Friday, March 23, 2018

ተአኪያሁ!

  ======= ======= ======= ======= =======

ታኦጎሎስ የተባለው ነባቤ መለኮት ቅዱስ ጎርጎርዮስ ክርስቶስን ሁለት አካል ሁለት ባሕርይ ብሎ የካደውን ንስጥሮስን ከቊስጥንጥንያ ቤተክርስቲያን ያሳደደበት ድርሳኑ ነው ተአኪያሁ! ትርጓሜውም “የወላዲተ እግዚአብሔር ማርያም ድርሳን” ማለት ነው። በዚህ ድርሳኑም ታላቁ ሊቅ እመ ብርሃን ድንግል ማርያምን እንዲህ ያመሰግናታል፦


“እኔ ወላዲተ እግዚአብሔር ሁለተኛ አርያም የሆንሽ ከእርሱ ከፍ ከፍ የምትዪ ከኪሩቤል የምትበልጭ እግዚአብሔርን ወለድሽ ስልሽ አላፍርም። እነርሱ ያዩት ዘንድ ችሎታ የላቸውም አንች ግን መለኮታዊ ቃልን በክንድሽ ተሸከምሽው። በሰማይና በምድር የመላ ሲሆን ከሰይፍ ጋራ በአራቱ እንስሳት ትከሻ ላይ የሚኖረውን በክንድሽ ቻልሽው እላለሁ። ደካማው ስምዖን በክንዱ ተሸከመው፤ ከእርሱም ሌላ የሚረዳውን ተማጻኝ ሳይኖር ያሳርፈው ዘንድ ፈለገ። ለእርሱም መወለዱን በማብሰርና ወደ ምድረ ግብጽም በመሸሽ ምስክር ሆነው” ይላል።

ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያምን እንደ ንስጥሮስ ወላዲተ ሰብእ ብሎ መናገር ምንኛ መረገም ነው። ሰማይና ምድር የማይችሉትን አምላክ በማኅጸኗ ተሸከመችው። ዓለምን በመኃል እጁ  የያዘውን አምላክ በእጇ ያዘችው። ፍጥረቱን ሁሉ የሚመግበውን አምላክ የድንግልና ጡቶቿን አጠባችው። ኪሩቤልና ሱራፌል በመፍራት እና በመንቀጥቀጥ የሚገዙለትን አምላክ እርሷ ዳሰሰችው። መላእክት አንተን ማየት አይቻለንም ሲሉ ፊታቸውን በክንፎቻቸው የሚሸፍኑለትን አምላክ እርሷ ተመለከተችው። የቶማስን እጅ እርር ኩምትር ያደረገውን እሳተ መለኮት ታቀፈችው አጠባችው ዳሰሰችው። ይህ ምንኛ ድንቅ ነገር ነው! ወዮ! ለዚህ አንክሮ ይገባል ከማለት በቀር በእውነት ምን እንላለን?

ሰነፉ አርዮስ ግን ወልድን ፍጡር ነህ አለው። ዝንጉው ንስጥሮስም ድንግል ማርያምን ወላዲተ ሰብእ ነሽ አላት። እኛስ ወልድንም ፈጣሪ እመ ብርሃን ድንግል ማርያምንም ወላዲተ አምላክ እንላታለን እንጅ በእነርሱ መንገድ ከቶ አንጓዝም። በድንግልና ጸንሶ በድንግልና መውለድ ምንኛ ልዩ ነገር ነው። ከሰው ወገን ከቶ ለማንም ያልተደረገ በድንግልና ጸንሶ በድንግልና መውለድ በድንግል ማርያም የተጀመረ በድንግል ማርያምም የተፈጸመ ብቸኛ ድንቅ ነገር ነው። አዳም ከኅቱም መሬት ቢገኝም ምድር አምላክን ወለደች አንላትም፡፡ ሔዋን ከኅቱም ገቦ ብትገኝም አዳም ወላዲተ አምላክ አልተባለም፡፡ አቤል በዘር በሩካቤ በመወለዱ በድንግል ለመጽነስ  በድንግልና ለመውለድም ለሔዋን አልተቻላትም፡፡ ከኅሊናችን በላይ ቢሆንብን ድንቅ ድንቅ ድንቅ ዕጹብ ዕጹብ ዕጹብ ብለን በአንክሮ እንናገራለን እንጅ ከኅሊናችን በላይ ስለሆነ ወልድን ፍጡር እናቱንም ወላዲተ ሰብእ እንላት ዘንድ አንደፍርም።

በድንግል ጸንሶ በድንግልና መውለድ ምንኛ ድንቅ ነው። አምላክ ፍጥረታትን ለጌጥ ብቻ አልፈጠራቸውም ለእኛ መማሪያ ይሆኑ ዘንድ እንጅ። ከፍጥረታትም መካከል በድንግልና መውለድን የሚያሳዩ ምሳሌዎች እነሆ አሉ። እነዚህንም ምሳሌዎች እንመልከት።

ማየት ከዓይን ይወለዳል ወዝም ከሥጋችን ይወለዳል መልካችንም ከመስታወት ይወለዳል ይህ ሁሉ ምሳሌ ይሆነናል። ይህንንም  በ፲፮ኛው ክፍለ ዘመን የነበሩ የኢትዮጵያ ሊቃውንት ተናግረውታል። በሃይማኖት መጽሐፋቸውም መዝግበውት ይገኛል።

ሊቃውንቱ ይህንን ሲያብራሩ “ማየት ዓይንን ቀድዶት የሚወጣ አይደለም የመልክ ምሳሌም መስታወቱን ሰብሮ የሚገባ አይደለም ወዝም ሥጋን ቀድዶ የሚወጣ አይደለም” ይላሉ። ለእኛ በሚገባን በምናየው በምናረጋግጠው ነገር መመሰል ነው እንጅ የቃል ከሥጋ ጋር ያለውን ተዋሕዶስ ከፈጣሪ በቀር ማንም አያውቀውምና ምሳሌም የለውም።

ዓይናችን ከብርሃን ጋር ተዋሕዶ ማየት እንደሚችል የታወቀ ነው። ዓይን ማየት በሚሻ ጊዜ በብርሃኑ አይቀደድም። ዓይናችን ሳይለወጥ ሳይቀደድ በብርሃኑ ሳይሸነፍ ሳይቸገር እንደሚያይ ሁሉ (ማየትን እንደሚወልድ) ወልድም ከሥጋ ማርያም ጋር ሲዋሐድ ሲጸነስ በኋላ ሲወለድም የድንግልናዋ ማኅተም አልተለወጠም አልፈረሰም አልጠፋም። ይህን እጹብ ብሎ ከማድነቅ ውጭ ምን እንላለን?

መስታወት መልካችንን ሲያሳየን መልካችንን ምሳሌያችንን በመስታወት እንመለከተዋለን። በትንሿ መስታወት ይህ ግዙፍ አካላችን ይታያል ። መስታወት የእኛን መልክ ሲወልድ አይሰበርም አይሰነጠቅም። ትንሿ መስታወት ሳትሰነጠቅ ሳትሰበር ሳትለወጥ ሳትቀየር ግዙፉን አካላችንን እንደምትወልድ  ሁሉ ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያምም እንዲሁ ድንግልናዋ ሳይለወጥ አምላክን በድንግልና ጸንሳ በድንግልና ወልዳለች። ይህን እጹብ ብሎ ከማድነቅ ውጭ ምን እንላለን?

ወዝ ከሥጋችን ይወጣል ይንጠፈጠፋል። የወዛችን ከሥጋችን መውጣት መንጠፍጠፍ ግን ሥጋችንን አይቀደውም አይበሳውም። አካላዊ ቃልም ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከእመ ብርሃን ከድንግል ማርያም ማኅጸን ሲያድር ሲዋሐድ ሲጸነስ በኋላም ሲወለድ ማኅተመ ድንግልናዋን አልለወጠውም አላጠፋውም። በታተመ ድንግልና ጸንሳ በታተመ ድንግልና ወለደችው እንጅ። ይህን እጹብ ብሎ ከማድነቅ ውጭ ምን እንላለን?

ሕዝቅኤል ወጣት ቀይ ጎልማሳ ሳይከፍት ገብቶ ሳይከፍት ሲወጣ እንደተመለከተው ድንግልናዋን ሳይጥስ ተጸንሶ ተወለደ ለዚህ ከማመስገን በቀር ሌላ ምን ይመለሳል?

ሌላም ምሳሌ አለ  መስታወት ብርሃንን አሳልፎ ወደ ውስጥ ያስገባል። የብርሃኑ በመስታወቱ አልፎ ከውስጥ መግባት መስታወቱን አይሰነጥቀውም አይሰብረውም። የቃል ከሥጋ ጋር ተዋሕዶ መጸነስ እና መወለድም እንዲሁ ነው። ድንግልናዋን ሳይጥስ ተጸንሶ ድንግልናዋን ሳይጥስ ተወለደ እንጅ።

ታዲያ ይችን ድንቅ እናት ይችን ሀመልማል ከነበልባል ነበልባል ከሀመልማል ተዋሕደው ሙሴ በደብረ ሲና ያያትን የምስጢር ቤት ስለምን እንንቃታለን ስለምንስ ወላዲተ ሰብእ ብለን የስድብ አፍን እንከፍትባታለን? ነበልባል ያላቃጠለው ሀመልማል የድንግል ማርያም ሥጋ ነው። ሀመልማል ያላጠፋው ነበልባልም ሥጋዋን የተዋሐደው አካላዊ ቃል ነው። ይህ ድንቅ ምሥጢር የተከወነባት ልዩ ተራራ ደብረ ሲና እመ ብርሃን ናት። መለኮት ከሥጋ፤ ሥጋም ከመለኮት ጋር የተዋሐደባት ልዩ የምስጢር ቤት እመ ብርሃን። በእውነት ፍቅሯ ጣዕሟ ቢገባን እርሷን ማመስገኛ ጊዜ ባጠረን ነበር። የምስጋና ጊዜ ቢያጥረንማ ወላዲተ ሰብእ የሚለውን ስድብ ባላመጣነውም ነበር። እርሷን ለማመስገን ምስጋና ከሚያጥረን ቃላት ከሚያንሰን በቀር ስለሷስ የስድብ አፋችንን እንከፍት ዘንድ አገባባችን አይደለም!

አምላከ ቅዱሳን የእናቱን የእመ ሕይወትን ጣዕም ፍቅር በልቡናችን ይሳልብን ያሳድርብን አሜን።



© መልካሙ በየነ

ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

መጋቢት ፲፬/ ፳፻፲ ዓ.ም

No comments:

Post a Comment