Friday, October 2, 2015

ልኩን ያለፈ አሜን ከጭብጨባና እልልታ ጋር

©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
እንደምን ሰነበታችሁ አምላከ ቅዱሳን እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ በሰላም በጤና አደረሳችሁ። በእርግጥ የመልካም ምኞት መግለጫዬ ብዙ ቀናትን ያሳለፈ መሆኑን እረዳለሁ። ነገር ግን የመናገር እና የመጻፍ መብቴን ፌስቡክ ስላልገደበኝ ብዬም በዓሉ ከመድረሱ በፊት ሳምንት እና ሁለት ሳምንት ቀድሜ እንኳን አደረሳችሁ አልልም። በዓላት የሚውሉባቸው ቀናት እንደ ፌስቡክ አቆጣጠር ቢሆን ኖሮ አንድ ዓመት የሚባለው 365 1/4 አይሆንም ነበር። ለምሳሌ የዘመን መለወጫ መስከረም 1 መሆኑን የቀን መቁጠሪያችን ያስረዳል። በፌስቡክ ግን ጳጉሜን 1 ጀምሮ ዘመን ይለወጣል። እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሳችሁ የሚሉ መልካም ምኞት መግለጫዎች እኔ እቀድም እኔ እቀድም እየተባባሉ በሚመስል ሁኔታ በየግለሰቦች ይለጠፋሉ። ሳንደርስ እንኳን አደረሳችሁ መባባልን ማን አመጣ ብትሉኝ መልሴ ፌስቡክ የሚል ነው። አንድ ደቂቃ ስንት ተአምር እንደምትሰራብን ያልተረዳን ሰዎች ነን እንዲህ ከሳምንት በፊት እንኳን አደረሳችሁ የምንባባለው። ለማንኛውም መልካም ምኞትን በተመለከተ በሌላ ርእስ እንገናኝ ይሆናል አምላክ ፈቃዱ ይሁንና። ለጊዜው ወደ ዛሬው ርእስ እንመለስ።
አሜን /amen/ የሚለው ቃል ዓለምን ሁሉ ያስተሳሰረ ብቸኛ ቃል ነው። ቻይናዎችና ጃፓኖች ምን እንደሚሉ ባላውቅም ሁሉም የዓለም ቋንቋዎች ሁሉ አሜን የሚለውን ቃል እንደሚጠቀሙ ይነገራል። አሜን ማለት ይሁን፣ይደረግ የሚል ትርጉም አለው። ወደ ሀገራችን ከዚያም ወደ ቤተክርስቲያናችን እንግባና አሜንን እንመልከተው። አሜን የሚለው ቃል በቤተክርስቲያናችንም ከላይ ያየነውን ትርጉም ይይዛል። አባቶቻችን ሲመርቁን አሜን እንላለን ምርቃታችሁ ይሁንልን ይደረግልን ለማለት ነው። አሁን አሁን ግን ልክ እና መጠኑን ያለፈ አሜን እንዲሁም እልልታና ጭብጨባ የዋጠን ይመስለኛል። የተሐድሶ መናፍቃን ካስለመዱን መጥፎ ጸባያችን መካከል አንዱ ይሄው ነው። ሁሉም የሚያምረው ልክ እና መጠን ሲኖረው ነው። ማር ሲበዛ ይመራል አይደል ያለው የሀገሬ ሰው። ልክ እና መጠንን ከምታስተምር ቤተክርስቲያን ውስጥ ልክ ያለፈ ነገርን ማድረግ ድፍረት ሳይሆን አይቀርም። በእርግጥ ይህን ልክ እንድናልፍ "የዘመኑ መምህራንም" እጅ አለበት። የሚናገሩትን ነገር የሚጀምሩት አስጨብጭበው ነው። ከዚያም ርእስ የሌለው "ትምህርታቸውን" ይጀምራሉ በእርግጥ ያልተዘጋጀ መምህር ከዚህ የተሻለ ነገር ማድረግ አይችልም። በተደጋጋሚ "ክብር ለእሱ ይሁን" እያሉ ህዝቡን ያስጨበጭባሉ እልል ያስብላሉ። ሕዝቡም የሚባለውን ነገር ሳይሰማ እንኳ ያጨበጭባል እልል ይላል። "እስኪ እጃችሁን አሳዩኝ" ይላል "መምህሩ" ህዝቡ አሁንም ያጨበጭባል አይሰማም ይላቸዋል አሁንም ከቅድሙ አብልጠው ያጨበጭባሉ። የኪነ ጥበብ ሰዎች ዘፈን ሊዘፍኑ ወደ መድረክ ሲመጡ የሚደረግላቸውን አቀባበል በቤተክርስቲያናችን አውደ ምሕረቶች እያየነው ነው። 
በተለይ ትላልቅ በዓላት ላይ ደግሞ እንዲህ ማድረግ የሚወዱ የመድረክ መሪዎችም አሉ። አንዴ ስላስለመደው ገና የዕለቱ መምህር እገሌ ናቸው ሲል ህዝቡ ያጨበጭባል። መምህሩ ሲመጡ እያጨበጨቡ ይቀበሏቸዋል። ፋታ የሌለው ጭብጨባና እልልታ በጣም ስልችት የሚል። መምህሩም "ክብር ለእሱ ይሁን" ይላል ህዝቡም ያጨበጭባል። እሽ ክብሩ ለማን ይሁን ብለን ነው ያጨበጨብነው? እሱ የተባለው ማነው? ሰይጣን ነው ወይስ እግዚአብሔር ነው? ዝም ብለን መጮህ አይደለም እሱ የጅራፍ ባሕርይ ነው። ዝም ብሎ እልል ማለት አይደለም እሱ የእንቁራሪት ባሕርይ ነው። "ክብር ለእሱ ይሁን" የተባለለት እግዚአብሔር ከሆነስ የቱን ክብሩን ነው በእንደዚያ ያለ እልልታና ጭብጨባ የምንገልጸው? አንዳንዶች ደግሞ "አይሰማም እጃችሁ የት አለ?" እያሉ ደግመው ደጋግመው ያስጨበጭባሉ። ክብሩ ለእግዚአብሔር ነው ከተባለ ያስጨበጨቡንንና እልል ያስባሉንን ጩኸት እንዴት እግዚአብሔር አልሰማም? አልተሰማንም የሚሉ እነርሱ ናቸው ያስጨበጨቡን ደግሞ ለእግዚአብሔር ብለው ነው ታዲያ ሁለቱ ሃሳብ አይጣረስም ትላላችሁ? 
በእርግጥ አሁን አሁን ልማድ አድርገነዋል። "የሰማነውን ቃለ እግዚአብሔር በልቡናችን ያሳድርልን" ተብለን ስንመረቅ አሜን በማለት ፋንታ ትርጉም በማይሰጥ መልኩ በጭብጨባ እንመልሳለን። "ቃለ ሕይወትን ያሰማልን" ስንባል ደግሞ በእልልታ እናቀልጠዋለን። ትርጉሙ ምን ይሆን? ይህን የምለው ግን ለእውነተኞች መምህራን አይደለም እነርሱ እንዲህ ስለማያስደርጉ። እንደአጠቃላይ ጭብጨባ በሚያስፈልግበት ጭብጨባ፣እልልታ በሚያስፈልግበት እልልታ፣አሜን ማለት በሚያስፈልግበት አሜን ማለት ይገባል እንጅ ከመጠን ባለፈ ያውም ያለቦታው ማጨብጨብ እና እልል ማለት ትርጉም አልባ ነው። ቃለ እግዚአብሔርም ለመማር የመጣን ሰው ለጆሮ በሚሰቀጥጥ እልልታና ጭብጨባ ልናደነቁር አይገባም።

Wednesday, September 23, 2015

አፍርሳችሁ ሥሩኝ

©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ሰላምና ጤናን የምመኝላችሁ ውድ ጓደኞቼ ቸርነት የማያልቅበት ባለፀጋ ሁሉን የፈጠረ አምላክ እንኳን ከዘመነ ሉቃስ ወደ ዘመነ ዮሐንስ አሸጋገራችሁ፡፡ አዲሱ ዓመት ከጥል ወደ ፍቅር፣ ከኃጢአት ወደ ጽድቅ፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከባርነት ወደ ልጅነት፣ ከቂም ከበቀል ወደ ይቅር ባይነት፣ ከበደል ከርኩሰት ወደ ንስሐ የምንመለስበት እንዲያደርግልን አምላካችንን ዘወትር በመትጋት እንለምን፡፡ በዚህ ዘመን የምንሰማውና የምናየው ነገር ሁሉ አስፈሪ ነው፡፡ ፍቅር ከሰው ልጆች እጅግ ርቃ የሄደችበት ዝርፊያ፣ ውንብድና፣ ስርቆት፣ መግደል የበረታበት ጊዜ ነው፡፡ ልማድ ሆኖብኝ ነው እኔም አንኳን አደረሳችሁ ያልኳችሁ እንጅ ለዚህ ዘመን ከመድረስስ አለመድረስ በተሻለ ነበር፡፡ ኃጢአት በአብዝተን ከፈጣሪያችን ጋር በዓይነ ቁራኛ የምንተያይበት የሰይጣን ባለሟልነት የበረከተበት ዘመን ነው፡፡ በእውነት የጥፋት ውኃ ቢኖርማ መጥፋት የነበረብን እኛ የዛሬዎቹ ነበርን ግን ቸርነቱ ምጡቅ የሆነ ፈጣሪ አለንና ትእግሥቱ ከለከለው፡፡ አቤት… ጉዳችን!!! አቤት… ኃጢአታችን!!! አቤት … ውርደታችን!!!
እኔ ለኃጢአት እጄን ከሰጠሁ ሰነባበትሁ ለዛም ነው አምላክ እንድጓዝበት ከሰጠኝ መንገድ ይልቅ የተሻለ የመሰለኝን ሰፊ መንገድ መርጨ መድረሻው በውል በማይታወቀው ጉዞ የምባክነው፡፡ ኃጢአትን ልትሰራት ስታስብ አቤት ያላት ጣፋጭነት አቤት ያላት ሰላም፡፡ ኃጢአትን ከመሥራትህ በፊት የሚፈጥርልህን ደስታ ከሰራኸው በኋላ አታገኘውም፡፡ ሰይጣን በጎ አስመስሎ የሚያሳየኝን ኃጢአት ስዳስስ ብዙ ባክኛለሁ እንዲያውም ኃጢአትን ከመሥራት ባለፈ መጠሪያዬም ሆኗል፡፡ ለኃጢአት እጄን አንሥቼ ምርኮኛነቴን አረጋግጫለሁ፡፡ በዚህ ብርሃናዊ በመሰለው የኃጢአት ዘመን ሁሉ የማይታሰበኝ ጽድቅ እጅግ ርቆኛል፡፡ ቅዳሴው፣ ኪዳኑ፣ የዕጣኑ ሽታ፣ የእመቤታችን ተአምር፣ የእነ እማሆይ መክፈልት… ሁሉንም ከመናፈቅ ባለፈ አይቻቸውም፣ ሰምቻቸውም፣ ቀምሻቸውም አላውቅም፡፡ ዘመኑ ዘመንን እየወለደ ይከንፋል እኔም በዕድሜዬ ላይ ዕድሜን እየጨመርሁ እኖራለሁ የልደት ዘመኔን አከብራለሁ ለካ ሞትን እየቀረብሁት እንጅ እየራቅሁት አይደለም፡፡ ጉዞዬ ወደ ሞት እየተቃረበ መሆኑን ግን እንዳላስብ ሰይጣን የማስብበትን ኅሊና ሰውሮብኛል፡፡ መተኛት፣ መነሣት፣ መብላትና መጠጣት መሳቅና መጫወት፣ መዝፈንና መጨፈር ብቻ ነው የዕለት ከዕለት ተግባሬ፡፡ ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደት፣ ምጽዋት የሚባሉት ምግባራት በስም ለመጥራት እንኳ ሳልረሳቸው አልቀረሁም፡፡
መጾም ሲሰለቸኝ መብላትን እመርጣለሁ፣ መመጽወት አልችል ስል እንዲያውም መስረቅን ገንዘቤ አደረግሁት ከዚህ የኃጢአት ሸክሜ ጋር ደግሞ እምነት አለኝ እላለሁ፡፡ መጾም ባትችልም እምነትህን አትለውጥ፣ መስገድ ባትችልም እምነትህን አትለውጥ፣ መመጽወት ባትችልም እምነትህን አትለውጥ እያሉ ያስተማሩኝ መምህር ትዝ ይሉኛል፡፡ ለመብላት፣ ለመጠጣት፣ ለመዝፈን ለመደነስ፣ ለመጨፈር ሲሉ ከተዋሕዶ እምነት የወጡ ወገኖቼ ትዝ ይሉኛል፡፡ ጹም፣ ጸልይ፣ መጽውት፣ ስገድ ከምትለዋ እምነታችን አፈንግጠው እንዲህ ወደማይለው ምንፍቅና የተሰገሰጉ ብዙዎች ናቸው፡፡ እኔ ግን ኃጢአቴን እንደያዝኩ በኃጢአት እንደተጨማለቅሁ፣ በኃጢአት ሸክም እንደጎበጥሁ እምነቴን ይዤ ተቀምጫለሁ፡፡ ከእምነት ሕጸጽ ይልቅ የምግባር ሕጸጽ ይበጅሃል ያሉኝን መምህር በተለየ ሁኔታ እወዳቸዋለሁ፡፡ ጻድቅ ሰባት ጊዜ ይወድቃል ሰባት ጊዜም ይነሣል እያሉ ያጽናኑኝ አንድ አባት ደግሞ የሁልጊዜ ትዝታዬ ናቸው፡፡

ታዲያ በዚህ የኃጢአት ዘመኔ አምላኬ ቢጠራኝስ? ከባዱ ችግር ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡ እኔ አሁን ላይ ሆኘ ሳስበው ኃጢአት መራራ ሆኖብኛል ስለዚህ ልተፋው እወዳለሁ፡፡ አዲስ ሰው እንድሆንም አፍርሳችሁ ልትሠሩኝ አደራው የናንተ ነው፡፡ ከወሬ ያለፈ የተግባር ሰው እንድሆን ደግሞ የናንተን ድጋፍ አሻለሁ፡፡ የምታፈርሱት በኃጢአት የቆሸሸ ኅሊናዬን ነው፡፡ አንተ ለእኔ መጥፋት ተጠያቂ እንዳትሆን እኔን ማትረፍ አለብህ፡፡ እኔም እንዲሁ ላንተ መጥፋት ተጠያቂ እንዳልሆን አንተን ማትረፍ አለብኝ፡፡ አንተ ለእኔ እኔም ለአንተ መዳን ምክንያቶች ነን፡፡ የመዳን ቀን ደግሞ ዛሬ ነው ነገ ሌላ ቀን ስለሆነ የነገንም መኖር ስለማናውቅ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ ሁሉ የኃጢአት ሸክም ለመገላገል አፍርሳችሁ ልትሰሩኝ ይገባል፡፡ ካህናት አባቶቼ የተሰጣችሁ ሥልጣን በእውነት ግሩም ነው እኮን፡፡ እናንተን ለእኔ ባይሰጠኝ ኖሮ በኃጢአት እንደጨቀየሁ ወደ ገሐነመ እሳት እጣል ነበር ነገር ግን እናንተን ስለሰጠኝ አፍርሳችሁ ትሠሩኛላችሁ፡፡ የተሸከምኩትን ከባድ ሸክም አራግፋችሁ ቀና ብየ እንድሄድም ታደርጉኛላችሁ፡፡ የኃጢአቴን እድፍና ቆሻሻ በንስሐ ሳሙና ታጥቡልኛላችሁ፡፡ እኔ ራሴን ለእናንተ አሳያለሁ የውስጤንም ማንነት እገልጥላችኋለሁ እናንተ ደግሞ አዲስ ሰው እንድታደርጉኝ አፍርሳችሁ ልትሰሩኝ የአምላክ ትእዛዝ አለባችሁ፡፡ ስለዚህም በኃጢአት የተገነባውን ማንነቴን በንስሐ አፍርሳችሁ እንድትሰሩኝ እማጸናችኋለሁ፡፡

Wednesday, August 26, 2015

ባማ

©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በርካታ አማርኛ ያልሆኑ ቃላትን እናገኛለን፡፡ ለምሳሌ፡- አማኑኤል፣ ኤልሻዳይ፣ አዶናይ እና የመሳሰሉትን ማየት ይቻላል፡፡ አሁን እነዚህ አማርኛ ያልሆኑ ቃላት ከእብራውያን፣ ከሮማውያን ወይም ከግሪካውያን የተወሰዱ ናቸው፡፡ ከሌሎች መወሰዳቸው ችግር ባይሆንም በትክክል ትርጉሙን መረዳት አለመቻል ግን ትልቅ ስህተት ነው፡፡ አማርኛ ብቻ የሚናገር ሰው ላይ በጥሬው ማለት ሳይተረጎሙ የቀሩ ቃላትን ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እየመዘዝን መጠቀም ትልቅ ሊያስብለን የሚችል አይመስለኝም፡፡ በእርግጥ ትርጉሙን ካወቅንና ለማሳወቅ ጥረት ካደረግን እውነትም ትልቆች ልንባል እንችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን አሁን እየተመለከትን ያለነው ነገር የዚህ ተቃራኒ ነው፡፡ እነዚህን መሰል ቃላት በባትሪ እየፈለግን ለመዝሙር ወይም ለስብከት ርእስነት ስንጠቀም እንስተዋላለን ትርጉማቸውና መዝሙሩ ወይም ስብከቱ ግን የማይገናኙ ነገሮች ናቸው፡፡ እኔ አሁን ማሳየት የምፈልገው ቃል ከላይ በርእሱ ላይ ያስቀመጥኩትን ቃል ይሆናል “ባማ”፡፡ ምናልባት ዘግይቼ ሊሆን ይችላል ለመጻፍ ያነሣሣኝ ግን በዩ ቲዩብ ላይ ኦርቶዶክስ መዝሙር ብየ ስፈልግ አንድ መዝሙር ስሰማ እጅግ በጣም ስለገረመኝ ነው፡፡ የመዝሙሩን ግጥሞች እና የአስተዋዋቂውን የባማ አተረጓጎም እንዲህ እንመልከተው፡፡ ማዳመጥ የሚፈልግ ደግሞ ይህንን ሊንክ ይጫን፡፡ https://www.youtube.com/watch?v=3fQzC6SfBpE
“ባማ የሚለው ቃል የእብራይስጥ ቃል ሲሆን ትርጉሙም ከፍታ ማለት ነው” ይላል አስተዋዋቂው፡፡ ከዛም ዘማሪዋ ይህንን ግጥም ትዘምረዋለች፡
ባማ በማ ነው ለሕይወቴ
ውበት ሰላም ነው ለቤቴ
ክብር የሆነኝ ከፍታ
እርሱ ነው የሞተልኝ ጌታ
መዳፌን አረሰረሰው
ጓዳዬን በረከት ሞላው
ሹመቴ ሆነኝ ከፍታ
ኢየሱስ የነፍሴ ጌታ
መቅረዜ ሆነኝ ብርሃን
ደህንነት ማረፊያ ዙፋን
ጠባቂ የነፍሴ እረኛ
ትጉህ ነው ከቶም አይተኛ
ከትቢያ ከወደቅሁበት
አነሣኝ መዳኔን ሽቶ
በፍቅር ምህረቱ በዝቶ
አዳነኝ ስለኔ ሞቶ
የጠላት ክንዱን አውርዶ
ቀኝ ሆነኝ በኃይሉ ወርዶ
ለክብሩ አንበረከካለሁ
ለስሙ እዘምራለሁ

በእውነት “ባማ” የሚለው ቃል አስተዋዋቂው እና ዘማሪዋ እንዳሉት ነውን? አረ ምን ነካህ በፍጹም እንደምትሉኝ አልጠራጠርም፡፡ ታዲያ ትክክለኛ ትርጉሙን በጋራ እንመልከተዋ፡፡ ሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ሽፈራው 1997 ዓ.ም ባሳተሙት መጽሐፈ ግስ ወሰዋስው መርኆ መጻሕፍት ላይ ገጽ 322 ላይ እንዲህ ይተረጉሙታል፡፡ ባማ፡- በተራራ ላይ የተሠራ የጣዖት ቤት ካሉ በኋላ ለማስረጃነትም እንዲህ ይጽፋሉ “ምንት ውእቱ ባማ ዘተሐውሩ አንትሙ” ሕዝ 20÷29 ብለው ይደመድሙታል፡፡ ስለዚህ የባማ ትክክለኛ ትርጉሙ ከፍታ ማለት ሳይሆን ከፍታ ላይ የተሠራ የጣዖት ቤት ማለት ነው፡፡ ይህንን ከላይ ጀምረን መጽሐፉን እናንብበው፡፡ ሕዝ 20÷28-31 እነዲህ ይላል፡፡ እሰጣቸውም ዘንድ ወደማልኹላቸው ምድር ባገባኋቸው ጊዜ ከፍ ያለውን ኮረብታ ሁሉ ቅጠልማውን ዛፍ ሁሉ አዩ በዚያም መስዋእታቸውን ሠዉ በዚያም የሚያስቆጣኝን ቁርባናቸውን አቀረቡ፡፡ በዚያም ደግሞ ጣፋጩን ሽታቸውን አደረጉ በዚያም የመጠጥ ቁርባናቸውን አፈሰሱ፡፡ እኔም እናንተ ወደርሱ የምትሄዱበት ከፍታ ምንድር ነው? አልኋቸው፡፡ እስከዛሬም ድረስ ስሙ ባማ ተብሎ ተጠርቷል፡፡ ቁርባናችሁን ባቀረባችሁ ጊዜ እስከ ዛሬ ድረስ ልጆቻችሁንም በእሳት ባሳለፋችሁ ጊዜ እስከዛሬ ድረስ በጣዖቶቻችሁ ትረክሳላችሁን? የእስራኤል ቤት ሆይ ከእናንተስ ዘንድ እጠየቃለሁን? እኔ ሕያው ነኝና ከእናንተ ዘንድ አልጠየቅም ይላል ጌታ እግዚአብሔር፡፡” ምንም ሳልጨምር ምንም ሳልቀንስ ቃሉን እንዲህ ጻፍሁላችሁ፡፡ እንግዲህ የባማ ትክክለኛ ትርጉም ይኼው ነው፡፡
ሌላው ኪዳነወልድ ክፍሌ መጽሐፈ ሕዝቅኤልን ተርጉመው በ1917 ዓ.ም ባሳተሙት መጽሐፈ ሕዝቅኤል ከትርጓሜው ጋራ ገጽ 208 ላይ ግእዙን በአማርኛ እንዲህ ተርጉመውት እናገኛለን፡፡ “ወእቤሎሙ ምንት ውእቱ ባማ ዘተሐውሩ አንትሙ ህየ” እኔ አንድ ነኝ ስል አንድ ቦታ አሳይቻችሁ ነበር እናንተ የእኔን ትእዛዝ አፍርሳችሁ በየቦታው የሰራችሁት ጧት ማታ የምትሄዱበት ቤተ ጣዖት ምን ልዖል ነው ምን ልዕልና አለው አልኋቸው፡፡ “ወተሰምየ ስሙ ባማ እስከ ዛቲ ዕለት” ስሙ እስከዛሬ ድረስ ባማ ተባለ ባማ ማለት ልዑል ነዋኅ ማለት ነው ይላሉ፡፡ አሁንም እንደቅድሙ ሁሉ ባማ ማለት ልዑል ነዋኅ (ከፍታ) ማለት ነው፡፡ ከፍታነቱ ግን ከላይ ሲተረጉሙት ዘተሐውሩ የምትሄዱበት ቤተ ጣዖት ልዑል ነዋኅ ትልቅ ከፍታ ነው ብለውታል፡፡ ስለዚህ ባማ ማለት ከፍታ ላይ ያለ ጣዖት ማለት ነው፡፡ ባማ ማለት ከፍታ ብቻ ቢሆን ኖሮ ለምን ወደዚያ ቦታ ሄዳችሁ? መስዋእታችሁም የረከሰ ነው ባላላቸው ነበር፡፡ ስለዚህ ባማ ማለት ከፍታ ላይ የተሠራ ጣዖት ማለት ነው፡፡
ስለዚህ ቃላትን ዝም ብለን በሚመስለን እየተረጎምን የማይገባ ሥራ ባንሠራ እላለሁ፡፡ ምክንያም ኢየሱስ ክርስቶስን ባማ በማ ነህ ለሕይወቴ ማለት ምን ማለት ነው? በትክክለኛ ትርጉሙ ካየነው እኮ በጣም ከባድ ኑፋቄ ነው፡፡ “ኢየሱስ ክርስቶስ ለሕይወቴ ከፍታ ላይ የተሠራህ ጣዖት ነህ ማለት እኮ ነው” ሎቱ ስብሐት፡፡ እኔም እንዲህ በመጻፌ “አቤቱ ማረኝ ይቅር በለኝ ብዬ እጸልያለሁ” ማስተማር ስላለብን ነው፡፡ እባካችሁ ልብ እናድርግ እናስተውል፡፡

ፈጸምኩ