Sunday, February 10, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 5


==================
ሦስተኛ ጉባኤ። 
ወአልበሶ አልባሰ ብሩሃ።
ከአራቱ ባሕርያት ፈጥሮ ከእንስሳት ከአራዊት ለይቶ በነባቢት ነፍስ አከበረው ብሎ ነበርና ልጅነትን ሰጠው ፤ እስመ አልበሰክኒ ልብሰ ትፍሥሕት ወልብሰ መድኃኒት እንዲል።   
አካሉን ሲያይ ብሩህ አለ ፤ ሀብቱን ሲያይ አልባስ ብሎ አበዛ ፤ ከዚህ ዕለቱን አስመስሎታል አክሲማሮስ በ፵ ቀን ብሎ ለይቶ ተናግሯል።
ወገብረ ሎቱ ሥልጣነ ለርእሱ።
ሥራ ሠርቶ ሊጠቀምበት መንፈሳዊ  ዕውቀትን ሰጠው። 
ወአኅጥዖ ሞተ።
በዓቂበ ሕግ እንዳይሞት አደረገው።
ወረሰዮ ሥሉጠ ላእለ ኩሉ ፍጥረት ዘታሕተ ሰማይ በአራቱ ማዕዘን ያሉትን ፍጥረት አሰገዛው፤ ወአሠልጠኖ አራቱ ማዕዘን ባሉ ፍጥረት አሠለጠነው።
ወፈጠረ ሎቱ እምሥጋሁ ረድኤተ።
ከአካሉ ልትረዳው ፈጠረለት  በአቅልሎ ክበደ ዋዕይ ልጅ በማስገኘት አንድም እሱ የአፍአውን እሷ የውስጡን በማከናወን ።   
ወሰመያ ሔዋን።      
ስሟን ሔዋን አላት ፤ ሕይወት ማለት ነው እንደግብሯስ ሞት በተባለች በተገባት ነበር ሕያዋን ጸድቃን ከሷ የሚወለዱ ስለሆነ ሕይወት አላት።
ወአንበሮሙ ውስተ ገነተ ዔዶም ጽባሐዊ ።
መወደድ ባለው በምሥራቅ በኩል በገነት አኖራቸው አንድም ጽባሐዊ መወደድ ባለው በገነት ምሥራቅ አኖራቸው አራት ማዕዘን አለውና።
ወወሀቦሙ ይትፈሥሑ በኵሉ ሠናያት አምላካውያት ዘእንበለ ክልዓት።
ወሀቦሙ ዘእንበለ ክልዓት ከአምላክ በሚገኘው ነገር ሁሉ ደስ ይላቸው ዘንድ ያለመከልክል ሰጣቸው ይትፈሥሑ ዘእንበለ ክልዒት ያለመከልከል ደስ ይላቸው ዘንድ 
ወወስነ ሎሙ ትእዛዘ በእንተ አሐቲ ዕፅ ባሕቲታ
ስለ አንዲት ዕዕ ብቻ ትእዛዝ ወሰነባቸው።
ወይእቲ ዕፅ እንተ ታሌቡ ሠናየ ወእኩየ ።
ያችም ዕፅ ባይበሏት በጐ ቢበሏት ክፉ የምታስታውቅ ናት።
ከመ ኢይብልዑ እምኔሃ።
ወሰነ ከመ ኢይብል አምኔሃ ከሷ አንዳይበሉ ትእዛዝ ወሰነባቸው። ሐተታ የገዥና የተገዥ ምልክት የዓቂበ ሕግ ምልክት ጾምንም በዚህ ነገረው።
እስመ አመ ይበልዑ እምኔሃ ሞተ ይመውቱ ።
ከሷ የበሉ እንደሆነ የሞት ሞት ይሞታሉና ብሎ
ወለእመ ሰምዑ እንከ ትእዛዞ ይከውኖሙ ሕይወተ ዘለዓለም ።
ትአዛዙን ቢጠብቁ የዘለዓለም ድኅነት ይሆናቸዋል ብሎ። አንድም ትእዛዙን ጠብቀው ቢሆን የዘለዓለም ድኅነት በሆናቸው ነበር ። ወለእመሰ ተዓደው ይከውኖሙ ሞተ። ትእዛዙን ግን ቢያፈርሱ ሞት ተፈረደባቸው ። ወሶበ ርእየ ሰይጣን ዕበየ ስብሐቲሁ ወክብራቲሁ ሰይጣን የራሱን ደግ ክብሩን ፤ ደግ ጌትነቱን ባየ ጊዜ
ወብርሃነ ዘይትዓፀፍ ቦቱ ።
ተሰጥቶት የነበረውን ጸጋውን ባየ ጊዜ።
ወርእየ ርእሶ በርእሱ እምድኅረ ክብር ወሢመት ዓባይ።  
ከሹመቱ ከተሻረ ከልዕልናው ከተዋረደ በኋላ ራሱን በራሱ በመረመረ ጊዜ ወደቀ አንድም መልስ የአዳም ደግ ክብሩን ደግ ጌትነቱን ባየ ጊዜ ለአዳም የተሰጠውን ጸጋውን ባየ ጊዜ አዳም ከተሾመ ከከበረ በኋላ የራሱን ክብር በአዳም ላይ ሁኖ ባየ ጊዜ ወድቀ በድቀተ ቅንዓት።
ቅንዓት ባመጣው ድቀት ወደቀ ደንገፀ በድንጋፄ ቅንዓት ፤ ቅንዓት ባመጣው ድንጋፄ ደነገጸ  ኃዘን ባዘነ ቅንዓት ተከዘ በትካዘ ቅንዓት፤ ኃዘን ትካዝ ባመጣው ቅንዓት አዘነ ፤ ወድቀ መውዱቅ ውዱቅ ይላል መውዱቅ ዲያብሎስ ውዱቅ አዳም ነው አዳምን ያሳተ ዲያብሎስ ወደቀ ድል ሆነ።
ወቀብጸ ተስፋሁ ። ተስፋ ቆረጸ
በእንተ ዘኢፈቂዶቱ እግዚአብሔር ኪያሁ፤
እግዚአብሔር እሱን ባለመሻቱ
ወኢያግብዖ ውስተ ዘቀዳሚ መንበሩ፤
ወደ ቀደመ ቦታው ወደ ቀደመ ማዕርጉ ባለመመለሱ ወኢተርፈ ሎቱ እምነ ዘይእኅዝ ዘእንበለ ዘያሰግዶ ለብእሲ ከመ ያውጽኦ እምፈቃደ ፈጣሪሁ ። ወይም እንጂ ይመልሰኝ ይሆናል ብሎ ነበርና አዳምን ከፈጣሪው ትእዛዝ ያወጣው ዘንድ አዳምን ከሚያስትበት ግብር በቀር ከያዘው ከረዘዘው የቀረለት የለም ። 
ወነሥአ ሎቱ ተኃይሎተ ዘበእኪት።
የበጐ መበረታታት አለና የከፉ መበራታትን አደረገ።
ወመንሱተ ወልታ 
ወልታ መንሱተ ሲል ነው አዳምን ድል የሚነሳበትን ጋሻ አነገበ።
ወመጽአ መንገለ ብእሲ በውእቱ ተኃይሎት ጸዋግ በክፉ መበራታት ወደ አዳም መጣ ሐተታ ፤ አሞንዮስ አውሳብዮስ በገነት እንዳሉ ሁነው ይጽፋሉ ወአምጽእዎ ለውእቱ ንዋይ እምኢየሩሳሌም እንዳለ ነቢይ በኢየሩሳሌም ሳለ በባቢሎን እንዳለ አድርጎ በእንተ ምክንያት ዘያወፅእ ቦቱ እምገድል ሠናይት ከበጐ ግብር ስለሚያወጣበት ምክንያት እምገነት ሠናይት እምፍኖት ሠናይት እምግእዝ ሠናይት እምዕረፍት ሠናይት ይላል ። 
ወጸንሆ እንከ።  
ሸመቀበት ሰው በጠላቱ እንዲሸምቅ ጦሩን ሰንግሎ ጋሻውን ወልውሎ፤ አንድም ድል የሚነሣበትን ግብር ዐወቀ ፤ አንድም የሚለያዩበትን ጊዜ ጠበቀ ።
በከመ የአምሮን ጸላዒ ለጊዜያት ለነኒ ይደልወነ ከመ ናአምር ድካማቲነ እንዲል ። ወናሁ ውእቱ ምስለ ረድኤቱ ተሠልጡ ውስተ ኵሉ ዕፀወ ገነት።   
ተሠልጡ ካለ ውእቱ ወረድኤቱ ምስለ ረድኤቱም ካለ ተሠልጠ ቢል በቀና ነበር ልማደ መጽሐፍ ነው ሌሊት ምስለ መዓልት ይትካፈልዎ ለዘመን በዕሪና። ከንቶ ይትናገሩ ፩ዱ ምስለ ካልዑ እንዲል እሷ እሱ በገነት ባለው ዕፅ ሁሉ ሠልጥነው ነበር ።
ዘእንበለ አሐቲ ዕፅ ባሕቲታ እንተ ከልኦ እምኔሃ ።
እሷን አትብላ ብሎ ከከለከለው ካንዲት ዕፅ በቀር ወተፈሥሐ እንከ ዓቢየ ፍሥሐ  
ፈጽሞ ደስ አለው ።
ወአእመረ ከመ በውእቱ ፅዕ ይመውኦ ።
በፅፀ በለስ ድል እንዲነሣው ዐውቋልና ።
ወያወፅኦሙ ለአዳም ወለሔዋን እምፍግዓሆሙ ።
አዳምና ሔዋንን ከተድላቸው ከደስታቸው እንዲለያቸው አንድም ተድላ ደስታ ከሚያደርጉባት ከገነት እንዲያወጣቸው ዐውቋልና።
ወተኀብአ እንከ ውስተ ሥጋ ከይሲ ። 
በሥጋ ከይሲ ተሰወረ ።
ወረሰያ ምክንያተ ለኃጕል ።
ለጉዳት ምክንያት አደረጋት ታሪክ እንስሳት አራዊት ከአዳም ዘንድ ሄዱ ስለምን ቢሉ ስም ለመሰየም ስምስ ተሰይመዋል እስከዚያ ወዴት ኑረው ብሎ ለደጅ ጥናት ሄደው አርደህ ብላን አሉት ። ምን አጥቼ በገነት ባለ ፅፅ ሁሉ አሠልጥኖኛል፤ እናንተስ ባላችሁበት ያርባችሁ ያብዛችሁ ያስፋፋችሁ ብሎ መርቆ ሰደዳቸው ፤ ዲያብሎስ ከመንገድ ቆይቶ ወዴት ሂዳትሁ ኑራችኋል አላቸው ። ከአዳም ከጌታችን አሉት። አዳም ጌታችሁ ምን ይመስላል አላቸ ከፀሐይ ሰባት እጅ ያበራል አሉት በዚያውስ ላይ ይህን ያህል ደስታ ምን ተገኝቷል አላቸው ። እንዲህ ብንለው እንዲህ አለን ሞት ሲቀርልን አሉት። ያችን ዕፅ ቆርጦ ማን ካፉ ባገባልኝ ነበር ብሏል ። በሌላው ቀን ሲሄዱ አገኛቸው ወዴት ትሄዳላችሁ አላቸው። ከአዳም ከጌታችን አሉት ። አስከትሉኝ አላቸው አዳም ጌታችን መልከ መልካም ነው አንተ መልከ ጥፉ ብለው ትተውት ሄዱ ። አብርል አዝርል የሚባሉ የገነት አዕዋፍ መጡ አስከትሉኝ አላቸው። አዳም ጌታችን መልካም አንተ ክፉ ብለው ጥለውት ሄዱ ። እባብ መጣች የገመል ወሳብሬ ታህል ነበር ወዴት ትሄጃለሽ ኣላት ወደ አዳም ወደ ጌታዬ አለችው፤ አስከትይኝ አላት አዳም ጌታዬ መልካም ነው አንተ ክፉ ነህ አይሆንም አለችው ። ከፉ ከሌለ መልካም በምን ይታወቃል መስሎሻል ። በዚያውስ ላይ ባንቺ እንጂ አምር የለም ብሎ በውዳሴ ከንቱ ጠለፋት፤ አስከትላው ሄደች። ቁልቁለቱን ጨርሰው እዳገቱ ደረሱ ፤ የቆላ መንገድ እንጂ ካልተዋወቁበት አይሆንም እየተዛዘልን እንውጣው አላት እሽ አለችው። ነይ ልዘልሽ አላት ጥቂት እልፍ አድርጎ በጽሐ ሥጋ ተባርዮ ዘጾርኪኪ ጹርኒ አላት አዘለችው። በሷ ሥግው ሆነ። ከአዳም ዘንድ ሄደ ጸሎት ይዞ አገኘው አስቀድሞ በዚህ ድል ነሣው በሐከ ንጉሠ ሰማያት ወምድር አለው ፍልጥ አርዌ ምድር። ንጉሠ ምድር ነኝ እንጂ ንጉሠ ሰማያት ፈጣሪዬ ነው አለው ። ሔዋን ወዴት ናት አለው ፤ ከዚያ አለች አለው ቢሄድ ሥራ ፈትታ አገኛት በዚህ ድል ነሣት።
ወአስተርአያ ለሔዋን በነገር ጥዑም ዘምሉዕ ጕሕሉተ ክዳት ተንኮልን በተመላ ደስ በሚያሰኝ አነጋገር ሔዋንን ተናገራት ፤ በሐኪ ንግሥተ ሰማይ ወምድር አላት ደስፈቅ አላት ፤  ወይቤላ በእንተ ምንት ይቤለክሙ እግዚአብሔር ኢትብልዑ እምኵሉ ዕፀው ዘውስተ ገነት።
ለይቼ የጠየቅኋት እንደሆነ ታውቅብኛለች ብሎ በገነት ካለው ዛፍ ሁሉ አትብሉ ያላችሁ ስለምን ነው።
ወትቤሎ ንበልዕሰ እምኵሉ ዕፀው ዘውስተ ገነት በገነትስ ካለ ዕፅ ሁሉ እንበላለን፤  
ወባሕቱ ፍሬ ዕፅሰ ዘውስተ ገነት ይቤለነ እግዚአብሔር ኢትብልዑ እምኔሃ። ነገር ግን በገነት አንዲት ዕፅ አለች እሷን አትብሉ ብሎናል። 
ከመ ኢትሙቱ ሞተ።
ያው ቅሉ ነፍጎን አይደለም የሞት ሞት ትሞታላችሁ ብሎ ነው እንጂ አለችው
ወይቤላ አኮ ሞተ ዘትመውቱ።  
ጣዖቱን ይሰብካል የሞት ሞት ትሞታላችሁ ብሎ ወባሕቱ የአምር እግዚአብሔር ከመ ሶበ በላዕክሙ እምኔሃ ይትከሠታ አዕይንቲክሙ ወትከውኑ ከመ አምላክ ። በበላችሁ ጊዜ የአምላክነት ዕውቀት እንድታውቁ እንደ አምላክ እንድትሆኑ ያውቃልና፤
ወተአምሩ ከመ ሠናየ ወእኩየ
የሰውነት የአምላክነት ዕውቀት እንድታውቁ ያውቃልና ስለዚሀ ነው እንጂ የሞት ሞት ትሞታላችሁ ብሎ አይደለም።
ወአፍተዋ ከመ ትብላዕ እምውእቱ ዕፅ ዕፀ በለስን ትበላ ዘንድ አስወደዳት ልብላ ልብላ አሰኛት።
ወታብልዖ ለአዳም፤  
ለአዳም ታበላው ዘንድ    
ከመ ይኩኑ ዘየአምሩ ሠናየ ወእኩየ።
የሰውነትን የአምላክነትን ዕውቀት ያውቁ ዘንድ ፤
ወሶበ ጸነት ኀበ ነገሩ ጸንዓ ላዕሌሃ ፍትወተ ጥዕመት ምስለ ሕሊና ትዕቢት ነገሩን በተቀበለችው ጊዜ አምላክ እሆናለሁ በማለት ልብላ ልብላ የማለት ፈቃድ አደረባት። ልብላ አሰኛት።
ወአፍጠነት ወበዓልት እምይእቲ ዕፅ፤ ፈጥና ቆርጻ በላት።
ወአብልዓቶ ለአዳም፤  ለአዳምም አበላችው ። ሐተታ ነገሩን እንደ ተቀበለችው አውቆ የአምላክነት ነገር እንዲህ አይደለም የተቀዳደማችሁ እንደሆነ ያንድኛችሁ ይቀርባችኋል ለርሱ በቀኝ እጅሽ ላንቺ በግራ እጅሽ ቆርጠሽ ፩ ጊዜ ጉረሷት አላት። የሷ ሲነሣት አይቶ እሱ ያመልጠኛል የሱ ሲነሣው አይታ እሷ ታመልጠኛለች ብሎ፤ ዛሬም ሴቶች ይህ አብነት ሁኖባቸው በቀኝ እጃቸው ለባሎቻቸው እያሳለፉ በግራ እጃቸው ይበላሉ።   
ወወጽኡ እምትእዛዘ እግዚኦሙ ወተዓደው እምነገሩ።
ከፈጣሪያቸው ትእዛዝ ወጡ።
ወኮኑ ቀታልያነ ርእሶሙ
ራሳቸውን አጥፊ ሆኑ።   
ወተሰዱ እምድረ ገነት ኀበ ምድረ ሕማም፤ 
ከገነት ወደ ምድረ ፋይድ ወረዱ፤ ሐተታ ምድረ ፋይድ ማለት ምድረ ኃሣር ወመርገም ምድረ ድንጋጼ ወረዓድ ማለት ነው ።  
ወአርአያ ኅሱም ወኅሱር፤
ክፉና መልካም ቀይና ጥቁር አጭርና ረጅም ቀጭንና ወፍራም ወደሚፈጠርበት። 
ወሲሳየ ኃዘን።
ቢያገኙት ቁንጣን ቢያጡት ቀጠና ወደሚሆንበት
ወፈትሐ ላዕሌሆሙ በሞት እስከ ለዝሉፉ
አምስት ሺሀ አምስት መቶ ዘመን እስኪፈጾም
በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስን፤ በርደተ መቃብር ላይ ርደተ ገሃነምን ፈረደባቸው።
ወእምድኅረ ተዓርቁ እምልብሰ ብርሃን ዘተአጽፉ ቦቱ። ከተሰጣቸው ከጸጋቸው ከተለዩ በኋላ  አንድም የተሰጣቸው ጸጋቸውን ባጡ ጊዜ።
ተኃፍረ አዳም እም እግዚአብሔር።
ከእግዚአብሔር የተነሳ አዳም ፈራ፤ ሐተታ ሰኰና ብአሲ እያሰማ ቢመጣ አዳም ፈርቶ ከእንጨት ውስጥ ተሰውሮ ተገኝቷል። 
በእንተ ተዓድዎቱ ።
ከትእዛዙ ስለወጻ ፈራ።
ወናሁ ቀደመ ቃል ከመ ነፍስ ነባቢት እንዘ አልቦ ዘይኴንና ወዘይኄይላ።
ተኃፍረ ብሎ ነበርና በምን አውቆ ትሉኝ እንደሆነ የሚገዛት የሚያዛት ሳይኖር ነፍስ አዋቂት እንደሆነች አስቀድሞ ተነግሯል ወገብረ ላቲ ሥልጣነ በውስቴታ ከመ ትግበር ዘከመ ኃረየት ተብሎ ወለእመሰ ነበረት በትእዛዙ እምኮነት ብርህተ በብርሃነ ትእዛዙ። ትእዛዙ ጠብቃ ኑራ ቢሆን ትእዛዙን ቢጠብቁ በሚገኝ ብርሃን ትእዛዙን በመጠበቅ ብርሃን ብርህት በሆነች ነበር ።
ወሶበ ጸነት እንከ ኀበ ተዓድዎተ ነገሩ ጸልመት በጽልመተ ተአደዎ። 
ትእዛዙን ግን ቢያፈርሱ። ትእዛዙን ቢያፈርሱ በሚመጣ ጨለማ ትእዛዙን በማፍረስ ጨለማነት ጨለመች ማለት ። ትእዛዙን ቢያፈርሱ በሚመጣ ድንቁርና ደነቆረች።
እስመ አልቦ ዘይኴንና ወዘይኄይላ በውስተ ፈቃደ በፈቃዷ የሚያዛት የሚገዛት የለምና እመ ነበረት ለበጎው የሚያዛት የሚገዛት ሳይኖር ሶበ ጸነት ለክፉው።
ወበእንተ ዝንቱ ይረክቦ ለብእሲ ገነት ፤
ገነተ ሲል ነው ፤ መገናኘት የጋራ ከሆነ ብሎ እንዲህ እለ እንጂ ። ስለዚህ አዳም ገነትን ይወርሳል ። ሶበ ተመይጠ እምእኵይ ውስተ ሠናይ ወገቢሮቱ ። ከክፉ ወደ በጎ ቢመለስ በጐውን ወደ ማድረግ ቢመለስ ገነትን ይወርሳል፤   
ወሶበ ጸነ እምሠናይ ኀበ እኩይ ወገቢሮቱ፤ ከበጎ ወደ ክፉ ቢመሰስ ክፉውን ቢያደርግ 
ደለዎ ኵነኔ
ሞት ተፈረደበት።
ወበጸኒኖቱ ለአዳም ኀበ ፈቃደ ሰይጣን ወተዓድዎተ ፈጣሪሁ ኮነ እንከ ገብሮ ለሰይጣን፤
አዳም የሰይጣንን ነገር በመከተሉ ከፈጣሪው ትእዛዝ በመውጣቱ የሰይጣን ተገዢ ሆነ። 
ወታሕተ ሥልጣኑ
ከሥልጣኑ በታች ነ፤  
ወተርፈ ውስተ ምድር ኅዙነ ወትኩዘ
በዚህ ዓለም ያዘነ የተከዘ ሁኖ ኖረ ፤ አንድም ኮነ ገብሮ ለሰይጣን ታሕተ ሥልጣነ፤ ከሥልጣኑ በታች ሁኖ ለሰይጣን ተገዢ ሆነ ። ወተርፈ በዚህም ዓለም ያዘነ የተከዘ ሁኖ ኖረ፤   
በእንተ ዘገብረ ተዓድዎተ፤    ከፈጣሪው ትእዛዝ ስለወጣ
ወዓለወ ትእዛዘ ፈጣሪሁ፤
የፈጣሪውን ትእዛዝ ስላፈረሰ፤  
ወእምንዳቤ እንተ ረከቦ።
ካገኘው ጸዋትወ መከራ የተነሣ፤   
እምኃዘን ወእምአውያት ፤     
ከኃዘን ከልቅሶ የተነሣ፤   
ወክኢወ አንብዕ ውዑይ።  
ቁጡ እንባን ከማፍሰስ የተነሣ ። ሐተታ ቁጡ እንባ ዓይን ከማጥፋት ያደርሳል ። አንድም ውዑይ እንባ ከማፍስስ የተነሣ።
ረስዓ ገነተ እንተ ነበረ ባቲ፤
የነበረባትን ገነትን ዘነጋ።
ወአልቦቱ ካልዕ ሕሊና ዘእንበለ ብካይ ላዕለ ኃጢአቱ።
በኃጢኣቱ ከማዘን ከማልቀስ በቀር ማዘን ማልቀስ ነው እንጂ ሌላ ግዳጅ አልነበረውም ፤ ሐተታ አዳምን የቤተ ፈት ልማድ አላገኘውም ቤተ ፈት በዚህ ጊዜ እበላ እጠጣ እለብስ አጌጥ የነበረ ቀረብኝ ብሎ ያዝናል ፤ እሱ ግን የማይገባ ሥራ ሠርቼ ፈጣሪዬን አሳዘንሁት ብሎ ነው እንጂ በገነት ሳለሁ አደርገው የነበረው ተድላ ደስታ ቀረብኝ ብሎ አይደለምና በኃጢአቱ ከማዘን ከማልቀስ በቀር በኃጢአቱ ማዘን ማልቀስ ነው እንጂ ግዳጅ አልነበረውም አለ፤
ወአእመረ እግዚአብሔር ይትለዓል ዝክሩ ንስሐሑ ወገዓሮ ብዙኃ ወምንዳቤ እንተ ረከቦ ተሣሃለ ላዕሌሁ ወምሕሮ ። 
በልብ መታስቡ በቃል መነገሩ ከፍ ከፍ ይበልና አላበጀሁም ማለቱን ብዙ መጨነቁን ጸዋትወ መከራውን አይቶ ይቅር አለው አዘነለት፤  
ወፈቀደ ያድኅኖ እምዳኅጹ በእንተ ፪ ገጻት ።
ስለ ሁለት ነገር ከፍዳው ሊያድነው ወደደ፤ 
፩ዱ በእንተ ንስሐሑ ፤  
ከሁለቱ አንዱ አላበጀሁም በማለቱ ነው፤ 
ወገዓረ ብካዩ ለኃሢሠ ሥርየት ፤
ኃጢአቱ ሊሠረይለት ኃጢአቱን ሊያሥተሰርይለት እያለቀሰ በመጨነቁ ነው።
ወረሲኦቱ ገነተ ወፍግዓሁ ወተድላሁ፤  
ገነትን በመዘንጋቱ ተድላው ደስታውን በመዘንጋቱ ነው።
ካልዕሰ በእንተ ዘተትሕተ ውእቱ ተትሕቶተ።
ወካልዕሂ ሲል ነው ሁለተኛውም እሱ ፈጽሞ ስለተዋረደ ነው ።
ወዓዲ አጥረየ ሰይጣን መዊዓ ወኃይለ ላዕለ አዳም ወቀነዮ
ዳግመኛ ሰይጣን በአዳም ላይ ኃይልን መዊዕን ገንዘብ እደረገ ።
ወኮነ ጼዋሁ ምርኮው ሆነ።
ወኵሉ ዘርዑ ምስሌሁ ፤
ልጆቹም ከሱ ጋራ እንደሱ ተገዙ።
ወተሰልጠ ሰይጣን ዲቤሆሙ ለአስግዶ በብዙኅ ግብራት። አሳታቸው ብሎ ነበርና ዳግመኛ በብዙ ነገር ለማሳት ሰይጣን ሠለጠነባቸው። 
ወመንክራት ትልዋት ፤
ቀጽሎ ቀጽሎ በሚደረግ በምትሐት ተአምራት ፤ አንድም ወመንክራት ትልዋት ይላል ። ቀጽሎ ቀጽሎ አራድፎ አራድፎ በሚመጣ መከራ ሠለጠነባቸው። ወቦ እምኔሆሙ ዘመሐረ ከመ ፍጥረት ተፈጥረት እምኀበ ርእሳ ባሕቲታ ዘእንበለ ሠራዒ ወገባሪ ። ከርሳቸው ወገን ፍጥረት ያለ ሠራዒ ያለ መጋቢ ከባሕርይዋ እንደ ተፈጠረች ያስተማረ አለ እነ ማኒ ወቦ እምኔሆሙ ዘመሐረ ከመ ፀሐይ ወወርህ ወከዋክብት እሙንቱ እለ ፈጠሩ ዓለመ፤ ሰማይ ምድርን የፈጠሩ ፀሐይ ጨረቃ ከዋክብት እንደሆኑ ያስተማራቸው አሉ ጽርዓውያን ፀሐይ ጨረቃን ሰባቱን ከዋክብት ያመልኩ ነበር ። ወቦ ዘመሐረ ከመ አምልኮ አራዊት ወእንስሳ ይእቲ ፍኖት በአማን ጥይቅት፤ አምልኮተ አራዊት አምልኮተ እንስሳ በውነት የተረዳች ሃይማኖት እንደሆነች ያስተማራቸው አሉ ።
ወባቲ ይትረከባ ፈቃዳት ።
የሚሹት ነገር በሷ እንዲገኝ ።
ወይትፌጸማ ባቲ ስእለታት ።
ልመናም በሷ እንዲገኝ ያስተማራቸው አሉ ። ሐተታ ግብጻውያን ላም ያመልኩ ነበር ባቢሎናውያንም ዘንዶ ያመልኩ ነበር፤ 
ወአርስኦሙ አግዚአብሔርሃ አምላኮሙ ።
ፈጣሪያቸው እግዚአብሔርን አስካዳቸው ።
ወቦኡ ውስተ ልጎተ ርስአት፤ ወደ ፍጹም ዝንጋኤ ገቡ ፤
ወተመንኖት ወተቀንዮት ለብዙኅ ኃጢአት ዘዘዚአሁ
ልዩ ልዩ የሚሆን ለብዙ ኃጢአትም ወደ መገዛት ወደ መናቅ ገቡ ።
እምቅትለት፤  ነፍስ ከመግደል ወገን
ወእምዝሙት ወሐሰት ወሐሜት ።
ከዝሙት ከሐሰት ከሐሜት ወገን አንዱ ብቻ ሠርቶት አይቀርምና በከፊል ተናገረው።
ወአምዖት ። 
ሰውን እግዚአብሔርን ከመበደል ወገን፤
ወትዕግልት  ከቅሚያ ወገን
ወአምልኮተ ጣዖት ዘግብረ እድ
የሰው እጅ ሥራ የሚሆን ጣዖትን ከማምለክ ወገን
ወክሂደ እግዚአብሔር ፤ 
እግዚአብሔርን ከመካድ ወገን ።
ወዘይመስሎ ለዝንቱ ።  
ነሣሣለትና ይህን ከመሰለ ወገን ለብዙ ኃጢአት ወደ መገዛት ገቡ።
ወኮኑ ስይጣናት ውኩላነ ፤
ስይጣናት ቁራኞች ሆኑ ። 
ወሥሉጣነ በአዳም ወበኵሉ ዘርዑ ውስተ አሕጉሎ
በአዳም በልጆቹም ሁሉ በቁራኝነት የሠለጠኑ ሆኑ
ከመ ጺዉዋን
ምርኮኞች እንደመሆናቸው ፤ አንድም ማራኪ በምርኮኞቹ እንዲሠለጥን ።   
ወለዘሞተ እምኔሆሙ የአሥሩ ነፍሶ ውስተ ሲኦል
ይህም ሊታወቅ ከሳቸው ወገን የሞተውን ሥጋውን በመቃብር ነፍሱን በሲኦል በገሃነም ተቈራኝተው ይኖሩ ነበር ። አሜሃ ይትፌነዋ ነፍሳት ውስተ ገሃነም እስከ ይመልአ አብያተ ሞት እንዲል ።
ወኮነ ቦሙ ዝንቱ ግብር ለዝሉፉ እስከ ተፍጸሜተ
፶፻ ወ፭፻ ዓመት እምፍጥረቱ ለአጻም። አዳም ከተፈጠረ ጀምሮ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን እስኪፈጸም ድረስ ቁራኝነት ፈጽሞ ተደረገባቸው ።   
ይቆየን
****************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
04/06/2011 ዓም

Saturday, February 9, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 4


==================
 ፪ተኛ ጉባኤ።
ወካልዑ በቁዔት ።

ሁለተኛውን በቁዔት ብለውታል በቁዔት ይባላል።
ወዳግሙ ይላል አብነት  
ወበቁዔተ ዝንቱ መጽሐፍ ንጹሕ ።
ከፈቃደ ሥጋ ንጹሕ የሚሆን የዚህ መጽሐፍ በቁዔቱ በቁዔትነቱ። 
ካዕበ እስመ ውእቱ በዘይትነበብ እምኔሁ ያጤይቅ አጥርዮ መድኃኒቱ ለአዳም ። 
በዘይትነበብ ካዕበ በቁዔት ካዕበ ያጤይቅ ካዕበ ብለህ ግጠም። እሱ ሁለተኛ በሱ በሚነገረው ነገር ሁለተኛ የአዳምን ድኅነት ማግኘቱን ሁለተኛ ያስረዳልና ስለዚህ ነው። አጥርዮ መድኃኒቱ ባለው
ግብረ መድኃኒቱ ይላል አብነት የአዳምን የድኅነቱን ሥራ ያስረዳልና ስለዚህ ነው። 
ወዘርዑ ።
የልጆቹንም ድኅነት ማግኘታቸውን ያስረዳልና ስለዚህ ነው። 
እምፄዋዌ ሰይጣን ርጉም   
ርጉም ከሚሆን ከሰይጣን  ምርኮኝነት የአዳምን ድኅነት ማግኘቱን ልጆቹም ድኅነት ማግኘታቸውን የድኅነቱን ሥራ የድኅነታቸውን ሥራ ያስረዳልና።
ወተፈድዮቶሙ ህየንተ ኅጒለት ዕረፍተ ሠናየ። ስስ ጉዳት ፈንታ በጐ ዕረፍት ማግኘታቸውን ዘከመ ተፈድዩ  በጎ ዕረፍትን እንዳገኙ ይናገራልና ስለዚህ ነው። ዕረፍተ ሠናይተ ገነተ ሠናይተ ፍኖተ ሠናይተ ግዕዘ ሠናይተ ገድለ ሠናይተ ይላል አብነት። 
ወዓርጉ እምጸናፌ ጽልመት ኀበ ብርሃነ ልዕልና የሰው ዳርቻ እንዲሉ ልዩ ከሚሆን ጨለማ ዳርቻ ልዕልና ወዳለው ብርሃን መውጣታቸውን። ዘከመ ዓርጉ እንደወጡ ይናገራልና  ስስዚህ ነው። ሐተታ  ልዩ አለው የዚህ ዓለም ጨለማ በዓይነ ሥጋ ይታያል የወዲያው ግን ለዓይነ ነፍስ እንጂ ለዓይነ ሥጋ አይታይምና ። ወፈግዑ በጣዕመ ግእዛን እምድኅረ ነበሩ በመሪር ኃዘነ ግብርናት ለዲያብሎስ መገዛት ባመጣው በጽኑ ኃዘን ከኖሩ በኋላ ጣዕመ ግዕዛንን አግኝተው ተድላ እንዳደረጉ ይናገራልና ስለዚሀ ነው ። 
ወዘኮነሰ ከመ ዲያብሎስ ኮነ ሊቀ ዓቢየ በውስተ መላእክት ።  
የሆነስ ሆነና ቀድሞ ዲያብሎስ ሊቀ መላእክት አኃዜ መንወጦላዕት እንደ ነበረ ስማኝ ልንገርህ  ያልተያያዘ ፤ አንድም ለዲያብሎስ መገዛት ባመጣው በጽኑ ኃዘን ከኖሩ በኋላ ጣዕመ ግእዛንን አግኝተው ተድላ ማድረጋቸው እንደምን ነው ትለኝ እንደሆነ የዚህስ ነገር ዲያብሎስ ቀድሞ ሊቀ መላእክት አኃዜ  መንጦላእት እንደነበረ ስማኝ ልንገርህ ።
ወሶበ ተዓደወ እመካኑ በስሕተት ወወፅአ እምትእዛዘ ፈጣሪሁ ዘውሱን ሎቱ ። 
በስሕተት ከቦታው በወጣ ጊዜ ፍጡር ነህ ቢሉት ፈጣሪ ነኝ ባለ ጊዜ ከተወስነለት ከፈጣሪው ትእዛዝ ወጣ ማለት ቀድስ ቢሉት ቀድሱኝ አለ ወድቀ ማንሻ። አንድም ፍጡር ነህ ቢሉት ፈጣሪ ቀድስ ቢሉት ቀድሱኝ ባለጊዜ ።     
ወድቀ እመንበሩ ።  
ከሹመቱ ተሻረ ከልዕልናው ተዋረደ ። 
ወወድቁ ምሰሌሁ ኵሎሙ ሠራዊቱ እለ ገብሩ ፈቃዶ
ነህ ያሉት ሁሉ ከሱ ጋራ እንደሱ ወደቁ ፤
ወወድቀ ውስተ ምድር ከመ ይግበር ባቲ በከመ ፈቀደ በትዕቢቱ ወበትዝኅርቱ ።  
በትዕቢቱ በትዝኅርቱ የወደደውን ያደርግባት ዘንድ ወደዚህ ዓለም ወደቀ ለመሐመድ ልጁ መቃብር ሊባርክለት መካ እስጥንቡል ወደቀ። ታሪክ ጌታ መላእክትን በነገድ መቶ በከተማ ዓሥር አድርጎ ፊጥሮ ተሰወራቸው ባሕርዩ ረቂቅ እንደሆነ ለማጠየቅ ካልሹኝም አልገኝም ሲል መላእከትም አእምሮ አላቸውና ተመራመሩ እምአይቴ መጸእነ ወመኑ ፈጠረነ ለሊነኑ እምኀበ ርእስነ ተፈጠርነ ወሚመ እምካልዕ ብለው ዲያብሎስን ከሁሉ አልቆት ፈጥሮት ነበርና ወደላይ ቢያይ ድምፅ አጣ ወደታች ቢያይ ሁሉ ከበታቹ ሁኖ አየ እኔ ፈጠርኋችሁ ልበላቸው ብሎ አሰበ አስቦም አልቀረ እኔ ፈጠርኋችሁ አላቸው ። መላእክትም በቦታ እንደሆነ እኛ ከበታቻችን ያሉትን  አልፈጠርናቸው በምን ምክንያት ፈጠርኋችሁ ይለናል ፈጥረህ አሳየን እንበለው ብለው አሰቡ አስበውም አልቀሩ በቦታ እንደሆነ እኛ ከበታቻችን ያሉትን አልፈጠርናቸው በምን ምክንያት ፈጠርኋችሁ ትለናልህ ፈጥረህ አሳየን አሉት ሊፈጥር እጁን ከእሳት አገባው ፈጀው ዋይ ብሎ ጮኸ ፈወሰው ። አፍአዊ አምላክ ቢሆን ነው እንጂ ውሳጣዊ አምላክማ ቢሆን ምን ስትል ነው ባላለኝም ነበር ብሎ አሰበ። ይሀን ያለበት ልቡን ተሰማው ፈጀው ዋይ ብሎ ጮኸ መላእክት ተናወጹ ይህ ስሑት ፍጥረት ፈጽሞ ሳያስታቸው ልገለጽላቸው ብሎ እሱ በማያይበት በምሥራቅ በኩል እንሰ እቤ እግዚአብሔር ለይኩን ብርሃን ብሎ የጎሑን ብርሃን ፈጠረላቸው የብርሃን ጎርፍ አፈሰለላቸው እሱንም ቀድሞ እፈጥራለሁ ብለህ እጅህን ከእሳት አገባኸው ፈጀህ ዋይ ብለህም ጮህህ ፈወስኩህ አፍአዊ ሕምላክ ቢሆን ነው እንጂ ውሳጣዊ አምላክማ ቢሆን ምን ስትል ነው ባላለኝም ነበር አልኸኝ ብሎ ሁለተኛ ፈውሶ ዛሬ ነገሥታት መኳንንት ጠላታቸውን በርጥብ ቁርበት ጠቅልለው ገደል እንዲጥሉ ባደረው ጭለማ አጐናፅፎ ከኢየሩሳሌም ሰማያዊት አውርዶ በኢዮር ካሉ መላእክት ደርቦታል እስከ ረቡዕ ከዚያ ይሰነብታል በዕለተ ሠሉስ የተፈጠሩ አዝርዕትን አትክልትን ዕፅዋትን አይቶ እንዲህ አድርጎ ፍጥረት ማከናወን ለዚህም እንጂ ገዢ አኑሮለት ይሆናል አለ ። ወደኸው እንደሆነ በዚህ ዓለም ላኑርህ አለው ለኔማ ደገኛውን ማን ነስቶኝ አለው ፤ በዕለተ ረቡዕ ፀሐይ ጨረቃ ከዋክብት ተፈጠሩ ያን አይተው መላእክት አመሰገኑ። ወአመ ተፈጥሩ ከዋክብትየ ሰብሑኒ መላእክቲየ እንዲል። አመስግነው አመስግን ቢሉት አንሰ ዕድው እምዝንቱ ሕሊና ፤ እኔ ከማመስገን ውፁእ ነኝ አላመሰግንም ይሆንላችሁስ እንደሆነ አራተኛ አድርጋችሁ አመስግኑኝ አላቸው ወዲያው አያይዞ አራት አለቆች አሉት ከሚካኤል ከገብርኤል ዘንድ ላካቸው ኢየሩሳሴም ሰማያዊት ቢሏችሁ ሦስቱ ሰማያት አይመስሏትም እኛም ከጩኸት በቀር ያገኘነው ነገር የለም ። ገዥ ነኝ የሚለውን ወግተን እጅ እናድርጋት ብሎ ላከ። ከትእይንተ ንጉሥ እንደገባ እብድ ውሻ አድርገው እብድ ውሻ አስመስለው ስደዷቸው ። መጥተው ነገሩት ሚካኤል ገብርኤል ቢሏችሁ በኔ ዘንድ ቁም ነገርን ናቸው እንደ ቀለምጺጸ እሳት እንጂ አይደሉ ብሎ ሰልፎ ተነሣ እሱ እቀብ የወጣሁ ይመስለዋል ቊልቊል ይወርዳል ። ጐየ እግዚእ ምስለ አርያሙ ሰማዩን ጠቅሎ ተመለሰ ብሎ አዝምሮ ተመለሰ። መላእከት ይህን ሰምተው ይህ ሰሑት ፍጥረት እስከ መቸ ድረሰ በፈጣሪው ሲታበይ ይኖራል ብለው ገጠሙት ድል አደረጋቸው ። ሁላለተኛ ገጠሙት ድል አደረጋቸው ። ፈቃድህ ባይሆን ነውን ብለው አመለከቱ ። ፈቃድስ ፈቃዴ ነው ድል የሚነሣበትን ግብር ታውቁ ብዬ ነው ብሎ የብርሃን ትእምርተ መስቀል ሰጣቸው እሱን ባየ ጊዜ ከዚህ በታች ወርዷል። ነው አይገባውም ያሉ አሉ  ነው ብሎስ አይገባውም ማለት አይመችም ብሎ እኛም እንደሱ ነን ያሉ አሉ  ከሱ በቀር ፈጣሪ ነኝ ያለም የለ ብሎ ነው ይገባዋል ያሉ አሉ፤ ይሆን  አይሆን ብለው የተጠራጠሩ አሉ ። ሳይመራመሩ የቀሩ አሉ፤ ነው ይገባዋል ያሉ አብረውት ወርደዋል ፤ ይሆን አይሆን ብለው የተጠራጠሩ በዚህ ዓለም ቀርተዋል ሳይመራመሩ የቀሩ በአየር ቀርተዋል ክብር ይሁናቸው ብሎ።
እፎ ፈቀደ ኀበ ፈቀደ። ከወደደ ዘንድ እንደምን ወደደ  
እስመ ሥልጣኑ እንተ ተፈጥረት ምስሌሁ ኢተዓተተት እምኔሁ ።
ፍጡር እንደሆነ የሚያውቅባት በተፈጥሮ የተሰጠችው ግዕዛኑ አልተነሳችውምና ።
ወእምዝ ተከሥተ ሎቱ ድኅረ ክብረ መንበሩ እንተ ሀለወ ባቲ አምጣና ወክብራ ።  አምጣና ወከብራ ለክብረ መንበሩ እንተ ሀለወ ባቲ ከሹመቱ ከተሻረ ከማዕርጉ ከልዕልናው ከተዋረደ በኋላ ቀድሞ የነበረባት የማዕርጉ ደግነት ተገለጸችለት ።
ወተዘከረ ፍሥሐ ወኃሤተ እንተ ኮነ ይትፌሣሕ ባቲ ምስለ መላእክት ወሊቃናት ወሥልጣናት ሰማያውያን።
ስመ ነገድ ከመላእክት ጋራ ያደርገው የነበረውን ተድላ ደስታውን አሰበ። 
በብዝኅ ቃላቲሆሙ ወኅብረተ ዜማሆሙ  
በነገራቸው ብዛት በምስጋናቸው አንድነት ሕተታ የነገር ብዛት ቅዱስ ውዱስ ስቡሕ ዕኩት ሃሌ ሉያ ማለት ነው ይህ ሁሉ በምሥጢር አንድ ነው።
ወዘይፈደፍድሰ እምኔሃ ፍሥሐ ወኃሤት ልዕልተ ወምዕዝተ እንተ ታቄርብ ኀበ እግዚአብሔር ይትለዓል ዝክሩ ። 
በልብ መታሰቡ በቃል መነገሩ ከፍ ከፍ ይበልና ይልቁንም ወደ እግዚአብሔር የምታደርስ ተመስጦ ነበረችው ያቺን አሰበ ። ሐተታ ተቀብቷል ቢሉ የተመቸ አልተቀባም ቢሉ ቢጸና ።
ወዘረከቦሂ ደኅረ ውእቱ እምድቀታት።
ከዚህ በኋላ ከድቀታት ወገን ያገኘውን አስቦ ሐተታ ድቀታት ብሎ አበዛ ከኢየሩሳሌም ሰማያዊት ወደ ኢዮር ከኢዮር ወደዚህ ዓለም ከዚህም በታች አውርዶታልና  
ወጽልመተ እንተ ገልበበቶ ወበዓፅፋ ላዕሌሁ
ከጸናችበት እሱም ከጸናባት ከድንቁርና ወገን ያገኘውን አስቦ ድቀታት ላለው ዋዌ አንድም ለላይኛው ልዕልተ ምዕዝተ ላለው ዋዌ የጸናችበትን የጸናባትን ድንቁርናውን አሰቦ ።
ወህየንተ ብርሃን ዘመላእክተ ትፍሥሕት በአርአያ ሰይጣናዊት ርኲስት። ደስ ብሏቸው የሚኖሩ መላእክት ስላገኙት ብርሃን ፈንታ በምታጸይፍ ባላጋራነት መልክ እንዳለ አውቆ።
ወሐለየ በትዕቢቱ ወበትዝኀርቱ ወይቤ እስመ ይፈቅድ እግዚአብሔር አግብኦትየ ከመ ያንብረኒ ኀበ ዘቀዳሚ ንብረትየ እንተ ተዓተተት እምኔየ ወእምእሊአየ በትዕቢቱ በትኅዝርቱ አስቦ ወይም እንጂ ወይም እኮን ከኔ ከወገኖቼም ከተለየች ወደ ቀደመች ማዕርጌ ሊመልሰኝ ይወድ ይሆናል አለ።
ወአእመረ እግዚአብሔር ይትለዓል ዝክሩ ሕሊናሁ እኩየ ወትዕቢቶ፤ 
በልብ መታሰቡ በቃል መነገሩ ከፍ ከፍ ይበልና ክፉ አሳቡን ትዕቢቱን ዐውቆ  
ወእፎ ኃደገ ምግባራተ ሠናያተ ።
በጐምግባራትን እንደተወ አውቆ
እንተ ይእቲ ትሕትና ወየዋሃት ወድኂን እምኃጢአት።
ምግባራት ሠናያት የተባሉም ትሕትና ወየዋሐት ድኂን እምኃጢአት ናቸው። ሐተታ ትሕትና ባለፈው መጸጸት ። የዋሃት ከሚመጣው መጠበቅ ። ድኂን ለሁለቱም ነው።   
ዘለፎ እግዚአብሔር በፈጢረ ብእሲ ዝልፈት ክሠተ
አዳምን በመፍጠሩ መዝለፍን ዘለፈው ማሳፈርን አሳፈረው ማስወተትን አስወተተው። 
በአሠንዮ ፍጥረቱ ለአዳም።
አዳምን አከናውኖ በመፍጠሩ እንደ ብርጭቆ የሚያንጸበርቅ እንደ ጽጌያት የሚያሸበርቅ አድርጎ በመፍጠሩ ይህስ ቁም ነገር አይደለም ዐዋቂ እድርጎ በመፍጠሩ።
እስመ ውእቱ ለሐኮ እም፬ቱ ጠባይዕ።
ከአራቱ ባሕርያት ፈጥሮታልና። 
ወይእቲ እሳት ወነፋስ ማይ ወመሬት።
አራቱ ባሕርያት የተባሉ እሳት ነፋስ ማይ መሬት ናቸው።
ሥጋ ዘፍጹም ቆሙ።
ቁመቱ ድልድል የሚሆን አካሉ እንደ ድንከ አያጥር እንደ ረዓይት አይረዝም። 
ዘቦቱ ፪ቱ ኃይል።    
ሁለት ግብር ሁለት ባሕርይ ያለው አድርጎ በመፍጠሩ።
ኃይለ ዘርዕ  የዘር ግብር የዘር ባሕርይ።
ወኃይለ አንስሳ።    
የደመ ነፍስ ግብር የደመ ነፍስ ባሕርይ።
ወኃይለ በቊላትሰ በሁከተ ነፍስ ይነውኅ ወይማስን
የዘር ግብር የዘር ባሕርይ ነፋስ እየወዘወዘው ያድጋል ነፋስ እየወዘወዘው ይደርቃል ፈርሶ በስብሶ ይቀራል።    
በከመ ዕውቅ ዝንቱ ውስተ ኩሉ አጽናፈ ምድር
ደህ በአራቱ ማዕዘን ታውቆ እንዳለ።
ወኃይልሰ እንሰሳዊት ህውክት ይእቲ በሥምረት
የእንሰሳ ግብር የእንስሳ ባሕርይ ልብላ ልብላ በማለት ፈቃድ የምትነሣሣ ናት።  
ወይእቲ ባ እምነ አእአምሮ።
ወለይእቲ  ሲል ነው ለሷም ከዕውቀት ወገን አላት ወከፈላ ምክረ እምጥበብ ለሰገኖ እንዲል።
ዛ ይእቲ እንስሳዊት  ያቺውም እንስሳዊት ናት
ወውስቴታ ይትረከብ ነጽሮ።  
በርሷም ማየት ይገኛል ፤ ሐተታ ማየት በሁሉ አለ ይልቁንም ጉጉት የባሕር ድመት በሌሊት ያያሉ ።
ወሰሚዕ መስማት ይገኛል ። ሰሚዕ በሁሉ አለ ይልቁንም በቅሎ ንቁሕ ነው።
ወጣዕም ጣዕም ይገኛል ፤ ጣዕም በሁሉ አለ ይልቁንም ፈረስ እህልና ዐፈር ቢሰጡት  የሰጡት እንደሆነ ዐፈሩን እየተወ እህሉን ይበላል።  
ወአጼንዎ።     
አጼንዎ ይገኛል ። ሐተታ አጼንዎ በሁሉ አለ ይልቁንም የሜዳ አህያ  ወይቀውም ሐለስትዮ ማዕከለ አድባር ወያበቁዕ እንፎ እንዲል፤ ከተራራ ላይ ወጥቶ አፍንጫውን ከፈት ከፈት ያደረገ እንደሆነ የሣር የውኃ ጣዕም ይመጣለታል የሦስት ቀን መንገድ ገሥግሦ ሄዶ ሣሩን በልቶ ውኃውን ጠጥቶ ዕለቱን ተመልሶ ከቦታው ገብቶ ያድራል።
ወገሢሥ።
ገሢሥ ይገኛል ፤ ገሢሥ በሁሉ አለ ይልቁንም ዝንጀሮ በትር ቈርጦ እስከ መማታት ይደርሳል። የላይ ቤት አማርኛ በችሐበችሆ ይላል።
ወዓዲ ተንሥኦ ወነቢር ።
አፍ ቁጭ አፍ ቁጭ ማለት ይገኛል ቡኸር አታርፍም ። አንድም አናበህ ተንሥአ ነቢር መቀመጥ ያለበት መነሣት ይገኛል ። ውሻ ድመት በኋላ እግራቸው ይቀመጣሉ በፊት እግራቸው ይቆማሉ ።
አንሳሕሖ።
አንሳሕስሖ ይገኛል። አንሳሕሰሖ በሁሉ አለ ይልቁንም ጥርኝ አታርፍም።  
ወኅድዓት።    
ኅድዓት ይገኛል  ኅድዓት በሁሉ አለ ይልቁንም አንበሳ ። በሬም ያግዛል።
ወፍትወት
ፍትወት ይገኛል ፍትወት በሁሉ አለ ይልቁንም ሰገኖ። ሰገኖ ታበዝኅ ፍትወተ ወእምከመ ኢፀንሰት ኢትበልዕ ሣዕረ እንዲል። 
ወወሊድ
ወሊድ ይገኛል ወሊድ በሁሉ አለ ይልቁንም ጎማ ያለሽል አታድርም ።
ወመዓት
መዓት ይገኛል መዓት በሁሉ አለ ይልቁንም ግሥላ ታንቆ ይሙታባሽ ያሏት እንደሆነ ታንቃ ትሞታለችና ።   
ወሣል።   ሣህል ይገኛል ። ሣህል በሁሉ አለ ይልቁንም ዝሆን።  ዝሆን ሆይ ዝሆን ሆይ ያሉት እንደሆነ መንገድ ይመራል።
ወሕማም።       
ሕማም ይገኛል ። ሕማም በሁሉ አለ ይልቁንም ነብር ዓይን ሕመም ይጸናበታል።   
ወተበቅሎ ።   
ተበቅሎ በሁሉ አለ ይልቁንም ግመል አጥብቆ የመታትን እስከ ስድስት እስከ ሰባት ዓመት ድረስ አትረሳውም ስፍራ ሲመቻት ገደል ገፍታ ትጥለዋለች ባጥ ብላ ትረግጠዋለች።   
ተፈስሖ።
ተፈስሖ በሁሉ አለ ይልቁንም ቀበሮ። ዱሮ ዘመን ቀበሮ ጣዝማ ያገኘ እንደሆነ ሲዘል በታው ይጠፋው ነበር ዛሬ ግን እጁን ጭኖ የሚዘል ሁኑዋል የጊዜውን ክፋት መናገር ነው ።   
ወኃዘን።
ኃዘን በሁሉ አለ ይልቁንም ዖፈ መንጢጥ ባሏ የሞተ እንደሆነ ወበፅፍራ
ትሴጽር ልሳና ይላል ፊቷን ጸፍታ አንደበቷን ሰንጥታ ትኖራለች፤ ሌላ መጥቶ ልድረስብሽ ያላት እንደሆነ ያን ታሳየዋለች ቢመለስ ይመለሳል የተጋፋት እንደሆነ ከወገኖቹዋ ትጠጋለች ያድኑዋታል።
ነዊም። መኝታ በሁሉ አለ ይልቁንም አዞ የያዘውን ከመጣል ይደርሳል።
ወነቂሕ። መንቃት በሁሉ አለ ይልቁንም ቆቅ። ያን ቆቅ ያሉ እንደሆነ ይህን በቅሎ።
ሕይወት።  ሕይወት በሁሉ አለ ይልቁንም ዖፈ ፊንክስ የሚባል ዖፍ አለ በ፭ በ፭ት
መቶ ዘመን ይታደሳልና ። ይህስ የታወቀ ነው ብሎ እንደፎገራ አሞራ ጥርሱ የተላለፈ እንደሆነ ጭሮ መብላት አይሆንለትም ከዕንጨት ከድንጋይም የመታው እንደሆነ ይተካከልለታል ጭሮ ይበላል ።
ወመዊት ። ሞት በሁሉ አለ ይልቁንም አይጥና ድንቢጥ ጭላት የበልጉ ለመኸር የመኸሩ ለበልግ አይገኙም።
ወአምሳለ ዝንቱ በከመ ይትረከብ ዝ በውስተ እንስሳ ነሳሳለትና ይህን የመሰለ ሁሉ በእንስሳት ባሕርይ እንዳለ በሰውም በእንስሳ ባሕርዩ ይህ ሁሉ አለ።
ወዓዲ አክበሮ በንፍሐት ዘይእቲ ማኅተመ ሕይወት መንፈሳዊት እንተ ባቲ አክበሮ እምኩሉ ፍጥረት ዘታኅተ ሰማይ ።  
ከአራቱ ባሕርያት አዋሕዶ ፈጠረው ብሎ ነበርና ዳግመኛ ባራቱ ማዕዘን ካለ ፍጥረት ለይቶ ባከበረበት የሥጋ ሕይወት የደመ ነፍስ ሕይወት በምትሆን በነባቢት ነፍስ አከበረው ።
ወትትዓወቅ በኃይለ ንባብ
ምሥጢር በመናገር ትታወቃለች ።
ዛ ይእቲ አርአያ ገጹ ለእግዚአብሔር ወአምሳሊሁ ይኸውም የእግዚአብሔር መታወቂያው ናት ምሳሌውም ናት። 
በከመ ይቤ መጽሐፍ። 
መጽሐፍ ንግበር ሰብአ በአርዓያነ ወበአምሳሊነ እንዳለ
ወይእቲ ዘኢትትለከፍ   
የማትያዝ የማትዳስስ ናት።     
ወዘኢግብርት። ግብር እምግብር ያልተፈጠረች ናት ። አንድም አጥብቅ  ያያገብሯት ናት።
ሀላዊት። ነዋሪት ናት።
ወዘኢመዋቲት የማትሞት ናት።
ኰናኒተ ሥጋ ወኃይሉ።  
ሥጋን ደመ ነፍስን የምትገዛ ናት አንድም ሥጋን የምትገዛ ናት ወኃይሉ ጠበቃው ናት።   
በእንተ ዘኮነት አሐተ ውሰተ ኩሉ ።
በፈቃድ አንድ ስለሆነች። 
ወባቲ ይትረከብ ጥበብ ዘየሐስብ ልብ ወየኃሪ።
ልብ የሚሻው ጥበብ በሷ ይገኛል።  
ፀሐይ መጸው ክረምት ሐጋይ ማወቅ በሷ ይገኛል ይህንስ እንስሳትም ያውቁታል ብሎ ዓዝማነ መንግሥተ ሰማያትን ማወቅ ይገኛል።
ወመካናት ። ቆላ ደጋን ማወቅ በሷ ይገኛል  ይህንስ እንስሳትም ያውቁታል ብሎ ቆላ
ገሀነም ደጋ መንግሥተ ሰማያት ማወቅን በሷ ይገኛል።
ወኩላ ምግባራት እንተ ትከውን በዘይእቲ ላዕሌሁ የሚሠራው ሥራ ሁሉ እሱን ተዋሕዳ ባለች በሷ ነው  አንድም እሷን ተዋሕዶ ባለ በሥጋ የሚሠራ ሥራ ሁሉ ባቲ ይትረከብ።
በሥልጣን ባሕታዊት።    በዕውቀት ልዩ ናት።
ሥዕልት ዘእንበለ ገቢር።
ግብር እምግብር ሳይሆን የተፈጠረች ናት።
ወገብረ ላቲ ሥልጣነ በውስቴታ ትግበር በከመ ኃርየት እንዘ አልቦ ዘይኴንና ወዘይኄይላ የሚገዛት የሚያዛት ሳይኖር የወደደችውን እንደወደደች ታደርግ ዘንድ አእምሮ ጠባይዕን ሳለባት ።
ከመ ይኩን ሠናያቲሃ ወአከያቲሃ በሥምረተ ሕሊናሃ። 
በጎነቷም ክፋቷም በፈቃዷ ይሆን ዘንድ ።
በአምሳለ መላእክት።

ሠናያቲሃ በአምሳለ መላእከት በሚካኤል በገብርኤል አምሳል።
እከያቲሃ በአምሳለ መላአክት ብለህ ግጠም።
በአጋንንት አምሳል ይሆን ዘንድ ።
ወተፈጸመ ፍጥረቱ ለአዳም በዝንቱ ግብር ። የአዳም ተፈጥሮ በዚህ ተፈጸመ ።
ዘቦ ውስቴቱ ፫ቱ ኃይል ።  
ሦሰት ግብር ሦስት ባሕርይ ባለው ።
ኃይለ ዘርእ። የዘር ግብር የዘር ባሕርይ ባለው ።
ወኃይለ እንስሳ ።  የደመ ነፍስ ግብር የደመ ባሕርይ ባለው።
ወኃይለ ንባብ። የነባቢተ ነፍሰ ግብር ባለው።
 ይቆየን
****************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
02/06/2011 ዓም