Wednesday, May 10, 2017

“ጳጳስ እያስተማረ አሁን እናንተ በስመ አብን ሳትሉ እምነት እናስተምር ይባላል”-- አቡነ ማርቆስ


 © መልካሙ በየነ
ግንቦት 2/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

ብጹእ አቡነ ማርቆስ የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ የበላይ ኃላፊ እንዲሁም የቤተክርስቲያናችን የቴሌቪዥን ሥርጭት ሰብሳቢ ናቸው፡፡ እነዚህን ቁልፍ ቁልፍ ቦታዎች ያገኙት ደግሞ በተሐድሶ መናፍቃኑ ከፍተኛ እገዛ እና ጥረት እንደሆነ የአደባባይ እውነት ነው፡፡ ሚያዝያ 30/2009 ዓ.ም የሐዋርያው የቅዱስ ማርቆስ የእረፍት መታሰቢያ በዓል ይከበራል፡፡ በእድሳት ምክንያት የዓመታት አገልግሎት ተቋርጦበት የነበረው መንበረ ጵጵስናቸው ደብረ ፀሐይ መልእልተ አድባር ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ምረቃ በ ሚያዝያ 28/2009 ዓ.ም ተፈጸመ፡፡ እርሳቸው ግን ህዝቡን በስፋት የሚያገኙበት ነውና ጉባዔውን ተጠቅመውበት አልፈዋል፡፡ በሚያዝያ 30/2009 ዓ.ም በሐዋርያው የእረፍት በዓል ላይ ካስተላለፉት መልእክት የተወሰነውን በቪዲዮ አስደግፌ እጽፍላችኋለሁ፡፡ ቪዲዮውን ግን ሁላችሁ ተመልከቱት፡፡
አቡኑ ብዙ ነገር ሲዝቱ ውለዋል ብዙ ነገር ሲያስፈራሩ ውለዋል እኔ ግን ከመኸል ቀንጭቤ የወሰድኳትን ልጻፍላችሁ፡፡
“ኦርቶዶክስ ነን እያሉ መናፍቃን እዚያ ገብተዋል” አሉ፡፡ ብጹእነታቸው ይህን የተናገሩት ስለ ተሐድሶ መናፍቃን አይደለም፡፡ ስለፕሮቴስታንቶችም አይደለም፡፡ ስለቅባት እና ፀጋዎችም አይደለም፡፡ ስለግቢ ጉባዔ ተማሪዎች እና ስለ ማኅበረ ቅዱሳን ነው፡፡ እርሳቸው መናፍቃን ያሏቸው ተሐድሶዎችን ቢሆን ኖሮማ በሥራቸው ደመወዝ እየከፈሉ ባላስቀመጧቸውም ነበር፡፡ ምሥራቅ ጎጃም ውስጥ በተሐድሶ መናፍቃን ሥልጠና ወስደው ቤተክርስቲያናችንን ለማፈራረስ የተነሡ በርካታ መናፍቃንን ደመወዝ እየከፈሉ በስራቸው ሸጉጠው አስቀምጠዋቸዋል፡፡
ቀጠሉና “እየው ተጠንቀቁ መናፍቃን ማለት እንዴ እኒህ ጎጃም ምን እንደው ታሪክ የሌለበት ጎጃም ሲያጠምቅ አዲስ አበባን ማን ያስተምረው እኮ አዲስ አበባ የየት አገር ሊቃውንት ነው ያሉ፡፡ በኢትዮጵያ የየት አገር እና በጣም በእውነት ሞራላቸው የወደቁ ልጆች አሉ” አሉን፡፡ ጎጃምንማ ቢያውቁት የእነ አቡነ ቴዎፍሎስ፤ የእነመልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ፤ የእነ አለቃ አያሌው ታምሩ አገር ነበር፡፡ ጊዜው ጅል ሆነና ስንት ሊቃውንትን እንዳላፈራ ስንት ቅዱሳንን እንዳላሳየ እርስዎን በመድረክ ላይ ተመለከትንበት እንጅ፡፡ ወንጌል በሚነገርበት መድረክ ላይ ቆመው ልጆችዎ ነን ብለው ከትቢያ ላይ ተቀምጠው የሚማሩትን ልጆች መናፍቃን ብለው ዘለፏቸው፡፡ “ሞራላቸው የወደቁ” ብለው የዘለፏቸው የግቢ ጉባዔ ተማሪዎች እና የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ነገ ታሪክ እንደሚሠሩ የሚያጡት አይመስለኝም፡፡ “በሰፈሩት ቁና…” እንዳይሆን ነገሩ በጊዜው ይቅርታ ማለት በተገባዎት ነበር፡፡
አሁንም ቀጠሉ “ካስፈለገም በጊዜው መዝግበናቸዋል፡፡ አዎ በእውነት ከዚያ ፊት ግን ይጎዳሉ ነው ይጎዳሉ፡፡ እንዴ ጎጃም ምን ሆኖ ነው እንዲህ እንዲህ ሞራሉን እንዲህ የማይከተበው አገር ተጠመቅ፡፡ ልጀ ይማራል ብሎ ዩኒቨርሲቲ ሰዶ… ያ ደሃ እኮ ልጁ እንዲማር ነው ጎጃም ሃይማኖት ብሎ ዩኒቨርሲቲ ይልካል እንዴ ልጁን አይልክም፡፡ አዎ ጥሩ ትምህርት መሐንዲስ ሆኖ ኑሮው እንዲያልፍለት ነው” አሉ፡፡ በጣም የሚያሳዝነው “ያለበት አብላላበት” የሚባለው ነገር ነው፡፡ ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በፌዴራል ደረጃ የሚታወቅ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሚማርበት ተቋም እንጅ የጎጃም ልጆች ብቻ የሚማሩበት ተቋም አይደለም፡፡ እንደ ዩኒቨርሲቲነቱ ደግሞ በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ በተሰጠው መሠረት ማኅበረ ቅዱሳን ግቢ ጉባዔን ያቋቁማል፡፡ በዚህ መሠረትም ትምህርተ ሃይማኖትን እያስተማረ ወደ ተዋሕዶ እምነታችን የሚመለሱትን ሁሉ እንዲጠመቁ ለካህናት ይመራል፡፡ ልብ በሉ! ለካህናት ይመራል ማለት ከሚያጠምቁ ካህናት ጋር አገናኝቶ የልጅነት ጥምቀትን እንዲጠመቁ ያደርጋል ማለት ነው፡፡ “ያመነ የተጠመቀ ይድናል” ይላል ወንጌል፡፡ አባታችን ግን ለምን ተጠመቁ ትላላችሁ እያሉ ሲያስተምሩ ምን ለማለት ፈልገው ይመስላቸኋል፡፡ አባታችን “ጎጃምን ያህል የሊቃውንት አገር” እያሉ የሚናገሩ ጎጃም አትጠመቁ ብሎ ስለሚያስተምር ይሆን፡፡ አይመስለኝም ዩኒቨርሲቲውንም በጎጃም ተማሪዎች ብቻ የወከሉት እና ጎጃሞች ተጠመቁ ተባሉ እያሉን ያለው የ“ቅብዓት” እምነትን የሚከተሉ ተማሪዎችን ወክለው ነው፡፡ እርሳቸው ለቅብዓት እምነት ዘብ መቆማቸው የተረጋገጠ ሀቅ ነው፡፡ ለዚህም “ወልደ አብ” እና “ሚሥጢረ ሃይማኖት ወትንቢተ ዘዝክሪ ወጳውሊ” የተባሉ መጻሕፍት በዘመነ ጵጵስናቸው መታተማቸው አማላካች ነው፡፡ እነዚህ በቅብዓት እምነት የሚኖሩ የጎጃም ተማሪዎች (ቅብዓት ከጎጃም ውጭ ስለማይታወቅ ማለቴ ነው) መሠረታዊ የሆነውን የተዋሕዶ እምነት ከተማሩ እና ከተቀበሉ በኋላ እንደማንኛውም ሁሉ የልጅነት ጥምቀትን ይጠመቃሉ፡፡ ይህ እኮ ማንም የሚፈርደው ለማንም የታወቀ እውነት ነው፡፡ ተጠመቅ የተባለ ማነው ብለን እንጠይቃቸው እስኪ፡፡ ጎጃም ትልቅ አገር ቢባል እነመልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬን እነ አለቃ አያሌው ታምሩን እነ አቡነ ቴዎፍሎስን እነ በላይ ዘለቀን እነ ሐዲስ አለማየሁን የመሣሠሉትን የእውቀት እና የአስተሳሰብ የእምነት እና የነጻነት ጀግኖች ስላስገኘ እንጅ በገዳማት ውስጥ ተደብቀው ምንፍቅናቸውን ስለጻፉ መሰልዎት እንዴ፡፡ “ስማቸውን መዝግበናቸዋል… ግን ይጎዳሉ” ብለው ያሏቸው የተዋሕዶ ልጆች ከእርስዎ በሚሰነዘር ቀስት እንደማይጎዱ እተማመናለሁ፡፡ ምክንያቱም ከእርስዎ ጋር ካለው ይልቅ ከእነርሱ ጋር ያለው ይበልጣልና፡፡ አንድ አባት በመድረክ ላይ ወጥቶ እንዲህ ያለ የረከሰ ንግግር ማድረግን ግን አልጠብቅምና አፈርሁብዎት፡፡ ዩኒቨርሲቲ የሚሠጠው ትምህርት ምህንድስና ብቻ መሰልዎት እንዴ፡፡ ዩኒቨርሲቲ የገባው ሁሉ መሐንዲስ ሆኖ የሚወጣ መስሎዎት የማይገባ ንግግርን ተናገሩ፡፡ ለነገሩ … ይተውት በቃ፡፡ እኔም ተውኩት፡፡
ቀጥለው “በዩኒቨርሲቲም ያላችሁ መምህራን እንዴ ዩኒቨርሲቲውን ዩኒቨርሲቲ አድርጉት እንጅ፡፡ ዩኒቨርሲቲ ማለት ገበያ ነው፡፡… ስእለት መቀበያ እየተባለ በዶርም ተለጥፎ ስእለት… እዶርም ስእለት ማነው ታቦቱ እ እኮ ግዛቸው ነው ይበልጣል… እዶርም ስእለት መረጃ ይዘናል” አሉ፡፡ በዚህ ንግግርዎ እንዴት እንዳፈርኩብዎ ቢያውቁልኝ ኖሮ እንዴት ደስ ባለኝ ነበር፡፡ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የትኛው ሃይማኖት ነው እየተራመደ ያለው፡፡ አባታችን! ተማሪዎች እኮ ቁርሳቸውን ትተው ምሳቸውን ከፍለው ዳቦ ሰብስበው ያንን ሸጠው ያገኙት ገንዘብ ነው፡፡ እርር ክስል ቢሉ እርስዎ ኪስ አምስት ሳንቲም ጠብ የማትል የግል ገንዘባቸው ናት፡፡ ዓይንዎን ከዚች ሳንቲም ያንሡ! እርስዎ እዛው ለመባረኪያ እና ለእድሳት ፈቃድ እያሉ በ10 ሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ ይሰብስቡ እንጅ ከግቢ ጉባዔውስ አምስት አያገኙም፡፡ አረ እንዲያውም አንድ መረጃ ወጥቷል እውነት መሆኑን እስኪ እራስዎ ይመስክሩልን፡፡ የገዳመ አስቄጥስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም ደብረ ማርቆስ የሚገኘውን ማለቴ ነው ግንቦት 12/2009 ዓ.ም ይህን አዲስ ቤተክርስቲያን ለመባረክ 40 ሺህ ብር ጠይቀዋል ብለው ብዙዎች መረጃውን አሰራጭተዋል፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ የግዛቸው እና የይበልጣልን ስም አንስተው ታቦት ናቸው ወይ ማለትዎ ነው፡፡ ታቦትማ የሆኑ እርስዎ ነበሩ አላወቁበትም እንጅ፡፡ ግዛቸው ማለት የማኅበረ ቅዱሳን የደብረ ማርቆስ ማእከል ጸሐፊ እንደሆነ ይበልጣልም ሰብሳቢ እንደሆነ ነበር የምናውቅ እርስዎ ግን ታቦት አደረጋችኋቸው እና አረፉ፡፡ እስኪ የትኛው ዶርም ነው ስእለት የሚሰበሰብበት ዛሬማ እውነትም አፍረዋል ምን ማፈር ብቻ እርር ብለዋል እንጅ፡፡ እናስታውሳለን ሁሉንም እናውቃለን፡፡ ግቢ ጉባዔ ተማሪዎች ገንዘባቸውን ለእኛ ይስጡን ብላችሁ ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ድረስ መጥታችሁ የተቋሙን ፕሬዝዳንት ሳይቀር እንዳናገራችሁ መረጃው አለን፡፡ ፕሬዝዳንቱን ግን በጣም እናደንቀዋለን “ተማሪዎች ቁርሳቸውን ትተው ዳቧቸውን ሸጠው የሰበሰቡትን ገንዘብ የትስ ቢያደርሱት ምን አገባችሁ” ብሎ አሳፍሮ ሰዷችኋል፡፡ ፍንድት ብትሏት ብትቋምጡ የግቢ ጉባዔውን አምስት ሳንቲም አታገኟትም፡፡ ዩኒቨርሲቲ ምን እንደሆነ ምን እንደሚካሄድበት ከእርስዎ ይልቅ እየሰደቡት ያለው ተማሪ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡
በመጨረሻም “ጳጳስ እያስተማረ አሁን እናንተ በስመ አብን ሳትሉ እምነት እናስተምር ይባላል” አሉ፡፡ አባቴ! ጵጵስና እውቀት አይደለም፤ ጵጵስና መዓርግ ነው፡፡ ጳጳስ ሁሉ አዋቂ አማኝ ነው ማለት አይቻልም ያውም ዘንድሮ አይይይ… አይሆንም፡፡ አቡናርዮስ የሎዶቅያ ጳጳስ ነበረ ነገር ግን “አብ እና ወልድ መንፈስ ቅዱስም አንድ ገጽ ናቸው” በማለት አንድ ገጽ ብሎ አስተማረ፡፡ ንስጥሮስ የቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ ነበረ ነገር ግን “ወልድ ከነቢያት እንደ አንዱ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ በዮርዳኖስ ባደረበት ጊዜ በጸጋ አምላክ ሆነ” በማለት ካደ፡፡ ፎጢኖስ የበሚርና ጳጳስ ነበረ ነገር ግን “የወልድ ሕልውና ከማርያም ከተወለደ ወዲህ ነው” በማለት ካደ፡፡ ሳዊሮስ የሕንድ ቴዎዶስዮስ ደግሞ የእስክንድርያ ጳጳስ ነበሩ ነገር ግን “የእግዚአብሔር ልጅ ያለፈቃዱ በግድ ሞተ” ብለው ካዱ፡፡ ልዮን የሮሜ ሊቀ ጳጳስ ነበረ ነገር ግን “ሥጋ ከመለኮት ያንሣል” በማለት ካደ፡፡ የኬልቄዶን ማኅበርተኞች ከ500 እስከ 600 የሚደርሱ ጳጳሳት ነበሩ ነገር ግን “መለኮት እና ሥጋ በሁለት መንገድ በሁለት ሥርዓት ናቸው” ብለው ካዱ፡፡ ስለዚህ ጳጳስ ስለሆኑ ብቻ አዋቂ ነዎት እምነት አለዎት ብለን አንናገርም፡፡ ስሙን ግን ለግል ዓላማዎ እየተጠቀሙበት እና እየነገዱበት እንደሆነ ማሳያ ነው፡፡ እርስዎም ስልጣነ ጵጵስናውን ስለያዙ አባታችን እያልን ብናከብርዎ ደንቆሮ መሆናችን አይደለም፡፡ የቀደሙ አባቶቻችንን በተመለከትንበት ዓይናችን ስለተመለከትንዎ ብቻ ነው፡፡ የእውቀት መለኪያው ስልጣን መጨበጥ ብቻ ከሆነ ስንት የክብር ዶክትሬት ያላቸው ሰዎች አሉ መሰልዎት፡፡ ጵጵስናም የክብር እየተባለ መሰጠት ተጀመረ አይሉኝም መቸም፡፡ እውነቴን ነው አሁንስ! የክብር ጵጵስና ነው የእርስዎስ፡፡ ታዲያ ወንጌል ጠፋብዎት እንዴ ዩኒቨርሲቲ ዶርም የገቡ፡፡ የምን ጓዳ ለጓዳ መልከስከስ ነው ወጣ ብለው ወንጌልን ይስበኩ እንጅ፡፡ ቆይ በእርስዎ ዘመነ ጵጵስና የቱን መናፍቅ ነው አስተምረው የመለሱ፡፡ እንዲህ በቅዱሱ መድረክ ላይ ቆመው ሲሰድቡ ሲዘልፉ እየዋሉ በስመ አብን ከማን እንማር፡፡ ተያይዘን ደነቆርን እንጅ፡፡
ወገን አስተውል ብጹእ አቡነ ማርቆስ የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ የበላይ ኃላፊ እንዲሁም የቤተክርስቲያናችን የቴሌቪዥን ሥርጭት ሰብሳቢ ናቸው ብለናል ታዲያ እንደዚህ ዓይነት ቁልፍ የኃላፊነት ቦታዎችን ከያዘ አባት ይህን ንግግር ትጠብቃላችሁ፡፡ ተወያዩበት፡፡ ተጨማሪ የቪዲዮም ሆነ የድምጽ መረጃ ያላችሁ ሁሉ በውስጥ መስመር ላኩልኝ፡፡

No comments:

Post a Comment