀኖና ቤተክርስቲያንን በመደንገግ ከዚህ አይለፍ ከዚህም አይትረፍ እያሉ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደአንድቃል ተናጋሪ በመሆን የተሰበሰቡ ሊቃውንትየአባትነት ምስክራቸውን ያሳዩባቸው ጉባኤዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ጉባኤዎች በኋላ ሁሉም ሊቃውንት ለጉባኤው ምክንያት ለሆኑት ምንፍቅናዎች በየራሳቸው ድርሳናትንና ተግሳጽን ጽፈዋል፡፡ እነዚህ ጉባኤዎች ቤተክርስቲያናችን ሉዓላዊት እንደሆነች ያሳየችባቸውም ጭምር ነበሩ፡፡ በእነዚህ ጉባኤዎች ትምህርተ ሃይማኖትን ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን እና ትውፊትን በአግባቡ እንድንረዳባቸው አባቶቻችን ብዙ አስተምረውናል፡፡ እውነተኛ አባቶቻችን እነማን እንደነበሩ፣ የክህደት ትምህርት አራማጆችና ጋፊዎችም እነማን እንደነበሩ አውቀንባቸዋል፡፡ በዚህም የአባቶቻችን የቀናች የተረዳች ሃይማታችን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እንደሆነችና ከዚህች ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን አንድነትም ያፈነገጡትን መናፍቃን ለይተን እንድናውቅ ረድቶናል፡፡
******************************************************************************
እነዚህ በየጉባኤው የተወገዙ የምንፍቅና አስተምህሮዎች ወደ ሀገራችን እንዴት እና መቼ መጡ የሚለውን የዚህን ቀጣይ ክፍል ከዚህ በተለየ ርእስ መቀጠል ስለፈለግሁ ይህንን ክፍል እዚህ ላይ ልፈጽመውና ወደ ሀገራችን ስለገባው የቅብአት እምነት ምንፍቅና አመጣጥ ጥንተ ነገሩን አንድ ብለን በአዲስ ክፍል እንመረምራለን!!!
********************************************************************************
ፈጸምኩ
ስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

No comments:

Post a Comment