Friday, October 2, 2015

ልኩን ያለፈ አሜን ከጭብጨባና እልልታ ጋር

©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
እንደምን ሰነበታችሁ አምላከ ቅዱሳን እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ በሰላም በጤና አደረሳችሁ። በእርግጥ የመልካም ምኞት መግለጫዬ ብዙ ቀናትን ያሳለፈ መሆኑን እረዳለሁ። ነገር ግን የመናገር እና የመጻፍ መብቴን ፌስቡክ ስላልገደበኝ ብዬም በዓሉ ከመድረሱ በፊት ሳምንት እና ሁለት ሳምንት ቀድሜ እንኳን አደረሳችሁ አልልም። በዓላት የሚውሉባቸው ቀናት እንደ ፌስቡክ አቆጣጠር ቢሆን ኖሮ አንድ ዓመት የሚባለው 365 1/4 አይሆንም ነበር። ለምሳሌ የዘመን መለወጫ መስከረም 1 መሆኑን የቀን መቁጠሪያችን ያስረዳል። በፌስቡክ ግን ጳጉሜን 1 ጀምሮ ዘመን ይለወጣል። እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሳችሁ የሚሉ መልካም ምኞት መግለጫዎች እኔ እቀድም እኔ እቀድም እየተባባሉ በሚመስል ሁኔታ በየግለሰቦች ይለጠፋሉ። ሳንደርስ እንኳን አደረሳችሁ መባባልን ማን አመጣ ብትሉኝ መልሴ ፌስቡክ የሚል ነው። አንድ ደቂቃ ስንት ተአምር እንደምትሰራብን ያልተረዳን ሰዎች ነን እንዲህ ከሳምንት በፊት እንኳን አደረሳችሁ የምንባባለው። ለማንኛውም መልካም ምኞትን በተመለከተ በሌላ ርእስ እንገናኝ ይሆናል አምላክ ፈቃዱ ይሁንና። ለጊዜው ወደ ዛሬው ርእስ እንመለስ።
አሜን /amen/ የሚለው ቃል ዓለምን ሁሉ ያስተሳሰረ ብቸኛ ቃል ነው። ቻይናዎችና ጃፓኖች ምን እንደሚሉ ባላውቅም ሁሉም የዓለም ቋንቋዎች ሁሉ አሜን የሚለውን ቃል እንደሚጠቀሙ ይነገራል። አሜን ማለት ይሁን፣ይደረግ የሚል ትርጉም አለው። ወደ ሀገራችን ከዚያም ወደ ቤተክርስቲያናችን እንግባና አሜንን እንመልከተው። አሜን የሚለው ቃል በቤተክርስቲያናችንም ከላይ ያየነውን ትርጉም ይይዛል። አባቶቻችን ሲመርቁን አሜን እንላለን ምርቃታችሁ ይሁንልን ይደረግልን ለማለት ነው። አሁን አሁን ግን ልክ እና መጠኑን ያለፈ አሜን እንዲሁም እልልታና ጭብጨባ የዋጠን ይመስለኛል። የተሐድሶ መናፍቃን ካስለመዱን መጥፎ ጸባያችን መካከል አንዱ ይሄው ነው። ሁሉም የሚያምረው ልክ እና መጠን ሲኖረው ነው። ማር ሲበዛ ይመራል አይደል ያለው የሀገሬ ሰው። ልክ እና መጠንን ከምታስተምር ቤተክርስቲያን ውስጥ ልክ ያለፈ ነገርን ማድረግ ድፍረት ሳይሆን አይቀርም። በእርግጥ ይህን ልክ እንድናልፍ "የዘመኑ መምህራንም" እጅ አለበት። የሚናገሩትን ነገር የሚጀምሩት አስጨብጭበው ነው። ከዚያም ርእስ የሌለው "ትምህርታቸውን" ይጀምራሉ በእርግጥ ያልተዘጋጀ መምህር ከዚህ የተሻለ ነገር ማድረግ አይችልም። በተደጋጋሚ "ክብር ለእሱ ይሁን" እያሉ ህዝቡን ያስጨበጭባሉ እልል ያስብላሉ። ሕዝቡም የሚባለውን ነገር ሳይሰማ እንኳ ያጨበጭባል እልል ይላል። "እስኪ እጃችሁን አሳዩኝ" ይላል "መምህሩ" ህዝቡ አሁንም ያጨበጭባል አይሰማም ይላቸዋል አሁንም ከቅድሙ አብልጠው ያጨበጭባሉ። የኪነ ጥበብ ሰዎች ዘፈን ሊዘፍኑ ወደ መድረክ ሲመጡ የሚደረግላቸውን አቀባበል በቤተክርስቲያናችን አውደ ምሕረቶች እያየነው ነው። 
በተለይ ትላልቅ በዓላት ላይ ደግሞ እንዲህ ማድረግ የሚወዱ የመድረክ መሪዎችም አሉ። አንዴ ስላስለመደው ገና የዕለቱ መምህር እገሌ ናቸው ሲል ህዝቡ ያጨበጭባል። መምህሩ ሲመጡ እያጨበጨቡ ይቀበሏቸዋል። ፋታ የሌለው ጭብጨባና እልልታ በጣም ስልችት የሚል። መምህሩም "ክብር ለእሱ ይሁን" ይላል ህዝቡም ያጨበጭባል። እሽ ክብሩ ለማን ይሁን ብለን ነው ያጨበጨብነው? እሱ የተባለው ማነው? ሰይጣን ነው ወይስ እግዚአብሔር ነው? ዝም ብለን መጮህ አይደለም እሱ የጅራፍ ባሕርይ ነው። ዝም ብሎ እልል ማለት አይደለም እሱ የእንቁራሪት ባሕርይ ነው። "ክብር ለእሱ ይሁን" የተባለለት እግዚአብሔር ከሆነስ የቱን ክብሩን ነው በእንደዚያ ያለ እልልታና ጭብጨባ የምንገልጸው? አንዳንዶች ደግሞ "አይሰማም እጃችሁ የት አለ?" እያሉ ደግመው ደጋግመው ያስጨበጭባሉ። ክብሩ ለእግዚአብሔር ነው ከተባለ ያስጨበጨቡንንና እልል ያስባሉንን ጩኸት እንዴት እግዚአብሔር አልሰማም? አልተሰማንም የሚሉ እነርሱ ናቸው ያስጨበጨቡን ደግሞ ለእግዚአብሔር ብለው ነው ታዲያ ሁለቱ ሃሳብ አይጣረስም ትላላችሁ? 
በእርግጥ አሁን አሁን ልማድ አድርገነዋል። "የሰማነውን ቃለ እግዚአብሔር በልቡናችን ያሳድርልን" ተብለን ስንመረቅ አሜን በማለት ፋንታ ትርጉም በማይሰጥ መልኩ በጭብጨባ እንመልሳለን። "ቃለ ሕይወትን ያሰማልን" ስንባል ደግሞ በእልልታ እናቀልጠዋለን። ትርጉሙ ምን ይሆን? ይህን የምለው ግን ለእውነተኞች መምህራን አይደለም እነርሱ እንዲህ ስለማያስደርጉ። እንደአጠቃላይ ጭብጨባ በሚያስፈልግበት ጭብጨባ፣እልልታ በሚያስፈልግበት እልልታ፣አሜን ማለት በሚያስፈልግበት አሜን ማለት ይገባል እንጅ ከመጠን ባለፈ ያውም ያለቦታው ማጨብጨብ እና እልል ማለት ትርጉም አልባ ነው። ቃለ እግዚአብሔርም ለመማር የመጣን ሰው ለጆሮ በሚሰቀጥጥ እልልታና ጭብጨባ ልናደነቁር አይገባም።

No comments:

Post a Comment