Wednesday, June 28, 2017

ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ



© መልካሙ በየነ

ሰኔ 22/2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ


አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከጵጵስናቸው በፊት መጠሪያ ስማቸው አባ መልአኩ ሲሆን የተወለዱት መስከረም ፲ ቀን ፲፱፻፲ ዓ.ም የንጉስ  ወልደ  ጊዮርጊስ  ታማኝ ወታደር ከነበሩት አባታቸው ከወታደር ወልደ ሚካኤል አዳሙ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ዘውዲቱ ካሳ  በጎንደር  ጠቅላይ  ግዛት  ማኅደረ  ማርያም  ተብላ  በምትታወቀው  ገዳም  አካባቢ  ጋዥን  በምትባል  ቦታ  ነው ።  




ገና በህጻንነት ጊዜያቸው አራስ በነበሩበት ጊዜ ነበር ወታደር አባታቸው በህመም ምክንያት በሞት የተለዩት፡፡በዚህም የተነሳ እናታቸው ወይዘሮ ዘውዲቱ ልጃቸው አባ መላኩ ትንሽ ጠንከር ሲሉ 
ይዘዋቸው  ወደ  ጎጃም ተመለሱ እና አባ መልአኩ እዚያው ጎጃም ውስጥ የረዝ ሚካኤል በሚባል አካባቢ ማደግ ጀመሩ። ነገር ግን ብዙም የመጀመሪያ ትምህርታቸውን እንደጀመሩ እናታቸውምበሞት ከዚህ አለም ስለተለዩባቸው የአባታቸው ዘመዶች ወደሚገኙበት ቦታ ወደ ጎንደር ተመለሱ።ዘመዶቻቸውም እዚያው አካባቢ ተዋቂ መምህር ለነበሩት መሪ ጌታ ወርቅነህ ሠጧቸው። በዚያም ፊደል ከቆጠሩ በኋላ ወደ ደብረ ታቦር ተሻግረው እናቲቱ ማርያም በተባለችው ደብር ያስተምሩ ከነበሩት አለቃ ቀለመወርቅ ዘንድ ሔደው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀቁ። ከዚህም በኋላ ወደ አዲስ አበባ መጥተው በወቅቱ የኢትዮጵያ ጳጳስ ከነበሩት ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ መዓረገ ዲቁናን ተቀበሉ። ከዚያም ወደ ማኅደረ ማርያም ተመልሰው በዲቁና ሲያገለግሉ ቆዩ።

አባ መልአኩ ህይወታቸውን በቤተ ክርስቲያን ትምህርት አጎልምሰው በትኅርምትና እግዚአብሔርንበህይወታቸው ሙሉ በማገልገል ሊኖሩ በመወሰን ከጓደኞቻቸው ጋር ቅኔ ለመማር ወደ ጎጃም ይሄዳሉ። በዚያም በእናታቸው ሃገር አጠገብ ወደሚገኘውና የረዝ ሚካኤል ወደ ተባለው ቦታ መምህርልሳነ ወርቅ ከተባሉ መምህር ዘንድ ቅኔንና ዜማን ለስምንት ዓመታት ያህል ተማሩ። 

ባሕታዊ አባ መላኩ በወላይታ እየተዘዋወሩ በሚያስተምሩመት ወቅት

የዜማውንና የቅኔውን ትምህርት በሚገባ ካጠናቀቁ በኋላ  በተማርኩት ደግሞ ጥቂት ላገልግል በማለት ወደ ደብረ ታቦር  ሔዱ። ይሁን እንጂ ወዲያውኑ የኢጣልያ ፋሺስት ጦር ኢትዮጵያን  በግፍ በመውሪሩ እንዳሰቡት በሰላም ሊያገለግሉ አልቻሉም፡፡ በመሆኑም የአገልግሎት አሳባቸውን በመተው ራቅ ወዳለ ቦታ ሔደው  በብሕትውና እየኖሩ ለመማር ወሰኑ፡፡ ይህንን ውሳኔያቸውን ተግባራዊ ለማድረግ የሚሔዱበትን ሀገር ለመወሰን ሲያወጡ ሲያወርዱ  እና የጓደኞቻቸውን ምክር ሲጠይቁ አንድ ጓደኛቸው በደቡብ  ኢትዮጵያ ወላይታ አካባቢ አጎቱ በመንግሥት ሥራ ተሠማርቶ  እንደሚኖርና አካባቢው በ፲፫ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጻድቁ አቡነ ተከለ ሃይማኖት የተጋደሉበት፣ እንደ ደብረ መንክራት አቡነ ተከለ ሃይማኖት ዓይነት ታላላቅ ገዳማት እንዳሉበት፣ ቦታው በጥምቀት  የቅድስት ሥላሴን ልጅነት ያላገኙ ሰዎች የሚበዙበት በመሆኑ  ለብሐትውናና ለአገልግሎት የሚመች መሆኑን መክሮ አብረው  ቢሔዱ ለጊዜው አጎቱ ቤት አንደሚያርፉ ይነግራቸዋል፡፡ ቅዱስነታቸውም የጓደኛቸውን ሀሳብ ተቀብለው በ፲፱፻፳፮ዓ.ም ሁለቱም ወደ  ወላይታ ጉዞአቸውን ጀመሩ፡፡


አድካሚ ከሆነው ከብዙ ቀናት የእግር ጉዞ በኋላ ወላይታ  ደርሰው ከጓደኛቸው አጎት ቤት ዐረፉ፡፡ አካባቢውን እስከሚላመዱ  በእንግድነት ከቆዩ በኋላም ዝናው ከጎንደር ስቦ ወዳስመጣቸው ደብረ  መንከራት አቡነ ተከለ ሃይማኖት ገዳም ገቡ፡፡ እግዚአብሔር እንደነ ጻድቁ አቡነ ዜና ማርቆስና ጻድቁ አቡነ ተከለ ሃይማኖት በአካባቢው ሥራ እንዲሠሩ መርጧቸዋለና ወደ ገዳሙ ሲገቡ በቦታው ረዘም ላለ  ጊዜ የቆዩትን አለቃ ደስታ የተባሉትን ባሕታዊ አገኙ፡፡  ከእሳቸውም ጋር በአንድ በአት ተወሰነው መኖር ጀመሩ፡፡


ቅዱስነታቸው በደብረ መንከራት አቡነ ተከለ ሃይማኖት ገዳም  ገብተው ጥቂት ከቆዩ  በኋላ የገዳሙ አበ ምኔት ከነበሩት መምህር ወልደ ኢየሱስ የቅዱሳት  መጻሕፍትን ትርጓሜ በተለይም የማር ይስሐቅንና የመጻሕፍተ  ሊቃውንትን ትርጓሜ በጥልቀት ተማሩ፡፡ ቅዱስነታቸው ከመማር  ጋር በነበራቸው የቁም ጽሕፈት ችሎታ በመምህራቸው ታዝዘው  ቅዱሳት መጻሕፍትን እየጻፉ ለገዳሙ ማኅበር እንጺዳረስ አድርገዋል፡፡ በዚህ ዓይነት የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢር ሲመረምሩና  ሥርዓተ ገዳምን ሲያጠኑ ከቆዩ በኋላ በዚያው መዓረገ ምንኩስናን  ተቀበሉ፡፡ ከዚያም ወደ አዲስ አበባ መጥተው ከግብፃዊው ብፁዕ  አቡነ ቁርሎስ መዓረገ ቅስናን ተቀብለው ወደ በአታቸው ተመለሱ፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተከለ ሃይማኖት ወደ ገዳማቸው  ከተመለሱ በኋላ በጾም በፀሎት፣ በሰጊድና በትኅርምት በገድልና  በልዩ ልዩ ትሩፋት ተወሰነው አስከ ፲፱፻፵ ዓ.ም ድረስ በአታቸውን  አጽንተው ቆዩ፡፡ ይህም የተባሕትዎ ጊዜ ከፈጣሪያቸው ከአግዚአብሔር ልዩ ጸጋና በረከት የተቀበሉበትና ለወደፊት ዓላማቸው ሁሉ  መመሪያ ያገኙበት ወቅት ነበር፡፡

በዚህ ዓይነት ለዓመታት በፍጹም ትኅርምት አና ተጋድሎ  አንደ አባቶቻቸው አግዚአብሔርን በጸሎት ከለመኑ በኋላ በ፲፱፻፵ ዓ ም በአታቸውን በዚያው ገዳም አድርገው በአውራጃው ልዩ ልዩ  ቦታዎች በመዘዋወር ማስተማር ጀመሩ፡፡ ቅዱስነታቸው በሚያስደንቅ ሁኔታ በአውራጃው ውስጥ በሚገኙት ሰባት ወረዳዎች አየተዘዋወሩ ሲያስተምሩ ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ  ዘንድ በአካባቢው እንዲንቀሳቀሱ የፈቃድ ደብዳቤ ከማግኘታቸው  በስተቀር የተቆረጠላቸው ደመወዝ የተሰፈረላቸው አህል አልነበረም፡፡  በቅዱስነታቸው ትምህርት  ከ፫ መቶ ሺህ በላይ የሆኑ  አማንያን አምነው እንደ ተጠመቁና የክርስቶስ ተከታዮች አንደ  ሆኑ ይነገራል፡፡ በጣዕመ ስብከታቸው ይህንን ያህል ምእመን ካፈሩም  በኋላ   በቤተ መንግሥቱ እውቅና የነበረውንና በአካባቢው የሚገኙ ሰባት አውራጃዎች ተወካዮችን በአባልነት የያዘ “የመገበሪያ ቦርድ” የተሰኘ አካል በማቋቋም  የአካባቢው ሕዝቦች ገንዘብ እንዲያዋጡ በማገድረግ፣ ከዚህም ጋር  የአካባቢውን የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ማፋጠንን ቀዳሚ ዓላማው  ያደረገውን “ብርሃነ ሕይወት” የተሰኘ ግብረ ሠናይ ድርጅት አቋቁመው የሚከተሉትን መንፈሳዊና ማኅበራዊ ተቋማት ሠርተዋል።

፩. ምአመናኑ እየተሰበሰቡ የሚጸልዩባቸውና ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን የሚፈጽሙባቸው በሁሉም ወረዳዎች ፷፭ አብያተ ክርስቲያናትን አሠርተዋል፡፡ እንዲሁም የመንፈስ ልጆቻቸው መንፈሳዊውንና ሥጋዊውን ትምህርት የሚማሩባቸውን ፳፬ ትምህርት ቤቶችን አቋቁመዋል። 
፪. በወላይታ ሶዶ ከተማ በደብረ መንከራት ፃድቁ አቡነ ተከለ ሃይማኖት ገዳም አካባቢ ፲፩  ከፍል የድኩማን ቤት በማሠራት ራሳቸውን ለመርዳት የማይችሉ  ድኩማን ምግብ ፣ ልብስና መጠለያ እንዲያገኙ በማድረግ ሐዋርያዊ  ግዳጃቸውን ተወጥተዋል፡፡
፫. በዚሁ ከተማ ውስጥ ከ፬ መቶ ያላነሰ ሕዝብ በአንድ ጊዜ መያዝ የሚችል “የወጣቶች የመጽሐፍ  ቅዱስ ማኅበር አዳራሽ” የተሰኘ መሰብሰቢያ አዳራሽ አሠርተው  በአገልግሎት ላይ ይገኛል፡፡ 
፬. በዚሁ ከተማ  ውስጥ አንድ ክሊኒክ አቋቁመው ሕዝቡ አንዲጠቀምበት አድርገዋል፡፡ 
፭. ከከተማው ወጣ ብሎ በሚገኘው ቆንቶ በተባለው ቀበሌ በ፲፱፻፶፬ ዓ.ም  ባሠሩት አዳራሽ የቃጫና የልዩ ልዩ ጥበበ እድ ሥራዎችን  በማቋቋም የአካባቢው ችግረኞች እየሠሩ ራሳቸውን አንዲረዱ አድርገዋል፡፡

በዚህ ዓይነት ሰፊ አገልግሎት ላይ ተጠምደው ቤተከርስቲያን የሰጠቻቸውን ኃላፈነት በመወጣት ላይ ሳሉ ንጉሣዊው  መንግሥት በወታደራዊው የደርግ መንግሥት ተተካ፡፡ በመሆኑም እንደ ቀድሞው ከሕዝቡ ገንዘብ ማሰባስብ አልቻሉዎ፡፡ በዚህ  የተነሣ የልማት አገልግሎታቸው አንዳይቋረጥ ወደ አዲስ አበባ እየመጡ ከቤተ ክርስቲያኗ ከምአመናን መለመን ጀመሩ፡፡ በዚህ  ዓይነት በተወሰነ ደረጃ እየተንቀሳቀሱ እያለ ደርግ ሁለተኛውን  የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን አላግባብ  አሰረ፡፡  ከቤተክርስትያኗ ቀኖና ውጭም ሌላ ፓትርያርክ እንዲመረጥ አዘዘ። ቀኖናውም “የተቀባ ፓትርያርክን ሞት ብቻ ነው የሚሽረው” በዚህም መሠረት “የተቀባ ፓትርያርክ ሳይሞት በላዩ ላይ ሌላ ፓትርያርክ አይሾምም” የሚል ነው፡፡ ነገር ግን ወታደራዊው የደርግ መንግሥት ራሱ ባቋቋመው አስመራጭ ኮሚቴ አማካይነት ከየክፍሉ ለፓትርያርክነት እንዲመረጡ እጩ የሚሆኑ አባቶች እንዲጠቆሙ አደረገ፡፡ 

በዚህም ጥቆማ አባ መላኩ ሳያስቡትና በእግዚአብሔር ፈቃድ አንዱ  እጩ ሆነው ተጠቆሙ። በመጨረሻም የማጣሪያ ምርጫ አድርጎ ከተጠቆሙት አባቶች   ውስጥ አምስቱ ብቻ እንዲቀሩ ካደረገ በኋላ ከ፭፷፭ ወረዳዎች ሁለት ሁለት ተወካዮች አንዲላኩና በአምስቱ አባቶች ላይ የፓትርያርክነት ምርጫ ድምፅ እንዲሠጡ ጥሪ አደረገ። 
እነኝህም አምስቱ እጩዎች የሚከተሉት ነበሩ።

፩. አቡነ እንድርያስ (በወቅቱ የቤጌምድርና ሰሜን ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ)
፪. አቡነ ሰላማ (በወቅቱ የጋሞ ጎፋ ሊቀ ጳጳስ)
፫. አባ ተወልደ ብርሃን ወልደ ስላሴ (በወቅቱ የደብረ ቢዘን ገዳም አበምኔት)
፬. አባ ዮሐንስ ከሐሊ (ከእየሩሳሌም)
፭. አባ መላኩ ወ/ሚካኤል (በደብረ መንክራት ተክለ ሃይማኖት ገዳም ባኅት) 

ባላሰቡት ሁኔታ ለዚህ ሃላፊነት የታጩት አባ መላኩም መንበሩ ለኔ አይገባኝም ብለው ተቃውመው እንደነበር ይነገራል። በዚህም የተነሣ ቅዱስነታቸው ቤተ ክህነት ውስጥ ተቀምጠው በዘበኛ እንዲጠበቁ ተደርጎ እንደነበር ይነገራል። በአምስቱ እጩዎች ላይ ድምፅ እንዲሠጡ ከየወረዳው በተገኙ ፱፻፱ ወኪሎች በተሠጠ ድምፅ መሠረት አባ መላኩ ፫፻፲፯ ድምፅ በማግኘት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ሦስተኛው ፓትርያርክ ሆነው ተመረጡ። “የተቀባ ፓትርያርክ ሳይሞት በላዩ ላይ ሌላ ፓትርያርክ አይሾምም” የሚለውን ሁለተኛውን እምነት ጥሰው ሰኔ ቀን ፲፱፻፷፰ ዓ/ም ሦስተኛው ፓትርያርክ እንዲሾሙ አደረጉ። ሹመታቸውም እውን ይሆን ዘንድ ሐምሌ፲፩ ቀን፲፱፻፷፰ ዓም መዓረገ ጵጵስና ተቀበሉ። በኋላም ነሐሴ ፳፫ ቀን ፲፱፻፷፰ ዓም በቅዱስ ሲኖዶስ “አባ ተክለ ሃይማኖት ሣልሳዊ የኢትዮጵያ ፓትርያርክ” ተብለው ተሾሙ፡፡ ብፁዕ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በፓትርያርክነት ዘመናቸው ለቤተክርስትያኗ ብዙ ተቃሚ ለውጦችን አምጥተዋል። ከነዚህም ለውጦች ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው።

፩. ቀደም ሲል በአቡነ ቴዎፍሎስ መሰረቱ ተጥሎ የነበረው የቃለ አዋዲ ደንብ ማሻሻልና አንዳንድ ሁኔታዎችን ከወቅቱ ጋር አንድሄዱ አድርገዋል፡፡
፪.  በእያንዳንዱ አጥቢያ  ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤት እንዲቋቋአድርገዋል፡፡ ቅዱስነታቸው ለነገዪቱ ቤተ ክርስቲያን ተረካቢዎች ለኾኑት የሰንበት /ቤቶች ተማሪዎች ከፍ ያለ አመለካከትና ትኩረት ነበራቸው፡፡ በዚኽም መሠረት በእያንዳዱ አጥቢያ የሰንበት ት/ቤቶች ተቋቁመው ሰፋ ያለ አገልግሎት እንዲያበረክቱ አድርገዋል፡፡ በአዲስ አበባ የሰንበት ት/ቤቶች እየተዘዋወሩ ያስተምሩ ለነበሩ መምህራን በየወሩ ፯፻፴ ብር ከደመወዛቸው አስተዋፅኦ ይሰጡም ነበር፡፡
፫. ለአብነት  መምህራን የወር ደመዎዝ እንዲመደብላቸው በሲኖዶሱ ማስወሰን፣ ተማሪዎችም ተመሳሳይ ድጎማ እንዲደረግላቸው ማድረግ
፬. በቅዱስ  ሲኖዶሱ ውሳኔ ስድስት  የካህናት ማሰልጠኛዎች እንዲቋቋሙ  ማድረግ
፭. በተለያዩ ጊዜያት ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መስፋፋት ፳፰  ኤጲስ ቆጶሳትን  ሾመዋል፡፡
፮. የሕፃናት አስተዳደግ ጉባኤ ማእከል በማቋቋበየአህጉረ ስብከቱ እና በየአብያተክርስትያናቱ  በጥቅሉ ስከ ፴፮ እጓለ ማውታ ማሳደጊያዎች  እንዲቋቋአድርገዋል፡፡ በፓትርያርክነቱ የቅድስና መንበር ከመቀመጣቸው በፊትም ይኹን በኋላ የሃይማኖት እና የብሔር ልዩነት ሳያደርጉ ከየአቅጣጫው እያሰባሰቡ በምግበ ሥጋ እና በምግበ ነፍስ የሚረዷቸው ድኻ አደጎችና ድኩማን እጅግ ብዙዎች ነበሩ፡፡ በድርቅ የተጎዱ ወገኖች በሚገኙባቸው አካባቢዎች፣ ያለምንም የሃይማኖት ልዩነት ኢትዮጵያውያን የሚገለገሉባቸው መሠረተ ልማቶችን፣ የአገልግሎት ተቋማትንና የጥበበ እድ የጎጆ ኢንዱስትሪዎችን አስፋፍተዋል፡፡
፯. ለዘመናት የምእመናን ጥያቄዎች ሆነው ሲያነጋግሩ የነበሩ ጉዳዮችን በማድመጥ ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ አንድሰጥባቸው ማድረግ። ከነዚህም ውስጥ ከሰባቱ አፅዋማት አንዱ  የሆነውን የልደትና የጥምቀት ፆመ ገሃድ፣ ፆመ ነቢያት የሚገባው በየዓመቱ  ሕዳር ፲፭ እንደሆነና ዓሣ በፆም ወራት እንደማይበላ ማስወሰን
፰. ልማትን በሚመለከትም ቅዱስነታቸው በሚሰጡት መመሪያ ያለምንም የሃይማኖት ልዩነት ኢትዮጵያውያን የሚገለገሉባቸው የእህል ወፍጮ ቤቶች አና ዳቦ ቤቶች አንዲቋቋሙ ማድረግ 
፱. በከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት፣ ለተወሰኑ ዓመታት ሥራውን አቋርጦ የነበረው የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ት/ቤት በ፲፱፻፸፬ ዓ.ም. ተከፍቶ ሥራውን እንዲጀምር አድርገዋል፡፡
፲. በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎት የሚሰጡ ስድስት የካህናት ማሠልጠኛዎች እንዲቋቋሙና ሥራ እንዲጀምሩም አድርገዋል፡፡

፲፩. በሀገር ውስጥ በርካታ
አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት በየአቅራቢያው እንዲሠሩ፤ በውጭም ለምእመናን መንፈሳዊ አገልግሎት ለማሟላትና እንዲኹም በቤተ ክርስቲያናችን ትምህርትና እምነት አምልኮተ እግዚአብሔርን ለመፈጸም ለሚፈልጉ የውጭ አህጉር አማንያን አብያተ ክርስቲያናትን በማሳነፅና አገልጋዮችን በመላክ ከፍተኛ የኾነ የዕድገትና የጥንካሬ ታሪክ አስመዝግበዋል፡፡

፲፪. በምሥራቁ እና በምዕራቡ ዓለም የሥራ ጉብኝት በማድረግ፤ ሌሎች የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎችም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን እንዲጎበኙ በማድረግ፤ በዓለም አቀፍ የሰላም ጉባኤዎች ላይ በመገኘትና ስለ ሰላም አስፈላጊነት በመመስከር፤ የቤተ ክርስቲያን ልኡካን በተለያዩ ዓለም አቀፍ ጉባኤያት ላይ እንዲገኙ በማድረግ፤ በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያናችን ስለሌላው የክርስትና ዓለም፣ ሌላውም ስለ ቤተ ክርስቲያናችን በበለጠ እንዲያውቅ ለማድረግ ይከተሉት የነበረው አቋም ለቤተ ክርስቲያናችን ከፍተኛ መታወቅን አትርፎላታል፤ ተፈላጊውን የተራድኦ ግንኙነት ለማጠናከር አስችሏታል፡፡ የቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ ተግባር የሚገልጹ መጽሔቶች በእንግሊዝኛ ቋንቋ እየታተሙ ለውጭው ዓለም እንዲሠራጩም አድርገዋል፡፡
፲፫. ለቤተ ክርስቲያን የህልውና አደጋ ጋርጦ የነበረው የወቅቱ መንግሥት ርእዮተ ዓለም፤ በሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ያደረሰው ጥፋት በእኛዋ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላይ እንዳያደርስ በጸሎት፣ በጥበብ እና በትዕግሥት በታለፈበት አመራራቸው ይታወሳሉ፡፡
፲፬. ቅዱስነታቸው እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሀገረ ሙላድ እያላቸው፣ ተወልጄ ያደግኹበት ቦታ ይህ ነው ብለው ከመናገር ይልቅ በፍጹም ኢትዮጵያዊነታቸው ብቻ ያምኑ ነበር፡፡ የካህነ እግዚአብሔር መልከ ጼዴቅን አሰረ ፍኖት በመከተል፤ እንደ አብርሃም አበ ብዙኃንነትን አጉልተው በማሳየት ኹሉን እኩል በመመልከት ብቃታቸው ብዙዎችን ሲያስገርሙ የኖሩ አባት ናቸው፡፡
፲፭. ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት መቼም ቢኾን አልጋ ላይ ተኝተው የማያውቁ ፍጹም ተኃራሚ አባት እንደነበሩ በቅርብ የሚያውቋቸው ይመሰክሩላቸዋል፡፡ በአመጋገብ በኩልም ቢኾን፣ በሀገር ውስጥ ይኹን በውጭ ከበሶ ወይም የተቀቀለ ድንች በስተቀር ሌላ ነገር ቀምሰው አያውቁም ነበር፤ ይባላል፡፡

ቅዱስነታቸው
 በፆም፣ በፀሎት፣ በቀዊምና በስግደት ተወስነው ቤተ ክርስቲያንን ሲያስተዳድሩ ከቆዩ በኋ በመጨረሻ ሰፊ አገልግሎትና ተጋድሎ ሲፈፅሙበት የቆዩበትን የደብረ መንክራት አቡነ ተክለ ሃይማኖትን ገዳም በመጎብኘት ላይ ሳሉ በድንገት ታመሙ። ወደ አዲስ አበባ ባስቸኳ መጥተው በዳግማዊ ምኒልክና የጦር ሀይሎች ሆስፒታል በህክምና ሲረዱ ቆዩም ሊድኑ አልቻሉም። መሆኑም   መታት የፓትርያርክነት አገልግሎት በኋላ ግንቦት ፳፰/፲፱፻፹  . በተወለዱ  መታቸው ከዚህ ዓለ በሞት ተለይተዋል። ቅዱስነታቸው መላ ዘመናቸውን በፆም፣ በፀሎትና በሰጊድ ያሳለፉት ከመሆናቸው ጋር ባደረባቸው ህመም የተነሣ ነፍሳቸው ከሥጋቸው ስትለይ የሰውነታቸው ክብደት 25 ኪሎ ግራም ደርሶ እንደነበር ይነገራል። አስከሬናቸውም በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ዐርፎ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጸሎተ ፍትሐት ሲደርስ ከቆየ በኋላ ሥርዓተ ቀብራቸው፣  ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ማኅበረ ካህናትና ማኅበረ ምእመናን በተገኙበት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ላሴ ቤተክርስቲያን ግንቦት ፴/፲፱፻፹ዓም ተፈፅሟል። ተፈጽሟል፡፡ የቅዱስነታቸው አገልግሎት ሲዘከር ይኖር ዘንድም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ አስከሬናቸው ባረፈበት ሥፍራ የመታሰቢያ ሐውልት አቁሞላቸዋል፡፡
ሐውልቱ ከ፳፰ ዓመታት በኋላ በማርጀቱና በመፈራረሱ ቅዱስ ሲኖዶሱ ትኩረት ሰጥቶ ለማስጠገን በዝግጅት ላይ ሳለ፣ ክቡር አቶ ቁምላቸው ገብረ ሥላሴ /ወልደ ዐማኑኤል/ በግል ወጪአቸው ለማስጠገን በጠየቁት መሠረት በቅዱስ ሲኖዶስ ተፈቅዶላቸው፣ በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ የቅርብ መመሪያና ክትትል በ1.5 ሚሊዮን ያማረ ዕድሳትና ጥገና የተደረገለት ሐውልት በአግባቡ ተሠርቶ ለምረቃ በቅቷል፡፡
ይህ የቅዱስነታቸው አገልግሎት ሲዘከር ይኖር ዘንድ አስከሬናቸው በክብር ባረፈበት መንበረ ጸባኦት ቅድስት ላሴ ቤተክርስቲያን የተሠራላቸው የመታሰቢያ ሐውልት ዛሬም ድረስ አምሮ ተውቦ ይገኛል ማለት ነው። ከዚህ በኋላ ዐራተኛው ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስ በመንበሩ ተተኩ፡፡
ከአባታችን ከብጹእ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በረከት አምላካችን ያሳትፈን፡፡
=====================================
አንብባችሁ ከጨረሳችሁ አስተያየት #comment ስጡ
#share አድርጉ፡፡

No comments:

Post a Comment