እምነት ማለት ማመን መታመን ማለት ነው:: ፈጣሪ መኖሩን ዓለምን ያስገኘ አንድ አምላክ መኖሩን ሳናይ ሳንዳስስ ሳንጨብጥ ያለጥርጥር ይደረግልኛል
ይሆንልኛል ማለት ማመን ነው:: ይህን ማመናችንን የምናረጋግጠው
ደግሞ በመታመን ብቻ ነው:: መታመን ማለት እምነትን በሥራ
መግለጥ ማለት ነው:: መጾም፣ መጸለይ፣ መስገድ፣ መመጽወት መታመንን ይገልጣሉ:: አንድ ሰው ፈጣሪ ያዘዘውን ካልሠራ ታመነ አይባልም:: ፈጣሪ ያስተማረህን እንድትሆን ያዘዘህን ሆነህ መገኘት
ካልቻልህ ታማኝ አይደለህም ማለት ነው:: እምነት መታመን ከሌለበት ከንቱ
ነው:: ዝም ብሎ ጠዋት ማታ ጌታዬ ጌታዬ ማለት ብቻውን አያድንም:: አንድ ዘበኛ ቤት እንዲጠብቅ ተቀጥሮ ሳለ የቀጣሪውን ንብረት ከሰረቀ ታማኝ እንደማይባልና ከሥራ እንደሚባረር ሁሉ
እምነታችንም መታመን ከሌለበት ከእምነት ለመውጣት እንገደዳለን:: እምነት በአፍህ ብቻ አምናለሁ እያልህ የምትቀልድበትና የምታሾፍበት አይደለም የምትታመንበት ነው እንጅ:: ለማመንህ መገለጫው መታመንህ ነው:: አምንሃለሁ ለምትለው ፈጣሪ ልትገዛ ትእዛዙን ልትጠብቅ
ያስፈልጋል:: አትብላ ሲልህ አለመብላት፤አትስረቅ ሲልህ አለመስረቅ፤አትዋሽ
ሲልህ አለመዋሸት፤አመስግነኝ ሲልህ ማመስገን፤ጹም ሲልህ መጾም፤ጸልይ ሲልህ መጸለይ ወዘተ አለብህ የመገዛትህ ወይም የመታመንህ
መገለጫ ነውና:: ጾም፣ጸሎት፣ስግደት፣ ምጽዋት የሌለበት እምነት ከንቱ ነው:: ለምታምነው አምላክ የመገዛትህን መገለጫ ማቅረብ አለብህ:: ይህ የመታመንህ መገለጫ ደግሞ በዘፈቀደ የሚደረግ ሳይሆን
ሥርዓት ሊኖረው ግድ ይላል:: ከዚህ ተነሥተን እምነትን
ለሁለት እንከፍለዋለን:-
1)
ሥርዓት ያለው እምነትና
2) ሥርዓት አልባ እምነት
በሌላ አነጋገር:-
1. እውነተኛና
2. ሐሠተኛ እምነት ማለት ነው::
በሌላ አነጋገር:-
1. እውነተኛና
2. ሐሠተኛ እምነት ማለት ነው::
v ሥርዓት
ሥርዓት ማለት ደንብ አሰራር
ማለት ነው:: ለማንኛውም
ሥራ ሥርዓት ሊኖረው ያስፈልጋል:: እምነት ውስጥ ያለው መታመን በዘፈቀደ ሳይሆን በሥርዓት መሆን አለበት:: አንድ
እምነት ሥርዓት ካለው ብቻ ነው እምነት የሚባለው:: አንድ እምነት ውስጥም አንድ አይነት ሥርዓት ብቻ ነው የሚፈቀደው:: ለእምነት
እውነተኛነት የመታመን ሥርዓት ነው:: ጾም ሥርዓት አለው ጸሎትም ሥርዓት አለው ሌሎችም እንዲሁ ሥርዓት አላቸው:: ይህ
ሥርዓት ሕገ ወጥ ከመሆን ይጠብቀናል:: ለምሳሌ ጸሎት ሥርዓት ከሌለው አንዱ ዓይኑን ወደ ሰማይ ሲያቀና ሌላው ወደ
ምድር ያቀረቅራል:: አንዱ “አባታችን
ሆይ” ሲል ሌላው “ሃሌ
ሉያ” እያለ ይንፈራፈራል:: አንዱ የሚለው ሌላው ከሚለው የተለየ ይሆናል:: የተለያየ
ሥርዓት በአንድ ቤት ውስጥ ሊሆን አይችልም:: ሁሉን አቀፍ የሆነ ሁሉን የሚገዛ ሥርዓት የሌለው እምነት ውሸተኛ /ሥርዓት
አልባ/ እምነት ይባላል::
የዚህ ተቃራኒ የሆነ እምነት ደግሞ እውነተኛ ይባላል:: እምነት
የሚባለው እውነተኛ መሆን ሲችል ብቻ ነው:: አንድ መድኃኒት ማዳን የሚችለው የመድኃኒት አወሳሰድ ሥርዓት ካለው እና
በሥርዓቱ ከተፈጸመ ብቻ ነው:: እውነተኛ እምነት በሥርዓት የሚመራ
እምነት ነው:: ይኸውም መጽሐፍ ቅዱስን በሕይወት
የኖሩትን ቅዱሳን መምሰል እነርሱን መከተል በሠሩት ሥርዓት መመራት ነው:: አንዳንድ እምነቶች መጽሐፍ ቅዱስን አንግበው “ኢየሱስ አንድ ጊዜ አድኖኛል ከዚህ
በኋላ ኩነኔ የለብኝም” ብለው ራሳቸውን ያስታሉ:: ቤተክርስቲያን ነው በሚሉት ባዶ አዳራሽ ውስጥ የሚሠሩት የቀልድ ሥራ ከእምነት
የወጡ ለመሆናቸው ምስክር ነው:: እኛ የተዋሕዶ ልጆች ቤተክርስቲያናችን ቅድስት ናት ብለን እናምናለን:: ለዚህም ዘጸ 3÷5 ላይ ሙሴን “የቆምክባት ምድር የተቀደሰች ናትና
ጫማህን አውልቅ” ያለውን አብነት አድርገን ቤተክርስቲያን ስንገባ የእግር ጫማችንን
የልብ ስንፍናችንን ኃጢአት በደላችንን አውልቀን ነው:: ሴትና ወንድ የራሳቸው የሆነ መቆሚያ ቦታ አላቸው:: ሴት ራሷን ተከናንባ ትጸልያለች:: ይህ ሁሉ ሥርዓት ነው ልብወለድ ያይደለ
መጽሐፍ ቅዱስ ያስቀመጠው ሥርዓት ነው:: ለዚህ ሥርዓት የሚገዛ እምነት ትክክለኛ ነው:: በፕሮቴስታንት እምነት ውስጥ ይህ
ሁሉ ሥርዓት አይታይም ሴቶች ተሸፋፍነው መጸለይ ቀርቶ ኢትዮጵያዊ አለባበስ እንኳ የላቸውም:: ባታቸውንና ጡታቸውን ለማስመረቅ የተቀመጡ
ነው የሚመስሉት:: ቤተክርስቲያን በሚሉት ውስጥ ሲገቡም
ከነጫማቸው ነው:: ቤተክርስቲያናቸው የተቀደሰ አለመሆኑን
በዚህ እናውቃለን:: የተቀደሰ ቢሆንማ ጫማህን አውልቅ በሚለው በሙሴ በኩል ለእኛ በተሰጠው ትእዛዝ ይመሩ ነበር:: ሌሎች በርካታ የፕሮቴስታንት እምነትን
ከእምነት ውጭ የሚያደርጉት ነገሮች አሉ:: መዝሙር በሚሉት ውስጥ
የሚጠቀሙት መሳሪያ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም፡፡ ማንኛውም ዘፋኝ የሚጠቀምባቸው መሣሪያዎችን እነርሱም ይጠቀሙበታል፡፡ ስለዚህ መዝሙር
ሳይሆን ዘፈን ሊባል ይችላል ማለት ነው፡፡ እኛ ግን የዜማ መሣሪያዎች አሉን፡፡
የዜማ መሣሪያዎች
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የአገልግሎት መሣሪያዎች (ንዋያተ ቅድሳት) በርካታዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል ለዜማ የሚያገለግሉትን የማኅሌት መሣሪያዎች እንመልከት፡፡ እነዚህ መሣሪያዎችን በሐዲስ ኪዳን መጠቀም እንዳለብን የሚገልጽ አንድም ምዕራፍ የለም፡፡ ነገር ግን ብሉይ ኪዳንን መሠረት አድርገን እንገለገልባቸዋለን፡፡ ከእነዚህም መሣሪያዎች መካከል፡-
ከበሮ፣ በገና፣ ዋሽንት፣ ጸናጽል፣ መቋሚያ እና መሰንቆ ይጠቀሱበታል፡፡
የዜማ መሣሪያዎች
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የአገልግሎት መሣሪያዎች (ንዋያተ ቅድሳት) በርካታዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል ለዜማ የሚያገለግሉትን የማኅሌት መሣሪያዎች እንመልከት፡፡ እነዚህ መሣሪያዎችን በሐዲስ ኪዳን መጠቀም እንዳለብን የሚገልጽ አንድም ምዕራፍ የለም፡፡ ነገር ግን ብሉይ ኪዳንን መሠረት አድርገን እንገለገልባቸዋለን፡፡ ከእነዚህም መሣሪያዎች መካከል፡-
ከበሮ፣ በገና፣ ዋሽንት፣ ጸናጽል፣ መቋሚያ እና መሰንቆ ይጠቀሱበታል፡፡
ከበሮ፡- የጌታችን ምሳሌ ሲሆን ትርጉሙም፡- ሰፊው አፍ እግዚአብሔር አምላክ ምሉዕ በኩለሄ /በሁሉ የሚገኝ/ መሆኑን የሚያሳይ ሲሆን ጠባቡ አፍ ደግሞ ምሉዕ በኩለሄ የሆነው አምላክ ስለሰው ፍቅር በጠባብ ደረት በአጭር ቁመት መወሰኑን ይገልጣል፡፡ በከበሮው ላይ የሚታዩት ሁለቱ አፎች የተያያዙበት ጠፍር አይሁድ ጌታችንን በገረፉት ወቅት በሰውነቱ ላይ የወጣውን ሰንበር አጥንቱ መቆጠሩን ሥጋው ማለቁን ያስታውሳል፡፡ በአንገታችን አንግተን መያዛችን ጌታችንን በአንገቱ ገመድ አስገብተው ያንገላቱትን ያጠይቃል፡፡
መሠንቆ፡- የእመቤታችን ምሳሌ ነው፡፡ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም “መሰንቆሁ ለዳዊት” ይላታል፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ መሠንቆ ያልኳት ሰማዕታት የለበሷት ቀናተኛ ሃይማኖት ናት ይላታል፡፡ መሠንቆ ክሩ አንድ መሆኑ የአንዲት ሃይማኖት ምሳሌ፡፡ መሰንቆ ድምጽ የሚሰጠው በዕጣን ሲታሽ ነው፡፡ ዕጣኑ የክርስቶስ ድምጹ የምስጋናዋ ምሳሌ ነው፡፡ መከርከሪያው የኖኅ ቃል ኪዳንን ያጠይቃል፡፡ ቋሚና አግዳሚ ተዋቅረው የሚሠሩት መስቀል ነገረ መስቀሉን እንድናስታውስ ያደርገናል፡፡
በገና፡- ሁለት ቋሚዎች አሉት ምሳሌነታቸውም ለብሉይ ኪዳንና ለሐዲስ ኪዳን ነው፡፡ አሥር አውታሮች አሉት እነዚህም የአሠርቱ ትዕዛዛት ምሳሌዎች ናቸው፡፡ በአጠቃላይ በሁለቱ ኪዳናት /ማለትም በሐዲስና በብሉይ/ ፍቅረ ቢጽና ፍቅረ እግዚአብሔር አሥርቱ ትእዛዛት እንደሚፈጸሙ ጌታ ያስተማረውን ያጠይቃል፡፡
ዋሽንት፡- የወንጌል ምሳሌ ነው፡፡ አራቱ ቀዳዳዎች የአራቱ ወንጌላውያን ምሳሌዎች ናቸው፡፡ /አራቱ ወንጌላውያን የሚባሉት ቅዱስ ማቴዎስ፣ ቅዱስ ሉቃስ፣ ቅዱስ ማርቆስና ቅዱስ ዮሐንስ ናቸው፡፡/ ዋሽንት ደስ የሚያሰኝ ድምጽን አውጥቶ ኅሊናን እንደሚያነቃቃ ወንጌልም ወልደ እግዚአብሔር ተወለደ ዲያብሎስ ተሻረ የሚልን የምስራች ትናገራለችና፡፡
ጸናጽል፡- ሁለት ቋሚዎች ሁለት አግዳሚዎች አሉት፡፡ ሁለቱ ቋሚዎች የያዕቆብ መሰላል ምሰሶ፣ የብሉይና የሐዲስ ኪዳን ምሳሌ ሲሆን አግዳሚዎቹ ደግሞ የያዕቆብ መሰላል መውጫና መውረጃ፣ የፍቅረ እግዚአብሔርና የፍቅረ ቢጽ ምሳሌ፡፡ በአግዳሚዎቹ ላይ ያሉት ሻሻታዎች በያዕቆብ መሰላል ላይ ሲወጡና ሲወርዱ የነበሩት መላእክት ምሣሌ፣ 5 ቢሆኑ የአምስቱ አእማደ ምስጢራት፣ 7 ቢሆኑ የሰባቱ ምስጢራተ ቤተክርስቲያን ምሳሌ፡፡ ሁለቱን ቋሚዎች የሚያገናኘው ደጋን በያዕቆብ መሰላል እግዚአብሔርን ያየበት ዙፋን፣ የኖኅ ቀስተ ደመና፣ የቀራንዮ ተራራ ምሳሌ፡፡ ከደጋኑ ላይ ያለው መስቀል በዙፋኑ ላይ ያለው እግዚአብሔር፣ ቀራንዮ ላይ የተተከለው እውነተኛ መስቀል፣ የተሰቀለው የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ የጸናጽሉ መያዣ የሕገእግዚአብሔር የፍቅር ምሳሌ ነው፡፡
መቋሚያ፡- ነገረ መስቀሉን የምናስታውስበት ለጸሎትና ለማኅሌት የምንጠቀምበት መሣሪያ ነው፡፡ ጸሎትም የራሱ የሆነ ሥርዓት አለው፡፡ ጸሎት ማለት ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር ነው ይላሉ ሊቃውንቱ በፍትሐ ነገሥት ላይ እንደጻፉት፡፡ ሊቃውንቱ ከዚህም በበለጠ ሲያስረዱ ጸሎትን ለማድረግ መጀመሪያ ቀጥ ብሎ እግዚአብሔር ፊት መቆም ቀጥሎም ወገብን መታጠቅ፣ መስገድና ማስተብረክ ወይም ከጉልበት ዝቅ ማለት ስግደትን በሚያነሣ ቃል ሁሉ መስገድ ቀጥሎም በመስቀል ምልክት ማማተብ እና እጅን ዘርግቶ መጸለይ እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡ በጸሎት ጊዜ ኅሊናን የሚዋጋ መንፈስ አለ፡፡ ይህ መንፈስ ከጸሎት ለማራቅ ብርቱ ፈተና ያደርሳል፡፡ ጠላት በኅሊና መዋጋቱን ስለማያቆም ብዙ ጊዜ እየደጋገሙ ማማተብ ተገቢ መሆኑንም ያክላሉ፡፡ ጠላት በዋናነት የሰውን ልጅ ማጥቃት የሚፈልገው ከጸሎት በማራቅ ነው፡፡ ስለዚህ ምንም ይሁን ምን ጸሎትን ከማቋረጥ ይልቅ ዝም ብሎ መጸለይ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ነው ይህን ሥርዓት የሰሩልን፡፡ ለሌሎችም በርካታ የመታመን ሥራዎች ላይ ሥርዓቶችን ሠርተዋል፡፡ ጠቅለል ለማድረግ ያህል ሃይማኖት አንዲት ናት እርሷም እኛ የምናምናት እምነት ናት፡፡ ማንም ሰው የራሱን እምነት የመከተል ሙሉ ፈቃድ አለው፡፡ ሰው የፈለገውን ሁሉ ዛፍን፣ ጸሐይን፣ ድንጋይንም ሳይቀር ማምለክ ይችላል ነገር ግን አምላክ ሊባል የሚገባው ምን መስፈርት ማሟላት አለበት የሚለውን መመርመር የእኛ ፈንታ ነው፡፡ እግዚአብሔር እርሱን ብቻ እንድናመልከው አላስገደደንም ነገር ግን እርሱ አምላክ መሆኑን እንድንመረምር አዋቂ አእምሮ ሰጥቶናል፡፡ ስለዚህም ወልድ ዋሕድ በተዋሕዶ ከበረ ብለን ከአባቶቻችን ያገኘናትን እምነት እናምናለን፡፡
Gerum new Berta Wendem...
ReplyDelete