Monday, May 9, 2016

“የቅዱስ ማርቆስ እረፍት በዓል በአቡነ ማርቆስ ስብከት”


© መልካሙ በየነ
ግንቦት 1/2008 ዓ.ም
ደብረማርቆስ፣ ኢትዮጵያ


ዕለቱ ዳግማይ ትንሣኤ የሚከበርበት ዕለተ ሰንበት የወሩ መጨረሻ ሚያዝያ 30 በምሥራቅ ጎጃም ብቸኛ በሆነው የቅዱስ ማርቆስ ታቦት ከሚገኝበት ከመልዕልተ አድባር ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ከቅዱሱ በረከትን ለመካፈል በዚያ ተሰባስበናል፡፡ ግቢው ከወትሮው በተለየ ከቅርብም ከሩቅም ሳይቀር በኮንትራት አውቶቡስ በመጡ ብዛት ባላቸው ሕዝበ ክርስቲያኖች ተሞልቷል፤ ክህነት የሚቀበሉ የቆሎ ተማሪዎችም ግቢውን አድምቀውታል፡፡ የቅዱስ ማርቆስ ታቦት ማደሪያ የነበረው ቤተክርስቲያን በመታደስ ላይ ስለሆነ የተቀደሰው እዚያው ግቢ ካለው ከቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ነበር፡፡ ቅዳሴውን የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል አቡነ ማርቆስ ቀደሱትና 1፡30 አካባቢ ተፈጸመ፡፡ ከዚያም የሚገርመው ስብከት ተሰጠ፡፡

ዕለቱ ዕለተሰንበት እንደመሆኑ መጠን የእመቤታችን ተአምር በየአጥቢያው ይነበባል እዚህ ግን አቡኑ ራሳቸው አንባቢ ስለነበሩ “እሰግድ ለኪ” የሚለው ከተአምሩ ክፍል ተነበበና እመቤታችን የአደረገችው ተአምር እና የእመቤታችንን 33 በዓላት የሚገልጸው የምንባቡ ክፍል ሳይነበብ “አባታችን ሆይ” ብለው አሰሩት፡፡ በእርግጥ አባታችን ከዚህ በፊት ነግረውናል “የእመቤታችንን 33 በዓላት ማነብነብ ካሌንደር መናገር ነው፡፡ ዝም ብላችሁ እለፉት” ብለውን ነበር አላስችል ብሎን እንጅ፡፡ ከዚህ በኋላ አንድ መነኩሴ ተነሡና ይቅርታ ስማቸውን ስለማላውቃቸው ነው “ከተማችን ደብረ ማርቆስ፣ ጳጳሳችን አቡነ ማርቆስ፣ የምናከብረው በዓል የቅዱስ ማርቆስ እረፍት ነው” ብለው አባታችንን በብዙ ነገር ገለጹላቸው፡፡ “አባታችን የወንጌል አባት የትምህርት አባት” እንደሆኑ በብዙ ነገር ተናገሩላቸው፡፡ ግን የተነገረው ሁሉ አባታችንን የሚገልጻቸው አልመሰለኝም ምክንያቱም ከዚህ በኋላ ያስተማሩት ትምህርት ከተባለው በታች እጅጉን የወረደ ስለነበር፡፡ መድረኩን ለአቡነ ማርቆስ ለቀቁላቸው፡፡ ከዚያም “አስተማሩን” ያስተማሩንን ግን አብረን እንየው፡፡

አቡኑ ማይኩን እንደያዙ “ቁጭ በሉ” አሉን፡፡ “ጭቃ ምናምን አይባልም ዛሬ የመጣችሁት የቅዱሱን ሐዋርያ ዜና እረፍት ልትማሩ ነው” ይህ ንግግራቸው እንዴት ያለ ማር ንግግር ነበር መሰላችሁ፡፡ ምክንያቱም ሐዋርያው ቅዱስ ማርቆስ የተቀበለውን መከራ ጭቃ ላይ ከመቀመጥ አሳንሰን ልንመለከተው ስለማይገባ፡፡ ግን ከዚህ በኋላ ያለው ትምህርት እውቀት ያልታከለበት ፍጹም ከጨዋም የማይጠበቅ የማይረባ ነገር ነበር፡፡ ሰውን እንዴት እስከ 3 ሰዓት ድረስ ላቆየው የሚል ብቻ ነበር፡፡ “መርሐ ግብራችን እስከ 3 ሰዓት ይቆያል፡፡ ዛሬ ስለሐዋርያው በስፋት እንማማራለን፡፡ ትምህርቱን ሳትጨርሱ እንዳትነቃነቁ ባላችሁበት አረፍ አረፍ በሉ” አሉና ስንክሳሩን ማንበብ ጀመሩ “ወበዛቲ ዕለት አእረፈ ቅዱስ ማርቆስ…” ብለው የቅዱሱን እረፍት ጀመሩና ወደግብረ ሐዋርያት ምእራፍ 12 ተሸጋገሩ በእርግጥ የትምህርታቸውም መነሻ ይኼው ግብረ ሐዋርያት ላይ ያለው ቃል ነበር፡፡ ስንክሳሩን ጨርሰው ማስተማር ወይም ማንበብ አልቻሉም መሰል ወደ ሌላ ርእስ ገቡ፡፡ የቅዱስ ማርቆስን እረፍት ለመማር የተቀመጠው ሰው የቅዱሱን እረፍት ሳይማር ዝም ብሎ ተቀምጦ ያልገባው ሲስቅ የገባው ደግሞ ሲቃጠል ቆየ፡፡ ትምህርቱ ወደ መባእ ተለወጠ እና “አንች ጥላ ይዘሽ የምትዞሪዪት በእውነት እግዚአብሔር ጥላ ቸገረውን እግዚአብሔር የቸገረው ሰው ነው፡፡ እናንተን ነው የሚፈልግ” አሉ በጣም መልካም ንግግር ነው፡፡ እግዚአብሔር እኛን ፍለጋ ነው የተሰቀለው የሞተው የተነሣው ነገር ግን መባዕ ማስገባት ካልተቻለ ለምን መባእ ተቀባዮችን ምንጣፍ አንጥፈው እንዲሰበሰቡ ፈቀዱላቸው ብየ ውስጤ ተቃጠለ፡፡ እዚያው ውስጥ መባእ ተቀባዮች አሉ እኮ ጥላውም የሚሸጠው ከእነሱው ነው፡፡ “ጥላ ይዛችሁ ዙሩ የሚል መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጻፈ ነገር አለን” ብለው ጠየቁ፡፡ “ታዲያ ያልተጻፈ ነገር ከየት አመጣችሁ እናቶች የምላችሁን ስሙ፡፡ እኮ ከእኔ ከጳጳሱ በላይ ማን ይንገራችሁ” አሉ፡፡ እኛ እኮ ተዋሕዶዎች ነን አይደል እንዴ፡፡ ትውፊት የምንቀበል ነን፡፡ በእምነታችን ውስጥ የምናደርጋቸው ነገሮች ሁሉ ጥቅስ ይገኝላቸዋል ብሎ መገመት ያዳግታል፡፡ ያንንማ የሚሉት መናፍቃኑ ናቸው እኮ፡፡ ታዲያ ጥላ ይዛችሁ ዙሩ የሚል ጥቅስ አሳዩን የሚሉን ከሆነማ እያስተማሩን የነበረው የቅዱስ ማርቆስ እረፍት ሚያዝያ 30 መሆኑን ጥቅስ ማሳየት ነበረባቸው ማለት እኮ ነው፡፡ በአንዴ ረሱት መሰለኝ እንጅ እኮ ስንክሳሩን ከማንበባቸው በፊት እንዲህ ብለውን ነበር “መጽሐፍ ቅዱስ ማንዋል ነው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱሱ መፍቻ ስንክሳር ገድል እና ተአምር ነው”፡፡ አሁን ጥላው ላይ ግን ጥቅስ አምጡ ሲሉን ገረመን፡፡ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ለሁሉ ነገር ግልጽ ናት፡፡ ወይ በግልጽ ጥላ አታስገቡ ብሎ ማስተማር ነው የሚሻለው፡፡ ከዚህ በኋላ የቅዱስ ማርቆስ እረፍት እንዴት እንደሆነ ሳንማር ወደ ሌላ ርእስ ገቡ፡፡ የጥምቀት ጉዳይ ተነሣ፡፡ “አንዴ ተጠምቃችኋል ዳግመኛ ጥምቀት የለም፡፡ ጥምቀት አንዲት ናት ልብ ብላችሁ ስሙኝ ዋናው መልእክት እዚህ ላይ ነው፡፡ ዳግመኛ ተጠመቁ ቢባል ኖሮ እኛ እንነግራችሁ ነበር እኮ ከእኛ ከጳጳሳትና ከካህናት ውጭ ማን ይንገራችሁ እንግዲህ፡፡ እኮ  አንድ ዲማ ብቻ ነው እንዴ ደብር ያለ፡፡ ዲማ እኮ አንድ ተራ እንደማንኛውም ሁሉ ደብር ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በተለይ እናንተ የመጣችሁ ልትማሩ ነው እሱን ተምራችሁ ሂዱ፡፡ መጠመቅ ምናምን የሚባል ነገር የለም፡፡ ወላጆችም ልጆቻችሁን እኔ በ40 በ80 አስጠምቄሃለሁ አስጠምቄሻለሁ ዳግም ጥምቀት አያስፈልግም በሏቸው፡፡ በዲማ በዚህም በአብማ በኩል እናጠምቃለን እያሉ የሚልከሰከሱ አሉ አሉ፡፡ ደግሞ እኮ የሚገርማችሁ በስመ አብን ያልተማሩ ናቸው” ብለው ምንታዌነትን ደግፈው አስተማሩ፡፡ ሰው በብዛት አልገባውም የገባው ግን ልቡ በንዴት ጨሷል፡፡ ሰው የተረዳቸው እነዚህ አጥማቂ ነን ባዮችን የገሰጹ አድርጎ ነው፡፡ ግልጽ ነው ምሥራቅ ጎጃም ላይ ቅብአት የሚባል እምነት አለ፡፡ እሱ እምነት በእኛው በተዋሕዶ እምነት ሥር ተደብቆ ራሱን ይፋ ሳያደርግ የሚኖር ነው፡፡ ተአምረ ማርያምን በ28 ጌታን የወለደችበት ነው በ29ም መድኃኒታችንን የወለደችበት ነው ይላል፡፡ በአራት ዓመት አንድ ጊዜ በዘመነ ዮሐንስ ገና በ28 ይከበራል በቅብአት እምነት ዘንድ ግን ሁልጊዜም በ29 ይከበራል፡፡ ይህንን በ28 መከበሩን እሳቸው አይቀበሉትም ለዚያም እኮ ነው ተአምረ ማርያም ሁለቱን ቀን ስለሚጠቅስ “ካሌንደር ነው” ለማለት የደፈሩ፡፡ ዲማ ጊዮርጊስ ሳይሆን አብማ ላይ ይልከሰከሳሉ የተባሉት ግለሰቦችም ብቻ ሳይሆኑ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ በፍትሐ ነገሥቷ ላይ አንቀጽ 3 ቁጥር 24 ላይ “ከመናፍቃን ጥምቀትን የተቀበለ ሰው ቢኖር አማኒ አይደለም” ይላል፡፡ ስለዚህ ጥምቀት አንዲት ናት አትከለስም አትደገምም ግን ቅብአት ያጠመቀው ሰው ክርስቲያን ሊባል ይችላል ወይ የሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት፡፡ አባታችን በእርግጥ “ኦርቶዶክስ አንዲት ጥምቀት ብላ ታምናለች ዳግም መጠመቅ የለባችሁም” ያሉት ተዋሕዶ የሆኑትን አይደለም ቅብአት የሆኑትን ነው፡፡ በዚያው እምነታችሁ ጽኑ ብለው በግልጽ ነው የተናገሩት፡፡ “በተለይ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እዚህ የመጣችሁ እምነታችሁን ልትለውጡ አይደለምና ዳግም መጠመቅ የለባችሁም፡፡ ዳግም ተጠመቁ የሚላችሁ ሰው ካለም ስም ዝርዝሩን በሊስት አቅርቡልኝ” ነው ያሉት ይህ ደግሞ ግልጽና ግልጽ ነው፡፡ በእርግጥ ከዚህ በፊት በሥውር ያስተምሩ የነበሩ የቅብአት አስተማሪዎችም አሁን በግልጽና በድፍረት ማስተማሩን ተያይዘውታል፡፡ ከዚህም አልፈው በአንድ ገዳም ስም “ወልደ አብ” የሚል መጽሐፍ አሳትመው እየሸጡ ናቸው፡፡ ይህ የተደረገው ደግሞ አሁን አቡነ ማርቆስ ምሥራቅ ጎጃም ላይ ከመጡ በኋላ ነው፡፡ ወደ ጥንተ ነገራችን እንመለስና ፍትሐ ነገሥቱ “ከመናፍቃን ጥምቀትን የተቀበለ ሰው ቢኖር አማኒ አይደለም” ይላል፡፡ አማኒ ካልሆነ ደግሞ ያ ከእነርሱ የተቀበለው ጥምቀት አንድ ተብሎ አይቆጠርም ዜሮ ተብሎ ይቆጠራል እንጅ፡፡ የቅብአት ካህናት መናፍቃን ናቸውን የሚል ጥያቄ ከተነሣ እኔ በበኩሌ መልሴ አዎ መናፍቃን ብቻ ሳይሆኑ መንፈስ ቅዱስን በማጭበርበር የተቀበሉ የመሰላቸው ስልጣኑ ያላደረባቸው ናቸው ብየ አምናለሁ፡፡ ይህን የምለው ክህነት የሚሰጡት ጳጳሳት በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥር ናቸው ቅብአት የራሱ ጳጳስ የለውም ስለዚህ ክህነቱን ለመቀበል የግድ ለአንድ ቀን ራሱን ተዋሕዶ ነኝ ማለት አለበት፡፡ ተዋሕዶ ነኝ ብሎ በተዋሕዶ ስም ክህነት ይቀበላል ክህነቱን ከተቀበለ በኋላ ግን ቅብአት ነኝ ይላል፡፡ ታዲያ ይህ ሰው ካህን ነውን እንግዲህ ራሳችሁ ፍረዱት፡፡ ስለዚህ ከዚህ ሰው ጥምቀትን የተቀበለ ሰው ዳግመኛ ይጠመቃል ምክንያም የመጀመሪያው ጥምቀት አማኒ ሊያደረገን የሚችል ስላልሆነ፡፡ ይህንን የሚለው ደግሞ መጽሐፋችን እንጅ አቡኑ የጠቃቀሷቸው አድባራትና ገዳማት ወይም ግለሰቦች አይደሉም፡፡ ስለዚህ ቅብአትና ተዋሕዶን ተምሮ የምስጢራቸውን ልዩነት የተረዳ ማንኛውም ሰው ዳግም ይጠመቃል አራት ነጥብ፡፡ እሳቸው ሰውን ለማደናገር “ክዶ የተመለሰ ሰው እንኳ ዳግም ተጠመቅ አይባልም እንኳን መጀመሪያ የተጠመቀና ሳይክድ እዚሁ የቆየ ሰው” አሉ፡፡ ይህማ እኮ ልክ ነው መጀመሪያ በትክክል ተጠምቆ ልጅነትን ያገኘ ሰው ከመናፍቅ ስላልተጠመቀ አማኒ ነው፡፡ ነገር ግን ሥጋ ፈትኖት ካደ በኋላም ተመለሰ፡፡ መጀመሪያ ተጠምቆ ስለነበር ክህደቱ ኃጢአት ስለሆነ የቄድር ጥምቀት ይጠመቃል ቅብአት የሆነ ሰው ግን ከዚያ ይለያል ምክንያቱም በመጀመሪያም አማኒ ስላልነበር ተጠመቀ ተብሎ አይቆጠርምና፡፡ በእውነት የማዝነው በዙሪያቸው ላሉት ሊቃውንት ነው፡፡ ደፍረው ማስተማር አይችሉም “እምነታችን ተዋሕዶ ናት” ማለት አይችሉም ምክንያቱም የሚመጣባቸውን ፈተና ያውቃሉና ስለዚህ በድፍኑ “ኦርቶዶክስ” ብለው ያልፉታል፡፡

ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ የስድብ ገፈት ተቋዳሽ የነበሩት በበዓላት ላይ ለታቦቱ ክብር ድካማቸውን ያራቁ ወጣቶች ነበሩ፡፡ “እውነት አሁን አስፋልት ላይ ጨፌ መነስነስ ምን የሚሉት ነገር ነው፡፡ እኔ ደጋግሜ ተናገርኩ የሚሰማኝ ግን አጣሁ፡፡ የእኔ ሥራ መናገር ብቻ ነው የሚሠማ ካለ ይስማኝ” አሉ፡፡ በእውነት ዳዊት ራቁቱን እስኪሆን ድረስ በፊቱ የዘመረለትን ታቦት፤ በሆሣዕና ዕለት ልብሳቸውንና ዘንባባቸውን እያነጠፉ የተቀበሉትን አምላክ ወጣቱ በቻለው ነገር ቢያደርግ ምኑ ነው ክፋቱ፡፡ ህዝቡን ለመሳብ ግን በድርቁ አሳብበው ገቡት “ስንት ወንድሞቻችን እየተራቡ እየተጠሙ አስፋልት ላይ ሳር መነስነስ ምንድን ነው፡፡ ብራብ አላበላችሁኝም እንጅ ሳር አልነሰነሳችሁልኝም ብሎ አይጠይቀንም፡፡ ሳር የሚነሰነሰው እናቶቻችን ቡና ሲያፈሉ ነው” ብለው አስተማሩን፡፡ በእውነት የሳሩ ገንዘብ ነው በድርቅ የተጎዱ ወገኖቻችንን የሚመግባቸው፡፡ በእውነት መቼ ነው በድርቅ ለተጎዱት ልጆቻችን ብለው ጸሎተ ምሕላ ያስያዙን፡፡ እንጃ ግን የመልእክቱ ዓላማው ሌላ ነው፡፡

በእውነት እኛን ያሰባሰበን የቅዱስ ማርቆስ እረፍት ነበር ግን አልታደልንምና ስንወናበድ ስንሰደብ ዋልን፡፡ ከዚያ በኋላ 3 ሰዓት አካባቢ ሆነ “ማሳሰቢያ ነገር አለችኝ ሰዓቱም ጥሩ ላይ ነው የጨረስኩ” አሉ፡፡ ማሳሰቢው እንዳለቀ ታቦቱ ይወጣል ዑደት ይካሄዳል ብለን ነበር ግን ማሳሰቢያቸው በጣም ረዘመብን፡፡ “በዚያ በቢቡኝ በኩል” ብለው ጀመሩና ስለአቻ ጋብቻ አስተማሩን፡፡ “ሴት ስትደርስ ምልክት ታሳያለች” ብለው በድንችና በበቆሎ እየመሰሉ አስተማሩን፡፡ እኛም ሴት የምትደርስበትን ጊዜ በሚገባ አወቅን፡፡ የቅዱስ ማርቆስ እረፍት ግን ተረሣ፡፡

ከዚህ በኋላ ግን መታገስ አልቻልኩምና ወደ ወንድሜ ዲ.ን ሰሎሞን ስልኬን ደወልኩ ‹‹የት ነህ አልኩት›› ‹‹እኔ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አስቀድሼ አሁን ዶርሜ ነኝ›› አለኝ፡፡ ‹‹በቃ መጣሁ›› አልኩና ስልኬን ዘግቼ ወስጤ እተቃጠለ የታቦቱን ዑደት ሳላከብር ሳላይ ወደ ዶርሜ አቀናሁ፡፡ አምላክ ዘመናችንን ይባርክልን መናፍቃንን ያስታግስልን፡፡

አሜን፡፡