© መልካሙ በየነ
ታህሳስ
11/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም
facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT,
LIKE ያድርጉ፡-
==============================================
ቅዱሳን ስለእናታችን ስለቅድስት ድንግል ማርያም አመስግነው እና
አስተምረው፣ ሰብከው እና አመስጥረው፣ አርቅቀውና አጉልተው ተናግረው በዚህም አገልግሎታቸው ረክተው እና ጠግበው አያውቁም፡፡ ሌሊት
በሰዓታቱ ንዒ እያሉ ተአምሯን እና ድንቅ ሥራዋን ሲያሰሙን እናታችንን ሲያመሰግኗት ያድራሉ፡፡ ጠዋት በኪዳኑም “ዘተወልደ እማርያም
እምቅድስት ድንግል” ብለው እናታችንን ያነሧታል፡፡ በሰርክ በቅዳሴውም እናታችን ድንግል ማርያምን ያመሰግኗታል፡፡ እንግዲህ ካህናቱ
እንዲህ ለ24 ሰዓታት ያህል አመስገነው ስሟን አንሥተው አይጠግቡም አይረኩምም፡፡ ምስጋናዋ የበዛላቸው እነ ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴዋ
እነ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴዋ እነ አባ ጊዮርጊስ በሰዓታቷ እነ አባ ጽጌ ድንግል በማኅሌተ ጽጌ እነ ቅዱስ ያሬድ በአንቀጸ ብርሃን
ምስጋናቸው በብዙ አምሳል በብዙ መልክእ አመስግነዋታል፡፡ ሆኖም ግን አልጠገቡም አልረኩምም፡፡ ለምን ምስጋናዋን አልጠገቡም ቢሉ
በእናታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ድንቅ ነገር ስለተደረገባት ነው፡፡ በእርሷ ድንቅ ነገር ተደርጓል ረቂቅ ምሥጢር ተፈጽሟል፡፡
ድንግል ሆይ ይህን ባንች የተደረገውን ድንቅ ምሥጢር ግለጭልኝ!
ይህን ባንች የተደረገውን ረቂቅ ምሥጢር አጉልተሸ አሳይኝ! ድንግል ሆይ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው እሳተ መለኮትን ከወዴት አስቀመጥሽው
ብሎ ጠይቆሽ ነበር፡፡ ሁሉ የእርሱ ሁሉ በእርሱ የሆነን አምላክ እንዴት ወለድሽው ይህ ድንቅ ነገር እጹብ እጹብ ሲባል ይኖራል እንጅ
በሥጋ ዓይን ረቂቅ ምሥጢር ነው፡፡ እናቴ ሆይ! ከሃና እና ከኢያቄም በዘር በሩካቤ እንድትወለጅ የፈጠረሽን አምላክ እንዴት ወለድሽው፡፡
ድንግል ሆይ! በምጥ በልብ ጋር ከሃና ማኅጸን የተወለድሽ ስትሆኝ ያለምጥ ያለልብ ጋር ፈጣሪን እንዴት አስገኘሽልን፡፡ ድንግል ሆይ!
ከአባት እና ከእናት ስትወለጅ ቀድሞ ያለእናት ከአብ የተወለደውን ዛሬ ያለ አባት እንዴት ወለድሽው፡፡ ድንግል ሆይ! ሴቶች ሁሉ
ድንግል ሆነው መውለድ የማይቻላቸው ሆኖ ሳለ አንች ግን በፍጹም ድንግልና አምላክን ለመውለድ በቃሽ ይህ ድንቅ ነገር እንዴት ተፈጸመልሽ፡፡
ድንግል ሆይ! ሰማይ መንበሩ ምድርም የእግሩ መረገጫ የሆነው አምላክ ማኅጸንሽ እንዴት ሊወስነው ቻለ፡፡ ድንግል ሆይ! ልብሱ እሳት
ክዳኑ እሳት እየተባለ የሚመሰገነውን አምላክ በማኅጸንሽ ስትሸከሚው እሳተ መለኮቱ እንዴት አላቃጠለሽም፡፡ ድንግል ሆይ! ኪሩቤልና
ሱራፌል ፈርተውና አፍረው ብርሃነ መለኮትህን ማየት አይቻለንም፤ እሳተ መለኮትህም ያቃጥለናል ሲሉ ፊታቸውን በመስቀል ምልክት አመሳቅለው የሚያመሰግኑትን አምላክ ማኅጸንሽ እንዴት
ተሸከመው፣ ያለበሽው ጨርቅስ እንዴት ልብስ ሆነው፡፡
ድንግል ሆይ! ባንች የተፈጸመው ድንቅ ነገር ለማንም ያልተደረገ
ለማንም የማይደረግ ረቂቅ ነገር ነው፡፡ ኅብስተ ሕይወት ጌታን ያስገኘሽልን ድንግል ሆይ እናመሰግንሻለን ከፍ ከፍም እናደርግሻለን፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋየን የበላ ደሜንም የጠጣ የዘላለም ሕይወትን ይወርሳል በማለት ያስተማረን ካንች የነሣውን ሥጋና ደም እንበላ
እና እንጠጣ ዘንድ ነው፡፡ በሄዋን ምክንያት የተዘጋ ገነት የተከፈተብሽ ድንግል ሆይ ባንች ድንቅ ነገር ረቂቅ ምሥጢር ተደረገልን፡፡
ካንች የተዋሐደውን ሥጋ እና ደም ተቀብለን ገነት መንግሥተ ሰማያትን
የምንወርስብሽ ድንግል ሆይ እናመሰግንሻለን፡፡ በድቅድቅ ጨለማ ሳለን ብርሃን የተመለከትንብሽ የብርሃን እናቱ ድንግል ማርያም ሆይ
እናመሰግንሻለን፡፡ በማኅጸን የፈጠረሽን አምላክ በማኅጸንሽ የተሸከምሽ ቅድስት ሆይ እናከብርሻለን፡፡ በዘር በሩካቤ ተፈጥረሽ ያለዘር
ያለሩካቤ አምላክን ያስገኘሽልን ድንግል ሆይ እናገንሻለን፡፡ ድንግልናዋን ከአጣች እናት ተወልደሽ በድንግልና አምላክን በመውለድሽ
ከፍከፍ እናደርግሻለን፡፡
No comments:
Post a Comment