Saturday, February 9, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 4


==================
 ፪ተኛ ጉባኤ።
ወካልዑ በቁዔት ።

ሁለተኛውን በቁዔት ብለውታል በቁዔት ይባላል።
ወዳግሙ ይላል አብነት  
ወበቁዔተ ዝንቱ መጽሐፍ ንጹሕ ።
ከፈቃደ ሥጋ ንጹሕ የሚሆን የዚህ መጽሐፍ በቁዔቱ በቁዔትነቱ። 
ካዕበ እስመ ውእቱ በዘይትነበብ እምኔሁ ያጤይቅ አጥርዮ መድኃኒቱ ለአዳም ። 
በዘይትነበብ ካዕበ በቁዔት ካዕበ ያጤይቅ ካዕበ ብለህ ግጠም። እሱ ሁለተኛ በሱ በሚነገረው ነገር ሁለተኛ የአዳምን ድኅነት ማግኘቱን ሁለተኛ ያስረዳልና ስለዚህ ነው። አጥርዮ መድኃኒቱ ባለው
ግብረ መድኃኒቱ ይላል አብነት የአዳምን የድኅነቱን ሥራ ያስረዳልና ስለዚህ ነው። 
ወዘርዑ ።
የልጆቹንም ድኅነት ማግኘታቸውን ያስረዳልና ስለዚህ ነው። 
እምፄዋዌ ሰይጣን ርጉም   
ርጉም ከሚሆን ከሰይጣን  ምርኮኝነት የአዳምን ድኅነት ማግኘቱን ልጆቹም ድኅነት ማግኘታቸውን የድኅነቱን ሥራ የድኅነታቸውን ሥራ ያስረዳልና።
ወተፈድዮቶሙ ህየንተ ኅጒለት ዕረፍተ ሠናየ። ስስ ጉዳት ፈንታ በጐ ዕረፍት ማግኘታቸውን ዘከመ ተፈድዩ  በጎ ዕረፍትን እንዳገኙ ይናገራልና ስለዚህ ነው። ዕረፍተ ሠናይተ ገነተ ሠናይተ ፍኖተ ሠናይተ ግዕዘ ሠናይተ ገድለ ሠናይተ ይላል አብነት። 
ወዓርጉ እምጸናፌ ጽልመት ኀበ ብርሃነ ልዕልና የሰው ዳርቻ እንዲሉ ልዩ ከሚሆን ጨለማ ዳርቻ ልዕልና ወዳለው ብርሃን መውጣታቸውን። ዘከመ ዓርጉ እንደወጡ ይናገራልና  ስስዚህ ነው። ሐተታ  ልዩ አለው የዚህ ዓለም ጨለማ በዓይነ ሥጋ ይታያል የወዲያው ግን ለዓይነ ነፍስ እንጂ ለዓይነ ሥጋ አይታይምና ። ወፈግዑ በጣዕመ ግእዛን እምድኅረ ነበሩ በመሪር ኃዘነ ግብርናት ለዲያብሎስ መገዛት ባመጣው በጽኑ ኃዘን ከኖሩ በኋላ ጣዕመ ግዕዛንን አግኝተው ተድላ እንዳደረጉ ይናገራልና ስለዚሀ ነው ። 
ወዘኮነሰ ከመ ዲያብሎስ ኮነ ሊቀ ዓቢየ በውስተ መላእክት ።  
የሆነስ ሆነና ቀድሞ ዲያብሎስ ሊቀ መላእክት አኃዜ መንወጦላዕት እንደ ነበረ ስማኝ ልንገርህ  ያልተያያዘ ፤ አንድም ለዲያብሎስ መገዛት ባመጣው በጽኑ ኃዘን ከኖሩ በኋላ ጣዕመ ግእዛንን አግኝተው ተድላ ማድረጋቸው እንደምን ነው ትለኝ እንደሆነ የዚህስ ነገር ዲያብሎስ ቀድሞ ሊቀ መላእክት አኃዜ  መንጦላእት እንደነበረ ስማኝ ልንገርህ ።
ወሶበ ተዓደወ እመካኑ በስሕተት ወወፅአ እምትእዛዘ ፈጣሪሁ ዘውሱን ሎቱ ። 
በስሕተት ከቦታው በወጣ ጊዜ ፍጡር ነህ ቢሉት ፈጣሪ ነኝ ባለ ጊዜ ከተወስነለት ከፈጣሪው ትእዛዝ ወጣ ማለት ቀድስ ቢሉት ቀድሱኝ አለ ወድቀ ማንሻ። አንድም ፍጡር ነህ ቢሉት ፈጣሪ ቀድስ ቢሉት ቀድሱኝ ባለጊዜ ።     
ወድቀ እመንበሩ ።  
ከሹመቱ ተሻረ ከልዕልናው ተዋረደ ። 
ወወድቁ ምሰሌሁ ኵሎሙ ሠራዊቱ እለ ገብሩ ፈቃዶ
ነህ ያሉት ሁሉ ከሱ ጋራ እንደሱ ወደቁ ፤
ወወድቀ ውስተ ምድር ከመ ይግበር ባቲ በከመ ፈቀደ በትዕቢቱ ወበትዝኅርቱ ።  
በትዕቢቱ በትዝኅርቱ የወደደውን ያደርግባት ዘንድ ወደዚህ ዓለም ወደቀ ለመሐመድ ልጁ መቃብር ሊባርክለት መካ እስጥንቡል ወደቀ። ታሪክ ጌታ መላእክትን በነገድ መቶ በከተማ ዓሥር አድርጎ ፊጥሮ ተሰወራቸው ባሕርዩ ረቂቅ እንደሆነ ለማጠየቅ ካልሹኝም አልገኝም ሲል መላእከትም አእምሮ አላቸውና ተመራመሩ እምአይቴ መጸእነ ወመኑ ፈጠረነ ለሊነኑ እምኀበ ርእስነ ተፈጠርነ ወሚመ እምካልዕ ብለው ዲያብሎስን ከሁሉ አልቆት ፈጥሮት ነበርና ወደላይ ቢያይ ድምፅ አጣ ወደታች ቢያይ ሁሉ ከበታቹ ሁኖ አየ እኔ ፈጠርኋችሁ ልበላቸው ብሎ አሰበ አስቦም አልቀረ እኔ ፈጠርኋችሁ አላቸው ። መላእክትም በቦታ እንደሆነ እኛ ከበታቻችን ያሉትን  አልፈጠርናቸው በምን ምክንያት ፈጠርኋችሁ ይለናል ፈጥረህ አሳየን እንበለው ብለው አሰቡ አስበውም አልቀሩ በቦታ እንደሆነ እኛ ከበታቻችን ያሉትን አልፈጠርናቸው በምን ምክንያት ፈጠርኋችሁ ትለናልህ ፈጥረህ አሳየን አሉት ሊፈጥር እጁን ከእሳት አገባው ፈጀው ዋይ ብሎ ጮኸ ፈወሰው ። አፍአዊ አምላክ ቢሆን ነው እንጂ ውሳጣዊ አምላክማ ቢሆን ምን ስትል ነው ባላለኝም ነበር ብሎ አሰበ። ይሀን ያለበት ልቡን ተሰማው ፈጀው ዋይ ብሎ ጮኸ መላእክት ተናወጹ ይህ ስሑት ፍጥረት ፈጽሞ ሳያስታቸው ልገለጽላቸው ብሎ እሱ በማያይበት በምሥራቅ በኩል እንሰ እቤ እግዚአብሔር ለይኩን ብርሃን ብሎ የጎሑን ብርሃን ፈጠረላቸው የብርሃን ጎርፍ አፈሰለላቸው እሱንም ቀድሞ እፈጥራለሁ ብለህ እጅህን ከእሳት አገባኸው ፈጀህ ዋይ ብለህም ጮህህ ፈወስኩህ አፍአዊ ሕምላክ ቢሆን ነው እንጂ ውሳጣዊ አምላክማ ቢሆን ምን ስትል ነው ባላለኝም ነበር አልኸኝ ብሎ ሁለተኛ ፈውሶ ዛሬ ነገሥታት መኳንንት ጠላታቸውን በርጥብ ቁርበት ጠቅልለው ገደል እንዲጥሉ ባደረው ጭለማ አጐናፅፎ ከኢየሩሳሌም ሰማያዊት አውርዶ በኢዮር ካሉ መላእክት ደርቦታል እስከ ረቡዕ ከዚያ ይሰነብታል በዕለተ ሠሉስ የተፈጠሩ አዝርዕትን አትክልትን ዕፅዋትን አይቶ እንዲህ አድርጎ ፍጥረት ማከናወን ለዚህም እንጂ ገዢ አኑሮለት ይሆናል አለ ። ወደኸው እንደሆነ በዚህ ዓለም ላኑርህ አለው ለኔማ ደገኛውን ማን ነስቶኝ አለው ፤ በዕለተ ረቡዕ ፀሐይ ጨረቃ ከዋክብት ተፈጠሩ ያን አይተው መላእክት አመሰገኑ። ወአመ ተፈጥሩ ከዋክብትየ ሰብሑኒ መላእክቲየ እንዲል። አመስግነው አመስግን ቢሉት አንሰ ዕድው እምዝንቱ ሕሊና ፤ እኔ ከማመስገን ውፁእ ነኝ አላመሰግንም ይሆንላችሁስ እንደሆነ አራተኛ አድርጋችሁ አመስግኑኝ አላቸው ወዲያው አያይዞ አራት አለቆች አሉት ከሚካኤል ከገብርኤል ዘንድ ላካቸው ኢየሩሳሴም ሰማያዊት ቢሏችሁ ሦስቱ ሰማያት አይመስሏትም እኛም ከጩኸት በቀር ያገኘነው ነገር የለም ። ገዥ ነኝ የሚለውን ወግተን እጅ እናድርጋት ብሎ ላከ። ከትእይንተ ንጉሥ እንደገባ እብድ ውሻ አድርገው እብድ ውሻ አስመስለው ስደዷቸው ። መጥተው ነገሩት ሚካኤል ገብርኤል ቢሏችሁ በኔ ዘንድ ቁም ነገርን ናቸው እንደ ቀለምጺጸ እሳት እንጂ አይደሉ ብሎ ሰልፎ ተነሣ እሱ እቀብ የወጣሁ ይመስለዋል ቊልቊል ይወርዳል ። ጐየ እግዚእ ምስለ አርያሙ ሰማዩን ጠቅሎ ተመለሰ ብሎ አዝምሮ ተመለሰ። መላእከት ይህን ሰምተው ይህ ሰሑት ፍጥረት እስከ መቸ ድረሰ በፈጣሪው ሲታበይ ይኖራል ብለው ገጠሙት ድል አደረጋቸው ። ሁላለተኛ ገጠሙት ድል አደረጋቸው ። ፈቃድህ ባይሆን ነውን ብለው አመለከቱ ። ፈቃድስ ፈቃዴ ነው ድል የሚነሣበትን ግብር ታውቁ ብዬ ነው ብሎ የብርሃን ትእምርተ መስቀል ሰጣቸው እሱን ባየ ጊዜ ከዚህ በታች ወርዷል። ነው አይገባውም ያሉ አሉ  ነው ብሎስ አይገባውም ማለት አይመችም ብሎ እኛም እንደሱ ነን ያሉ አሉ  ከሱ በቀር ፈጣሪ ነኝ ያለም የለ ብሎ ነው ይገባዋል ያሉ አሉ፤ ይሆን  አይሆን ብለው የተጠራጠሩ አሉ ። ሳይመራመሩ የቀሩ አሉ፤ ነው ይገባዋል ያሉ አብረውት ወርደዋል ፤ ይሆን አይሆን ብለው የተጠራጠሩ በዚህ ዓለም ቀርተዋል ሳይመራመሩ የቀሩ በአየር ቀርተዋል ክብር ይሁናቸው ብሎ።
እፎ ፈቀደ ኀበ ፈቀደ። ከወደደ ዘንድ እንደምን ወደደ  
እስመ ሥልጣኑ እንተ ተፈጥረት ምስሌሁ ኢተዓተተት እምኔሁ ።
ፍጡር እንደሆነ የሚያውቅባት በተፈጥሮ የተሰጠችው ግዕዛኑ አልተነሳችውምና ።
ወእምዝ ተከሥተ ሎቱ ድኅረ ክብረ መንበሩ እንተ ሀለወ ባቲ አምጣና ወክብራ ።  አምጣና ወከብራ ለክብረ መንበሩ እንተ ሀለወ ባቲ ከሹመቱ ከተሻረ ከማዕርጉ ከልዕልናው ከተዋረደ በኋላ ቀድሞ የነበረባት የማዕርጉ ደግነት ተገለጸችለት ።
ወተዘከረ ፍሥሐ ወኃሤተ እንተ ኮነ ይትፌሣሕ ባቲ ምስለ መላእክት ወሊቃናት ወሥልጣናት ሰማያውያን።
ስመ ነገድ ከመላእክት ጋራ ያደርገው የነበረውን ተድላ ደስታውን አሰበ። 
በብዝኅ ቃላቲሆሙ ወኅብረተ ዜማሆሙ  
በነገራቸው ብዛት በምስጋናቸው አንድነት ሕተታ የነገር ብዛት ቅዱስ ውዱስ ስቡሕ ዕኩት ሃሌ ሉያ ማለት ነው ይህ ሁሉ በምሥጢር አንድ ነው።
ወዘይፈደፍድሰ እምኔሃ ፍሥሐ ወኃሤት ልዕልተ ወምዕዝተ እንተ ታቄርብ ኀበ እግዚአብሔር ይትለዓል ዝክሩ ። 
በልብ መታሰቡ በቃል መነገሩ ከፍ ከፍ ይበልና ይልቁንም ወደ እግዚአብሔር የምታደርስ ተመስጦ ነበረችው ያቺን አሰበ ። ሐተታ ተቀብቷል ቢሉ የተመቸ አልተቀባም ቢሉ ቢጸና ።
ወዘረከቦሂ ደኅረ ውእቱ እምድቀታት።
ከዚህ በኋላ ከድቀታት ወገን ያገኘውን አስቦ ሐተታ ድቀታት ብሎ አበዛ ከኢየሩሳሌም ሰማያዊት ወደ ኢዮር ከኢዮር ወደዚህ ዓለም ከዚህም በታች አውርዶታልና  
ወጽልመተ እንተ ገልበበቶ ወበዓፅፋ ላዕሌሁ
ከጸናችበት እሱም ከጸናባት ከድንቁርና ወገን ያገኘውን አስቦ ድቀታት ላለው ዋዌ አንድም ለላይኛው ልዕልተ ምዕዝተ ላለው ዋዌ የጸናችበትን የጸናባትን ድንቁርናውን አሰቦ ።
ወህየንተ ብርሃን ዘመላእክተ ትፍሥሕት በአርአያ ሰይጣናዊት ርኲስት። ደስ ብሏቸው የሚኖሩ መላእክት ስላገኙት ብርሃን ፈንታ በምታጸይፍ ባላጋራነት መልክ እንዳለ አውቆ።
ወሐለየ በትዕቢቱ ወበትዝኀርቱ ወይቤ እስመ ይፈቅድ እግዚአብሔር አግብኦትየ ከመ ያንብረኒ ኀበ ዘቀዳሚ ንብረትየ እንተ ተዓተተት እምኔየ ወእምእሊአየ በትዕቢቱ በትኅዝርቱ አስቦ ወይም እንጂ ወይም እኮን ከኔ ከወገኖቼም ከተለየች ወደ ቀደመች ማዕርጌ ሊመልሰኝ ይወድ ይሆናል አለ።
ወአእመረ እግዚአብሔር ይትለዓል ዝክሩ ሕሊናሁ እኩየ ወትዕቢቶ፤ 
በልብ መታሰቡ በቃል መነገሩ ከፍ ከፍ ይበልና ክፉ አሳቡን ትዕቢቱን ዐውቆ  
ወእፎ ኃደገ ምግባራተ ሠናያተ ።
በጐምግባራትን እንደተወ አውቆ
እንተ ይእቲ ትሕትና ወየዋሃት ወድኂን እምኃጢአት።
ምግባራት ሠናያት የተባሉም ትሕትና ወየዋሐት ድኂን እምኃጢአት ናቸው። ሐተታ ትሕትና ባለፈው መጸጸት ። የዋሃት ከሚመጣው መጠበቅ ። ድኂን ለሁለቱም ነው።   
ዘለፎ እግዚአብሔር በፈጢረ ብእሲ ዝልፈት ክሠተ
አዳምን በመፍጠሩ መዝለፍን ዘለፈው ማሳፈርን አሳፈረው ማስወተትን አስወተተው። 
በአሠንዮ ፍጥረቱ ለአዳም።
አዳምን አከናውኖ በመፍጠሩ እንደ ብርጭቆ የሚያንጸበርቅ እንደ ጽጌያት የሚያሸበርቅ አድርጎ በመፍጠሩ ይህስ ቁም ነገር አይደለም ዐዋቂ እድርጎ በመፍጠሩ።
እስመ ውእቱ ለሐኮ እም፬ቱ ጠባይዕ።
ከአራቱ ባሕርያት ፈጥሮታልና። 
ወይእቲ እሳት ወነፋስ ማይ ወመሬት።
አራቱ ባሕርያት የተባሉ እሳት ነፋስ ማይ መሬት ናቸው።
ሥጋ ዘፍጹም ቆሙ።
ቁመቱ ድልድል የሚሆን አካሉ እንደ ድንከ አያጥር እንደ ረዓይት አይረዝም። 
ዘቦቱ ፪ቱ ኃይል።    
ሁለት ግብር ሁለት ባሕርይ ያለው አድርጎ በመፍጠሩ።
ኃይለ ዘርዕ  የዘር ግብር የዘር ባሕርይ።
ወኃይለ አንስሳ።    
የደመ ነፍስ ግብር የደመ ነፍስ ባሕርይ።
ወኃይለ በቊላትሰ በሁከተ ነፍስ ይነውኅ ወይማስን
የዘር ግብር የዘር ባሕርይ ነፋስ እየወዘወዘው ያድጋል ነፋስ እየወዘወዘው ይደርቃል ፈርሶ በስብሶ ይቀራል።    
በከመ ዕውቅ ዝንቱ ውስተ ኩሉ አጽናፈ ምድር
ደህ በአራቱ ማዕዘን ታውቆ እንዳለ።
ወኃይልሰ እንሰሳዊት ህውክት ይእቲ በሥምረት
የእንሰሳ ግብር የእንስሳ ባሕርይ ልብላ ልብላ በማለት ፈቃድ የምትነሣሣ ናት።  
ወይእቲ ባ እምነ አእአምሮ።
ወለይእቲ  ሲል ነው ለሷም ከዕውቀት ወገን አላት ወከፈላ ምክረ እምጥበብ ለሰገኖ እንዲል።
ዛ ይእቲ እንስሳዊት  ያቺውም እንስሳዊት ናት
ወውስቴታ ይትረከብ ነጽሮ።  
በርሷም ማየት ይገኛል ፤ ሐተታ ማየት በሁሉ አለ ይልቁንም ጉጉት የባሕር ድመት በሌሊት ያያሉ ።
ወሰሚዕ መስማት ይገኛል ። ሰሚዕ በሁሉ አለ ይልቁንም በቅሎ ንቁሕ ነው።
ወጣዕም ጣዕም ይገኛል ፤ ጣዕም በሁሉ አለ ይልቁንም ፈረስ እህልና ዐፈር ቢሰጡት  የሰጡት እንደሆነ ዐፈሩን እየተወ እህሉን ይበላል።  
ወአጼንዎ።     
አጼንዎ ይገኛል ። ሐተታ አጼንዎ በሁሉ አለ ይልቁንም የሜዳ አህያ  ወይቀውም ሐለስትዮ ማዕከለ አድባር ወያበቁዕ እንፎ እንዲል፤ ከተራራ ላይ ወጥቶ አፍንጫውን ከፈት ከፈት ያደረገ እንደሆነ የሣር የውኃ ጣዕም ይመጣለታል የሦስት ቀን መንገድ ገሥግሦ ሄዶ ሣሩን በልቶ ውኃውን ጠጥቶ ዕለቱን ተመልሶ ከቦታው ገብቶ ያድራል።
ወገሢሥ።
ገሢሥ ይገኛል ፤ ገሢሥ በሁሉ አለ ይልቁንም ዝንጀሮ በትር ቈርጦ እስከ መማታት ይደርሳል። የላይ ቤት አማርኛ በችሐበችሆ ይላል።
ወዓዲ ተንሥኦ ወነቢር ።
አፍ ቁጭ አፍ ቁጭ ማለት ይገኛል ቡኸር አታርፍም ። አንድም አናበህ ተንሥአ ነቢር መቀመጥ ያለበት መነሣት ይገኛል ። ውሻ ድመት በኋላ እግራቸው ይቀመጣሉ በፊት እግራቸው ይቆማሉ ።
አንሳሕሖ።
አንሳሕስሖ ይገኛል። አንሳሕሰሖ በሁሉ አለ ይልቁንም ጥርኝ አታርፍም።  
ወኅድዓት።    
ኅድዓት ይገኛል  ኅድዓት በሁሉ አለ ይልቁንም አንበሳ ። በሬም ያግዛል።
ወፍትወት
ፍትወት ይገኛል ፍትወት በሁሉ አለ ይልቁንም ሰገኖ። ሰገኖ ታበዝኅ ፍትወተ ወእምከመ ኢፀንሰት ኢትበልዕ ሣዕረ እንዲል። 
ወወሊድ
ወሊድ ይገኛል ወሊድ በሁሉ አለ ይልቁንም ጎማ ያለሽል አታድርም ።
ወመዓት
መዓት ይገኛል መዓት በሁሉ አለ ይልቁንም ግሥላ ታንቆ ይሙታባሽ ያሏት እንደሆነ ታንቃ ትሞታለችና ።   
ወሣል።   ሣህል ይገኛል ። ሣህል በሁሉ አለ ይልቁንም ዝሆን።  ዝሆን ሆይ ዝሆን ሆይ ያሉት እንደሆነ መንገድ ይመራል።
ወሕማም።       
ሕማም ይገኛል ። ሕማም በሁሉ አለ ይልቁንም ነብር ዓይን ሕመም ይጸናበታል።   
ወተበቅሎ ።   
ተበቅሎ በሁሉ አለ ይልቁንም ግመል አጥብቆ የመታትን እስከ ስድስት እስከ ሰባት ዓመት ድረስ አትረሳውም ስፍራ ሲመቻት ገደል ገፍታ ትጥለዋለች ባጥ ብላ ትረግጠዋለች።   
ተፈስሖ።
ተፈስሖ በሁሉ አለ ይልቁንም ቀበሮ። ዱሮ ዘመን ቀበሮ ጣዝማ ያገኘ እንደሆነ ሲዘል በታው ይጠፋው ነበር ዛሬ ግን እጁን ጭኖ የሚዘል ሁኑዋል የጊዜውን ክፋት መናገር ነው ።   
ወኃዘን።
ኃዘን በሁሉ አለ ይልቁንም ዖፈ መንጢጥ ባሏ የሞተ እንደሆነ ወበፅፍራ
ትሴጽር ልሳና ይላል ፊቷን ጸፍታ አንደበቷን ሰንጥታ ትኖራለች፤ ሌላ መጥቶ ልድረስብሽ ያላት እንደሆነ ያን ታሳየዋለች ቢመለስ ይመለሳል የተጋፋት እንደሆነ ከወገኖቹዋ ትጠጋለች ያድኑዋታል።
ነዊም። መኝታ በሁሉ አለ ይልቁንም አዞ የያዘውን ከመጣል ይደርሳል።
ወነቂሕ። መንቃት በሁሉ አለ ይልቁንም ቆቅ። ያን ቆቅ ያሉ እንደሆነ ይህን በቅሎ።
ሕይወት።  ሕይወት በሁሉ አለ ይልቁንም ዖፈ ፊንክስ የሚባል ዖፍ አለ በ፭ በ፭ት
መቶ ዘመን ይታደሳልና ። ይህስ የታወቀ ነው ብሎ እንደፎገራ አሞራ ጥርሱ የተላለፈ እንደሆነ ጭሮ መብላት አይሆንለትም ከዕንጨት ከድንጋይም የመታው እንደሆነ ይተካከልለታል ጭሮ ይበላል ።
ወመዊት ። ሞት በሁሉ አለ ይልቁንም አይጥና ድንቢጥ ጭላት የበልጉ ለመኸር የመኸሩ ለበልግ አይገኙም።
ወአምሳለ ዝንቱ በከመ ይትረከብ ዝ በውስተ እንስሳ ነሳሳለትና ይህን የመሰለ ሁሉ በእንስሳት ባሕርይ እንዳለ በሰውም በእንስሳ ባሕርዩ ይህ ሁሉ አለ።
ወዓዲ አክበሮ በንፍሐት ዘይእቲ ማኅተመ ሕይወት መንፈሳዊት እንተ ባቲ አክበሮ እምኩሉ ፍጥረት ዘታኅተ ሰማይ ።  
ከአራቱ ባሕርያት አዋሕዶ ፈጠረው ብሎ ነበርና ዳግመኛ ባራቱ ማዕዘን ካለ ፍጥረት ለይቶ ባከበረበት የሥጋ ሕይወት የደመ ነፍስ ሕይወት በምትሆን በነባቢት ነፍስ አከበረው ።
ወትትዓወቅ በኃይለ ንባብ
ምሥጢር በመናገር ትታወቃለች ።
ዛ ይእቲ አርአያ ገጹ ለእግዚአብሔር ወአምሳሊሁ ይኸውም የእግዚአብሔር መታወቂያው ናት ምሳሌውም ናት። 
በከመ ይቤ መጽሐፍ። 
መጽሐፍ ንግበር ሰብአ በአርዓያነ ወበአምሳሊነ እንዳለ
ወይእቲ ዘኢትትለከፍ   
የማትያዝ የማትዳስስ ናት።     
ወዘኢግብርት። ግብር እምግብር ያልተፈጠረች ናት ። አንድም አጥብቅ  ያያገብሯት ናት።
ሀላዊት። ነዋሪት ናት።
ወዘኢመዋቲት የማትሞት ናት።
ኰናኒተ ሥጋ ወኃይሉ።  
ሥጋን ደመ ነፍስን የምትገዛ ናት አንድም ሥጋን የምትገዛ ናት ወኃይሉ ጠበቃው ናት።   
በእንተ ዘኮነት አሐተ ውሰተ ኩሉ ።
በፈቃድ አንድ ስለሆነች። 
ወባቲ ይትረከብ ጥበብ ዘየሐስብ ልብ ወየኃሪ።
ልብ የሚሻው ጥበብ በሷ ይገኛል።  
ፀሐይ መጸው ክረምት ሐጋይ ማወቅ በሷ ይገኛል ይህንስ እንስሳትም ያውቁታል ብሎ ዓዝማነ መንግሥተ ሰማያትን ማወቅ ይገኛል።
ወመካናት ። ቆላ ደጋን ማወቅ በሷ ይገኛል  ይህንስ እንስሳትም ያውቁታል ብሎ ቆላ
ገሀነም ደጋ መንግሥተ ሰማያት ማወቅን በሷ ይገኛል።
ወኩላ ምግባራት እንተ ትከውን በዘይእቲ ላዕሌሁ የሚሠራው ሥራ ሁሉ እሱን ተዋሕዳ ባለች በሷ ነው  አንድም እሷን ተዋሕዶ ባለ በሥጋ የሚሠራ ሥራ ሁሉ ባቲ ይትረከብ።
በሥልጣን ባሕታዊት።    በዕውቀት ልዩ ናት።
ሥዕልት ዘእንበለ ገቢር።
ግብር እምግብር ሳይሆን የተፈጠረች ናት።
ወገብረ ላቲ ሥልጣነ በውስቴታ ትግበር በከመ ኃርየት እንዘ አልቦ ዘይኴንና ወዘይኄይላ የሚገዛት የሚያዛት ሳይኖር የወደደችውን እንደወደደች ታደርግ ዘንድ አእምሮ ጠባይዕን ሳለባት ።
ከመ ይኩን ሠናያቲሃ ወአከያቲሃ በሥምረተ ሕሊናሃ። 
በጎነቷም ክፋቷም በፈቃዷ ይሆን ዘንድ ።
በአምሳለ መላእክት።

ሠናያቲሃ በአምሳለ መላእከት በሚካኤል በገብርኤል አምሳል።
እከያቲሃ በአምሳለ መላአክት ብለህ ግጠም።
በአጋንንት አምሳል ይሆን ዘንድ ።
ወተፈጸመ ፍጥረቱ ለአዳም በዝንቱ ግብር ። የአዳም ተፈጥሮ በዚህ ተፈጸመ ።
ዘቦ ውስቴቱ ፫ቱ ኃይል ።  
ሦሰት ግብር ሦስት ባሕርይ ባለው ።
ኃይለ ዘርእ። የዘር ግብር የዘር ባሕርይ ባለው ።
ወኃይለ እንስሳ ።  የደመ ነፍስ ግብር የደመ ባሕርይ ባለው።
ወኃይለ ንባብ። የነባቢተ ነፍሰ ግብር ባለው።
 ይቆየን
****************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
02/06/2011 ዓም

No comments:

Post a Comment