Friday, December 30, 2016

“እርሷ እናቴ ናት!”


© መልካሙ በየነ
ታህሳስ 21/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT, LIKE ያድርጉ፡-
==============================================
የሰማያዊው ንጉሥ የመድኅን ክርስቶስ እናቱ የሆነች ድንግል በክልኤ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሥም አጠራሯ ከፍ ከፍ ይበልና እናቴ መመኪያ ዘውዴ የመወደድ ግርማ ሞገሴ እርሷ ናት፡፡ በብርሃን መውጫ ምሥራቅ የተመሰለች እውነተኛ ብርሃን ኢየሱስ ክርስቶስን ያስገኘችልን እርሷ እናቴ  ናት፡፡ ከሩቅ እንደ ፋና የምታበራ ለእውራን ብርሃናቸው ለኃንካሳዎችም ምርኩዛቸው ለተራቡትም ምግባቸው ለተጠሙትም መጠጣቸው እርሷ እናቴ  ናት፡፡ ሰባ ስምንት ሰዎችን የበላውን የበላኤ ሰብእን ነፍስ አማልዳ ገነትን እንድትወርስ ያደረገች የበላኤ ሰብእ እመቤት እርሷ እናቴ  ናት፡፡ የሌሊቱ ጨለማ የተገፈፈባት እውነተኛ ብርሃን ያየንባት የእርቅ ምልክታችን የመግባቢያ ሰነዳችን እርሷ እናቴ  ናት፡፡ የአዳም ፍዳ እንደ ደንጊያ ከላያችን ላይ ተጭኖ የቅድስና ሰማይን ቀና ብለን እንዳናይ ሲያደርገን ፈጥና ደርሳ ከላያችን ላይ የወረወረችልን እርሷ እናቴ  ናት፡፡ በሄዋን ምክንያት የተድላ የደስታ ቦታችን ገነት ተዘግቶብን ለ5500 ዘመናት ያህል በእግረ አጋንንት ስንረገጥ እና ስንጠቀጠቅ ብንኖርም ዘመኑ ሲደርስ ገነትን ከፍታ ግቡ ያለችን ደግ እመቤት እርሷ እናቴ ናት፡፡ ስሄድ አብራኝ የምትሄድ ስጓዝ አብራኝ የምትጓዝ መንገዴን ቀድማ የምታስተካክልልኝ ከፊቴ ሆና የምትመራኝ እርሷ እናቴ ናት፡፡ በማድርበት የምታድር በእንግድነቴም የምታረጋጋኝ እና የምታጽናናኝ እርሷ እናቴ ናት፡፡ ማንነቴ የተመሠረተባት እኔነቴን ያወቅሁባት እርሷ እናቴ  ናት፡፡

መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ፈርቶ እና አክብሮ “ትጸንሻለሽ ወንድ ልጅንም ትወልጃለሽ” ብሎ ያበሠራት እርሷ እናቴ  ናት፡፡ የዓለም መድኃኒት አምላክን በበረት የወለደችው በጨርቅ የጠቀለለችው እርሷ እናቴ ናት፡፡ የሥላሴን አንድነት እና ሦስትነት በሚገባ ያስተማረችን ረቂቅ ምሥጢርን ያሳየችን እርሷ እናቴ ናት፡፡ እሳትን በማኅጸኗ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን የተሸከመች እርሷ እናቴ ናት፡፡ እሳተ መለኮትን የታቀፈች ኀሊበ ድንግልናዋን ያጠባች እርሷ እናቴ ናት፡፡ ከሔሮድስ ሸሽታ የተወደደ ልጇን ይዛ ከዮሴፍና ከሰሎሜ ጋር በግብጽ በረሃ የተሰደደችው የተንከራተተችው እግሯ በእሾህ እና በስለት ድንጋይ ደም ያጎረፈው እርሷ እናቴ ናት፡፡ የተወደደ ልጇ በማእከለ ምድር በቀራንዮ ለዓለም ቤዛ ሆኖ በእንጨት መስቀል ላይ በአደባባይ ተሰቅሎ ባየችው ጊዜ መሪር እንባን ያነባችው ከመስቀሉ ሥር የተገኘቸው እርሷ እናቴ  ናት፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዮሐንስ እነኋት እናትህ ብሎ የሰጠው እርሷንም አነሆ ልጅሽ ብሎ የሰጣት አዛኝቷ እመቤት እርሷ እናቴ ናት፡፡ እውነተኛ መብልን እና እውነተኛ መጠጥን ያስገኘችልን ቤተ ልሄም እርሷ እናቴ  ናት፡፡ በኃጢአት ስወድቅ በንስሐ የተነሣሁባት ምርኩዝ ድጋፌ እርሷ እናቴ ናት፡፡ ለተጠማ ውሻ በወርቅ ጫማዋ ውኃ ቀድታ የምትሰጥ ርኅርኅተ ልብ እመቤቴ እርሷ እናቴ ናት፡፡ ለኃጥአን የምትራራ አማልዳ ገነት መንግሥተ ሰማያት የምታገባ እመቤቴ እርሷ እናቴ ናት፡፡ መርኅ ለመንግሥተ ሰማያት የተባለች ገነት መንግሥተ ሰማያት እየመራች የምታገባ ንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም እርሷ እናቴ  ናት፡፡ ለጠፋው በግ አዳም መገኘት ምክንያት የሆነችው ንጽህት ዘር እርሷ እናቴ ናት፡፡ የአዳም መርገም ያላገኛት ከፍጡራን ሁሉ በላይ የሆነች ልዩ ዘር እርሷ እናቴ ናት፡፡ ስሟ ከማር ከወተት ይልቅ የሚጥመው እርሷ እናቴ ናት፡፡ ምግበ ሥጋ እና ምግበ ነፍስን ያገኘንባት የወርቅ መሶብ እርሷ እናቴ ናት፡፡ መላእክት የሰውን ልመና ወደ አምላክ ለማድረስ የሚወጡባት እና የአምላክን ምሕረት ቸርነት ረድኤት ለሰዎች ለማድረስ የሚወርዱባት የወርቅ መሰላል የመገናኛ ድልድይ እናታችን እርሷ ናት፡፡

መናፍቃን እና አጋንንት የሚርዱላት የሚንቀጠቀጡላት የመፈራት ግርማ ሞገስን የተጎናጸፈች እርሷ እናቴ ናት፡፡ ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች የተባለላት የንጉሡ እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርም እርሷ እናቴ ናት፡፡ ሙሴ በነደ እሳት ጫፎቿ ሳይቃጠሉ ባያት ዕጽ የምትመሰል የመለኮት እናት ድንግል ማርያም እርሷ እናቴ  ናት፡፡ ሳይተክሏት እና ውኃ ሳያጠጧት ለምልማ አፍርታ በተገኘችው በትረ አሮን የምትመሰለው እመቤቴ እርሷ እናቴ ናት፡፡ እውነተኛ ዝናም ያገኘንባት እውነተኛ ደመናችን ድንግል ማርያም እርሷ እናቴ ናት፡፡ ስለምናት ከዓይን ጥቅሻ ፈጥና የምትደርስልኝ የችግሬ ደራሽ እመቤቴ እርሷ እናቴ ናት፡፡

ፍቅሯ ያልገባችሁ መናፍቃን እና አጋንንት የምትሉትን በሉ እንጅ የእናቴ ስሟ በደሜ ውስጥ ይዘዋወራል ፍቅሯም በልቤ ጽላት ታትሞ ለዘላለም ይኖራል፡፡ ምክንያቱም በአርባ ቀኔ የበላሁት ሥጋ እና የጠጣሁት ደም ከእርሷ የተገኘውን ነውና፡፡ ደሟ ደሜ ሥጋዋም ሥጋየ ሆኗል፡፡ ስለዚህም እርሷ እናቴ ናት!!!!

Tuesday, December 20, 2016

“ድንቅ ነገር የተደረገብሽ ድንግል ሆይ!”

© መልካሙ በየነ

ታህሳስ 11/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT, LIKE ያድርጉ፡-
==============================================
ቅዱሳን ስለእናታችን ስለቅድስት ድንግል ማርያም አመስግነው እና አስተምረው፣ ሰብከው እና አመስጥረው፣ አርቅቀውና አጉልተው ተናግረው በዚህም አገልግሎታቸው ረክተው እና ጠግበው አያውቁም፡፡ ሌሊት በሰዓታቱ ንዒ እያሉ ተአምሯን እና ድንቅ ሥራዋን ሲያሰሙን እናታችንን ሲያመሰግኗት ያድራሉ፡፡ ጠዋት በኪዳኑም “ዘተወልደ እማርያም እምቅድስት ድንግል” ብለው እናታችንን ያነሧታል፡፡ በሰርክ በቅዳሴውም እናታችን ድንግል ማርያምን ያመሰግኗታል፡፡ እንግዲህ ካህናቱ እንዲህ ለ24 ሰዓታት ያህል አመስገነው ስሟን አንሥተው አይጠግቡም አይረኩምም፡፡ ምስጋናዋ የበዛላቸው እነ ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴዋ እነ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴዋ እነ አባ ጊዮርጊስ በሰዓታቷ እነ አባ ጽጌ ድንግል በማኅሌተ ጽጌ እነ ቅዱስ ያሬድ በአንቀጸ ብርሃን ምስጋናቸው በብዙ አምሳል በብዙ መልክእ አመስግነዋታል፡፡ ሆኖም ግን አልጠገቡም አልረኩምም፡፡ ለምን ምስጋናዋን አልጠገቡም ቢሉ በእናታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ድንቅ ነገር ስለተደረገባት ነው፡፡ በእርሷ ድንቅ ነገር ተደርጓል ረቂቅ ምሥጢር ተፈጽሟል፡፡

ድንግል ሆይ ይህን ባንች የተደረገውን ድንቅ ምሥጢር ግለጭልኝ! ይህን ባንች የተደረገውን ረቂቅ ምሥጢር አጉልተሸ አሳይኝ! ድንግል ሆይ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው እሳተ መለኮትን ከወዴት አስቀመጥሽው ብሎ ጠይቆሽ ነበር፡፡ ሁሉ የእርሱ ሁሉ በእርሱ የሆነን አምላክ እንዴት ወለድሽው ይህ ድንቅ ነገር እጹብ እጹብ ሲባል ይኖራል እንጅ በሥጋ ዓይን ረቂቅ ምሥጢር ነው፡፡ እናቴ ሆይ! ከሃና እና ከኢያቄም በዘር በሩካቤ እንድትወለጅ የፈጠረሽን አምላክ እንዴት ወለድሽው፡፡ ድንግል ሆይ! በምጥ በልብ ጋር ከሃና ማኅጸን የተወለድሽ ስትሆኝ ያለምጥ ያለልብ ጋር ፈጣሪን እንዴት አስገኘሽልን፡፡ ድንግል ሆይ! ከአባት እና ከእናት ስትወለጅ ቀድሞ ያለእናት ከአብ የተወለደውን ዛሬ ያለ አባት እንዴት ወለድሽው፡፡ ድንግል ሆይ! ሴቶች ሁሉ ድንግል ሆነው መውለድ የማይቻላቸው ሆኖ ሳለ አንች ግን በፍጹም ድንግልና አምላክን ለመውለድ በቃሽ ይህ ድንቅ ነገር እንዴት ተፈጸመልሽ፡፡ ድንግል ሆይ! ሰማይ መንበሩ ምድርም የእግሩ መረገጫ የሆነው አምላክ ማኅጸንሽ እንዴት ሊወስነው ቻለ፡፡ ድንግል ሆይ! ልብሱ እሳት ክዳኑ እሳት እየተባለ የሚመሰገነውን አምላክ በማኅጸንሽ ስትሸከሚው እሳተ መለኮቱ እንዴት አላቃጠለሽም፡፡ ድንግል ሆይ! ኪሩቤልና ሱራፌል ፈርተውና አፍረው ብርሃነ መለኮትህን ማየት አይቻለንም፤ እሳተ መለኮትህም ያቃጥለናል ሲሉ  ፊታቸውን በመስቀል ምልክት አመሳቅለው የሚያመሰግኑትን አምላክ ማኅጸንሽ እንዴት ተሸከመው፣ ያለበሽው ጨርቅስ እንዴት ልብስ ሆነው፡፡

ድንግል ሆይ! ባንች የተፈጸመው ድንቅ ነገር ለማንም ያልተደረገ ለማንም የማይደረግ ረቂቅ ነገር ነው፡፡ ኅብስተ ሕይወት ጌታን ያስገኘሽልን ድንግል ሆይ እናመሰግንሻለን ከፍ ከፍም እናደርግሻለን፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋየን የበላ ደሜንም የጠጣ የዘላለም ሕይወትን ይወርሳል በማለት ያስተማረን ካንች የነሣውን ሥጋና ደም እንበላ እና እንጠጣ ዘንድ ነው፡፡ በሄዋን ምክንያት የተዘጋ ገነት የተከፈተብሽ ድንግል ሆይ ባንች ድንቅ ነገር ረቂቅ ምሥጢር ተደረገልን፡፡ ካንች የተዋሐደውን ሥጋ እና ደም ተቀብለን  ገነት መንግሥተ ሰማያትን የምንወርስብሽ ድንግል ሆይ እናመሰግንሻለን፡፡ በድቅድቅ ጨለማ ሳለን ብርሃን የተመለከትንብሽ የብርሃን እናቱ ድንግል ማርያም ሆይ እናመሰግንሻለን፡፡ በማኅጸን የፈጠረሽን አምላክ በማኅጸንሽ የተሸከምሽ ቅድስት ሆይ እናከብርሻለን፡፡ በዘር በሩካቤ ተፈጥረሽ ያለዘር ያለሩካቤ አምላክን ያስገኘሽልን ድንግል ሆይ እናገንሻለን፡፡ ድንግልናዋን ከአጣች እናት ተወልደሽ በድንግልና አምላክን በመውለድሽ ከፍከፍ እናደርግሻለን፡፡