Thursday, November 15, 2018

ቅብዐቶችን ወደ ብጥብጥ የገፏቸው ተሐድሶ መናፍቃን ናቸው፡፡


፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
ይህን የምለው ዝም ብዬ ከምድር ተነሥቼ አይደለም እየኾነ ያለው ነገር ኹሉ ከነባር የቅብዓቶች አስተምህሮ እና እንቅስቃሴ ውጭ የኾኑ ነገሮች እያየን ስለኾነ ነው፡፡ አንድ ቀን እግዚአብሔር ፈቃዱ ሲኾን በጅምላ እየተነዳ ያለው የዋሕ ምእመን እውነቱን አውቆ ወደ እውነተኛዪቱ ጎዳና መምጣቱ አይቀሬ ነው፡፡ ትናንት ሕዳር 1/2011 ዓ.ም ደብረ ወርቅ ላይ የነበረው ሕግ የጣሰ ድርጊት በጀርባ ኾነው የሚገፉት ተሐድሶ መናፍቃን እንደነበሩ በግልጽ ታውቋል፡፡ አሁን ቅብዐቶች ከተሐድሶዎች ጋር እጅ እና ጓንት ኾነው እየሠሩ ያለበት ወቅት ነው፡፡ ይህን ለማስተባበል ነጠላውን ወስደህ ዝም ብለህ አትጻፍ የሚሉ ቅብዓታዊ ተሐድሶዎች ከራሳቸው መጽሐፍ ላይ የተጻፈውን አቀርብላቸውና አንድምታ ትርጓሜውን እንዲያስረዱኝ ለእነርሱ እተወዋለሁ፡፡ ይህን ማንም ሕጻን አንብቦ የሚረዳውን ቃለ ኑፋቄ በነጠላ አትውሰደው ማለት ለእኔ ምንም ትርጉም አይሰጠኝም፡፡
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠

  • -     ቅብዐቶች እንደ ተሐድሶዎቹ ለቅዱሳን እና ለመስቀል ስግደት አይገባም ይላሉ፡፡

  • -     ቅብዐቶች እንደ ተሐድሶዎች ወንጌል በአሚን ብቻ ታድናለች ይላሉ፡፡

  • -     ቅብዐቶች እንደ ተሐድሶዎቹ ሥጋ ወደሙ ላይ ያላቸው የተጣመመ ትምህርት ነው፡፡

፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠

የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ ሳያውቅ አብሮ ለጥፋት የሚጓዘውን የዋሕ ሕዝብ እውነቱን መንገር ነው፡፡ ከታች ‹‹ወልደ አብ›› የተባለው መጽሐፍ ላይ የተጻፈውን ትምህርታቸውን በፎቶ ትመለከቱታላችሁ፡፡ እነዚህ ትምህርቶች የተሐድሶ አስተምህሮ መኾናቸው ቤተክርስቲያናችንን ለመከፋፈል ሌት ከቀን እየደከመ ያለው የጥፋት ቡድን መኾኑን እንድትረዱ ማድረግ ግዴታ ነው፡፡ አሁን ቅብዓት ነን ብለው እንሰብካለን የሚሉት ግለሰቦችም ዋና ትስስራቸው ከመናፍቃኑ ጋር ነውና የዋሑ ሕዝብ ወደ እውነቱ ልታዘነብል ያስፈልግሃል፡፡ ጎጃም ዳግም ተጠመቅ ተባልህ፣ ሃይማኖትህን ለውጥ ተባልህ ወዘተ የሚለው የመናፍቃኑ ፕሮፖጋንዳ የሀሰት ነውና ቆም ብለህ አስተውል፡፡ ዳግም ጥምቀት የለም ሥርዓተ ቤተክርስቲያንም አይደለም፡፡ መጠመቅ የሚገባው ልጅነት ማግኘት የሚሻው ግን ሊጠመቅ ሥርዓት አለው ሕግ አለው፡፡ አሁን ወደ ዋና መልእክቴ ላምራ፡፡
ቅብዐቶች ለቅዱሳን ያላቸው አመለካከት የተዛባ ነው። ይህ አመለካከት ምናልባትም ለፕሮቴስታንት መናፍቃን ያላቸውን አጋርነት እያረጋገጡ መኾኑ ለማንም የማይካድ እውነታ ነው። ብዙ የቅብዐት እምነት ተከታዮች የእናት የአባቴን እምነት አልተውም ከማለት የዘለለ መከራከሪያ ነጥብ አያቀርቡም። የቅብዐትን ምስጢር በሚገባ ጠንቅቀን እናውቃለን የሚሉ የሄኖክ ደቀ መዛሙርትም እንዲህ ያለውን የዶግማ ልዩነት ደብቀው በበዓላት እና በአጽዋማት ላይ ሲከራከሩ ነው የሚታዩት። እውነታው ይገለጥ ከተባለ ግን ልዩነታችን የዶግማ ነው።
ቅዱሳን እና መስቀል ላይ ያላቸውን የተጣመመ ትምህርት እንመለከታለን። ለዚህም ከታች በፎቶ የተያያዘውን «ወልደ አብ» በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ ያለውን ማስረጃ ተመልከቱ። ፎቶው ለማይከፍትላችሁ ግን ከታች ጽፌላችኋለሁ። ብዙ የቅብዐት እምነት ተከታዮች ይህን ተመልክታችሁ ዛሬውኑ ከዚህ ምንፍቅና ካልወጣችሁ በእውነት በራሳችሁ ፈቃድ ሞትን እንደመረጣችሁ እውቁት።
 ወልደ አብ ገጽ ፪፻፶፩ ላይ እንዲህ ይላሉ፡-
«የጻድቃን እናቶች ይሰገድላቸዋልን ስንኳንስ ለእናቶቻቸው ለእርሳቸውም አይሰገድላቸውም። … ለመስቀልም መሰገዱ የእርሱን የባሕርይ ልጅነቱን ያጠይቃል እንዴት ቢሉ እንግዲያው የቅዱስ ጴጥሮስ የቅዱስ ጊዮርጊስ መስቀል ይሰገድለታልን፤ ስንኳንስ ለመስቀሉ ለእርሳቸውም አይሰገድላቸውም» ይላል።
ይህ ምንም ማብራሪያ የማያስፈልገው ቁልጭ ያለ ክህደት ነው። ለቅዱሳን እናቶች መስገድ ይቅርና ለቅዱሳን ልጆቻቸውም ስግደት አይገባም እያለ ነው የሚናገረው። ይህንን ኑፋቄ በውኑ ከወዴት አመነጫችሁት? እስኪ አንድምታ ትርጉሙን አስረዱኝ፡፡ ይህ በእውነት ምን ትርጓሜ ያሻዋል?
በርግጥ ወልድን ፍጡር ነው ብሎ ለሚያምን ሰው ለቅዱሳን ስግደት አይገባም ማለት ቀላሉ ስለኾነ ምንም ላይመስላቸው ይችላል። ለእኛ ግን ይህ ጉዳይ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
ሌላው ቅብዐቶች መስቀል ላይ ያላቸው ትምህርትም የተዛባ መኾኑን በመጽሐፋቸው ላይ አይተናል። «የቅዱስ ጴጥሮስ የቅዱስ ጊዮርጊስ መስቀል ይሰገድለታልን፤ ስንኳንስ ለመስቀሉ ለእርሳቸውም አይሰገድላቸውም» የሚለው ትምህርታቸው እንኳንስ ለመስቀላቸው ይቅርና ለቅዱሳኑ ለእነ ቅዱስ ጊዮርጊስም ለእነ ቅዱስ ጴጥሮስም ስግደት አይገባቸውም የሚል ነው። ይህ ማለት ለመስቀልም ስግደት አይገባም ማለት ነው። በእውነት ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ስግደት አይገባምን? ነቢዩ ቅዱስ ዳዊት መዝ ፻፴፩÷፯ ላይ “ወደ ማደሪያዎቹ እንገባለን እግሮቹ በሚቆሙበት ሥፍራ እንሰግዳለን” ማለቱን እናስተውል፡፡ እግሮቹ የቆሙበት ስፍራ በእውነት ከመስቀሉ በላይ ምናለ? እግሮቹ ብቻ ያይደለ መላ አካሉን ምቹ ዙፋኑ አድርጎ ያሳረፈበት ቦታ በእውነት መስቀሉ አይደለምን? እኛ የተዋሕዶ ልጆች ግን «እሰግድ ለመስቀለ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘተቀደሰ በደሙ ክቡር - ዓለምን ኹሉ ለማዳን ኢየሱስ ክርስቶስ ለተሰቀለበት [በክቡር ደሙ ለቀደሰው] መስቀልም እሰግዳለሁ» እያልን በዘወትር ጸሎታችን እናነሣዋለን እንሰግድለታለንም።
 የቅብዐት እምነት ተከታዮች ሆይ! የውስጡን ምስጢር ደብቀው በጾም እና በበዓላት እንድትነታረኩ ያደረጓችሁን ሐሰተኛ መምህራን አትስሟቸው። ከቅዱሳን አንድነት ሊለይዋችሁ ነው የተነሡት። ለመስቀል አይሰገድም እያሏችሁ ነው ያሉት። ከመስቀል ከለይዋችሁ ከቅዱሳን ከለይዋችሁ ታዲያ ምን ሕይወት አላችሁ? ቅዱስ ጊዮርጊስ አያስፈልጋችሁም አቡነ ተክለ ሃይማኖት አይጠቅሟችሁም እያሏችሁ መኾኑን ልብ ብላችሁ ወደ እውነተኛዪቱ ሃይማኖት ተመለሱ እንላለን።
በጾም እና በበዓላት ላይ እንድትከራከሩ ያደረጓችሁ አውቀው ነው። ዋናውን ምንፍቅናቸውን በአንድ ጊዜ ወደ እናንተ ለማድረስ ስለተቸገሩ ነው እንጂ ነገ ከነገ ወዲያ የምን ቅዱሳን ነው የምን መስቀል ነው የምን ስግደት ነው የምን ጾም ነው ማለታቸው አይቀርም። በመጽሐፍ ጽፈውላችኋል እኮ ነገ ደግሞ በተቀደሰው ዐውደ ምሕረት ላይ ቆመው ይህንኑ ማስተማራቸው አይቀርምና አትከተሏቸው።
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
‹‹ወንጌል በአሚን ብቻ ታድናለች›› ሌላው የቅብዐቶች ትምህርት፡፡ ሄኖክ የተባለው የቅባቶች ሊቅ ጥላሁን መኮንን በተባለ የተሐድሶ መናፍቅ «ከተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ውጡ ጳጳስ እኔ ከእስክንድርያ አመጣላችኋለሁ እንዲያውም እርስዎን የቅብዐቶች የመጀመሪያ ጳጳስ እንድትኾን አደርጋለሁ» ብሎ ለሦስት ወራት ያህል የተሐድሶ ሥልጠና ሰጥቶ ስለላከው እንዲህ ያለውን ነገር ቢጽፍ የሚፈረድበት አይመስለኝም። ቅብዐቶች እንደሚሉት ከኾነ «ወልደ አብ» የተባለው መጽሐፍ ከጥንት ጀምሮ በብራና ተጽፎ የነበረ ነው። ያ ማለት ደግሞ ቅብዐቶች እውነት ነው ያሉትን የሚያምኑበትን እምነታቸውን በመጽሐፋቸው ላይ ጽፈውታል ማለት ነው። ስለዚህ ቅብቶች በአጽዋማትና በበዓላት ላይ ያላቸውን የተዛባ ትምህርት ወደ ጎን አድርገን ዶግማው ላይ ብቻ ብንነጋገር ብዙ ልዩነቶች እንዳሉን እንመለከታለን። ኢየሱስ ክርስቶስን ፍጡር ከማለት የበለጠ ምን ልዩነት ሊመጣ ነው? ለቅዱሳን እና ለመስቀል ስግደት አይገባም ከሚል ልዩነት በላይ ምን ልዩነት ሊመጣልን ነው? ወንጌል በአሚን ብቻ ታድናለች ከማለት በላይ ምን የባሰ ልዩነት ሊመጣ ነው? ይህን የዶግማ ልዩነት እየተነጋገርን ባለንበት ሰዓት እንኳ ስለጾመ ነቢያት እና ስለጾመ ሐዋርያት ብሎም ስለልደት በዓል አከባበር ሽንጣቸውን ገትረው ሊከራከሩ የሚንፈራፈሩ ቅብዐቶች መኖራቸው አይቀሬ ነው። ወልድን ፍጡር እያሉ ልደቱ መቼስ ቢከበር ምናቸው ነው? ጾም ቢጾምም አይጠቅምም ባይጾምም ኩነኔ የለውም እያሉ ጾም መቼስ ቢገባ መቼስ ቢወጣ ምናቸው ነው? ወንጌል በአሚን ብቻ ታድናለች እያሉ ክርስቲያናዊ ምግባራት ላይ መከራከር እንዴት ይችላሉ? ለቅዱሳን ስግደት አይገባም ለመስቀሉም ስግደት አይገባም እያሉ ስለቅዱሳን እና ስለመስቀሉ ምን አከራከራቸው?

ቅብዐቶች ‹‹ወልደ አብ›› በተሰኘ መጽሐፋቸው ገጽ ፻፺፫ ላይ፡«ዳግመኛም ኦሪት ጀምሮ የፈጸማትን ታድን ነበረ እንጅ እንደ ወንጌል በአሚን ብቻ አታድንም ነበረ» ይላሉ። በእውነት ወንጌል በአሚን ብቻ ታድናለችን? አዎ ካላችሁ ለምን ትጾማላችሁ? ለምን በዓላትን ታከብራላችሁ? ለምን ትመጸውታላችሁ? ለምን ትሰግዳላችሁ? ለምን ምግባር መሥራት አስፈለጋችሁ? አረ ወንጌል በአሚን ብቻ አታድንም ካላችሁ ግን ለምን ቅብዐት ትኾናላችሁ? ለምን «ወልደ አብ» የተባለውን ምናምንቴ መጽሐፍ ትቀበላላችሁ? ለምን በተዋሕዶ እምነት አታምኑም? ለምን ወደ ተዋሕዶ እናታችሁ አትመለሱም? ይህ ትምህርት ፍጹም ፕሮቴስታንታዊ ነው። «ኢየሱስን ካመንህ በቃ ድነኃል የምን ንስሐ ነው? የምን ጾም ነው? የምን ስግደት ነው? የምን ምጽዋት ነው? የምን ምንኲስና ነው? የምን ብሕትውና ነው? የምን ስለኃጢት ማዘን ነው?» የሚለው የፕሮቴስታንቱ ትምህርት ነው ቅብዐቶች ላይም እያየነው ያለነው። እኔ የማዝነው የእናቴ የአባቴ ነው እያለ እስካሁን ድረስ ቅብዐት ነኝ እያለ ቁጭ ያለው ሰው ነው። ይህንን ልዩነት ቢያውቀው ኖሮ ማን በቅብዐት ይጨማለቅ ነበር? አረ ማንም።
ለማንኛውም እምነት ብቻውን አያድንም። የቆማችሁ የመሰላችሁ ቅብዐቶች «እንደቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ» ፩ኛ ቆሮ፲÷፲፪ እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ ውድቀታችሁን አታፋጥኑ በጊዜ ራሳችሁን ፈልጉ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ እንዲህ ይላል «…ሥራኽን አውቃለሁ ሕያው እንደመኾንህ ስም አለኽ ሞተኸማል» ራእ ፫÷፩። ስም ያለን መስሏችሁ የሞታችሁ የከፋ ሥራችሁ የከረፋ እምነታችሁ በእግዚአብሔር ዘንድ የታወቀው እናንተ ቅብዐቶች ሆይ ወደ ልቡናችሁ ተመለሱ። ወንጌል በአሚን ብቻ ታድናለች ካላችሁ ሐዋርያው ያዕቆብ በመልእክቱ ምን እንደጻፈ ልንገራችሁ እስኪ። ያዕ ፪÷፲፬ ላይ «ወንድሞቼ ሆይ እምነት አለኝ የሚል ሥራ ግን የሌለው ሰው ቢኖር ምን ይጠቅመዋል እምነቱስ ሊያድነው ይችላልን?» ብሎ ይጠይቀናል። እኛ ለሐዋርያው የምንመልስለት መልስ ሊያድነው አይችልም ብለን ነው ቅብዐቶች ግን አዎ ያድነዋል ብለው ነው ማለት ነው። ስለዚህ ወንጌል በአሚን ብቻ አታድንም። አሚን ያለሥራ የሞተ ነው እንላለን አብነታችንም ሐዋርያው ያዕቆብ ነው። ያዕ ፪÷፲፯ «ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው» ይለናል። ስለዚህ ወንጌል በአሚን ብቻ ታድናለች የሚለው የቅብዐት እምነት በራሱ የሞተ ነው ማለት ነው። የሞተን እምነት የሚከተል ሰው ደግሞ በራሱ የሞተ ነው። ስለዚህ ከሞት ለመውጣት ከቅብዐት እምነት ዛሬውኑ መውጣት ያስፈልጋል ማለት ነው። ቅብዐቶች በአጽዋማት ላይ ሲከራከሩ ለምን በዚህ ቀን አንጀምርም ለምን ጾሙ አጠረብን ወዘተ ብለው እንዳልኾነ ልብ ማለት ተገቢ ነው። ዋና ምክንያታቸው ወንጌል በአሚን ብቻ ታድናለችና ጾም አይጠቅምም የሚለው ትምህርታቸው ነው። በመጀመሪያዪቱ የቅብዐቶች መጽሐፍ በመሰረተ ሐይማኖት ላይ እኮ ጾምን ሸክም ነው ብሎታል። ቀጥሎ ደግሞ ቢጾምም አይጠቅምም ባይጾምም ኩነኔ የለውም ብለዋል ስለዚህ በአሚን ብቻ የምትለዋ ናት ዋና ትምህርታቸው። ወደ ምእመኑ ጾም አያስፈልግም ብሎ መግባት አይችሉም ጿሚ ምእመን ስላለ እንዴት ብሎ መጠየቁ አይቀርምና። ወደ ዋና ጉዳያቸው ጾም አያስፈልግም አሚን ብቻዋን ታድናለች ወደሚለው ኑፋቄ ለመግባት ቀስ ብለው መጀመር ስላለባቸው ነው በአጽዋማት መግቢያ ላይ እንዲከራከሩ ያደረጓቸው። ስለዚህ ይህን እውነታ ለምእመናን ማድረስ ግዴታችን ይኾናል።
በነገራችን ላይ ቅብዐት አለ በሚባልባቸው አካባቢዎች ያሉ ምእመናን ይጾማሉ፣ ይጸልያሉ፣ ይሰግዳሉ፣ ይመጸውታሉ። ይህን በሚገባ አውቃለሁ በሚገባም አይቻለሁ። ለመስቀልም ለቅዱሳንም ስግደት እንደሚገባ ያምናሉ በተግባርም ይፈጽማሉ። ምክንያቱም «እምነቴ የእናቴ ነው የአባቴ ነው» ከማለት ውጭ ጠለቅ ያለውን ምስጢር ስለማያውቁት ነው። ዛሬ የቅብዐት መምህራን ነን የሚሉ ገዳማውያኑን ጨምሮ ግን የቅብዐት መሠረተ እምነቱ ምን እንደኾነ ጠንቅቀው ያውቁታል። ይህንን ትምህርት ለመስቀል ሲሰግድ ለቅዱሳን ሲሰግድ ለኖረ ምእመን እንዴት አድርገው በአንድ ጀንበር ለቅዱሳን እና ለመስቀል አይሰገድም ይበሏቸው? ባለፈው ዓመት በጥቅምት ወር ጒንደ ወይን ላይ ወጣቶችን ሰብስበው ስለቅብዐት ሲያስተምሩ የነበሩት መምህራን «ወልደ አብ ማለት ግጸዌ ማለት ነው፤ ማውጫ ነው» ሲሉ ሰምቻለሁ። ግጸዌው ወይም ማውጫው «ወልደ አብ» ለቅዱሳን አይሰገድም፣ ለመስቀልም አይሰገድም፣ ወልድ ፍጡር ነው፣ ወንጌል በአሚን ብቻ ታድናለች ካለ ዋናው መጽሐፍ ምን ሊኾን እንደሚችል መገመት የሚከብድ አይመስለኝም።
አሁን እኔ የጻፍኩትን አንብበው በውስጥ መስመር «እኔ ቅብዐት ነኝ ግን ለቅዱሳን ስግደት አይገባም፣ ለመስቀል ስግደት አይገባም፣ ወንጌል በአሚን ብቻ ታድናለች፣ ወልድ ፍጡር ነው የሚል ትምህርት አልተማርኩም አላውቅምም» እንደሚሉኝ እጠብቃለሁ። በእውነት እግዚአብሔር በሚያውቀው ለእነዚህ ሰዎች በጣም አዝንላቸዋለሁ። ምክንያቱም «ቅብዐት ናችሁ» እያሉ በእልህ እና በትዕቢት እንዲነዱ እያደረጓቸው ያሉት ቀሳጢ እና መናጢ «መምህራን» ናቸውና። ይህን ከ«ወልደ አብ» አግኝቼ የጻፍኹላችሁን ኑፋቄ ዐውደ ምሕረት ላይ ቆመው ቢሰብኩት አንድ የቅብዐት ምእመን አያገኙም በዚህ እተማመናለሁ። ለዚህ ነው ውስጥ ውስጡን እንደ ሰደድ እሳት በኑፋቄ እየለበለቡ በእልህ የሚነዳ ደጋፊ ለመሰብሰብ እንቅልፍ አጥተው በመሥራት ላይ የሚገኙት። እስኪ ዋናውን ምስጢር ጠይቁ። እስኪ የቅብዐት ሊቃውንትን ጠይቁ። በተለይ ደግሞ መጽሐፉን ያሳተመችውን ገዳም ቆጋ ኪዳነ ምሕረትን ሄዳችሁ በትሕትና ጠይቁ። ወልደ አብ ገጽ እዚህ ላይ ለቅዱሳን ስግደት አይገባም ይላል፣ እዚህ ገጽ ላይ ደግሞ ወልድ ፍጡር ነው ይላል፣ እዚህ ገጽ ላይ ደግሞ ወንጌል በአሚን ብቻ ታድናለች ብሏል፣ እዚህ ገጽ ላይ ደግሞ ለመስቀል ስግደት አይገባም ብሏል ወዘተ ምን ለማለት ተፈልጎ ነው አብራሩልን በሏቸው። በርግጥ አሁንም ቢኾን እውነታውን ደብቀው በጾም እና በበዓላት ልዩነታችን (በቀኖና) ሊደልሏችሁ እንደሚነሡ የታወቀ ነው። ያም ኾነ ይህ ግን ቅብዐት ነኝ ብሎ ስለቅብዐት እምነት አውቃለሁ ያለ ሰው የጻፈው መጽሐፍ «ወልደ አብ» እንደ እኔ አመለካከት የቅብዐቶችን ሙሉ ትምህርት የያዘ ነውና ለእነርሱ ትክክል ነው። ትክክል ነው ብለው ከተቀበሉት ደግሞ በዚያ የተጻፈውን ኹሉ እምነቴ ነው ሊሉ ይገባል ማለት ነው። ቀስ በቀስ ምእመኑን ካስለመዱ በኋላ መጽሐፉ ወደያዘው መሠረታዊ ክህደት ማምራታቸው አይቀርምና ከወዲሁ በስመ ቅብዐት በእልህ የምትንቀሳቀሱ ወገኖቼ ቆም ብላችሁ በሰከነ እና በተማረ አስተሳሰብ ራሳችሁን ቃኙት።
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
ሥጋ ወደሙ ላይ ያላቸው የተጣመመ ትምህርት ሌላኛው ተሐድሶ መናፍቃን የሰጧቸው ትምህርት ነው፡፡
እዚህ ላይ የምንመለከተው ቅብዐቶች ሥጋ ወደሙ ላይ ስላላቸው የተጣመመ ትምህርት ነው። ቅብዐቶች ወልደ አብ ገጽ ፪፻፴፬ ላይ «ሥጋውስ በሰውነቱ ተበልቶ በአምላክነቱ ያድናል፣ ደሙም በሰውነቱ ተጠጥቶ በአምላክነቱ ያስተሠርያል» በማለት ሥጋ ወደሙ ላይ ያላቸውን ብዥታ ያለበት የደበዘዘ ትምህርት ጽፈዋል። ነገር ላለማብዛት ስለሥጋ ወደሙ ወይም ስለቅዱስ ቊርባኑ ብዙ አልጽፍም ግን ሥጋ ወደሙ የሚያድነን የዘላለም ርስት መንግሥተ ሰማያትን የምንወርስበት እንዴት ነው? የሚለውን ጥያቄ እንዲመልሱልን መጠየቅ እፈልጋለሁ። በርግጥ እንደነርሱ አስተምህሮ ከኾነ ሥጋ ወደሙ በአምላክነቱ የሚያድነው በሰውነቱ ተበልቶ እና ተጠጥቶ ነው። ይህ ሥጋ ወደሙ ላይ የመጣው የተጣመመ ትምህርት ሥግው ቃል ላይ ያለ ስህተታቸው ነው። ሥግው ቃልን አንድ ነው በማለት ፈንታ በቃል ርስት ፈጣሪ በሥጋ ርስት ፍጡር እያሉ በተዋሕዶ አንድ የኾነውን ወደ ኹለት በመለያየት የጀመሩት ስህተት ሥጋ ወደሙ ላይም መጣባቸው። ሥጋ ወደሙ መለኮት የተዋሐደው ነፍስ ግን የተለየው አማናዊ (እውነተኛ) መብልና መጠጥ ነው። የቅብዐቶች አስተምህሮ ግን ሥጋ ወደሙ ለመታሰቢያነት ይደረጋል እንጅ አማናዊ አይደለም ከሚሉት ከፕሮቴስታንቶች ትምህርት የሚርቅ አይደለም። ቅብዐቶች «ሥጋውስ በሰውነቱ ተበልቶ በአምላክነቱ ያድናል፣ ደሙም በሰውነቱ ተጠጥቶ በአምላክነቱ ያስተሠርያል» ሲሉ ሥጋ ወደሙ ሰውነቱ ለብቻው አምላክነቱ ደግሞ ለብቻው የተከፈሉ ናቸው ማለታቸው ነው። ምክንያቱም «በሰውነቱ እንበላዋለን እንጅ በሰውነቱ አያድነንም፤ በሰውነቱ እንጠጣዋለን እንጅ በሰውነቱ አያስተሠርይልንም» ማለታቸው ነውና። በሌላ አነጋገር ደግሞ «በአምላክነቱ አንበላውም አንጠጣውም ግን በአምላክነቱ ያድነናል ያስተሠርይልንማል» ማለታቸው ነው። ታዲያ እንዲህ ከኾነ የተዋሕዶ (አንድ የመኾን) ምስጢር ወዴት አለ? «በሰውነቱ ይበላል ይጠጣል በአምላክነቱ ግን አይበላም አይጠጣም» ብሎ መናገር የዕሩቅ ብእሲ ሥጋ እና ደም እንበላለን እንጠጣለን ወደ ማለት አያደርስም ብላችሁ ነው? መለኮት የተዋሐደውን ነፍስ የተለየውን ሥጋ እና ደም እንበላለን እንጠጣለን ካላሉ በጣም ከባድ ኑፋቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው። ሃይማኖተ አበው ዘአትናቴዎስ ፳፰÷፳፪ ላይ «ዳግመኛም የሚያድን የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ እና ደም እንደኾነ በከበረ ቊርባን እናምናለን። ቄሱ ሳያከብረው ኅብስት ወይን የነበረ ፤ ቄሱ ባከበረው ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በላዩ ይወርዳል። ኅብስት ከመኾን የወልደ እግዚአብሔር ቃል አማናዊ ሥጋ ወደ መኾን ይለወጣል። ወይኑም እንዲሁ ወይን ከመኾን የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ አምላካዊ ደም ወደ መኾን ይለወጣል። ከሥጋው ጋር አንድ ኾኖ» ይላል። ሊቁ አማናዊ ሥጋ እና ደም ወደ መኾን ይለወጣል ካለን ታዲያ የክርስቶስ እውነተኛ ሥጋ እና ደሙ ሰውነት እና አምላክ ተብሎ የተከፈለ ነውን? አይደለም በፍጹም ሎቱ ስብሐት! ታዲያ ክርስቶስን ከኹለት ባሕርያት አንድ ባሕርይ፤ ከኹለት አካላት አንድ አካል ነው ካልን በሰውነቱ የሚበላ በአምላክነቱ የሚያድን ነው ልንለው እንዴት እንደፍራለን? በሰውነቱ ይጠጣል በአምላክነቱም ያስተሠርያል ልንለውስ እንዴት በሐሰት እንነሣሣለን? ሥጋው ሰውነቱ እና አምላክነቱ ተለያይተው የሚገኙበት አይደለም። ደሙም ሰውነቱ እና አምላክነቱ የተለያዩበት አይደለም። ሥጋውም ደሙም ሰውነቱ እና አምላክነቱ ተዋሕደው አንድ የኾኑበት ነው። ስለዚህ መለኮት የተዋሐደውን ሥጋ እና ደም እንበላለን እንጠጣለን እንላለን እንጅ ሰውነቱን ከመለኮቱ ለይተን በሰውነቱ ይበላል ይጠጣል በአምላክነቱ ያድናል ያስተሠርያል አንልም።
========================================
© መልካሙ በየነ
ኅዳር 2/2011 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ