Sunday, March 12, 2017

ዓለም አቀፍ የቤተክርስቲያን ጉባኤያት---ክፍል ፪ (አርዮስ ማነው?)



© መልካሙ በየነ

መጋቢት 3/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT, LIKE ያድርጉ፡-
=============================================
ርዮስ የተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ ደቀ መዝሙር ነው፡፡ ተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስበመንበረ ማርቆስ 17ኛ ሊቃነ ጳጳሳት የነበረ ሲሆን ታሪካቸውና ግብራቸው የሚጠቀሱ አኪላስ፣እለእስክንድሮስ እና አርዮስ የሚባሉ ደቀመዛሙርት ነበሩት፡፡ ለዚህ ጉባኤ መጠራት ምክንያት የሆነው አርዮስ የሊብያ ቄስ እንደነበር ድርሳናት ያሳያሉ፡፡ ይህ አርዮስ የወልድን የባሕርይ አምላክነት ይጠራጠር ነበር፡፡ አንድ ቀን ከቤተ መዛግብት ገብቶ መጻሕፍትን ሲመለከት ሰይጣን ከሰሎሞን መጻሕፍት ከአንዱ ከመጽሐፈ ምሳሌ ምእራፍ 8 ቁጥር 22 ላይ ወሰደው፡፡ በዚህ የመጽሐፍ ክፍልም “ትቤ ጥበብ ፈጠረኒ አብ ከመ እኩን መቅድመ ኩሉ ተግባሩ፤ ጥበብ እግዚአብሔር ፈጠረኝ ለፍጥረቱም ተቀዳሚ አደረገኝ” ከሚለው ቃል ሰይጣን መርቶ አደረሰው፡፡ ከዚያም ለጥርጥሩ ማስረጃ በማግኘቱ ኑፋቄውን በማስረጃ አስደግፎ ክህደቱን በግልጽ ጀመረ፡፡ ይህንን “ፈጠረኝ” የሚለውን ቃል ለራሱ በመተርጎም ጥበብ የተባለው ወልድ ፍጡር በመሆኑ ነው “ጥበብ እግዚአብሔር ፈጠረኝ” ብሎ ጠቢቡ ሰሎሞን የተናገረው በማለት ክርክር ጀመረ፡፡ ይህ የኑፋቄ ትምህርቱ ከመምህሩ ከተፍጻሜተ ሰማዕት ከቅዱስ ጴጥሮስ ዘንድ ስለደረሰ መምህሩ አርዮስን በመጥራት “ይህን እኔ ያላስተማርኩህን መጻሕፍት ያልተረጎሙልህን እንግዳ ትምህርት ከወዴት አገኘኸው? ከዚህ በኋላ ይህንን እንግዳ ትምህርት አትናገር በልብህም አታስብ” በማለት መከረው ገሰጸው፡፡ አርዮስም በመምህሩ ፊት እሽ ብሎ ከወጣ በኋላ ይህን የኑፋቄ ትምህርቱን ማስተማር ጀመረ፡፡ ይህንን የአርዮስን አልመለስም ባይነት የተመለከተው ሊቀጳጳሳቱ ጴጥሮስ ከሹመቱ ሽሮ ከማዕርጉ አዋርዶ ሰደደው፡፡ በዚህ ዘመን የነበረው ጨካኙ ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ ክርስቲያኖችን ለመጨረስ በሰይፍ እያስመታ ይገድላቸው ነበር፡፡ ሆኖም ግን የክርስቲያኖች ቁጥር እየጨመረ እንጅ እየቀነሰ አልሄድለት ሲል ንጉሡ ለምን እንዲህ ይሆናል? ብሎ ይጠይቅ ነበር፡፡ በእምነት ጽኑአን የሆኑ አባቶች ዲዮቅልጥያኖስ በሰማዕትነት ከሚገድላቸው የበለጡ ክርስቲያኖችን ያሳምኑ ያጠምቁ ነበርና ለንጉሡ ያልተፈታ እንቆቅልሽ ሆኖበት ነበር፡፡ ከዚያም ንጉሥ ሆይ ሽህ ዓመት ንገሥ እያሉ ከእግሩ ሥር የሚደፉ ጸረ ክርስቲያኖች ከንጉሡ ዘንድ ይህንን ነገር ሲሰሙ አንተ ከምትገድላቸው እጥፍ እና ከዚያ በላይ የሚሆኑትን በቀን የሚሳምን ሊቀጳጳሳት አላቸው በማለት መምህር ጴጥሮስን ጠቆሙለት፡፡ በዚህም የተነሣ ጸረ ክርስቲያን የነበረው ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስሊቀጳጳሳት ጴጥሮስን ይገድሉት ዘንድ ጋላት የሚባሉ ጭፍሮችን ላከበት፡፡ አርዮስም ይህንን ከንጉሡ የወጣውን የሊቀጳጳሳቱን የግድያ ትእዛዝ ሲሰማ አኪላስና እለእስክንድሮስ ከመምህሩ ከጴጥሮስ ጋር እንዲያስታርቁት ከስህተቴ ተመልሻለሁና አስታርቁኝ ብሎ ላካቸው፡፡ እነዚህ ደቀመዛሙርትም ከመምህራቸው ዘንድ በመሄድ አርዮስ ከክህደቱ ተመልሷልና ውግዘትህን አንሳለት ወደ ማዕርጉም መልሰው በማለት ጠየቁት፡፡ መምህሩ ጴጥሮስም ከተመለሰማ ምን አግዶኝ ከውግዘቱም እፈታዋለሁ ያንንም የማደርገው ዛሬ አይደለም ብሎ ቀጠሮ ሰጥቶ አሰናበታቸው፡፡ በዚህን ሌሊት ጴጥሮስ ራዕይ ተገለጠለትና ጌታ የተቀደደ ልብስ ለብሶ በአምሳለ ሕጻን ሆኖ ራሱን ይዞ ሲያዝን ሲተክዝ ተመለከተው፡፡ ጴጥሮስም ጌታ መሆኑን አውቆ ጌታየ ሆይ ልብስህን ማን ቀደደው? ብሎ ይጠይቃል ጌታም የአንተ ደቀመዝሙር የሆነው አርዮስ ልብሴን ቀደደው ከባሕርይ አባቴ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቴ ከመንፈስ ቅዱስ ለይቶ ፍጡር ብሎኛልና፡፡ አንተም ከግዘቱ እንዳትፈታው ከዚህ ተጠበቅ እርሱ ከልቡ የማይመለስ መናፍቅ ነውና ብሎ አስጠነቀቀው፡፡ ደቀመዛሙርቱ በቀጠሯቸው አርዮስን ይዘውት መጡ፡፡ ጴጥሮስም በራዕይ ሁሉ ነገር ተገልጦለታልና የአርዮስ  አንዱ እግሩ ከቤት ውስጥ አንድ እግሩ ከውጭ እንዳለ “ውጉዝ አርዮስ በሰማይ ወበምድር፤ አርዮስ በሰማይና በምድር የተወገዘ ነው” በማለት ግዘቱን ጨመረበት፡፡ እነአኪላስና እነ እለእስክንድሮስ ፈዘው ደንግዘው ደንግጠው ቆመው ቀሩ አርዮስ ግን ወደኋላው ተመልሶ ጠፍቷል፡፡ ጴጥሮስም ልጆቸ አትደንግጡ የጌታየን ፈቃድ መተላለፍ አልችልምና እኔ የዕረፍት ጊዜየ ደርሷል፡፡ ከእኔ ቀጥሎ አኪላስ በመንበሬ ይተካል እርሱም ውዳሴ ከንቱ ጠልፎ ባለንጀርነት ፍቅርም አገብሮት ከሹመቱ ይመልሰዋል እርሱም አይጠቀምም ይቀሰፋል እንጅ፡፡ ከዚያም እለእስክንድሮስ በመንበሩ ይሾማል በእርሱ ዘመን ዐቢይ ጉባኤ ይደረጋል የአርዮስ ኃፍረትም በዐደባባይ ይገለጣል በማለት ራእዩን ነገራቸው፡፡ እነርሱም ይህን ድንቅ ነገር ሰምተው ተመልሰዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ጋላት የሚባሉ ጭፍሮች መጥተው ጴጥሮስን ገድለውታል፡፡ ከዚህ በኋላም አርዮስ የምንፍቅና ጦርነቱን በአዲስ መልኩ ቀጥሏል፡፡ ከተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ ሞት በኋላ መንበር ያለሹም አያድርምና አኪላስ በመንበሩ ተተካ፡፡አርዮስም ከውግዘቴ ይፈታኛል ብሎ ስላሰበ ዛሬ ገና የተማረ ግብረ ገብ ጳጳስ ተሾመ እያለ ከንቱ ውዳሴውን በልዩ ልዩ መንገዶች በመጠቀም መርዙን መርጨት ጀመረ፡፡ አኪላስም በከንቱ ውዳሴ ተጠልፎ ባልንጀርነት እና ፍቅር አገብሮት አርዮስን ከግዘቱ ፈትቶ ከሹመቱ መልሶታል፡፡ በአንድ ቤተክርስቲያንም የክህነት ሃላፊነት ተሰጥቶት ቅዱሳት መጻሕፍትን  እንዲያስተምር ሾሞታል፡፡ ሆኖም ግን አኪላስ ብዙ ዘመናትን በመንበሩ መቆየት አልቻለም ነበርና ከአንድ ዓመት በኋላ እለእስክንድሮስ በመንበሩ ተሾሞበታል፡፡አርዮስ ፓትርያርክነቱን ይመኝ ስለነበር ሹመቱ ለእርሱ እንዳልሆነ ሲረዳ ጊዜያዊ ክብር እና ቅንዓት ውስጡን አቃጠለው፡፡ በዚህም የተነሣ አርዮስ እለእስክንድሮስን የሚጣላበትን ምክንያ ይፈልግ ነበር፡፡ ሆኖም እለእስክንድሮስ ሕይወቱ የተቀደሰ ነበርና አርዮስ የሚጣላበትን ምክንያት ስላጣ የእለእስክንድሮስን ትምህርት በድፍረት በመቃወም ሰይጣናዊ ተልእኮውን እንደገና ጀምሮታል፡፡ እለእስክንድሮስ ግን ትክክለኛውን ሐዋርያት ያስተማሩትን ትምህርት ወልድ ከባሕርይ አባቱ ከአብና ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እኩል እንደሆነ ያስተምር ጀመረ፡፡ አርዮስ ደግሞ በሰይጣናዊው ጎራ ተሰልፎ ወልድ የባሕርይ አምላክ አይደለም እርሱ ፍጡር ነው እንደ ቅዱሳን ሁሉ በገድል በትሩፋት የባሕርይ አምላክ ያደረገው እግዚአብሔር አብ ነው እያለ እንደ አዝማሪ በየመንደሩና እና በየሰፈሩ እየቀላወጠ መርዙን ይረጭ ጀመረ፡፡ ይህንን የተመለከተው እለእስክንድሮስ ነገሩን በጥንቃቄ በምክር እና በተግሳጽ አርዮስ ስህተቱን በመረዳት ከመጥፎ ግብሩ እንዲመለስ ብዙ ጥረት አደረገ፡፡ ይሁን እንጅ አርዮስ በእልህ ይህንን ኑፋቄውን ሥራየ ብሎ ስለተያያዘው እና የኑፋቄው ተከታዮችን ማፍራት ስለጀመረእለእስክንድሮስ እና በእስክንድርያ የሚገኙ ካህናት ፈርመው ከስህተቱ እንዲመለስ ደብዳቤ ሰጡት፡፡ ይህ ቢሆንም አርዮስ ከክህደት ትምህርቱ ሊመለስ አልቻለም፡፡ በዚህ ውጤት ማምጣት ስላልተቻለ በግብጽ እና በሊብያ ያሉ ጳጳሳት በእስክንድርያ ተሰብስበው በጉባኤ የአርዮስን ስህተት በሚገባ መርምረው አርዮስንና የእርሱን ተከታዮች አውግዘዋቸዋል፡፡ሆኖም አርዮስ ከያዘው ኑፋቄ ሊገታው አልቻለም፡፡ እንዲያውም ኑፋቄውን ህዝቡ በቀላሉ እንዲረዳው አጫጭር ግጥሞችን እና መዝሙራትን በማዘጋጀት ለወጣ ለወረደው ላለፈ ላገደመው ሁሉ ያሰራጭ ጀመር፡፡ በዚህም የተነሣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት በየቤቱና በየጓዳው መነጋገሪያ ጉዳይ ሆነ፡፡ አርዮስ ግን አሁንም ተከታዮቹን በማፍራት በኩል ሰፊ እንቅስቃሴውን ተያይዞታል፡፡ ከዚያም “ፓትርያርክ እለእስክንድሮስ እውነተኛውን ትምህርት ለምን አስተማርክ በማለት በግፍ አወገዘኝ” እያለ እርሱን ለሚመስሉ ሁሉ መልእክት ይልክ ነበር፡፡ በዚህም መልእክቱ በርካታ ግብረ አበሮችን ለማፍራት በቅቷል፡፡ በተለይ የኒቆምድያው ጳጳስ አውሳብዮስ፣ የቂሣርያው ጳጳስ አውሳብዮስ፣ የጢሮሱ ጳጳስጳውሊኖስ የአርዮስን ትምህርት የሚደግፉ በመሆናቸው አርዮስ እንዲበረታ ይመክሩት ነበር፡፡ አርዮስም አይዞህ ባይ ከጎኑ የሚቆምለት ሰው በማግኘቱ እጅግ ደስ ስላለው ኑፋቄውን አጠናክሮ ቀጠለ፡፡ሙሉ ኃይሉን ለጥፋት የተጠቀመው የኒቆምድያው ጳጳስ አውሳብዮስ ለአርዮሳውያን መስፋፋት ትልቅ ድርሻ ነበረው፡፡እንዲያውም በንጉሥ ቆሥጠንጢኖስ ቤተሰቦች ዘንድ ቀረቤታ ስለነበረውና የቤተ መንግሥት ጳጳስ ስለነበረ ብዙ አርዮሳውያን ጳጳሳትን በመጥራት በኒቆምድያ ጉባኤ በማካሄድ የአርዮስን ትክክለኛነት ዐውጇል፡፡ የዚህን ውሳኔም ለእለእስክንድሮስ ሳይቀር ልኮለታል፡፡ በሌላው ጎን ደግሞ ፓትርያርክ እለእስክንድሮስ የአርዮስን ትምህርት አውግዞ ከቤተክርስቲያን አንድነት በመለየት አርዮስን እና እና መሰል ግብረ አበሮቹን እንዳይቀበሏቸው እና በእንዲህ ያለው አሳዛኝ የቤተክርስቲያን ጉዳይም ሁሉም እንዲያዝኑበት የሚያሳስብ ደብዳቤን ለየአብያተ ክርስቲያናቱ ላከ፡፡
ይቆየን፡፡
ይቀጥላል፡፡

No comments:

Post a Comment