Thursday, July 31, 2014

ድንግል ማርያምና መናፍቃን /የመጀመሪያ ክፍል/


እመብርሃን ድንግል ማርያም
የበኩር ልጇን እስክትወልድ ድረስ ዮሴፍ አላወቃትም/ማቴ1:25/
ይህን ቃለ ንባብ በራሱ ምንገድ ተርጉሞ ኑፋቄውን የጀመረው ሔልቪዲስ ሲሆን የኑፋቄው አስተሳሰብ “ድንግል ማርያም የበኩር ልጇን ኢየሱስ ክርስቶስን ከወለደች በኋላ በግብር አወቃት ልጆችንም /የጌታ ወንድሞች የሚባሉትን ማለት ነው/ ከዮሴፍ ወልዳለች” የሚል ነው፡፡ ሊቃውንቱ “አወቀ” የሚለውን ቃል በሁለት መልኩ ይፈቱታል፡፡
1.      አወቀ----› በግብር ማወቅን/ሩካቤን/ ያሳያል
ለምሳሌ፡- “አዳምም ሚስቱ ሔዋንን አወቀ ጸነሰችም ቃንንም ወለደች” ዘፍ4፡1
“ሕልቃና ሚስቱን ሐናን አወቃት፣ እግዚአብሔርም አሰባት የመጽነሷም ወራት ካለፈ በኋላ ሐና ወንድ ልጅ ወለደች” 1ኛ ሳሙ1፡19-20
ከእነዚህ ጥቅሶች እንደምንረዳው “ማወቅ” ማለት በሩካቤ ሥጋ መተዋወቅን የሚያሳይ ነው፡፡
2.     አወቀ-----› ተገነዘበ፣ተረዳ፣አስተዋለ የሚለውን ትርጉም ይይዛል
ለምሳሌ፡- “የሁለቱም ዓይኖች ተከፈቱ እነርሱም እራቁታቸውን እደሆኑ አወቁ የበለስንም ቅጠሎች ሰፍተው ለራሳቸው ግልድም አደረጉ” ዘፍ3፡7
“ዳሩ ግን በዚያ ስፍራ  ሕዝብ ስለነበሩ ኢየሱስ ፈቀቅ ብሎ ነበርና የተፈወሰው ሰው ማን እንደሆነ አላወቀም” ዮሐ5፡14
በእነዚህ ሁለት ጥቅሶች ደግሞ “ማወቅ” የሚለው ቃል መረዳት፣ ማስተዋል፣ መገንዘብ የሚለውን ትርጉም ይሰጣል፡፡
ለሁለቱም የአተረጓጎም ስልቶች በርካታ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃዎችን መስጠት የሚቻለ፤ ቢሆንም የቃሉን ትርጉም ለመረዳት ያህል እነዚህ በቂዎች ናቸው፡፡
መናፍቃን “የበኩር ልጇን እስክትወልድ ድረስ ዮሴፍ አላወቃትም” የሚለውን ቃል በመጀመሪያው አፈታት /ማለትም ሩካቤ በሚለው/ ይተረጉሙታል፡፡ በማቴ 13፡53-55 ያለውን ምንባ በመጥቀስም እመቤታችን ከዮሴፍ ልጆች ወልዳለች ይላሉ፡፡ ምንባቡ እንዲህ የሚል ነው “ይህን ጥበብና ተአምራት ከወዴት አገኘው? ይህ የጸራቢ ልጅ አይደለምን? እናቱስ ማርያም ትባል የለምን? ወንድሞቹስ ያዕቆብና ዮሳ ስምዖንም፣ ይሁዳም አይደሉምን? እህቶቹስ በእኛ ዘንድ ያሉ አይደሉምን?” ማቴ 13፡53-55
በመጀመሪያ ይህን የተናገሩት እነማን ናቸው? ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን አይደሉምን? ታዲያ እነርሱ የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት ያልተረዱ የተናገሩት ተራ ወሬ እንደ ማስረጃ ሊጠቀስ እንዴት ይቻላል? ሊቃውንቱ “አላወቃትም” የሚለውን ሲተረጉሙ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ክርስቶስን በጸነሰች ጊዜ ኅብረ መልኳ ለዮሴፍ ይቀያየርበት ነበር የበኩር ልጇን ከወለደች በኋላ ግን በአንድ ኅብረ ምልክ ሆና መልኳን ማወቅ መቻሉን ያስረዳሉ” ሊቁ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው “ኦ ድንግል አኮ ለዮሴፍ ዘተፍኅርኪ ለተቃርቦ አላ ይዕቀብኪ ንጹሐ”---› ‹‹ ድንግል ሆይ ለዮሴፍ የታጨሽ ለመገናኘት አይደለም በንጽሕና ሊጠብቅሽ ነው እንጅ›› ይላል፡፡ ዮሴፍ ዕድሜው ከ 50 የተረፈ ከ 60 ያለፈ ነበር፡፡ ስለዚህ እርሱ በዚያ ዕድሜው በንጽሕና ሊጠብቃት እንጅ ለጋብቻ አይደለም እጮኛ የሚለው፡፡ መታጨት ለጋብቻ ብቻ አይደለም ለሹመት፣ ለምርጫም ያገለግላል፡፡ ለምሳሌ እጩ ወታደር፣ እጩ መኮንን፣ እጩ ምልምል፣ እጩ ተወዳዳሪ ወዘተ እንደማለት ያለ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ሲገልጽ “ለእግዚአብሔር ቅንነት አቀናችኋለሁና እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና” 2ኘ ቆሮ 11፡2 በዚህ አገባብ  “አጭቻችኋለሁና” የሚለው ቃል ጋብቻን የሚያሳይ አይደለም፡፡ ስለዚህ ዮሴፍ “አላወቃትም” የሚለው በግብር ማወቅን የሚተረጉም አይደለም፡፡ “የጌታ ወንድሞች” የሚላቸውና “በኩር” የሚለውን ቃል ትርጉም በሚቀጥለው ክፍል እናያለን፡፡
ይቆየን
አሜን፡፡

የበላይነት ጉዳት

አንድ በዱር የሚኖር የእንስሳት ሁሉ የበላይ አለቃ የሆነ አንበሳ የሚባል እንስሳ ነበር፡፡ በበላይነቱ አብዝቶ የሚመካው አንበሳ አንድ ቀን እንስሳትን ሁሉ ለስብሰባ ጠራቸው፡፡ በውኃ የሚኖሩ፣ በሰማይ የሚበሩ፣ በየብስ የሚመላለሱ በሙሉ ጥሪው ደርሷቸዋል፡፡ ከስብሰባው መቅረት የሚባል ነገር አይታሰብም ከላይ አንገቱን ከታች ባቱን ይቆረጣልና፡፡ ቀኑ ደርሶ ሁሉም እንስሳት ተሰበሰቡ ዓሣ ግን በዚያው በውኃ ውስጥ ቀረች፡፡ “ሁሉም እንስሳ መጥተዋል አይደል? አለ አንበሳ እየተጎማለለ፡፡ “ከዓሣ በቀር ሁሉም መጥተዋል” አለች አዞ፡፡ “ምን ያህል ብትንቀኝ ነው ዓሣ ስብሰባዬን ያቃለለችው? አለ አንበሳ በብስጭት፡፡ ቀጠለ “እዚህ ላይ ሳልረሳው ለአዞ የምሰጥሽ ትዕዛዝ አለኝ ዓሣን በገባችበት ገብተሽ ታጠፊልኛለሽ፡፡ ዓሣ የሚለው ሥም ከእንስሳት ሥም ጋር ሊቆጠር አይገባውም፡፡ ሌሎችን እንስሳት ሳይቀር ለአመፅ የምታነሣሣ አመፀኛ ናት፡፡ ስለዚህ አርሷን የመከታተልና አከርካሪዋን ሰብሮ የመጣል ጉዳይ ለአዞ የተሰጠ ኃላፊነት ነው፡፡ ለማንኛውም የስብሰባችንን አጀንዳ እንቀጥል፡፡ አጀንዳው መደራጀትን የሚመለከት ነው፡፡ ልብ ብላችሁ ተከታተሉኝ ነገ ወደ ሥራ የምንገባበት ስለሆነ፡፡” ብሎ ማስጠነቀቂያ ሰጠ አንበሳ፡፡ “በፊት ከነበረው አለቃችሁ ይልቅ እኔ ተደራጅታችሁ መሥራትን አበረታታለሁ ስለዚህ እንስሳ የሆነ ሁሉ ሊደራጅ ግዴታ አለበት፡፡ አንበሳነቴን ይቃወምም ይደግፍም እኔ ለእንስሳቱ ይጠቅማል ያልኩትን ፖሊሲ ሁሉ የመፈጸም ግዴታ አለበት፡፡ ሁላችሁም ተደራጅታችሁ አንዱ አንዱን ይከታተላል፣ ይደግፋል፣ ይፈርጃል፣ ችግሩን ያሳያል፣ ያርማል፣ ይፈትሻል፣ ከእኔ የሚወርዱ መመሪያዎችን ያስጠናል፡፡ ሌላው እኔ ከምናገረው እና ከማወርደው መመሪያ ውጭ ሌላ ነገር መተንፈስ አይፈቀድም፡፡ አሁን ለደረስንበት እድገት መደራጀታችን ወደር የማይገኝለት አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ ነገር ግን ጥቂት ክፍተቶች ነበሩብን የዛሬውም ስብሰባ ዋና ዓላማ እነዚህን ክፍተቶች መሙላትና ወደ ሥራ መሰማራት ነው፡፡” አለ አንበሳ የራሱን ፍላጎት ብቻ እየተከተለ፡፡ እንስሳት በጸጥታ ይከታተሉታል፡፡ መቃወም አይቻልም፡፡ ተቃራኒ ሃሳብም ማንሣት አይፈቀድም፡፡ ምክንያቱም አመፀኛ፣ ዘረኛ፣ ትምክህተኛ፣ ጎሰኛ ወዘተ የሚል ሥም ይሰጣልና፡፡ አንበሳ ቀጠለ “ዛሬ በዋናነት የያዝነው አጀንዳ በመደራጀት ከላይ የሚወርዱትን መመሪያ በመፈጸም እድገታችንን ማረጋገጥና አደጉ ከሚባሉት ጋር እኩል መቆጠር ነው፡፡ በተጨማሪም እኔ ከምለው ውጭ ሌላ መናገር ለእድገታችን ፀር ስለሆነ ሁሉም የየቡድኑ መሪዎች በቡድናችሁ ያሉትን አባላት በሚገባ ማጥናት ያስፈልጋል፡፡ የአመለካከት ችግር ያለባቸውን አባላት በሚገባ መፈረጅ አለባችሁ፡፡” ብሎ አደራጅቶ አሰናበታቸው፡፡ አዞ የተሰጣትን ኃላፊነት ለመወጣት ወደ ዓሣ ሄደች፡፡ “እዚህ ቤት” አለች አዞ የዓሣን ቤት እያንኳኳች፡፡ “አቤት” ብላ ዓሣ ወጣች፡፡ “ዛሬ ከስብሰባ የቀረሽ ስብሰባውን ንቀሽ ነው ወይስ አንበሳን ተቃውመሽ ነው?” አለቻት፡፡ ዓሣ ቀጠለች “በስመ አብ! እንዴት ነው ስብሰባውን የምንቀው አንበሳንስ የምቃወመው? የእኔ ችግር እኮ ማንም የሚያውቀው ነው፡፡ ከውኃ ከወጣሁ እሞታለሁ፡፡ ስለዚህ ስብሰባውን መተው መረጥኩ ከሕይዎት በላይ ምን አለ?” አለች ዓሣ በሚያሳዝን ንግግር፡፡ አዞ ቀጠለች “ምንም ይፈጠር ምን ስብሰባውን መተው የለብሽም ነበር፡፡ አንች አኮ ለአመፅ ተባባሪ እንደሆንሽ ነው ሁሉም የተረዳው፡፡ አንበሳም የበላይነቱን የተቀማ ያህል ነው ያንገሸገሸው፡፡ ለእድገታች እኮ መሥዋዕትነትን ይጠይቃል፡፡ ዝም ብሎ የሚመጣ ጉዳይ አይደለም፡፡” አለች አዞ፡፡ ዓሣ ቀጠለች “አውቃለሁ ክብርት አዞ፡፡ የእኔ ጉዳይ እንደማንኛውም እንስሳ የሚታይ አይደለም፡፡ ስብሰባው ውኃ ውስጥ ቢሆን ኖሮ ማን ነበር ስብሰባውን የሚመራው? ሁሉም እኮ ራሱን ለማኖር ነው የሚታገለው፡፡ ይህን በመናገሬ ጽንፈኛ፣ ጎጠኛ፣ ዘረኛ፣ ትምክህተኛ የሚል ሥም እንደሚሰጠኝ አምናለሁ፡፡ ነገር ግን ማንነቴን ራሴ ስለማውቅ ብዙም አልደነቅም፡፡ እሽ ዛሬ አንችን ወደ እኔ ከመላክ ይልቅ ራሱ አንበሳ መጥቶ ለምን አልጠየቀኝም?” አለች ቁጣዋን ዋጥ እያደረገች፡፡ “እንዴ ላንች ብሎ የተከበረው አንበሳ እዚህ ድረስ ይምጣ?” አዞ ሳቀች፡፡ ሳቋን ጨርሳ ንግግሯን በቁጣ ቀጠለች “እንዲህ አይነት አመለካከት ይዘሽ ነው እድገትን እናመጣለን እያልን የምንታገል? በአንድ አለቃ መመራት ድሮ ቀረ አኮ፡፡ አሁን ሥልጣን ለየሁሉም ተዳርሷል፡፡ ሁሉም እንስሳት ተደራጅተው የየራሳቸው መሪ መርጠው በዚያ ነው መመሪያ የሚመጣላቸው፡፡ አንችን ደግሞ እንድመራ ሥልጣኑ የተሰጠ ለእኔ ነው፡፡ ስለዚህ አሁንም ቢሆን አመለካከትሽን አስተካክይ፡፡ ይህን ማድረግ ካቃተሸ ግን አሁንም ቢሆን አንበሳ ዘንድ ወስጄ ማስቀጣቴ አይቀርም፡፡” አለች አዞ፡፡ “የእኔ ጉዳይ ልዩ ነው ይታይልኝ ማለት ወንጀል ከሆነ ይቅርታ” አለች ዓሣ፡፡ አዞ እየተጎማለለች ዓሣን አስጠንቅቃ ሄደች፡፡ አንበሳ መመሪያዎችን ለሁሉም የቡድን መሪዎች አስተላለፈ፡፡ ሁሉም አባሎቻቸው እውቅና ፈጠሩ “ከአንበሳ የመጣውን መልእክት ሁላችንም ማዎቅ፣ ማክበር አለብን፡፡” አሉ የእንስሳቱ ቡድን መሪዎች፡፡ ሁሉም አባላት ሊፈጽሙት አንበሳ የተናገረውን በሙሉ ሊያከብሩ ለየራሳቸው ቃል ገቡ፡፡ አንዱ አንዱን መፈረጅ፣ አመለካከታቸውን ማጥናት ጀመሩ፡፡ የየአንዳንዱን ቡድን መሪ ሪፖርት አንበሳ ይከታተላል፡፡ አንበሳ በበላይነቱ ተመክቶ ይጎማለላል፡፡ እያንዳንዱን የቡድን መሪ ያሸማቅቃል፡፡ አንዳንዶች በሥውር ሃሳቡና አመራሩ እንዳልተመቻቸው ሲገልጹ የተለያየ ሥም ያወጡላቸዋል፡፡ እንስሳ ሆኖ መኖርን በጣም የሚያማርሩ በዙ፡፡ ለመኖር የሚሠሩትን ሥራ ስብሰባ በሚል ሰበብ ትተውታል፡፡ በስብሰባዎች መብዛት ምክንያት አዝመራቸውን ዝናብ ያበላሸባቸውም እንስሳት ነበሩ፡፡ በዚህ ሁኔታ ሳሉ አንበሳ ድንገተኛ አደጋ ደረሰበት፡፡ ሁሉም እንስሳት በአደጋው ክፉኛ አዘኑ፡፡ ሊያዩት ተሰበሰቡ፡፡ እባካችሁ “ሐኪም ቤት ውሰዱኝ” አለ አንበሳ፡፡ የቡድን መሪዎች አባሎቻቸውን “ሐኪም ቤት ውሰዱኝ” አሉ አንበሳ ያለውን እንደወረደ ነውና ለአባላቸው የሚያስተላልፉት፡፡ “በጣም ጠናብኝ ልሞት ነው በነፍሴ ድረሱባት” አለ አንበሳ እያቃሰተ፡፡ አሁንም ሁሉም ይህንኑ ተናገሩ፡፡ የተናገረውን እንደበቀቀን መድገም እንጅ ቀርቦ የሚረዳው አጣ፡፡ እኔ ካልኩት ውጭ ሌላ እንዳትናገሩ ያለው አንበሳ በከፋ ሁኔታ ሞተ፡፡ አንበሳ እንደሞተ ወንበሩን ለመያዝ ሽኩቻ ሆነ፡፡ ዓሣ ሞቷን ስትጠብቅ አንበሳ ቀደማት፡፡ “አምላኬ ሆይ ችግሬን የሚረዳልኝ አለቃ ስጠኝ” እያለች ፈጣሪዋን መለመን የዕለት ከዕለት ሥራዋ ሆነ፡፡ እኔ ካልኩት ውጭ ሌላ አትናገሩ እያለ ሲጎማለል የነበረ አንበሳ አሟሟቱ የከፋ ሆነ፡፡ ለቀሩትም የማይገባ ልምድ አውርሶ አለፈ፡፡ ለእድገት የሚሠሩ የመሰሉት ሁሉ ማንነታቸው ተገለጠ፡፡ አንበሳን ማዎደስ ብቻ ሆነ የዕለት ከዕለት ሥራቸው፡፡ ወንበሩን ለመያዝ ግን ዛሬ ድረስ ሽኩቻ ነው፡፡

፩ አንድ

“፩ ማለት ሁለት መሆን አይቻልም ማለት ነው እንዴ?” አለ ዮናስ፡፡ ዳዊት ቀጠለ “ምን ለማለት ነው አልገባኝም?” አለው፡፡ “አልሰማህም እንዴ? የኢትዮጵያ  ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አንዲት አገር አንዲት እምነት እያለች የእምነት ነጻነትን ተጋፍታለች ተብላ ተከሰሰች እኮ” አለ ዮናስ፡፡ ዳዊት ቀጠለ “መጀመሪያ ከሳሹ ያልተባለውን ነው ያለው፡፡ አንድ ጌታ፣ አንዲት ጥምቀት፣ አንዲት እምነት የሚል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል ነው፡፡ እዚህ ክፍል ላይ አንዲት አገር የሚል የለውም ቢል እራሱ ኢትዮጵያ ስንት አገር ናት ፩ አይደለችም እንዴ? ለማንኛውም ኤፌ4፥4 ን ያንብቡና ክሳቸውን ያስተካክሉ” አለ ዳዊት፡፡ ዮናስ ቀጠለ “የእኔም ጥያቄ ይህ ነበር እኮ አንድ ሰው አንድ እምነት አንድ አገር ነው የሚኖረው ይህ ተፈጥሯዊ ግዴታ ነው፡፡ በአንድ ጊዜ እስላምም ክርስቲያንም መሆን አይችልም አንዱን መምረጥ አለበት፡፡ አንድ ጊዜ ኢትዮጵያዊም ኤርትራዊም መሆን አይችልም አንዱን መምረጥ አለበት፡፡ አንድ እምነት ማለት ሌላ ሁለተኛ እምነት ሊኖር አይገባውም ማለት አይደለም፡፡ ከሳሾች ያልገባቸው ይህ እውነታ ብቻ ነው እንጅ ቢገባቸው ኖሮ እኛ ያልነውን እነርሱም ይሉት ነበር” አለ፡፡ ዳዊት ማብራራት ጀመረ “አንተ እንዳልከው ፩ እምነት ማለት ሁለተኛ እምነት ሊኖር አይገባውም ማለት አይደለም፡፡ ምን ይመለከተናል እኛ ድንጋይ፣ ዕፅዋትን፣ ፀሐይ፣ ጨረቃን ቢያመልክ? ማንም ሰው የመሰለውን ማምለክ ይችላል መብቱ ነው፡፡ ነገር ግን የሚያመልከው አንድ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ አንድ እምነት ቢል ማንም አይቃወመውም አንድ እምነት ነዋ ያለው፡፡ አንድ እምነት አለኝ ሲል ግን ብዙ ቁጥር ያለው እምነት በል ተብሎ ሊገደድ አይገባውም፡፡ እርሱ አንድ ነዋ! አንድ ወንድ አንድ ሚስት አለችኝ ቢል የግድ ሁለት ሚስት በል ይባላል እንዴ? አንድ ወንድ ለአንድ ሴት ማለትስ ወንጀል ነውን? የፈለገው ቁጥር ወንድ ለፈለገው ቁጥር ሴት በል ተብሎ ሊከሰስ ነውን?” አለ፡፡ ዮናስ በዳዊት ንግግር ላይ ቀጠለ “ልክ ነህ ዳዊት ወንዶች ተሰብስበው አንድ ወንድ አንድ ሚስት ቢሉ ሊከሰሱ ነው ማለት ነው? እና አንድ ወንድ ስንት ሚስት እንዲኖረው ነው የሚፈለገው ፩ አይደለም እንዴ? ነው ወይስ የፈለገው ቁጥር ያላቸው ሚስቶች ይፈቀዱለታል ማለት ነው? ከሳሾች ያልገባቸው ብዙ ነገር አለ፡፡ ሲገባቸው ግን እነርሱም እንደእኛ ማለታቸው አይቀርም፡፡” አለ፡፡ “ቆይ እንጅ ግን አንድ ጌታ፣ አንዲት ጥምቀት፣ አንዲት እምነት አትበሉ የሚባለው መጽሐፍ ቅዱሳችንን ሰርዘን ነው ወይስ አቃጥለን፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ነው እኮ! ማንም ስላለ የምንፍቀው አይደለም፡፡ እግዚአብሔርን ስናመልክ አብሮ የተሰጠን የፈጣሪ ቃል ነው፡፡ ይህን መስማት የማይፈልግ ፈጣሪን ይክሰስ እንጅ እኛ በሕይወት እስካለን ድረስ ለዚህ ቃል እንገዛለን፡፡” አለ ዳዊት፡፡ ዮናስ ቀጠለ “እነርሱ የፈሩት ፩ ማለት ሁለት መሆንን ይቃወማል ብለው መሰለኝ፡፡ ይህ እኮ ቀላል አማርኛ ነው እንዴት አልተረዱትም ግን? የሰው ልጅ ሁለት ጾታዎች ነው ያሉት ሴት ወይም ወንድ፡፡ ወንዱ አንድ ጾታ ነው ያለው ሴቲቱም እንዲሁ፡፡ የሰው ልጅ ሁሉ አንድ ጾታ እያለ ሰላማዊ ሰልፍ ቢወጣ ማነው የሚከሰው? ሁለት ጾታ እና ከዚያ በላይ ያላቸው ሰዎች ወይስ ጾታ የሌላቸው ሰዎች? ማንም አይከስም፡፡ ምክንያቱም አንድ ሰው አንድ ጾታ ብቻ ነውና ያለው፡፡ እምነትም እንዲሁ ነው፣ አገርም እንዲሁ ነው፡፡ አንድ ሰው ፩ እምነት ፩ አገር ብቻ ነውና ያለው” አለ፡፡ “ምኑ እንደተሰወረባቸው አልገባኝም፡፡ ከሳሾች ስንት እምነትና ስንት አገር እንዳላቸው ግራ ገባን እኮ፡፡ ኢትዮጵያ አንድ መሆኗን አጠራጠሩን፡፡ ኢትዮጵያ ለእኛ አንድ አገር ነበር የምትመስለን ለካ ብዙ አገር አድርገዋታል?” አለ ዳዊት፡፡ “፩ አምነት በአንድ አገር ውስጥ የሚል አቋም ቢኖረን ኖሮ ኢትዮጵያ አንድ እምነት ብቻ በነበራት ወቅት የመጡትን የእስልምና እምነት ተከታዮች በእንግድነት ማን ይቀበላቸው ነበር? በእንግድነት ከተቀበልን በኋላስ ግድ የእኛን እምነት ካልተከተላችሁ ብለናቸዋል እንዴ? በፍጹም እንዲህ ያላቸው የለም፤ ብለውናል ያለ ካለም ይመስክር፡፡ እንድ ጌታ፣ አንዲት ጥምቀት፣ አንዲት እምነት የሚለው ቃል ያን ጊዜም ነበር እኮ ነገር ግን ትርጉሙ እንደከሳሾች ያለ ስላልሆነ ነው ዝም ብለን ከእነእምነታቸው የተቀበልናቸው” አለ ዮናስ፡፡ “ልክ ነሀ ዮናስ! አሁንም ቢሆን ፩ እምነት ፩ አገር የምንለው አንድ ሰው አንድ እምነት አንድ አገርም ብቻ ይኑረው ማለት ነው፡፡ ያች አንዲት እምነት ማናት? አንዲት አገርስ ማናት? ላለ መልሱ ለየግሉ ነው፡፡ ለእኔ ፩ እምነት የምለው ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን ነው፤ ፩ አገርም የምለው ኢትዮጵያን ነው፡፡ ለሌላው ደግሞ ፩ እምነት ፩ አገር የሚለው ሌላ ነው፡፡ ስለዚህ ይህን መረዳት ያስፈልጋቸዋል” አለ ዳዊት፡፡ በዳዊት ሃሳብ ተስማምተው ተሰነባበቱ፡፡
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠

ፈውስ


እመቤታችን ከአረጋዊው ዮሴፍ ጋር
የፈውስ አይነቶች 2 ናቸው
1. የሥጋ ፈውስ
2. የነፍስ ፈውስ
የሥጋ ፈውስ ማለት ከሰውነት አካላት በሽታዎች መዳን ነው፡፡ የእጅ የእግር የዓይን የጆሮ ወዘተ የነፍስ ፈውስ ስንል ግን የነፍስ ከኃጢአት፣ ከበደል፣ ከአጋንንት ቁራኝነት መዳን ነው፡፡
ፈውስ ከማን ይገኛልያልን እንደሆነ ከእግዚአብሔር በባሕርይው ከቅዱሳን በጸጋ ይገኛል፡፡ መላእክት፣ ጻድቃን፣ ሰማዕታት፣ አበው መነኮሳት ነቢያ ካሕናት ይፈውሳሉ፡፡
ፈውስ የት ይገኛል ስንል


1 በቤተ ክርስቲያን /ሐዋ3፡1-10/
2 በመጠመቂያ ቦታዎች /ዮሐ5፡1-18;
3 እግዚአብሔርን በመከተል /ማር 5፡25-34/
ፈውስ እውነተኛ እና ሐሰተኛ ተብሎም ይከፈላል፡፡ እውነተኛው ፈውስ ከእግዚአብሔር የሚገኘው ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ስንል እግዚአብሔር በባሕርይው የሚሰጠን ፈውስ ወይም በቅዱሳኑ አድሮ በጸጋ የሚገኘውን ፈውስ ማለታችን ነው፡፡ ያ ፈውስ ለነፍስም ለሥጋም የሚጠቅም ሊሆን ይገባዋል፡፡ የመጠመቂያ ቦታዎች ላይ እግዚአብሔር አጋንንትን አሥሮ ያሰቃያቸዋል ለጥቂት ጊዜያት እንኳ ለመቆየት አይችሉምና ከሰዎች ዘንድ ይወጣሉ፡፡ ዳግም ላይመለሱም ይምላሉ ይገዘታሉ፡፡ በማርቆስ ወንጌል ምእራፍ 5፡25-34 የተጠቀሰችው ሴት 12 ዓመት ያህል ደም ይፈሳት ነበር የክርስቶስን ልብስ ነክታ ዳነች ዳግም ያ ደዌ አልመጣባትም፡፡ ዮሐ5፡1-18 የምናየው የ38 ዓመት በሽተኛው መጻጉእ ከደዌ ዳኛ ከአልጋ ቁራኛ ተፈውሶ አላጋውን ተሸክሞ ሄዷል፡፡ ሐዋ3፡1-10 የተገለጠው ሽባ ቅዱስ ጴጥሮስ እና ቅዱስ ዮሐንስ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሥ ብለው ፈውሰውታል ዳግም ወደ ሽባነት አልተመለሰም፡፡ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ያላስገረመው ሰው አሁን ይሠራል በሚሉት ነገር ሲደነቁ ልዩ ተአምር ተደረገ እያሉ ሲታለሉ በጣም ያሳዝናል፡፡ ትውልዱ ሆይ አትደናገር በሽታ መፈወስ ብቻ አይደለም ቅዱሳኑ ሙት አንሥተዋል እኮ፡፡ ኤልያስ አንድ ሙት ኤልሳዕ 2 ሙት አንሥተዋል፡፡ /መጽሐፈ ነገሥትን ተመልከቱ፡፡/የሰው ልጅ በባሕርዩ ድንቅ በሚባል ተአምር ይታለላል፡፡ ተአምረ ማርያምና ተአምረ ኢየሱስን እነዲሁም ሌሎችን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ተአምራት የምናቃልል ሰዎች ዛሬ ተአምር እንደርጋለን በሚሉ ተኩላዎች አፋቸውን ከፍተው ጉድ ተሠራ እያሉ ሲከተሉ ማዬት አይቶም ዝም ማለት ሞኝነት ብቻ ሳይሆን ጅልነትም ነው፡፡ አጋንንትን የማውጣት ጸጋ  የተሰጣቸው ቅዱሳን ጸጋቸው እንዳይገለጥባቸው ያደርጉ ነበር እግዚአብሔር ያስተማራቸው ያንን ነበርና፡፡ እግዚአብሔር በወንጌሉ በርካታ ቦታዎች ላይ ፈውስ ካደረገላቸው በኋላ ይህንን ተአምር ለማንም እንዳትናገሩ ይላቸው ነበር፡፡/ማር7፤36-37//ዮሐ5፡15/ ቅዱሳን  ፈውስን የሚያደርጉት በነጻ ያለምንም ክፍያ ነበር፡፡ ክርስቶስ ሐብተ ፈውስን ለሐዋርያት ከሰጣቸው በኋላ እንዲህ አላቸው ለእናንተ ለእጀጠባባችሁ ኪስ አይኑራችሁ እኔ በነጻ የሰጠኋችሁን እናንተም እንዲሁ በነጻ ስጡ፡፡/ማቴ10፡9/ ለዚህም ነው ወርቅና ብር የለንም ነገር ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሣ እያሉ በነጻ ሽባዎችን እየተረተሩ ለእግዚአብሔር አገልጋዮች ያደርጉ የነበረው፡፡ ሐሰተኛ ፈውስ የምንለው ግን የዚህ ተቃራኒ ነው፡፡ ይህ ፈውስ ጊዜያ ነው፡፡ በዓይናችን ስናየው እንደነቃለን ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ተአምር ይመስለናል፡፡ አሁን ያልገባን ነገር አለ አጋንንት ደረጃ ደረጃ አላቸው፡፡ ተራ አጋንንት ወይም በደረጃቸው ዝቅ ያሉ አጋንንት በአለቃቸው ወይም ከእነርሱ በበለጡ አጋንንት ይወጣሉ፡፡ የቡዳ መንፈስ፣ መተት፣ ድግምት ወዘተ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያሉ አጋንንት ናቸው እነዚህን በአለቃቸው በብዔል ዜቡል ማውጣት ተአምር አይደለም፡፡ እነዚህ መናፍስት አኮ በነጭ ሽንኩርት ማንም ሰው የሚያባርራቸው ተራ አጋንንት ናቸው፡፡ ተራ አጋንንት በአለቃቸው ለምን ይወጣሉ ቢሉ አለቃቸው ነፍስን ተቆራኝቶ በገሐነመ እሳት ለዘላለም መያዝ ስለሚፈልግ ነው፡፡ የሰይጣንን ጥበብ ብዙዎቻችን አልተረዳነውም ለዚህም ነው አባታችን እንዲህ አድርገው ይፈውሳሉ እያልን አምላክ እስከሚመስሉን ድረስ ያመንነው፡፡ ሰው የሚደነቀው በሥጋው መፈወሱን ብቻ ነው ከፈውስ ባሻገር ነፍሱ ምን እንደምትሆን አይረዳም፡፡ ሥጋህ ለምን አይታመም ዋናው እኮ የነፍስ በሽታ ነው፡፡ የስጋ በሽታ እኮ ይፈውሱ የነበሩት እነ ቅዱስ ጳውሎስ እና ቅዱስ ጴጥሮስም ነበረባቸው፡፡ ነፍስህን አስብ ትውልዱ!!!!!
በዚህ ዘመን አጋንንትን እናወጣለን የሚሉ ሰዎች የእግዚአብሔርን ስም ጠርተው ነው የሚያወጡ እንላለን፡፡ እውነት ነው የእግዚአብሔር ስም ሲጠራ እንሰማለን ከእግዚአብሔር ስም በስተጀርባ ምን ይደረጋል እርሱ እግዚአብሔር ይወቀው፡፡ ገና ብዙ ነገር ይቀረናል እኮ ምንም አልገባንም ክርስትናው፡፡ የእግዚአብሔርን ስም እየጠራ ስንቱ መጫኛ ያቆማል፣ ድውይ ይፈውሳል፣ የግሉን ገንዘብ ያካብታል መሰላችሁ፡፡ የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ ውስጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኩላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ፡፡/ማቴ7፡15-16/ የበግ ለምድ የተባለው የእግዚአብሔር ቃል፣ የእግዚአብሔር ስም፣ ጥምጣሙ፣ ካባው፣ አስኬማው ነው፡፡ ይህ ከላይ የምናየው ለምድ ነው በግ የሚያስመስለው፡፡ ውስጡ ግን እምነቱ፣ ምግባሩ፣ ቅድስናው ወዘተ ተኩላዎች ነጣቂዎች ያደርጋቸዋል፡፡ እነዚህ የሚያፈሩት ትውልድ ለእግዚአብሔር የሆነ አይደለም ለራሳቸው መመጻደቂያ፣ ቡና የሚያፈላላቸውን፣ ጫማ የሚያስርላቸውን፣ በየሔዱበት አባቴ አባቴ የሚሏቸውን ነው፡፡ ትውልዱ በዚህ አትደነቅ በመጨረሻው ዘመን ከዚህ የበለጠ ተአምር እንደሚሠራ መጽሐፋችን ይነግረናል፡፡ በምትሀት ፀሐይን እና ጨረቃን ይዞ የሚመጣ ትውልድ የሚነሣበት ዘመን ይመጣል ያን ጊዜ የተመረጡ የሚባሉት እንኳ እስኪስቱ ድረስ ብዙ ተአምራትን ያደርጋሉ፡፡ አስቡት እንግዲህ የምጡን መጀመሪያ ዛሬ በዚህ ተራ በሆነ ቀላል ነገር ሕዝቡ እንዲህ ካመነ ያን ጊዜ ማን ይሆን ጸንቶ የሚቆመው? ማንም ሰው እንዲህ አድርግ እንዲህ አታድርግ ተብሎ የሚመለስበት ጊዜ ላይ አይደለንም ነጻ ፈቃድ የራሳችን ነው፡፡ የፈለግነውን የመከተል መብታችን የራሳችን ነው፡፡ አመጸኛ ትውልድ ምልክትን ይሻል እንዲል መጽሐፉ ተአምራትን ቤተክርስቲያን ገብታችሁ ተመልከቱ፡፡ ጸበል ቦታዎች ሄደን መጽናት ሲደክመን በቀላሉ የተገላገልን እየመሰለን ሰው አንከተል፡፡ አጋንንት የሚወጡት በጾምና በጸሎት ነው፡፡ ሐዋርያት በአንድ ወቅት አጋንንት ያደረበትን ሰው መፈወስ አልችል አሉ፡፡ ኢየሱስም መጣ እና ያንን አጋንንት አስወጣው፡፡ ሐዋርያቱም እኛ ለምን አላወጣነውም ብለው ጠየቁት እርሱም መልሶ እንዲህ አይነቱ መንፈስ በጾምና በጸሎት ካልሆነ በቀር አይወጣም አላቸው ይላል፡፡ ለዚህም ነው በጸበል ቦታ አጋንንት የሚቃጠሉት እዚያ ላይ ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደት አለ፡፡ በአጠቃላይ እውነተኛ ፈዋሽ እንዴት እናውቃለን ለሚለው የሚከተሉትን ነገሮች ሙሉ በሙሉ መሟላት አለበት፡፡
1. ጸጋ እግዚአብሔር ያደረበት
2. የሚጾም፣ የሚጸልይ፣ የሚሰግድ፣ በእምነት የጸና
3. ለፈወሰበት ጸጋ ገንዘብ የማይቀበል
4. ጸጋው በአደባባይ እንዳይገለጥ የሚያደርግ
5. ቃለ እግዚአብሔርን ብቻ የሚናገር
ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ የተባልነው ያንን የሚሠሩትን ሥራ እንድንገመግም ነው፡፡ በበለጠ ገዳማት ሔዳችሁ እውነተኛ ፈውስ ምን እንደሆነ አረጋግጡ፡፡ በእምነት አትጎስቁሉ፡፡ ቃለ እግዚአብሔርን እንደ ሽፋን ተጠቅመው የዋሃንን ከሚያታልሉ ተኩላዎች ራስህን ጠብቅ መልእክቴ ይህ ነው

አባት እና ልጅ

አባትና ልጅ በመኪና እየተጓዙ ናቸው፡፡ አንድ ሽማገሌ ለመጫን መኪናው ቆመ፡፡ ሽማግሌው ገቡ “ጤ-ኤኤኤ-ና ይ-እእእ-ስ-እእእ-ጥ-እእእ-ል-እእእ-ኝ” አሉ በተቆራረጠ የሽምግልና ንግግር፡፡ ሽማግሌው ከ90 ዓመት ያለፋቸው ይመስላሉ፡፡ አስተውሎ ላያቸው ደግሞ “ይህን ሳታይ አትሞትም” የተባለውን ስምዖን አረጋዊን ይመስላሉ፡፡ መኪናው ጉዞውን ጀመረ፡፡ ሽማግሌው የሚቀመጡበት ወንበር የለም በረዳቱ ቋንቋ“ትርፍ” ናቸው፡፡ የመኪናው ፍጥነት ሽማግሌውን ወደ ግራም ወደ ቀኝም እያላቸው በጣም እንደተቸገሩ የተመለከተ አንድ እንደ ሽማግሌው “ትርፍ” የሆነ ወጣት አንድ ከአባቱ ጋር የተቀመጠን በግምት የ15 ዓመት የሚሆን ልጅ ተነሥቶ እንዲያስቀምጣቸው ተማጸነው፡፡ “እባክህ እነኚህን ሽማግሌ አስቀምጣቸው ትጸድቃለህ” አለ የቆመው ወጣት፡፡ “እንዴት ምን እያልክ ነው? ወንበሩን እኮ በትግል ነው ያገኘነው እንዴት ልጄን ተነሥ ትለዋለህ?” አሉ የልጁ አባት፡፡ “ምን ችግር አለው እርሱ ቢቆም ከእርሳቸው እኮ ይጠነክራል፡፡ አክብሯቸው ቢነሣና ቢያስቀምጣቸውስ ምረቃው ቀላል ነው እንዴ?” አለ ወጣቱ፡፡ “አልነሣም! ምረቃው ይቅርብኝ!” አለ የአባቱን ድጋፍ ያገኘው ልጅ፡፡ መኪናው ይሮጣል ሽማግሌውም ግራ ቀኝ ይወዛወዛሉ፡፡ “ኧ-ረ ተ-ኧኧ -ው በ-እእ-እ-ኔ ም-እእ-ክ-እእ-ን-እእ-ያ-ኣኣ-ት አ-ት-እእ-ጨ-ኧኧ-ቃ-ኣኣ-ጨ-ኧኧ-ቁ” አሉ ሽማግሌው፡፡ “ምን የአሁን ልጅ አባት እናቱን ማክበር ትቷል እኮ፡፡ እናትና አባት የሚባሉትም በሥርዓት ማሳደግ ትተዋል፡፡ ይገርማል እኮ አባቱስ ቢሆኑ አትነሣ፣ ሽማግሌ አታክብር አይደል እንዴ ሲሉት የነበረው?” አለ ወጣቱ፡፡ አንድ ሌላ ወንበር ላይ የተቀመጡ ሽማግሌ ተሳፋሪ የወጣቱን ንግግር ሰምተው “አክብር አባከ ወእምከ የሚለው የፈጣሪ ትዕዛዝ ተረሳ፡፡ እኛም ልጆቻችንን የ8ኛው ሽህ ልጅ እንዲህ አድርጎ ማለት እንጅ ሥርዓት አላስተማርናቸውም፡፡ አታይም እንዴ አሁንስ ሽማግሌ ቆሞ አትነሣላቸው አታክብራቸው የሚል አባት ነው እኮ ያለው፡፡ አክብር አባከ ወእምክ የሚለውን አክብር መንበርከ ብለው ቀየሩት እኮ፡፡ አሁን ጥለነው ለምንወርደው ወንበር ይህን ያህል መስገብገብ ምንድን ነው? ፈጣሪ ይጠብቀን እንጅ መኪናው ቢገለበጥ ወንበር ላይ የተቀመጠ አይጎዳም መሰላቸው እንዴ?” አሉ ሁኔታው በጣም አሳዝኗቸው፡፡ “ዘመኑ በጣም ያስፈራል፡፡ ልጆችን በሥርዓት የሚመራ ወላጅ ጠፍቷል፡፡ ስድብና ክፋት ነው እኮ እያስተማርን ያሳደግናቸው፡፡ በለጋነት ዘመናቸው አልገራናቸውም፡፡ በቤት ውስጥም ዱላ እየሰጠን እገሌን ደብድበው እያልን ነው ያለማመድናቸው፡፡ እኔ ግን ዘመኑ በጣም ያስፈራኛል፡፡ ምን አይነት ትውልድ ሊፈጠር እንደሚችል ሳስበው እንባዬ ይመጣል” አለ ወጣቱ፡፡ “በጣም የሚያስፈራ ዘመን ነው፡፡ መከባበር፣ መረዳዳት፣ መተባበር ተረሱ እኮ፡፡ እንደገባህ ውጣው የሚለው በዝቷል፡፡ የትውልዱ አቅጣጫ የት እንደሚያደርሰን ዕድሜ ሰጥቶ እንዳያሳየኝ ነው ጠዋት ማታ ፈጣሪዬን የምለምው፡፡ የዚህን ትውልድ ዕጣ ፈንታ ፈጣሪ ይወቀው፡፡ ለእምነቱ ትኩረት የማይሰጥ መብላት መጠጣት ብቻ ኑሮ የሚመስለው ትውልድ በጣም በዝቷል፡፡ እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ!” አሉ የተቀመጡት ሽማግሌ፡፡ መኪናው መናኸሪያ ደረሰና ሁሉም ተሳፋሪዎች ከመኪናው ወረዱ፡፡ ወጣቱ የልጁን አባት ተጠጋና “አባቴ ልጅዎን ጥሩ ምግባር ያስተምሩት፡፡ በነፍስ በሥጋ መጠቀም የሚችል በዚህ ሁኔታ አይደለም፡፡ እርስዎም እንዲህ አይነቱን መጥፎ ምግባር እንዲሠራ ማበረታት የለብዎትም፡፡ ልጅዎ አይደለም እንዴ? ልጅ እኮ ልጅ የሚሆነው ከሥር ከሥሩ ሲኮተኮት ነው፡፡ አገር የሚጠቅም ቤተሰብ የሚረዳ የሚሆነው ጥሩ ምግባር ሲይዝ ብቻ ነው፡፡ ከዚያ ውጭ ቀማኛ ወንበዴ ሆኖ ያለዕድሜው ይቀሰፋል፡፡ ስለዚህ ልጅዎን እንዲህ አይነት በባህላችን ያልተለመደ ነገር አያስተምሩት፡፡ ይህን ሁሉ የምልዎ እንዳይጎዱ በማዘን ነው ልጅዎም በረከት ረድኤት እንዲያገኝ ነው” አላቸው ወጣቱ፡፡ የልጁ አባት ግን ጆሮ የሰጡት አይመስሉም፡፡ ወጣቱ ተሰናበታቸው አባትና ልጅም አብረው ወደ ቤታቸው ሄዱ፡፡ ከብዙ ዓመታት በኋላ በመጥፎ ምግባር ያሳደጉት ልጃቸው በትምህርት ክፍያ ተጣላቸው፡፡ ልጁ በትምህርቱ ደካማ ስለነበር በነጻ የመማር ዕድል አላገኘም ነበርና “የትምህርት ክፍያ ክፈልልኝና በግል ልማር” ይላል አባቱን፡፡ አባቱም “ልጄ የቤታችንን ነገር እያወቅኸው እንዲህ ትላለህ? የምንበላው የምንጠጣው እየቸገረን እያለ አንተን ማስተማር እንዴት እችላለሁ? ከዚያስ እዚሁ አብረን እየሠራን ገንዘብ ስናገኝ ትማራለህ፡፡ የነጻ ትምህርት ዕድልም ልታገኝ ትችላለህ ትንሽ ታገስ፡፡” አሉት፡፡ ልጁ የሚሰማቸው አይመስልም “የግድ ነው ትከፍላለህ፡፡ እዚህ ቤት ውስጥ ከዚህ በኋላ መኖርም አልፈልግም፡፡ ቁጭ ብዬ እንዴት ነው የምውል ወይስ እርሻ እንዳርስልህ ፈልገህ ነው፡፡ እስከዛሬ ድረስ ተምሬ እንዴት ነው ካንተ ጋር በግብርና ሥራ የምበሰብስ” አለ አባቱን በማስፈራራት፡፡ አባቱም “ትሞታለህ እንጅ በግል አላስተምርህም፡፡ ገበሬ መሆን ከጠላህ እንደ ጓደኞችህ አታጠናም ነበር? ስታውደለድል ኖረህ ዛሬ ገንዘብ የምትጠይቅ ከየት ልወልድልህ ነው? ገንዘብ ተሠርቶ የሚገኝ እንጅ እንደ ቅጠል ተቆርጦ የሚመጣ አይደለም፡፡ ዳሩ ግን አንተ አይገባህ፡፡” አሉት ቆጣ ብለው፡፡ ልጁም ዱላ አነሣና አናታቸውን ፈነከታቸው አባትም ጮኹ ጎረቤት ተሰበሰበ፡፡ የሆነውን ሁሉ ለተሰበሰበው ጎረቤታቸው ተናገሩ እያለቀሱም “የኔ ነገር አይድረስባችሁ!” አሏቸው፡፡ ጆሮ ሰጥቶ የሰማቸው የለም “ድሮም አስተዳደጋቸው ስድ ነበር ይበላቸው የእጃቸውን ነው ያገኙ” እየተባባሉ ይንሾካሸካሉ፡፡ “ለማንኛውም ጤና ጣቢያ ይሂዱና ቁስሉ ይታሸግልዎ” አላቸው አንድ ጎረቤት፡፡ ደማቸውን እያዘሩ ጤና ጣቢያ ሄዱ፡፡ በወቅቱ የጤና ባለሙያ ሆኖ ያገኙት ከብዙ ዓመታት በፊት መኪና ውስጥ ብዙ የመከራቸውንና ከመኪና እንደወረዱም ልጃቸውን በሥርዓት እንዲያሳድጉ የነገራቸውን ወጣት ነው፡፡ ቁስላቸውን እያሸገ “ምን ሆነው ነው? ወድቀው ነው እነዴ?” አላቸው፡፡ “ኧረ የኔስ ጉድ ነው ለሰውም የሚነገር አይደለም፡፡ ልጄ ነው እንዲህ ያደረገኝ” አሉት እያለቀሱ፡፡ “አንድ ጊዜ መኪና ውስጥ ተነጋግረናል እንዴ? ጊዜው ትንሽ ረዘም ስላለ ዘነጋሁ መሰለኝ፤ ነው ተሳስቻለሁ ልበል” አለ የጤና ባለሙያው፡፡ “አዎ ተነጋግረናል፡፡ እኔ እንኳ አልረሳሁህም፡፡ የዚያን ጊዜማ ብዙ ነገር ብለኸኝ ነበር ያን ጊዜ ግን ምንም አልመሰለኝም ነበር፡፡ ይኸውልህ ዛሬ ራሴ ላይ ሲደርስ ተረዳሁት፡፡ ለካስ መቅጣት በሕጻንነት ዘመኑ ኖሯል፡፡ እኔ ሞኙ ልቅ አሳድጌ ዛሬ የሚያሳፍር ሥራ ሠራልኝ፡፡” አሉ ታካሚው፡፡ “ልጅን በሥርዓት ማሳደግ የሚጠቅመው ወላጁን ብቻ አይደለም ሀገሩን፣ ወገኑን፣ ቤተክርስቲያንን በሙሉ ነው፡፡ ለዚህም ነው ያን ያህል ብዙ ነገር ያልኩዎት፡፡ አሁን በራስዎ ሲደርስ አወቁት አይደል? እኔም ይህንን ፈርቼ ነበር ያለዕድሜዬ እርስዎን መካሪ የሆንኩት” አለ የጤና ባለሙያው፡፡ “ወይኔ! ያን ጊዜ ምክርህን ሰምቼ ኖሮ እንዲህ መች ጉድ እሆን ነበር፡፡ ብልጥ ከሰው ይማራል ሞኝ ግን ከራሱ ይማራል እንደሚባለው ሁሉ እኔ ሞኙ ከራሴ ተማርኩ፡፡” አሉ ሽማግሌው፡፡ የጤና ባለሙያው ቁስላቸውን አሽጎ ጨረሰና መድኃኒት ሰጣቸው፡፡ የመድኃኒቱንም አጠቃቀም አስረዳቸውና ተሰነባበቱ፡፡

Wednesday, July 30, 2014

ግልጥ ሥውር

“ኧረ የእንደሻው ነገር እንዴት ነው?” አለ አንድ የእንደሻው ጓደኛ፡፡ “የሰፈሩ ሰው ሁሉ ሥሙን ቀይሮታል እኮ” አለ ሌላኛው፡፡ “ማን አሉት?” አለ ለመስማት ጆሮውን እየኮረኮረ፡፡ “እንዴ! አልሰማህም ማለት ነው ግልጥ ሥውር እያሉ ነው የሚጠሩት” አለ፡፡ ሥሙን ከምን አንጻር እንደሰጡት የተረዳ ይመስላል፡፡ ራሱን ነቀነቀና “ልክ ነው ይህ ሥም ይገባዋል፡፡ እኛ በግልጥ ብናየው፣ አብሮን ቢውል፣ አብሮን ቢያወራ እርሱ ግን ሥውር ነው፡፡ የሚገርም ሥም! የተቃራኒ ቃላት ጥምርታ ግ-ል-ጥ-- ሥ-ው-ር” አለ ፊደላቱን አንድ በአንድ በቀስታ ረገጥ እያደረገ፡፡ ሌላኛው ተቀበለ “የሰፈሩ ሰዎች ሁሉ የሚጠሩት በዚህ ሥም ነው፡፡ እኔም እንደሰፈር አባልነቴ በዚሁ ነው የምጠራው፡፡ እንደሻውም አምኖበታል መሰለኝ አቤት ይለናል፡፡ ደግሞም እኮ ማንነቱን የሚገልጽ ትክክለኛና ተገቢ ሥም ነው፡፡ ይህን ሥም ያወጣለትን ሰው ባጣም አድንቄያለሁ፡፡ እንደሻው ማለት እኮ እንደፈለገው፣ እርሱ እንዳለ፣ እንደፍላጎቱ በፈለገው አቅጣጫ የሚሄድ፣ የፈለገውን ሁሉ የሚያደርግ እንደማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከሥራው ጋር በፍጹም የሚገናኝ ሥም አይደለም፡፡ ግልጥ ሥውር ያሉትም ሥራውን አይተው ይመስለኛል፡፡ እኔም ብሆን የተቃራኒ ቃላትን ጥምርታ የያዘ ሥም አይሁን እንጅ ሥም ባወጣለት ደስ ይለኝ ነበር፡፡ እንደሻው ብዬ ለመጥራት እሰቀቅ ነበር፡፡ ሥራው ሌላ ሥሙ ሌላ ነው የነበረው፡፡ ይህ አዲስ ሥም ግን የሚገባው ነው” አለ፡፡ ራሱን ነቀነቀና ጣቱን አፋተጋቸው “በጣም ይገባዋል እንጅ፡፡ ጫማ ቢሰፋ፣ ጸጉሩ ቢንጨፈረር፣ ሱሪው ቢተለተልም በልቡ ያለው ንጹህ እምነት ሥውር አድርጎታል፡፡ ይገርምሃል ጫማ ሲሰፋ ውሎ ያገኘውን ገንዘብ ትንሽ ሳያስቀር ለነዳያን እና ለቤተክርስቲያን ይሰጣል፡፡ ይህን ሥራውን ለማንም አይነግርም፡፡ እኔ ራሱ አንድ ቀን ነው ይህን ያረጋገጥኩ፡፡ ያገኘውን ገንዘብ ሁሉ መጽውቶ ሆቴል ለምኖ ትርፍራፊ ተመግቦ ያድራል፡፡ ይህ ብቻ በራሱ ሥውር አያሰኘውም እንዴ ሌላው የጽድቅ ሥራው እንኳ ቀርቶ፡፡” አለ፡፡ በንግግሩ የተስማማ ሌላኛው ቀጠለ “ልክ ነህ፡፡ እኔስ ይህም ያንሰዋል ባይ ነኝ፡፡ ሰው ሁሉ የሚያየው ጫማ ሰፍቶ ገንዘብ ተቀብሎ በኪሱ ሲያስገባ ነው እንጅ ገንዘቡን ሲመጸውት አይደለም፡፡ ይህን ተግባሩን በሥውር ነው የሚያደርገው፡፡ በጸጉሩ መንጨፍረር ስንቱ ከሰው በታች ይቆጥረዋል መሰለህ፡፡ ጫማ የሰፋለት ቀለም የቀባለት ሰው ሁሉ የጸጉርህ መስተካከያ ይሁንህ እያለ ገንዘብ ትቶለት ይሄዳል፡፡ እርሱ ግን ያው ነው አይስተካከለውም፡፡ አሁን ሲገባኝ ነው እኔም ጸጉርህን ተስተካከለው ማለቴን ያቆምኩ፡፡ በዚህ ሁሉ ያገኘውን ገንዘብ ለድሆች ይመጸውተዋል፡፡ አየኸው ሥውርነቱን፡፡ ይህን ሥውርነቱን የምናውቅ እኔና አንተ ብቻ ነን፡፡ የሰፈሩ ሰው ይህን ሥም የሰጠው በቤቱ ውስጥ ባለው አልጋ ነው፡፡” ሌላኛው ንግግሩን አቋረጠውና “ይቅርታ በማቋረጤ እንጅ አልጋው ደግሞ ምን ተአምር ሠራ ነው የምትል?” አለው፡፡ ንግግሩን ካቆመበት ቀጠለ “አንድ የሰፈሩ ሕጻን በቤቱ በር ቀዳዳ አጮልቆ እንደሻው ወደ አልጋው ሄዶ አልጋዬ በይ ደህና ሁኝ አንች ላይ በምቾት ማደርን አልፈልግም፡፡ የሚያድርብሽን ሰው ስትራቢ ትኖሪያለሽ እንጅ በፍጹም አላድርብሽም፡፡ አንች ለሥጋዬ እንጅ ለነፍሴ ምንም ጥቅም የለሽም፡፡ ብሎ አልጋውን ተሰናብቶ ወደ ሳሎን ተመልሶ ከወለሉ ላይ በሰላም አሳድረኝ ብሎ ሲተኛ በተደጋጋሚ እንደተመለከተው ለሰፈሩ ሰዎች ያወራል፡፡ እርሱ ግን ይህን ሁሉ አልሰማም፡፡ ወዲያውም ግልጥ ሥውር የሚለውን ሥም ሰጡት፡፡ ያ የሚያምር አልጋው እኮ ለማንም የሚታይ ግልጥ ነው፡፡ እንደእኛ አስተሳሰብም አልጋ ለመኝታ የተሠራ ስለሆነ ተኝቶ እንደሚያድርበት ነበር የምንረዳው፡፡ ነገር ግን ግልጥ የሆነውን እርሱ ሠውሮታል፡፡ አይተኛበትማ!!!” አለ፡፡ ሌላኛው ንግግሩን ቀጠለ “እርሱ እኮ በጣም የተለየ ፍጡር ነው፡፡ ከእኛ መካከል ማንም የማያደርገውን የቅድስና ሥራ ነው እኮ የሚሠራ፡፡ ጾሙ፣ ጸሎቱ፣ ስግደቱ፣ ምጽዋቱ ቀላል መሰለህ እንዴ? እርሱ ግን እንደማይጾም፣ እንደማይጸልይ፣ እንደማይሰግድና እንደማይመጸውት ነው የሚናገረው፡፡ ባለፈው እንዲያውም ጸሎት ማለት ምን ማለት ነው ብሎ ጠይቆኛል፡፡ በጣም ይገርምሃል እኮ! የቅድስናሥራውን ሁሉ ሠውሮ ነው የሚኖረው፡፡ ታዲያ ይህን ግልጥ ሥውር ቢሉት ያንሰዋል እንጅ ይበዛበታል እንዴ? ባለፈው ደግሞ በአጋጣሚ ልብሱን ነፋስ ሲገረባው ጉድ አየሁ፡፡ ወገቡን በሰንሰለት አስሮ ነው ለካ ጫማ የሚቀባና የሚሰፋ፡፡ በጣም ተደንቄ እርሱንም ምንድን ነው ብዬ አልጠየቅሁትም፡፡ ሁሉም ነገር ሲገባኝ ገና ዛሬ ማውራቴ ነው፡፡” ሌላኛው ቀጠለ “እኛ ከእንደሻው ብዙ ነገር መማር አለብን፡፡ ነጠላ ለብሰን ቤተክርስቲያን ስለተመላለስን ብቻ ራሳችንን እንደጻድቅ እየቆጠርን አይደል እንዴ ያለነው? የእርሱን ሥራ ያህል መሥራት ባንችል እንኳ ብዙ የጽድቅ ሥራ ማንም ሳያውቅብን በሥውር ልንሠራ እንችላለን፡፡ እንደሻውን እኮ እንኳን ይህን ያህል የጽድቅ ሥራ ይሠራል ለማለት ቀርቶ በሥም ያውቃቸዋል ብሎ የሚገምተው ሰው የለም፡፡ ሰው የሚያየው በግልጥ ያለውን አለባበሱን ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ከእርሱ ልንማር ያስፈልጋል፡፡ በከንቱ ውዳሴ ስንቱ ያልሠራውን የቅድስና ሥራ እንደሠራ አስመስሎ ይናገራል መሰለህ፡፡” አለ፡፡ ሌላኛው ቀጠለ “ልክ ነህ፡፡ እኛም ቢሆን ከከንቱ ውዳሴ ርቀን የቅድስና ሥራዎችን በሥውር ልንሠራ ይገባናል፡፡” አለ፡፡ በዚህ ሃሳብ ተስማሙ፡፡ የቅድስና ሥራዎችንም በሥውር ሊሠሩ ለየግላቸው ቃል ገቡ፡፡ ከንቱ ውዳሴ ተገቢ እንዳልሆነ ተነጋግረው የጽድቅን ሥራ በሥውር ሠርተው ግልጥ የሆነውን በረከት ለመቀበል እና “ግልጥ ሥውር” ተብለው እንዲጠሩ የሚያደርገውን የጽድቅ ሥራ ለመሥራት ወስነው ተለያዩ፡፡

የሰበካና የሰበቃው ታሪክ

በአንድ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ሰበካ እና ሰበቃ የተባሉ ሰዎች ነበሩ፡፡ የእነዚህ ሁለት ሰዎች የሁልጊዜ ተግባር ጭቅጭቅና ንትርክ ነው፡፡ በጠረንጴዛ ዙሪያ ተወያይተው በሦስተኛ አካል ተሸምግለው እንኳ ሥምምነት ላይ መድረስ ቀርቶ የሥምምነቱን ጉዞ መጀመር አይችሉም፡፡ አንድ ቀን እጅግ በጣም የተፋፋመ ጠብ ጀመሩ፡፡ ጎረቤት ሰማ፡፡ ሊያስማሟቸው በጠረንጴዛ ዙሪያ ተሰበሰቡ፡፡ “ልማደኛ” አለ ሰበካ፡፡ ሰበቃ ሊደባደብ ተነሣ ተገለገለ፡፡ “ግሩም ነው! ይህን ያህል ዘመን አብራችሁ ስትኖሩ እንዲህ ያለ ነገር አይታዎቅባችሁም ነበር፡፡ አሁን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የምናየው ነገር ተለውጧል፡፡ ለጎረቤት ሳይቀር አስቸገራችሁ እኮ!” አሉ አንድ የጎረቤት ሽማግሌ፡፡ “እስከ አሁንማ ከጊዜ ጊዜ ይሻሻላል በሚል በትዕግሥት ነበር የቆየሁት፡፡ ነገር ግን ሊሻሻል አልቻለም፡፡ ከወንበርህ ውረድ እኔ ያንተን ቦታ ልቀመጥበት አለኝ ጭራሽ፡፡ አንተ ሥራህን አቁም እኔ አዲስ አሠራር አለኝ ብሎ ጮኸብኝ፡፡ የቤታችን አሠራር እና የአኗኗር ሥርዓት በአዲስ መልኩ በዘመናዊ አኗኗር ዘይቤ ሊቀየር ይገባዋል አለኝ፡፡ በአሮጌ ሕግና ሥርዓት በአሮጌ ትምህርት እስከመቼ እንኖራለን? ከሥር ከመሠረቱ ጀምሮ ለቤታችን አዲስ ለውጥ ሊኖረው ይገባል፡፡ እያለ ብዙ ጊዜ ይጠይቀኛል፡፡ እኔ ግን አባታችን በሠራልን ቤት የሠራልንን ሥርዓት አክብረን እርሱ በሄደበት መንገድ ሄደን በወጣበት ወጥተን በገባበት ገብተን መኖር እንደሚገባን መከርኩት ሊመለስ ግን አልቻለም፡፡” አለ ሰበካ፡፡ “ከየት ወደ የት ነው የምመለሰው አሁንም ቢሆን አቋሜ ያው ነው፡፡ አባታችን የሠራልን ቤት እና ሥርዓት እንደእኛ የአኗኗር ዘይቤ ሙሉ በሙሉ መለወጥ ያስፈልገዋል፡፡ የእርሱ ሥርዓት ለዘመናዊነት የተመቸ በፈለግሁት ወጥቼ በፈለግሁት የምገባበት አይነት አይደለም፡፡ ስለዚህ ልንቀይረው ያስፈልጋል፡፡ ቆዩ ግን እስከመቼ ድረስ ነው ባረጀ እና ባፈጀ ቤት ያረጀ እና ያፈጀውን ሥርዓት፣ ሕግና ትምህርት እየተከተልን የምንኖረው?” አለ ሰበቃ፡፡ “ኧረ ተው ልጅ ሰበቃ ለጆሮ የሚሰቀጥጥ ንግግር አትናገር” አሉ የጎረቤቱ ሽማግሌ፡፡ “ምኑ ነው ለጆሮ የሚሰቀጥጠው? አንድ በድሮ ጊዜ የተፈጠረ ሰው በሠራው አሠራር ዛሬ ላይ ሆኜ ልኖርበት እንዴት እችላለሁ፡፡ ትናንት ሌላ ቀን ነበር ሥርዓቱም ሌላ ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ ከትናንት የተለየ ቀን እንደሆነ ሁሉ ልዩ ሥርዓት ያስፈልገናል፡፡ ልተዳደር ልመራ የሚያስፈልገውም ዛሬ ላይ በሚሠራ በተስማማሁበት ሥርዓት፣ ሕግና ትምህርት እንጅ አንድ አካል ባስቀመጠው ሥርዓት፣ ሕግና ትምህርት ሊሆን አይችልም፡፡” አለ ሰበቃ፡፡ “ይቅር ይበልህ፡፡ አባታችን የሠራው ሥርዓት እኮ ልጆቹ እንድንኖርለት እንጅ እንድንጠፋበት አይደለም፡፡ ትናንት ሌላ ቀን ዛሬ ደግሞ ሌላ ቀን ቢሆንም እንኳ የቤታችን መተዳደሪያ ሥርዓት፣ ሕግና ትምህርት ግን ቅንጣት ታህል እንዲሻር እንዲለወጥ አልሻም፡፡ ሥርዓት፣ሕግና ትምህርት አልባ በመሆን ቤታችንን ማንም ሲቀልድበትና ሲፈነጭበት ማዬት አልፈልግም፡፡ እንዲህ ከሚሆን ለቤታችን መሞትን እመርጣለሁ፡፡” አለ ሰበካ፡፡ ሽማግሌው ከሃሳብ ባሕር ወጥተው ጉሮሯቸውን ሞረድ ሞረድ አድርገው ንግግራቸውን ቀጠሉ፡፡ “ልጅ ሰበካ ጥሩ ብለሃል፡፡ የአባታችሁ ቤት የወንበዴ ዋሻ ሲሆን ማዬት እንዴት ያስችላል? ሥርዓቱ፣ ህጉና ትምህርቱ ተቀይሮና ተበርዞ ማንም ቤቱን ሲፈነጭበት መመልከት ልጅ የሚለውን ሥም ያሳጣል፡፡ አባታችሁ ሕግና ሥርዓቱን ከትምህርት ጋር የሰጣችሁ እኮ ቤቱንና የቤቱን ኗሪዎች ለመጠበቅ እንጅ ለውጭ ጠላት አሳልፎ ለመስጠት አይደለም፡፡ በዚህ ቤት ውስጥ እየኖራችሁ ሕግና ሥርዓቱን እናፍርስ ማለት ያሳፍራል፡፡ በቤቱ ለመኖር የቤቱን ሕግና ሥርዓት መከተል የግዴታዎች ሁሉ ግዴታ ነው እኮ፡፡ አባታችሁ ቤታችሁን ያጠረው ጠላት እንዳይነጥቃችሁ፣ ማንም ቤታችሁ ውስጥ እየገባ ቤታችሁን እንዳያቆሽሽባችሁ እንጅ እናንተ ቤታችሁን እንድትጠሉ ለማድረግ አይደለም፡፡” አሉ ሽማግሌው፡፡ “ምን እያሉ ነው! በቤቱ ለመኖር የቤቱን ሕግና ሥርዓት ማክበር ሳይሆን የየግላችንን ሕግና ሥርዓት ልንከተል ያስፈልጋል፡፡ የቤቱ ሥርዓት እኮ ዛሬን ያላገናዘበ ለትናንት ብቻ የወጣ ነው፡፡ መብላትና መጠጣት በፈለግሁ ጊዜ ካልበላሁና ካልጠጣሁ የእኔ መኖር ምኑ ጋር ነው? እንዳልበላና እንዳልጠጣ ጹም የሚል የቤቱ መመሪያ አለ፡፡ እኔ የምፈልገው ማድረግ የሚገባኝን ሁሉ እየሠራሁ መኖር ብቻ ነው፡፡ ምንም አይነት አጥር እንዲኖርብኝ አልፈልግም፡፡ የቤቱ ሕግና ሥርዓት በጣም ይከብዳል፡፡ አሁንም ቢሆን ሊቀየር ይገባዋል፡፡ በየግላችን ሕግና ሥርዓት እየተመራን በአንድ ቤት መኖር አንችልም እንዴ?” አለ ሰበቃ፡፡ “የቤታችን ሕግና ሥርዓት ሰበካ ወይም ሰበቃ ስላልተመቻቸው የሚቀይሩት ተራ ሕግ አይደለም፡፡ ይህ ሕግና ሥርዓት ስንፈልግ ሆ ብለን ወጥተን የምንሽረው ወይም በእጅ ብልጫ የምናሻሽለው ሳይሆን ለመኖር የምናከብረው ነው፡፡ የቤቱም አባል ሆኖ ለመቀጠል በቤቱም ለመኖር የግድ የምንጠብቀው ነው፡፡ ይህን ሕግና ሥርዓት ከበደኝ የሚል ሰው ቤቱን መልቀቅ እንጅ በቤቱ ተቀምጦ የመኖሪያ ሕግና ሥርዓቱን መጣስ እንደፈለገው መለወጥ ማሻሻል መብት የለውም፡፡ አባታችን አውጥቶ አውርዶ ከእግዚአብሔር ጋር ተመካክሮ ያወጣው ደገኛ ሕግ ነው እኮ ሰበቃ! ትናንትን ብቻ አስቦ ሳይሆን ዛሬን ነገን ጭምር አስቦ ነው ሕግና ሥርዓቱን የሠራልን፡፡ ለአንተ እንዲከብድ ለሌላው እንዲቀል ሆኖ የተዘጋጀ አይደለም ለሁሉም የቤቱ ኗሪ እኩል የተሰጠ ነው እንጅ፡፡ ታዲያ አንተ ሕግና ሥርዓቱ የከበደህ ላንተ ምን የተለየ ነገር ኖሮ ነው? የቤታችንን ሕንጻ ብንቀይረው እንኳ ሕግና ሥርዓቱ ግን አይቀየርም፡፡ ወደድንም ጠላንም በቤቱ እስከኖርን ድረስ የቤቱን ሕግና ሥርዓት መጠበቅ ግዴታ ነው፡፡ የቤቱ ሕግና ሥርዓት የከበደው ቤቱን መልቀቅ እንጅ በቤቱ እየኖረ ሌላ አዲስ ሕግና ሥርዓት አውጥቶ አብሮ ሊኖር አይችልም፡፡ በአንድ ቤት እያለን የተለያየ ሕግና ሥርዓት ይኑረን ማለት የማይታሰብ ነው፡፡ በአንድ ቤት ውስጥ ሁለት የተለያዩ ህጎች ኖሩን ማለት እኮ አንዱ ሲዘጋ ሌላው ይከፍታል፤ አንዱ ሲከፍት ሌላው ይዘጋል፡፡ እንዱ ሲያጸዳ ሌላው ያቆሽሻል፤ አንዱ ሲያቆሽሽ ሌላው ያጸዳል፡፡ አንዱ ሲጠግን ሌላው ያፈርሳል፤ አንዱ ሲያፈርስ ሌላው ይጠግናል፡፡ አንዱ ሲያጥር ሌላው ይጥሳል፤ አንዱ ሲጥስ ሌላው ያጥራል፡፡ አንዱ ሲበላ ሌላው ይጾማል፤ አንዱ ሲጾም ሌላው ይበላል፡፡ አንዱ ሲተኛ ሌላው ይነሣል፤ አንዱ ሲነሣ ሌላው ይተኛል፡፡ አንዱ ሲቀመጥ ሌላው ይቆማል፤ አንዱ ሲቆም ሌላው ይቀመጣል፡፡ አንዱ ሲያበራ ሌላው ያጠፋል፤ አንዱ ሲያጠፋ ሌላው ያበራል፡፡ አንዱ ሲስቅ ሌላው ያለቅሳል፤ አንዱ ሲያለቅስ ሌላው ይስቃል፡፡ አንዱ ሲጎዳ ሌላው ይጠቀማል፤ አንዱ ሲጠቀም ሌላው ይጎዳል፡፡ አንዱ ሲሠራ ሌላው ይቀመጣል፤ አንዱ ሲቀመጥ ሌላው ይሠራል፡፡ ማለት ነው እኮ፡፡ ስለዚህ ሁለት የሚቃረኑ ህጎች አንድ ቤት ውስጥ ሊኖሩ አይገባቸውም፡፡ አንድ ቤት ውስጥ እንዲህ የማይስማሙ ህጎችና ሥርዓቶች ሊኖሩ እንዴት ይቻላል? አንድ ቤት ስንት ሕግና ሥርዓት ሊኖረው እንሻለን? አንድ ቤት አንድ ሕግና ሥርዓት ብቻ ነው ሊኖረው የሚገባ፡፡ የዚያ ቤት ሕግና ሥርዓት የማይስማማው ደግሞ ያን ቤት መልቀቅ እንጅ ሌላ ሕግና ሥርዓት መፈለግ የለበትም፡፡ በአባታችን ሕግ እመራለሁ ያለ ብቻ በዚህ ቤት ይኖራል፡፡ ከዚያ ውጭ የራሴን ሕግ በዚህ ቤት ውስጥ አራምዳለሁ ማለት ግን ደም እስከመፋሰስ የሚያደርስ ከባድ ጉዳይ ነው፡፡ ቤቱን መልቀቅ ያልፈለገ የቤቱን ሕግና ሥርዓት መከተል ግዴታው ነው፡፡” አለ ሰበካ ቆጣ ባለ ንግግር፡፡ ሽማግሌው በደስታ ተሞልተው “ያሳድግህ! ለቁምነገር ያድርስህ! በዚህ ቤት እስከ ፍጻሜህ ለመኖር ያብቃህ! ልክ ነው ምድር ጠብ የማይል ቁም ነገር ነው ልጅ ሰበካ የተናገረው፡፡ ሁለት የተለያዩ ህጎችና ሥርዓቶች በአንድ ቤት ውስጥ በፍጹም መስማማት አይችሉም፡፡ ጨለማና ብርሃን፣ ጣዖትና ታቦት፣ ኃጢአትና ጽድቅ፣ ሐሰትና እውነት አንድ ላይ እንዴት ተባብረው መኖር ይቻላቸዋል? ጨለማ ከሆንን ብርሃን ልንሆን አንችልም፡፡ ሌላውንም እንደዚሁ፡፡ ስለዚህ ትክክለኛው መፍትሔ በቤቱ ሕግና ሥርዓት የማይመራ ሰው ሁሉ ቤቱን ለቅቆ የራሱን ቤት መሥራት ብቻ ነው፡፡ ሕግና ሥርዓቱ ሳይመቸው ማንም ቢሆን በግድ በዚህ ቤት ውስጥ መኖር አለብህ የሚል አካል የለም ሊኖርም አይገባው፡፡” አሉ ሽማግሌው፡፡ ሰበቃ ልቡ ተረበሸ፡፡ በቀላሉ ይቀበሉኛል የሚል አመለካከት ነበረው ሊሆን ግን አልቻለም፡፡ አሁን የወሰነ ይመስላል፡፡ “በቃ ተቀብያችኋለሁ፡፡ የምትሉት ሁሉ ልክ ነው፡፡ አሁን የሕግና የሥርዓቱ ጉዳይ በትክክል ገብቶኛል፡፡ ባለማዎቅ የቤታችን ሕግና ሥርዓት ይታደስ ማለቴ ጥፋት ነበር፡፡ ስለዚህ በቤቱ ሕግና ሥርዓት እየተመራሁ በዚሁ ቤት መኖርን መርጫለሁ፡፡” አለ ሰበቃ፡፡ “ተባረክ! እግዚአብሔር ያሳድግህ! ለቁም ነገር ያብቃህ!” አሉ ሽማግሌው በሰበቃ መመለስ ተደስተው፡፡ ሰበቃ ግን ይህን ያለበት የራሱ ዓላማ ነበረው፡፡ ቤቱን ለቅቆ ሌላ ቤት ከሠራ በኋላ ወደዚህ ቤት ቢመለስ እንደፈለገው በቤቱ ላይ የማዘዝ ሥልጣን የለውም፡፡ ስለዚህ በዚሁ ተቀምጦ የቤቱን ሕግ ያከበረ መስሎ በራሱ ሕግ መኖርን መርጦ ነው የተመለሰ የመሰለው፡፡ የተመለሰ ስለመሰላቸው በቤቱ እንዲኖር ፈቀዱለት፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ ሰበቃ የአባቱን ቤት ንብረቶች ቀስ በቀስ አውጥቶ መሸጥ ጀመረ፡፡ በዚህ ጊዜ ሰበካ “ከቤቱ ውጣ! አንተን እሹሩሩ እያልኩ የአባቴን ንብረት የቤቱን ልዩ ሃብቶች አውጥተህ ስትጨርሳቸው ማዬት አልፈልግም፡፡ የተመለስክ የመሰልከው ለዚህ ነው አይደል?” አለ ሰበካ የመጨረሻ ውሳኔ መሆኑን ለማሳዬት፡፡ ሰበቃ እንደተነቃበት ስላወቀ የአባቱን ቤት ሕግና ሥርዓት ትቶ የራሱን ቤት መሥርቶ ለመኖር ከቤቱ ኮበለለ፡፡ ነገር ግን ያሰበው ሳይሳካ ከአባቱ ቤት በወጣ በዓመቱ በከፋ አደጋ ሞተ፡፡

የዓለም ባሕር

አዳምና ሔዋን ትዕዛዝ አፍርሰው ሕግ ጥሰው ከጸጋ ልብሳቸው ከተራቆቱ በኋላ ስቃይና ፍዳ ወደበዛባት ምድር እንዲወርዱ ተፈርዶባቸው ፈተና ወደበዛባት ዓለም ቢመጡም በልቡናቸው የሚቀጣጠለው የእግዚአብሔር ፍቅርና የገነት ሰላማዊ ኑሮ ህሊናቸውን ስለነሣ ው "አጥፍተናል በድለናል ይቅር በለን ማረን ራራልን " እያሉ በትሕትና ሆነው በጸሎት ቢተጉም የበጎ ሥራ ጠላት የሆነ ዲያብሎስ በእባብ ተሰውሮ እንዳሳታቸው የብርሃን መልአክ መስሎ "ቅዱስ ገብርኤል ነኝ እግዚአብሔር ጸሎታችሁን ሰምቷል " በማለት ጸሎታቸውን እንዲያቋርጡ አድርጓቸዋል፡፡ አዳም የብርሃን መልአክ መስሎት ሲከተለው መልኩን ቀይሮ ከመንገድ ላይ በድንጋይ ፈንክቶ ያፈሰሰውን ደም ወደ እግዚአብሔር ቢረጭም የእርሱ ደም ለዓለም ሁሉ መድኃኒት ስለማይሆን ለሰው ልዩ ፍቅር ያለው አምላክ ከ5500 ዘመን በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ፣ በመስቀል ተሰቅዬ፣ ደሜን አፍስሼ፣ ሥጋዬን ቆርሼ፣ ሞቼ፣ ተነሥቼ አድንሃለሁ የሚለውን የተስፋ ቃል ስለሰጠው ይህን ተስፋ በትዕግሥት ሲጠብቅ ኖሮ ኢየሱስ ክርስቶስ ከድንግል ማርያም ተወልዶ ሥጋን ለብሶ መድኃኒት መስቀል ቀራንዮ በተተከለ ጊዜ ተፈጽሞለታል፡፡ለመግቢያነት ይህን ያህል ካልን ወደ ዋናው ርእሳችን እንግባ፡፡ በዓለም ባሕር ውስጥ ሰይጣን ጥቁር ብቻ ስለሚመስለን የብርሃን መልአክ መስሎ ሲመጣ እንታለላለን፡፡ የዲያብሎስ መገለጫ የሆኑ መልኮችን በዓለም ባሕር ውስጥ ከሰው ልጅ ኑሮ ጋር ያለውን ቁርኝት እንመልከት፡፡ ዲያብሎስ በአንድ ወቅት በሰው አምሳል ተገለጠልኝ አብረን ስንጫወት ከቆየን በኋላ "አቤት ሙቀት" ሲለኝ እኔም እንደእርሱ እንዴ ! እንዴት ይሞቃል ባክህ አልኩ፡፡ እርሱም በአቅራቢያችን ካለ ትልቅ ባሕር ሄደን መዋኘት እንዳለብን ስለገፋፋኝ በሐሳቡ ተስማምቼ ወሬዬንና ወጌን እየቀጨሁ አብሬው መክነፍ ጀመርሁ፡፡ ከባሕሩ እንደደረስን የነካኝን ሳላውቀው ፈጥኜ ልብሴን አውልቄ ከባሕሩ ዘልዬ ስገባ እርሱ ግን ቆሞ በፌዝ ዓይን ይመለከተኝ ነበር፡፡ ዘለህ ግባና አብረን እንዋኝ ስለው "ዋና ስለማልችል ሌላ ዋና የሚችል አመጣልሃለሁ አንተ ግን እንዳትወጣ ስትዋኝ ቆይ" ብሎኝ ሄደ መጀመሪያ ዋና የሚችል መስሎ የመዋኘትን ሃሳብ ያቀረበ እርሱ መሆኑን ዘንግቶ፡፡ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ከባሕሩ ሳለሁ በርካታ ዋናተኞችን አምጥቶ ባሕሩን አጨናነቀው፡፡ በመዋኘት ላይ ሳለሁ ዋና ያስጀመረኝን ከዋናተኞች መካከል ፈልጌ በጭራሽ ላገኘው ባለመቻሌ አዲስ የመጡ ዋናተኞችን የት እንደሄደ ብጠይቃቸው እነርሱም የሄደበትን እንዳላወቁ መለሱልኝ፡፡ በዓለም ባሕር እየዋኜን ሳለ ቅጠሏ የለመለመች "ጫት" የምትባል ዛፍ ለእንስሳት የተፈጠረች መሆኗን ብናውቅም እኛም እንደ እንስሳት ልናላምጣት ዋናተኞች በሙሉ ድምጽ ስላጸደቅነው ቅጠሏን እንደ ፍየል ማላመጥ ጀመርን፡፡ አረንጓዴ ልብስ የለበሰ እርሱ ሳይበላ "ብሉ" እያለ ቅጠሏን ለዓይን የምትማርክ አድርጎ የሚያቀርብልን ሰው በመካከላችን አለ፡፡ ቅጠል መብላቴን ባላቆምም ሳይበላ የሚያበላን ዋና ያስጀመረን ሊሆን እንደሚችል ገመትኩ፡፡ ያ አረንጓዴ ልብስ የለበሰ ሰው ወዲያውኑ "የወረቀት ጥቅል ለምን አንጨምርበትም? ቅጠል ብቻውን እኮ ዋጋ የለውም" አለን፡፡ እኛም አዲስ የሆነውን "ሲጋራ" የተባለ የወረቀት ጥቅል ለመጠቀም በመስማማታችን አጠቃቀሙን እንዲያስረዳን በጠየቅነው ጊዜ ክብሪት አምጥቶ በእሳት ለኩሶ ጢሱን ወደ ውስጥ ከማገ በኋላ በአፍንጫው የፋብሪካ ጢስ ሲያስመስለው ያንን ለመፈጸም በመጓጓት ሲጋራ የተባለውን የወረቀት ጥቅል ሁላችንም በእሳት አያይዘን በከንፈራችን መካከል ይዘን በጋራ የደመራ ጢስ እስኪመስል ድረስ አትጎለጎልነው፡፡ ከዚህ በኋላ ከጫት ጋር የሁልጊዜ ሥራችን አድርገን አፋችንን ምድጃ አፍንጫችንን የጢስ መውጫ በማድረግ አብሪ ትል መስሎ መኖርን ተያያዝነው፡፡ ሳያደርግ የሚያስደርገን ልማደኛ ዛሬ ደግሞ ጫቱን በእጃችን ሲጋራውን በኪሳችን አስይዞ ራቁታቸውን የሚደንሱ ሴቶች ካሉበት ደብዛዛ ክፍል መርቶ አስገባን፡፡ በዚህ ክፍል ልክ የሌለው ሳቅ፣ ጫጫታ፣ መዳራት ወዘተ… የበዛበት ከመሆኑም በላይ በመጠጥ ብዛት አእምሯቸውን የሳቱት በዝሙት አልጋ የሚጋደሙበት ልዩ ትዕይንት የሚስተናገድበት ነው፡፡ በዓለም ባሕር ውስጥ ዋና ያስጀመረን ሰው የክፍሉ መጠሪያ "ጭፈራ ቤት" ይባላል ካለን በኋላ ልዩ ነው ያለውን "ቢራ" የሚባል መጠጥ በተቀመጥንበት ወንበር ደርድሮ "ጠጡ!" በማለት ራሳችንን እስክንስት ካጠጣ በኋላ ከሴቶች ጋር በዝሙት አልጋ ላይ አጋደመን፡፡ ይህን ሥራ ከጫትና ሲጋራ ጋር በማስተባበር ለብዙ ዘመናት ሥሙ በውል በማይታወቅ ማኅበር ተደራጅተን ቀን በጫትና በሲጋራ ማታ በቢራ፣በጭፈራና በዝሙት ቀናትን ልናሳልፍ በሙሉ ድምጽ ተስማምተን ለዚህ ሥራ ማስፈጸሚያ በጀት አስፈላጊ በመሆኑ "ስርቆት" የሚባል አዲስ ሥራ መፍጠር እንዳለብን የማኅበራችን ሊቀ መንበር ስላስጠነቀቀን በጀት በሚገኝበት ዙሪያ ለመምከር የስብሰባ ቀን ወስነን ተለያየን፡፡ በቀጠሯችን ተገናኝተን ስንወያይ ከመካከላችን አንዱ "አቶ ከበደ ተሰማ የተባለ ብዙ ገንዘብ ያለው ነጋዴ በከተማችን ስላለ ዛሬ ሰው ሁሉ በሚተኛበት ሌሊት 9፡00 የቤቱን ቁልፍ ሰብረን በመግባት ስርቆት የተባለ ሥራችንን መጀመር አለብን፡፡" ሲል ሁላችንም በጭብጨባ ድጋፋችንን ስንገልጽለት ሊቀመንበራችን በእንቅልፍ እንዳንሸነፍ ቀን ተኝተን ውለን አስፈላጊ መሣሪያዎችን ይዘን ከምሽቱ 3፡00 እንድንገናኝ ማሳሰቢያ ሰጥቶን በሰዓቱ ለመገኜት ወስነን ተለያየን፡፡ በሥምምነታችን መሠረት ከምሽቱ 3፡00 ተገናኝተን ሲጋራችንን እያጤስን በሊቀመንበራችን መሪነት ወደ አንድ መጠጥ ቤት ገብተን መጠጣት ጀመርን፡፡ ልክ 6፡00 ሲሆን መጠጥ ቤቱ ሊዘጋ በመሆኑ "ውጡ!" ተብለን ወደ አንድ ጨለማ ቦታ ተቀምጠን ስለ 9፡00 ሥራችን በጥልቀት እየተወያየን ሳለ አንድ ነጭ ልብስ የለበሰ ወፍራም ሰው በአጠገባችን ሲያልፍ ገንዘብ የያዘ ስለመሰለን ስብሰባ አቋርጠን ለቁልፍ መስበሪያ በያዝነው መዶሻ አናቱን ብለን ከገደልን በኋላ ብንፈትሽ ምንም ገንዘብ ባለማግኜታችን እየተሳሳቅን ወደ ስብሰባችን ተመልሰን የሥራ ክፍፍል በማድረግ ሰዓቱ 8፡45 ሲሆን ጉዟችን ወደ አቶ ከበደ ተሰማ ሱቅ አደረግን፡፡ ከሱቁ እንደደረስን ቁልፉን ለመስበር የተመደቡ አባላት ቁልፉን ሰብረው ገንዘብ በርባሪነት ላይ የተመደቡት ገንዘብ በመፈለግ ላይ ሳሉ አቶ ከበደ ተሰማ ስለነቃ ለመጮኽ ሲሞክር በያዝነው ሽጉጥ አናቱን ብለን ገደልነው፡፡ መሸከም እስኪሳነን ድረስ ብዙ ንብረት ይዘን ወደ ቤታችን ከተመለስን በኋላ ለመካፈል በመስማማታችን ለአባላቱ በሙሉ እኩል ተካፍለን እንደጨረስን ከአቶ ከበደ ተሰማ ቀብር ሄደን የአዞ እንባችንን ስናፈስ ውለን ባለቤቱን ያጽናሽ ብለን ተሰናብተን ተመለስን፡፡ ለተወሰኑ ቀናት እንደጨፈርንበት ገንዘቡ በማለቁ ከሊቀ መንበራችን አስቸኳይ የስብሰባ ጥሪ ደረሰን ሁሉም የማኅበሩ አባላት ተሰበስብን ሳለ ሊቀመንበራችን "ሽብር የሚባል ገንዘብ ማግኛ ዘዴ ስላለ በገንዘብ ማጣት አትዘኑ" ብሎ ሲያጽናናን በጣም ተደሰትን፡፡ እኛም "ሽብር" የተባለውን እንዴት መፈጸም እንደምንችል ከሊቀመንበራችን ዝርዝር ገለጻ ከተቀበልን በኋላ ከትልቅ ገበያ ሄደን በተለያዩ በርካታ ቦታዎች ላይ ቦንብ በመጣል "ሽብሩን" ጀመርን፡፡ ልክ ቦንቡን እንደጣልነው ገበሬ ማሩን፣ ቅቤውን፣ እንቁላሉን ፣ እህሉን ወዘተ… ነጋዴም ብሩን እናትም ልጇን እየጣሉ ነፍሴን አውጭኝ እግራቸው ወደመራቸው ሲሯሯጡ በትዕይንቱ እየተደሰትን በየተመደብንበት ቦታ ገንዘብ ለቀማችንን ተያያዝነው፡፡ በጣም በርካታ ገንዘብ ከሰበሰብን በኋላ ገንዘብ ወደምንካፈልባት ቦታ በኅብረት እየሮጥን ሄደን ያገኘነውን ገንዘብ እኩል ተካፍለን በጫት በሲጋራ በመጠጥ ወዘተ… መከስከሳችንን በቀጠልንበት ወቅት ሊቀመንበራችን ሌሎችን ያልተጠናከሩ ማኅበራት ለማጠናከር ትቶን ሄደ፡፡ ለብዙ ቀናት በቀደመ ግብራችን ጸንተን ብንጠብቀውም ሊመለስ ባለመቻሉ በተለያዩ ሃሳቦች ልንከፋፈል ተገደድን፡፡የእኔ ሃሳብ ከሌሎች እጅጉን ልዩ ስለነበር ከማኅበሩ ተለይቼ እኔ ማነኝ? ሥራዬ ምን ነበር? የት ነበርሁ? ወዘተ… የሚሉትን የማንነት ጥያቄዎች እያወጣሁና እያወረድኩ ፊቴን በእንባ እያጠብኩ እግሬ ወደ መራኝ በረሐ ጉዞዬን ቀጠልኩ፡፡ ሌሎች የማኅበሩ አባላት በርካታ በሆኑ ፖሊሶች ተይዘው ወደ እሥር ቤት እንደወረዱ በሰማሁ ጊዜ የበረሐ ጉዞዬን አፈጠንኩት፡፡ በጉዞዬ ወቅት ምድር ተከፍታ የምትውጠኝ ሰማይ ተሰብሮ የሚጫነኝ ፀሐይ የምትጨልምብኝ ወዘተ… ይመስለኝ ስለነበር ወዮልኝ፣ ወዮ ለእኔ እያልሁ መሪር በሆነ እንባ ፊቴ ይቃጠል ነበር፡፡ በሳቅ ያሳለፍኩትን በልቅሶ፣ በደስታ ያሳለፍኩትን በኃዘን ቀይሬ ጫት ፣ሲጋራ ፣ስርቆት፣ ሽብር ፣መዳራት፣ስካር ወዘተ… ለእኔ አንዳልሆኑ ዳግምም ላልመለስባቸው ለራሴ ቃል እየገባሁ ስጓዝ አንድ ጽሕማቸው የረዘመ በግራ እጃቸው መቋሚያ በቀኝ እጃቸው መስቀል በራሳቸው የምንኩስና ቆብ የደፉ ቢጫ ልብስ የለበሱ መነኩሴ ከርቀት ስላየሁ ልደርስባቸው ፈጠንኩ፡፡ እንደደረስኩባቸው አባቴ ጤና ይስጥልኝ አልኳቸው፡፡ እርሳቸውም "አብሮ ይስጥልን ልጄ" ብለው በመስቀላቸው ባርከው "እግዚአብሔር ይፍታህ" ካሉኝ በኋላ "ምነው ልጄ በዚህ ፀሐይ እዚህ በረሐ ውስጥ ትቅበዘበዛለህ? " አሉኝ፡፡ እኔም የሆነውን ሁሉ አንዲት ሳላስቀር እየነገርኳቸው የበረሐውን ጉዞ ከአባ ጋር ተያያዝኩት፡፡ መድረሻዬን ባላውቅም አባ ከደረሱበት ደርሼ ለማረፍ ስለወሰንኩ ድካሜን በብርታት አድሼ በእያንዳንዲቱ እርምጃቸው እየተከተልኩ አባ ከሚኖሩባት መቃብር ቤት ስንደርስ ለዛ ባለው አንደበታቸው "የእኔ መኖሪያ እዚህ ገዳም ውስጥ ሲሆን የጸሎት ቤቴ ደግሞ ይህች ናት" ብለው በያዙት መቋሚያ ጠቆሙኝ፡፡ ከዚያም "ቤተክርስቲያን ገብቼ ጸሎት አድርሼ እስክመጣ ድረስ በዚህ ቆየኝ " ብለውኝ ሲሔዱ የአባን ቤት ዙሪያዋን ስቃኛት ቀልቤን የሳበ አንድ ጽሑፍ ከበሩ አጠገብ አነበብኩ፡፡ "ወጣት አያሌው እጅጉ ባልታሰበ ድንገተኛ አደጋ በ21 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፡፡" የሚል ጽሑፍ ነው፡፡ ቀጣዩ የሞት ዕጣ ለእኔ እንደሆነ በማሰብ አለቀስኩ፡፡ ዓለም ለምኔ በሞት ሳልጠራ አሁኑ መመለስ አለብኝ ብዬ ወሰንኩ፡፡ አባ ጸሎታቸውን ጨርሰው የጸሎት ቤታቸውን ከፍተው ካስገቡኝ በኋላ "ነፍስ ያለ ሥጋ አትቆምምና ለድካምህ መጠገኛ ይህን ተመገብ" ብለው ኮቸሮ አቀረቡልኝ፡፡ እኔም የቀረበልኝን ኮቸሮ በልቼ እንደጨረስኩ አባቴ እደነገርኩዎት የእኔ ሕይወት የተበላሸ ነው፡፡ በኃጢአት የቆሸሸ የተጨማለቀ ታሪክ ነው ያሳለፍኩት፡፡ ታዲያ አሁን ምን ባደርግ አምላኬ ይታረቀኛል? አልኳቸው እንባዬን እያፈሰስኩ፡፡ አባም "አይዞህ ልጄ አንተ ያን የኃጢአት ዓለም ንቀህ ስትመጣ አምላክ ታርቆሃል፡፡ ብዙዎች አሁንም በዓለም ባሕር የሚዋኙ ሆነው ሳለ አንተን ግን እግዚአብሔር ለቤቱ የመረጠህ ምርጥ ሰው ሆነሃል፡፡ ሰይጣን ከጥንት ጀምሮ የሰውን ልጅ በማሳት ወደ ሲዖል ያጋዘ የሐሰት አባት ነው፡፡ ሔዋንን ዕፀ በለስን ያበላ፣ አቤልን ያስገደለ፣ 14 ሽህ ከ 400 የቤተ ልሔም ሕጻናትን በአንድ ቀን ያስገደለ! ኧረ ስንቱን እነግርሃለሁ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሊፈትንም እኮ የቀረበ ደፋር ነው፡፡ በአጠቃላይ ሰይጣን የበጎ ሥራ ጠላት በመሆኑ በሰው፣ በእንስሳት፣ በዕፅዋት እያደረ መልኩን እየቀያየረ ይፈታተነናል፡፡ እስስት አታውቅም? ልክ እንደዚያ ነው፤ ዛሬ ጥቁር፣ ነገ ቀይ ፣ ከነገ ወዲያ ነጭ፣ ከዚያ ወዲያ ደግሞ ሌላ ሆኖ ማንነቱን እየቀያየረ ነው የሰውን ልጅ የሚያጠቃው፡፡ አንተ ደግሞ ልጄ ይህን ሁሉ አሻፈረኝ ብለህ ከዚያ የኃጢአት ባሕር በመውጣትህ የተመረጥክ ሆነሃል፡፡ " አሉኝ፡፡ እኔም እና እግዚአብሔር ይቅር ይለኛል? አልኳቸው፡፡ አባም "ልጄ የእግዚአብሔርን ይቅር ባይነት ትጠራጠራለህ እንዴ? አትብላ የተባለውን ዕፀ በለስ በልቶ የነበረ አዳምን በመስቀል ተሰቅሎ ይቅር ያለ፤ ወንበዴ ሽፍታ የነበረ ጥጦስን ገነት ያገባ ይቅር ባይ አምላክ ይቅር ይልሃል፡፡ የእኔ አና የአንተ አምላክ አኮ ኃጢአትን እንጅ ኃጢአተኛን የሚጠላ አምላክ አይደለም፡፡ " አሉኝ፡፡ እኔም አባቴ ከዚህ በኋላ ዳግም ወደ ዓለም ላልመለስ ከእርስዎ ጋር ልኖር ወስኛለሁ ብዬ ከእግራቸው በታች ተደፋሁ፡፡አባም "አይዞህ ልጄ ተነሣ በጾም በጸሎት በስግደት ተወስነህ የምትኖርባት ትሕትና የተባለች ቤት በዚህ ገዳም ውስጥ ስላለች ቤትህን ላሳይህ የሚከብድህ እና የሚያስቸግርህ ነገር ሲገጥምህ እኔ ዘንድ እየመጣህ ትጠይቀኛለህ፡፡ እኔም ካንተ አልለይም አይዞህ ጽና ዳግም እንዳትበድል ተጠንቀቅ " ብለው ወደ ቤቷ ወሰዱኝ፡፡ እኔም፡- አቤቱ በቁጣህ አትቅሰፈኝ፣ በመዓትህም አትገስጸኝ፣ የበደሌን ብዛት አይተህ፣ አትቅጣኝ ጌታ በመቅሰፍትህ፣ ተመልሻለሁ ወደ ቤትህ፣ የዓለምን ባሕር ትቼዋለሁ፣ ላልመለስ ወስኛለሁ፣ በ “ትሕትና” ቤቴ እኖራለሁ፣ ተቀበለኝ መጥቻለሁ፡፡ የሚለውን መዝሙር እየዘመርኩ "ትሕትና" ወደ ተባለች ቤቴ በንስሓ ገባሁ፡፡

አጋንንትን መቼ ማሸነፍ ይቻላል?

አጋንንትን መቼ ማሸነፍ ይቻላል? የሳጥናኤል ሠራዊት አጋንንት ሰይጣናት ሰውንና እንስሳትን የሚያስቱ ረቂቃን የሆኑ ከደመና በላይ የሚኖሩ ተፈጥሯቸው እንደ ብርሃን መላእክት ከእሳትና ከነፋስ የሆኑ ነፍስና ሥጋ የሌላቸው ከበደሉ በኋላ እንደጢስ የሆኑ እውራን ከጌትነት ብርሃኑ የተራቆቱ አሉ፡፡ ዳግመኛም በባሕርና በየብስ የሚኖሩ ሥጋ የለበሱ፣ የሚጋቡ፣ የሚዋለዱ፣የሚሞቱ መልካቸው እንደ ሰው፣ እንደ እባብ የሆኑ ሌላም ልዩ ልዩ መልክ ያላቸው ማንንም የማያስቱ በሽታ፣ደዌ የሚሆኑ የሚያሳምሙ የእግዚአብሔር ትዕዛዝና ፈቃድ ካልተጨመረ ነፍስን ከሥጋ መለየት የማይቻላቸው አሉ፡፡ እነዚህ በማሳትና ደዌ በመሆን የተሰማሩ አእምሮ የጎደላቸው የሰውን ልጅ ከጥንት ጀምረው በማሳትና ደዌ በመሆን ለራሳቸው አድርገው በገሐነመ እሳት ሊጥሉ ዝግጁዎች ናቸው፡፡ ሔዋንን ያሳተ፣ ክርስቶስ ኢየሱስን በጲላጦስ አደባባይ ለፍርድ ያቆመ ደፋር ዛሬም ድረስ የቀደመ ተንኮሉን ባለመተው “በአንተና በሴቲቱ መካከል በዘርህና በዘሯ መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ” ዘፍ3፥15 ተብሎ እንደተጻፈ ጠላታችን በመሆን ሊውጠን ያገሳል፡፡ ዳግመኛም አስተዋይ አእምሮ የላቸውምና በእግዚአብሔር አምነው ይንቀጥቀጡ እንጅ በጎ ሥራን ለመሥራት ዝንጉአን ናቸው፡፡ ያዕ2፥19 በምጽአት ጊዜ አእምሯቸው ሲመለስ የማይጠቅም ንስሓ ቢገቡም ለዘላለም ገሐነመ እሳት ይገባሉ እንጅ መንግሥተ ሰማያትን መውረስ አይቻላቸውም፡፡ እነዚህን ለማሸነፍ ከእኛ የሚጠበቀው ነገር ለኑሯቸው ምቹ ሆኖ አለመገኘት ብቻ ነው፡፡ ለዝንብ የሚስማማት ቆሻሻ ቦታ ነው፤ ለጅብ የሚስማማው የሞቱ እንስሳት የወደቁበት ቦታ ነው፤ እንደዚሁም ለአጋንንት የሚስማማቸው ልቡናው የቆሸሸ በቁሙ የሞተ ሰው ነው፡፡ በልቡና መቆሸሽ፣ በቁም መሞት ማለት በኃጢአት መዘፈቅ ፣ ከእግዚአብሔር መለየት ማለት ነው፡፡ በቆሸሸ ፊታችንና ልብሳችን ላይ ያረፉ ዝንቦችን ለጊዜው በጭራ ማባረር ቢቻልም ተመልሰው መምጣታቸው አይቀርም፡፡ የሞተ እንስሳ ከወደቀበት ቦታ የተሰበሰቡ ጅቦችን ለጊዜው ድንጋይ ወርውረን ልናባርራቸው ብንችልም ተመልሰው መምጣታቸው አያጠራጥርም፡፡ ዝንብን እስከ መጨረሻው ማባረር የምንችለው ፊታችንንና ልብሳችንን ስናጸዳ ብቻ ነው፤ ጅብን ደግሞ የሞተውን እንስሳ በመቅበር አልያም በጣም አርቀን በመጣል ነው፡፡ ጠቅለል ባለ መልኩ ዝንብንም ሆነ ጅብን እስከመጨረሻው ማባረር የሚቻለው ለማረፍ የሚስማማቸውን ነገር ይዞ ባለመገኘት ብቻ ነው፡፡ አጋንንትን በኃጢአት ሳለን ለጊዜው በጸሎት፣ በጾም ፣በስግደት ልናባርራቸው ብንችል ተመልሰው መምጣታቸው አይቀሬ ነው፡፡ ምክንያቱም ለእነርሱ ተስማሚ የሆነ ያልጸዳ ነገር በውስጣችን ተደብቋልና፡፡ እስከመጨረሻው ማባረር የምንችለው አጋንንት የሚወዱትን ነገር ይዞ ባለመገኘት ብቻ ነው፡፡ አዲስ እንግዳ ሰው አብሯችሁ ተቀምጦ ሳለ አይዞህ አይዞህ ባትሉት ጭራሽ ባታነጋግሩት ጭንቅ ጭንቅ ስለሚለው የሚሄድበት ሳይኖረው “እዚህ ቦታ ደርሼ ልምጣ” ብሎ ታቷችሁ እንደሚሄድ ሁሉ አጋንትም እንዲሁ ናቸው፡፡ ስለዚህ አጋንንትን ለማባረር በዝሙት፣ በርኩሰት፣ በመዳራት፣ ጣዖትን በማምለክ፣ በምዋርት፣ በጥል፣ በክርክር፣ በቅንዓት፣ በቁጣ፣ በአድመኛነት፣ በመለያየት፣ በመናፍቅነት፣ በምቀኝነት፣ በመግደል፣ በስካር፣ በዘፋኝነት ወዘተ… ቋንቋዎች ልናነጋግራቸው አይገባም፡፡ እነዚህን ቋንቋዎች በሚገባ የሚያውቋቸውና የሚወዷቸው የሁልጊዜ መግባቢያዎቻቸው ስለሆኑ እነርሱ ያልተማሯቸውን፣ የማያውቋቸውን ሲነገሩም ጆሯቸውን የሚያሳክኳቸውን ቋንቋዎች መርጠን ልናናግራቸው ያስፈልጋል፡፡ እነዚህም ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የዋሃት፣ ራስን መግዛት ወዘተ… የመሳሰሉት መግባያዎች ናቸው፡፡ በእነዚህ መግባቢያዎች የሚግባቡ ሰዎችን መግባባት የማይችሉ አጋንንት ለሰዎች ባዕድ ሲሆኑ መባረራቸው የግድ ነው፡፡ ይሁን እንጅ አጋንንት ሁል ጊዜ “ምን አዲስ ነገር አለ” ብለው ሊፈትሹን ስለሚመጡ ለቅጽበትም ቢሆን ከመግባቢያ ቋንቋችን ውጭ ማውራት ተገቢ አይደለም፡፡ ምክንያቱም በዚያች ቅጽበት ውስጥ ለሲኦል አደጋ የሚጥሉበትን ምቹ ጊዜ የሚያመቻቹበት ሊሆን ቢችልስ ምን ማረጋገጫ አለን? አጋንንትን እስከመጨረሻው ለዘላለም ለማባረር እስከሞታችን ድረስ በውስጣችን ልናሰርጸው የሚገባው ቋንቋ የመንፈስ ፍሬ የሚባለውን ሊሆን ይገባል፡፡ ከዚያ ውጭ በእኛ ውስጥ የገባ ርኩስ መንፈስ ሌሎችንም ርኩሳን መናፍስት ስቦ በማምጣት ለሚያጨናንቅ አደጋ አሳልፎ ይሰጠናል፡፡ ማቴ12፥43-45 በመሆኑም በአጋንንት ላይ ድልን ልንቀዳጅባቸው የምንችልባቸውን ሥራዎች መሥራት ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል፡፡ ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደት ወዘተ… ባለበት አጋንንት እንዴት ሊቀርቡ ይችላሉ? እሳት በላያቸው ላይ እየነደደ እንዴት ሊታገሱ ይችላሉ? በርግጥ ለተወሰነ ጊዜ የሚነድባቸውን እሳት ሊታገሱ ይችሉ ይሆናል ሁልጊዜ የሚነድባቸውን እሳት ግን የሚታገሱበት ኃይል ከቶ አያገኙም፡፡ ከጾም፣ ከጸሎት፣ ከስግደት፣ ከበጎ ሥራ፣ ከንስሓ ወዘተ… የማንርቅ ከሆነ ከእነዚህ ሥራዎች ወደራቁት ይሄዳሉ እንጅ ከእኛ ጋር የሚታገሉበት ጦራቸው መሰበሩ አይቀርም፡፡ ጠቅለል ባለ መልኩ የመንፈስ ፍሬ በማፍራት የሥጋ ሥራን በማስወገድ የቆሸሸ ልቡናችንን በንስሓ በማጽዳት ከአጋንንት ጦር የምናመልጥበትን ጋሻ ስንይዝ የአጋንንትን ሠራዊት ልናብረከርካቸው የምንችልበትን ኃይል ከኃያሉ እግዚአብሔር እንቀዳጃለን፡፡ በሥራችን ገነት መግባት ባንችል ሰይጣን ደስ እንዳይለው ኃጢአትን መሥራት የለብንም፡፡ አጋንንት ድል የምናደርግበትን ኃይል እገዚአብሔር አምላክ ለሁላችንም ያድለን፡፡ አሜን፡፡ ማቴ 17፥19-21

የእውቀት መጨረሻው


እውቀት መጻሕፍትን በማንበብ፣ ከሌሎች በመስማት፣ በማየትና በሌሎችም ልዩ ልዩ መንገዶች የሚገኝ ሃብት ነው፡፡ ይሁን እንጅ በዚህ መልኩ የምናገኘውና በአእምሯችን ስልቻ የምናጠራቅመው ሁሉ በራሱ አውቀት ሊባል የሚችል አይደለም፡፡ ምክንያቱም እውቀት እውቀትነቱ የሚረጋገጠው በሥራ ሲተረጎም በተግባር ሲገለጽ ነውና፡፡ እምነት ያለሥራ የሞተ እንደሆነ ሁሉ እውቀትም ያለ ተግባር የሞተ ነው፡፡ ያዕ2፥17 መጽሐፍ ቅዱስ ከዘፍጥረት እስከ ራእየ ዮሐንስ ድረስ አንብበን እውቀት ብንይዝና የእግዚአብሔርን ሕግጋት የማንጠብቅ ፣ ፈሪሐ እግዚአብሔር የሌለን ከሆነ አዋቂነታችን ወዴት አለ? “ከመቶ ሃምሳ ዳዊት የልብ የዋሕነት ይሻላል” የሚሉ ይህንኑ ለማጠናከር ነው፡፡ እንደ አምላክ ልብ የሆነ ዳዊት የጻፈውን መቶ ሃምሳ መዝሙራት በቃላችን እስከመያዝ ብናውቅ ነገር ግን የማይራራ ፣ ጨካኝና ፍቅር የሌለበት ልብ ያለን ከሆነ አዋቂዎች ሳንሆን መቶ ሃምሳ ዕዳዎችን የተሸከምን ባዕዳዎች ነን፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በመጀመሪያው ቆሮንቶስ መልዕክቱ ላይ በሚገባ አብራርቶ እንዲህ በማለት ጽፏል “በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሿሿ ጸናጽል ሆኛለሁ፡፡ ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና አውቀትን ሁሉ ባውቅ ፣ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ፡፡ ድሆችን ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል ፣ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳለፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም፡፡” 1ኛ ቆሮ 14፥1-7 አዋቂ ሰው የሚናገረውን የሚሠራ፣ ያወቀውን ተግባራዊ ማድረግ የሚችል ነው፡፡ ከዚያ ውጭ ግን ለታይታ በሰዎች ፊት አዋቂነታችን እንዲታወቅልን የሆነ ያልሆነውን እየቀባጠርን በተግባራችን ስንመዘን የተናገርነውን እንኳ በሥራ መተርጎም የማንችል ሆነን ከተገኘን የእኛ አዋቂነት ከንቱ ነው፡፡ አዋቂዎች መሆን የምንችለው ደግሞ የምናነበውንና የምንሰማውን ለምን? እንዴት? ምን ማለት ነው? ወዘተ… የሚሉትን ጥያቄዎች እየመለስን የምንሄድ ከሆነ እና ለሕይወታችን አስፈላጊ የሆኑትን በመሥራት ነው፡፡ እዚህ ላይ አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ አንድ ተማሪ ውዳሴ ማርያምን በቃሉ ለመያዝ የቃሉን ትርጉም ሳይረዳ ብዙ ጊዜ እየደጋገመ ይጮኸል፡፡ ይህን የሰማ አንድ መናፍቅ “ በዕለተ ረቡዕ ኩሉ ሠራዊተ ሰማያት ይብሉ” ይላልና ረቡዕን መጾም አያስፈልግም፡፡ ምክንያቱም “ኩሉ ሠራዊተ ሰማያት ይብሉ” ተብሏልና፡፡ ታዲያ የሰማይ ሠራዊት መላእክት ሲበሉ እኛ ለምን እንጾማለን? ከእነርሱ እንበልጣለን እንዴ? ሲለው ተሜ የሸመደዳትን ማመላለስ ጀመረ፡፡ ከረቡዕ ውዳሴ ማርያም ሲደርስ እንዲህ አለ “ውዳሴሃ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ ዘይትነበብ በዕለተ ረቡዕ፡፡ ኩሉ ሠራዊተ ሰማያት ይብሉ ብጽእት አንቲ…” ለካ በዕለተ ረቡዕ ኩሉ ሠራዊተ ሰማያት ይብሉ ተብሏል በማለት ረቡዕን ሻረ ይባላል፡፡ ይህ ተማሪ የቃሉን ትርጉም በሚገባ ሳይረዳ በቃሉ ለመያዝ ብቻ ይደክም ስለነበር መናፍቁ ከምንባቡ መካከል ቆራርጦ ባገናኛቸው ቃላት ለመታለል ተገደደ፡፡ ስለዚህ ለምን? ምን ማለት ነው? ወዘተ… የሚሉትን ጥያቄዎች በሥራችን መካከል እየመለስናቸው ማለፍ አለብን፡፡ የአንዲትን ቃል ትርጉም በሚገባ ሳንረዳ ወደ ሌላኛዋ የምንሸጋገር ከሆነ ትርጉም አልባ በሆነ ነገር አእምሯችንን ለጭንቀት እንዳርገዋለን፡፡ በሥራ መተርጎም ከቻልን ለጠቢብ አንዲት ቃል ትበቃዋለች” የሚለው በራሱ በቂ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በ 1ኛቆሮ 14፥1-7 በጻፈው መልእክቱ በርካታ የቅድስና ሥራዎችን ዘርዝሮ ማሰሪያ ያደረገው አንዲትን ቃል ፍቅርን ነው፡፡ ስለንስሓ አስፈላጊነት፣ በንስሓ ስለተጠቀሙ ሰዎች ወዘተ… ብዙ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃዎችን ብንሰጥ፣ ብዙ መጻሕፍትን ብንጽፍ፣ ለሰዎች ብናስተምር እኛ ራሳችን ንስሓ የማንገባ ከሆነ ምን ይጠቅመናል? “ንስሓ ግቡ” ለማለትማ ቴፑስ መቼ አነሰን? እርሱ ንስሓ ገብቶ አላሳየንም እንጅ፡፡ ስለዚህ ያወቅነውን አውቀት ወደ ተግባር በመቀየር እና በእውቀታችን ተጠቃሚ በመሆን መቶ፣ ስድሳ እና ሠላሳ ያማሩ ፍሬዎችን ልናፈራ ይገባናል፡፡ ማቴ 13፥8 በአእምሯችን ውስጥ የሚንጫጫውን የእውቀት ተልባ በአንድ የተግባር ሙቀጫ ውስጥ በማስገባት ልንወቅጠው ያስፈልጋል፡፡ “የእውቀት መጨረሻው እውቀትን በተግባር ማዋል ነው፡፡” ብጹእ አቡነ በርናባስ የምዕራብ ጎጃም ሊቀ ጳጳስ የነበሩ፡፡

ራስን አለማዎቅ

ራስን አለማዎቅ ትልቅ በሽታ ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ራሳቸውን አለማዎቃቸው የሚገባቸው እጅግ በጣም ዘግይቶ ነው፡፡በከፋ ችግር ውስጥ ሲዘፈቁ ወይም ደግሞ አቻዎቻቸው ከእነርሱ ቀድመው ትልቅ ደረጃ ሲደርሱ ያን ጊዜ ራሳቸውን እንዳላዎቁ ይገባቸዋል፡፡ አንድ ሰው ብዙ ገንዘብ በሚያስገኝ ትልቅ ውድድር ላይ ይሣተፋል፡፡ ውድድሩ እንዲህ ነው ውኃ እና ሌሎች መጠጦችን ሳይጠጡ ለ4 ተከታታይ ቀናት ያህል በየቀኑ አንድ አንድ ኪሎ ጨው በመመገብ ለፈጸመ 10 ሚሊዮን ብር ሽልማት የሚያገኝ ሲሆን ውድድሩ ከተጀመረ በኋላ ከ4ኛው ቀን በፊት ውኃ ወይም ሌላ መጠጥ የቀመሰ ግን አውራ ጣቱን ሊቆረጥ የሚል ነው፡፡ ታዲያ ራሳቸውን ያላዎቁ ብዙዎች የ 10 ሚሊዮን ብር ተሸላሚ ለመሆን ተስማተው ለውድድሩ ተራ ይዘዋል፡፡ እነዚህ ተወዳዳሪዎች ሳይንስን ከራሳቸው በላይ ያውቁታል፡፡ ሳይንስ እንደሚለው የሰው ልጅ ያለውኃ 7 ቀናት መቆየት ይችላል፡፡ ይህን የሳይንሱን ሃሳብ የሚጋሩና በሚገባ የሸመደዱ ተወዳዳሪዎች ከውድድሩ አዳራሽ ውስጥ ተሰልፈዋል፡፡ የውድድሩ የመጀመሪያ ቀን ደረሰ እና ለተወዳዳሪዎች በየስማቸው አንድ አንድ ኪሎ ጨው ከአንድ አንድ ሊትር ውኃ ጋር ተሰጣቸው፡፡ ሁሉም አንድ ብለው ጀመሩ፡፡ 1 ኪሎ ጨው ለ 1 ቀን የሚለውን የውድድሩ መርኅ አክብረው ለ2ኛው ቀን ደረሱ፡፡ አሁንም እንደተለመደው ጨውና ውኃ ተሰጣቸው፡፡ አንዳንዶች ግን ውድድሩ በጣም እየከበዳቸው መጥቷል፡፡ አሁን ሳይንሱን ረስተው ራሳቸውን አስታወሱ፡፡ የወደቀ የተረሳ የወደቀ ማንነታቸውን ማንሣት ጀመሩ፡፡ የተሰጣቸውን ውኃ ማሽተት የጀመሩም አሉ፡፡ እንዳይጠጡ የአውራ ጣታቸው ጉዳይ አስቸገራቸው፡፡ ስለአውራ ጣታቸው ይህን ቀን እንደምንም ታገሱ፡፡ የ 3ኛው ቀን ውድድር ተጀመረ፡፡ አብዛኞቹ የመጣው ይምጣ ብለው የተሰጣቸውን ውኃ መጠጣት ግዴታ ሆነባቸው፡፡ በገቡት ውል መሠረት አውራ ጣታቸውን እተቆረጡ ከውድድሩ ተሰናበቱ፡፡ ጥቂቶች ግን የአውራ ጣታቸውን ጉዳይ በማምሰልሰል በጨው ብዛት አንጀታቸው ተቃጠለ፡፡ 3ኛውን ቀን ታገሰው ወደ ፈጻሜው 4ኛ ቀን ሊሸጋገሩ ባለመቻላቸው ሆዳቸው ተቃጥሎ ነፍሳቸው አለፈች፡፡ አሁን ይህ ከባድና የከፋ ችግር ሲደርስባቸው ራሳቸው እነማን እንደሆኑ ተረዱ፡፡ ለእነዚህ ሰዎች ጣት መቆረጥና ነፍስ መጥፋት ምክንያት የሆናቸው ራሳቸውን አለማዎቃቸው ነው፡፡ ታዲያ ጣታቸውን ከተቆረጡት ሰዎች መካከል አንዱ እንዲህ አለ ይባላል፡፡ “ወይኔ ወይኔ ተቆረጠ ጣቴ ወይኔ እያየ ዓይኔ” ሌላኛው ደግሞ እንዲህ አለ “ለእነ እገሌ መሞት ለእኔ ጣት መቆረጥ ራስን አለማዎቅ መሆኑን አዎቅሁት” አያችሁ ወገኖቼ! እነዚህ ተወዳዳሪዎች የተመለከቱት ከውድድሩ በኋላ የሚያገኙትን ሽልማት ነው፡፡ ነገር ግን ያን ሽልማት ለማግኘት እኔ ብቁ ነኝ ወይ? የሚለውን ጥያቄ መመለስ አልቻሉም፡፡ ወደ ራሳቸው መልሰው ያለውኃ አራት ቀን መቆየት መቻል አለመቻላቸውን ማዎቅ የማንም ድርሻ አይደለም የራሳቸው ድርሻ ነው፡፡ ስለራሴ ማዎቅ የሚገባኝን ነገር ማዎቅ ያለብኝ እኔ እንጅ ሌላው አይደለም፡፡ አንዳንዶች ሲመክሯቸው ራሳቸውን ያዎቁ እየመሰላቸው “ከራሴ በላይ ለእኔ የለም” እያሉ በዝሙት አልጋ እንደወደቁ በአስከፊ በሽታ ሲማቅቁ ሰው ሁሉ ሲያገልላቸው፣ መሳቂያ መሳለቂያ ሲያደርጋቸው ያን ጊዜ “ወይኔ ይህን ባላደርግ ኖሮ” ይላሉ፡፡ በሽታው ከያዘህ በኋላ ራስህን ብታውቅ ምን ዋጋ አለው በፊት ነበር እንጅ፡፡ በእርግጥ አሁን ላይ ሆነህም ቢሆን ራስህን ማዎቅህ ጥሩ ነው፡፡ በፊት ራስህን ሳታውቅ የሠራኸው ሥራ ትልቅ ዋጋ እንድትከፍል አድርጎሃል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሁሉን አውቀናል ብለን ሳለ የሚመጡብንን ጥያቄዎች መመለስ ከማንችልበት ደረጃ ላይ ስንደርስ ቆም ብለን “ለካ ይህን አላውቅም ነበር” እንላለን፡፡ አያችሁ ገና አሁን ነው ራሳችንን ያወቅነው፡፡ አብሮን እየኖረ እኛም አብረነው እየኖርን ራሳችንን ራሳችን ማዎቅ ካልቻለ በጣም አደጋ ነው፡፡ አንድ ከጓደኛው እየኮረጀ ጥሩ ውጤት የሚያመጣ ተማሪ ያ ውጤት የራሱ አለመሆኑን የሚረዳው ብቻውን ተፈትኖ ብቻውን ተወዳድሮ ማለፍ አልችል ሲል ነው፡፡ አንድ አስተማሪ ራሱን አለማዎቁ የሚገባው ተማሪዎቹ የሚጠይቁትን ጥያቄ በአግባቡ መመለስ አልችል ሲል ነው፡፡ አንድ እስከ 6 እና 7 ሰዓት ድረስ በመጾሙ ራሱን የበቃ አድርጎ የሚቆጥር ሰው ራሱን አለማዎቁ የሚገባው ጓደኞቹ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መሠረት እስከ ዘጠኝም እስከ አሥራ አንድ ሰዓትም ከዚያም በላይ እንደ ጾሙ ሁኔታ ሲጾሙ ሲመለከት ነው፡፡ አንድ ራሱን ምሉእ አድርጎ የሚቆጥር ሰው ምሉእ አለመሆኑን የሚረዳው መናፍቃን ሲነሡ መርታት አላውያን ሲነሡ መጽናት ሲያቅተው ነው፡፡ አንድ እንደምንም ቁጭ ብድግ እያለ ለ 10 ደቂቃ ያህል የነግህ ጸሎት ብቻ በማድረጉ ራሱን እንደ ጻድቅ የቆጠረ ሰው ሰባት የጸሎት ጊዜያት እንዳሉ የተረዳ ቀን ወይም ቅዳሴ ያስቀደሰ ቀን ራሱን ማዎቅ ይጀምራል፡፡ አንድ አርብ ረቡዕን ብቻ በመጾሙ ራሱን ከብቃት ደረጃ ላይ ያስቀመጠ ሰው ራሱን ማዎቅ የሚጀምረው ሰባቱን አጽዋማት መማር ከቻለ ነው፡፡ አንድ መጽሐፍ ቅዱስን አንብቤ ተረድቼዋለሁ በማለት ራሱን እንደ ትልቅ የሚቆጥር ሰው ራሱን አለማዎቁ የሚገባው ቃሉን በተግባር መቀየር አልችል ብሎ “እርሱን ብሎ ክርስቲያን” ብለው ሰዎች ሲመጻደቁበት ነው፡፡ አዳምና ሔዋን ምክረ ከይሲን ሰምተው አምላክ ለመሆን ሽተው እፀ በለስን በበሉ ጊዜ የጸጋ ልብሳቸው በተገፈፈና እርስ በርሳቸው ተፋፍረው በተሸሸጉ ጊዜ ለማንነታቸው ጥያቄ መልስ አግኝተዋል፡፡ ራሳቸውን በሚገባ ባለማዎቃቸው ራሳቸውን መሆን ያቃታቸው አዳምና ሔዋን የሠሩት ስህተት ገነትን ያህል ቦታ እግዚአብሔርን ያህል ጌታ አሳጥቷቸዋል፡፡ ለ5500 ዘመናትም በእግረ አጋንንት እንዲጠቀጠቁ አድርጓቸዋል፡፡ ራሳቸውን ያዎቁት ከዚህ ሁሉ ውድቀትና መከራ በኋላ ነው፡፡ የማንነትን ጥያቄ በሚገባ መመለስ ትልቅነት ነው፡፡ በዚህ ዘመንም የተሻለ ሰው ሆኖ ለመገኘት ራስን ማዎቅ ትልቅ ቦታ አለው፡፡ እኔ ማነኝ ብለን ራሳችንን ብንፈትሸው እንደ ሳጥናኤል ሐሰተኛ፣ እንደ ፈርዖን ትዕቢተኛ፣ እንደ አዳምና ሔዋን ትዕዛዝ የምናፈርስ፣ አምላክ መሆንን የምንሻ፣ እንደ ቃየን ወንድማችንን የምንገድል፣ እንደ ጎልያድ ትምክህተኛ፣ እንደ ይሁዳ አምላካችንን በገንዘብ የምንለውጥ ገንዘብ አምላኪዎች፣ እንደ ሎጥ ሚስት ወደ ኃጢአት ከተማ ፊታችንን የምናዞር፣ እንደ አይሁዳውያን አምላካችንን የምንሰቅል ሰዎች ነን፡፡ ነገር ግን ራሳችንን ለማዎቅ ትኩረት ባለመስጠታችን ብዙ ጉዳቶችን በማስተናገድ ላይ እንገኛለን፡፡ የዘመኑ ሰማእትነት ራስን ማዎቅ ይመስለኛል፡፡ ለማንኛውም ሥራ መሠረቱ ራስን ማዎቅ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን እኛ ማድረግ የሚገባን ነገር ቢኖር ራስን መፈለግና ማዎቅ ከዚያም ራስን መሆን ነው፡፡ ይህንን ለማድረግም አምላከ ቅዱሳን ወደ ማንነታችን መልሶ ራሳችንን አውቀን በትሕትናና በመታዘዝ እንድንኖር ይርዳን፡

የተዋሰከውን መልስ

የሰው ልጅ ያለው ከሌለው፣ የሌለው ካለው በመዋዋስ ይኖራል፡፡ ጎረቤት ከጎረቤት፣ መስሪያ ቤት ከመስሪያ ቤት፣ ተማሪ ከተማሪ፣ ነጋዴ ከነጋዴ ወዘተ መዋዋስ ልማድ ነው፡፡ አንዳንዱ መጽሐፍ አንዳንዱም የሚለበስ ነገር ይዋሳል፡፡ አሁን አሁን ግን የውሰቱ ጉዳይ ትንሽ ወጣ ሳይል አልቀረም፡፡ ባሕልም ማዋሻ መዝገብ ላይ መስፈር ከጀመረ ብዙ ጊዜያትን አስቆጥሯል፡፡ ሴቶች የወንዶችን ወንዶችም የሴቶችን፣ አፍሪካ የአውሮፓን አውሮፓም የአፍሪካን ወዘተ መዋዋስ ጀምረዋል፡፡ በውሰት ሕግ መሠረት መመለስ ግዴታ ነው፡፡ ማንም ሰው መዋስ ይችላል ነገር ግን በቀጠሮው ለመመለስ መዘግየት አመኔታን ያሳጣል፡፡ አንዳንድ ሰዎች የተዋሱትን ነገር የራሳቸው አድርገው የሚያስቀሩ አሉ አንዳንዶቹ ደግሞ በአንጻሩ የተዋሱበትን ዓላማ እንደጨረሱ የሚመልሱ አሉ፡፡ የተዋሱት ነገር የራሳቸው የሚመስላቸው ሰዎች ሲዋሱ የተጠቀሙበትን ትሕትና ሲመልሱም ይጠቀሙበት የሚለው አባባል ላይ ቅሬታ አላቸው፡፡ የእነዚህ ሰዎች ዓላማ የራሳቸው ያልሆነን ነገር በውሰት ሰበብ ማጠራቀም ነው፡፡ እንደነዚህ አይነት ሰዎች ከቦታ ቦታ እየተዟዟሩ ካልሆነ በቀር አዋሽ አያገኙም፡፡ ምክንያቱም የእነርሱ ነገር እንደ ግድግዳ ስልክ ውጦ ዝም ነዋ፡፡ እንደነዚህ አይነት ሰዎች በዓይናቸው ያዩትን፣ በጆሯቸው የሰሙትን ሁሉ ይዋሳሉ መመለስ ግን የለም፡፡ ፊደላትን፣ ቃላትን፣ አነጋገርን፣ አረማመድን፣ አለባበስን ወዘተ… ሁሉንም ነገር ይዋሳሉ መመለስ ግን የለም፡፡ ድሮ ድሮ ሰው የሚዋሰው ከሰው ነበር የአሁኑ ትውልድ ግን ከቴሌቪዥን፣ ከኮምፒዩተር፣ ከተንቀሳቃሽ ስልክ በቃ ከማንኛውም የቴክኖሎጅ መሣሪያ ሁሉ ከእንስሳቱ እንኳ ሳይቀር ጠቀመውም ጎዳውም ብቻ ይዋሳል፡፡ ይህን የተዋሰውን ነገር መመለስ የሚባለው ነገር ደግሞ በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነው፡፡ ወጣቱ ስማኝ አንተ የተዋስከው አነጋገር፣ አረማመድ፣ አለባበስ በእውነት እናት አገርህ የእነዚህ ሁሉ ድሃ ሆና ነው? አይደለም ድሃው አንተ ነህ፡፡ እኛ ኢትዮጵያውን የምንታወቀው በባሕላችን፣ መላእክትን በሚያስመስለው አለባበሳችን ነው እኮ፡፡ ታሪክን መርሳት ባሕል መዋስን ማምጣት የለበትም፡፡ የአንተ የሆነውን  ለምልክት እንኳ ሳታስቀር አውሰህ ጨረስከው፡፡ ታዲያ የአንተን ለሌላው የሌላውን ላንተ የምታደርግ ሌባ ቀማኛ ነህ ወይስ ዘራፊ? ዘመኑ የመረጃ ዘመን ነው ትላለህ ነገር ግን ምንም ጠቃሚ መረጃ የለህም፡፡ በሚጠቅመው በማይጠቅመው ጊዜህን በከንቱ ታሳልፋለህ፡፡ አናቶችህ እሳት ተጫጫሩ ልብስ ተዋዋሱ አንተ እሳቱን በኪስህ ከተትከው ሰውነትህ ደንዝዞ ሲያቃጥልህ እንኳ አይሰማህም፡፡ የሚጠቅም ነገር ተውሰህ ብታስቀር እንኳ ጥሩ ነበር፡፡ የሥራ ባህላቸውን መዋስ ስትችል 90 ደቂቃ እግር ኳስ ሲጫወቱ፣ሲታገሉ፣ ሲዳሙ ወዘተ ቁጭ ብለህ ትጮኸለህ፡፡ አስበው እስኪ በቀን ስንት ጨዋታ ትመለከታለህ? በቀላሉ ሦስት ጨዋታ ቢሆን እንኳ 270 ደቂቃ ወይም 4.5 ሰዓት ማለት ነው፡፡ በቀላሉ 8 ሰዓት ትተኛለህ፡፡ ለሌላው ጥቃቅን ነገር በድምሩ 2.5 ሰዓት ቢሆን  ከ24 ሰዓት ምን ያህል ተረፈህ? በከንቱ የሚባክነው ሰዓት በቀላሉ 15 ሰዓት የቀኑን 62.5% የሚሸፍን ነው፡፡ አየኸው የተዋስከውን መጥፎ ነገር፡፡ ታዲያ ይህን አልመልስም ብለህ እስከመቼ ትከራከራለህ? ጸጉርህን አፍተልትለህ ሱሪህን ተልትለህ ሰው ፊቱን እየዞረ እብድ ነው ወይስ ጤነኛ እያለ ሲወራረድብህ የተዋስኩትን አልመልስም ትለላህ? ወንድ ነው ወይስ ሴት እየተባባለ ሰው ሲመጻደቅብህ የተዋስኩትን አልመልስም ትላለህ? ሁሉም በቦታው ሲደረግ ያምራል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን በቦታችን ሳለን የሚያምርብን ራሳችንን ስንሆን ብቻ ነው፡፡ ልቅሶ ቤት ውስጥ የሚዘፍን፣ ሰርግ ቤት ውስጥ የሚያለቅስ ሰው ምን ያምርበታል፡፡ እኛ የተዋስነው ነገር እንደዚህ ያለ የማያምር ነገር ነው፡፡ስለዚህ የተዋስከውን ነገር በፍጥነት ልትመልስ ይገባሃል፡፡ የራስህ ያልሆነን ነገር ሞጭጨህ መገኘት በራሱ ኢትዮጵያዊነትን የሚያስነቅፍ ጉዳይ ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ከሌላው ሳንዋስ ያለን ነገር በራሱ በቂ ከበቂም በላይ ነው፡፡ አሁንም ደግሜ እላለሁ እኛ ኢትዮጵያውያን ከሌላው ሳንዋስ ያለን ነገር በራሱ በቂ ከበቂም በላይ ነው፡፡ ማዋስ ስንችል እንዴት የማይጠቅም ነገር ተውሰን እንገኛለን፡፡ ኩሩ እና ጀግና የነበረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ማስደፈር አይሆንም እንዴ? ታሪካችንስ ቢሆን በደም የተጻፈውን ፍቀህ በውኃ ቀለም ትቀይረዋለህ እንዴ? ዓለም የሚያውቀን በጀግንነት፣ በሐይማኖት፣ በጥሩ ባሕላችን ነው፡፡ ታዲያ ዛሬ በቴሌቪዥን መስኮት የተመለከትነውን ሁሉ እንሆናለን ስንል የነበረንን ሁሉ ትተን እንዳልነበረን ስንሆን ትንሽ አይሰማንም እንዴ? አንድ አይጥ ነበረች አሉ፡፡ ከምትኖርበት ጉድጓድ ውስጥ የምትበላው በየአይነቱ ተዘጋጅቶላት ያን እየተመገበች በደስታ ትኖራለች፡፡ በጉድጓዱ ውስጥ የተጠራቀመው ምግብ ሳያንሳት አንዳንድ ቀን ከጉድጓዱ ወጣ እያለች ሌሎች ይመገቡት የነበረውን ምግብ መመገብ ጀመረች፡፡ ይህች አይጥ መመገብ የጀመረችው የአንዱን ድሃ ጤፍ ነበር፡፡ አይጥ እንደበላችበት የተረዳው ያ ድሃ መርዝ ገዝቶ ከጤፉ አጠገብ አስቀመጠ፡፡ አይጧም እንደለመደች መብላት ጀመረች፡፡ ነገር ግን ያንን መርዝ አብራ በልታው ስለነበር ወዲውኑ ሞተች፡፡ የዚች የአይጥ ታሪክ አሁን ወደኛ ሕይወት ከገባ ውሎ አድሯል፡፡ ስለዚህ የማይገባውን የእኛ ያልሆነውን የተዋስነውን ነገር ልንመልስ ያስፈልጋል፡፡

የከሰረ ትውልድ

ትውልድ ሲያልፍ ትውልድ ይተካል፤ ሰውም በየጊዜው ይፈራረቃል፡፡ ቀናትም እንዲሁ ቀናትን ወልደው ወራትን ያመጣሉ፤ ወራትም ወራትን ተክተው ዓመታትን ይስባሉ ፤ ዓመታትም ዘመናትን ፤ ዘመናትም ዘመናትን አበርክተው ጊዜያት ያልፋሉ፡፡ የልቅሶው ዘመን የሳቁን፤ የክፉው ዘመን የበጎውን፤ የኃዘኑ ዘመን የደስታውን ፤ የኃጢአት ዘመን የንስሓውን፤ የባርነት ዘመን የልጅነትን ዘመን ይተካሉ፡፡ ቀኑ ይመሻል ሌሊቱ ይነጋል ፤ ቀኑ ይነጉዳል ሌላ ቀን ይተካል፤ ትውልድ ያልፋል ትውልድ ይተካል፡፡ የሚገርመው ግን ካለፈው ትውልድ ታሪክ ካለፈው ዘመን ታሪክ የሚበጅ ነገር መማር አለመቻላቸን ነው፡፡ ሰው የሰውን ልጅ እንደ አውሬ ይቆጥርበት የነበረው ያ የባርነት የሞት የዋይታ የልቅሶ ዘመን ጊዜ ሲሽረው ዘመን ሲተካው እኛ ዛሬም ያው እንደቀድሞሙ ልማድ ሆኖብን የሰውን ልጅ እንደ አውሬ እንቆጥራለን እኛም እንዲሁ እንደ አውሬ እንቆጠራለን፡፡  የቀን እረፍት የሌሊት እንቅልፍ የአእምሮ ሰላም የነሳን በራሳችን ፍላጎት የምንፍጨረጨረው አንዳች የማይጠቅም ሥጋዊ ፍልስፍናችን ነው፡፡ የቀደሙ ሰዎች በጠፉበትና ባለቁበት መንገድ እየተጓዝን እንኳ ጉዟችን የቀናና የተስተካከለ እስኪመስለን ድረስ በኩራት አፋፍ ላይ ተኮፍሰን የትዕቢት አየር እየሳብን እንዝናናለን፡፡ ያ የጥፋት ዘመን ምን ያህል ሰው እንደወሰደ ጉዳቱ ምን ድረስ እንደነበር እንኳ የምናውቅ አይመስለኝም፡፡ ምድር የሰው ደም ጠምቷት በነበረ ወቅት ደማቸው የምድር ሲሳይ ሥጋቸው የአራዊት መጫወቻ የሆኑ ወገኖቻችን ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፡፡ አሁን ያለን እኛ በዛሬው እግራችን እየተራመድን ከዚያ የደም ዘመን ለመድረስ ብንሞክር ምን ያህል ርቀት እንጓዝ ይሆን? በኅሊናችን ማመላለስ የምንችል ሆኖ ቢሆን ለሀገራቸው፣ ለወገናቸው፣ ለነጻነታቸውና ለእምነታቸው ምትክ የሌላት ሕይወታቸውን ያሳለፉትን አባቶቻችንንና አናቶቻችንን ብናስታውሳቸው እንቅልፍ የሚኖረን ይመስላችኋል? ሠርተው ድካምን የማያውቁ፣ ለመታዘዝ እንቢታ የሌላቸው፣ ለመስጠት ንፍገት የሌላቸው፣ ለማሳዎቅ የማይሰለቹ የነበሩ የትሕትና ምንጮች፣ የርኅራኄ ወንዞች፣ የነጻነት ተራሮች፣ የአስተዋይነት ኮረብቶች …  ለእነርሱ የምንከፍለው ውለታ ባይኖረን የእነርሱን ታሪክ አጥፍተን ልንኖር ግን እንዴት እንደፍራለን? ብንችል ጽፈን ደጉሰን ለትውልድ ባስተላለፈነው ነበር ያ ቢቀር በቃል የሰማነውን ለልጅ ልጆች መናገር እንዴት ይሳነናል? ብዙ ደጋግ አባቶችና እናቶች ፤ወንድሞችና እህቶች እንዲሁም ሕጻናት ያለፉባት ይች ምድር አፍ አውጥታ ስለደግነታቸው እስክትነግረን ድረስ በዝምታ መጠበቅ ያለብን አይመስለኝም፡፡ የአባቶቻችንንና የእናቶቻችንን የእምነት፣ የምግባር ጉዞ በመጻሕፍት የተቀመጠውን አንብበን፤ በመጽሐፍ ያልተቀመጠውን ደግሞ ከሚያውቁት በቃል ጠይቀን ማዎቅ የምንችልበት አእምሮ ተሸክመን የማንጠቀምበት ከሆነ የእኛ ሰው መሆን አጠራጣሪ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡  የዚህን ዘመን ልጆች በማጥቃት ሽባ እስከ ማድረግ ድረስ ያደረሱን በርካታ የቴክኖሎጅ ውጤቶች በየጊዜው አዲስ ነገር ያመጡ በመምሰል ለታሪካችን ደንታ ቢሶች አድርገውናል፡፡ በቴሌቪዥን መስኮቶች ላይ ሰዎች ሲገዳደሉ ፣ ሲደማሙ ከተመለከትን ያንን ለመፈጸም ሰው ማድማትና መግደል ባንችል እንኳ ጊዜያችንን ግድግዳ በመደብደብ የምንጨርስ የቴክኖሎጅ ሰለባዎች ብዙዎች ሆነናል፡፡ የባዕዳውያን ተገዥ ሆነን ማንነታችን አስኪጠፋ ድረስ ሁለንተናችን ተቀይሮ በባዕዳውያን የቴክኖሎጅ ውጤቶች ተሸብበን ለእኛነታችን ጊዜ ለመስጠት የማንችል የቴክኖሎጅ ባሪያዎች ሆነናል፡፡ እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባው ነገር የቴክኖሎጅ ጥላቻን ለመፍጠር ሳይሆን በቴክኖሎጀው ዘንድ እንዳንጠላ ጊዜና ቦታ አመቻችተን በአግባቡ መጠቀምን መልመድ ይገባናል የሚለውን ምክር ነው፡፡ የሚገርመው ነገር ከእነዚህ ቴክኖሎጅዎች የኮረጅነውን ባህል ተው ስንባል ለመተው መቁረጥ አለመቻላችን ነው፡፡ እስኪ ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰበት የአለባበሳችንን ባህል ተመልከቱት፡፡ አይዞህ ባይ ያጣ ከጎኑ ሆኖ የሚንከባከበው ሰው ጠፍቷል እኮ፡፡ ሰዎች ወንድን ከሴት ለመለየት የተቸገሩበት የጥፋት ጊዜ ቢኖር ይህ ያለንበት ዘመን ነው፡፡ ታሪክ ራሱን የደገመበት ዘመን ለማለት የሚያስደፍር ወቅት መሆኑን ማንም የሚስማማበት እውነት ነው፡፡ አዳምና ሔዋን በበደሉ ጊዜ ዕርቃናቸውን እንደሆኑ አውቀው እርስበርሳቸው በመተፋፈር እንደተሸሸጉ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ /ዘፍ3፥10-11/ የዚህ ዘመን ትውልድ ከአዳምና ከሔዋን የሚለየው ዕርቃኑን ሲሄድ አለማፈሩና አለመሸሸጉ ነው፡፡ አሁን አሁንማ ደግሞ ትክክለኛው ኢትዮጵያዊ አለባበስ በስደት ባሕር ተሻግሮ ውጮቹ መልበስ ጀምረዋል፡፡ ሞኙ የኢትዮጵያ ሕዝብ የውጩን ኮተት ሲሰበስብ እነርሱ ደግሞ የእኛን ንብረት ያጉዛሉ፡፡ ነገ ልጅህ የእነርሱን በሙሉ ይረከባል፤ ውጮቹም የእኛን በሙሉ ይወስዳሉ ከዚያ በኋላ “የኛ ባሕል ይህ ነው” ብለው የኢትዮጵያ የነበረውን አለባበስ የግላቸው ያደርጉታል፡፡ እኛም “የባህል ሙዚየም” የለን ማሳመኛ ማምጣት እንቸገራለን፡፡ ለመሆኑ ወገኖቼ የማናውቀው የውል ሥምምነት ተፈራርመናል እንዴ እኛ የእነርሱን እነርሱ የእኛን የምንቀያየረው? ወገኔ እዚህ ላይ ነው እንግዲህ ቆም ብለህ ማሰብ፡፡ ዛሬ በፈጠርነው ስህተት የነገው ትውልድ የውጮቹን ባሕል የራሱ አድርጎ ወስዶ የራሱ የነበረውን ባሕል መደምሰሱ አይቀርም፡፡ ጥሩ ነጋዴ የሚያተርፈውን መርጦ ይይዛል እንጅ ገንዘብ ስላለው ብቻ ያገኘውን ሁሉ አያግበሰብስም፡፡  አሁን እኛ ልንላበሰው የሚያስፈልገው የዚህን የጥሩ ነጋዴ ባሕርይ መሆን አለበት፡፡ በደንብ አስተውሉ ዘመቻውን ባሕላቸውን በቴክኖሎጅ ላኩልን ተቀበልን፤ እነርሱ በኢንቨስትመንት ሥም ሀገራችን ገቡ ተቀበልናቸው፤ ዛፎቻቸውንና እንስሶቻቸውን ላኩልን ተቀበልናቸው፤ ዲቪ ሙሉ አሉን ሞላንላቸው፤ እኛን ወደ ሀገራቸው ወሰዱን ሀገራችንን ለቀቅንላቸው፡፡ በቃ እንደፈለጉ በሀገራችን በወንዛችን  ላይ ይፈነጩብናል እኛም ሁለተኛ ዜጎች የመሆን እጣ ፈንታው ይደርሰናል፡፡ የለውጡን ሥምምነት አያችሁት? እነርሱ ባሕላቸውን ብቻ አይደለም የላኩት ድመት እና ውሻ ሳይቀር ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያን ከሌላ ሳንቀበል ያለን በራሱ ከበቂ በላይ ነው፡፡ ለእናት ሀገራችን ሊበጃት የሚገባውን ሥራ ብንሠራ ለወገን ኩራት ከመሆኑም ባሻገር ታሪክን ጠብቆ ለመኖር ፋይዳው የላቀ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ የሆነ መልካችንን ፍቀን ልንቀይር የተነሣሣንበት ዓላማ የት ሊጥለን እንደሚችል መገመት አእምሮ ላለው ሁሉ አያዳግትም፡፡ የአባቶቻችንን ምክርና ተግሳጽ ንቀን በውጮች የባሕል ተጽዕኖ እንጹም ሲሉን እንብላ፣ እንዘምር ሲሉን እንዝፈን፣ ንስሓ እንግባ ሲሉን ኃጢአት እንሥራ ፣ ቤተ ክርስቲያን እንሒድ ሲሉን ወደ ጠንቅዋይ ቤት ፣ ወዘተ… የምንል ሰዎች ንግዳችን ኪሳራ ነው፡፡ የመጨረሻ ውጤቱም የዘላለም እሳት ነው፡፡ እየተቸገርን ያለነው ትርፍና ኪሳራ ማዎቅ ባለመቻላችን ነው፡፡ ያተረፍን እየመሰለን ስንከስር አይገባንም አንረዳምም፡፡ ኪሳራ ትርፍ የሚመስለው ትውልድ ያለው ዛሬ ነው፡፡ ትርፍና ኪሳራ ማወቅ ከቻልን ቤተ ክርስቲያን ሁሌም በነጻ የምትሰጠውን አንዴ ከበሉት የማያስርበውን አንዴ ከጠጡትም የማያስጠማውን  የክርስቶስ እውነተኛ ሥጋና ደም መቼ ተመገብነው? ቀን ከሌሊት የምናስበው ለሥጋ ብቻ ነው እኮ፡፡ ነፍስ የሌለው የሚመስለው ትውልድ ተበራክቷል፡፡ አቅጣጫችን ከሁለት ያጣ ሆኗል፡፡ አንድ ወጣት በዝሙት ቢወድቅ ከእግዚአብሔር ጋር ተጣላ ማለት ነው የነፍስ ቅጣት አለበት በንስሓ እስካልተመለሰ ድረስ፡፡ በዝሙቱ ሳቢያ በሚመጡ በሽታዎች ተይዞ ለእናት ለአባቱ የዕድሜ ልክ ሸክም መሆኑ ደግሞ የሥጋ ቅጣት አገኘው ማለት ነው፡፡ አያችሁ ነፍሱንም ሥጋውንም በአንድ ጊዜ ሲያጣ፡፡ ከሁለት ያጣ ሆነ ማለት ይህ ነው፡፡ የዓለማዊ ትምህርት ተማሪዎች ከቤተሰብ ርቀው ዶርም ተከራይተው የሚበሉትንና የሚጠጡትን ቤተሰብ ይልኩላቸዋል፡፡ ወላጆቻቸው ሊለብሱት ቀርቶ አይተውት የማያውቁትን ልብስ ለመልበስ እህል እንስሳትን ያሸጣሉ፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ግን የወላጆቻቸውን ውለታ በመዘንጋት የመጡበትን ዓለማ ረስተው በሳቅ በጨዋታ በዝሙት በመዳራት ጊዜያቸውን የሚጨርሱ ውለታ ቢሶች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፡፡ ለትምህርታቸው ትኩረት ሰጥተው የቤት እና የክፍል ሥራ የማይሠሩ  በመሆኑ ውጤታማ ሳይሆኑ ይቀሩና ተመልሰው ለቤተሰቦቻቸው ሸክም ይሆናሉ፡፡ እነዚህ ውለታ ቢሶች የእናት ቤተ ክርስቲያንን ጥሪ በፍጹም መስማት አይፈልጉም፡፡ መንፈሳዊ ድግሷን አዘጋጅታ ብትጠራቸው እንኳ ተሳስተው አይመጡም፡፡ ከቤተሰብ ጋር ያሉትም ቢሆኑ እንዲሁ ናቸው፡፡ የት አምሸሽ? የት አመሸህ? ሲባሉ “መከረኛው ላይበራሪ” ሁልጊዜ ሲጠራ ፍዳውን ሲበላ ይኖራል፡፡ እውነት እነርሱ እንደሚሉት ቤተ መጻሕፍት ሲያነብቡ ነው ያመሹ? እንጃ እግዚአብሔር ይወቀው፡፡ እንደ ትልቅ መደበቂያና መሸሸጊያ እየተቆጠረ ነው እኮ ያለው፡፡ የብልግና ሥራን በአደባባይ ሲሠሩ አምሽተው ይመጣሉ ዛሬም ነገም “ላይበራሪ”፡፡ ታዲያ እንዲህ ሁሌም “ላይበራሪ” የሚያጠኑ ከሆነ ዜሮ የሚያመጡበት ትምህርት ለምን ይበዛል? ከክፍል ክፍልስ ለምን መዘዋወር ይሳናቸዋል? ታዲያ እንደዚህ አይነቶችን የከሰሩ ብንላቸው ቅር የሚሰኝ ይኖራል እንዴ? ዓለም ለራሷ ያደረገቻቸው በመረቧ ውስጥ ያጠመደቻቸው አያሌ ፍጥረታት ዓለም ባዘጋጀችው ባሕር ሲዋኙ ጊዜያቸውን በከንቱ የሚጨርሱ የዓለም ልጆች ብዙ ናቸው፡፡ ወላጆችም ለልጆቻቸው መክሰር ዋና ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ የት እንደዋሉ የት እንዳመሹ መጠየቁ ብቻውን ፋይዳ የለውም፡፡ ቤተክርስቲያንን ማሳየት በሚገባ ሃይማኖታቸውን እንዲጠብቁ በበጎ ምግባር እንዲጎለብቱ ማስተማር ይጠበቅብናል፡፡ የመንፈስ ፍሬዎችን እንዲያፈሩ መምከር መገሰጽ ያስፈልጋል፡፡ ልቅ በሆነ አስተዳደግ እያሳደግናቸው ስለሆነ ነው ለእምነታቸው ደንታ ቢሶች እየሆኑ ያለው፡፡ ያለጊዜያቸው ማየት የማይገባቸውን ሁሉ ማሳየት የለብንም ሲደርሱበት ራሳቸው ያዩታል፡፡ ስለዚህ ለልጆቻችን መክሰር ተባባሪዎች ከመሆን ልንቆጠብ ያስፈልጋል፡፡ ትውልዱ እየከሰረ ነውና!
እባካችሁ ወገኖቼ ከዚች ካሸበረቀች የኃጢአት ዓለም ጊዜ ሳንሰጥ በፍጥነት ወጥተን ባሕላችንን ጠብቀን ንስሓ ገብተን ሥጋውን በልተን ደሙን ጠጥተን የዘላለም ሕይወትን ወደምናገኝበት የጽድቅ ከተማ እንግባ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ እየተጓዝን ያለበትን የከሰረ ጉዞ በቸርነቱ እንዲያስተካክልልን መጸለይ ነው አማራጩ፡፡ የከሰርንበትን ሥራ ትተን የትርፍ ሥራ እንድንሠራ አምላከ ቅዱሳን ይርዳን፡፡ አሜን፡፡