Thursday, March 31, 2022

ገለሳ ዲልቦ ጠባያቸውን ወድጀላቸው ርእዮታቸውን (ማያቸውን) የተጸየፍኩባቸው ሰው ነበሩ በመምህር ፋንታሁን ዋቄ

ገለሳ ዲልቦ ጠባያቸውን ወድጀላቸው ርእዮታቸውን (ማያቸውን) የተጸየፍኩባቸው ሰው ነበሩ

መ/ር ፋንታሁን ዋቄ
ሁሉን የሚያውቅና የሚፈትሽ ሁሉን ቻይ አምላካችን የገላሳን ነፍሳቸውን ያሳርፍልን። ባመኑበትና በገባቸው መጠን ደክመዋል። ዜጎች የዚህ አይነት ትጋትን ከእርሳቸው መውረስ አለባቸው። ነገር ግን የተጉለት ግብና የተከተሉት ርእዮት ቀሳፊና አጥፊ ነበር። እኔ የፅናት ጠባያቸውን ለመውረስና መንገዳቸውን ለማውገዝ ብዥታ የለብኝም።

======

ለጠቅላይ ሚንስትራችንና ለሌሎች የሀዘን መግለጫችሁ ላይ "ለነፃነትና ለእኩልነት" የሚል ቃል ለተጠቀማችሁ ጥያቄ አለኝ፦

--- ገላሳ የመራው ኦነግ ውጤቱን የምናውቅና የሞት ተራችንን የምንጠብቅ እኛ ሁላችን ትምህርት

ገለሳ ዲልቦ
መቅሰሙን ትተን ክፉ ውጤት ያተረፈውን መንገድ ሁሉ ማወደስ ለምን አስፈለገ?

"ለእኩልነትና ለነፃነት ታገሉ" የምትለዋ ቃል በበደኖ፣ በአርባ ጉጉ፣ በደደር፣ በሀረዋጫ፣ በወተር፣ በቀቀሊ፣ ወዘተ እንዴት እንደምትተረጎም ትንሽ ሰርቬይ ብትሠሩ ምን እንደሚሆን ታውቃላችሁ?

እኩልነትና እኲይነት ትርጉማቸው ምን ያህል ይቀራረባል?

በዚያን በእነገላሳ ኦነግ ዘመን የደረሰበን እልቂትና ሰቆቃ አሁን በወለጋና በምዕራብ ሸዋ ከሚካሄደው ጋር በማጣመር የዚያን ዘመን የኦነግ መሪዎች እና አሁን መግለጫ የምትሰጡትን የሚያሰላስል ሰው "የቆቃ አስቀጣዮች" ብሎ ቢያማችሁ ምን መልስ አላችሁ?

አኔ ይህን መልዕክት የምጽፍ ሰው 70 ዓመት ሴት አያቴ / ሙሉነሽ በለጠ ጉደታና የመጨረሻ ልጃቸው አጎቴ ሽፈታው ተስፋዬን በግድያ ያጣሁት ገላሳ በሚመራው ኦነግ ነው። አረጋዊ አያቴ በሠይፍ ተቆራርጣ እና ወጣቱ ሽፈታው እስከነ ሕይወቱ ጥልቅ ገደል ውስጥ ተጥሎ በረሀብ ደርቆ ነው የሞተው። ያኔ ቤተሰቦቻችን ሲጨፈጨፉ ገላሳ የኦነግ መሪ ሆኖ እዚያው አካባቢ ብቅ እያለ የገበያ ቀን ለሕዝብ ንግግር ያደርግ ነበር። ለምሳሌ በደደር ከተማ።

የአያቴና የአጎቴ ወንጀል የሸዋ ኦሮሞ ኦርቶዶክስ መሆናቸው ብቻ ነበር። ይህንን ከነፃነትና ከእኩልነት ትግል እንዴት ማቆራኘት ይቻላል?? ኦርቶዶክስ የሆነ ሁሉ ጠላት እና ኦርቶዶክስ የሆነ ሁሉ ኦሮሞነት እንደማይስማማው ተደርጎ በአፍና በመጽሐፍ ባይነገረንም በተግባር ተገልፆልናል።

ሁላችንም በቅድስት ሥላሴ ስም የተጠመቅነው ሁሉ "ነፍጠኞች" ተብለናል። ከዚያም "ነፍጠኛን" ከአማራ ማቆራኘት፥ ከዚያም ማጥቃትና እየፈጁ ይህን ሂደት "የነፃነትና የእኩልነት ትግል" ብሎ መጥራት እንዴት አያሳፍርም?

ለዚያ ዘመንና አሁንም ተጠናክሮ ለቀጠለው ኦርቶዶክስን በብሔር ስም የማጽዳቱን ወንጀል በሚመለከት ተጠያቂው ማነው??? መቼ ነው ለፍትሕና ለእውነት መቆም የምንጀምረው??? መቼ ነው የጥፋቱን መንገድ ለመግታት ሐቅን የምንጋፈጠው? ነፃነትና እኩልነት የሚተረጎመው በማን ለማን ነው?