Tuesday, October 7, 2014

ንቁም በበሕላዌነ / በያለንበት ጸንተን እንቁም/

ማተባችን መለያ ማኅተማችን ነው፡፡
በሥነ ፍጥረት ታሪክ ላይ የመጀመሪያዎቹ ፍጥረታት ላይ ማለትም በመላእክት ዘንድ የተፈጠረ ሽብር ነበር፡፡ የሽብሩ ቀስቃሽ የዚያን ጊዜ አኃዜ መንጦላእት የነበረው በክብር ስሙ ሳጥናኤል በውርደት ስሙ ደግሞ ዲያብሎስ ነበር፡፡ ዲያብሎስ ቀና ቢል ከእርሱ የበለጠ ፍጡር አጣ ፈጣሪም ተሰውሮበታልና ባለማስተዋል ዝቅ ብሎ ሲመለከት እልፍ አእላፋት መላእክትን ተመለከተ፡፡ ያን ጊዜ “አነ ፈጣሪሆሙ ለእሉ ፍጡራን” ብሎ አረፈው፡፡ ምን ማለት ነው “እነዚህን ሁሉ የፈጠርኳቸው እኔ ነኝ” አለ፡፡ ልብ በሉ ወገኖቼ በማእረግ ከሌሎች መብለጥ ወይም ከሌላው በስልጣን ከፍ ብሎ መገኘት ማለት መፍጠር ማለት አይደለም፡፡ ምናልባት ከአንተ በላይ ሌላ የሚበልጥህ ነገር ላይኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን ከአንተ በታች ያለውን ሁሉ የፈጠርከው አንተ አይደለህም፡፡ የሳጥናኤል ጉዳይ ግን ይህ ነበር፡፡ ከእርሱ በታች እልፍ አእላፋት መላእክት ስለተረበረቡ የእነዚያ ሁሉ ፈጣሪ እርሱ እንደሆነ አሰበ አስቦም ተናገረ ተናግሮም አሸበረ፡፡ በዚህ ሽብር መካከል እርሱን ተከትልው የሄዱ ነበሩ፡፡ ነገር ግን እርሱን የተጠራጠሩም ነበሩ፡፡ እርሱን መጠራጠር ብቻም አይደለም አምላክ አይደለም ብለው ያመኑ መላእክት ነበሩ፡፡ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል “ንቁም በበሕላዌነ / በያለንበት ጸንተን እንቁም/” በማለት መላእክትን አጽናናቸው፡፡ ሽብሩን ዲያብሎስ ቢፈጥረውም ቅሉ በቅዱስ ገብርኤል ከሽፎበታል ምንም እንኳ የተወሰኑ ተከታዮችን ይዞ ቢጠፋም፡፡ ወገኖቼ ከመቸውም በላይ በቅዱስ ገብርኤል ቃል የምንጽናናበት ዘመን ዛሬ ነው፡፡ ማንም ምንም ሊል ይችላል፡፡ ከእኔ በላይ ማንም የለም ብሎ የሚያስብ ሰው በርካታ ነገሮችን ሊናገርና ሽብርና ሁከትን ሊፈጥር ይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ለሁሉም ጊዜ አለውና ቅዱስ ገብርኤል በያላችሁበት ጸንታችሁ ቁሙ ማንም አያስፈራችሁ የሚልበትን ሰዓት መጠበቅ አለብን፡፡ አንድ ፈራሽ በስባሽ ሰው ማተብህን አታስርም ስላለኝ ማተቤን አልበጥሰውም ይህን በሚገባ አውቀዋለሁ፡፡ ከእርሱ በላይ ሌላ አካል የሌለ የሚመስለው አእምሮ ቢስ ሁሉንም በእርሱ ቁጥጥር ሥር ማኖር ይፈልጋል፡፡ ነገር ግን ከእርሱ የበለጠ አካል ፈጣሪያችን የተሰቀለበትን መስቀል እናስረዋለን፡፡ በዚህም ብዙ ዘመናትን አሳልፈናል ወደፊትም እንዲሁ እናደርጋለን፡፡ የትምህርት ተቋማት ከዚህ ነጻ ናቸው ካሉንም ትምህርቱ እና ሥራው ይቀራል እንጅ ማተቡ መታሰሩ አይቀርም ፡፡ ማተብ ሌላ ጉዳይ ነው ትምህርት ደግሞ ሌላ ነው፡፡ ምንም ሊገናኙ የሚችሉ ጉዳዮች አይደሉም፡፡ ወገኖቼ ማንም ምንም ነገር ስለተናገረ ብቻ አትሸበሩ፡፡ ይህ ሽብር የተጀመረው በመላእክት ዘንድ ነው፡፡ አሁን ደግሞ በእኛ መካከል ተፈጠረ ይሁን እንጅ በያለንበት ጸንተን ልንቆም ያስፈልገናል፡፡ በያሉበት ጸንተው የቆሙት ፈጣሪያቸውን አግኝተውታል፡፡ እኛም እንዲሁ ጸንተን እንቆይ ፈጣሪያችንን እናገኘዋለን፡፡ አትጠራጠሩ ይህን ሃሳባ ያመጣው ሰው እንጦሮጦስ ይወርዳል ምክንያቱም ሃሳቡ ዲያብሎሳዊ ስለሆነ፡፡ በእርግጥ ዘመኑ ዘመናቸው ጊዜው ጊዜያቸው ነው ነገ ደግሞ የሌላ ዘመንና ጊዜ ነው፡፡ ስለዚህ ጸንተን እንቆይ፡፡ አንድ ተራ ሰው በተናገረው ተራ ወሬ ቦታ ሰጥታችሁ አትሸበሩ፡፡

No comments:

Post a Comment