አንድ በዱር የሚኖር የእንስሳት ሁሉ የበላይ አለቃ የሆነ አንበሳ የሚባል እንስሳ ነበር፡፡ በበላይነቱ አብዝቶ የሚመካው አንበሳ አንድ ቀን እንስሳትን ሁሉ ለስብሰባ ጠራቸው፡፡ በውኃ የሚኖሩ፣ በሰማይ የሚበሩ፣ በየብስ የሚመላለሱ በሙሉ ጥሪው ደርሷቸዋል፡፡ ከስብሰባው መቅረት የሚባል ነገር አይታሰብም ከላይ አንገቱን ከታች ባቱን ይቆረጣልና፡፡ ቀኑ ደርሶ ሁሉም እንስሳት ተሰበሰቡ ዓሣ ግን በዚያው በውኃ ውስጥ ቀረች፡፡ “ሁሉም እንስሳ መጥተዋል አይደል?” አለ አንበሳ እየተጎማለለ፡፡ “ከዓሣ በቀር ሁሉም መጥተዋል” አለች አዞ፡፡ “ምን ያህል ብትንቀኝ ነው ዓሣ ስብሰባዬን ያቃለለችው?” አለ አንበሳ በብስጭት፡፡ ቀጠለ “እዚህ ላይ ሳልረሳው ለአዞ የምሰጥሽ ትዕዛዝ አለኝ ዓሣን በገባችበት ገብተሽ ታጠፊልኛለሽ፡፡ ዓሣ የሚለው ሥም ከእንስሳት ሥም ጋር ሊቆጠር አይገባውም፡፡ ሌሎችን እንስሳት ሳይቀር ለአመፅ የምታነሣሣ አመፀኛ ናት፡፡ ስለዚህ አርሷን የመከታተልና አከርካሪዋን ሰብሮ የመጣል ጉዳይ ለአዞ የተሰጠ ኃላፊነት ነው፡፡ ለማንኛውም የስብሰባችንን አጀንዳ እንቀጥል፡፡ አጀንዳው መደራጀትን የሚመለከት ነው፡፡ ልብ ብላችሁ ተከታተሉኝ ነገ ወደ ሥራ የምንገባበት ስለሆነ፡፡” ብሎ ማስጠነቀቂያ ሰጠ አንበሳ፡፡ “በፊት ከነበረው አለቃችሁ ይልቅ እኔ ተደራጅታችሁ መሥራትን አበረታታለሁ ስለዚህ እንስሳ የሆነ ሁሉ ሊደራጅ ግዴታ አለበት፡፡ አንበሳነቴን ይቃወምም ይደግፍም እኔ ለእንስሳቱ ይጠቅማል ያልኩትን ፖሊሲ ሁሉ የመፈጸም ግዴታ አለበት፡፡ ሁላችሁም ተደራጅታችሁ አንዱ አንዱን ይከታተላል፣ ይደግፋል፣ ይፈርጃል፣ ችግሩን ያሳያል፣ ያርማል፣ ይፈትሻል፣ ከእኔ የሚወርዱ መመሪያዎችን ያስጠናል፡፡ ሌላው እኔ ከምናገረው እና ከማወርደው መመሪያ ውጭ ሌላ ነገር መተንፈስ አይፈቀድም፡፡ አሁን ለደረስንበት እድገት መደራጀታችን ወደር የማይገኝለት አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ ነገር ግን ጥቂት ክፍተቶች ነበሩብን የዛሬውም ስብሰባ ዋና ዓላማ እነዚህን ክፍተቶች መሙላትና ወደ ሥራ መሰማራት ነው፡፡” አለ አንበሳ የራሱን ፍላጎት ብቻ እየተከተለ፡፡ እንስሳት በጸጥታ ይከታተሉታል፡፡ መቃወም አይቻልም፡፡ ተቃራኒ ሃሳብም ማንሣት አይፈቀድም፡፡ ምክንያቱም አመፀኛ፣ ዘረኛ፣ ትምክህተኛ፣ ጎሰኛ ወዘተ የሚል ሥም ይሰጣልና፡፡ አንበሳ ቀጠለ “ዛሬ በዋናነት የያዝነው አጀንዳ በመደራጀት ከላይ የሚወርዱትን መመሪያ በመፈጸም እድገታችንን ማረጋገጥና አደጉ ከሚባሉት ጋር እኩል መቆጠር ነው፡፡ በተጨማሪም እኔ ከምለው ውጭ ሌላ መናገር ለእድገታችን ፀር ስለሆነ ሁሉም የየቡድኑ መሪዎች በቡድናችሁ ያሉትን አባላት በሚገባ ማጥናት ያስፈልጋል፡፡ የአመለካከት ችግር ያለባቸውን አባላት በሚገባ መፈረጅ አለባችሁ፡፡” ብሎ አደራጅቶ አሰናበታቸው፡፡ አዞ የተሰጣትን ኃላፊነት ለመወጣት ወደ ዓሣ ሄደች፡፡ “እዚህ ቤት” አለች አዞ የዓሣን ቤት እያንኳኳች፡፡ “አቤት” ብላ ዓሣ ወጣች፡፡ “ዛሬ ከስብሰባ የቀረሽ ስብሰባውን ንቀሽ ነው ወይስ አንበሳን ተቃውመሽ ነው?” አለቻት፡፡ ዓሣ ቀጠለች “በስመ አብ! እንዴት ነው ስብሰባውን የምንቀው አንበሳንስ የምቃወመው? የእኔ ችግር እኮ ማንም የሚያውቀው ነው፡፡ ከውኃ ከወጣሁ እሞታለሁ፡፡ ስለዚህ ስብሰባውን መተው መረጥኩ ከሕይዎት በላይ ምን አለ?” አለች ዓሣ በሚያሳዝን ንግግር፡፡ አዞ ቀጠለች “ምንም ይፈጠር ምን ስብሰባውን መተው የለብሽም ነበር፡፡ አንች አኮ ለአመፅ ተባባሪ እንደሆንሽ ነው ሁሉም የተረዳው፡፡ አንበሳም የበላይነቱን የተቀማ ያህል ነው ያንገሸገሸው፡፡ ለእድገታች እኮ መሥዋዕትነትን ይጠይቃል፡፡ ዝም ብሎ የሚመጣ ጉዳይ አይደለም፡፡” አለች አዞ፡፡ ዓሣ ቀጠለች “አውቃለሁ ክብርት አዞ፡፡ የእኔ ጉዳይ እንደማንኛውም እንስሳ የሚታይ አይደለም፡፡ ስብሰባው ውኃ ውስጥ ቢሆን ኖሮ ማን ነበር ስብሰባውን የሚመራው? ሁሉም እኮ ራሱን ለማኖር ነው የሚታገለው፡፡ ይህን በመናገሬ ጽንፈኛ፣ ጎጠኛ፣ ዘረኛ፣ ትምክህተኛ የሚል ሥም እንደሚሰጠኝ አምናለሁ፡፡ ነገር ግን ማንነቴን ራሴ ስለማውቅ ብዙም አልደነቅም፡፡ እሽ ዛሬ አንችን ወደ እኔ ከመላክ ይልቅ ራሱ አንበሳ መጥቶ ለምን አልጠየቀኝም?” አለች ቁጣዋን ዋጥ እያደረገች፡፡ “እንዴ ላንች ብሎ የተከበረው አንበሳ እዚህ ድረስ ይምጣ?” አዞ ሳቀች፡፡ ሳቋን ጨርሳ ንግግሯን በቁጣ ቀጠለች “እንዲህ አይነት አመለካከት ይዘሽ ነው እድገትን እናመጣለን እያልን የምንታገል? በአንድ አለቃ መመራት ድሮ ቀረ አኮ፡፡ አሁን ሥልጣን ለየሁሉም ተዳርሷል፡፡ ሁሉም እንስሳት ተደራጅተው የየራሳቸው መሪ መርጠው በዚያ ነው መመሪያ የሚመጣላቸው፡፡ አንችን ደግሞ እንድመራ ሥልጣኑ የተሰጠ ለእኔ ነው፡፡ ስለዚህ አሁንም ቢሆን አመለካከትሽን አስተካክይ፡፡ ይህን ማድረግ ካቃተሸ ግን አሁንም ቢሆን አንበሳ ዘንድ ወስጄ ማስቀጣቴ አይቀርም፡፡” አለች አዞ፡፡ “የእኔ ጉዳይ ልዩ ነው ይታይልኝ ማለት ወንጀል ከሆነ ይቅርታ” አለች ዓሣ፡፡ አዞ እየተጎማለለች ዓሣን አስጠንቅቃ ሄደች፡፡ አንበሳ መመሪያዎችን ለሁሉም የቡድን መሪዎች አስተላለፈ፡፡ ሁሉም አባሎቻቸው እውቅና ፈጠሩ “ከአንበሳ የመጣውን መልእክት ሁላችንም ማዎቅ፣ ማክበር አለብን፡፡” አሉ የእንስሳቱ ቡድን መሪዎች፡፡ ሁሉም አባላት ሊፈጽሙት አንበሳ የተናገረውን በሙሉ ሊያከብሩ ለየራሳቸው ቃል ገቡ፡፡ አንዱ አንዱን መፈረጅ፣ አመለካከታቸውን ማጥናት ጀመሩ፡፡ የየአንዳንዱን ቡድን መሪ ሪፖርት አንበሳ ይከታተላል፡፡ አንበሳ በበላይነቱ ተመክቶ ይጎማለላል፡፡ እያንዳንዱን የቡድን መሪ ያሸማቅቃል፡፡ አንዳንዶች በሥውር ሃሳቡና አመራሩ እንዳልተመቻቸው ሲገልጹ የተለያየ ሥም ያወጡላቸዋል፡፡ እንስሳ ሆኖ መኖርን በጣም የሚያማርሩ በዙ፡፡ ለመኖር የሚሠሩትን ሥራ ስብሰባ በሚል ሰበብ ትተውታል፡፡ በስብሰባዎች መብዛት ምክንያት አዝመራቸውን ዝናብ ያበላሸባቸውም እንስሳት ነበሩ፡፡ በዚህ ሁኔታ ሳሉ አንበሳ ድንገተኛ አደጋ ደረሰበት፡፡ ሁሉም እንስሳት በአደጋው ክፉኛ አዘኑ፡፡ ሊያዩት ተሰበሰቡ፡፡ እባካችሁ “ሐኪም ቤት ውሰዱኝ” አለ አንበሳ፡፡ የቡድን መሪዎች አባሎቻቸውን “ሐኪም ቤት ውሰዱኝ” አሉ አንበሳ ያለውን እንደወረደ ነውና ለአባላቸው የሚያስተላልፉት፡፡ “በጣም ጠናብኝ ልሞት ነው በነፍሴ ድረሱባት” አለ አንበሳ እያቃሰተ፡፡ አሁንም ሁሉም ይህንኑ ተናገሩ፡፡ የተናገረውን እንደበቀቀን መድገም እንጅ ቀርቦ የሚረዳው አጣ፡፡ እኔ ካልኩት ውጭ ሌላ እንዳትናገሩ ያለው አንበሳ በከፋ ሁኔታ ሞተ፡፡ አንበሳ እንደሞተ ወንበሩን ለመያዝ ሽኩቻ ሆነ፡፡ ዓሣ ሞቷን ስትጠብቅ አንበሳ ቀደማት፡፡ “አምላኬ ሆይ ችግሬን የሚረዳልኝ አለቃ ስጠኝ” እያለች ፈጣሪዋን መለመን የዕለት ከዕለት ሥራዋ ሆነ፡፡ እኔ ካልኩት ውጭ ሌላ አትናገሩ እያለ ሲጎማለል የነበረ አንበሳ አሟሟቱ የከፋ ሆነ፡፡ ለቀሩትም የማይገባ ልምድ አውርሶ አለፈ፡፡ ለእድገት የሚሠሩ የመሰሉት ሁሉ ማንነታቸው ተገለጠ፡፡ አንበሳን ማዎደስ ብቻ ሆነ የዕለት ከዕለት ሥራቸው፡፡ ወንበሩን ለመያዝ ግን ዛሬ ድረስ ሽኩቻ ነው፡፡
No comments:
Post a Comment