Thursday, July 31, 2014

አባት እና ልጅ

አባትና ልጅ በመኪና እየተጓዙ ናቸው፡፡ አንድ ሽማገሌ ለመጫን መኪናው ቆመ፡፡ ሽማግሌው ገቡ “ጤ-ኤኤኤ-ና ይ-እእእ-ስ-እእእ-ጥ-እእእ-ል-እእእ-ኝ” አሉ በተቆራረጠ የሽምግልና ንግግር፡፡ ሽማግሌው ከ90 ዓመት ያለፋቸው ይመስላሉ፡፡ አስተውሎ ላያቸው ደግሞ “ይህን ሳታይ አትሞትም” የተባለውን ስምዖን አረጋዊን ይመስላሉ፡፡ መኪናው ጉዞውን ጀመረ፡፡ ሽማግሌው የሚቀመጡበት ወንበር የለም በረዳቱ ቋንቋ“ትርፍ” ናቸው፡፡ የመኪናው ፍጥነት ሽማግሌውን ወደ ግራም ወደ ቀኝም እያላቸው በጣም እንደተቸገሩ የተመለከተ አንድ እንደ ሽማግሌው “ትርፍ” የሆነ ወጣት አንድ ከአባቱ ጋር የተቀመጠን በግምት የ15 ዓመት የሚሆን ልጅ ተነሥቶ እንዲያስቀምጣቸው ተማጸነው፡፡ “እባክህ እነኚህን ሽማግሌ አስቀምጣቸው ትጸድቃለህ” አለ የቆመው ወጣት፡፡ “እንዴት ምን እያልክ ነው? ወንበሩን እኮ በትግል ነው ያገኘነው እንዴት ልጄን ተነሥ ትለዋለህ?” አሉ የልጁ አባት፡፡ “ምን ችግር አለው እርሱ ቢቆም ከእርሳቸው እኮ ይጠነክራል፡፡ አክብሯቸው ቢነሣና ቢያስቀምጣቸውስ ምረቃው ቀላል ነው እንዴ?” አለ ወጣቱ፡፡ “አልነሣም! ምረቃው ይቅርብኝ!” አለ የአባቱን ድጋፍ ያገኘው ልጅ፡፡ መኪናው ይሮጣል ሽማግሌውም ግራ ቀኝ ይወዛወዛሉ፡፡ “ኧ-ረ ተ-ኧኧ -ው በ-እእ-እ-ኔ ም-እእ-ክ-እእ-ን-እእ-ያ-ኣኣ-ት አ-ት-እእ-ጨ-ኧኧ-ቃ-ኣኣ-ጨ-ኧኧ-ቁ” አሉ ሽማግሌው፡፡ “ምን የአሁን ልጅ አባት እናቱን ማክበር ትቷል እኮ፡፡ እናትና አባት የሚባሉትም በሥርዓት ማሳደግ ትተዋል፡፡ ይገርማል እኮ አባቱስ ቢሆኑ አትነሣ፣ ሽማግሌ አታክብር አይደል እንዴ ሲሉት የነበረው?” አለ ወጣቱ፡፡ አንድ ሌላ ወንበር ላይ የተቀመጡ ሽማግሌ ተሳፋሪ የወጣቱን ንግግር ሰምተው “አክብር አባከ ወእምከ የሚለው የፈጣሪ ትዕዛዝ ተረሳ፡፡ እኛም ልጆቻችንን የ8ኛው ሽህ ልጅ እንዲህ አድርጎ ማለት እንጅ ሥርዓት አላስተማርናቸውም፡፡ አታይም እንዴ አሁንስ ሽማግሌ ቆሞ አትነሣላቸው አታክብራቸው የሚል አባት ነው እኮ ያለው፡፡ አክብር አባከ ወእምክ የሚለውን አክብር መንበርከ ብለው ቀየሩት እኮ፡፡ አሁን ጥለነው ለምንወርደው ወንበር ይህን ያህል መስገብገብ ምንድን ነው? ፈጣሪ ይጠብቀን እንጅ መኪናው ቢገለበጥ ወንበር ላይ የተቀመጠ አይጎዳም መሰላቸው እንዴ?” አሉ ሁኔታው በጣም አሳዝኗቸው፡፡ “ዘመኑ በጣም ያስፈራል፡፡ ልጆችን በሥርዓት የሚመራ ወላጅ ጠፍቷል፡፡ ስድብና ክፋት ነው እኮ እያስተማርን ያሳደግናቸው፡፡ በለጋነት ዘመናቸው አልገራናቸውም፡፡ በቤት ውስጥም ዱላ እየሰጠን እገሌን ደብድበው እያልን ነው ያለማመድናቸው፡፡ እኔ ግን ዘመኑ በጣም ያስፈራኛል፡፡ ምን አይነት ትውልድ ሊፈጠር እንደሚችል ሳስበው እንባዬ ይመጣል” አለ ወጣቱ፡፡ “በጣም የሚያስፈራ ዘመን ነው፡፡ መከባበር፣ መረዳዳት፣ መተባበር ተረሱ እኮ፡፡ እንደገባህ ውጣው የሚለው በዝቷል፡፡ የትውልዱ አቅጣጫ የት እንደሚያደርሰን ዕድሜ ሰጥቶ እንዳያሳየኝ ነው ጠዋት ማታ ፈጣሪዬን የምለምው፡፡ የዚህን ትውልድ ዕጣ ፈንታ ፈጣሪ ይወቀው፡፡ ለእምነቱ ትኩረት የማይሰጥ መብላት መጠጣት ብቻ ኑሮ የሚመስለው ትውልድ በጣም በዝቷል፡፡ እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ!” አሉ የተቀመጡት ሽማግሌ፡፡ መኪናው መናኸሪያ ደረሰና ሁሉም ተሳፋሪዎች ከመኪናው ወረዱ፡፡ ወጣቱ የልጁን አባት ተጠጋና “አባቴ ልጅዎን ጥሩ ምግባር ያስተምሩት፡፡ በነፍስ በሥጋ መጠቀም የሚችል በዚህ ሁኔታ አይደለም፡፡ እርስዎም እንዲህ አይነቱን መጥፎ ምግባር እንዲሠራ ማበረታት የለብዎትም፡፡ ልጅዎ አይደለም እንዴ? ልጅ እኮ ልጅ የሚሆነው ከሥር ከሥሩ ሲኮተኮት ነው፡፡ አገር የሚጠቅም ቤተሰብ የሚረዳ የሚሆነው ጥሩ ምግባር ሲይዝ ብቻ ነው፡፡ ከዚያ ውጭ ቀማኛ ወንበዴ ሆኖ ያለዕድሜው ይቀሰፋል፡፡ ስለዚህ ልጅዎን እንዲህ አይነት በባህላችን ያልተለመደ ነገር አያስተምሩት፡፡ ይህን ሁሉ የምልዎ እንዳይጎዱ በማዘን ነው ልጅዎም በረከት ረድኤት እንዲያገኝ ነው” አላቸው ወጣቱ፡፡ የልጁ አባት ግን ጆሮ የሰጡት አይመስሉም፡፡ ወጣቱ ተሰናበታቸው አባትና ልጅም አብረው ወደ ቤታቸው ሄዱ፡፡ ከብዙ ዓመታት በኋላ በመጥፎ ምግባር ያሳደጉት ልጃቸው በትምህርት ክፍያ ተጣላቸው፡፡ ልጁ በትምህርቱ ደካማ ስለነበር በነጻ የመማር ዕድል አላገኘም ነበርና “የትምህርት ክፍያ ክፈልልኝና በግል ልማር” ይላል አባቱን፡፡ አባቱም “ልጄ የቤታችንን ነገር እያወቅኸው እንዲህ ትላለህ? የምንበላው የምንጠጣው እየቸገረን እያለ አንተን ማስተማር እንዴት እችላለሁ? ከዚያስ እዚሁ አብረን እየሠራን ገንዘብ ስናገኝ ትማራለህ፡፡ የነጻ ትምህርት ዕድልም ልታገኝ ትችላለህ ትንሽ ታገስ፡፡” አሉት፡፡ ልጁ የሚሰማቸው አይመስልም “የግድ ነው ትከፍላለህ፡፡ እዚህ ቤት ውስጥ ከዚህ በኋላ መኖርም አልፈልግም፡፡ ቁጭ ብዬ እንዴት ነው የምውል ወይስ እርሻ እንዳርስልህ ፈልገህ ነው፡፡ እስከዛሬ ድረስ ተምሬ እንዴት ነው ካንተ ጋር በግብርና ሥራ የምበሰብስ” አለ አባቱን በማስፈራራት፡፡ አባቱም “ትሞታለህ እንጅ በግል አላስተምርህም፡፡ ገበሬ መሆን ከጠላህ እንደ ጓደኞችህ አታጠናም ነበር? ስታውደለድል ኖረህ ዛሬ ገንዘብ የምትጠይቅ ከየት ልወልድልህ ነው? ገንዘብ ተሠርቶ የሚገኝ እንጅ እንደ ቅጠል ተቆርጦ የሚመጣ አይደለም፡፡ ዳሩ ግን አንተ አይገባህ፡፡” አሉት ቆጣ ብለው፡፡ ልጁም ዱላ አነሣና አናታቸውን ፈነከታቸው አባትም ጮኹ ጎረቤት ተሰበሰበ፡፡ የሆነውን ሁሉ ለተሰበሰበው ጎረቤታቸው ተናገሩ እያለቀሱም “የኔ ነገር አይድረስባችሁ!” አሏቸው፡፡ ጆሮ ሰጥቶ የሰማቸው የለም “ድሮም አስተዳደጋቸው ስድ ነበር ይበላቸው የእጃቸውን ነው ያገኙ” እየተባባሉ ይንሾካሸካሉ፡፡ “ለማንኛውም ጤና ጣቢያ ይሂዱና ቁስሉ ይታሸግልዎ” አላቸው አንድ ጎረቤት፡፡ ደማቸውን እያዘሩ ጤና ጣቢያ ሄዱ፡፡ በወቅቱ የጤና ባለሙያ ሆኖ ያገኙት ከብዙ ዓመታት በፊት መኪና ውስጥ ብዙ የመከራቸውንና ከመኪና እንደወረዱም ልጃቸውን በሥርዓት እንዲያሳድጉ የነገራቸውን ወጣት ነው፡፡ ቁስላቸውን እያሸገ “ምን ሆነው ነው? ወድቀው ነው እነዴ?” አላቸው፡፡ “ኧረ የኔስ ጉድ ነው ለሰውም የሚነገር አይደለም፡፡ ልጄ ነው እንዲህ ያደረገኝ” አሉት እያለቀሱ፡፡ “አንድ ጊዜ መኪና ውስጥ ተነጋግረናል እንዴ? ጊዜው ትንሽ ረዘም ስላለ ዘነጋሁ መሰለኝ፤ ነው ተሳስቻለሁ ልበል” አለ የጤና ባለሙያው፡፡ “አዎ ተነጋግረናል፡፡ እኔ እንኳ አልረሳሁህም፡፡ የዚያን ጊዜማ ብዙ ነገር ብለኸኝ ነበር ያን ጊዜ ግን ምንም አልመሰለኝም ነበር፡፡ ይኸውልህ ዛሬ ራሴ ላይ ሲደርስ ተረዳሁት፡፡ ለካስ መቅጣት በሕጻንነት ዘመኑ ኖሯል፡፡ እኔ ሞኙ ልቅ አሳድጌ ዛሬ የሚያሳፍር ሥራ ሠራልኝ፡፡” አሉ ታካሚው፡፡ “ልጅን በሥርዓት ማሳደግ የሚጠቅመው ወላጁን ብቻ አይደለም ሀገሩን፣ ወገኑን፣ ቤተክርስቲያንን በሙሉ ነው፡፡ ለዚህም ነው ያን ያህል ብዙ ነገር ያልኩዎት፡፡ አሁን በራስዎ ሲደርስ አወቁት አይደል? እኔም ይህንን ፈርቼ ነበር ያለዕድሜዬ እርስዎን መካሪ የሆንኩት” አለ የጤና ባለሙያው፡፡ “ወይኔ! ያን ጊዜ ምክርህን ሰምቼ ኖሮ እንዲህ መች ጉድ እሆን ነበር፡፡ ብልጥ ከሰው ይማራል ሞኝ ግን ከራሱ ይማራል እንደሚባለው ሁሉ እኔ ሞኙ ከራሴ ተማርኩ፡፡” አሉ ሽማግሌው፡፡ የጤና ባለሙያው ቁስላቸውን አሽጎ ጨረሰና መድኃኒት ሰጣቸው፡፡ የመድኃኒቱንም አጠቃቀም አስረዳቸውና ተሰነባበቱ፡፡

No comments:

Post a Comment