© መልካሙ በየነ
የካቲት
21/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም
facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT,
LIKE ያድርጉ፡-
==============================================
በመጀመሪያ እንኳን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል
ማርያም ወርኃዊ በዓል በሰላም በፍቅር በአንድነት አደረሳችሁ፡፡ መዋእለ ጾሙን በሰላም በፍቅር አስፈጽሞ ለብርሃነ ትንሣኤው ያደርሰን
ዘንድ የአብ ልጅ የድንግል ልጅ ፈቃዱ ይኹንልን፡፡ አሜን፡፡
በክፍል ፩ ሮማውያን በተዋሕዶ እምነታችን ላይ ቀስታቸውን
ሊወረውሩ ሲዘጋጁ ንጉሡ ዐፄ ገላውዴዎስ የኢትዮጵያን ሊቃውንት ሰብስቦ ምን እናድርግ ብሏቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሊቃውንትም ፍርድ በቃ
ይስጡን እንከራከርና ሮማውያን ቢረቱን እንልቀቅላቸው ብንረታቸው ይልቀቁልን አሏቸው፡፡ ንጉሡም ፈቅደው ጉባዔ ተደረገ ለኢትዮጵያ
ሊቃውንት አፈ ጉባኤ ዝክሪና ጳውሊ ኾኑ፡፡ ዝክሪና ጳውሊም በጎጃም ጠቅላይ ግዛት በዲማ ቅዱስ ጊዮርጊስ አጠገብ የሚገኝ የደብረ
ጽሙና ገዳም ሊቃውንት እንደሆኑ ዓይተናል፡፡
እየጻፍኩላችሁ ያለሁት ከራሴ ከመነጨ የመታጀር እውቀት
አይደለም በክፍል ፩ እንደገለጽኩላችሁ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ ካሳተሙት መድሎተ አሚን ከተሰኘው ድንቅ መጽሐፋቸው ከመቅድም
ክፍላቸው ላይ በቀጥታ ገልብጨ ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንድ የቅብአት እምነት ገብቶናል የሚሉ ጥቃቅን ቀበሮዎች መልአከ ብርሃን አድማሱ
ጀንበሬ ከጥንት የታሪክ መጽሐፍ ወስደው የጻፉትን ታሪክ እኔ ስጽፈው ሲያዩ ታሪክ አበላሽተሃል ብለው ይዘላሉ፡፡ የሚገርመው ይህ
መጽሐፍ የታተመው ዛሬ አለመሆኑ ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ ጥንት የተጻፈ ነው (በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት) ታዲያ ያን ጊዜ
መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ ተሳስተዋል ባሏቸው ነበር፡፡ ግን የት አሉ ስም አጠራር የላቸውም ነበርና ተደብቀው ውስጥ ውስጡን
እንደ ፍልፈል የምንፍቅና ጉድጓድ ይምሱ ነበር፡፡ ይህ መጽሐፍ በዕድሜ ቢያንስ የእነዚህን የጥቃቅን ቀበሮዎችን ዕድሜ ሳይበልጥ አይቀርም፡፡
እኔም እየጻፍኩላችሁ ያለሁት ከዚህ የቤተክርስቲያናችን ድንቅ መጽሐፍ እንጅ በድብቅ፣ በስርቆት ማተሚያ ቤቱ እንኳ ማን እንደሆነ
ሳይታወቅ እንደታተመው እንደ “ወልደ አብ” ካለ የክህደት መጽሐፍ ላይ አይደለም፡፡ ስለዚህ ይህ የመቅድም ገጻቸውን አሁንም እጽፍላችኋለሁ
መልካም ንባብ!!!
ኹለተኛ
ጥያቄ፡
ከጥቂት ጊዜ በኋላ አንድ ሮማዊ ተነሥቶ መለኮት ሥጋ
አልሆነም ሥጋም መለኮት አልሆነም ሥጋ ለመለኮት እንደ ብረት ልብስ እንደ ጥሩር ኾነው መለኮትና ሥጋ እንደ ኀዳሪና ማኅደር ኾነው
መለኮት የመለኮትን ሥራ ትስብእትም የትስብእትን ሥራ ሲሰሩ ኖረው በዕርገቱ ጊዜ የለበሰውን ሥጋ አውልቆ በሦስተኛው ሰማይ አኑሮት
በየማነ አብ በዘባነ ኪሩብ ተቀመጠ፡፡ የዚህም ምሳሌው አንድ ንጉሥ ለጦርነት ወደ ሰልፍ ሲገባ የጦርነት ልብስ ይለብሳል፡፡ ሲዋጋ
ውሎ ድል ካደረገ በኋላ የለበሰውን የጦር ልብስ አውልቆ ከግምጃ ቤት ሰቅሎ ልብሰ መንግሥቱን ለብሶ በዙፋኑ ላይ እንደሚቀመጠው ያለ
ነው እንጅ ትስብእቱን ከመለኮቱ ጋራ በአባቱ ቀኝ አያስቀምጠውም አለ፡፡
አባ ዝክሪ ሲመልስ ነፍስ ርቀቷን ሳትለቅ ሥጋ ግዙፍ
ውሱን መኾኑን ሳይለቅ ተዋሕደው አንድ ሰው እንዲኾኑ መለኮት ምልዐቱን ስፍሐቱን ርቀቱን ሳይለቅ ትስብእትም ግዙፍነቱን ውሱንነቱን
ሳይለቅ በተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ኾኗል እንጅ እንደ ልብስና እንደ ገላ አይደለም አለ፡፡
ሮማዊ መለኮት ከደረሰበት ኹሉ ይህ መዋቲ ትስብእት
ደረሰ ትላለህን አለ፡፡
አባ ዝክሪ ሲመልስ እኔስ መለኮት እና ትስብእት በተዋህዶ
አንድ ስለሆኑ መለኮት በሥጋ ውሱን ግዙፍ ኾነ፤ ትስብእትም በመለኮት ምሉዕ ስፉሕ ረቂቅ ኾነ እላለሁ፡፡ ትስብእት ከመለኮት ተለይቶ
በሦስተኛው ሰማይ እንዳልቀረ በየማነ አብ በዘባነ ኪሩብ እንደተቀመጠም
ሲያስረዳ አሜሃ ትሬእይዎ ለወልደ እጓለ እመሕያው እንዘ ይነብር በየማነ እግዚአብሔር ብሏል፡፡ በክበበ ትስብእት በግርማ መለኮት
ዳግም እንዲመጣ ሲያስረዳም ወአመ ይመጽእ ወልደ እጓለ እመሕያው በስብሐተ አቡሁ ወኲሎሙ መላእክቲሁ ምስሌሁ ብሏል፡፡ ይህ ንባብ
በቅዱስ ወንጌል መጻፉን ታምናለህ ትክዳለህ? አለው፡፡ ሮማዊ መልስ አጥቶ ዝም አለ፡፡
ሦስተኛ
ጥያቄ፡፡
ሮማዊ እኔ ክርስቶስን ፍጡር እለዋለሁ አለ፡፡
አባ ጳውሊ ሲመልስ ክርስቶስን ፍጡር የሚል ንባብ
ከምን ታገኛለህ አለው፡፡
ሮማዊ አምላክ ከኾነ ከሣምራዊት ውኃ እስኪለምን ድረስ
ለምን ተጠማ ከላይ ያለው ሐኖስ ከታች ያለው ውቅያኖስ በመኃል እጁ ሲሆን አምላክ ይጠማልን አለ፡፡
አባ ጳውሊ ሲመልስ ፍጡር ከኾነ የእግዚአብሔርንስ
ስጦታ አውቀሽ ቢኾን ይህ ውኃ አጠጭኝ ብሎ የሚለምንሽ ማን እንደሆነ ተገንዝበሽ አንች የሕይወት ውኃን አጠጣኝ ብለሽ በለመንሺው
ነበረ እርሱም በሰጠሸ ነበረ ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ኹሉ ዳግመኛ ይጠማል እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ግን ዳግመኛ ይህ እኔ የምሰጠው
ውኃ ለዘላለም ሕይወት ሊኾነው ከውስጡ ሲመነጭ ይኖራል እንጅ ዳግመኛ አይጠማም ለምን አላት አለው፡፡
======================================================
ከላይ የተመለከትናቸው ጥያቄዎችና መልሶች ኢትዮጵያውያን
ሊቃውንት የተዋሕዶ እምነትን ለማስጠበቅ ያደረጉትን ክርክር ነው፡፡ በእያንዳንዱ ጥያቄ ላይ ሰፊ፣ ግልጽ፣የማያሻማ እና አሳማኝ ማስረጃ
በማቅረብ እየረቱ ያሉት የኢትዮጵያ ሊቃውንት ናቸው፡፡ የዛሬ የቅብአት ምንፍቅና አራማጆች እነዚህን ሊቃውንት ስማቸውን ብቻ ወስደው
ለግል ፍላጎታቸው እየተጠቀሙባቸው ይገኛሉ፡፡ በቅርቡም በእነዚህ ሊቃውንት ስም እንደ “ወልደ አብ” የት እንደታተመ የት እንደሚከፋፈል
በማይታወቅበት መልኩ በስውር መጽሐፍ አሳትመው ምንፍቅናቸውን እንደሚዘሩ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ እነዚህ መናፍቃን የሚጠቀሙት ስማቸውን
(ዝክሪ እና ጳውሊ የሚለውን) ብቻ እንደሆነ ግን ልብ ይሏል፡፡ ምክንያቱም ዝክሪ እና ጳውሊ የኢትዮጵያን ሊቃውንት በአፈ ጉባዔነት
እየመሩ የሮማውያንን የካቶሊክ ክህደት ያሳደዱ ናቸውና ከካቶሊክ እምነት ቅርንጫፍ ከሆነው ቅብአት ጋር ኅብረት የላቸውም፡፡
ይቆየን
ይቀጥላል፡፡