፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
አውቀናል በቅተናል የሚሉ የቅብዓት አስተማሪዎች ቅብዓት ምስጢር ነው ባህለ ትምህርት ነው እንጅ
ሃይማኖት አይደለም ይላሉ፡፡ ካሳሁን ምናሉ የተባለው የመሠረተ ሐይማኖት መጽሐፍ ጸሐፊ ግን እውነቱን እንዲህ ሲል ተናግሮታል፡፡
“የናንተ የሆነ አሐዳዊ መጽሐፍ የላችሁ ጳጳስ የላችሁ እዚህ በሃይማኖት በኩል አናሳ የምንባለው ግፍና መከራ ዛሬ እንሆ የእግዚአብሔር
ፈቃድ ሆኖ ለመጀመሪያ ጊዜ ይኸው መሠረተ ሐይማኖት መጽሐፍ ታትሞ በገበያ ላይ ዋለ” ይላል፡፡ ስለዚህ ቅብዓት የእምነት ስም እንጅ
ባህለ ትምህርት ወይም ምሥጢር አይደለም፡፡ ምስጢር ነው እንዳንል በቤተክርስቲያናችን የምናውቃቸው ምሥጢራት አምስቱ አእማደ ምሥጢራት
እና ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን ናቸው፡፡
እነዚህም
1ኛ. አምስቱ አእማደ ምሥጢራት
1. ምሥጢረ ሥላሴ
2. ምሥጢረ ሥጋዌ
3. ምሥጢረ ጥምቀት
4. መሥጢረ ቁርባን
5. ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን ናቸው፡፡
2ኛ. ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን
1. ምስጢረ ጥምቀት
2. ምሥጢረ ሜሮን
3. ምስጢረ ቁርባን
4. ምስጢረ ክህነት
5. ምሥጢረ ተክሊል
6. ምሥጢረ ንስሐ
7. ምሥጢረ ቀንዲል ናቸው፡፡ በእነዚህ
ምሥጠራት ውስጥ “ምሥጢረ ቅብዓት” የሚል አናገኝም፡፡ መጻሕፍትም መዝግበውት አናገኝም ስለዚህ “ቅብዓት” ምሥጢር አይደለም የእምነቱ
መለያ ስም እንጅ፡፡
ምሥጢረ ሥጋዌ ውስጥ ነው “ምሥጢረ ቅብዓት” ሊገኝ መቻል ያለበት፡፡ ሆኖም ግን በዚህ ምሥጢር
ውስጥ “ምሥጢረ ተዋሕዶን” እንጅ “ምሥጢረ ቅብዓትን” ሊቃውንት ጽፈውት አናገኝም፡፡ “ቀባ” አከበረ አዘጋጀ አዋሐደ ወዘተ በሚል
ቃሉን ሊቃውንት በተለያየ ቦታ ተጠቅመውበት እናገኛለን፡፡ እንደ አንድ የቤተክርስቲያናችን ምሥጢር አድርገው ግን ጽፈውት የምናገኘው
ነገር የለም፡፡ ስለዚህ ቅብዓት ምሥጢር አይደለም ማለት ነው፡፡
ባህለ ትምህርት ነው የሚሉትም እንደዚሁ ሁሉ ማታለያ ማደናገሪያ ነው፡፡ “በመንፈስ ቅዱስ ቅብዓትነት
ከበረ” የሚል ባህለ ትምህርት የለንም፡፡ “ወልድ ፍጡር” የሚል ባህለ ትምህርት የለንም፡፡ “ወልድ መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ አምላክ
ሆነ ባይቀበል ኖሮ እንደ አብ እንደመንፈስ ቅዱስ አይገዛም አያዝዝም ነበር” የሚል ባህለ ትምህርት የለንም፡፡ “ወልድ በቅብዓተ
መንፈስ ቅዱስ ሐዲስ አምላክ ሆነ” የሚል ባሕለ ትምህርት የለንም፡፡ ያማ ከሆነ አርዮስም ንስጥሮስም መቅዶንዮስም ልዮንም ባህለ
ትምህርት ነበር ያላቸው ማለት ነዋ፡፡ ወዴት ወዴት! ክህደት ባህለ ትምህርት ሊሆን አይገባውም አይችልምም፡፡ የዚህ ሃሳብ ዋና አቀንቃኝ
“መጋቤ ብሉይ” አእመረ አሸብር ናቸው፡፡ እኒህ ግለሰብ ዲያቆን ኢንጅነር ዓባይነህ ካሴ ለ “ወልደ አብ” ምላሽ በሰጠበት ጌራ መድኃኒት
በተሰኘው መጽሐፉ ምረቃ ቀን ላይ ተገኝተው ይህንኑ ሃሳብ አንጸባርቀዋል፡፡ ሊቀ ሊቃውንት ስምዓ ኮነ መልአክ እንዲሁም ሙሐዘ ጥበባት
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በዚሁ ሃሳብ ላይ ምላሽ ሰጥተውበታል፡፡ ሙሉውን ለመከታተል ይህን ማስፈንጠሪያ ጠቅ ያድርጉ፡፡ https://www.youtube.com/watch?v=QqpOxzbHbJw
ስለዚህ ባህለ ትምህርት ነው ምሥጢር ነው የሚሉት ለማደናገር ነው፡፡ በአንድ ጥምቀት ሁለት
እምነት ሊኖር አይችልም በአንድ ቤተክርስቲያን ሁለት እምነቶች ሊገለገሉ አይገባቸውም፡፡ ነገር ግን በቁጥር አነስተኛ በመሆናቸውና
በመንግሥት ዘንድም እውቀና የተሰጣቸው ስላልሆነ ቁጥራቸውን ለማብዛት የሚጠቀሙበት ማደናገሪያ ነው፡፡
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
© መልካሙ በየነ
የካቲት ፪
/ ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣
ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
No comments:
Post a Comment