Wednesday, December 26, 2018

የነገው ገዳመ አስቄጥስ የዛሬው እነጋትራ ቅድስት ሃና አንድነት ገዳም!


==========================================================
ይህ ገዳም በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሥር ከሚገኙ በርካታ ጥንታውያን ገዳማት መካከል አንዱ ነው። አብርሃ ወአጽብሐ እንደመሠረቱት የሚነገርለት ይህ ጥንታዊ ቦታ በአዋበል ወረዳ ቤተክህነት ሥር የሚገኝ የአንድነት ገዳም ነው። ገዳሙ በእናታችን ጽዮን ጽላት የተቆረቆረ ቢኾንም ከዘመናት በኋላ 13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አሁን የምትገኘው የቅድስት ሃና ጽላት እንደገባች ይነገራል። በአጼ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት በዚህ ገዳም 3000 መነኮሳት በላይ ይኖሩበት እንደነበር ምዕላድ በተባለው መጽሐፍ ላይ ተመዝግቦ ይገኝ እንደነበር ቦታውን ስንመለከት ተነግሮናል።
ቦታው እነታድራ በምትባል በንጉሥ ልጅ ይጠራ እንደነበር ከጊዜ በኋላ ግን እነጋትራ እየተባለ መጠራት ጀምሯል። ይህ የበረከት እና የጽሙና ቦታ ለጸሎት እና ለአርምሞ ምቹ ነው። ከደብረ ማርቆስ ከተማ 50 . በላይ የማይርቀው ይህ ቦታ የቦቅላ ከተባለች ከተማ ወደ ቁይ ስንሄድ እነጋትራ ትምህርት ቤት እንደደረስን ከቁይ መንገድ ተገንጥሎ ወደ ሰሜን አቅጣጫ ያለውን የጠጠር መንገድ ተከትሎ ቀጥታ በመሄድ ገዳሙ ላይ መድረስ ይቻላል።
 
ገዳሙን ለሚመለከቱም ኾኑ ተአምረኛ በኾነው ጠበል ለሚጠምቁ ሰዎች ወደ ገዳሙ ሲመጡ ምግብ ይዞ መሄድ ፈጽሞ የተወገዘ ነው። ለገዳሙም ኾነ በገዳሙ ውስጥ ለሚገኙ መነኮሳት 5 ሳንቲም ምጽዋት መስጠት ውጉዝ ነው። ቦታውን ለማየትም ይኹን ብዙ ጊዜ ተቀምጦ ከበረከቱ ለመካፈል የፈለገ ኹሉ 5 ሳንቲም ወጭ አይጠየቅም ቢሰጥ እንኳ የተወገዘ ነው።

ገዳሙን እያስተዳደሩት ያሉት አባ ገብረ ሥላሴ (በአካባቢው ምእመናን በጎ ስም የላቸውም) የግብጽ እና የኢየሩሳሌም ገዳማትን በሚገባ የተመለከቱ ናቸው። በገዳሙ እየተሠሩ ያሉ በርካታ የሴትና የወንድ መነኮሳት የጸሎት ቦታዎች በአባ ገብረ ሥላሴ መሐንዲስነት በሚገባ በሚያምር መልኩ እየተገነቡ እንደሚገኙ ተመልክተናል። አርቆ አሳቢው ገዳሚው አባ ገብረ ሥላሴ ዓላማቸው ግብጽ የሚገኘውን ገዳመ አስቄጥስ ጎጃም ላይ መትከል ነው። የግብጹ ገዳመ አስቄጥስ ዘመናዊውን እና ሃይማኖታዊውን ትምህርት በሚገባ ጎን ለጎን በገዳሙ ውስጥ እየተማሩ ዶክተር እና ኢንጅነር ኾነው ገዳማቸውን በምንኩስና ያገለግላሉ። ዘመናዊውን ዓለም የዋጁ በርካታ መነኮሳት ይገኙበታል ይህን እነጋትራንም እንደዚያ ማድረግ እፈልጋለሁ ይላሉ አስተዳዳሪው። ለዚህም ማሳያ የኾኑት በግንባታ ላይ ያሉት በሚያምር መልኩ የተጀመሩት 3 3 የኾኑ 15 በላይ የሚኾኑ የወንዶች እና 15 በላይ የሚኾኑ የሴቶች መኖሪያ ቤቶች ምስክሮች ናቸው። ወደፊት ለመሥራት ያቀዱት ከወጣኒነት ወደ ማእከላዊነት እና ፍጹምነት ሲደርሱ መነኮሳት የሚያርፉበትን ቦታ መሥራት ነው። አሁን በቦታው የሚገኙት መነኮሳትና መነኮሳዪያት የሚኖሩበት ቦታ እንዴት ደስ እንደሚያሰኝ የሚያውቀው ቦታውን ያየ ሰው ብቻ ነው።

አባ ገብረ ሥላሴ ዓላማቸው ኹሉንም የጉባዔ ቤት ማለትም የቅኔ፣ የመጻሕፍት፣ የቅዳሴ፣ የአቋቋም  መምህራንን ቀጥረው የተማሪዎችና የመምህራን መኖሪያ ቤቶችን እና መማሪያ ክፍሎችን ከዚህ በተጨማሪም የዘመናዊ ትምህርት መማሪያ ትምህርት ቤቶችን መገንባት በቦታው ነው። ምእመናንም ቦታውን ዘወትር እንዲመለከቱት ሕጻናትን ሊስቡ የሚችሉ ገዳማዊ ሕይወት በሕጻንነት አእምሯቸው እንዲቀረጽባቸው የሚያደርጉ ማረፊያ ክፍሎችንና የሚታዩ የሚዳሰሱ የሚቀመሱ ነገሮችን ማስቀመጥ ነው፡፡ የሚመጡ መምህራንን እና ተማሪዎችን እንዲሁም ምእመናንን እና ልጆቻቸውን ቀለባቸውን እየሰጠን ለቤተክርስቲያናችን መልካም ልጆችን ማፍራት ነው ይላሉ። እርሳቸውን መደገፍ ማለት ይበርቱ አይዞዎት ማለት ቤተክርቲያናችንን ከተቃጣባት ፍላጻ መታደግ ነው ብየ አምናለሁ። የገዳም ኑሮ የምንኩስና ሕይወት ገብቷቸው የሚኖሩ ናቸው።

አባ ገብረ ሥላሴ ማን እንደኾኑ በመጻፍ የገዳሙን ስም ማስረሳት ጥሩ እንዳልኾነ አውቃለሁ። ነገር ግን ቦታውን ያላዩ ወይም ደግሞ በዚያ ቦታ እንደዚያ ያለ ገዳም እንዲመሠረት የማይፈልጉ ሰዎች በርካታ የሐሰት እና የውንጀላ ወሬዎችን ሲያናፍሱ መመልከት የተለመደ ኾኗል። ይህን ቦታ እንዳይ ያደረገኝም ‹banteamlak zewdu› የተባለ ማንነቱ የማይታወቅ ሰው ፌስቡክ ላይ የገዳሙን አስተዳዳሪ በሐሰት ክስ ሲያብጠለጥላቸው ሳይ ጊዜ ነው። ቦታውን ሳላይ ማን እንደኾኑ ሳላረጋግጥ ቦታው እንዲህ ነው፤ እርሳቸውም እንዲህ ናቸው ብየ ውል የሌለውን የአሉ እና የፈጠራ ወሬ ማውራት ስለማልፈልግ ነው። ይህ ልጅ አባ ገብረ ሥላሴንአቶ ገብሬ› እያለም ሲጽፍ የነበረ እና ከጌታቸው አሰፋ ጋር እንደሚገናኙ ስልካቸውን ጠልፎ እንደሰማቸው አስመስሎ ጽፎ ተመልክቻለሁ። የሕወኃት ተላላኪ ናቸው፤ የአዜብ መስፍን ወንድም ናቸው፤ ከትግራይ የመጡ ናቸው፤ ምንም የቤተክርስቲያን ትምህርት እውቀት የላቸውም ወዘተ እያለም ብዙ ብዙ ነገር ብሏል። ይህ ሰው የጻፈው ኹሉ ውሸት እንደኾነ በሦስት ነገሮች አረጋግጫለሁ።

እርሱሼር አድርጉት› ብሎ ቀስቅሶ ኹሉም ሳያጣራ ሼር ሲያደርግለት ከዚህም አልፎ ኮፒ እያደረጉ ብዙዎች በራሳቸው የፌስቡክ ገጽ ላይ ሳያጣሩ ሲጽፉለት ሲያይ እርሱ ማንነቱን ሰውሮ ስሙን ኹሉ አጥፍቶ አሁን አካውንቱ ተፈልጎ አይገኝም። ወይ ስሙን ቀይሯል ወይ ለጊዜው አካውንቱን አጥፍቶታል። እውነት ተናግሮ ቢኾን ኖሮ አካውንቱን ማጥፋት ለምን አስፈለገው? ወይስ ደግሞ ብከሰስ ምን እመልሳለሁ ብሎ ይኾን?

ትናንት በ15/04/2011 ዓ.ም ማታ አባ ገብረ ሥላሴ እኛን እንግዶቻቸውን አግኝተው ደስ ብሏቸው ከእኛ ማረፊያ ቦታ ላይ መጥተው እስከ ሌሊቱ 6 ሰዓት ድረስ ብዙ ነገር እያወሩን ነበር። በዚያ እርሳቸው እኛን እያወሩን በነበረበት ሰዓት ይኸው ልጅ ‹›አሁን በዚህ ሰዓት ከጌታቸው አሰፋ ጋር እየተነጋገሩ ነበር ንግግራቸውን ጠልፌ ስሰማቸው ነበር፤ ወደ ፊት ድምጹን እልክላችኋለሁ› ብሎ ጽፎ ሳይ ለእርሱ አፈርኩለት። ከእኛ ጋር ቁጭ ብለው እያወሩን ሳሉከጌታቸው አሰፋ ጋር እየተነጋገሩ ነበር፤ ጠልፌ ሰማኋቸው› ብሎ ውሸት ያስጠላል። ሰውን ሽብር እየፈጠሩ አብያተ ክርስቲያናትን ማጥፋት የማን ሴራ ነው? እኛ ሼር የምናደርግ ሰዎችስ ይህን ውሸት ከፈጠረው ሰው በምን እንለያለን? ለምን አናረጋግጥም? አሉ ከማለት ይልቅ እንዲህ ነው ማለት አይበልጥምን? ቦታውን በትክክል በዓይን መመልከት እየኾነ ያለውና እየተባለ ያለው ምን ያህል እንደሚለያይ ማረጋገጥ አይቻልም ወይ?
 
ትናንት ታኅሣሥ 15/2011 ዓ.ም ምሽት 130 አካባቢ ላይ ነው ወደ ገዳሙ የገባን። ከገባንበት ሰዓት ጀምረው ያሳዩን ኹሉ ነገራቸው ገዳማዊነታቸውን ያሳያል። እስከ 6 ሰዓት ድረስ ስለገዳሙ ኹኔታ ብዙ ነገር ሲያወሩን አመሸን። እንደደከመን ሲያዩ ደህና እደሩ ብለውን ሄዱ። ጠዋት ላይ ገስግሰው ተነሥተው መልክአ ቅዱሳንን፤ መልክአ ሰማእታትን፤ መልክአ መላእክትን በቃላቸው ሞክሸ ጠልፎ ሰይወስዳቸው አሰምተው ሲጸልዩ ሰይጣን ምን ያህል እንደሚርድ አምላከ ቅዱሳን ይወቀው? መልክአ ጉባዔን በቃል መቱን ያለምንም መሳሳት ማድረስ መታደል ነው? አንድ የሕወኃት ሰላይ ይህን ሊያደርግ አይችልም። ይህን ያህል ትምህርት አይማርም። እርሳቸው እኮ ቅዳሴን አጠናቅቀው ተምረዋል፣ መጻሕፍትን አጥንተዋል፣ ቅኔ አዋቂ ናቸው። እነዚህን ትምህርቶች ለማዎቅ ስንት ዓመት ይፈጃል? እርሳቸው ይህን ገዳም ማስተዳደር ከጀመሩ 33 ዓመታት ተቆጥረዋል። ከ33 ዓመት በፊት ነው እነዚህን ትምህርቶች የተማሩ፡፡ ታዲያ የሕወኃት ሰላይ ለመኾን ቅዳሴ መማር፤ ቅኔ ማወቅ፤ መጻሕፍትን ማጥናት የግድ ነው ወይ? የሕወኃት ተላላኪ የኾነ ሰውስ ጉዳዩን ሲጨርስ አይሄድም ወይ? እርሳቸው ለተዋሕዶ ሃይማኖት ሲሉ ራሳቸውን አሳልፈው የሚሰጡ ናቸው፡፡ ገዳሙን ለማስከበር የማይኾኑት የማያደርጉት ነገር የለም፡፡ አለማወቅ ለሐሜት ይዳርጋል። አንድ የኔ ቢጤ አላዋቂ ቤተክርስቲያን ሄዶ ካህናት መቋሚያ ሲያነሡ ሲመለከት እየሮጠ አባቱ ላይ ይሄድና አባቴ ዛሬ ካህናት በመቋሚያ ተጫረሱ ይላል። እንዲያው መርጌታም የሉ እርሳቸው አይሻሉም ባይኾን? ይሉታል። እንዲያውም ዋናው የድብድቡ ጀማሪ እኮ እርሳቸው ናቸው አለ ይባላል። ቀረብ ብሎ የማያውቅ ሰው ከዚህ የተሻለ ነገር ሊል አይችልም።

ቤተክርስቲያናችን እንደዚህ ያሉ ነገሮች ሲመጡባት የምትመልሰው መልስመጥተህ እይ› የሚል ነው። ሄዶ ቦታውን ማየትና ማረጋገጥ መልካም ነው። በቃላት የማይገለጡ በርካታ ነገሮችን ታገኛላችሁ። ስለገነት ከመጻፍ፣ ከመናገር፣ ከማስተማር የተሻለው ነገር በጎ ነገር ሠርቶ ገነትን ማየት ብቻ ነው። ይህ ቦታ ትልቅ ተስፋ ያለው ቦታ ነው። አባ ገብረ ሥላሴ ማንም ይኹኑ ማን፣ ከየትም ይምጡ ከየት፣ ምግባራቸው ጥሩም ይኹን መጥፎ ቦታውን ብታዩት ምን ትኾናላችሁ? ቦታውን ብትረግጡት ትኮነኑ፣ ትረክሱ ይኾን? ገዳም ስትሄዱ የገዳሙን አስተዳዳሪ ብላችሁ ነው ወይ የምትሄዱ? አረ ቆም ብለን እናስብ። ምን አይነት አዚም ነው የተጠናወተን?

አባ ገብረ ሥላሴ ከትግራይ ነው የመጡ የሚለው ሲታይ አያሳፍርም ግን? ይህንን አምነህ የተቀበልክ ሰውስ አታፍርምን? እስኪ ታሪክ አገላብጥ አቡነ ተክለሃይማኖት የት ተወልደው ነው ዳሞት የመጡ? አቡነ አረጋዊ የት ተወልደው ነው ደብረ ዳሞ የመጡ? አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የት ተወልደው ነው ዝቋላ የመጡ? ባሕታዊ ገዳማዊ ሰው የሃይማኖት ሰው ሀገር አለው? ሀገሩንስ መጠየቅ አለበት? ከየት መጣህ መባልስ አለበት? እንኳን ከታቦተ ጽዮን መዲና ቀርቶ ከመሐመድ ሐገር ከዐረብስ ለምን አይመጡም? እኛ ምን አገባን? ይህንን አይተን ስለነበር እርሳቸውን ጠይቀናል። መጀመሪያ ይህ ጥያቄ መጠየቅ የማይገባው እንደኾነ እናውቃለን። ግን የሰውን አእምሮ ነጻ ለማድረግ መጠየቅ አስፈላጊ ስለነበር ጠይቀናል እርሳቸውም መልሰውልናል፡፡ ምንኩስናቸው ዋልድባ አብረንታንት ገዳም ነው። የተወለዱት ጎንደር ነው። ግን ጎንደር ተወለዱ ትግራይ ተወለዱ ለእኛ ምን አገባን? ወደዚህ ገዳምም ሳያስቡት እንደመጡ ቅድስት ሀና ቤተ ክርስቲያን መቅደስ ውስጥ ሳለሁ እጄን ማን እንደኾነ ሳላውቅ ታሥሬ ቀረሁ ይላሉ። ከዚያ ገዳም ወጥቼ ሄጀ ነበር ነገር ግን በደም ተመትቼ ከሞት ተርፌ ያየሁትን አይቼ ተመልሸ መጣሁም ብለውናል። ብታይዋቸው በነጻነት እኮ ነው የሚያናግሩ። እገሌ free ነው እኮ እንላለን አይደል? እንደርሳቸው ያለ ግን free ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡ እብድ ነው የሚመስሏችሁ እኮ፡፡ ሰው ለጠየቃቸው ኹሉ መልሳቸው ጠያቂው ያላቸው ነው፡፡ ‹አባ ሽፍታ ነዎት ይባላል እውነት ነው?› ብትሏቸው ‹አዎ ልጄ እንደእኔ ያለ ወንበዴ እኮ የለም ነው› የሚሉ፡፡

የቤተ ክርስቲያን እውቀት የላቸውም የሚለው ክስ ግን ሄዶ በመጠየቅ አስተምሩኝ በማለት የሚፈታ መልስ ነው። ቅኔውንም፣ መጽሐፉንም፣ ቅዳሴውንም መጠየቅ ትችላላችሁ። እስኪ አረጋግጡ በሐሜት አትታመሱ። ቦታውን ያየ በተአምሩ የተደነቀ ሰው በጣም ይታዘባችኋል። ጠበሉን ተጠምቆ 1 ቀን እየተፈወሰበት ያለ ከዚህም በላይ ገና ቦታውን ሲረግጡ መንፈስ ርኩስ ለቆ የሚሄድበት ከኤድስ ጀምሮ ሌሎችንም ከባድ የሚባሉ በሽታዎችን በጥቂት ቀናት የሚገላገሉበት ተአምረኛ ቦታ ነው። አሁን አሁን እንዲያውም የገዳሙን እንጀራ ሲቀምሱ ያለባቸው ደዌ በሙሉ የሚጠፋበት ልዩ በረከት ያለበት ነውም ብለውናል፡፡


ገዳሙ እንዳይታወቅ በአስተዳዳሪው ላይ የተነዛው ወሬ ለምን መጣ? የሚለውን ለማረጋገጥም ሞክረናል። ጉዳዩ በበጀት የሚመራ የመናፍቃን እጅ ያለበት ነው። የአካባቢው ምእመናንንም እንዲነሡባቸው የተደረገው ይህን ቦታ እንደ ዲማ ሊያደርጉብን ነው በሚል ነው። ምእመናን የገዳሙን የእርሻ ቦታ መውረስ ይፈልጋሉ። ከዚህ በተጨማሪ 3000 በላይ የኾኑ ሀገር በቀል የጽድ ዛፎችን ቆርጠው ለግል ጥቅማቸው ማዋል ይፈልጋሉ። ከዚህ ኹሉ የበለጠው ግን አካባቢው ላይ የሚኖሩት ምእመናን አብዛኞቹ ቅብዐቶች መኾናቸው ነው። አባ ዐሥራት ገዳም እዚህ ደብረ ማርቆስ አጠገብ የቅብዐት ምንፍቅና እየተማሩ እያሠለጠኑ ሲያስመርቁ እያየን ተኝተናል። አንድ ተው ባይ እንኳ የለበትም። እንዲያውም ይህን ጉዳይ አታንሡት እየተባለ ያለበት ጊዜ ነው። ጅብ እግሩን እየበላው ጓደኛውንተው ዝም በል የእኔን እግር ነው የሚበላ› ያለውን ጅል ሰው የኾንበት ዘመን አሁን ነው። HIV የተያዘ ሰውተው እባካችሁ ኤድስ እያላችሁ አታውሩ ተውት ዝም በሉ ስሙን አትጥሩት› እያለ መድኃኒት ባይፈልግለት ውስጥ ለውስጥ ገዝግዞ ገዝግዞ ሚገድለው ራሱን በሽተኛውን እንጂ በሽታውን አይደለም። የእኛ ቤተክርስቲያን አሁን ላይ ጤንነቷ ያሰጋል። የእነጋትራ አካባቢ ሰዎችም አባ ገብረ ሥላሴ ላይ የሐሰት ወሬ እየዘሩ የሚገኙት ከዚህ የተነሣ እንደኾነ ተረድቻለሁ። አባ ገብረ ሥላሴ ለሃይማኖታቸው ምንም ድርድር የላቸውም አድር ባይነት አያውቁም። የፈውስ ጥምቀት ለመጠመቅ እንኳ ተዋሕዶ መኾኑን ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ ተዋሕዶ ያልኾነን ሰው ለፈውስ ጥምቀት አያስገቡትም፡፡ ማንም ይሁን ማን ለማንም ይሁን ለማን አያጎበድዱም። ቅብዐት ምንፍቅና ነው ተጠመቅ እያሉ ያስተምራሉ። ይህን ጥምቀት የማይፈልጉ ሰዎች ናቸው እንግዲህ ይህን ሁሉ ውሸት የሚፈበርኩ። በእነዚህ የሀሰት ፋብሪካዎች አእምሯችሁን የቆለፋችሁ ሰዎች ሂዱና ቦታውን ተመልከቱትማ።

አርብ ታኅሣሥ 19/2011 ዓ.ም በቅዱስ ገብርኤል በዓል በገዳሙ ውስጥ በሚገኘው ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ውስጥ ቅዳሴ ይቀደሳል በዓሉም ይከበራልና እባካችሁ የበረከቱ ተካፋይ መኾን የሚፈልግ ኹሉ ይምጣና ቦታችንን አይቶልን ይሂድ በረከቱንም ይካፈለን ብለዋል። እስኪ ሄደን የማረጋገጥ ነገር ይኑረን። አሉ የሚባለውን በሽታ እናሰወግድ። እዚህ ላይ ብጽፈው በተቃራኒው ለቆሙ ሰዎች መረጃ ስለሚኾናቸው መጻፍ አልፈልግም እንጂ እንደ አባ ገብረ ሥላሴ ፈሊጥ አዋቂ መነኩሴ አላየሁም። በእውነት ነው የምላችሁ ፈሊጠኛ ናቸው።

ትናንት የለጠፈውን ዛሬ የሚያጠፋ ውሸታም የበተነውን የሀሰት ወሬ ወደ ጎን ጣሉትና እስኪ ቦታውን ተመልከቱ። እርሳቸው ምንም ይኹኑ ምን ቦታው ግን የእኛ ነው። እርሳቸው ሥጋ ለባሽ ናቸው በጎ ሊባሉ አይችሉም ግድ ነው። በታሪክ ደግሞ በጎ የተባለ መነኩሴ አላውቅም። አቡነ ተክለሃይማኖትን ተመልከቱ። አቡነ ተክለ አልፋን ተመልከቱ። ማንም እየተነሣ እኮ ነው የሚዘምትባቸው። ክርስቶስስ ምን እንደተባለ ጠፍቷችሁ ነው? አባ ገብረ ሥላሴ ሽፍታ ወንበዴ ናቸው ነው የሚባሉ። እርሳቸው ሽፍታ ወንበዴ እንደመባል የሚያስደስታቸው ስም የለም። ሊቃነ ጳጳሳት እየደወሉአሁንም ስምህ ሽፍታ እና ወንበዴ መባል ነው?› ብለው ይጠይቁኛል።አዎ› ስላቸውበርታ በዚያው ቆይ በጎ ሰው ነው ያሉህ ቀን ግን አንድ ቀን እንዳታድር› ይሉኛል ብለውናል። እርሳቸው ቦታውን እንዲለቁ ከፈለጋችሁ እሽ ብላችሁ ያቀዱትን ሥራ አግዟቸው። ያንን ሠርተው ከጨረሱ እርሳቸው ሌላ ዓላማ የላቸውም። ለመነኮስኩበት ለዋልድባ አፈር አብቃኝ እያሉ የሚጸልዩ አባት ናቸው፡፡ የሚደንቀኝ ነገር 5 ሳንቲም አምጡ የማይባልበት ቦታ ላይ፣ ዓመት ኹለት ዓመት ብትኖር ዝም ብለህ ብላ ጠጣ በሚባልበት ቦታ ላይ የምእመናን መነሣሣት ምንድን ነው? የአካባቢው ምእመናን የዘሩትን በማበላሸት ያጨዱትን በመስረቅ ላይ ናቸው ዛሬ ድረስ። ጎጃም ውስጥ ገዳም አይውጣ የተባለ ይመስላል እኮ። እኔ የማውቀው አንድ ቦታ አለ። ቦታ ገዳሙ ተፈቶ የቅዱሳኑን አጽም በማረሻ እያረሱ እያወጡ በዚያ ስንዱ ዘርተው የሚበሉ አሉ። ይህንንም ገዳም ልክ እንደዚያ ለማድረግ ነው የሚጣጣሩት። በርካታ መጻሕፍትን ምእመናን ዘርፈዋል የአብነት ትምህርት ቤቶችንም አቃጥለዋል። የዚህን ገዳም ታሪክ የያዘው ምእላድ የተባለውን መጽሐፍም አብረው አቃጥለውታል። ታዲያ ይህ ሲኾን እኛ ገዳሙን ማገዝ ሲገባን አሉ የሚሉ ሰዎችን ሼር እያደረግን ገዳሙ እንዲፈታ ባናደርግ መልካም ነው። ብዙ የሚባል ነገር አለ እኔ አልጽፈውም ሄዳችሁ አረጋግጡ። ቅዱሳት መካናትን የምንሳለመው የቃልኪዳን ቦታ በመኾናቸው እንጂ አስተዳዳሪዎችን ብለን አይደለም። ከአስተዳዳሪዎች በረከት የሚሻ እነርሱንም ጸልዩልን ይበል ካላመነባቸው ቦታውን ተሳልሞ ይመለስ በቃ። ምንም እኮ አውጡ አልተባልንም። በቪዲዮ የያዝነውን መረጃ ወደ ፊት እናቀርባለን።

19 የቅዱስ ገብርኤሉን ቅዳሴ ግን አስቡበት።

0911791828
ላይ ደውላችሁ ራሳቸውን አባ ገብረ ሥላሴን ማግኘት ትችላላችሁ። እስኪ አይዞዎት በሏቸው፡፡ ዓላማቸው የግብጹን ገዳመ አስቄጥስ በጎጃም መትከል ነው፡፡ ምእመናንም የተነሡባቸው ዲማን አመጣብን ብለው ነው፡፡ እውነታው ይኼው ነው!

Wednesday, December 12, 2018

የጸሎት ጊዜያት!


ባለፈው ስለ ሰንበተ ሰንበታት አከባበር ጽፌ የነበረ ሲኾን ብዙዎቻችሁ ሌሎች መምህራን ከጻፉት ጽሑፍ ጋር ተለያየብን ብላችሁ ጠይቃችሁኛል፡፡ እኔ የጻፍሁላችሁ ሰንበተ ሰንበታት ባሕረ ሐሳብ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ስለዚህ ግራ ያጋባችሁን ነገር ብዥታውን ለማስወገድ ተጨማሪ የጸሎት ጊዜያት የሚባሉት ልዩ የጸሎት ጊዜያትን ማሳወቅ እፈልጋለሁ፡፡ እነዚህን የጸሎት ጊዜያትም የምጽፍላችሁ ከዚያው ከባሕረ ሐሳብ መጽሐፎቻችን ነው፡፡
1ኛ. ሰንበተ ሰንበታት
=============
ሰንበተ ሰንበታት ማለት ጸሎትን ወደ እግዚአብሔር የሚያሳርጉበት ዕለት ማለት ነው፡፡ በዓመቱ ከሚውሉ ሰንበታት ኹሉ ተለይታ ጸሎት ወደ እግዚአብሔር የሚሳርጉባ እሁድ ናት፡፡ ይች ዕለትም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግመኛ ለሚመጣባት ሰንበተ ሰንበታት አምሳል ናት፡፡ ሰንበተ ሰንበታት በዓመት ሦስት ጊዜ ይከበራል፡፡ በርካታ የጸሎት ጊዜያት አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ሰንበተ ሰንበታት አንዱ ነው፡፡ የአከባበሩ ሥርዓት  እንደሚከተለው ነው፡፡
ዘመን መለወጫ (ዕለተ ዮሐንስ) ሰኞ ከዋለ ከዚህ ሰኞ ጀምሮ ከሰኞ ውጭ ከዋለ ግን ካለፈው ወይም ከሚመጣው ሰኞ እፈልጋለሁጀመረን 133 ቀናትን እንቆጥራለን ያች 133ኛዋ ዕለት እሁድ ናት፡፡ ይች እሁድ የመጀመሪያዋ ሰንበተ ሰንበታት ትባላለች ማለት ነው፡፡ ከዚህ ጀምረን ሰኞን አንድ ብለን ቀጣይ 133 ቀናትን ስንቆጥር ኹለተኛዋን ሰንበተ ሰንበታት እናገኛለን፡፡ ሦስተኛዋ ሰንበተ ሰንበታት ግን ከኹለተኛዋ ሰንበተ ሰንበተ ሰንበታት ቀጥለን 98/99 ቀናትን ቆጥረን የምናገኛት እሁድ ናት፡፡ እዚህ ላይ ግን ዕለተ ዮሐንስ መቼ መቼ ሲውል ነው ያለፈውን ሰኞ የምንወስደው መቼ መቼ ሲውልስ ነው የሚመጣውን ሰኞ መነሻ የምናደርገው የሚለውን የሚያብራራልን ካለ እፈልጋለሁ፡፡ የተመለከትኳቸው ውሱን መጸሕፍት በዚህ ዙሪያ ሰፊ ማብራሪያ ስላላገኘሁባቸው ነው፡፡ ሰንበተ ሰንበታት ግን የሚውሉት አንዱ በጥር አንዱ በግንቦት አንዱ ደግሞ በጳጉሜን ወር ላይ ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የሰንበቶች ሰንበት የምትባለዋ ዕለት እግዚአብሔር ዓለምን የፈጠረባት፣ የተጸነሰባት፣ ከሙታን ተለይቶ የተነሣባት፣ ዳግመኛም ዓለምን ለማሳለፍ የሚመጣባት ዕለተ እሁድ ናት፡፡
2ኛ. ሰንበተ ረቡዕ
=============
ይህም ለእግዚአብሔር ጸሎት የሚደረስበት ልዩ ዕለት ነው፡፡ ይህን ዕለት ለማግኘት አቆጣጠሩ እንደሚከተለው ነው፡፡ ዘመን መለወጫ (ዕለተ ዮሐንስ) ኀሙስ ከዋለ ከኀሙስ ጀምረን በሌሎች ዕለታት ከዋለ ግን ከሚመጣው ኀሙስ ጀምረን 91 ቀናትን በመቁጠር የሚገኝ ነው፡፡ አቆጣጠሩ ካለፈው ኀሙስም የሚጀምርበት አለ፡፡ (መቼ መቼ ሲኾን የሚለውን ግን አሁንም ሊቃውንቱ እንዲያብራሩልን እጠይቃለሁ)፡፡ የሚውለውም አንዱ በኅዳር/ታኅሣሥ ፤ አንዱ በየካቲት /መጋቢት፤ አንዱ ግንቦት/ሰኔ፤ አንዱ ነሐሴ/ጳጉሜን ይውላሉ፡፡ ዕለቱ ረቡዕ ይኾናል በዓመት 4 ጊዜም ይውላል ማለት ነው፡፡
3ኛ. ርኅወ ሰማይ
=============
ይህ ዕለት ሰማይ የሚከፈትበት ሲኾን ውኃ እና ዘይት ላይ ተጸልዮ ለፈውስና ለረድኤት የሚጠመቁበትና የሚጠጡበት ልዩ የጸሎት ዕለት ነው፡፡ ዕለቱን ለማወቅ ከጳጉሜን 2/3 ጀምረን በ52 በ52 ቀናት በመከፋፈል ይገኛል፡፡ በዓመት 7 ጊዜም ይውላል፡፡ ይኸውም በጥቅምት 20 በታኅሣሥ 12 በየካቲት 4 በመጋቢት 26  በግንቦት 18 በሐምሌ 10 በጳጉሜን 2/3፡፡ አንዳንድ መጻሕፍት የታኅሣሡን ታኅሣሥ 22 አድርገው ሌሎችን እንዳሉ ይወስዳሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ የሐምሌውን ሐምሌ 20 አድርገው ሌሎችን ባሉበት ያከብራሉ፡፡ የጳጉሜኑንም እንዲሁ አንዳንዶች 2ን አንዳንዶች 3ን ወስደው ሌላውን ባሉበት ያከብራሉ፡፡ 52 የሚለው ቀን የሚቆረው ከማግስት ጀምሮ ነው፡፡
4ኛ. ምሕላ ዘስብከተጌና
=============
ዕለቱ እሁድ ይውላል፡፡ አቆጣጠሩም ታኅሣሥ 1 ኤልያስ የሚውልበትን ቀን መነሻ ያደርጋል፡፡ በዚህም መሠረት ኤልያስ ማክሰኞ ሲውል ታኅሣሥ 13፣ ረቡዕ ሲውል ታኅሣሥ 12፣ ሐሙስ ሲውል ታኅሣሥ 11፣ ዓርብ ሲውል ታኅሣሥ 10፣ ቅዳሜ ሲውል ታኅሣሥ 9፣ እሁድ ሲውል ታኅሣሥ 8 ከአቡነ ተክለ አልፋ በዓል ጋር ይደረባል፤ ሰኞ ሲውል ታኅሣሥ 7 ይውላል ማለት ነው፡፡
5ኛ. ምሕላ ዮሐንስ
=============
ይህ የጸሎተ ምሕላ ጊዜ ጳጉሜንን መነሻ አድርጎ የሚቆር ነው፡፡ ይኸውም ጳጉሜን 1 ዓርብ ከዋለ ነሐሴ 29፣ ጳጉሜን 1 ቅዳሜ ከዋለ ነሐሴ 28፣ ጳጉሜን 1 እሁድ ከዋለ ጳጉሜን 4፣ ጳጉሜን 1 ሰኞ ከዋለ ጳጉሜን 3፣ ጳጉሜን 1 ማክሰኞ ከዋለ ጳጉሜን 4፣ ጳጉሜን 1 ረቡዕ ከዋለ ጳጉሜን 3፣ ጳጉሜን 1 ሐሙስ ከዋለ ጳጉሜን 2 ይውላል፡፡ ምሕላ ዮሐንስ ከነሐሴ 28 አያንስም ከጳጉሜን 4ም አይበልጥም፡፡ ከነሐሴ 28 እስከ ጳጉሜን 4 ብቻ እንዲውል ተደርጎ የተሠራ የጸሎት ጊዜ ነው፡፡
6ኛ. ምሕላ መስቀል
=============
ይኸኛው የምሕላ ጸሎት አቆጣጠሩ መስከረም 1ን መነሻ ያደረገ ነው፡፡ መስከረም 1 ረቡዕ እና ሰኞ ከዋለ መስከረም 24፣ መስከረም 1 ሐሙስ እና ማክሰኞ ከዋለ መስከረም 23፣ መስከረም 1 ዓርብ ከዋለ መስከረም 22፣ መስከረም 1 ቅዳሜ ከዋለ መስከረም 19፣ መስከረም 1 እሁድ ከዋለ መስከረም 20 ይውላል፡፡ የዚህ ጸሎት ጊዜ ከ19 አያንስም ከ24 አይበልጥም፡፡ ከመስከረም 19-መስከረም 24 ድረስ ባሉ ቀናት ውስጥ ይውላል፡፡
7ኛ. ምሕላ ጽጌያት
=============
ይህ ምሕላ የአበባዎች ምሕላ ነው፡፡ የዚህ ምሕላ አቆጣጠር መነሻው የኅዳር ወር ነው፡፡ ኅዳር 1 ዓርብ ሲውል ጥቅምት 29፤ ኅዳር 1 ቅዳሜ ሲውል ጥቅምት 28፤ ኅዳር 1 እሁድ ሲውል ኅዳር 1፣ ኅዳር 1 ሰኞ ሲውል ኅዳር 3፣ ኅዳር 1 ማክሰኞ ሲውል ኅዳር 2፣ ኅዳር 1 ረቡዕ ሲውል ኅዳር 1፣ ኅዳር 1 ሐሙስ ሲውል ጥቅምት 30 ይውላል፡፡ ይህም ከጥቅምት 28 አያንስም ከኅዳር 4ም አይበልጥም፡፡ ከጥቅምት 28 እስከ ኅዳር 4 ባለው ውስጥ ይውላል ማለት ነው፡፡
8ኛ. ምሕላ በአተ ክረምት
=============
ይህ ምሕላ የክረምት መግባት (ግባት) ምሕላ ነው፡፡ አቆጣጠሩ መነሻ የሚያደርገው የሰኔ ሚካኤልን (ሰኔ 12ን) (አዊት)ን ነው፡፡ ሰኔ 12 ረቡዕ ሲውል ሰኔ 21፣ ሰኔ 12 ሐሙስ ሲውል ሰኔ 20፣ ሰኔ 12 ዓርብ ሲውል ሰኔ 19፣ ሰኔ 12 ቅዳሜ ወይም ሰኞ ሲውል ሰኔ 23፣ ሰኔ 12 እሁድ ወይም ማክሰኞ ሲውል ሰኔ 22 ይውላል፡፡ ከሰኔ 19 አያንስም ከሰኔ 23ም አይበልጥም፡፡ ምንጊዜም ከሰኔ 19-ሰኔ 23 ድረስ ባሉ ቀናት ብቻ ይከበራል፡፡
ለዚህ ጽሑፍ ምንጮቼ የባሕረ ሐሳብ መጻሕፍት ናቸው፡፡
================
© መልካሙ በየነ
ታኅሣሥ 3/2011 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

Friday, December 7, 2018

ሰንበተ ሰንበታት



=============
ሰንበተ ሰንበታት ማለት ጸሎትን ወደ እግዚአብሔር የሚያሳርጉበት ዕለት ማለት ነው፡፡ በዓመቱ ከሚውሉ ሰንበታት ኹሉ ተለይታ ጸሎት ወደ እግዚአብሔር የሚሳርጉባ እሁድ ናት፡፡ ይች ዕለትም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግመኛ ለሚመጣባት ሰንበተ ሰንበታት አምሳል ናት፡፡ ሰንበተ ሰንበታት በዓመት ሦስት ጊዜ ይከበራል፡፡ በርካታ የጸሎት ጊዜያት አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ሰንበተ ሰንበታት አንዱ ነው፡፡ የአከባበሩ ሥርዓት  እንደሚከተለው ነው፡፡
.
.
.
ዘመን መለወጫ (ዕለተ ዮሐንስ) ሰኞ ከዋለ ከዚህ ሰኞ ጀምሮ ከሰኞ ውጭ ከዋለ ግን ካለፈው ወይም ከሚመጣው ሰኞ እፈልጋለሁጀመረን 133 ቀናትን እንቆጥራለን ያች 133ኛዋ ዕለት እሁድ ናት፡፡ ይች እሁድ የመጀመሪያዋ ሰንበተ ሰንበታት ትባላለች ማለት ነው፡፡ ከዚህ ጀምረን ሰኞን አንድ ብለን ቀጣይ 133 ቀናትን ስንቆጥር ኹለተኛዋን ሰንበተ ሰንበታት እናገኛለን፡፡ ሦስተኛዋ ሰንበተ ሰንበታት ግን ከኹለተኛዋ ሰንበተ ሰንበተ ሰንበታት ቀጥለን 99 ቀናትን ቆጥረን የምናገኛት እሁድ ናት፡፡ እዚህ ላይ ግን ዕለተ ዮሐንስ መቼ መቼ ሲውል ነው ያለፈውን ሰኞ የምንወስደው መቼ መቼ ሲውልስ ነው የሚመጣውን ሰኞ መነሻ የምናደርገው የሚለውን የሚያብራራልን ካለ እፈልጋለሁ፡፡ የተመለከትኳቸው ውሱን መጸሕፍት በዚህ ዙሪያ ሰፊ ማብራሪያ ስላላገኘሁባቸው ነው፡፡ ሰንበተ ሰንበታት ግን የሚውሉት አንዱ በጥር አንዱ በግንቦት አንዱ ደግሞ በጳጉሜን ወር ላይ ነው፡፡
.
.
.
በዚህ መሠረት የዘንድሮውን የ2011 ዓ.ምን ሰንበተ ሰንበታት ለማወቅ ዕለተ ዮሐንስ የዋለበትን ማክሰኞ ያዙና ወደ ኋላ የ133 ቀናት መነሻችንን ሰኞን ያዙ፡፡ መነሻ ቀኑ ጳጉሜን 5 ዕለቱ ሰኑይ ይኾናል ማለት ነው፡፡ ከጳጉሜን 5 ጀምራችሁ 133 ቀናትን ስትቆጥሩ የምታገኙት የመጀመሪያው ሰንበተ ሰንበታትን ይኾናል፡፡ ይህ ቀን ማነው?
.
.
.
ኹለተኛውን ለማግኘት ደግሞ ከመጀመሪያው ሰንበተ ሰንበታት ቀጥለን ከምናገኘው ሰኞ ጀምረን ሌላ 133 ቀናትን ቁጥሩ፡፡ ያ ቀን ማነው እስኪ ሂሳቡን አስሉት?
.
.
.
ሦስተኛውን ሰንበተ ሰንበታ ለማወቅ ደግሞ ኹለተኛው ሰንበተ ሰንበታት ከዋለበት ዕለት ቀጥለን ከምናገኘው ሰኞ ጀምረን 99 ቀናትን ስንቆጥር የምናገኘው ይኾናል፡፡ ቀኑ ማነው አስሉት?
.
.
.
የሰንበተ ሰንበታት አከባበር ይህን የሚመስል ነው፡፡ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ይህ ዕለት በደማቅ ክብረ በዓል የሚከበር ትልቅ በዓል ነው፡፡ የበለጠ ስለ አሰላሉ የምታውቁ ሊቃውንት አስረዱን፡፡ እኔ የማውቀው የሰንበተ ሰንበታት አሰላል ይኼ ነው፡፡ ከዚህ የተለየ ካለ አስረዱን፡፡