ሰላም ለሁላችሁ ይሁን፡፡ አንድ ጓደኛዬ ያጫወተኝን ጨዋታ ላካፍላችሁ ሳስብ ርእሱን ምን እንደምለው በጣም ብዙ ጊዜያትን ወስጄ ነበር፡፡ አሁን ከብዙ ድካም በኋላ ከላይ ያለውን ርእስ ሰጠሁት ፡፡ ርእሱ ምን ያህል ደረጃ እንዳለው ባላውቅም ‹‹ስትሆን አለመሆን›› በሚል ሰይሜዋለሁ፡፡ ወሬ አበዛሁባችሁ መሰለኝ… “አዎ አብዝተሃል” ይለኝ ነበር አንድ ወጣት እንዲህ የሚል ነገር ሳነሣበት፡፡ ነገር ስዘበዝብበት አይወድም ወይ ጉዴ በነገር ላይ ሌላ ነገር ደረብኩባችሁ በእርግጥ ርእሱም ‹‹ስትሆን አለመሆን›› ስለሚል መድረኩ ሲመቻችልኝ እንደ መድረኩ ሆኜ አልተገኘሁም፡፡ ነገሩ ከጓደኛዬ የተገኘ ነው፡፡ ጓደኛዬ በስእለት ይሁን በሹመት በወሬም ይሁን በሆነ አጋጣሚ ብቻ ‹‹ስልጣን›› ነገር አለችው፡፡ ብዙ ጊዜውን የሚያሳልፈው ተሸከርካሪ ወንበር ላይ ነው፡፡ ስልኩም አይቆጥርበትም መሰል የቢሮው ስልክ እንደ ሴቶች የጆሮ ጌጥ ከጆሮው ላይ ተጣብቆ ይውላል፡፡ ባለጉዳይ የሚያስተናግደው መስማት እንደተሣናቸው ወገኖቻችን በምልክት ብቻ ነው፡፡ አንድ ባለጉዳይ ባለፈው ትዝ አለኝ “ስልኩን ይጨርሳል ብዬ ወንበር ላይ ተቀምጬ ብጠብቀው! ብጠብቀው! አንዱን ሲጨርስ ሌላውን ሌላ ሲጨርስ ደግሞ ሌላውን እያለ እኔም ሲመሽብኝ ተስፋ ቆርጬ ከቢሮ ወጣሁና ጉዳዬን ስልክ ደውዬ አናገርኩት” ሲለኝ እንባ እስኪወጣኝ ድረስ ነው የሳቅሁት፡፡ በእርግጥ ጓደኛዬ ነው… ቢሆንም ግን በሰው ልጅ ላይ የሚፈጸም ታሪክ በመሆኑ ብዙም አልገረመኝም፡፡ እንዲህ አይነት ነገር በጣም ያበሳጨው የነበረ ሰው ሲበሳጭበት በነበረው ነገር ውስጥ ሲገባ በጣም ያሳዝናል፡፡ አንድ ቀን የዓመት ፈቃዱን ሊጠይቅ ወደ ቢሮ ጎራ ይላል፡፡ ከቢሮ ሲገባ ጉዳይ ያለው ሰው አልነበረም፡፡ ጉሮሮውን ሞረደና “የዓመት ፈቃድ ፈልጌ ነበር” አላቸው፡፡ አንዲት የማይመለከታት ሰራተኛ “አንተ ደግሞ ሰራተኛ ሆነህ ሞተህ የዓመት ፈቃድ ትጠይቃለህ?” አለችው፡፡ “ምን ለማለት ፈልገሽ ነው? እኔ ሠራተኛ አይደለሁም ማለት ነው? የምትሰሪልኝ ከሆነ በሥርዓት አስተናግጅኝ” በማለት ጮኸባት፡፡ ከዚያ ዚያ እየተንጎራደደች “በእርግጥ የዓመት ፈቃድ የምጽፍ እኔ አይደለሁም፡፡ እርሱ እስኪመጣ መጠበቅ ከፈለግህ ተቀምጠህ ጠብቀው አለችው፡፡” እርሱም በጣም ተናድዶ ወንበሩን ሳበና ተቀመጠ፡፡ ቢጠብቀው ቢጠብቀው በፍጹም ሊመጣለት አልቻለም፡፡ ልክ 11፡20 ሲሆን በጣም ተበሳጨና “ስልኩን ስጡኝ” አላቸው፡፡ አንዲት ስልኩን ሰጠችው ስልክ ሞከረለት፡፡ ስልኩ “ጥሪ አይቀበልም” ይላል፡፡ ከቅድሙ የባሰ አሁን ቅጥል እስኪል ድረስ ተናደደ፡፡ የቢሮውን በር በርግዶት ወጣ፡፡ ፊቱ በርበሬ መስሏል፤ ግንባሩ ተቋጥሯል፡፡ “ምን ሆነህ ነው?” አልኩት፡፡ “እባክህ የቢሯቸው ቢሮክራሲ በጣም ያናድዳል፡፡ እነዚህ ሰዎች ግን ድንጋዮች ናቸው ወይስ አስተናጋጅ ናቸው፡፡ የሰውን ጉዳይ ከምንም አይቆጥሩም እኮ፡፡ ይገርምሃል አንዲት ሰራተኛ ተብዬ በማያገባት ነገር ገብታ አንተ ደግሞ ሰራተኛ ሆነህ ሞተህ የዓመት ፈቃድ ስትል አታፍርም አለችኝ እኮ! ይች ደደብ ባልሠራላት እኔ አይደለሁም” አለኝ፡፡ “አይዞህ!!! ግን የሰውን ልጅ ያህል ፍጡር ደደብ ብለህ በመሳደብህ ቅር ብሎኛል፡፡ በእርግጥ የሰው ልጅ ወደኋላ ዞር ብሎ ያለፈ ተጋሪኩን ስለማያስታውስ ያናድድ ይሆናል፡፡ ግን ምንም ማድረግ አይቻልም ዘመኑ ነው እያልክ መቀመጥ ነው” አልኩት፡፡ “እንዴ ተው እንጅ ምን ዓይነት ጅልነት ነው የምታወራው? ዘመኑ ነው እያልክ እስከመቼ ድረስ ዝም ብለህ ትቀመጣለህ? እንደዚህ ዓይነቱን ሰው እኮ መንጥረን ማውጣት አለብን፡፡ ዘመኑ ድሮም ዘመን ነበር አሁንም ዘመን ነው እኛ ሰዎች ግን በየጊዜው እንደ እስስት እንለዋወጣለን፡፡ ብቻ ተወው የእኛ ጉድ እንዲህ በቀላሉ የሚነገር አይደለም” ብሎ በረዥሙ ተነፈሰ፡፡ “ይህ እኮ የሚያናድድ ነገር አይደለም፡፡ የሰው ልጅ እኮ ማግኘት የተመኘውን ነገር ሲያገኝ እንደ ድሮው አይሆንም አንተም ነገ ይህን ወንበር ብታገኘው ብትብስ እንጅ አትሻልም አልኩት፡፡ ድሮ ላይ የነገርኩት ነገር ዛሬ ላይ ሲፈጸም እኔ እንደ ነቢይ ትንቢት ተናጋሪ ሆኜ ራሴን አገኘሁት፡፡ ያ ድሮ ላይ ሲለው የነበረውን ነገር ዛሬ ራሱ ላይ ሲደገም በጣም ገረመኝ፡፡ ሰዎች ስለእርሱ ብዙ ነገር ሲሉኝ አንድ ቀን ስልክ ደወልኩለትና ተቀጣጠርን፡፡ በቀጠሯችን ተገናኘንና ከነገር ነገር ያን የድሯችንን ነገር ስናነሣ ስንጥል ብዙ ሰዓታትን አሳለፍን፡፡ እየተሳሳቅን “አንተስ ያው ሆነሃል አላሉ” አልኩት፡፡ “ተወው እባክህ?” አለኝ፡፡ “ግን ለምንድን ነው የሰው ልጅ ድሮ ሲበሳጭበት በነበረው ነገር ውስጥ ራሱ የሚወድቅ? አልኩት፡፡ እርሱም ብዙ ሳያስብ በሳቅ ፍርስ የሚያደርገውን ንግግር ነገረኛ!፡፡ “ምን መሰለህ የሰው ልጅ ድሮ በተጎዳበት ነገር ይጎዳበታል እንጅ አይጠቅምበትም፤ ሰው ድሮ በተበሳጨበት ነገር ያበሳጭበታል እንጅ አያስደስትበትም፤ ሰው ድሮ በታሰረበት ነገር ያስርበታል እንጅ አይፈታበትም፡፡ ድሮ ላይ እኔ እበሳጭ የነበረው እኮ እነርሱ ቦታ ላይ እኔ ስላልሆንኩ ነው፡፡ ዛሬ ግን እኔ በእነርሱ ቦታ ላይ ስላለው በራሴ ስለማልበሳጭ ሌሎች በእኔ መበሳጨት አለመበሳጨታቸው አይገባኝም፡፡ እኔ ጥሩ የሰራሁ እንጅ መጥፎ ነገር ያደረግሁ አይመስለኝም፡፡ ጠቅለል ሲል ‹‹ስትሆን አትሆንም›› ማለቴ ለመሆን የተመኘኸውን ነገር ስትሆን ድሮ እንደተመኘኸው አትሆንም፡፡ በእጅ የያዙት ወርቅ ከመዳብ ይቆጠራል ይሉ የለም፡፡ ተማሪ ሆነህ ሰራተኞችን ስታይ እንደእነርሱ መሆንን ትሻለህ፡፡ ነገር ግን አንተ ያንን የተመኘኸውን ስትሆን አትሰራበትም፡፡ ስንቱ ሰዎችን ሲኮንን በነበረበት ሃሳብ ገብቶ አይደል እንዴ ራሱ የሚሠራው፡፡ ሙስና የሚፈጽም ሰራተኛ ያየ ሰው ለምን ሙስና ይፈጽማል ብሎ ይደነፋል፡፡ ነገ በዚያ ሰው ቦታ ሲቀመጥ ግን የበለጠ ሙስና ሰሪ ራሱ ይሆናል፡፡ መሆን እና መናገር እኮ የሰማይ እና የምድርን ያህል ይራራቃሉ፡፡ ሰው የተባለ ፍጡር በአጠቃላይ “ሲሆን አይሆንም” --› ታማኝ አይሆንም ማለቴ ነው፡፡ የሚፈልገውን ነገር ሲያገኝ እንደሞፈልገው ሆኖ አይገኝም” አለኝ፡፡ እኔም በጣም ገረመኝና በሳቅ ተለያየን፡፡
Thursday, October 30, 2014
Tuesday, October 7, 2014
ንቁም በበሕላዌነ / በያለንበት ጸንተን እንቁም/
ማተባችን መለያ ማኅተማችን ነው፡፡ |
Subscribe to:
Posts (Atom)