ከዚህ በፊት የምርጫ ካርድ እና እኛ ሆድና
ጀርባዎች እንደነበርን ማስታወሱ አይከፋም፡፡ በተለይ እኔ የምርጫ
ካርድ ማውጣትን እንደ ኃጢአት ነበር የምቆጥረው፡፡ በርግጥም ኃጢአት ሆኖ ነበር፡፡ ምክንያቱም ካርዳችን ዋጋዋ ምንም ስላልነበር፡፡
1997 ዓ.ም ዕድሜዬ ለመምረጥ
አልደርስልኝ ቢል መታወቂያየ ላይ ዕድሜየ እንዲሞላ ፍቄ ሰርዤ ነበር ካርድ ያወጣሁ፡፡ ያ ይመስለኛል በተከታታይ ለነበሩ ምርጫዎች
ካርድ የሚባል ነገር እንዳላይ ብዬ የመምረጥ መብቴን ከራሴ ላይ እንድገፍ ያደረገኝ፡፡ ዘንድሮ 2012 ዓ.ም በትክክል ምርጫው መካሄድ
አለመካሄዱን ባላውቅም መምረጥ ብቻ አይደለም መመረጥም ይኖርብናል ብየ አስባለሁ፡፡


አባቶቻችን ሞተው ያቆዩንን ታሪካችንን እኛም በደማችን ጽፈን ለሚመጣው ትውልድ ሳይበረዝ ሳይከለስ ማውረስ ይኖርብናል፡፡
ድምጹ ተጽእኖ የሚፈጥር የምክር ቤት አባል ሊኖረን ይገባል፡፡ የገቡትን አንግፋቸው ሊገቡ ያሰቡትን እንደግፋቸው፡፡ እኔ ፖለቲከኛ
አይደለሁም፡፡ እንዴት ማሳመን እንደሚቻልም አላውቅም፡፡ ነገር ግን ሀገርን ለማፍረስ ፖለቲካን ሽፋን አድርጎ ከሚመጣ ሰው ለሀገሬ
መልካም ነገር አስባለሁ ብየ እገምታለሁ፡፡ ታዲያ ምንም ባልሠራ እንኳ የዚያን ሰው ወንበር መያዜ ትልቅ ነገር እንደሆነ አስባለሁ፡፡
ስለዚህ የተሻለውን የምንመርጥበትና ተሽለን በመገኘትም የምንመረጥበትን ነገር ከወዲሁ ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ ሌሎች ቀድመውናል ነገር
ግን ዕድሉ አለን ተስፋ የሚያስቆርጥ ደረጃ ላይ አይደለንም፡፡ ሠርተን እናሳይ!
ሃይማኖትና ፖለቲካ ለየግል ናቸው በሚል የጅልነት ብሂል ሀገራችንን ለጠላት አሳልፈን ልንሰጣት አይገባም፡፡ ዳዊትም
ሰሎሞንም ንጉሦች ነበሩ፡፡ በሀገራችን ቅዱስ ላሊበላም ንጉሥ ነበር፡፡ ነገር ግን ከቤተ ክህነት ጋር ያጋጫቸው ነገር አልነበረም፡፡
በመልካም ጥበብ መሩ አስተዳደሩ እንጅ፡፡ ንግሥናን ከክህነት ጋር አስተባብሮ መምራትን አስተምረውን አልፈዋልና በግብር በሃይማኖት
ልንመስላቸው ይገባል፡፡
No comments:
Post a Comment