ትውልድ ሲያልፍ ትውልድ ይተካል፤ ሰውም በየጊዜው ይፈራረቃል፡፡ ቀናትም እንዲሁ ቀናትን ወልደው ወራትን ያመጣሉ፤ ወራትም ወራትን ተክተው ዓመታትን ይስባሉ ፤ ዓመታትም ዘመናትን ፤ ዘመናትም ዘመናትን አበርክተው ጊዜያት ያልፋሉ፡፡ የልቅሶው ዘመን የሳቁን፤ የክፉው ዘመን የበጎውን፤ የኃዘኑ ዘመን የደስታውን ፤ የኃጢአት ዘመን የንስሓውን፤ የባርነት ዘመን የልጅነትን ዘመን ይተካሉ፡፡ ቀኑ ይመሻል ሌሊቱ ይነጋል ፤ ቀኑ ይነጉዳል ሌላ ቀን ይተካል፤ ትውልድ ያልፋል ትውልድ ይተካል፡፡ የሚገርመው ግን ካለፈው ትውልድ ታሪክ ካለፈው ዘመን ታሪክ የሚበጅ ነገር መማር አለመቻላቸን ነው፡፡ ሰው የሰውን ልጅ እንደ አውሬ ይቆጥርበት የነበረው ያ የባርነት የሞት የዋይታ የልቅሶ ዘመን ጊዜ ሲሽረው ዘመን ሲተካው እኛ ዛሬም ያው እንደቀድሞሙ ልማድ ሆኖብን የሰውን ልጅ እንደ አውሬ እንቆጥራለን እኛም እንዲሁ እንደ አውሬ እንቆጠራለን፡፡ የቀን እረፍት የሌሊት እንቅልፍ የአእምሮ ሰላም የነሳን በራሳችን ፍላጎት የምንፍጨረጨረው አንዳች የማይጠቅም ሥጋዊ ፍልስፍናችን ነው፡፡ የቀደሙ ሰዎች በጠፉበትና ባለቁበት መንገድ እየተጓዝን እንኳ ጉዟችን የቀናና የተስተካከለ እስኪመስለን ድረስ በኩራት አፋፍ ላይ ተኮፍሰን የትዕቢት አየር እየሳብን እንዝናናለን፡፡ ያ የጥፋት ዘመን ምን ያህል ሰው እንደወሰደ ጉዳቱ ምን ድረስ እንደነበር እንኳ የምናውቅ አይመስለኝም፡፡ ምድር የሰው ደም ጠምቷት በነበረ ወቅት ደማቸው የምድር ሲሳይ ሥጋቸው የአራዊት መጫወቻ የሆኑ ወገኖቻችን ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፡፡ አሁን ያለን እኛ በዛሬው እግራችን እየተራመድን ከዚያ የደም ዘመን ለመድረስ ብንሞክር ምን ያህል ርቀት እንጓዝ ይሆን? በኅሊናችን ማመላለስ የምንችል ሆኖ ቢሆን ለሀገራቸው፣ ለወገናቸው፣ ለነጻነታቸውና ለእምነታቸው ምትክ የሌላት ሕይወታቸውን ያሳለፉትን አባቶቻችንንና አናቶቻችንን ብናስታውሳቸው እንቅልፍ የሚኖረን ይመስላችኋል? ሠርተው ድካምን የማያውቁ፣ ለመታዘዝ እንቢታ የሌላቸው፣ ለመስጠት ንፍገት የሌላቸው፣ ለማሳዎቅ የማይሰለቹ የነበሩ የትሕትና ምንጮች፣ የርኅራኄ ወንዞች፣ የነጻነት ተራሮች፣ የአስተዋይነት ኮረብቶች … ለእነርሱ የምንከፍለው ውለታ ባይኖረን የእነርሱን ታሪክ አጥፍተን ልንኖር ግን እንዴት እንደፍራለን? ብንችል ጽፈን ደጉሰን ለትውልድ ባስተላለፈነው ነበር ያ ቢቀር በቃል የሰማነውን ለልጅ ልጆች መናገር እንዴት ይሳነናል? ብዙ ደጋግ አባቶችና እናቶች ፤ወንድሞችና እህቶች እንዲሁም ሕጻናት ያለፉባት ይች ምድር አፍ አውጥታ ስለደግነታቸው እስክትነግረን ድረስ በዝምታ መጠበቅ ያለብን አይመስለኝም፡፡ የአባቶቻችንንና የእናቶቻችንን የእምነት፣ የምግባር ጉዞ በመጻሕፍት የተቀመጠውን አንብበን፤ በመጽሐፍ ያልተቀመጠውን ደግሞ ከሚያውቁት በቃል ጠይቀን ማዎቅ የምንችልበት አእምሮ ተሸክመን የማንጠቀምበት ከሆነ የእኛ ሰው መሆን አጠራጣሪ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ የዚህን ዘመን ልጆች በማጥቃት ሽባ እስከ ማድረግ ድረስ ያደረሱን በርካታ የቴክኖሎጅ ውጤቶች በየጊዜው አዲስ ነገር ያመጡ በመምሰል ለታሪካችን ደንታ ቢሶች አድርገውናል፡፡ በቴሌቪዥን መስኮቶች ላይ ሰዎች ሲገዳደሉ ፣ ሲደማሙ ከተመለከትን ያንን ለመፈጸም ሰው ማድማትና መግደል ባንችል እንኳ ጊዜያችንን ግድግዳ በመደብደብ የምንጨርስ የቴክኖሎጅ ሰለባዎች ብዙዎች ሆነናል፡፡ የባዕዳውያን ተገዥ ሆነን ማንነታችን አስኪጠፋ ድረስ ሁለንተናችን ተቀይሮ በባዕዳውያን የቴክኖሎጅ ውጤቶች ተሸብበን ለእኛነታችን ጊዜ ለመስጠት የማንችል የቴክኖሎጅ ባሪያዎች ሆነናል፡፡ እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባው ነገር የቴክኖሎጅ ጥላቻን ለመፍጠር ሳይሆን በቴክኖሎጀው ዘንድ እንዳንጠላ ጊዜና ቦታ አመቻችተን በአግባቡ መጠቀምን መልመድ ይገባናል የሚለውን ምክር ነው፡፡ የሚገርመው ነገር ከእነዚህ ቴክኖሎጅዎች የኮረጅነውን ባህል ተው ስንባል ለመተው መቁረጥ አለመቻላችን ነው፡፡ እስኪ ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰበት የአለባበሳችንን ባህል ተመልከቱት፡፡ አይዞህ ባይ ያጣ ከጎኑ ሆኖ የሚንከባከበው ሰው ጠፍቷል እኮ፡፡ ሰዎች ወንድን ከሴት ለመለየት የተቸገሩበት የጥፋት ጊዜ ቢኖር ይህ ያለንበት ዘመን ነው፡፡ ታሪክ ራሱን የደገመበት ዘመን ለማለት የሚያስደፍር ወቅት መሆኑን ማንም የሚስማማበት እውነት ነው፡፡ አዳምና ሔዋን በበደሉ ጊዜ ዕርቃናቸውን እንደሆኑ አውቀው እርስበርሳቸው በመተፋፈር እንደተሸሸጉ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ /ዘፍ3፥10-11/ የዚህ ዘመን ትውልድ ከአዳምና ከሔዋን የሚለየው ዕርቃኑን ሲሄድ አለማፈሩና አለመሸሸጉ ነው፡፡ አሁን አሁንማ ደግሞ ትክክለኛው ኢትዮጵያዊ አለባበስ በስደት ባሕር ተሻግሮ ውጮቹ መልበስ ጀምረዋል፡፡ ሞኙ የኢትዮጵያ ሕዝብ የውጩን ኮተት ሲሰበስብ እነርሱ ደግሞ የእኛን ንብረት ያጉዛሉ፡፡ ነገ ልጅህ የእነርሱን በሙሉ ይረከባል፤ ውጮቹም የእኛን በሙሉ ይወስዳሉ ከዚያ በኋላ “የኛ ባሕል ይህ ነው” ብለው የኢትዮጵያ የነበረውን አለባበስ የግላቸው ያደርጉታል፡፡ እኛም “የባህል ሙዚየም” የለን ማሳመኛ ማምጣት እንቸገራለን፡፡ ለመሆኑ ወገኖቼ የማናውቀው የውል ሥምምነት ተፈራርመናል እንዴ እኛ የእነርሱን እነርሱ የእኛን የምንቀያየረው? ወገኔ እዚህ ላይ ነው እንግዲህ ቆም ብለህ ማሰብ፡፡ ዛሬ በፈጠርነው ስህተት የነገው ትውልድ የውጮቹን ባሕል የራሱ አድርጎ ወስዶ የራሱ የነበረውን ባሕል መደምሰሱ አይቀርም፡፡ ጥሩ ነጋዴ የሚያተርፈውን መርጦ ይይዛል እንጅ ገንዘብ ስላለው ብቻ ያገኘውን ሁሉ አያግበሰብስም፡፡ አሁን እኛ ልንላበሰው የሚያስፈልገው የዚህን የጥሩ ነጋዴ ባሕርይ መሆን አለበት፡፡ በደንብ አስተውሉ ዘመቻውን ባሕላቸውን በቴክኖሎጅ ላኩልን ተቀበልን፤ እነርሱ በኢንቨስትመንት ሥም ሀገራችን ገቡ ተቀበልናቸው፤ ዛፎቻቸውንና እንስሶቻቸውን ላኩልን ተቀበልናቸው፤ ዲቪ ሙሉ አሉን ሞላንላቸው፤ እኛን ወደ ሀገራቸው ወሰዱን ሀገራችንን ለቀቅንላቸው፡፡ በቃ እንደፈለጉ በሀገራችን በወንዛችን ላይ ይፈነጩብናል እኛም ሁለተኛ ዜጎች የመሆን እጣ ፈንታው ይደርሰናል፡፡ የለውጡን ሥምምነት አያችሁት? እነርሱ ባሕላቸውን ብቻ አይደለም የላኩት ድመት እና ውሻ ሳይቀር ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያን ከሌላ ሳንቀበል ያለን በራሱ ከበቂ በላይ ነው፡፡ ለእናት ሀገራችን ሊበጃት የሚገባውን ሥራ ብንሠራ ለወገን ኩራት ከመሆኑም ባሻገር ታሪክን ጠብቆ ለመኖር ፋይዳው የላቀ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ የሆነ መልካችንን ፍቀን ልንቀይር የተነሣሣንበት ዓላማ የት ሊጥለን እንደሚችል መገመት አእምሮ ላለው ሁሉ አያዳግትም፡፡ የአባቶቻችንን ምክርና ተግሳጽ ንቀን በውጮች የባሕል ተጽዕኖ እንጹም ሲሉን እንብላ፣ እንዘምር ሲሉን እንዝፈን፣ ንስሓ እንግባ ሲሉን ኃጢአት እንሥራ ፣ ቤተ ክርስቲያን እንሒድ ሲሉን ወደ ጠንቅዋይ ቤት ፣ ወዘተ… የምንል ሰዎች ንግዳችን ኪሳራ ነው፡፡ የመጨረሻ ውጤቱም የዘላለም እሳት ነው፡፡ እየተቸገርን ያለነው ትርፍና ኪሳራ ማዎቅ ባለመቻላችን ነው፡፡ ያተረፍን እየመሰለን ስንከስር አይገባንም አንረዳምም፡፡ ኪሳራ ትርፍ የሚመስለው ትውልድ ያለው ዛሬ ነው፡፡ ትርፍና ኪሳራ ማወቅ ከቻልን ቤተ ክርስቲያን ሁሌም በነጻ የምትሰጠውን አንዴ ከበሉት የማያስርበውን አንዴ ከጠጡትም የማያስጠማውን የክርስቶስ እውነተኛ ሥጋና ደም መቼ ተመገብነው? ቀን ከሌሊት የምናስበው ለሥጋ ብቻ ነው እኮ፡፡ ነፍስ የሌለው የሚመስለው ትውልድ ተበራክቷል፡፡ አቅጣጫችን ከሁለት ያጣ ሆኗል፡፡ አንድ ወጣት በዝሙት ቢወድቅ ከእግዚአብሔር ጋር ተጣላ ማለት ነው የነፍስ ቅጣት አለበት በንስሓ እስካልተመለሰ ድረስ፡፡ በዝሙቱ ሳቢያ በሚመጡ በሽታዎች ተይዞ ለእናት ለአባቱ የዕድሜ ልክ ሸክም መሆኑ ደግሞ የሥጋ ቅጣት አገኘው ማለት ነው፡፡ አያችሁ ነፍሱንም ሥጋውንም በአንድ ጊዜ ሲያጣ፡፡ ከሁለት ያጣ ሆነ ማለት ይህ ነው፡፡ የዓለማዊ ትምህርት ተማሪዎች ከቤተሰብ ርቀው ዶርም ተከራይተው የሚበሉትንና የሚጠጡትን ቤተሰብ ይልኩላቸዋል፡፡ ወላጆቻቸው ሊለብሱት ቀርቶ አይተውት የማያውቁትን ልብስ ለመልበስ እህል እንስሳትን ያሸጣሉ፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ግን የወላጆቻቸውን ውለታ በመዘንጋት የመጡበትን ዓለማ ረስተው በሳቅ በጨዋታ በዝሙት በመዳራት ጊዜያቸውን የሚጨርሱ ውለታ ቢሶች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፡፡ ለትምህርታቸው ትኩረት ሰጥተው የቤት እና የክፍል ሥራ የማይሠሩ በመሆኑ ውጤታማ ሳይሆኑ ይቀሩና ተመልሰው ለቤተሰቦቻቸው ሸክም ይሆናሉ፡፡ እነዚህ ውለታ ቢሶች የእናት ቤተ ክርስቲያንን ጥሪ በፍጹም መስማት አይፈልጉም፡፡ መንፈሳዊ ድግሷን አዘጋጅታ ብትጠራቸው እንኳ ተሳስተው አይመጡም፡፡ ከቤተሰብ ጋር ያሉትም ቢሆኑ እንዲሁ ናቸው፡፡ የት አምሸሽ? የት አመሸህ? ሲባሉ “መከረኛው ላይበራሪ” ሁልጊዜ ሲጠራ ፍዳውን ሲበላ ይኖራል፡፡ እውነት እነርሱ እንደሚሉት ቤተ መጻሕፍት ሲያነብቡ ነው ያመሹ? እንጃ እግዚአብሔር ይወቀው፡፡ እንደ ትልቅ መደበቂያና መሸሸጊያ እየተቆጠረ ነው እኮ ያለው፡፡ የብልግና ሥራን በአደባባይ ሲሠሩ አምሽተው ይመጣሉ ዛሬም ነገም “ላይበራሪ”፡፡ ታዲያ እንዲህ ሁሌም “ላይበራሪ” የሚያጠኑ ከሆነ ዜሮ የሚያመጡበት ትምህርት ለምን ይበዛል? ከክፍል ክፍልስ ለምን መዘዋወር ይሳናቸዋል? ታዲያ እንደዚህ አይነቶችን የከሰሩ ብንላቸው ቅር የሚሰኝ ይኖራል እንዴ? ዓለም ለራሷ ያደረገቻቸው በመረቧ ውስጥ ያጠመደቻቸው አያሌ ፍጥረታት ዓለም ባዘጋጀችው ባሕር ሲዋኙ ጊዜያቸውን በከንቱ የሚጨርሱ የዓለም ልጆች ብዙ ናቸው፡፡ ወላጆችም ለልጆቻቸው መክሰር ዋና ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ የት እንደዋሉ የት እንዳመሹ መጠየቁ ብቻውን ፋይዳ የለውም፡፡ ቤተክርስቲያንን ማሳየት በሚገባ ሃይማኖታቸውን እንዲጠብቁ በበጎ ምግባር እንዲጎለብቱ ማስተማር ይጠበቅብናል፡፡ የመንፈስ ፍሬዎችን እንዲያፈሩ መምከር መገሰጽ ያስፈልጋል፡፡ ልቅ በሆነ አስተዳደግ እያሳደግናቸው ስለሆነ ነው ለእምነታቸው ደንታ ቢሶች እየሆኑ ያለው፡፡ ያለጊዜያቸው ማየት የማይገባቸውን ሁሉ ማሳየት የለብንም ሲደርሱበት ራሳቸው ያዩታል፡፡ ስለዚህ ለልጆቻችን መክሰር ተባባሪዎች ከመሆን ልንቆጠብ ያስፈልጋል፡፡ ትውልዱ እየከሰረ ነውና!
እባካችሁ ወገኖቼ ከዚች ካሸበረቀች የኃጢአት ዓለም ጊዜ ሳንሰጥ በፍጥነት ወጥተን ባሕላችንን ጠብቀን ንስሓ ገብተን ሥጋውን በልተን ደሙን ጠጥተን የዘላለም ሕይወትን ወደምናገኝበት የጽድቅ ከተማ እንግባ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ እየተጓዝን ያለበትን የከሰረ ጉዞ በቸርነቱ እንዲያስተካክልልን መጸለይ ነው አማራጩ፡፡ የከሰርንበትን ሥራ ትተን የትርፍ ሥራ እንድንሠራ አምላከ ቅዱሳን ይርዳን፡፡ አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment