Tuesday, November 5, 2019

“ኑ! ጌራ መድኃኒት ጅረት መድኃኔ ዓለም አንድነት ገዳምን እንታደገው”

=========================
የገዳሙ አስተዳዳሪ “ይህ ቦታ ለዚህ ትውልድ መዳኛ ቦታ ነው፡፡ ነገር ግን ለትውልዱ ተሠውሯል፡፡ ዓይንና ጆሮ ለየቅል ናቸውና ቦታውን አይታችሁ በግልጥ በረከትን ስትቀበሉ ያላችሁ” ይላሉ፡፡

#የቦታው_መገኛ፡-

በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት በጎንቻ ሲሶ እነሴ ወረዳ በመራጉፍ ቀበሌ ነው፡፡

#ወደ_ቦታው_ለመድረስ፡-

ከደብረ ማርቆስ 147 ኪ.ሜ ከአዲስ አበባ 322 ኪ.ሜ እንደተጓዙ ገምቦሬ ከምትባል ትንሽ ከተማ ይደርሳሉ፡፡ ከዚያም ወደ ምሥራቅ  አቅጣጫ በእግር ከ1 ሰዓት እስከ 1፡30 ተጉዘው ገዳሙን የሚያገኙት ሲሆን በመኪና ለሚጓዙ ደግሞ በእነጎዴ በኩል (ዋናውን የሞጣ  የአስፋልት መንገድ ይዘው ለሚመጡ) ከገንቦሬ ተገንጥሎ በሚገባው ጠጠር መንገድ ከ15-20 ደቂቃ ተጉዘው እነጎዴ ይደርሳሉ፡፡ ከዚያም በእግር ከ10-15 ደቂቃ ተጉዘው ገዳሙን ያገኙታል፡፡ በመርጡለ ማርያም አቅጣጫ ለሚመጡ ደግሞ በጨሞ በኩል የ1 ሰዓት የእግር ጉዞ ተጉዘው የሚያገኙት ሲሆን መደበኛ መኪና ስለሌለው በኮንትራት መኪና እስከ እነጎዴ ድረስም በመኪና መሄድ የሚቻልበት ዕድል አለ፡፡ ከሞጣ ለሚመጡ ደግሞ ጉንደ ወይን ከተማ እንደደረሱ እነጎዴ ድረስ 12 ኪ.ሜ በመኪና ሄደው ከ10-15 ደቂቃ የእግር ጉዞ አድርገው ገዳሙን ያገኙታል፡፡ የኮንትራት መኪና ወይም የግል መኪና ይዘው ለሚሄዱ ግን ከእነጎዴም የተወሰነ ርቀት ያህል ወደ ገዳሙ መጓዝ የሚያስችል መንገድ አለው፡፡

#የገዳሙ_አመሠራረት፡-

1213 . በአጼ ይኩኑ አምላክ ተመሠረተ፡፡ ይህ ዕድሜ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ጥንታውያን ገዳማት መካከል አንዱ ያደርገዋል፡፡
#ምክንያተ_ምሥረታው፡- ዓፄ ይኩኖ አምላክ ሠራዊታቸውን እና ካህናትን አስከትለው የኦሪት መሥዋእት ይሰዋባት የነበረችውን ጥንታዊቷን መርጡለ ማርያምን ገዳም ጎብኝተው እና ተሳልመው ወደ  ሸዋ ሲመለሱ መሽቶባቸው አሁን ገዳሙ በሚገኝበት ቦታ ላይ ከነሠራዊታቸው አደሩ፡፡ ንጉሡ ዓፄ ይኩኖ አምላክ ሌሊት በህልማቸው በዚህ ቦታ ላይ በአምሳለልመ ያዕቆብ (ያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ እንዳየው መሰላል) መላእክት ወደ ላይ ሲወጡ ወደ ታችም ሲወርዱ ተመለከቱ፡፡ ካህናቱ ታቦተ ሕጉን፤ ንጉሡ ሠራዊቱን ይዘው ዋሻው ውስጥ በድንኳን አድረዋል፡፡ ንጉሡ ጠዋት ተነሥተው ሊሄዱ  ሲሉ በጉዟቸው ሁሉ ይዘውት የሚንቀሳቀሱት ታቦተ መድኃኔዓለም ለካህናቱ አልነሣላቸው አለ፡በዚህ ጊዜ ንጉሡ ሕልማቸውን ለካህናቱ ነገሩዋቸው እነርሱም በዚህ ቦታ ገዳም እንዲገደም ፈቃደ እግዚአብሔር ነው ብለው ለንጉሡ ነግረው አሳመኗቸው፡፡ ንጉሡም በአካባቢው ያለውን ህዝብ በመሰብሰብ ከዛሬ ጀምሮ በዚህ ቦታ ላይ በፈቃደ እግዚአብሔር ገዳም መሥርተንላችኋል በማለት በትግዳር እና በብና በሁለቱ ወንዞች መካከል ባለው ጅራት መሰል ቦታ የመድኃኔዓለም ገዳም ተመሠረተ፡፡ ስሙም ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ጅረት መድኃኒአለም ተብሎ ይጠራል ንጉሡ ይኩኖ አምላክ በጊዜው ታቦቱን ከንጉሡ ጋር አጅበው ከነበሩት ካህናት መካከል የመጀመሪያውን አባት አባ ሲኖዲስ የተባሉትን ካህን የገዳሙ አበ ምኔት አድርገው በመሾም ወደ ሸዋ ሄዱ፡፡
#የአባ_ሲኖዲስ_ተጋድሎ፡- አባ ሲኖዲስ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የተለያየዩ ገቢረ ተአምራት በማድረግ ገዳሙን በማስፋፋት እና በአካባቢው አድባራትንና ገዳማትን በመመስረት አገልግሎት ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ ከእነሱም መካከል ዛሬ አቃቤት ኪዳነምሕረት ተብላ የምትጠራውን ሞፈር ቤት /እቃቤት/ በማድረግ፤ ቋሚ ጨርቅ እና እነጎዴ መካከል ከበረሀው ውስጥ የቅዱስ ቂርቆስን ገዳም ገድመዋል፡፡ይህንን እና ሌሎችን የትሩፋት ሥራወችን በመሥራት ገድላቸውን ፈጽመዋል፡፡

#ገዳሙ_ላይ_ይሠሩ_የነበሩ_ታላላቅ_ሥራዎች፡-

ለብዙ ዘመናት ገዳሙ እንደ ጥንታውያ ገዳማት እንደነ ዲማ ቅዱስ ጊዮርጊስ፤ እንደነ መርጡለ ማርያም እና እንደሌሎች አድባራትና ገዳማት ዘወትር ይቀደስበት ነበር፡፡ የአብነት መምህራን በአይነት ማለትም የቅኔ፡ የድጓ፡ የአቋቋም፡ የቅዳሴ እና የትርጓሜ መጻሕፍት መምህራን ነበሩበት፡፡ ሁለት አቃቢዎችም ነበሩት፡፡

#የቦታው_ቃል_ኪዳን፡- አባታችን አባ ሲኖዲስ ስለገዳሙ ቃል ኪዳን ሲቀበሉ ከገዳሙ መጥቶ የተማጸነ የረገጠ ሁሉ እምርልሀለሁ የሚል እና ገዳሙን እስከለተ ምጽዓት ፈተና ቢበዛበት እንኳን ጸንቶ እንደሚኖር ቃልኪዳን ተቀብለውበታል፡፡ በዚህ ቦታ ታሪካዊ እና ተአምረኛ ጸበል የሚገኝ ሲሆን ብዙ ሕሙማን ከቅርብም ከሩቅም እየመጡ በጠበሉ እየተጠመቁ ከደዌአቸው ይፈወሳሉ፡፡ በዚህ ቅዱስ ቦታ 3 እስከ 4 ቀን ሱባኤ የያዘ እና የተጠመቀ ፈውስ ያገኛል በተከታታይም 22 ቅዱሳን አባቶች ለገዳሙ ቃልኪዳን ተቀብለውበታል፡፡

#የጥንታዊነቱ_ማስረጃዎች፡-

ጥንታዊ ቅርሳ ቅርሶች በውስጡ ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እና ባለቤታቸው እቴጌ መነን በአንድ ወቅት የገዳሙ መነኮሳት በጸሎት እንዲያስቧቸው ከመባዕ ጋር ለገዳሙ መነኮሳት ደብዳቤ ልከው እንደነበረ እና ደብዳቤው ዛሬም ድረስ በዕቃ ቤት ይገኛል፡፡ ከታች የምትመለከቱት ፎቶ ነው፡፡ ደብዳቤው የተጻፈው ጥቅምት 30/1950 ዓ.ም ነው፡፡ ከዛሬ 62 ዓመት የተጻፈ በፊት መሆኑ ነው እንግዲህ፡፡ ኃይለ ሥላሴ ይህ ቦታ ጥንታዊ መሆኑን ስለሚያውቁም በገዳሙ የሚደረገው ጸሎትም ቅድመ እግዚአብሔር እንደሚደርስ የሚያምኑበት እንደሆነም መረዳት ይቻላል፡፡

#የገዳሙ_መተዳደሪያ፡-

ቀደም ብሎ መርጡለ ማርያም ወረዳ ይብራዛ ሥላሴ፡ እናርጅ እናውጋ ወረዳ አንጎታ ሥላሴ ፤ የዲጥ፡ ጎንቻ ሲሶ እነሴ ወረዳ ውኂዝ ኢየሱስ እና ሌሎችን ጨምሮ 21 ጉልት መተዳደሪያ ነበረው፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በገዳሙ ውስጥ ባለው ይዞታ የሰብል ልማት፤ የእንስሳት እርባታ እና የአትክልትና ፍራፍሬ ሥራ በመሥራት ይተዳደራሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በገዳሙ ውስጥ 58 መናንያን የሚኖሩ ሲሆን ወንድ 38 ሴት 20 ከእነዚህም መናንያን 43 አቅመ ደካማ ሲሆኑ መሥራት የሚችሉት ግን 15 ብቻ ናቸው፡፡ ይህም በመሆኑ ለጊዜው የገዳሙን መሬት ለአካባቢው አርሶ አደር በማከራየት በሚገኝ መጠነኛ ገቢ ይተዳደራሉ፡፡ ገዳሙ በደረሱበት የተለያየዩ ፈተናዎች እና ችግሮች ምክንያት የቀድሞ ይዞታው ባለመኖሩ በሸመት እና ልመና መተዳደር ጀምሮ ነበር አሁን ብዙ ገቢ ባይኖርም እንኳን በራሱ ለመተዳደር ጥረት እያደረገ ይገኛል

#በገዳሙ_ላይ_የደረሱ_ፈተናዎችና_አሁን_ያሉ_ችግሮች፡-

በየዘመኑ በደረሱ የተለያየዩ ችግሮች ገዳሙ በመጥፋት እና በመልማት ላይ ሲፈራረቅ ቆይቷል፡፡ በደረሰበት ፈተና መንፈሳዊ አገልግሎት ሲሰጥ ከቆየ በኋላ ገዳሙ በመፈታቱ የገዳሙ ቅርሳቅርሶች በመርጡለ ማርያም፤ በእነጎዴና ቋሚ ጨርቅ በሚገኘው በቅዱስ ቂርቆስ ዋሻ ተበትኖ ብዙ ዘመናትን ካሳለፈ በኋላ አባ ገብረማርያም በሚባሉት አበምኔት የቦታው ቅድስና ወደነበረበት እንዲመለስ በመንፈስ ቅዱስ ተገልጾላቸው ገዳሙን አቅንተው ቅርሳቅርሶችን ከያሉበት ሰብስበው ወደ ገዳሙ መልሰዋል፡፡ በአጼ ምኒልክ ዘመንሁለተኛ ጊዜ በመፍረሱ ቅርሳቅርሶች በወቅቱ ባለአባቶች /ባለርስቶች/ እጅ ቆይቷል፡፡ ታቦተ ህጉ እነጎዴ ማርያም ተደርቦ 50 ዓመታት በላይ አሳልፏል፡፡ የአቸፈር ተወላጅ የሆኑት አባ ወልደ ሐዋርያት በዲማ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዋሻ ሱባኤ ገብተው መልሰው ገዳሙን እንደሚያቀኑት በመንፈስ ቅዱስ ተነግሯቸው እንደገና 1945 . ወደ ገዳሙ መጥተው እንደገና አቋቋሙት፡፡ እኒህ አባት 1947 . ታቦተ ህጉንና ቅርሳቅርሶችን ከያሉበት ሰብስበው ወደነበሩበት መልሰዋል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስካሁን 6 አበምኔቶች አስተዳድረውታል በየተለያዩ ቦታዎች ያሉ የገዳሙ ይዞታዎች በየጊዜው በሚደረገው የመንግስት ለውጥ ተወስደዋል፡፡

#ገዳሙ_አሁን_እያጋጠመው_ያለው_ችግር፡-

1ኛ. ቤተክርስቲያኑ በዘመን ብዛት በአሁኑ ጊዜ በመፍረስ ላይ ይገኛል፡፡ (ከታች በቶው እንደምትመለከቱት በአሳዛኝ ሁኔታ ቅኔ ማኅሌቱ ፈርሷል፤ ጣሪያውም መቅደሱ ላይ የሚያፈስ መሆኑ)
2ኛ. በገዳሙ የአገልጋይ እጥረት መኖሩ 1 አባት ውጭ /ን፤ ካህን፤ መምህር ወዘተ አለመኖር እና በአሁኑ ወቅት ሁሉንም መንፈሳዊ አገልግሎት ከሌላ አካባቢ በመፈለግ አገልግሎት ማግኘቱ፡፡ በዓመት 3 ጊዜ ብቻ የሚቀደስ ሲሆን ቀዳሽ ካህናትም ከመርጡ ለማርያም እና ከዲማ የሚመጡ ናቸው፡፡
3ኛ. ከመናንያኑ ውስጥ መሥራት የሚችሉት 15 ብቻ በመሆናቸው ገዳሙን ለማስተዳደር ሌላ ፈተና መሆኑ፡፡
4ኛ. ገዳሙ የተለያየ ጸጋ ያለው ቢሆንም በዘመናዊ የገቢ ማስገኛ ውስጥ አለመግባቱ፡፡
5ኛ. በአካባቢው ያለው ህብረተሰብ እና ወረዳው ለገዳሙ ትኩረት አለመስጠቱ፡፡
6ኛ. በጥንታዊነቱ ልክ እንደሌሎች ገዳማት ባለመታወቁ ጎብኝ አለመኖር፡፡
7ኛ. የእቃቤት ባለመኖሩ ጥንታዊ እና ታሪካዊ ቅርሶች ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑ
በአሁኑ ወቅት ገዳሙ የሚፈልገው ድጋፍ፡-
1ኛ. ገዳሙን በአገር ውስጥና በውጪው ዓለም የሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን እንዲያውቁት ማድረግ፡፡ (ለዚህም ይህን መልእክት ለሌሎች ማጋራት አንዱ ኃላፊነት መወጫ መንገድ ነው፡፡)
2ኛ. በተሠራለት አዲሱ ዲዛይን መሠረት ቤተክርስቲያኑ እና ለንዋየ ቅድሳት እቃ ቤት እዲሠራለት ማድረግ፡፡
3ኛ. በበጎ አድራጊ ምዕመናን የአብነት መምህር ተቀጥሮለት ተተኪ ዲያቆናት እና ካህናት እንዲወጡበት ማድረግ፡፡
4ኛ. ለገዳሙ መተዳደሪያ የሚሆን ቋሚ የገቢ ማስገኛ ፕሮጀክት የሚሠሩ አካላትን መጋበዝ፡፡
5ኛ. በአገር ውሥጥና በውጭ የሚገኙ ምእመናን ለአዲሱ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ማሠሪያ ገንዘብ እንዲለግሱ ማድረግ፡፡
6ኛ. የገዳሙ ታሪክ እና ቅርስ በህጋዊ መንገድ EOTC ቲቪ እና በማኅበረ ቅዱሳን ቲቪ ዘጋቢ ፊልም ተሠርቶለት በሚድያ እንዲተዋወቅ ማድረግ፡፡ (ይህ ለማድረግ አሁን ገዳን እያስተዳደሩት ያሉት አባት ለዚሁ ሥራ አዲስ አበባ መሄዳቸው ጅማሬው ጥሩ መሆኑን ያሳያል፡፡)
7ኛ. በኅትመት ውጤቶች በጋዜጣና በመጽሔት እንዲተዋወቅ በማድረግ በአገርና በውጭው ዓለም የሚኖሩ ምዕመናን የቦታውን ተዓምርና በረከት ተረድተው ለገዳሙ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አድርገው እነሱም የበረከቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ ማስተለለፍ፡፡
8ኛ. በገዳሙ ውስጥ ያለው ታሪካዊ ዋሻ ሱባኤ ለሚገቡ ምዕመናን እንዲተዋወቅ ማድረግ፡፡

#የገዳሙ_እንቅስቃሴ_አሁን_ያለበት_ሁኔታ፡-

1ኛ. በማኅበረ ቅዱሳን አዲስ ለሚሠራው ቤተ ክርስቲያን ዲዛይን በነጻ ተዘጋጅቶለታል፡፡ ይህን ለማስፈጸም ይረዳ ዘንድም ዓቢይ እና ንዑስ ኮሚቴ በማዋቀር ሕንጻ ግንባታውን ለመሥራት እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ እስካሁን ድረስ በተደረገው እንቅስቃሴ 120,000 ሽህ ብር ገቢ ተሰብስቧል፡፡
2ኛ. የገዳሙን የግንባታ ፈቃድ ማስጨረስ ተችሏል፡፡
የአሁኑ የቤተክርስቲያን ሕንጻ አሰሪ ኮሚቴ ስም ዝርዝር
1. ቆሞስ አባ ዮሐንስ መርሻ ... ሰብሳቢ
2. አባ ገብረሥላሴ ታረቀኝ .........ጸሐፊ
3. አባ ጣሰው ታምሬ ............../ያዥ

#ገዳሙን_መርዳት_ለምትፈልጉ_ወገኖች_ሁሉ፡-

ጌራ መድኃኒት ጅረት መድኃኔ ዓለም አንድነት ገዳም ህንጻ ቤተ ክርስቲያን (G/M JERET M/ALEM ANDNET GEDAM HINTSA)
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሂሳ ቁጥር፡1000260115937

#ስለገዳሙ_ተጨማሪ_መረጃዎችን_ለማግኘት

የገዳሙን አስተዳዳሪ ቆሞስ አባ ዮሐንስ መርሻን በስልክ ማግኘት ይቻላል፡፡ የጸሎት ሰዓታቸውን በማይነካ መልኩ ሰዓቱን እያመቻቻችሁ ደውላችሁ መጠየቅ ትችላላችሁ፡፡ የሞባይል ስልካቸው 0912361153 ነው፡፡
*** እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ አንድ ቀን ቦታውን በአካል ተገኝቼ ተመልክቼ ያለውን ሙሉ ነገር በዓይን እንዳየ ሰው ሆኜ የምጽፍላችሁ መሆኑን አሳውቃለሁ***
(ምንጭ፡- Tewaney Betsidiq Ethiopia የፌስቡክ ገጽ፡፡)