Tuesday, September 23, 2014

ትምህርት በምሳሌያዊ አነጋገር ክፍል ሦስት

በሬ ሆይ…
ሥነ ቃሉ “በሬ ሆይ ሳሩን አየህና ገደሉን ሳታይ” ተብሎ ይሟላል፡፡ በሬ ሣር አብዝቶ የሚመገብ እንስሳ ከመሆኑ የተነሣ ሣሩ የበቀለበት ከገደል መሆኑን ሳያውቅ ለሆዱ ሲል ብቻ ገደል ይገባል፡፡ ከሥነ ቃሉ የምንረዳው በሬ ሕይወቱን የሚያጣው ሳያስተውልና ሳያገናዝብ ገደሉን ሳያይ ሣሩን ብቻ በመመልከቱ ነው፡፡ ይህ ምሳሌያዊ አነጋገር መናፍቃንን ይጠቁማል፡፡ መናፍቃን በገንዘብ ተታልለው ፈጣሪያቸውን ክደው ለጣዖት ሰግደው ባለማስተዋል የሚኖሩ ናቸው፡፡ “መክፈልት ሲሹ መቅሰፍት” እንዲሉ ገደል የተባለ ሲኦልን ሳያዩ ገንዘቡን ብቻ አይተው ሊበሉ ሲጠጉ ባልገመቱት የሲኦል ገደል ይወድቃሉ፡፡ በሬ ሣርን ብቻ እንዳየ እነርሱም ገንዘብን ብቻ ይመለከታሉና በዘላለም እሳት ለመቃጠል የሞት ሞት ይፈረድባቸዋል፡፡ በአጠቃላይ ይህ ምሳሌያዊ አነጋገር ለምንሠራት ለእያንዳንዲቱ ተግባር በማስተዋልና በመገንዘብ ልንንቀሳቀስ እናደሚገባ የሚገልጽ ነው፡፡ ክርስቲያን የሆነ ሁሉ ከመሥራቱ በፊት ሥርዓትን ሊገነዘብ ግዴታ አለበት ሰማይ ሰማይ እያየ የሚሄድ የሚረግጠውን እንደማያስተውል የሚበላውን ፣ የሚጠጣውን ፣ ገንዘብን እየተመለከተ የሚሄድም የሚገባበትን አያስተውልምና ለከፋ አደጋ ይጋለጣል፡፡ ስለዚህ በምኞት ጎምጅተን የምንገባበትን ሳናስተውል ልንንቀሳቀስ አይገባም፡፡
ድመት መንኩሳ… 
ድመት የቤት እንስሳ ከሚባሉት ውስጥ አንዷ መሆኗ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ይህ ምሳሌያዊ አነጋገር የሚነገረው ድመት የምትመነኩስ ሆና ሳይሆን በግብር የሚመስሏትን ለመጠቆም ነው፡፡ ድመትን ምንም ያህል ጊዜ ቢያሠለጥኗት፣ ንጹህ ውኃ ቢያቀርቡላት ፣ ፊቷን በምራቅ ማበሷን ፣ አይጥ በሰው ፊት መብላቷን ወዘተ… አትተውምና “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ” ይባላል፡፡ ከሰው ልጅ ሕይወት ጋር ስናያይዘው ከኃጢአት ተመልሰው ንስሓ ገብተው ሥጋና ደሙን ተቀብለው ሳለ የቀደመ አመላቸውን /ግብራቸውን/ ባለመርሳት ሲፈጽሙ የሚገኙ አሉ፡፡ ለምሳሌ፡- ቤተሰብ ሲበጠብጥ የነበረን ልጅ ተማሪ ብታደርጉት ተማሪዎችን፤ ዲያቆን ሆኖ ቢሾም ቀዳስያንን መበጥበጥ ይጀምራል፡፡  ከዚህም ወደ በለጠ ማዕርግ ቢደርስ ያን የቀደመ ግብሩን የሚተው ስላልሆነ “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ” ይባልበታል፡፡ በወጣትነቱ በዘማዊነት የሚታወቅ ሰው ዕድሜው ገፍቶ አርጅቶ ዓይኑ ፈዞ ሳለም ያንኑ የቀደመ ግብሩን የሚፈጽም ከሆነ ዕድሜው ዋጋ አጥቷልና “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ” የሚለውን ምሳሌያዊ አነጋገር ይጠቅሱለታል፡፡ እንግዳ ባለመቀበል የሚታወቅ ሰው ሕግጋቱን እጠብቃለሁ ብሎ ለምንኩስና ማዕርግ በቅቶ ሳለ እንደቀድሞው እንግዳ ሲያይ ዓይኑ የሚቀላ ከሆነ ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ የሚለው ምሳሌያዊ አነጋገር ይለጠፍበታል፡፡
በአጠቃላይ አንድ ሰው ለውጥ ማምጣት ባለበት ደረጃ ምንም ለውጥ ማምጣት የማይችል፣ የማይመከር፣ የማይመለስ ወዘተ ከሆነ ዕድሜው፣ ማዕርጉ፣ ሥልጣኑ ወዘተ… ሊያስተምረው የማይችል ስለሆነ “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ” ተብሎ ይነገርበታል፡፡ ስለዚህ ባለንበት ማዕርግ፣ዕድሜ፣ ሥልጣን ደረጃ ልንሠራ የሚገባን ትተን ለደረጃችን የማይመጥን ሥራ በመሥራት በረከሰ ቦታ ልንገኝ አይገባም፡፡ ዳግም ላንፈጽመው በንስሓ ከተመለስን በኋላ ወደ ቀደመው ኃጢአታችን ልንመለስ እንዲሁም አላስፈላጊ የሆነን ነገር ለውጥ ባለማምጣት ይዘን ልንገኝ ተገቢ አይደለም፡፡
ዓሣ ጎርጓሪ… 
ይህን ምሳሌያዊ አነጋገር ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጋር አያይዘን እንመልከተው፡፡ የለመድነውን፣ የምናውቀውን መልካም ነገር በጥልቀት ስንመረምር ያልለመድነው፣ የማናውቀው ክፉ ነገር የሚያጋጥመን ከሆነ “ዓሣ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል” በሚለው ምሳሌያዊ አነጋገር ይገስጹናል፡፡ ለምሳሌ፡-መጽሐፍ ቅዱስን ለመልካም ብለን አላዋቂ በሆነ አእምሯችን በማንበብ ላይ ሳለን በምናገኛቸው ጥሬ ቃላት ተደናገረን ፣ በራሳችን አስተሳሰብ ተርጉመን እግዚአብሔርን እስከ መካድ በደረሰ ኑፋቄ ልንወድቅ እንችላለን፡፡ ብዙዎች ለምንፍቅና ሕይወት የተጋለጡት መርዝ የሌለበትን የለመዱትን ዓሣ ሊያወጡ ሲጎረጉሩ መርዝ ያለበት ዘንዶ እየወጣባቸው ነው፡፡ የሚያውቁትን ዓሣ ጎርጉረው አውጥተው ለመብላት ሲጥሩ የማያውቁት ዘንዶ ወጥቶ ይበላቸዋል፡፡ “መጽሐፍ ቅዱስ ቃል በጥሬው የብረት ቆሎ ነው” የሚሉት ትርጓሜ ስለሚያስፈልገው ነው፡፡ “ፊደል ይገድላልና መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል” 2ኛቆሮ 3÷6  ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ ከዚህ በፊት የምናውቀውን ፣ የለመድነውን ነገር በጠባብ አእምሯችን በጥልቀት እንመርምር ስንል ክህደት ይመጣብናል፡፡ “ዓሣ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል” የሚለው ምሳሌያዊ አነጋገር ገንዘባችን ይሆናል፡፡ የሥላሴን አንድነት ሦስትነት፣ የቃል ሥጋ መሆንን፣ በጥምቀት ያገኘነውን የሥላሴ ልጅነት፣ የሥጋ ወደሙን ምሥጢር፣ የሙታንን መነሣት በጥልቀት መመርመር በማይችል የሰው አእምሮ እንመርምር ብንል ከጥልቀቱ ከምጥቀቱ የተነሣ የማንደርስበት ስለሚሆን የመጨረሻ ውሳኔያችን ክህደት ይሆናል፡፡ አርዮስ ከመመራመሩ የተነሣ “ወልድን ፍጡር”፣  “ድንግል ማርያምን ወላዲተ ሰብእ” በማለት ክህደቱን ጀመረ፡፡ ሌሎችም ቢሆኑ እንዲሁ ነው ክህደት የመጣባቸው ሳያውቁ ያወቅን እየመሰላቸው፡፡
ስለዚህ በመጽሐፍ የተጻፉትን በግላችን የምናነብ ከሆነ በራሳችን ፍልስፍና ከመተርጎም ይልቅ መንፈስ ቅዱስ የቀደሳቸው አባቶችን ይህ ማለት ምን ማለት ነው? ለምን እንዲህ ሆነ? መቼ ተደረገ? እንዴት ሊሆን ይችላል? ወዘተ… የሚሉ ጥያቄዎችን በሰከነ አስተዋይ አእምሮ ሆነን በመጠየቅ መረዳት ያስፈልጋል፡፡  ከዚያ ውጭ ለበረከት ያልነው ለመርገም ፣ ለጽድቅ ያልነው ለኃጢአት ፣ ለትርፍ ያልነው ለኪሳራ ፣ ለመክፈልት ያልነው ለመቅሰፍት፣ ለእምነት ያልነው ለክህደት ፣ ለመጽናት ያልነው ለመናወጥ ፣ ለዓሣ ያልነው ለዘንዶ ሊሆንብን ስለሚችል ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝንብናል፡፡ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ ስምንት ቁጥር ሠላሳ አራት ላይ የተገለጸው ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ትንቢተ ኢሳይያስን ሲያነብብ በነበረበት ወቅት ተርጓሚ ሳላገኝ እንዴት እረዳዋለሁ በማለቱ ተርጓሚ ተሰጠው፡፡ በአግባቡም ትርጉሙን ከተረዳ በኋላ ለመጠመቅ ወሰነ ተጠመቀም፡፡ ያለ ተርጓሚ እያነበበ ቢሆን ኖሮ ግን የቃሉ ምንነት ስለማይገባው ለመጠመቅ ባልቻለ ነበር፡፡
ነገርን ከሥሩ…
ለውጤታማ ሥራ መነሻ ከታች መጀመር ነው፡፡ ጥሩ ቤት ለመሥራት መጀመሪያ ከታች ከመሠረቱ መጀመር አለብን፡፡ መሠረት የሌለው ነገር ሁሉ ከንቱ ነው፡፡ በትምህርት ዓለም ውስጥ ከማንበብ አስቀድሞ ፊደል መቁጠር መሠራታችን ነው፡፡ ማንበብ መጻፍ የምንችለው ፊደላትን መለየት ከቻልን ብቻ ነው፡፡ በሒሳብ ትምህርት ደግሞ የቁጥሮችን አጻጻፍ ማዎቅ ለመደመር፣ ለመቀነስ፣ ለማባዛትና ለማካፈል መሠረት ነው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በሕጻንነት የለመድነው ማንኛውም ነገር ለወጣትነትና ለሽምግልና ጊዜያችን መሠረት ነው፡፡ ከሕጻንነቱ ጀምሮ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ያደገ በወጣትነትም ጊዜው ቤተ ክርስቲያን ይገኛል፡፡ በሕጻንነቱ ከእናቱ ቦርሳ ሣንቲም በመስረቅ ያደገ በወጣትነቱም የሰውን ንብረት ሲዘርፍ የሚገኝ ይሆናል፡፡ ከመሠረቱ በሥርዓት ያልታነጸ ገና በለጋነቱ ያልተቀጨ ነገር መራራ ፍሬ ስለሚያፈራ አስቀድሞ ከሥሩ መቆጣጠር አስፈላጊ እንደሆነ ለመግለጽ “ነገርን ከሥሩ ውኃን ከጥሩ” የሚለው ምሳሌያዊ አነጋገር ይቀጸላል፡፡ “ታሞ ከመማቀቅቀ አስቀድሞ መጠንቀቅ” እንዲሉ የማይጾም፣ የማይጸልይ፣ የማይሰግድ፣ የሚሰርቅ፣ የሚገድል ትውልድ እንዳይፈጠር በፈለግነው አቅጣጫ መምራት በምንችልበት በሕጻንነት ጊዜ ልጆችን ሥርዓት ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ በእውነት ሁላችንም ልጆቻችንን ቤተ ክርስቲያን ወስደን ዕጣኑ ቢሸታቸው ፣ ቅዳሴው ቢሰማቸው፣ ሥጋና ደሙን ተቀበለው፣ የቅዳሴ ጸበል ጠጥተው አብረውን ወደ ቤታችን ቢመለሱ እኛ የምንጎዳው ነገር ምንድን ነው? በእርግጥ እኛ ላናስቀድስ ፣ ሥጋና ደሙን ላንቀበል እንችል ይሆናል፡፡ ታዲያ ልጆቻችን ማንን ሊመስሉ ነው? እኛን ወይስ ሌላውን? አስቡት እኛን ከመሰሉ ማስቀደስን ሥጋና ደሙን መቀበልን መቼ ልናሳውቃቸው ነው? ወይስ ምን እንደሆነ ሳያውቁት ይኑሩ? ይኼ ምቀኝነት ይመስላል፡፡ እኔ ስለማስቀድስ ልጄም ማስቀደስ የለበትም፣ እኔ ስለማልቆርብ ልጄም መቁረብ የለትም የሚል አስተሳሰብ ለክርስትና ሕይወት አደገኛ ነው፡፡ ምክንያቱም ነገርን ከሥሩ መንከባከብ አስፈላጊ ነውና፡፡ ነገ ልጄ ሰርቆኝ፣ ልጄ ደብድቦኝ ወዘተ… እያልን በየፍርድ ቤቶች ቆመን ከምናነባ ዛሬ ልጆቻችንን በሥርዓት ማሳደግ መንከባከብ ግዴታችን ነው፡፡ ከልጅነት ጀምሮ የሚቆራኝን ጋኔን ከሥሩ ነቅለን ካልጣልንላቸው የሚመጣውን ዕዳ ራሳችን የምንሸከመው ይሆናል፡፡ ማንኛውም ነገር እንክብካቤ የሚፈልገው ራሱን ባልቻለበት በለጋነት ዕድሜው እንጅ በበሰለበት ራሱን በቻለበት ወቅት አይደለም፡፡ ሲሳደብ ያልገሰጻችሁት ሕጻን ሲያድግ ቢደበድባችሁ ማንም አይደነቅም፡፡ ምክንያቱም መጀመሪያ ሲሳደብ ዝም ያልነው ለዚሁ ነዋ! ኃጢአትን ካልተውናት ከሐልዮ ወደ ነቢብ፣ ከነቢብ ወደ ገቢር እንደምታድግ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ኃጢአትን ከመሠረቱ በለጋነቱ እየነቀልን ልንጥለው ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ነው ኃጢአት እያሠራ ወደ ሲኦል የሚያግዝ ዲያብሎስ የኃጢአት ሁሉ ሥር በመሆኑ እናታችን ቅድስት ቤተ ክርስቶስ ሰምራ እግዚአብሔር እንዲምረው የለመነች፡፡ እናታችን ዲያብሎስን ወድዳው መሰላችሁ እንዴ? ነገርን ከሥሩ ውኃን ከጥሩ እንዲሉ የሰው ልጆች ወደ ሲኦል እንዳይወርዱ የኃጢአትን ሥር ለማድረቅ እንጅ፡፡ ዲያብሎስ ምሕረት ካገኘ የሰው ልጆችን ስለማያስት ሁሉም የአዳም ልጆች ገነት ይገባሉ የሚል ቅን አስተሳሰብ ስለነበራት ነው፡፡ ይህ ነው ነገርን ከሥሩ ውኃን ከጥሩ ማለት፡፡
በርካታ አስተማሪ የሆኑ ሥነ ቃሎች እንዳሉ ቢታወቅም ከላይ ያየናቸው ስምንት ሥነ ቃሎችን ለማንሣት ተገድደናል፡፡ እነዚህ የተነሡት ሥነ ቃሎች በውስጣቸው ያለው ትምህርት የተጠቀሰው ብቻ ነው የሚል ግምት የለንም፡፡ አንድ ምሳሌያዊ አነጋገር ከአንድ በላይ ብዙ ትምህርቶች እንደሚይዝ ይታወቃል፡፡ ከመጽሐፉ ርእስ ጋር የሚሔዱትን ትምህርቶች ብቻ ያነሣን በመሆኑ ለአንድ ምሳሌያዊ አነጋገር በርካታ ትርጉም ላንሰጠው ተገድደናል፡፡
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠


No comments:

Post a Comment