Wednesday, December 12, 2018

የጸሎት ጊዜያት!


ባለፈው ስለ ሰንበተ ሰንበታት አከባበር ጽፌ የነበረ ሲኾን ብዙዎቻችሁ ሌሎች መምህራን ከጻፉት ጽሑፍ ጋር ተለያየብን ብላችሁ ጠይቃችሁኛል፡፡ እኔ የጻፍሁላችሁ ሰንበተ ሰንበታት ባሕረ ሐሳብ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ስለዚህ ግራ ያጋባችሁን ነገር ብዥታውን ለማስወገድ ተጨማሪ የጸሎት ጊዜያት የሚባሉት ልዩ የጸሎት ጊዜያትን ማሳወቅ እፈልጋለሁ፡፡ እነዚህን የጸሎት ጊዜያትም የምጽፍላችሁ ከዚያው ከባሕረ ሐሳብ መጽሐፎቻችን ነው፡፡
1ኛ. ሰንበተ ሰንበታት
=============
ሰንበተ ሰንበታት ማለት ጸሎትን ወደ እግዚአብሔር የሚያሳርጉበት ዕለት ማለት ነው፡፡ በዓመቱ ከሚውሉ ሰንበታት ኹሉ ተለይታ ጸሎት ወደ እግዚአብሔር የሚሳርጉባ እሁድ ናት፡፡ ይች ዕለትም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግመኛ ለሚመጣባት ሰንበተ ሰንበታት አምሳል ናት፡፡ ሰንበተ ሰንበታት በዓመት ሦስት ጊዜ ይከበራል፡፡ በርካታ የጸሎት ጊዜያት አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ሰንበተ ሰንበታት አንዱ ነው፡፡ የአከባበሩ ሥርዓት  እንደሚከተለው ነው፡፡
ዘመን መለወጫ (ዕለተ ዮሐንስ) ሰኞ ከዋለ ከዚህ ሰኞ ጀምሮ ከሰኞ ውጭ ከዋለ ግን ካለፈው ወይም ከሚመጣው ሰኞ እፈልጋለሁጀመረን 133 ቀናትን እንቆጥራለን ያች 133ኛዋ ዕለት እሁድ ናት፡፡ ይች እሁድ የመጀመሪያዋ ሰንበተ ሰንበታት ትባላለች ማለት ነው፡፡ ከዚህ ጀምረን ሰኞን አንድ ብለን ቀጣይ 133 ቀናትን ስንቆጥር ኹለተኛዋን ሰንበተ ሰንበታት እናገኛለን፡፡ ሦስተኛዋ ሰንበተ ሰንበታት ግን ከኹለተኛዋ ሰንበተ ሰንበተ ሰንበታት ቀጥለን 98/99 ቀናትን ቆጥረን የምናገኛት እሁድ ናት፡፡ እዚህ ላይ ግን ዕለተ ዮሐንስ መቼ መቼ ሲውል ነው ያለፈውን ሰኞ የምንወስደው መቼ መቼ ሲውልስ ነው የሚመጣውን ሰኞ መነሻ የምናደርገው የሚለውን የሚያብራራልን ካለ እፈልጋለሁ፡፡ የተመለከትኳቸው ውሱን መጸሕፍት በዚህ ዙሪያ ሰፊ ማብራሪያ ስላላገኘሁባቸው ነው፡፡ ሰንበተ ሰንበታት ግን የሚውሉት አንዱ በጥር አንዱ በግንቦት አንዱ ደግሞ በጳጉሜን ወር ላይ ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የሰንበቶች ሰንበት የምትባለዋ ዕለት እግዚአብሔር ዓለምን የፈጠረባት፣ የተጸነሰባት፣ ከሙታን ተለይቶ የተነሣባት፣ ዳግመኛም ዓለምን ለማሳለፍ የሚመጣባት ዕለተ እሁድ ናት፡፡
2ኛ. ሰንበተ ረቡዕ
=============
ይህም ለእግዚአብሔር ጸሎት የሚደረስበት ልዩ ዕለት ነው፡፡ ይህን ዕለት ለማግኘት አቆጣጠሩ እንደሚከተለው ነው፡፡ ዘመን መለወጫ (ዕለተ ዮሐንስ) ኀሙስ ከዋለ ከኀሙስ ጀምረን በሌሎች ዕለታት ከዋለ ግን ከሚመጣው ኀሙስ ጀምረን 91 ቀናትን በመቁጠር የሚገኝ ነው፡፡ አቆጣጠሩ ካለፈው ኀሙስም የሚጀምርበት አለ፡፡ (መቼ መቼ ሲኾን የሚለውን ግን አሁንም ሊቃውንቱ እንዲያብራሩልን እጠይቃለሁ)፡፡ የሚውለውም አንዱ በኅዳር/ታኅሣሥ ፤ አንዱ በየካቲት /መጋቢት፤ አንዱ ግንቦት/ሰኔ፤ አንዱ ነሐሴ/ጳጉሜን ይውላሉ፡፡ ዕለቱ ረቡዕ ይኾናል በዓመት 4 ጊዜም ይውላል ማለት ነው፡፡
3ኛ. ርኅወ ሰማይ
=============
ይህ ዕለት ሰማይ የሚከፈትበት ሲኾን ውኃ እና ዘይት ላይ ተጸልዮ ለፈውስና ለረድኤት የሚጠመቁበትና የሚጠጡበት ልዩ የጸሎት ዕለት ነው፡፡ ዕለቱን ለማወቅ ከጳጉሜን 2/3 ጀምረን በ52 በ52 ቀናት በመከፋፈል ይገኛል፡፡ በዓመት 7 ጊዜም ይውላል፡፡ ይኸውም በጥቅምት 20 በታኅሣሥ 12 በየካቲት 4 በመጋቢት 26  በግንቦት 18 በሐምሌ 10 በጳጉሜን 2/3፡፡ አንዳንድ መጻሕፍት የታኅሣሡን ታኅሣሥ 22 አድርገው ሌሎችን እንዳሉ ይወስዳሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ የሐምሌውን ሐምሌ 20 አድርገው ሌሎችን ባሉበት ያከብራሉ፡፡ የጳጉሜኑንም እንዲሁ አንዳንዶች 2ን አንዳንዶች 3ን ወስደው ሌላውን ባሉበት ያከብራሉ፡፡ 52 የሚለው ቀን የሚቆረው ከማግስት ጀምሮ ነው፡፡
4ኛ. ምሕላ ዘስብከተጌና
=============
ዕለቱ እሁድ ይውላል፡፡ አቆጣጠሩም ታኅሣሥ 1 ኤልያስ የሚውልበትን ቀን መነሻ ያደርጋል፡፡ በዚህም መሠረት ኤልያስ ማክሰኞ ሲውል ታኅሣሥ 13፣ ረቡዕ ሲውል ታኅሣሥ 12፣ ሐሙስ ሲውል ታኅሣሥ 11፣ ዓርብ ሲውል ታኅሣሥ 10፣ ቅዳሜ ሲውል ታኅሣሥ 9፣ እሁድ ሲውል ታኅሣሥ 8 ከአቡነ ተክለ አልፋ በዓል ጋር ይደረባል፤ ሰኞ ሲውል ታኅሣሥ 7 ይውላል ማለት ነው፡፡
5ኛ. ምሕላ ዮሐንስ
=============
ይህ የጸሎተ ምሕላ ጊዜ ጳጉሜንን መነሻ አድርጎ የሚቆር ነው፡፡ ይኸውም ጳጉሜን 1 ዓርብ ከዋለ ነሐሴ 29፣ ጳጉሜን 1 ቅዳሜ ከዋለ ነሐሴ 28፣ ጳጉሜን 1 እሁድ ከዋለ ጳጉሜን 4፣ ጳጉሜን 1 ሰኞ ከዋለ ጳጉሜን 3፣ ጳጉሜን 1 ማክሰኞ ከዋለ ጳጉሜን 4፣ ጳጉሜን 1 ረቡዕ ከዋለ ጳጉሜን 3፣ ጳጉሜን 1 ሐሙስ ከዋለ ጳጉሜን 2 ይውላል፡፡ ምሕላ ዮሐንስ ከነሐሴ 28 አያንስም ከጳጉሜን 4ም አይበልጥም፡፡ ከነሐሴ 28 እስከ ጳጉሜን 4 ብቻ እንዲውል ተደርጎ የተሠራ የጸሎት ጊዜ ነው፡፡
6ኛ. ምሕላ መስቀል
=============
ይኸኛው የምሕላ ጸሎት አቆጣጠሩ መስከረም 1ን መነሻ ያደረገ ነው፡፡ መስከረም 1 ረቡዕ እና ሰኞ ከዋለ መስከረም 24፣ መስከረም 1 ሐሙስ እና ማክሰኞ ከዋለ መስከረም 23፣ መስከረም 1 ዓርብ ከዋለ መስከረም 22፣ መስከረም 1 ቅዳሜ ከዋለ መስከረም 19፣ መስከረም 1 እሁድ ከዋለ መስከረም 20 ይውላል፡፡ የዚህ ጸሎት ጊዜ ከ19 አያንስም ከ24 አይበልጥም፡፡ ከመስከረም 19-መስከረም 24 ድረስ ባሉ ቀናት ውስጥ ይውላል፡፡
7ኛ. ምሕላ ጽጌያት
=============
ይህ ምሕላ የአበባዎች ምሕላ ነው፡፡ የዚህ ምሕላ አቆጣጠር መነሻው የኅዳር ወር ነው፡፡ ኅዳር 1 ዓርብ ሲውል ጥቅምት 29፤ ኅዳር 1 ቅዳሜ ሲውል ጥቅምት 28፤ ኅዳር 1 እሁድ ሲውል ኅዳር 1፣ ኅዳር 1 ሰኞ ሲውል ኅዳር 3፣ ኅዳር 1 ማክሰኞ ሲውል ኅዳር 2፣ ኅዳር 1 ረቡዕ ሲውል ኅዳር 1፣ ኅዳር 1 ሐሙስ ሲውል ጥቅምት 30 ይውላል፡፡ ይህም ከጥቅምት 28 አያንስም ከኅዳር 4ም አይበልጥም፡፡ ከጥቅምት 28 እስከ ኅዳር 4 ባለው ውስጥ ይውላል ማለት ነው፡፡
8ኛ. ምሕላ በአተ ክረምት
=============
ይህ ምሕላ የክረምት መግባት (ግባት) ምሕላ ነው፡፡ አቆጣጠሩ መነሻ የሚያደርገው የሰኔ ሚካኤልን (ሰኔ 12ን) (አዊት)ን ነው፡፡ ሰኔ 12 ረቡዕ ሲውል ሰኔ 21፣ ሰኔ 12 ሐሙስ ሲውል ሰኔ 20፣ ሰኔ 12 ዓርብ ሲውል ሰኔ 19፣ ሰኔ 12 ቅዳሜ ወይም ሰኞ ሲውል ሰኔ 23፣ ሰኔ 12 እሁድ ወይም ማክሰኞ ሲውል ሰኔ 22 ይውላል፡፡ ከሰኔ 19 አያንስም ከሰኔ 23ም አይበልጥም፡፡ ምንጊዜም ከሰኔ 19-ሰኔ 23 ድረስ ባሉ ቀናት ብቻ ይከበራል፡፡
ለዚህ ጽሑፍ ምንጮቼ የባሕረ ሐሳብ መጻሕፍት ናቸው፡፡
================
© መልካሙ በየነ
ታኅሣሥ 3/2011 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

No comments:

Post a Comment