Wednesday, August 26, 2015

ባማ

©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በርካታ አማርኛ ያልሆኑ ቃላትን እናገኛለን፡፡ ለምሳሌ፡- አማኑኤል፣ ኤልሻዳይ፣ አዶናይ እና የመሳሰሉትን ማየት ይቻላል፡፡ አሁን እነዚህ አማርኛ ያልሆኑ ቃላት ከእብራውያን፣ ከሮማውያን ወይም ከግሪካውያን የተወሰዱ ናቸው፡፡ ከሌሎች መወሰዳቸው ችግር ባይሆንም በትክክል ትርጉሙን መረዳት አለመቻል ግን ትልቅ ስህተት ነው፡፡ አማርኛ ብቻ የሚናገር ሰው ላይ በጥሬው ማለት ሳይተረጎሙ የቀሩ ቃላትን ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እየመዘዝን መጠቀም ትልቅ ሊያስብለን የሚችል አይመስለኝም፡፡ በእርግጥ ትርጉሙን ካወቅንና ለማሳወቅ ጥረት ካደረግን እውነትም ትልቆች ልንባል እንችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን አሁን እየተመለከትን ያለነው ነገር የዚህ ተቃራኒ ነው፡፡ እነዚህን መሰል ቃላት በባትሪ እየፈለግን ለመዝሙር ወይም ለስብከት ርእስነት ስንጠቀም እንስተዋላለን ትርጉማቸውና መዝሙሩ ወይም ስብከቱ ግን የማይገናኙ ነገሮች ናቸው፡፡ እኔ አሁን ማሳየት የምፈልገው ቃል ከላይ በርእሱ ላይ ያስቀመጥኩትን ቃል ይሆናል “ባማ”፡፡ ምናልባት ዘግይቼ ሊሆን ይችላል ለመጻፍ ያነሣሣኝ ግን በዩ ቲዩብ ላይ ኦርቶዶክስ መዝሙር ብየ ስፈልግ አንድ መዝሙር ስሰማ እጅግ በጣም ስለገረመኝ ነው፡፡ የመዝሙሩን ግጥሞች እና የአስተዋዋቂውን የባማ አተረጓጎም እንዲህ እንመልከተው፡፡ ማዳመጥ የሚፈልግ ደግሞ ይህንን ሊንክ ይጫን፡፡ https://www.youtube.com/watch?v=3fQzC6SfBpE
“ባማ የሚለው ቃል የእብራይስጥ ቃል ሲሆን ትርጉሙም ከፍታ ማለት ነው” ይላል አስተዋዋቂው፡፡ ከዛም ዘማሪዋ ይህንን ግጥም ትዘምረዋለች፡
ባማ በማ ነው ለሕይወቴ
ውበት ሰላም ነው ለቤቴ
ክብር የሆነኝ ከፍታ
እርሱ ነው የሞተልኝ ጌታ
መዳፌን አረሰረሰው
ጓዳዬን በረከት ሞላው
ሹመቴ ሆነኝ ከፍታ
ኢየሱስ የነፍሴ ጌታ
መቅረዜ ሆነኝ ብርሃን
ደህንነት ማረፊያ ዙፋን
ጠባቂ የነፍሴ እረኛ
ትጉህ ነው ከቶም አይተኛ
ከትቢያ ከወደቅሁበት
አነሣኝ መዳኔን ሽቶ
በፍቅር ምህረቱ በዝቶ
አዳነኝ ስለኔ ሞቶ
የጠላት ክንዱን አውርዶ
ቀኝ ሆነኝ በኃይሉ ወርዶ
ለክብሩ አንበረከካለሁ
ለስሙ እዘምራለሁ

በእውነት “ባማ” የሚለው ቃል አስተዋዋቂው እና ዘማሪዋ እንዳሉት ነውን? አረ ምን ነካህ በፍጹም እንደምትሉኝ አልጠራጠርም፡፡ ታዲያ ትክክለኛ ትርጉሙን በጋራ እንመልከተዋ፡፡ ሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ሽፈራው 1997 ዓ.ም ባሳተሙት መጽሐፈ ግስ ወሰዋስው መርኆ መጻሕፍት ላይ ገጽ 322 ላይ እንዲህ ይተረጉሙታል፡፡ ባማ፡- በተራራ ላይ የተሠራ የጣዖት ቤት ካሉ በኋላ ለማስረጃነትም እንዲህ ይጽፋሉ “ምንት ውእቱ ባማ ዘተሐውሩ አንትሙ” ሕዝ 20÷29 ብለው ይደመድሙታል፡፡ ስለዚህ የባማ ትክክለኛ ትርጉሙ ከፍታ ማለት ሳይሆን ከፍታ ላይ የተሠራ የጣዖት ቤት ማለት ነው፡፡ ይህንን ከላይ ጀምረን መጽሐፉን እናንብበው፡፡ ሕዝ 20÷28-31 እነዲህ ይላል፡፡ እሰጣቸውም ዘንድ ወደማልኹላቸው ምድር ባገባኋቸው ጊዜ ከፍ ያለውን ኮረብታ ሁሉ ቅጠልማውን ዛፍ ሁሉ አዩ በዚያም መስዋእታቸውን ሠዉ በዚያም የሚያስቆጣኝን ቁርባናቸውን አቀረቡ፡፡ በዚያም ደግሞ ጣፋጩን ሽታቸውን አደረጉ በዚያም የመጠጥ ቁርባናቸውን አፈሰሱ፡፡ እኔም እናንተ ወደርሱ የምትሄዱበት ከፍታ ምንድር ነው? አልኋቸው፡፡ እስከዛሬም ድረስ ስሙ ባማ ተብሎ ተጠርቷል፡፡ ቁርባናችሁን ባቀረባችሁ ጊዜ እስከ ዛሬ ድረስ ልጆቻችሁንም በእሳት ባሳለፋችሁ ጊዜ እስከዛሬ ድረስ በጣዖቶቻችሁ ትረክሳላችሁን? የእስራኤል ቤት ሆይ ከእናንተስ ዘንድ እጠየቃለሁን? እኔ ሕያው ነኝና ከእናንተ ዘንድ አልጠየቅም ይላል ጌታ እግዚአብሔር፡፡” ምንም ሳልጨምር ምንም ሳልቀንስ ቃሉን እንዲህ ጻፍሁላችሁ፡፡ እንግዲህ የባማ ትክክለኛ ትርጉም ይኼው ነው፡፡
ሌላው ኪዳነወልድ ክፍሌ መጽሐፈ ሕዝቅኤልን ተርጉመው በ1917 ዓ.ም ባሳተሙት መጽሐፈ ሕዝቅኤል ከትርጓሜው ጋራ ገጽ 208 ላይ ግእዙን በአማርኛ እንዲህ ተርጉመውት እናገኛለን፡፡ “ወእቤሎሙ ምንት ውእቱ ባማ ዘተሐውሩ አንትሙ ህየ” እኔ አንድ ነኝ ስል አንድ ቦታ አሳይቻችሁ ነበር እናንተ የእኔን ትእዛዝ አፍርሳችሁ በየቦታው የሰራችሁት ጧት ማታ የምትሄዱበት ቤተ ጣዖት ምን ልዖል ነው ምን ልዕልና አለው አልኋቸው፡፡ “ወተሰምየ ስሙ ባማ እስከ ዛቲ ዕለት” ስሙ እስከዛሬ ድረስ ባማ ተባለ ባማ ማለት ልዑል ነዋኅ ማለት ነው ይላሉ፡፡ አሁንም እንደቅድሙ ሁሉ ባማ ማለት ልዑል ነዋኅ (ከፍታ) ማለት ነው፡፡ ከፍታነቱ ግን ከላይ ሲተረጉሙት ዘተሐውሩ የምትሄዱበት ቤተ ጣዖት ልዑል ነዋኅ ትልቅ ከፍታ ነው ብለውታል፡፡ ስለዚህ ባማ ማለት ከፍታ ላይ ያለ ጣዖት ማለት ነው፡፡ ባማ ማለት ከፍታ ብቻ ቢሆን ኖሮ ለምን ወደዚያ ቦታ ሄዳችሁ? መስዋእታችሁም የረከሰ ነው ባላላቸው ነበር፡፡ ስለዚህ ባማ ማለት ከፍታ ላይ የተሠራ ጣዖት ማለት ነው፡፡
ስለዚህ ቃላትን ዝም ብለን በሚመስለን እየተረጎምን የማይገባ ሥራ ባንሠራ እላለሁ፡፡ ምክንያም ኢየሱስ ክርስቶስን ባማ በማ ነህ ለሕይወቴ ማለት ምን ማለት ነው? በትክክለኛ ትርጉሙ ካየነው እኮ በጣም ከባድ ኑፋቄ ነው፡፡ “ኢየሱስ ክርስቶስ ለሕይወቴ ከፍታ ላይ የተሠራህ ጣዖት ነህ ማለት እኮ ነው” ሎቱ ስብሐት፡፡ እኔም እንዲህ በመጻፌ “አቤቱ ማረኝ ይቅር በለኝ ብዬ እጸልያለሁ” ማስተማር ስላለብን ነው፡፡ እባካችሁ ልብ እናድርግ እናስተውል፡፡

ፈጸምኩ

No comments:

Post a Comment