የአቡነ
ማርቆስን ጠልነት ተጠቅመው ያንሰራሩት ከመቃብር አፋፍም የወጡት ቅባቶች ኩላዊት አሐቲ ቅድስት የኾች ቤተ ክርስቲያንን ለመከፋፈልና ምእመናንን ግራ
ለማጋባት በጀት ተመድቦላቸው በስፋት እየሠሩ ናቸው፡፡ ውስጥ ለውስጥ
እየሠሩት ያለውን ነገር አሁን አሁን ወደ ምእመናንም በመውረድ በአንዲት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን ውስጥ መከፋፈልን እየፈጠሩ ናቸው፡፡
በጀቱ የማን እንደኾነ የሚታወቅ ነው፡፡ ለዚህ የበጀት ምንጭ ኹለት ነገሮችን እጠረጥራለሁ፡፡
1ኛ.
የተሐድሶ መናፍቃን ሴራ ይኾናል ብየ እገምታለሁ፡፡ ቅባቶች በመጽሐፎቻቸው ውስጥ ያሰፈሯቸው በርካታ ትምህርቶች ከመናፍቃኑ በቀጥታ
የተቀዱ ናቸው፡፡ ከዚህ በፊት በዚህ ዙሪያ ብዙ ነገሮችን ብያለሁ፡፡
ተሐድሶ መናፍቃን ሰርገው ለመግባት አመቺ ሖኖ ያገኙትን ሁሉ ከመጠቀም ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ስለዚህም አንዲትን ቤተክርስቲያን ለተለያዩ
ጎራዎች እንድትከፈል የማድረግ አጀንዳ አንግበዋል፡፡ በአንዱ እግዚአብሔር በአንዲት ጥምቀት አንድ ሃይማኖት እንጅ ሁለት ሃይማኖት
ሊመሠረት እንደማይችል ለማንም የተገለጠ እውነት ነው፡፡
2ኛ.
አሁን ያለው ያልተረጋጋ የመንግሥት ፖሊቲካዊ አሠራር ይመስለኛል፡፡ በየዩኒቨርሲቲዎቻችን በየከተሞቻችን እና በተለያዩ ድንበር ቦታዎች
ላይ እስካሁን ድረስ በርካታ መከፋፈሎች ይስተዋላሉ፡፡ ይህ ሴራ የማን እንደኾነ በግልጥ የሚታወቅ ነው፡፡ ወደ ሃይማታዊ ተቋማትም
በመግባት ይህንን ነገር በገንዘብ እየደገፉ እንደኾነ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በክልል እንዳይስማማ በዞን እንዳይስማማ በወረዳ በቀበሌ
እንዳይስማማ እንደሀገርም አንድ እንዳይኾን በሚፈለግበት በዚህ ወቅት እነዚህ መነሣታቸው በኩንታል ከሚታደለው የጥፋት ገንዘብ መካከል
ተቋዳሽ መኾናቸውን ያሳያል፡፡
እነዚህ
ከላይ የገለጥኳቸው ጉዳዮች ለእኔ መስለው የሚታዩኝ ናቸው እንጂ እውታው ግን በእያንዳንዳችሁ ሀሳብ ውስጥ ሊመላለስ እንደሚችል እገምታለሁ፡፡
ያም ኾነ ይህ ቤተክርስቲያናችን አሁን ባለው ኹኔታ ተደፍራለች ተጠቅታለች፡፡ ትራስ በትራስ ላይ እየደራረብክ ተኝተሃል ጠላት ደግሞ
ጦሩን ሰብቆ ቤትህ ውስጥ ሰተት ብሎ ገብቷል፡፡ በዚህ ዙሪያ ላይ ለዘብተኛ አመለካከት ያላችሁ ወገኖች ወይ የጥፋቱን ሠራዊት ተከተሉ
ወይ ቤተክርስቲያንን ነቅቶ ከጠላት ከሚከላለከለው ሠራዊተ እግዚአብሔር ጋር ተሰለፉ፡፡
የቅባቶች
ፌስቡክ አካውንቶች ዛሬ ታኅሣሥ 22/2011 ዓ.ም በጥንታዊቷ ርእሰ ርኡሳን መርጡለ ማርያም ከተማ ውስጥ በምትገኘው ቅድስት አርሴማ
ቤተክርስቲያን ውስጥ ስብሰባ እንደሚያካሂዱ ሲለፉ ሰንብተዋል፡፡ እኛም የሚኾነውን ነገር እየተከታተልን ነበር፡፡ ቅዳሜ ዕለት ታኅሣሥ
20/2011 ዓ.ም ለሞጣ፣ ለደብረ ወርቅ፣ ለጎንቻ አካባቢ የቅባት አማኞች ደብዳቤ ተበተነላቸው፡፡ ስብሰባቸውን ደግሞ መርጡለ ማርያም
እንደሚያደርጉ አሳወቋቸው፡፡ ካልጠፋ ቦታ ካላጡት ገዳም ለምን መርጡለ ማርያም ተደረገ? ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ መርጡለ ማርያም ማካሄድ ያስፈለጋቸው፡-
1ኛ.
መርጡለ ማርያም ገዳም የምትታወቀው በጥንታዊነቷ ነው፡፡ የኦሪት መሥዋእት ይሠዋባቸው ከነበሩ አምስት ቦታዎች መካከል አንዷ ናት፡፡
መርጡለ ማርያም ገዳም ውስጥ ከጥንት ጀምሮ የቅባት አማኞች ወደ ተዋሕዶ እየተመለሱ የልጅነት ጥምቀትን ያጠምቁባት የነበረች ቦታም
ናት፡፡ እውነታቸውን ይኹን አይኹን ባላውቅም ዛሬም የተወሰኑ ቅልቅሎች ሊኖሩ ቢችሉም ጥምቀት እንደሚካሄድባት ነው ቅባቶች የጠቀሱት፡፡
2ኛ.
የሚቃወመን የለም በሚል ነው፡፡ በእውነቱ ይህ አመለካከት የመርጡለ ማርያምን ሕዝብ በትክክል ካለመረዳት የመጣ ይኾናል ብየ አስባለሁ፡፡
ለእመነቱ ሲል የሚሞት ስንት ደገኛ ምእመን እንዳለ የሚያውቁ አልመሰለኝም፡፡
በዋናነት
ጥንታዊነቷን ለስማቸውና ለሃይማኖታቸው መገለጫ ማድረግን ይሹ ስለነበር ነው መርጡለ ማርያምን ለስብሰባቸው የመረጡት፡፡ ጉባዔ ከለባት
(የውሾች ጉባዔ) በመርጡለ ማርያም ከተማ እንዲደረግ በዚህ መልኩ ተወሰነ፡፡ የሚገርማችሁ ነገር መርጡለ ማርያም ከተማ ውስጥ ቢሮ
ከፍተው በመሥራት ላይ እንደኾኑ መረጃው ሊኖራችሁ ይገባል፡፡
ዛሬ
ታኅሣሥ 22/2011 ዓ.ም በቀጠሯቸው መሠረት ከየወረዳው በእልህና በትዕቢት የሚንቀሳቀሱ የቅባት አማኖች መርጡለ ማርያም ከተማ
ወደምትገኘው ቅድስት አርሴማ ቤተክርስቲያን ተሰባሰቡ፡፡ ኾኖም ግን ወረዳ ቤተክህነቱም ሰበካ ጉባዔውም የሚያውቀው ነገር ስለሌለው
ወደ ቤተክርስቲያኗ መግባት አልቻሉም ነበር፡፡ ሌሊቱን ሙሉ መፍትሔ ሲያፈላልጉ የነበሩት የመርጡለ ማርያም የስበት ትምህርት ቤት
ተማሪዎች እና የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ቅባቶች ይሰበሰቡበታል ወደተባለው ቤተክርስቲያን ገስግሰው አቅንተዋል፡፡ የጸጥታ አካላትም
በቦታው በመገኘት ከኹለቱም ወገን ከቅባትም ከተዋሕዶም ወደ ቤተክርስቲያኗ እንዳገቡ ያደርጋሉ፡፡ ቅባቶች በዚህ የተነሣ ከቤተክርስቲያኗ
ራቅ ብለው አጀንዳቸውን መወያየት ጀመሩ፡፡ አሁን ላይ የመርጡለ ማርያም የተዋሕዶ አርበኞች ቤተክርስቲያኗን ከበው እየጠበቁ ናቸው፡፡
በእውነት ለእነዚህ ወንድሞቻችን ምን ይከፈላቸዋል? የቅባቶች ስብሰባ የከሸፈው ቤተክርስቲያን ከመደረጉ ነው እንጂ ውይይት ከማድረግ
ማንም አላስቆማቸውም፡፡ ዳግም ጥምቀት እና ማኅበረ ቅዱሳን እየተወገዙ ያለበት ሰዓት ነው አሁን፡፡
በዚህ
ላይ ለማኅበረ ቅዱሳንም እና ለዘብተኛ አመለካከት ላላቸው ሰዎች ኹሉ መልእክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ፡፡
1ኛ.
ለማኅበረ ቅዱሳን
====================================================
ማኅበረ
ቅዱሳን በመንግሥት፣ በተሐድሶ፣ በቅባት እና በሌሎችም እምነቶች በከፍተኛ ደረጃ የሚወቀስ የሚወገዝ ማኅበር ነው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን
እንዲህ ያደርጋል ማኅበሩ እንዲህ ይሠራል እያሉ ሲያሸማቅቁት እየተመለከትን ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ምሥራቅ ጎጃም ላይ ስላለው የቅባቶች
እንቅስቃሴ ማኅበረ ቅዱሳን እንደ ማኅበር አቋም ይዞ እየታገለ ነው ለማለት እቸገራለሁ፡፡ አቡነ ማርቆስ በነበሩበት ሰዓት ይነሣ
የነበረው ይህ ሃይማኖታዊ በደል ዛሬ ላይ ስሙን ለማንሣት እንኳ የተፈራበት ሁኔታ ነው ያለ፡፡ ስብከት ሲሰጥም ቅብዐት የሚለው መነሣት
የለበትም እየተባለ ለስብከት የሚቆሙ ሊቃውንት ምን ያህል ቃላትን ለመምረጥ እንደሚጠነቀቁ ሳይ አዝናለሁ፡፡ ጥምቀት ጋር በተያያዘ
ማኅበረ ቅዱሳን ማጥመቅ እንደማይችል ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ማኅበረ ቅዱሳን እያጠመቀ ነው ተብሎ ስለተከሰሰ ብቻ ጥምቀቱ ላይ ለዘብተኛ
መኾን እየታየ ነው፡፡ ቅብዐት ምንፍቅና ነው በቅብዐት ካህናት የተጠመቁም መጠመቅ አለባቸው ብሎ ደፍሮ ማስተማር ላይ ችግር አለ፡፡
ይህን ሳልጠቅስ ማለፍ አልፈልግም፡፡ እኛ ቅባት ብለን ስላልጠራን፣ ዳግም ጥምቀት ላይ ብዙም አይጫኑም ስለተባልን ከቅባቶች ስድብና
ከሰሳ የምናመልጥ ከመሰለን ተሳስተናል፡፡ ግልጽ እንነጋገር ከተባለ እኔ ያለኝ አቋም እውነቱን እውነት ሐሰቱን ሐሰት እያልን መደራደር
ባለብን ዙሪያ እየተደራደርን መደራደር በሌለብን ጉዳይ ደግሞ መደራደር ሳያስፈልግ በግልጽ መቀጠል ነው፡፡ አሁን በየግቢ ጉባዔው
እያስተማርን ነው፡፡ ቅባቶች አምነው ተመለሱ እና ምን እናድርግ አሉ? መልሳችን ምንድን ነው የሚኾነው? ምሥራቅ ጎጃም ላይ ያለው
የማኅበሩ እንቅስቃሴ በቀጥታ ሳይኾን በተዘዋዋሪ ኾኗል፡፡ ከተወገዘ ይወገዝ የተለመደ ነው፡፡ ከተለየም ይለይ የታወቀ ነው፡፡ እውነቱን
መነጋገር ግን የግድ ነው፡፡ ሱቃችን እና ከፌያችን እንዳይዘጋ አይደለም እኮ የምንሠራው፡፡ ሥራችን የጠፉ በጎችን መፈለግ ነው አለቀ፡፡
እኛ
ብንሸፍነው ብናሽሞነሙነው አንድ ቀን መፈንዳቱ የሚቀር እንዳይመስላችሁ፡፡ መንግሥት ላይ ያለውን አትመለከቱም እንዴ? ሽህ ዓመት
ይገዙናል ብለን ራሳችንን ለስቃይና ለመከራ ስናስበው እኮ ነው ይችን ሰላም ያገኘናት፡፡ ሊገዙን ያሰቡት ሰዎችም ባላሰቡበት ጊዜ
ነው ያ ሁሉ ነገር የገጠማቸው፡፡ ባሠሩበት እስር ቤት አንገታቸውን ደፍተው የታሠሩበት ጊዜው ለእነርሱ ስላልኾነ ነው፡፡ ስለዚህ
ማኅበሩም ይህንን በአቋም መሄድ አለበት፡፡ ፍናፍንት በሆነ አስተሳሰብ መዝለቅ አይቻልም፡፡ ያውም የችግሩ ምንጭ ላይ ተቀምጠን፡፡
ከአባታችን ጋር ያለውን መልካም ግንኙነት የሚያሻክር መስሎ ከተሰማችሁ መጀመሪያ ግንኙነታችን ሃይማኖታዊ መኾን አለበት፡፡ ቅባቶች
ይጠመቁ የሚሉ መጻሕፍትን በማባረር ቅብዐትን የሚያነሡ መጻሕፍትን በማስወገድ ግንኙነታችንን ማሳመር አንችልም፡፡ ነገ አባታችን ማኅበሩን
ሰብስበው ዳግም ጥምቀት መፈጸም የለበትም እናንተም ስታስተምሩ ጥምቀት እንደማይገባ ተናገሩ ብለው አጀንዳ አስይዘው ፈርሙ ቢሉ የሚፈርም
ይኖራል በእርግጠኝነት፡፡ የማኅበሩ ዓላማ ነፍሳትን ማዳን ነው፡፡
ያስተምራል ቀኖና ቤተክርስቲያን በሚያዝዘው መልኩ ሥርዓት ያስፈጽማል አለቀ፡፡ የማኅበሩ ሥራ መጻሕፍተ ቤተ ክርስቲያንን በሚገባ
ማስተማር ነው፡፡ ሌላው ነገር ለአባቶች የሚተው ነው፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ደብረ አሚን የተሰኘችው መጽሐፌ በማኅበሩ ሱቅ ለምን አትገባም
እያላችሁ ለጠየቃችሁኝ ኹሉ መልሴ ይኼ ነው፡፡ መጽሐፍህ ቅባቶች ዳግም ይጠመቁ ይላል ይህን ማሰራጨት አንችልም የሚል ነው፡፡ ታዲያ
መጠመቅ የለባቸውም ወይ? መልሱ ይገርመኛል፡፡ ለማንኛውም አቋም መያዝ ግድ ይለናል፡፡ በማንደራደርበት አንደራደር፡፡ የነቀርሳ በሽተኛ
ሰው እባክህ ነቀርሳ የሚለውን ስም አትጥራ ሕክምና የሚባለውንም ነገር አታንሣ እያለ ቢኖር መጨረሻው በበሽታው መሞት እንጂ ከበሽታው
ማገገም አይችልም፡፡ ስሙ አይጠራ ስላልን ብቻ በውስጣችን ያለውን ነቀርሳ ያስወገድን ከመሰለን ተሳስተናል፡፡ ገና ለገና ከአባ ዮሴፍ
ጋር ተስማምተን እንድንኖር በሚል አመለካከት መንጋውን ማጣት የለብንም፤ ትክክለኛውን ትምህርትም መዘንጋት የለብንም፡፡
2ኛ.
ለዘብተኛ አመለካከት ላላቸው
==============================
እነዚህ ሰዎች ቅባት ተዋሕዶ
ተብሎ ልዩነቱ ሲነገር ለምን ልዩነታችንን እናሰፋለን ባዮች ናቸው፡፡ ታዲያ ለምንድን ነው ስለፕሮቴስታንት፣ ስለካቶሊክ የምንጽፈው
የምናስተምረው? ቅባት ከእነዚህ የተለየ ነውን? ሁለት ጓደኛሞች
ተኝተው ሳለ የአንዱን እግር ጅብ ይይዘዋል፡፡ ያንጊዜ ጓደኛው ፈርቶ አረ ምንድን ነው? ይለዋል ያ በጅብ የተያዘው ልጅም ተው ዝም
በል የእኔን እግር ነው አለ የሚባል ተረት አለ፡፡ መርጡለ ማርያም ላይ ስብሰባ የተደረገው አባ ዐሥራት ላይ ሥልጠና ሲሰጡ ሲመረቁም
ዝም ስላልን ነው፡፡ ዛሬ መርጡለ ማርያም ላይ ከሸፈ ያልነው የቅባቶች ጉባዔ ነገ የኾነ ቦታ ላይ ማንም ሳይጠይቃቸው ስብሰባቸውን
እንደሚያካሂዱ እርግጠኛ ነኝ፡፡ እስከመቼ ነው ቆይ እንዲህ ስንጃጃል የምንኖረው? ቤተክርስቲያኒቱ እኮ የእኛ ናት፡፡ ማንም ሲፈነጭባት
ዝም ማለታችን የጤና ነው? ስለዚህ ጉዳይ መጻፍም መናገርም ፖለቲካ የሚመስላቸው ነገር ግን ቤተክርስቲያን የሚመላለሱ ሰዎች አሉ፡፡
እስከመቼ ነው ቤታችንን እየለቀቅን የምንሄደው? እነርሱ ለአንድ ጉባዔ እስከ 600 ሺህ ብር ድረስ ወጭ እንደሚደረግላቸው እየሰማን
ነው፡፡ በእውነት ይህ ገንዘብስ ከየት የመጣ ይኾን? አባ ማርቆስ እንዲነሡልን የተጋነውን ያህል አሁን መትጋት ያቃተን ለምንድን
ነው? አባ ማርቆስ ጋር የግል ጠብ ያለን እስኪመስል ድረስ እርሳቸው ከሄዱ በኋላ ኹሉም ተሸፋፍኖ ነው ለጥ ያለው፡፡ የመርጡለ ማርያም
ጥቃት ለዚህም ጥቃት ኾኖ ካልተሰማን ቤተክርስቲያን አንዲት ናት የምንለው የት ላይ ነው? በአጼ ሱስንዮስ ዘመነ መንግሥት ጎንደር
በነበረው የእርስ በርስ ግድያ ላይ የጎጃም ገበሬዎች ሳይቀሩ ሰማእትነት አያምልጠን ብለው ጎንደር ላሄደው በሰማእትነት አርፈዋል፡፡ ታዲያ የእኛ ለዘብተኛ መኾን ምንድን ነው? በፍናፍንት ሃሳብስ እስከ መቼ
ድረስ ነው የምንቀጥለው?
ይህን
ዛሬ የከሸፈውን ሙከራ ቀላል አድርጋችሁ ከተመለከታችሁት ነገ ምን እንደሚመጣ ማሰብ አያዳግትም፡፡ በራሳችን በቤተክርስቲያን ውስጥ
ወልድ ዋሕድ በተዋሕዶ ከበረ ብለን ለማስተማር እየተሸማቀቅን እስከመቼ ነው የምቀጥል? እስከ መቼ ድረስስ ዲማ እየሄድን ስቆርብና
ስናስጠምቅ እንኖራለን? አስቡት እንጂ፡፡ ነገ ዲማ ላይስ ምን እንደሚፈጠር ምን እናውቃለን? ሥራ እንሥራ ካላችሁ እንደ ኮርኮች
የራሳችንን አጥቢያዎች የራሳችንን አድባራት እና ገዳማት ነጻ እናውጣቸው፡፡ እዚሁ ባለንበት ቦታ ክርስትና እናስነሣ፣ ተክሊል እንፈጽም፣
ንስሐ እንፈጽም እንቁረብ፡፡ ይህ ጉዳይ ሰፊ ውይይት የሚጠይቅ ይመስለኛል፡፡ የዛሬው ጉዳይ ካላስተማረን የእኛ የስም ተዋሕዶነት
አይጠቅመንም፡፡ ከታች በፎቶ በምታዩት መልኩ ነው የመርጡለ ማርያም የተዋሕዶ ልጆች ቅባቶችን ከቤተክርስቲያን ያባረሯቸው፡፡ ቅባቶችም
ከዛፍ ሥር በምታዩት መልኩ እየተነጋገሩ ናቸው፡፡
==================
ታኅሣሥ
22/2011 ዓ.ም
ደብረ
ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ